በሀገራችን የክረምቱን መውጣት፣ የጸደይና የበጋው ወቅት መምጣትን ተከትሎ በርካታ በአላት ይከበራሉ። ባለፈው አንድ ወርም በእዚህ መሰረት አያሌ በአላት ተከብረዋል። የቡሄ ፣ የአሸንዳ /ሶለል፣ አሸንድዬ/፣የዘመን መለወጫ/ እንቁጣጣሽ እና የመስቀል በአላት ተከብረዋል። ሁሉም በአላት ከክረምቱ ወቅት ማብቃትና ከአዲሱ አመት መምጣት ጋር በተያያዘ መልእክት የተላለፈባቸው ናቸው። የምስጋናና የመልካም ምኞት መግለጫ የተላለፈባቸው ናቸው። መልእክቶቹ ደግሞ በዜማ በውዝዋዜ በምስጋና እና በመሳሰሉት ነው የቀረቡት።
አሁን ደግሞ ተራው የእሬቻ በአል ነው። በኦሮሞ ብሄር ዘንድ በደማቅ ስነስርአት የሚከበረው ይህ የምስጋና፣ የፍቅር፣ የሠላም፣ የእርቅና የይቅርታ በዓል፣ ጥላቻ የሚወገድበት እርቅ የሚደረግበት ፍቅር የሚሰምርበት ነው። ለዚህ ታላቅ በአል መላው የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች እንኳን በሰላም አደረሳችሁ እንላለን።
በሐይቆች እና ወንዞች አካባቢ የሚከበረው ይህ በአል ሌላው የሀገራችን ውበት እና ድምቀት ነው። በአሉ በመስከረም ሦስተኛው ሳምንት እሁድ በሆራ / ሀሮ ማለትም ሐይቆችና ለምለም ጨፌ በበዛበት አካባቢ ሲከበር ከክረምቱ ጨለማ ላወጣ ‹‹ዋቀ ቶኪቻ››/ አንድ አምላክ/ ምስጋና ይቀርባል። በርዕሳችንም የክረምት መውጫ ፣የፀደይ መባቻ የምስጋና በዓል ኢሬቻ ያልነው ይህንኑ ስለሚያሳይ ነው ። በአሉ ‹‹ቢራን ብሪኤ አባቦን ደራሬ›› /Birraan brii’e abaabon daraaree/ መስከረም ጠባ ኢዮሃ አበባ) እየተባለ ይከበራል።
ኢሬቻ ስዕላዊ በዓል ነው፤ ከኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ የብሔሩ ተወላጆች እንደ የአካባቢያቸው ባህላዊ የአለባበስ ስርአት በልዩ ልዩ አልባሳት አሸብርቀው ለፈጣሪያቸው ምስጋና እያቀረቡ ያከብሩታል። እዚያም እዚያም ሆነው በቡድን በቡድን ሆነው ሲያዜሙ ሲወዛወዙ ለተመለከተ ልዩ ስሜትን ያጭራሉ።
በአሉ በኦሮሚያ ክልል ሁሉም አካባቢዎች በወንዞች ወይም ሀይቅ ዳርቻዎች ላይ ይከበራል። የማይከበርበት ስፍራ የለም። በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ግን በሚሊዮኖች የሚቆጠር የክልሉ ህዝብ ፣ ቱሪስቶች፣ወዘተ በተገኙበት በልዩ ድምቀት ሲከበር ነው የኖረው።
በአሉ ከሀገራዊው ለውጥ ወዲህ ደግሞ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሆራ ፊንፊኔ በሚል መከበር ጀምሯል። በአዲስ አበባ ባለፈው አመት ከኮቪድ ጋር በተያያዘ በርካታ ህዝብ ባልተገኘበት ሁኔታ ቢከበርም፣ በ2011 ዓ.ም በደማቅ ስነስርአት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ በተገኘበት በፊንፊኔ መከበሩ ይታወቃል።
ዘንድሮም ትናንት በመስቀል አደባባይ ሆራ ፊንፊኔ በደማቅ ስነስርአት ተከብሯል። ገና በዋዜማው የአዲስ አበባ ጎዳናዎችና አደባባዮች በሰንደቅ አላማዎች ፣ በአሉን አስመልክቶ በተዘጋጁና ልዩ ልዩ መልእክቶችን በሚያስተላለፉ ፓስተሮች ደምቀው የሰነበቱ ሲሆን፣ ከትናንት በስቲያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የበአሉ ታዳሚዎች አዲስ አበባ ገብተው የከተማዋን ጎዳናዎች፣ አደባባዮች፣ በሚያሰሟቸው ዜማዎች እና በውዝዋዜያቸው በአለባበሳቸው አድምቀው ውለው አምሽተዋል።
በሆራ ፊንፊኔ ትናንት በተካሄደ ደማቅ ስነስርአት የአዲስ አበባው አከባበር በሰላም የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ዛሬ ደግሞ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ በልዩ ድምቀት ይከበራል። በበአሉ ለመታደም ሚሊኖች ቢሾፍቱ ገብተዋል።
