መንግስት በዓለም አቀፍና እርዳታ ተቋምነት ስም በአንዲት ሉዓላዊት አገር ውስጥ “ሲወሰልቱ ያዝኳቸው”፤ “ደረስኩባቸው”፤ “እጅ ከፍንጅም ደረስኩባቸው” ባላቸው የዓለም አቀፉ ተቋም (ዩኤን) ሰራተኞች ላይ (ብዙዎች “ባልተገባ ትእግስት ምክንያት የዘገየ” ያሉትን) እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ እርምጃው ከተወሰደበት እለት ማምሻ ጀምሮ ዓለም ሲንጫጫ ይኸው አሁንም ድረስ አለ።
በጣም ግልፅ የሆነውን፣ ማለትም የእርዳታ አቅራቢው ድርጅት ሰራተኞች የሽብር ኃይሉ በትግራይ እያካሄደ ያለውን አገር የማፍረስ ተግባር ተከትሎ “ለትግራይ ህዝብ እንድረስለት” ሲሉ በጠየቁትና የኢትዮጵያ መንግስትም በፈቀደው መሰረት ወደ ክልሉ ገብተዋል። ይሁንና ጉዳዩ የተገላቢጦሽ ሆኖ ለማመን የሚያስቸግሩ፣ ለወሬ እንኳን የማይመቹ ተግባራት በእርዳታና ሰብአዊ መብት ሽፋን ሲፈፀሙ ቆይተዋል።
በትግራይ ህዝብ ስም የመጡ የእርዳታ አቅርቦቶች “ለሽብርተኛው ቡድን እንዲደርስለት” መደረጉ በተጨባጭ ታይቷል። ከዛም አልፈው በዓለም አቀፍ መርህ መሰረት ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ የዓለም አቀፍ ተቋማት አንዳንድ ሰራተኞች ከመጡበት ዓላማና ተልእኮ ጫፍ ወርደው በአገር ማፍረሱ ተግባር ውስጥ ሲርመጠመጡ ተገኝተዋል።
መንግስት ጉዳዩን በሆደ ሰፊነት በማየት በተደጋጋሚ በጉዳዩ ዙሪያ የሚመለከተው አካል ተገቢውን የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ደጋግሞ ጠይቋል። ይመለከተዋል የተባለው አካልም እርምት ከማድረግ ይልቅ በመንግስት ላይ ያልተገቡ ጫናዎችን ለማሳደር ብዙ ጥሯል። የአገሪቱንና ህዝቧን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ሃላፊነት ያለበት መንግስታችን በ72 ሰአታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ (አብዮታዊ እርምጃ መውሰድ ሲገባው) መወሰኑን ተከትሎ በባለሙያ ያልተቃኘ የሙዚቃ ቢት በሚመስል ደረጃ ዓለም አቀፉ ጫጫታና ኳኳታ ቀልጧል።
በርግጥ ይህ አይነቱ አደንቋሪ ጫጫታና ኳኳታ ለኢትዮጵያ አዲስ ጉዳይ እንዳልሆነ፤ ይልቅም ሁሌም ጊዜ እየጠበቀ የሚከሰት አገርንና ህዝብን ከመናቅ የመጣ የሚመስል ተግባር መሆኑን አንድ የቅርብ ምሳሌ በመጥቀስ እንይ ።
በዚህ 30 ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ የሆነውን እንኳን ብንምለከት ይህ አይነቱ የአገራችንን ሉዓላዊነት የመዳፈር ተግባር ከአንዴም ሁለትና ሶስቴ ተከስቷል። የቢቢሲ የጋጠኞች ቡድን “በቱሪዝም ላይ ልሰራ እፈልጋለሁ” በማለት ላቀረበው ጥያቄ ተፈቅዶለት (እንደ ሩሲያውያኑ የቱሪስት ቡድን ከነ ሙሉ ክብሩ መጥቶ ይሄዳል በሚል ታሳቢ) ከገባ በኋላ ሌላ ነገር ውስጥ ሲርመጠመጥ በመገኘቱ ባስቸኳይ እንዲሰናበት ተደረገ። ጫጫታውና ኳኳታው ከዓለም ዙሪያ ተሰማ። ይሰማ እንጂ ያመጣው አንዳችም ፋይዳ የለም። ሌላም አለ።
የስዊድን ጋዜጠኞች ድንበር ጥሰው በመግባት ከተፈቀደላቸው ውጪ በሆነ ሌላ ድብቅ ዓላማ ስር ተወሽቀውና የአገርን ሉዓላዊነትና የህዝብ ማንነት የናቀ ተግባር ውስጥ ሲልከሰከሱ በመገኘታቸው መንግስት ፈጣን እርምጃን ወሰደ። አሁንም ዓለም ተንጫጫ። ይንጫጫ እንጂ የህግ የበላይነት ተገቢውን ስፍራ እንዳይዝ ያገደው አንዳችም አካል አልነበረም። (በነገራችን ላይ የስዊድን ጋዜጠኞች ከእስር ተፈትተው ወደ አገራቸው ሲመለሱ ለኤቲቪ ጋዜጠኛ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የፈፀሙት ተግባር የሞት ቅጣትን የሚያስከትል እንደነበር፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት ባለው ሩህሩህነት የተነሳ በአጭር ጊዜ የእስር ቤት ቆይታ ብቻ እንዲለቀቁ መደረጉ እንዳስደሰታቸው መግለፃቸው ይታወሳል።)
