የተወለዱት በቀድሞው አጠራር ወሎ ክፍለሃገር ወልዲያ ከተማ የጁ አውራጃ ውስጥ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን መልካ ቆሌ እና ጣይቱ ብጡል የተማሩ ሲሆን መድሃኒያለም ትምህርት ቤት ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። የሁለተኛ ደረጃ ትህርታቸውን በማጠናቀቅ ላይ ሳሉ ግን አየር ወለድ ተመልምለው የውትድርና ዓለምን ተቀላቅለውም ነበር። በሰራዊቱ ውስጥ የሬዲዮ ኦፕሬተርነትና የወታደሩን የጦር ሜዳ ውሎ የሚዘክሩ በርካታ የሥነ- ፅሁፍ ስራዎችን በማበርከት ህወሓት የሀገሪቱን መንግስት በትረ ስልጣን እስከሚረከብ ድረስ አገልግለዋል። የመንግስት ለውጡን ተከትሎ እንደአብዛኞቹ የቀድሞ ሰራዊት አባላት በተሃድሶ ሰበብ ለእስር ተዳርገውም ነበር።
ጦላይ ለሶስት ወራት ከታሰሩ በኋላ ለጥየቃ የሚመጡ ቤተሰቦች በመጡበት ላንድሮቨር መኪና ውስጥ የረዳቱን ቱታ ለብሰው ከማሰልጠኛው አምልጠው ወደ አዲስ አበባ መጡ። ይሁንና የቀድሞ ሰራዊት አባላት በየትኛው የመንግስት መስሪያ ቤት እንዳይቀጠሩ በመደረጉ ምክንያት ስራ ማግኘት አልቻሉም። በዚህ ግን ተስፋ አልቆረጡም፤ በሰራዊቱ ውስጥ ሳሉ የስነፅሁፍና ኪነጥበባዊ ስራዎችን መስራታቸውን ቀጠሉ። እናም በኢትዮጵያ ታሪክ ሁለተኛውን ”ፀፀት‘ የሚለውን ፊልም ፃፉ። በተለይም ከእነ ተፈሪ አለሙና አብራር አብዶ የመሳሉት የሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ተዋናዮችና አመራሮች ጋር የተለየ ቅርበት ስለነበራቸውም የቀን ተቀን ውሎአቸው ከቲያትር ቤቱ ርቀው አያውቁም ነበር። በእነዚህ ታላቁ ከያኒዎች የጥበብ ፍቅር ተለክፈው ማደጋቸውን የሚናገሩት እንግዳችን ሙሉ ትኩረታቸውን ለኪነጥበባዊ ስራዎች ሰጡ።
በእንግሊዝ ነፃ የትምህርት እድል አግኝተው የፎቶ ጋዜጠኝነት ሙያ በሮዝ ዌስት ኮሌጅ ዲፕሎማቸውን አገኙ። በአትሌቲክስ ስፖርት ላይ በመገኘት የሚያነሷቸው አነጋጋሪ ፎቶዎቻቸው ዓለምአቀፍ እውቅና አስገኝቶላቸዋል። በማህበራዊ ሚዲያው የሀገራቸውን ታሪክ፤ ቅርስ፤ ባህል በማስተዋወቅ እንዲሁም የሀገር አንድነትን በመስበክ ስማቸው ጎልቶ ይነሳል። በተለይም በአገሪቱ ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ ለውጡ እንዲቀጥል ድጋፋቸውን ሲያደርጉ ቆይቷል።
ኑሯቸውን በስደት በእንግሊዝ ሀገር በለንደን ከተማ አድርገው ለ28 ዓመታት ህወሓትን በመቃወም እና ተቃዋሚዎችን ይበልጥ በማቀናጀትና በማስተባበር፤ በሰላማዊ ሰልፎችና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ትስስር ባለው ተግባር ሁሉ በግንባር ቀደምትነት የሚገኙትና ሙሉ ጊዜያቸውን በመጠቀም በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የሚያሳልፉ ሰው ናቸው።
በኢትዮጵያዊነታቸው ፍጹም የማይደራደሩ፣ የሀገራቸው ታሪክ እና ባህል ቅድሚያ በመስጠት የሚታወቁ ሲሆን በእንግሊዝ ሀገር በሚኖሩበት ወቅት፤ ከሀገራችን በስርቆት፣ በተጭበረበረ ሁኔታ ወደ ውጭ ሀገር በቀላል ገንዘብ ተሽጠውና ተለውጠው የወጡ ጥንታዊ ታሪክ ያላቸውን እድሜ ጠገብ ቅርሶችን በእራሳቸው ገንዘብ በመግዛት እና በማሰባሰብ ደግሞ ስማቸው ጎልቶ ይነሳል። መኖሪያ ቤታቸውን እንደ ሙዚየም በመጠቀም፤ የሀገራቸው ቅርሳዊ መረጃ ያለው የቀደምት አበው የታሪክ አሻራ በባዕዳን እጅ ተወርሶ እንዳይቀር፤ ማንነታቸውም እንዳይጠፋ በማሰባሰብ ግምታቸው ከመቶ ሃምሳ ሺህ ፓውንድ በላይ የሆኑ ቅርሶችን በአግባቡ ጠብቀው ይዘዋል።
ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ወደ ተለያዩ ሀገሮች ያደረጓቸውን ጉብኝቶች ተከትሎ፤ ወደ ጀርመን በመጡበት ወቅት እንግሊዝ ሀገርን ጨምሮ በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በማስተባበር ኮሚቴ በማዋቀርና የኮሚቴው አመራር በመሆን በጀርመን ሀገር ለተደረገው ደማቅ አቀባበል ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ የለውጡ ግንባር ቀደም ደጋፊ ናቸው። በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተግባር ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ዋና ክፍል ተጠሪ በመሆን፤ በስደት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ለውጡን መሠረት አድርጎ የተከፈቱትን እድሎች በማጠናከር የሚታዩትን ስህተቶች በማረም፤ ዜጎች በወደፊት የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበረሰባዊ አስተዋጾ እንዲያበረክቱ በማበረታታት የራሳቸውን አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው።
አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግም ከሰሞኑ የዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ልዑካንን በመምራት ከ28 ዓመት በኋላ ሀገራቸው ገብተዋል። እንግዳችን አቶ አለባቸው ደሳለኝ በግል ገንዘባቸው የሰበሰቧቸውን ቅርሶች እና የወደፊት ዕጣ ፋንታ አስመልክቶና በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ለመምከር ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከእንግዳችን ጋር በዚህና በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ውይይት እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡- ከኢትዮጵያ ውጭ በነበርዎ ቆይታ ዲያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ ላይ እንዲሳተፍ በማስተባበር እንዲሁም ስልጣን ላይ የነበረው መንግስት የሚሰራቸውን ኢ-ፍትሃዊ ተግባራት በግልፅ የሚቃወሙ ሰልፎችን በማዘጋጀት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ ቆይተዋል። ይህን ለማድረግ ያስገደዶት የተለየ ምክንያት ካሎት ይንገሩንና ውይታችንን ብንጀምር?
አቶ አለባቸው፡– የሚገርምሽ በተለይ የነበረውን መንግስት እቃወም የነበረው በእኔ ላይ በደረሰው ነገር ተነሳስቼ አይደለም። በመሰረቱ በብቀላ የማምን ሰው አይደለሁም። ግን ኢትዮጵያን በተመለከተ ከፍተኛ የሆነ የመቆርቆር ስሜት ስላለኝ ነው። አያቴም ሆነ ቅድም አያቴ አርበኞች ነበሩ። በተለይ አያቴ ሀበሻ አግደው ማይጨው ላይ ጣሊያንን ሲታገሉ ነው የሞቱት። አክስቶቼም እጅግ ብርቱ የሴት አርበኞች ነበሩ። ይሄ የአርበኝነት ታሪክ ታዲያ ዝም ብሎ የመጣ አይደለም፤ ለሀገራቸው ካላቸው ጥልቅ ፍቅር የመነጨ እንጂ!። እኔም ያንን ታሪክ እየሰማሁ በማደጌ ኢትዮጵያ ሲባል ያመኛል።
ወታደር እያለሁ በኤርትራ በርሃዎች ላይ የጦር ሜዳ ውሎን በምዘግብበት ጊዜ ጀግኖች ለሀገራቸው ዋጋ ሲከፍሉ፤ መተኪያ የሌለውን ህይወታቸውን ለሀገራቸው ሲሰጡ አይቻለሁ። እነዚህ ለሀገራቸው የተዋደቁ ጀግኖች ያላቸውን ኮቸሮ እያከፋፈሉን እነሱ ሳይበሉ ለእኛ እየተዋደቁ ያለፉ የጦር ጓዶቼን ሳስብ አሁንም ድረስ ልቤ በኀዘን ይደማል። እነዚህ ጀግኖች ምንም እንኳን ዛሬ በህይወት ባይኖሩም ያሳለፉት ስቃይና መከራ በአይኔ ላይ ተቀርፆ ነው የቀረው። የራሳቸውን ቤት አፍርሰው የኢትዮጵያን ቤት በአጥንታቸው በደማቸው ሰርተዋል። ይህንን ማየት እኔ ለነበርኩበት ትውልድ ጥሎት ያለፈው ሃላፊነትና ግዴታ ዛሬ ላለው ማንነቴ መሰረት ጥሏል።
የሰው ልጅ በጦር ሜዳ ላይ አካሉ ተቆራጦ ወድቆ የሚቀብረው እንኳን አጥቶ የአሞራ ሆኖ ቀርተዋል። እነዚህን ነገሮች ሁሉ እያየሁ ማለፌ ነው ለሀገሬ የተለየ ፍቅር እንዲኖረኝ ያደረገኝ። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ስለተወለድሽ ብቻ ኢትዮጵያዊ ልትሆኚም ልትወጂም አትቺይም። በተለይም የቤተሰብ አስተዳደግ ትልቅ ወሳኝ ሚና አለው። አሁን ላይ ይሄ ሁሉ ፍጅት የመጣው ታሪካችንን ጠንቅቀን ካለማወቃችን ነው። ታሪካችንን ጠንቅቀን በማወቃችን ደግሞ እኛ ተርፈናል። ኢትዮጵያንም ለማትረፍ ታግለናል።