በአዲስ አበባ በአሉ በሰላም ተከብሮ እንደተጠናቀቀ ሁሉ በቢሾፍቱም ለሚከበረው ለዚህ በዓል ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በሰላም እንዲጠናቀቅ ማድረግ ይገባል። የአዲስ አበባው ጥንቃቄ የተሞላበት አከባበር በሌሎች በአላት ወቅትም መቀጠል ይኖርበታል።
በአጠቃላይ በአሉ በሰላም እንዲከበር በቂ ዝግጅት መደረጉን በበዓሉ አስተባባሪ የቴክኒክ ኮሚቴ በኩል ተጠቁሟል። ኮሚቴው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በዓሉን ለማክበር የሚወጣው ሕዝብ አባገዳዎች በወሰኑት መሠረት በዓሉን ከሚገልጹ ነገሮች ውጪ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፓርቲ ባንዲራና አርማ መያዝ የተከለከለ መሆኑን አስታውቋል። ይህም አንዳንድ ወገኖች በበአሉ ላይ ያልተገባ መልእክት ከማስተላለፍ እንዲቆጠቡ ማድረግ ያስችላል።
እሬቻ የምስጋና በአል ነው። ኢሬቻ የሚከበረው ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ ለመግለጽ ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመቃወም ሲባል አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል። ኢሬቻ ምስጋና ማለት እንደመሆኑ የምስጋና ቀን እንጂ ፣ የፓርቲዎች መታያ፣ ፓርቲዎች የሚነቀፉበት ወይም የሚደገፉበት ቀን አለመሆኑን ማስተዋል ያስፈልጋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓርማ መያዝ በዓሉን ከማደብዘዝ የዘለለ ፋይዳ የለውም።
እርጥብ ሣር ይዘው ወደ መልካ(ወንዝ) ሄደው (Ganna irraa gara Bona kaan nuu cheesisee waaqaa kenyaa galata issaf hagaahuu) ከክረምቱ ወደ ጸደይ ያሸጋገረን ፈጣሪ ምስጋና ይድረሰው ነው። በመሆኑም በእዚህ የኢሬቻ በአል ላይ ጥላቻን ከሚያስተላለፍ አመለካከት መታቀብና መቆጠብ ይገባል።
ኦሮሞ በኢትዮጵያ በአቃፊነቱ ታሪክ የሚያውቀው ነው፤ዛሬ ተምረናል የሚሉ ጥራዝ ነጠቆች አንቂዎችና አናቂዎች (አክቲቪስት) የተወሰኑ የኦሮሞን የፖለቲካ ፓርቲዎች ደርሰው አቃፊውን ኦሮሞ ገፊ ነቃፊና ዘላፊ ሊያደርጉት ሲፍጨረጨሩ ይታያል። የዴሞክራሲ ተምሳሌት የሆነውን የአባገዳዎች አመራረጥና የሥልጣን ገደብ ያውቃሉ ተብለው የሚታሰቡ ለኦሮሞ ህዝብ እንታገላለን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እንኳ ሳይቀሩ በአሉን በአል ማክበሪያ ብቻ ሲያደርጉት አይታይም። ሁሉም ጥቅማቸውን ለማሳደድ ሲፍጨረጨሩ ይታያሉ። ስለፓርቲዎች ስናነሳ ‹‹ሸኔ ጆሌፊ ጀሌ ወያኔ›› ይታወሰናል።
እናቅልሃለን የሚያቀነቅኑት እነዚሁ አካላት በአላዋቂነታቸው ትናንት ኦሮምን ሲጨፈጭፉ እንደነበር አይዘነጋም። ከእነዚሁ መካከል ሸኔን የመሳሰሉ አራሙቻዎች ኦሮሞን ሲጨፈጭፍ ከነበረው ወያኔ ጋር ትስስር ፈጥረዋል። ይህም በኦሮሞ ህዝብ የሚነግዱ መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። እኛም በአባ ገዳዎች ምርቃት ልንሰናበታችሁ ወደድን፤ ትርጉሙን በግርድፉ አስቀምጠነዋል።
Xiqqan kee sii Yaagudatuu (ህፃኑ ይደግልህ/ሽ)
gudaan kee sii Yaabuuluu (ትልቁ ይድረስልህ/ሽ)
waan kale dhabdee argadhuu (ትናንት ያጣኸ(ሽ)ውን አግኝ/ኚ)
biiyaa etiiyopiiarattii jabaadhaa jirraadhaa( በኢትዮጵያ ምድር ላይ ውለዱ ክበዱ) ይላል ምርቃቱ። መልካም በዓል ይሁንልን።
ሀይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን መሰከረም 23 ቀን 2014 ዓ.ም