ይህ በቂ ማሳያ ስለመሆን አለመሆኑ መናገር ባያስፈልግም፣ አንድን ሉዓላዊት አገር የመዳፈር፣ የውክልና ጦርነት የማካሄድና መንግስትና ህዝብን ከመሰረቱ የማናጋት ተግባር በኢትዮጵያ ላይ ሲሴር፣ ሲሸረብና ሲደገስ ይህ የመጀመሪያ እንዳልሆነ ግን ማረጋገጫ ነው። አሁን ጥያቄው “ይህ ሁሉ ሲሆን፤ ሲደረግ፤ ድንበር ሲጣስና በዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ስም ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት አገርን ለማፍረስ ምለው ከተገዘቱ ወገኖች ጋር ሲያብሩ ሲተባበሩ መንግስት ዝም ብሎ ይመልከት፣ እጁን አጣጥፎ ይቀመጥ?” የሚለው ሲሆን፤ መንግስት የሚባለው አካል ይህን ካደረገ፣ ጉዳዩ ጥላሁን ገሠሠ “ምኑን ፍቅር ሆነ …” እንዳለው “ምኑን መንግስት ሆነው”። መቸም ይህ በመርህ ደረጃ መንግስትን በህዝቡ ተጠያቂ እንደሚያደርገው ለምእራቡ ዓለም የሚጠፋው አይመስለኝም።
በአሁኑ ሰአት እንኳን መንግስት እኛ እያንዳንዳችን በማንስተው ደረጃ የውጭ ጣልቃ ገብነት ግዘፍ ነስቶ በአካል “ሲንቀሳቀስ” እያየነው ነው። የሽብር ቡድኑ ህወሓት በአካል እየተዋጋ ይምሰል እንጂ ዓለም “አንቱ” ያላቸው ወገኖችና ረጃጅም እጆቻቸው ከጀርባው ስለመኖራቸው ለማረጋገጥ ምንም አይነት መማማል አያስፈልግም። በመሆኑም መንግስት አሁን በእርዳታ ድርጅቱ ሰራተኞች ላይ (ልብ እንበል የምንነጋገረው ስለ ድርጅቱ አይደለም።) በወሰደው እርምጃ መንጫጫቱ የትም አያደርስም።
እርግጥ ነው፣ በድርጅቱ ለተሰለፉበት ዓላማና ሰብአዊ ተልእኮ እራሳቸውን ያስገዙና በጠንካራ ዲሲፕሊን ላይ ቆመው ስራቸውን የሚሰሩ መኖራቸው የሚካድ አይደለም። የእነዚህን፣ አርአያ የሚሆኑ ሰራተኞችን ስራና አስተዋፅኦ ከአንካሳም ባለፈ ጎዶሎ የሚያደርጉ፤ ተለጣፊ ተልእኮ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ስለመኖራቸው ግን ብዙ መናገር የሚያስችሉ ዓለም አቀፍ ክስተቶች ስለመኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር ሲሆን፤ አንዱም ይሄው በእኛው አገር የሆነው ነው።
ዓለም አቀፍ ተቋማቱም ሆኑ አንዳንድ የአሜሪካ ባለስልጣናት መንግስት በተቋማቱ ሰራተኞች ያልተገቡ ስራዎች እየተካሄዱ መሆኑን ደጋግሞ ሲያሳውቅ ምን እየሆነ ነው ብለው መጠየቅ በተገባቸው ነበር። ከዛም በላይ የመንግስትን ውሳኔ ‹‹አስደንጋጭ ውሳኔ ነው…›› ወዘተ በሚል አደባባይ ከመውጣታቸው በፊት ከችግሩ አንጻር ‹‹አስደንጋጭ›› የሚሆነው የተቋማቱ ሰራተኞች ተግባር ነው ወይስ መንግስት ሃላፊነቱን ለመወጣት የወሰደው ህጋዊ እርምጃ?” በሚለው ላይ ሊያስቡበት በተገባ ነበር። ግን አልሆነም፤ የሚያሳዝነውም አለመሆኑነው ነውና ያስተዛዝባል።
እውነታውን ጊዜ ወስደው ለመመርመር ለምን አልሞከሩም? ጉዳዩ እስኪጣራ በምትካቸው ሌላ ሰራተኛ መላክ ለምን ከበዳቸው? ጉዳዩን ከአቅሙ በላይ ባልተገባ መንገድ ማጯጯህ ለምን አስፈለገ? መረጃና ማስረጃ ተገኝቶባቸው ተጠያቂ ለሆኑ ግለሰቦችስ ይህን ያህል ጥብቅና (ማፈር ሲገባ) ለምን አስፈለገ?
