እንኳን ለኢሬቻ በዓል አደረሳችሁ!
የኦሮሞ ሕዝብ ፍቅር፣ ወንድማማችነት እና ዕርቅን በሚገነቡ ባህላዊ ዕሴቶች እጅጉን የበለጸገ ሕዝብ ነው። ከእነዚህ ድንቅ ባህላዊ ዕሴቶች መካከል አንዱ የኢሬቻ በዓል ነው። ይህን ትልቅ ባህላዊ ዕሴት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ያበረከቱ ቀደምት አባቶቻችን ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል።
ኢሬቻ – የምስጋና፣ የዕርቅ እና የሰላም በዓል ነው። የፍቅር፣ የይቅርታ እና የአንድነት በዓል ነው። ኢሬቻ መጪው ጊዜ ብሩህ እንዲሆን ቃል የምንገባበት በዓል ነው። ሁሉን አስተካክሎና ውብ አድርጎ የፈጠረ ፈጣሪ የሚመሰገንበት፣ ቀጣዩ ጊዜ ብሩህ እንዲሆን መልካም ምኞት የሚቀርብበት በዓል ነው።
ኢሬቻ- ትናንትን የማመስገኛ እና ነገን ሰላም የማድረጊያ በዓል ነው። ያለፈውን ዓመት አሳልፎ ለዚህ ያደረሰንን ፈጣሪ የማመስገኛ እና ቀጣዩን ዓመት በመልካም ምኞትና በመልካም ተግባር የመጀመሪያ በዓል ነው። ሰው በዋናነት የሚኖረው ከተፈጥሮ ጋርና በተፈጥሮ ውስጥ ነው። የተፈጥሮ ጤና መሆን የሰው ልጅን ጤና ይወስነዋል። የተፈጥሮ መበላሸትም የሰው ልጅን ሥጋት ይጨምረዋል። ለዚህ ነው ቀደምቶቻችን ለተፈጥሮ ዋጋ የሚሰጠውን የኢሬቻን በዓል እንድናከብረው የሠሩልን።
የክረምቱ ወቅት የምግብ እጥረት እና የመገናኛ ችግር የሚከሠትበት ወቅት ነው። ወባን የመሳሰሉ ወረርሽኞች የሚያይሉበት ጊዜ ነው። በዚህ የተነሣ የችግር ወቅት ተደርጎ፣ በጨለማ ተመስሎ ይወሰድ ነበር። ወንዞች በመሙላታቸው ምክንያት መገናኘት አስቸጋሪ ነው። ከላይ ዝናቡ፣ ከታች ጭቃው ኑሮን ከባድ ያደርገዋል። በጥር ወር አካባቢ የተሰበሰበው ምርት በክረምት ወቅት ስለሚያልቅ፣ ክረምቱ በቂ ምግብ የሚገኝበት ወቅት አይደለም።
ይህ ወቅት የሚያልፈው ፈታኙን ጊዜ በጠንካራ ትግል በመገዳደር ነው። በአንድ በኩል ለወቅቱ የሚሆነውን ሰብል በማምረት፣ በሌላ በኩል ለዘለቄታው የሚበጀውን እህል በማረስ ነው – መከራው የሚሸነፈው። በቆሎ፣ ገብስና ድንችን የመሳሰሉ ሰብሎችን ለክረምቱ እንዲደርሱለት አድርጎ ገበሬው ይዘራል። ሌሎቹን ደግሞ ለዓመት ጉርስ እንዲሆኑት ያመርታቸዋል። ጤናን አጥብቆ በመጠበቅ ነው ወረርሽኙን የሚቋቋመው።
ኢሬቻ- በንጹሕ ኅሊናና አስተሳሰብ በፍጹም ደስታ የሚከበር በዓል ነው። በባህሉ መሠረት ወደ ኢሬቻ በዓል ከመገባቱ በፊት የተጣላ ታርቆ፣ ቂም እና ጥላቻ በይቅርታና ፍቅር ታክሞ፣ ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ምኞትን በመግለጽ በታላቅ አንድነትና ኅብረት የሚከበር በዓል ነው። በዓሉ የምስጋናና የአንድነት በዓል በመሆኑ በኦሮሞ ሕዝብ ብቻ የሚከበር አይደለም። ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የኢሬቻን መሠረታዊ ዕሴቶች የሚጋሩ በመሆናቸው በበዓሉ ላይ በባህላዊ አልባሶቻቸው ተውበው፣ እያዜሙ እና እየጨፈሩ የሚያደምቁት፣ ኢሬቻ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያስተሣሥር አንዱ ጠንካራ ሐረግ መሆኑን በተግባር የሚያሳዩበት ዕለት ነው። ስለሆነም በዓሉ የመላው ኢትዮጵያውያን በዓል ነው።
