ቀዳሚዎቹ የአዲስ አበባ ምዕራፎች፤
“አዲስ አበባ ቤቴ!” እያለ ለበርካታ ዐሠርት ዓመታት የጣይቱን ሌጋሲ በመረዋ ድምጹ ሲያሞካሽ የኖረው ዕውቁ የሙዚቃ ሰው ነፍሰ ሄሩ ዓለማሁ እሸቴ በአፀደ ሥጋ የተለየን አዲስ አበባ “አዲሱን ምዕራፏን” ልትገልጥ የቀናት ዕድሜ ሲቀራት ነበር፡፡ ነፍስ ይማር! አዲስ አበባ ርእሰ መዲና ብቻም አይደለችም፡፡ የሀገርም ተምሳሌት ናት፡፡ “ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ፣ ሀገርም እንደ ሰው ይናፍቃል ወይ” የሚለውን የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴን የስደት ዘመን እንጉርጉሮ ማስታወስ ይቻላል፡፡
የአዲስ አበባ “አማላይ ስም” እየደለለን ዕድሜዋን አዘውትረን ስለማናስታውስ እንጂ ለአዛውንቷ ከተማችን የ 135 ዓመታት የዕድሜ ጸጋ የልደት ሻማዋን የምንደረድርላት “አዲስ” በተቀበልነው በዚህ የዘመነ ማርቆስ መባቻ ላይ ነው፡፡ አለቆቻችን “አዲስ ምዕራፍ ከፍተንላታል” ብለው ካወጁልን ከዚህች አዲስ አበባ ጋር በጓደኝነት አብረው ያረጁት የእማማ ብርቅ እሸት የተዘወተረ አባባል ሁሌም ትዝ ይለኛል፤ “አይ ዕድሜ! ለካስ ሞት አይቀርም አዳሜ!” ግሩም አባባል ነው፡፡ የአዲስ አበባን አዲስ ምዕራፍ ከመቃኘታችን አስቀድሞ ጥቂት ወደ ኋላ በመንደርደር በራሴ የዘመን ትውስታ ውክልና የአዲስ አበባን ቀዳሚ ምዕራፎች ላስታውስ፡፡
ምዕራፍ አንድ፤
አዲስ አበባን አፈር አቡክተን፣ ውሃ ተራጭተን አድገንባታል፡፡ በሚሚና በማሙሽ ዕድሜያችን በሰንሰል ቬሎና በኮባ ልጣጭ ግልድም ተውበን እርስ በእርስ ተዳድረናል፡፡ የቅጠል እንጀራ በአፈር ወጥ እየጠቀስን “በሞቴ እየተባባልን” ተጎራርሰናል፤ በኮርኪ ሽክና አፍ ለአፍ ገጥመን ወራጅ ውሃ ተጎንጭተናል፡፡ ቡሄና አበባ አየሽ ወይ ጨፍረን ተመርቀናል፡፡ በችቦ ብርሃን ልጅነታችንን አፍክተናል፡፡ በየሠፈሮቻችን ሜዳዎች እንደ ዋላ እየቦረቅን ፈንጥዘናል፡፡ የፊደል ገበታችንንና ውሃ በሞላ ብርጭቆ ውስጥ የተከተተልንን የአሹቅ ስንቅ በብብታችን ሸጉጠን ከየኔታ መንበር ዕውቀት ልንቀስም ተቃቅፈን ተመናል፡፡
ምዕራፍ ሁለት፤