ውጭ በነበርኩባቸው ጊዜያት ኢትዮጵያ ችግር ባጋጠማት ቁጥር በግንባር ቀደምትነት ነው የምገኘው። በነገራችን ላይ እኔ የማንም ፖለቲካ ፓርቲ አባልም፤ ደጋፊም አይደለሁም። በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ግን ከመጀሪያው ረድፍ ላይ ነው የምገኘው። ከእንግሊዝ ባሻገር በመላው አውሮፓ በሚካሄዱ ሰልፎችና ስብሰባዎች ላይ በማስተባበርም ሆነ በመሳተፍ ባሉት አጋጣሚዎች ሁሉ ለሀገሬ ድጋፍ ሳደርግ ነው የቆየሁት።
ከዚያ አልፎም የእንግሊዝ ማህረሰብ ታሪካችን ማወቅ አለበት በሚል የኢትዮጵያ የቅርስ ማበልፀጊያ ማህበር አቋቁሜያለሁ። በዚያ ማህበር አማካኝነት ላለፉት 24 ዓመታት በግል ገንዘቤ በመላው ዓለም ያሉትን የኢትዮጵያን ቅርሶች በመግዛት እየሰበሰብኩኝ አስቀምጣለሁ። አሁን ላይ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ሙዚየም እንዲከፈት ዋና ግፊት እያደረኩኝ ነው ያለሁት። እነዚህን ከማስተባበርና ከመሰብሰብ ባሻገር ከአክሱም ሃውልት ጀምሮ እስከ አፄ ሹሩባ ድረስ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ የራሴን አስተዋፅኦ አበርክቻለሁ። በተለይም የመቅደላ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ውስጥ ከሪቻርድ ፓንክረስት ጋር በመተባበር እንሰራ ነበር።
አስቀድሜ እንዳልኩሽ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ከመሬት ተነስቶ አይፈጠርም። ሀገርሽን የምትወጂ ከሆነ በተግባር ማረጋገጥ አለብሽ። ለኢትዮጵያ ከተባለ ደግሞ ዋጋ መክፈል አለብሽ። እኔ ቤትም ሆነ መኪና የለኝም። ግን ከ180 ሺ ፓውንድ በላይ ወጪ በማውጣት አባቶቻችን ለዓለም ስልጣኔ ያበረከቱትን ዋጋ ያላቸውን ታሪካዊ ቅርሶች በሌላ ባዕድ እጅ እንዳይገኙ ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርጌያለሁኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እነዚያን ቅርሶች ሲያሰባስቡ የኖሩት አሁን ለመገንባት የታቀደውን ሙዚየም በማሰብ ነበር?
አቶ አለባቸው፡– እኔ ቅርስ የሌለው ህዝብ ከወደቀበት ቦታ የሚነሳበት ምርኩዝ የለውም ብዬ ነው የማምነው። በነገራችን ላይ ምዕራባውያኑ ቅርስሽንና ታሪክሽን የሚዘርፉት አንገት ለማስደፋት እና ባዶ ሊያደርጉሽ ስለሚፈልጉ ነው። እንደእኔ እምነት እነሱ ታሪካችንን ሊነግሩን አይገባም። ራስሽንና ታክሪክሽን ስታከብሪ እነሱም ያከብሩሻል። በተለይም እንግሊዞች በጣም ብልጥ በመሆናቸው እንደዚህ ስትበረቺ አቅም ሲኖርሽ ያከብሩሻል። ለዚህም ነው እኔ በኢትዮጵያን በማስተዋወቅ በሰራሁት ስራ እነሱ ሚሊኒየማቸውን ሲያከብሩ የእውቅና ሽልማት የሰጡኝ። ዛሬ ለንደን በሚገኝ ሙዚየም ውስጥ የእኔ የሕይወት ታሪክ አለ። አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ቅርሶች ባሉበት ቦታ እየዞርኩ እመዘግባለሁኝ። አንዳንድ መመለስ ያለባቸው ቅርሶች እንዲመለሱ የበኩሌን ጥረት አደርጋለሁ። መመለስ ባይችሉ እንኳን ዋጋ ያለውን ቅርስ በማይክሮ ፊልም አስቀዳዋለሁኝ። ሌሎቹን ደግሞ አቅም በፈቀደ ቁጥር እመዘግባለሁ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ገጠመኜን ልንገርሽ፤ የመቅደላ ቅርሶችን አንድ ቦታ ላይ ሳሳድድ ኢምፔሪያል ዋር ሙዚየም በሚባል መዘክር ስጎበኝ አፍሪካውያኖች ለባርነት ሲጋዙ የታሰሩበት ሰንሰለት ተደርድሮ ተመለከትኩኝ። አንድ ቦታ ላይ ግን ነጮች መቅደላ ላይ የታሰሩበት ሰንሰለት ሳይ ልቤ ስንጥቅ ነው ያለብኝ። ይህ ሁሉ ጥቁር ህዝብ በባርነት ሲጋዝ በነበረበት ሁኔታ አንድ ኢትዮጵያ ግን ለነጮች ያልተንበረከከች ሀገር መሆንዋን የሚያሳይ ማስረጃ በማየቴ እጅግ ተደንቅሁኝ። ያ ሁኔታ በኢትዮጵያዊነቴም ሁልጊዜም እድኮራ አድርጎኛል። ኢትዮጵያዊነት መጨረሻውን ልኩን ያየሁበት ሰዓት ስለሆነ የመንፈስ ኩራት ይሰማኛል። ይህ ሁኔታ ዛሬም ድረስ ተጨማሪ ነዳጅ ሆኖ ያገለገለኝ ነው ያለው። የእኛ አባቶች ለዚህች ሀገር የከፈሉትን ዋጋ ብናውቅ ኖሮ ዛሬ ያለንበት ተራ ትርምስ ውስጥ አንገባም ነበር ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት 27 ዓመታት ልክ እርሶና ጥቂት ዲያስፖራዎች በስተቀር ሌላው ውጭ ያለው ማህበረሰብ ለሀገሩ በዚህ መልኩ ዘብ ሲቆም፤ በኢኮኖሚም ሲደግፍ አይስተዋልም። ይህ ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