ኢሬቻ- የመሻገር በዓል ነው። በጨለማ ከሚመሰለው ክረምት ወደ ብርሃናማው መጸው፣ ከጥላቻ ወደ ፍቅር፣ ከጠላትነት ወደ ወንድማማችነት፣ ከጸብ ወደ ዕርቅ፣ ከቂም በቀል ወደ ይቅርታ ከክፋት ወደ መልካምነት ሽግግር የሚደረግበት በዓል ነው።
ኢትዮጵያ ሀገራችን የዘንድሮውን ኢሬቻ የምታከብረው በፈተና እና በተስፋ መካከል ሆና ነው። የክረምቱ ወቅት ምንም ፈታኝ ወቅት ቢሆን፣ በገበሬዎቻችን ትግል ግን የተስፋ መፀነሻ ወቅት ይሆናል። በመጸውና በበጋ ወቅቶች ምርት የሚትረፈረፈው በክረምቱ ወቅት በተሠራው ሥራ ነው። የነገዋ ኢትዮጵያ ብልጽግና እንዲትረፈረፍባት ከፈለግን፣ ዛሬ በአስቸጋሪው ጊዜ ችግሩን የሚያስወግድና መጪውን ዘመን ብሩህ የሚያደርግ ሥራ መሥራት አለብን። የሞሉት ወንዞች ይጎድላሉ፤ ጭቃውም ይደርቃል፤ ብርዱም ይሞቃል፤ የሰማይ መስኮቶች ይዘጋሉ፤ የምድር ቀላያት ይከደናሉ።
ከማዶ ብሩህ ተስፋ አለ፤ ከክረምቱ ባሻገር የተዘራው ቡቃያ ፍሬ ያፈራል፣ አበቦች ይፈካሉ፣ ምድር አረንጓዴ ትለብሳለች፤ ከናፈቁት ዘመድ ጋር መገናኘት፣ ገበያ መውጣት፣ መነገድ፣ ከአድማስ ባሻገር በተስፋ ይታያሉ። ፈተናዎቹን በጽናት ተቋቁሞ ወደ ብሩህ ጊዜ በተስፋ የመሻገር በዓል ነው። የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የዕርቅ፣ የመቻቻል፣ የቤተሰባዊነት ዕሴቶች የሽግግሩን ፈተናዎች የሚያሻግሩና ወደ ብሩህ ጊዜ የሚያደርሱ ድልድዮች ናቸው። የመሻገሪያ ድልድዩን ደራሽ ጎርፍና ድንገተኛ አውሎ ነፋስ ሊያነቃንቀው ይችል ይሆናል፤ ግን ከቶውኑም ሊያፈርሰው አይችልም። ድልድዩ በማይፈርሱ ዕሴቶች የተዋቀረ ነውና።
ያለ ጥርጥር ኢትዮጵያ ከፊቷ የሚያስጎመጅ ጊዜ ይጠብቃታል። እንደ መጸው የሚያጓጓ፤ እንደ በጋው የሚናፍቅ ጊዜ ከፊታችን እየመጣ ነው። እንደምታውቁት በአባቶቻችንና በእናቶቻችን ዘመን የነበረው ክረምትና የዛሬው ክረምት የተለያየ ነው። የሰው ልጆች ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት የክረምቱን መከራ ቀንሰውታል፤ መንገዶችንና የመገናኛ መሣሪያዎችን ሠርተው ችግሩን ቀርፈውታል፤ የእርሻ መሣሪያዎችን ፈልስፈው ግብርናን አቅልለውታል፤ የጤና ተቋማትን አሻሽለው የክረምትን ወረርሽኞች እያጠፏቸው መጥተዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን የገጠማትን ፈተና ማለፍ የምትችለው ፈታኙን አምርረን ስንታገለው ነው። ኢትዮጵያን ከፈተና ፈጽሞ መለየት አይቻል ይሆናል። የፈተናውን ዓይነት