ይኼኛው የወጣትነት ምዕራፋችንና የአዲስ አበባ መልክ ለንባብ ባይገለጥ ደስ ይለኛል፡፡ “ከታሪክ መሰዊያ ላይ አመዱን ሳይሆን እሳቱን ጫሩ” እንዲል የጠቢባን ምክር፤ ቢቻልም ከእኔና ከዘመነ እኩዮቼ ታሪክ ውስጥም ሆነ ከአዲስ አበባ ምዕራፍ ውስጥ የዚህ ምዕራፍ ገጽ ተገንጥሎ ቢወጣ ፈቃዴ ነበር፡፡ ታሪክን መደምሰስ ያለመቻሉ ግን ጠፍቶኝ አይደለም፡፡ የማይሆን ምኞት እንደሆነም ይገባኛል፡፡ ይህ ምዕራፍ በአጭሩ ይገለጥ ከተባለ በነጭና በቀይ ቀለማት ስያሜ እየተቧደንን የተጠፋፋንበት፣ በግራና በቀኝ አይዲዮሎጂ ተከፋፍለን የተላለቅንበት፣ ለጦርነትና ለስደት የተዳረግንበት፣ “ከሞት መላዕክት ጋር” ፊት ለፊት ተጋጥመን የተሞሻለቅንበት ምዕራፍ ነበር፡፡ ለእኛም ለአዲስ አበባም፡፡
እናቶች በኀዘን ጨርቅ እንደተቆራመዱ፣ አባቶች ጥቁር ቱቢት ደረታቸው ላይ እንደለጠፉ “ምነው ባልተወለዳችሁ ኖሮ” እያሉ እንባቸውን ቀለባቸው፣ እዬያቸውን መዝሙራቸው አድርገው የኖሩበት ዘመን ነበር፡፡ በዚህቺው “ስሟ እንደ ግብሯ” ባላማረላት አዲስ አበባችን፡፡ ይህ የወጣትነት ዕድሜያችን የተጻፈበት ቀለምም ሆነ ቀለሙ የፈሰሰበት ብራና እንደ ከሰል የጠቆረ፣ ህይወቱም እንደ ሲዖል የጨለመ ነበር ብሎ መደምደሙ ይበጃል፡፡
ምዕራፍ ሦስት፤
ወደ ጉርምስና የተሸጋገርንበት ይህ የዕድሜያችን ምዕራፍና የአዲስ አበባም መልክ ተጎሳቁሎ፣ ወይቦና ተኮማትሮ የገረጣበት ወቅት ነበር፡፡ በታዳጊነትና በወጣትነት የእድሜያችን ምዕራፎች ላይ በጋራ የጠጣንበት ሽክና እንክትክት ተደርጎ ስለተሰባበረ ፖለቲካውን እንድንጋት የተፈረደብን ውሃ በማይቋጥረው ስብርባሪ ገል ከየብሔረሰባችን ምንጭ እየቀዳን በየታዛችን ሥር በመጠለል እንድንጎነጭ ታቅዶ ነበር፡፡ በጋራ የቦረቅንበት ሜዳ እንኳን ሳይቀር “የብሔር ታርጋ” ተለጥፎበት እንዳንረግጠው ብቻም ሳይሆን ዞረን እንኳን እንዳናየው ጭምር ማዕቀብ ተጥሎብን ተሳቀናል፡፡
ተወላጆቹ ባዕዳን፤ ባዕዳኑ ባለርስት በመሆን አንገታችንን ደፍተን ቁልቁል እንድናነባ ተደርገናል። ዘር ከልጓም የመሳቡ ምሥጢር በገሃድ ተጽፎና በህገ መንግሥትነት ማኅተም ጸድቆም እንድንተዳደርበት ተሰጥቶናል፡፡ በዚህ ምክንያትም ፍልቅልቁ ሐጎስ ጓደኛችን ፊቱን አኮሳትሮ አስደንግጦናል፡፡ የዋሁ እስማኤል፣ ቱትና ሞቱማ ከአንድ ኪስ ንፍሮ እየዘገንን እንዳልበላን ሁሉ ዛሬ “እዚያው በየጥጋችን” እየተባባልን ገደብ አበጅተንና እርስ በእርስ ተፈራርተን ማዶ ለማዶ መተያየትን መርጠናል፡፡ ደምስ፣ ይርጋ፣ ላዕከ፣ ከድጃ፣ ንፁህ፣ ዶዮና መሐመድ (ስንቱ ተዘርዝሮ ይዘለቃል) በየአጋጣሚው ስንገናኝ እንደማይተዋወቁ ሆነን ስንተላለፍ “እምባችንን” እያፈሰስን ነው፡፡ በዚህኛው ዘመን በሀገር እየኖሩ “ሀገር አልባ” የመሆን ትርጉሙ በእጅጉ የገባን የምዕራፋችን ገጽ ነው፡፡