አቶ አለባቸው፡- ምንድነው መሰለሽ፤ በተለይ እኛ በተሰደድንበት ወቅት በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ተፅዕኖ ነበር። እርግጥ ነው እንደ ህንድ ቻይና ያሉ ሀገራት በዲያስፖራዎቻቸው ብርቱ ድጋፍ ማድረግ ችለዋል። አሁን ላይ እንኳን እነግሪክ መቆም የቻሉት በዲያስፖራው ድጋፍ ነው። የትም ዓለም ያለ ዲያስፖራ ገንዘቡን ይዞ የሚሸሸው በዲያስፖራው ገንዘብ ነው። እኔ በምኖርበት እንግሊዝ ውስጥ የህዝቡን ግማሽ የሚያክሉት ህንዶች ቢሆኑም እያንዳንዱ ህንዳዊ ከመኖሪያ ቤት በስተቀር ገንዘቡን በሙሉ ወደ ሀገሩ ነው የሚልከው።
ወደእኛ ስትመጪ ግን ይህንን አታይም። ይህ የሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ በነበረው መንግስት የፖለቲካ ጫና ምክንያት ነው። ፀረ-መንግስት አቋም የነበራቸውም ድርጅቶች ኢትዮጵያውያኖችን የእነሱ መፈክር ተሸካሚና አጃቢ ከማድረግ ባለፈ የሰሩት ስራ የለም። ሁሉም የራሱን የፖለቲካ አጀንዳ ይዞ ነው እንጂ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሀገራዊ ስሜት ኖሮት አልነበረም። ከዚያ በኋላም ቢሆን ዲያስፖራውን በጎሳ፤ በቋንቋ ሲከፋፍሉት ነው የኖሩት። እነሱን ወደ ስልጣን ሊያመጣ የሚችል አድርገው ስለሆነ ያዘጋጁት ዲያስፖራው ደግሞ ካለበት ችግርና ስለሀገሩም ደግሞ ጠንቅቆ ያወቀ ባለመሆኑ የተነሳ ለእንደዚህ አይነት አደጋዎች የተጋለጠ ነበር።
አብዛኛው ዲያስፖራ ስለሀገር ከምታወሪው ይልቅ ስለክልል እና ብሄር ብታወሪው የሚመረጥ ነው። በዚህ የተነሳ ስር የሰደደ መከፋፈል ነበር። በመሰረቱ የመንግስትም የውጭ ፖሊሲው ይሄ ነበር። የውጭ ፖሊሲው ዋነኛ ዓላማው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያኖችን መበተን እስከሚመስል ድረስ የውጭ ጉዳዩ ሰራተኞች ልዩነትን የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎችን ነበር ሲያደርጉ የኖሩት። የኤምባሲዎቻችን ሰራተኞችም ዲያስፖራውን በማስተባበር ለአገር ጥቅም ማዋል አልቻሉም።
ማህበራትንም የሚያደራጁት ራሳቸው በፈለጉት ሁኔታ ነበር። አሁንም ቢሆን የአማራ ዲያስፖራ፤ የኦሮሞ ዲያስፖራ እየተባለ ነው በመሃላችን መከፋፈል እንዲፈጠር እየተደረገ ያለው። በዘር ከፋፍለው ስለበተኑት ወደአንድነት ለመምጣት በጣም አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል። እርግጥ ነው፤ አሁንም በኢትዮጵያ ችግሮች ላይ ግንባር ቀደም ሆኖ እየተሰለፈ ያለና እንደእኔ የሀገሩ ፍቅር ዛሬም ያልበረደለት ከልቡ ለህዝቡ ዘብ የቆመ ዲያስፖራ አለ። በተለይ ከለውጡ ወዲህ ዲያስፖራው ወደ አንድነት የመምጣት እሳቤ ይዞ እየሰራ ነው። ዶክተር ዐቢይን በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ ስራ እየሰራ ነው ያለው።
ከዚህ ቀደም በነበረው ሁኔታ ግን የበሰበሰ እንቁላልና ቲማቲም ይዘን የመንግስት ባለስልጣኖችን ስናባርር ነው የቆየነው። ዶክተር አብይ ጀርመን ሀገር ሲመጡ ከእንግሊዝ ሀገር የአውሮፕላን ትኬት ቆርጦ የሄደው በርካታ ዲያስፖራ ነው። በዚያ መድረክ ላይ እኔ የዲያስፖራው ተወካይ ሆኜ ንግግር አድርጌያለሁ። በአጠቃላይ አሁንም ዲያስፖራው በለውጡ ላይ ትልቅ ተስፋ አለው። በተለይም ጁንታው የጦር ሃይሉን ከመታው በኋላ ከጫፍ እስከጫፍ ነው የተነቃነቀው። ኢትዮጵያን ለማጥፋት በሚደረገው ዘመቻ ላይ ከጁንታው ልጆችና ደጋፊዎች በስተቀር ሁሉም በሚባል ደረጃ ለሀገሩ ዘብ የቆመበት ወቅት ነው ማለት እንችላለን። አሁን እኔ ይዤ የመጣሁት የዲስያፖራ ልዑካን ቡድን የኢትዮጵያ የገባበት ዋና ምክንያትም ለሀገሩና ለህዝቡ ያለውን አለኝታነት ለማረጋገጥ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እስቲ አሁን ደግሞ እርሶ ስላሉበት የዲያስፖራ የተግባር ምክርቤት ምንነትና ስራ ያጫውቱን?