በትግራይ ለሚገኙ ወገኖቻችን ከኛ በላይ አሳቢ ለመሆን የሚደረገው ጥረት በራሱ ጤነኛ እንዳልሆነ ለማንም ባለ አእምሮ የሚሰወር አይደለም። እነ አሜሪካ ለትግራይ ህዝብ ሲያስቡ እኛ ለእናትና አባቶቻችን፣ ለወንድምና እህቶቻችን ማሰብ የማይችል አእምሮ፣ መራራት የተሳነው አንጀት እንዴት ሊኖረን ይችላል? “ላም ባልዋለበት ….” ስንል አንዱም ምክንያታችን ይህ ነው።
በሚመለከታቸው አካላት በይፋ እንደተገለፀውና እኛም እንደተከታተልነው መንግስት ከችግሩ ማግስት ጀምሮ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ አውጥቶ የእርዳታ ድጋፎችን አቅርቧል። ስለ ሰላም ካለው የጸና ፍላጎት በመነጨም የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ከክልሉ ሲወጣ ከበቂ በላይ የእርዳታ አቅርቦቶችን በመጋዘኖች አከማችቶ መሆኑና ለትራንስፖርት አገልግሎት በሚልም ከፍ ያለ የነዳጅ ክምችት አስቀምጦ መውጣቱም እንደዛው። ይህ የትግራይን ህዝብ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተከማቸን ንብረት ማን እየተጠቀመበት ነው? ለምንስ አገልግሎት እየዋለ ነው? የሚለውን እዛው ያሉና በዓለም አቀፉ የእርዳታ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ ለሙያና ተልእኳቸው ታማኝ የሆኑ ሰራተኞች አንድ፣ ሁለት …. በማለት ቆጥረው ሊናገሩ ይችላሉ፤ እውነቱንም እንደዛው። ከዚህ ይልቅ እሚሰማው “የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ክልሉ እርዳታ እንዳይገባ ከልክሎ ህዝቡን በረሃብ አስጨረሰ” የሚል ነው። ጥያቄው “ነው ወይ?” የሚለው ነውና መልስ ይፈልጋል።
መንግስትም የሀሰት ስሞታና ክሱ ቢበዛበት ያለ ገደብ ፈቀደና መግባት የሚፈልገው ሁሉ ያለ ገደብ ገባ። ሳይውል ሳያድር ግን ብስኩቶች ሽብርተኞች መጋዘንና ምሽግ ውስጥ ለእይታ በቁ። ለእርዳታ ማጓጓዣና ማመላለሻ ይውላል የተባለውና ከዩኤን ተነስቶ ማይካድራ የተገኘው ነዳጅ ወደ ታንክና የሽብርተኛው ታንከር ውስጥ ተንቆረቆረ። ይህ ሁሉ ወንጀል በአሸባሪው ቡድን ሲካሄድ አንድም አካል ትንፍሽ ሲል አይሰማም፤ ጭራሽ ተከሳሹ ታጋሹ መንግስት ሆነና አረፈው። “ላም ባልዋለበት ….” ስንል ያለ ምክንያት ስላለመሆኑ ይህም ሌላው ማሳያ ነው።
በእነዚህና ሌሎች እዚህ ባልጠቀስናቸው ምክንያቶች መንግስት “ሁሉም ነገር ማብቂያ አለው” በሚል መንግስታዊ ቃል ወደ እርምጃ ሲገባ ጩኸቱ ተበራከተ፤ ጫጫታው ተደበላለቀ፤ እሪታው ቀለጠ። “ለምን???” ጥያቄው ይሄ ነው።
ያለውን በትክክል ለሚያውቅ፣ በእርዳታ ስም በሀገሪቱ እየሆነ፣ እየተፈፀመ ያለውን ለተገነዘበ፤ በግልፅና ስውር እጆች እየጠፋ ያለውን የንፁሃን ህይወት ለተመለከተ የመንግስት ውሳኔ የሚያስጮህ ሳይሆን ባስለቀሰ፤ መንግስትንም ይበል ባሰኘ ነበር። ግን አልሆነም።
አገሪቷን ካላፈረስኩ ሞቼ እገኛለሁ በሚል ወገን ላይም ሆነ የእሱ ቀኝ እጅ በሆነ አካል ላይ እርምጃ ቢወሰድ ምኑ ነው ለኳኳታና ጫጫታ የሚያበቃው? ምኑስ ነው የሚገርመው? ሌላው አገር ሰርቶ እሚበላን፣ በላቡና ወዙ ጥሮ ግሮ የሚኖርን ሰው ውጡልኝ ይል የለም እንዴ? ታዲያ ኢትዮጵያ ሊያፈርሳት የመጣን አፍራሽ “ወግድ ይሁዳ!” ብትል ምኑ ጋር ነው ሀጥያቱ? ምኑስ ነው እነ ሰማንታ ፓወርን ሁሉ ሳይቀር ወገብ አስይዞ የሚያውረገርገው? ኧረ በህግ!!!