በምዕራፍ አራት መሸጋገሪያ የዘመነ ሽበታችን ዳር ዳርታና ዋዜማ ላይ እንደ አረንቋ ያሰመጠን ይህን መሰሉ ሀገራዊ መከራ ተተርኮም ይሁን ተነግሮ የሚጠናቀቅ አይደለም፡፡ በታዳጊነት ዕድሜያችን የቦረቅነው ከአዲስ አበባችን ጋር አብረን እየፈነጠዝን ሲሆን በወጣትነታችን ምዕራፍ ቅስማችን እንክትክት እንዳለ በስሜታችንና በሥጋ ዓይናችን መንታ መንታ ያነባነው እኩል ከአዲስ አበባ ጋር ተስፋችን ጨልሞብን ነበር፡፡ እንድንሞት የተፈረደብንም ከአዲስ አበባችን ጋር ተቆራኝተን በጭካኔ በትር እየተመታን ነበር፡፡ ዳሩ “ይብቃሽ” ብሎ ያልፈረደባት ነፍስ ሆኖ እኛም ሆንን አዲስ አበባ ዛሬን ደርሰን እነሆ ታሪክ ለማስታወስ ዕድል አግኝተናል፡፡
ይህ ሁሉ “በላ” እየወረደብንም ቢሆን ይህ ጸሐፊ በዘመነ ወጣትነቱ (በ1979 ዓ.ም) የአዲስ አበባ መቶኛ ዓመት በዓል ሲከበር በሠፈሮቿ ስያሜ ላይ “የመቶ ዓመት ሻማ ሲቀጣጠል” በሚል ርእስ ለሚወዳት ከተማው ዝርዝር ጥናት ሰርቶ የወዳጅነቱን አበርክቶላታል፡፡ የዚህ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ መንትያ የነበረችው የዘመኑ ተወዳጅ “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጣም ጥናቱን በተከታታይ ዕትሟ አውጥታ ትብብር ስላደረገችለች ከሦስት ዐሠርት ዓመታት በፊት በግፈኞች ለተሰዋችው ለዚህች ጋዜጣ ይህ ጸሐፊ “ነፍስ ይማር!” ይላል፡፡
በዘመነ ጉልምስናችንም መከራው ባይገፈፍልንም እንኳን ይህቺው አዲስ አበባ ህዳር 2005 ዓ.ም የ125ኛ ዓመት የልደት በዓሏን ስታከብር “የአዲስ አበባ ከተማ አመሠራረትና የአካባቢዎቿና የሠፈሮቿ አሰያየም” በሚል ርዕስ ከተማሪ ቤት ጓደኛው ከነፍሰ ሄር ብቃለ ስዩም (ዶ/ር) ጋር በጋራ ጥምረት በሀገር አቀር ሲምፖዚዬም ላይ ዳጎስ ብሎ የተዘጋጀ ጥናት በማዘጋጀትና በማቅረብ በዓሏ ሳይደበዝዝ በድምቀት እንዲከበር አስተዋጽኦ አድርገናል።
የቀዳሚ ምዕራፎቿ ዝንጉርጉርነት በዘረዘርናቸው መሰል የመከራ ዓይነቶች የወረዛው አዲስ አበባችን ትናንት በመስቀል ዋዜማ “አዲስ ምዕራፍ” ተከፍቶላታል፡፡ ታሪኳንም በአዲስ የጅማሮ ምዕራፍ “ሀ” ብላ እየጀመረች። ነው፡፡ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የመረጥናቸውን የምክር ቤት አባላት ሰብስባና በሹመት ያንበሸበሸቻቸውን ፊት-ቀደም መሪዎቻችንን ለይታ ስታስተዋውቀን መዋሏም አበጀሽ ያሰኛታል። “ሹመት ያዳብር!” እንዳንል ትርጉሙ ደግም አይደል ስለተባልን አንደግመውም፡፡