አቶ አለባቸው፡– የዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የተመሰረተው በዓለም ላይ ያለን አክቲቪስቶች በማህበራዊ ሚዲያ በምገናኝበት መድረክ አማካኝነት ነው። በተለይም ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ጁንታውና ደጋፊዎቹ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርጉትን ሲራ በማጋለጥና የለውጡን ሃይል በመደገፍ ረገድ ትልቅ ስራ ሰርተናል። በየኤምባሲው ላይ ሰንደቅ ዓላማዎቻችን እየወረዱ ሲጣሉ ትልቅ ቁጭት ነው ተፈጥሮብን የነበረው።
በተለይም እንግሊዝ በነበረው ሁኔታ ሰንደቅ ዓላማችን እንዳይወርድ እስከመጨረሻው ድረስ ብርቱ ትግል አድርገናል። እኔ በነበረኝ ቅርበት የተለያዩ ሚዲያዎች ላይ እየገባሁ ሴራውን ለማጋለጥ ሃላፊነቴን ስወጣ ነበር። በተለይ አብዛኛዎቹ ጋዜጠኞች ያውቁኝ ስለነበርና ጀርመን ሬዲዮ ፕሮግራም እስራ ስለነበር ያንን አጋጣሚ በመጠቀም የወያኔ ሥርዓት እንዲንኮታኮት ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ነበር ስንሰራ የነበረው።
እንደምታውቂው ደግሞ ጋዜጠኛ በሙያው የህዝብ ወታደር ነው። እያንዳንዱን ጉድፍ እንደወረንጦ ሆኖ ለህዝብ ፍርድ የማቅረብ ሃላፊነት አለበት። በዚህ መሰረት በመላው ዓለም ያሉ ጋዜጠኞች ድጋፍ አድርገውልናል። ከዚያ በኋላ የዲያስፖራ ምክር ቤት መቋቋም አለበት በሚል እሳቤ ከተለያየ ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያኖች ተሰባስበን ያንን እውን ለማድረግ የሰራነው ያለነው። የሚገርምሽ እርስበርሳችን በአካል ባንተዋወቅም ከአንድ ዓመት በላይ ኢትዮጵያ አትፈርስም እያልን ስናስተባብር ቆይተን የተገናኘነው በቅርቡ ሀገራችን በገባንበት ወቅት ነው።
በነገራችን ላይ የምክርቤቱ አባላት 125ኛው የአድዋ በዓል በድምቀት እንዲከበር ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከፍተኛ ስራ ሲሰራ ነው የቆየው። በዓሉ ዓለምአቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ትልቅ ስራ ሰርተናል። የአርበኞች የምስጋና ቀን በሚልም ጀግኖቻችንን የማክበር፣ የማወደስና የመደገፍ ተግባራትን ስንሰራ ቆይተናል። አሁንም በትውልድ ቀረፃ ላይ ከፍተኛ ስራ እየሰራን ነው ያለነው። መከላከያም መጀመሪያ በጁንታው ከተመታበት ጊዜ ጀምሮ ድጋፍ ስናደርግ ቆይተናል። በጎፈንድ አማካኝነት በርካታ ገንዘብ ድጋፍ አድርገናል።
በህዳሴ ግድብም ሆነ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ምክር ቤቱ ብቻውንም ሆነ ከተለያዩ አጋሮች ጋር በመተባበር የሰራቸው ስራዎች አሉ። በተቻለ መጠን በህዳሴው ግድብ ላይ ሰው ስለ አባይ ወንዝ እውቀት እንዲኖረው ብዙ ፅፌያለሁኝ። በየጊዜው የግል ገንዘባችን እያዋጣንና የፈጠራ ሃሳቦችን እያመጣን ኢትዮጵያን ይጠቅማሉ በሚባሉ ነገሮች ሁሉ ተሳትፈናል። አሁን እንኳን እዚህ የመጣነው በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ሀገራት እንቅስቃሴ ገደብ ቢጥሉም በእምቢተኝነት ስሜት ነው ለሀገራችን አለኝታነታችንን ለማሳየት ከየሀገሩ ተሰባስበን የመጣነው። ሀገራችን ሰው በሚያስፈልጋት ሰዓት ሰው ሆነን መገኘት አለብን በሚል ነው ተነሳስተን እያንዳንዳችን ሁለት ሁለት ሺ ዶላር አዋጥተን የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳያጋጥመው ያደረግነው። ይህ ገንዘብ የሚውለው በዋናነት የጎርጎራን ፕሮጀክት የማልማት እቅድ ስላለን ለዚያ ዓላማ ነው።
ሌላው የዲያስፖራ ሙዚየምን እዚህ ሀገር ለመገንባትና መሰረት ለመጣልና ቅርሶቻችን ወደዚህ ሀገር እንዲመለሱ ለማድረግ ነው። በዚህ ፕሮጀክት አማካኝነት ዲያስፖራው ማረፊያ የሚሆኑ ስራዎች ይሰራሉ። ይህም ቱሪዝም እንዲስፋፋና የውጭ ምንዛሬ ግኝታችንን እናሳድጋለን ማለት ነው። ወደፊት በጣም በትልቁ የምንሰራበት ይሆናል።