ከእርዳታ ጋር በተያያዘ ትልቅ ዋጋ ለመክፈል የተገደድን ህዝቦች መሆናችንን አንዳንዶች የረሱት ይመስላል። እኛም ከትናንት ታሪክ የማንማር የዋህ የምንመስላቸውን ያሉም ይመስላል። በ1977 ዓ.ም በሀገሪቱ በተፈጠረ ድርቅ ምክንያት በእርዳታ ስም ሀገሪቱን ያጥለቀለቁ አካላት የቱን ያህል በወገኖቻችን ችግር እንደነገዱበት አሁን ላይ ልናስታውሳቸው ይገባል። ዛሬ ያንኑ ታሪክ ለመድገም መሞከር ህዝባችንን እንደ ህዝብ መናቅ ነው። ለዚህ የሚሆን ስብእና ደግሞ የለንም።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ሀገርን እንደሀገር ወደ አዲስ የታሪክ ምእራፍ ለማሻገር ብዙ ፈተናዎችን በጽናት እየተጋፈጠና ብዙ ስኬቶችን እያስመዘገበ ነው። ይህ ከኢትዮጵያዊ የማንነት ጽናት የሚቀዳው የመንግስት አቋም በቀላሉ የሚሸረሸር አይደለም። መላው ህዝባችን በዘመናት ሲጠብቀው እና ከሩቅ ሲሰናበተው የኖረ ተስፋው አሁን ህያው ሆኖ ወደሚጨበጥ (ኦብጀክቲቭ ወደ መሆን) ደረጃ እየተጓዘ ነው። ይህ ተስፋችን ከዚህም የበለጠ ተግዳሮትን አሸንፎ መውጣት የሚያስችል የዘመናት ስንቅ ያለው ነው። (እዚህ ላይ ግን ተስፋ ኖረም አልኖረ አገሩ ሲፈርስ፣ ህዝብ ሰላም አጥቶ ሲሰቃይ ዝም የሚል መንግስትም ሆነ ዜጋ አለመኖሩን ልብ ማለት ያስፈልጋል። በደማቁ ሊሰመርበትም የግድ ነው።)
ይሁን እንጂ ይህን ያልተረዱም ይሁኑ ወይም ተረድተው አውቀው የእኛን የተስፋ ጉዞ ለማሰናከል የሚሹ፤ በሚመስለውም በማይመስለውም የተስፋችን አደናቃፊ ሰልፈኞች ሆነውብን ቆይተዋል። አሁንም ያው ነው። ያለ አግባቡ መንግስትን መክሰስ፤ ሉአላዊነነታችንን መዳፈር፤ ከዛም ባለፈ “አባይን አትገድቡ” ማለታቸው የዚሁ ተጨባጭ እውነታ አካልና ማሳያ ነው። ይህ ደግሞ በትህትናና በራሳችን ምሳሌያዊ አነጋገር ቁጭ ስናደርገው “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” ነውና ትርፉ ሽንኩርት በሽልንግ ገዝቶ “ስንት ሸጥከው?” ሲባል “ሽልንግ” እንዳለው “ዜሮ ሰም ጌም” ነው።
ኢትዮጵያ አትፈርስም!!! ሉአላዊነቷም አይደፈርም!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2014