ይህ ጸሐፊ ጉልምስናውን ተሻግሮ በነጭ የፀጉር ዕድሜ ዋዜማ ጠርዝ ላይ ቆሞ ከአዲስ አበባ ከራሷ አንደበት “አዲስ ምዕራፍ” ሊገለጥ ነው ተብሎ ሲጨበጨብ እምባ ባቀረረ ዓይኑ ሥርዓቱን ቤቱ ቁጭ ብሎ ተከታትሏል። ባቆጠቆጠው የሺህ ውበቱ ትውስታም “እውነት ይሆንን?” በማለት በጥርጥርና በተስፋ መሃል መዋዠቁን አይክድም፡፡ “አዱ ገነት ሆይ!” በእርግጡ የምትገለጪበት አዲሱ ምዕራፍ “የአዲስ ኪዳን” ማስጀመሪያ ነው ወይንስ ነባሩን “ብሉይ ኪዳን” አዲስ በገለጥሽው ገጽ ላይ ለመጻፍ? መልሱ እያደር ስለሚገለጥ ለፍርድ አንቸኩልም፡፡
”የአዲሱ ምዕራፍ አዲስ ጅማ‘፤
መስከረም 18 ቀን 2014 ዓ.ም አዲሱ የአዲስ አበባ አስተዳደር ክሱት ሆኖ መዋሉን ጠቅሰናል፡፡ በግሌ ክብርት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ወንበራቸው ላይ ለተጨማሪ አምስት ዓመታት እንዲሰነብቱ ፈጣሪ በቸርነቱ፣ ፓርቲያቸው በበጎነቱ አመኔታ ስለጣሉባቸው እኔም “ይደልዎ!” ብዬ ፈቃዴን ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ መልካም የሥራ ዘመን አንዲሆንላቸውም ተመኝቼላቸዋለሁ፡፡
አዲስ አበባ ከተማችን ቢትወደድ ወልደ ጻድቅ የመጀመሪያው ከንቲባ ሆነው ከተሾሙላት ከ1901 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት 130+ ዓመታት ውስጥ 32 ያህል ዋና ከንቲባዎች መርተዋታል፡፡ ከእነዚህ ከንቲባዎች መካከል ወሰኔ ዘአማኔልና ነሲቡ ዘአማኔል ወንድማማቾች ነበሩ። ብላቴን ጌታ ዘውዴ በላይነህ፣ ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ሥላሴ፣ ዶ/ር ቢትወደድ ዘውዴ ገ/ሕይወትና ኢንጂኒር ዘውዴ ተክሉ በስመ ሞክሼ ከንቲባነት ይጠቀሳሉ። በቢትወደድ፣ በደጃዝማች፣ በራስ፣ በብላቴን ጌታና በፊታውራሪነት ማዕረግ አስራ ስምንት ያህል ከንቲባዎች አስተዳድረዋታል፡፡ ሦስት ያህል ዶክተሮችም ነበሩበት፡፡ በጾታ ረገድ ሠላሳ አንዶቹ ከንቲቦች ወንዶች ሲሆኑ በ135 ዓመታት ውስጥ 32ኛዋን ሴት ከንቲባ ያገኘቸው ዘንድሮ ነው፡፡ የእቴጌ ጣይቱ ነፍስ እንዴት ደስ ይላት!?