በነገራችን ላይ ይህንን ሙዚየም ፕሮጀክት ከጀመርን ሶስት ዓመት ሆኖታል። የተጠነሰሰውም ዶክተር ሂሩት እንግሊዝ በመጡበት ጊዜ እኔ ያሰብሰብኳቸውን ቅርሶች ከተመለከቱ በኋላ ከመንግስት ምን እንደምፈልግ ሲጠይቁኝ እነዚህ ቅርሶች ተገቢ ቦታ እና ክብር የሚሰጥ ሙዚየም እንዲገነባ በጠየኩት መሰረት ነው ይህ ፕሮጀክት ተነድፎ ስራ ላይ ለማዋል እየተሯሯጥን ያለነው። እርግጥ ነው፤ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ አሁን ጉዳዩ እልባት አላገኘም። ይህንን ለማስፈፀምና መሬት ለማውረድ በምናደርገው ጥረት ውስጥ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ቢሮክራሲ እንቅፋት እየፈጠረብን ባሰብነው ጊዜ እውን ለማድረግ አዳጋች አድርጎብናል። እስካሁን ባለው ሁኔታ የየመስሪያቤቱ አመራር መልካም ፈቃድ ካልታከለበት በስተቀር በአሰራር ሥርዓት የሚሰራ ነገር አላየሁም።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶች የኢትዮጵያዊነት ስሜት አሁን ላይ ጨርሶ በመጥፋት ላይ ነው ብለው ያምናሉ፤ ለዚህ ደግሞ ህገ-መንግስቱንና የህወሓትን መንግስት ይወቅሳሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ አለባቸው፡– እንዳልሽው ይህ ሁኔታ ለእኔ ከባድ ነው። እንደአንድ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ይህ የህወሓት የልዩነት ስትራቴጂ ያመኛል። እነዚህ ሰዎች ባለፈው 27 ዓመታት የጨለማ ዘመን ውስጥ ህዝቡን መክተታቸው ሳይበቃ ኢትዮጵያንም ገለው ነው የሄዱት። አሁንም በደረሱበት ሁሉ ኢትዮጵያን እየገደሏት ነው ያሉት። እኔ ኢትዮጵያን በዚህ ደረጃ ለማፈራርስ ምን አይነት ሰይጣናዊ ተልዕኮና አምልኮት እንዳላቸው ለመረዳት ይከብደኛል። የሚያሳዝነው ነገር ኢትዮጵያ ጠንክራ እንዳትወጣ ከውጭ ጠላት በላይ በትግራይ ውስጥ መሽጎ ያለው የጁንታው ቡድን ነው። ይህ ሃይል የማይሽር ጠባሳ ኢትዮጵያ ላይ አኑሯል። ከሀገር አልፎ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያኖችም እንዲበተኑ በማድረግ ብቻ ሳይሆን በኤምባሲው አካባቢ ተሰግስገው የነበሩት የስዩም መስፍን እና የቴድሮስ አድሃኖም ቤተሰቦች ሴራ እስካሁንም ያልጠራ ጉዳይ ነው።
እንደሚታወቀው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአሁኑ ወቅት ሪፎርም አደርጋለሁ ብለው የተነሱትም ለዚሁ ነው። አብዛኛዎቹ የኤምባሲ ሰራኞች ለሀገራቸው መልካም አመለካከት ቢኖራቸውም ክፉዎቹ ደግሞ አሁንም ወደ ሀገር አልተመለሱም ኢትዮጵያን ከድተዋታል። በነበሩበትም ሰዓት የኢትዮጵያ ባንዲራ እየወረደ እንዲቃጠል በር እየከፈቱ ኤምባሲ ውስጥ ሲያስገቡ ነበር የነበረው። ይህንን አይነት መጥፎ ሴራዎች እየሰሩ ያሉ ኢትዮጵያውያኖች አሁንም አሉ። እናም በአጠቃላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የነበሩ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ናቸው ለውድቀታችን መነሻ የሆኑት። ህዝቡንም ሆነ ብለው ይከፋፍሉት ነበር።
በነገራችን ላይ እኔ በ28 ዓመት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የሀገሬን መሬት መርገጥ የቻልኩት። ሀገሬ እንዳልገባ ለንደን ላይ ከተከሰሱት ሰዎች ውስጥ አንዱ ነኝ። በመሰረቱ እኔ የማንም የፖለቲካ ድርጅት አባል ባልሆንም የፖለቲካ አክቲቪስት ተብዬ ክስ ከተመሰረተባቸው ሰዎች አንዱ ነበርኩ። የሚገርመው በጀርመን ድምፅ ሬዲዮም ሆነ በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ድምጼ እንዳይሰማ አግደውኝም ነበር። ብዙ ጊዜ የእኛ አትሌቶች በሚሮጡበት ወቅት እዛ ላይ እሳተፋለሁ። ሁልጊዜም ታዲያ ቦርሳዬ ውስጥ የኢትዮጵያ ባንዲራ አይጠፋም። ልክ አትሌቶቹ ሮጠው ሲያሸንፉ የሀገሬን ባንዲራ የምሰጣቸው እኔ ነኝ። እነ ሃይሌን ጨምሮ የደጋፊዎች ማህበር አቋቁሜ ስታዲየሞ በደጋፊዎች እንዲሞላ በማድረግ ረገድ ትልቅ ስራ መስራት ችያለሁ።
አውቶብስ እየተከራየን ይዘን እየሄድን የኢትዮጵያን ዝናና ስም እንዲታወቅ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እናደርግ ነበር። ሆኖም ይህ ሁኔታ የነበረውን መንግስት አላስደሰተውም ነበር። ለሯጮቹ የምሰጠው የቀድሞውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ መሆኑ ይበልጥ እያበሳጫቸው መጣ። ከእኔም አልፎ አትሌቶቹ አሸንፈው ሀገራቸው ሲገቡ ለምን ያንን ባንዲራ ያዛችሁ በሚል ከባድ ፈተና ይደርስባቸው ጀመር።
እኔም ከሙያው ሥነምግባር ውጭ ነው የሚሰራው ተብዬ በለንደን ማራቶን ላይ ክስ ቀረበብኝ። ይሄ የኢትዮጵያን ክብር የሚመጥን ባንዲራ አይደለም፣ የነፍጠኞች ነው ብለው በኤምባሲ ደረጃ ለምሰራበት ተቋም ደብዳቤ ፅፈውብኝ ነበር። ይሁንና ሰዎቹ ደንታ አልሰጣቸውም። የደረሰብኝ ነገር የለም። እናም እነዚህ ሰዎች አይደለም ሀገር ውስጥ ያለውን በውጭ ተሰዶ ያለውን ዜጋ ሳይቀር ስራውን እንዳይሰራ የማያደርጉት ተፅእኖ የለም። በመሰረቱ እነዚህን ፅንፈኛ ሃይሎች መታገሉ በራሱ አንዱ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው። አሁንም ቢሆን ለሃገሬ ዝመት ብባል በደስታ ነው የምዘምተው።
አዲስ ዘመን፡- ከስልጣን ዘመናቸው አልፎ አሁንም በቀሰቀሱት ጦርነት በበርካቶች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየፈፀሙ ነው ያሉት። እንዳውም እርሶ ለረጅም ጊዜ ከአገር ውጭ እንደመቆየትዎ የዓለም ህብረተሰብ የህወሓት ትክክለኛ መሰሪ ባህሪ ተገንዝቧል ብለው ያምናሉ?
አቶ አለባቸው፡– ትክክለኛና መሰረታዊ ጥያቄ ነው ያነሳሽው። ይሄ ጥያቄ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መመለስ የሚገባው ጥያቄ ነው። እንደእኔ እምነት በተለይ በመንግስት በኩል አንድ የሆነ የዲፕሎማሲ ሽንፈት ነበር። በዚያ ውስጥ እነዚህ አኩራፊ የሚባሉት ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመከራከር እኛ ከስራ መጥተን እንቅልፍ አጥተን ስንጮህ እንደመንግስት ግን ያገባናል ብለው የሰሩት ስራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ያ ሁሉ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በቢሲ በአልጀዚራ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲነዛብን የእኛ የመንግስት ባለስልጣኖች እንደመንግስት ያገባናል የመልስ ምት መስጠት አልቻሉም። ሚዛናዊ ዘገባ በሚዲያ እንዲሰራም ስለሀገራቸው አልሞገቱም። በየሀገሩ ያሉት ዲፕሎማቶቻችን የየሀገሩን ባለስልጣናት የማናገር የመገሰፅ መብት አላቸው።
የሚሾሙት ባለስልጣናት የሚሄዱበትን ሀገር ባህልና ቋንቋ አያውቁም፤ ጥራዝ ነጠቅ ነገሮችን ነው ይዘው የሚጓዙት። ዲያስፖራውንም አያውቁትም። ታሪኩን ባህሉን በማታውቁበት ማህበረሰብ ነው የሚሄዱት። ብቃትና ችሎታቸውን ከማሳግ ይልቅ ‹‹እከሌ ለውጡን አይደግፍም፤ እከሌ ለውጡን ይደግፋል›› እያሉ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ላይ ሪፖርት ማድረግ እንደ ዋና ስራና ልዩ ችሎታ አድርገው የሚወስዱ ናቸው። መስራት የሚገባቸውን ስራ ቢሰሩ ኖሮ እንደዚህ አይነት ብሄራዊ ውርደት በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ሊመጣ ይችላል ብዬ አልገምትም። ያንንም ባለመስራታቸው ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን እርምጃ ለመውሰድ የተገደዱት። እኛም የዲጂታል ዲፕሎማሲ ስራ የጀመርነው እነሱ ሃላፊነታቸውን መወጣት ባለመቻላቸው ነው።
ወደ አንቺ ጥያቄ ስመለስ በሰሜኑ አሁን የተነሳው ጦርነት ቅርንጫፎቹን ሁሉ ሰዶ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ እንዲስፋፋ ሲደረግ አስቀድሞ ከእኛ በላይ በገንዘብ ወደ 26 ቢሊዮን ዶላር ነው ተዘርፎ የወጣው። ይህም ማለት ሌላ አዲስ አበባ ከተማ መገንባት የሚያስችል ገንዘብ ነበር። ወይም ኢትዮጵያ ያለባትን ብድር የምትሸፍንበት ነው። በመሰረቱ ወያኔ ይህንን ጦርነት የቀሰቀሰው ለትግራይ ህዝብ አስቦ ሳይሆን ለፎቅ አስመላሽ ኮሚቴዎች ጥቅም ሲል ነው። ከ400 በላይ ፎቆች ባለቤት አልባ ሲሆኑ የትግራይ ህዝብ ግን ቆፍሮ የሚጠጣው ውሃ የለውም