ከታሪክ ትውስታ ወደ ጉዳያችን እንመለስ፡፡ የክብርት ከንቲባዋ “የአዲሱ ምዕራፍ” የጉባዔ መክፈቻ ንግግር በትህትና፣ በማስተዋልና መራጫቸውን ህዝብ ባከበረ መልኩ የተላለፈ ስለሆነ ወድጄላቸዋለሁ፡፡ ቁርስ ምሳና የከሰዓት በኋላ መክሰሴን የተመገብኩት ከቴሌቪዥኔ መስኮት ላይ ዓይኔን ሳልነቅል የምሥረታውን ሂደት ከሀሌታ እስከ መሰናበቻ ልብ ተቀልብ ሆኜ በመከታተል ነው፡፡ የምክር ቤቱ መሪ ሰነድ በዝርዝር ከቀረበ በኋላ የጉባዔው አባላት ማብራሪያ የጠየቁባቸውን ጉዳዮችና መስተካከል ቢችሉ ብለው የዘረዘሯቸውን ስጋቶቻቸውን በሙሉ በሚገባ አጢኜዋለሁ፡፡ ምንም አንኳን “የአንድ ፓርቲ ልጆች” መሆናቸው ባይዘነጋም የተንሸራሸሩትን ሃሳቦች ስንመለከት “በአንድ የድርጅታዊ አሰራር ሙቀጫ ውስጥ ተደልዘው ያልወጡ ስለመሆናቸው” ፍንጭ ሰጥቶናል፡፡
ያልገባኝና ሊገባኝ ያልቻለው፣ ወደፊትም ይገለጥልኛል ብዬ ተስፋ የማላደርገው አንድ ጉዳይ ግን ከምርጫው ሰሞን እስከ ዛሬ እንደከነከነኝ አለ፡፡ ለፖለቲካው ጉዳይ ልቤ ዝግ ስለሆነም እንደሆን አልገባኝም፡፡ ብልፅግና ፓርቲን ወክለው ተመርጠው “የብልፅግና ፓርቲ አባል አይደለሁም” የሚለው የአራት ተመራጭ የቅርብ ወዳጆቼ ክርክር ስላልገባኝ አልጣመኝም፡፡ እነርሱ ለሚከራከሩበት “የፖለቲካ ጃርገን” አንግዳ ባለሀገር ሆኜም ሊሆን ይችላል።
እንደሚመስለኝ ግን “ጃንጥላውን አልወደውም፤ የተጠለልኩት ግን በጃንጥላው ሥር ነው” የሚለውን ተቃርኖ የሚያስታውስ ይመስለኛል፡፡ ይበልጥ እናብራራው ከተባለም “ከመረቁ አውጡልኝ ለሥጋው ፆመኛ ነኝ” ከሚለው ብሂል ጋር አስተሳሰቡ በሚገባ ይጎዳኛል፡፡ ለማንኛውም ግን በአዲሱ ምዕራፍ ገፆች ላይ “ከፋም ለማም” የግላቸውን አሻራ ስለሚያሳርፉ እኛ መራጮች የምንገመግማቸው በውጤታቸው ሲሆን ታሪክም በፊናው አሻራቸውን መመርመሩ አይቀርም፡፡
ለጊዜው የጉባዔው ስብጥር የተሻለ ይመስላል፡፡ አንዳንድ ተናጋሪዎች ግን የመጀመሪያ አስተያየታቸውን ሲሰጡ “ቀድሞ የታየና የተሰማ ለዘለቄታው ይታወሳል” (First impression lasts long) የሚለውን አባባል ለጊዜው ያስታወሱት አይመስልም፡፡ “በአነጋገር መፈረዱን፤ ከአያያዝ መቀደዱን” ልብ ቢሉ ባልጠላን ነበር፡፡ “የእከሌ ብሔር ለምን አልተካተተም?” የሚለው የአንድ ጉባዔተኛ አስተያየት “አፍ ሲያመልጥ ራስ ሲመለጥ አይታወቅም” ወደሚለው ነገረ ብሂል ገፍቶናል። “በብሔር መቋሰል ዳግም ሊያገረሽ ይሆንን?” በማለትም ተሳቀናል፡፡
አንዲት የጉባዔው አባል “የአዳዲሶቹ የካቢኔ አባላት ሹመት ነባሩን አስተዳደር ያስቀጠለ ይመስላል” የሚለው አስተያየትም በዚህ ጸሐፊ መረዳት “A” ማርክ አሰጥቷታል፡፡ “ከትምህርት ዝግጅት ይልቅ የካሁን ቀደም ውጤታማነታቸው ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶበታል” በሚል ድምጸት ከክብርት ከንቲባዋ የተሰጠው አስተያየት ይህንን ጸሐፊ ትንሽ ጎፍነን አድርጎታል፡፡ ንግግራቸው “ፖለቲካዊ ብያኔ” ይባል ካልሆነ በስተቀር ከአካዳሚክሱ መርህና ከነዋሪው ግምገማ ጋር በእጅጉ ይቃረን ይመስለናል፡፡
በተለይም አንዳንዶች የቢሯቸውን ጠንካራ የብረት በር ዘልቆ እንኳን ለመግባት እንደማይቻልና በእለት ህይወታቸውም ጭምር ህዝቡ በሚገባ እያወቃቸው የተሞካሹበት ቋንቋ የሚገባቸው ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ያዳግታል፡፡ በትራንስፖርት ሰልፍ ፀሐይ እየከካው፣ በጤና ጣቢያዎች ውስጥ በጉልበተኞች እየተገፈተረ፣ የዕለት ጉርሱን ማግኘት ተስኖት ምድር ዞራ ያዞረችው ወገን በሚሊዮኖች ስሌት እየተገመተ፣ የአደባባዮቻችን መሃልና ዳርቻ በጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት ተጣቦ በምናስተውልበት፣ የሥራ ፈላጊው ብዛት የአራት ኪሎን “ኖቲስ ቦርድ” አጣቦ ለኮቪድ ደዌ ማዳበሪያ የሆነበት ትዝብት አፍጥጦ እያለ “የትናንቷን አዲስ አበባ” ሲመሩ የነበሩ ግለሰቦች ውጤታቸው ከትምህርት ዝግጅታቸው በልጦ መሞካሸታቸውን አልወደድኩላቸውም፡፡ ብዙዎችም የወደዱላቸው አይመስልም፡፡
ሚኒስትሮች ዝቅ ብለው ቢሮዎችን እንዲመሩ መደረጉም በጉልህ መስተጋባቱ አስፈላጊነቱ አልታየንም። “ተራ ሰው” መሆንም እኮ ይኖራል፡፡ “አገልግለውን የት እንጣላቸው” ተብሎም ከሆነ ሀገራዊ ልማዳችን ስለሆነ በሆደ ሰፊነት እናልፈዋለን፡፡ የአስፈጻሚ ቢሮዎች ስያሜዎች ላይ የተሰጡት የማሻሻያ አስተያየቶች እንደሚታረሙ ተስፋ ይደረጋል፡፡ በተለየ ሁኔታ ግን የትኛውም አስተያየት ሰጪ ያልጠቀሰው የከተማው “የባህል፣ የኪነ ጥባባትና የቱሪዝም” ስያሜ “አጀብ” የሚያሰኝ ነው፡፡ ለመሆኑ ኪነ/ሥነ ጥበብ የባህል አካል አይደለም? አካል ብቻም ሳይሆን እስትንፋስም ቢሰኝ አያንስበትም፡፡
እኮ እንዴት ተብሎ ነው “የመሾሚያ መስኮት” ለመክፈት ሲባል ብቻ ኪነ/ሥነ ጥበብ ተነጥሎ በስያሜው ውስጥ ሊገለጽ የተቻለው? ነገ ለዚህ ዘርፍ አዲስ ምክትል የቢሮ ኃላፊ ሊሾም እንደሆነ እንጠረጥራለን። ለማንኛውም በአዲሱ የከተማችን ምዕራፍ ላይ ሊጻፉ የተዘጋጁት የሪፎርም አጀንዳዎች የሚተገበሩት እንዲህና እንዲያ እየተደረገ ነው፡፡ አዲስ አበባ ሆይ ገና ለገና በስምሽ ላይ “አዲስ” የሚል ቅጽል ጎልቶ በመታየቱ ብቻ “አዲስ” ነሽ እያልን በማንቆለጳጰስ እድሜሽንም እድሜያችንንም መፍተጀቱ አታክቶናል፡፡ “አዲሱ ምዕራፍ” አሮጌውን ምዕራፎቻችንን የማይደግም ከሆነ እሰየው! “አዲሱን ወይን በአሮጌ አቁማዳ” እንዲሉ ከሆነ ግን እንጃልሽ! እንጃልን! ፡፡ ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com አዲስ ዘመን መስከረም 22/2014