ነበር። ስለዚህ እነዚህ ፎቅ አስመላሽ ሃይሎች የከፈቱትን ጦርነት ለመመከት ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት የራሱ የሆነ ስትራቴጂ ቀይሶ ዓለምአቀፍ ተፅዕኖዎችን መቋቋም የሚያስችል ስራ ብዙም አልተሰራም። አሁን ላይ ግን ብዙ መሻሻሎች አሉ። መንግስት በተወሰነ መልኩም ቢሆን ተንቀሳቀሶ እውነታውን ለማሳወቅ በመጣሩ አሁን የዓለም ህዝብ ዓይኑን እየገለጠና እውነታውን ለመረዳት እየሞከረ ነው። ለምሳሌ ሰሞኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኒውዮርክ ሄደው የሰሩት የዲፕሎማሲ ስራ ምዕራባውያኑ ራሳቸውን እንዲፈትሹ ያደርጋቸዋል ብዬ አምናለሁ።
ለዓመታት የዘረፉት ገንዘብ ግን አሁንም ግልገል ባንዳዎቹ ለፀረ ኢትዮጵያ ትግላቸውና ሴራቸው እየዋለ ነው የሚገኘው። በመሆኑም አሁን ኢትዮጵያ ከምታካሂደው ጦርነት በላይ የዲፕሎማሲው ጦርነት በፍፁም ፋታ ሊሰጣት አልቻለም። እናም ዲያስፖራው ግን ከለውጡ ሃይል ጎን በመቆም ስለተነሳ አንፃራዊ የሆነ የዲፕሎማሲ ስኬት እየተገኘ ነው። በነገራችን ላይ ምዕራብያውያኑ አሁን ላይ ጫናዎቸቸውን ለማንሳት ምንተፍረት ስለሆነባቸው እንጂ እውታውን ሳይረዱት ቀርተው አይደለም። ይህ የጁንታ ቡድን ከአሁን በኋላ ተመልሶ ሀገር ይመራል ብለው በማመን አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ምንም እንኳን ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጡ ችግሮች ባሻገር ኢትዮጵያ ተስፋ ያላት ሀገር መሆን በተጨባጭ በማሳየት ረገድ ከማን ምን እንደሚጠበቅ ይንገሩንና ውይይታችንን እናብቃ?
አቶ አለባቸው፡- በመጀመሪያ ደረጃ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ማንም ሰው ተስፋ ሊቆርጥ አይገባውም። ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረ ሥርዓት ያለፈች ሀገር ናት። ብዙ ችግሮች እና ከዚህ በባሰ ሁኔታ ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ ችላለች። ዝም ብላ ተጠፍጥፋ ተሰርታ በአንድ ቀን እዚህ የደረሰች ሀገር አይደለችም። ስትወድቅ ስትነሳ፤ አባቶቻችን እየሞቱ አፅማቸው አጥር እየሆነ እየገነቧት ያቆዩልን ሀገር ናት ያለችን። እነዚህ በየአደባባዩ ቆመው የምታያቸው ሃውልቶች የከተማ ማጌጫ አይደሉም፤ የታሪክ ማስታወሻዎቻችን እንጂ!። የእኛ አባቶች ለሀገራቸው የከፈሉትን ዋጋ የሚያስታውሱን ምልክቶቻችን ናቸው።
እንደዚህ አይነት ነገሮች መበራከት አለባቸው። ለሀገራቸው ታሪክ ሰርተው ያለፉ ሰዎች ከየጉራንጉሩ አፅማቸው ተሰብስቦ ለእነሱ መታሰቢያ የሚሆን ሃውልት መቋቋም አለበት። ከሀገር ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ለአገር መክፈል የሚገባውን ውለታ መገንዘብ ነው ያለብን። ይህንም ደግሞ ለምሳሌ እያንዳንዳችን አንድ ህፃን ልጅ ብናሳድግ፤ ተካፍለን ብንበላ የተሻለ ለውጥ መምጣ ይችላል ብዬ አምናለሁ። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እጅ ለእጅ ተያይዞ ከወደቀበት ቦታ በመነሳት አቧራውን ጠርጎ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማምጣት አለበት።
በመንግስት ደረጃም በመላው ዓለም ላለው ዲያስፖራ ብሄራዊ የዜግነት ግዴታ ጥሪ መደረግ አለበት ። አቅሙ በሚፈቅደው መጠን ወደ ሀገሩ ገብቶ መደገፍ አለበት። በዓለም ላይ ብዙ ምሁራኖች አሉን፤ ለአንድ ወር ለሁለት ወር ቢመጣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎችን ቢያስተምር፤ በህክምና ዘርፍ ቢያገለግል ቀላል ድጋፍ አይደለም። ስለዚህ ልክ እንደእናት ሀገር ጥሪ በተለያየ ሙያ ውስጥ ላሉ ሁሉ መጥተው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ ብሄራዊ ጥሪ ሊደረግ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ አለባቸው፡- እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2014