መቀየር፣ የፈተናውንም መጠን መቀነስ ግን ይቻላል። ይህ አሁን የገጠመን ጉጅሌ አብሮን እንዲኖር ሊፈቀድለት አይገባም። ሰንኮፉ ከኢትዮጵያችን ላይ ተነቅሎ መወገድ አለበት። ባህላችንን፣ እምነታችንን፣ሥልጣኔያችንን፣ አብሮ የመኖር ዕሴታችንን፣ ፖለቲካዊ ካፒታላችንን፣ ሉዓላዊነታችንን፣ መልካም ሰብእናችንን አጥፍቶ ባዶ እጃችን ሊያስቀረን የመጣው ሀገር አፍራሽ ቡድን ካልተወገደ፣ የኢትዮጵያ ብሩህ ዓመት አይመጣም።
ገበሬዎቻችን የክረምቱን ወቅት ለመሻገር የሚሆን ሥራ ብቻ አይሠሩም፤ መጪውን ጊዜ ለመዋጀት የሚያስችል ተግባር ጭምር እንጂ። እኛም አሁን የገጠመንን ፈተና ለማሸነፍ የሚሆን ሥራ ብቻ መሥራት የለብንም። የነገውን የብልጽግና ጉዟችንን የሚዋጅ ጭምር እንጂ። የተወረወሩብን ድንጋዮች ድልድይ እንገንባባቸው፤ ትምህርት ቤት እንሥራባቸው፤ የጤና ተቋም እናንጽባቸው፤ መከላከያችንን እናዘምንባቸው፤ ግብርናችንን እናሠልጥንባቸው፤ የአገልግሎት አሰጣጣችንን እናቀልጥፍባቸው።
ኢትዮጵያ መንገዷን እንደ አዲስ ለመቃኘት በምትዘጋጅበት ዋዜማ ነው የዘንድሮው ኢሬቻ እየተከበረ ያለው። ዴሞክራሲያችን፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን፣ የፍትሕ ሥርዓታችን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሥሪታችን፣ የውጭ ግንኙነትና የሀገር ውስጥ ጉዳዮቻችን በአዲስ ቅኝት ይቃኛሉ። የትናንትናው ስሕተት እንዳይደገም፤ የትናንቱ ፈተና ዳግም እንዳይመጣ፤ የትናንት ፈታኞቻችንም ዳግም ዕድል እንዳያገኙ፤ የትናንቱ ስብራት እንዲጠገን፤ የትናንቱ መዛነፍ እንዲቃና የሚያደርግ አዲስ ቅኝት ያስፈልገናል። የክራሩ ጅማቶች የራሳችን ናቸው። መቃኘትም ያለብን ራሳችን ነን።
የኢሬቻ በዓል ሲከበር ያለፈው ጎርፍ አልፎ በአዲስ ውኃ፣ ደረቁ ሣርም ረግፎ በአዲስ ለምለም ሣር ነው። ያለፈው ይበቃል – የሚል ነው መልዕክቱ። እውነት ነው ያለፈው ይበቃል። የደረቁ ሣሮችንና የደፈረሱ ጎርፎችን – በቃችሁን – ብለን በአዲስ ለምለም ሣር በዓሉን እናከብረዋለን። ነባሩ ምድር አዲስ ሣር ያበቅላል። አዲስ የጠራ ምንጭ ኩልል ብሎ ይወርድበታል። ኢትዮጵያውያን ከዚህ በኋላ የደፈረሱ ጎርፎችን እምቢ ብለዋል። የደረቁ ሣሮችን እምቢ ብለዋል። ለምለም ቄጤማ ይዘው ኩልል ያለውን ምንጭ ፍለጋ መጥተዋል። ማንም ወደ ደረቀው ሣርና ወደ ደፈረሰው ጎርፍ ሊመልሰን አይቻለውም። የደረቀው ሣር እየወጋ፣ የደፈረሰው ጎርፍ እያሠጋ ሊመልሰን ሞክሮ ነበር። “ሆ” ብለን፣ አንድ ሆነን፣ አምርረን፣ ወጥተናል።
ከወጣ ውረዶቹና ከፈተናዎቹ ባሻገር ተስፋ አለ፤ የተሻለ ዘመን የተሻለ ሀገር እንደሚኖረን ማሰብ ያስፈልጋል። ለዚህም በጽናት በተስፋ፣ በጋራ፣ በመቻቻል፣ በቤተሰባዊነት መንፈስ መቆምን ኢሬቻ ያስተምረናል። ፈተናዎቹን በመቻቻል፣ በመረዳዳት፣ በዕርቅ፣ በይቅርታና በሰላም መሻገር የኢሬቻ አስተምህሮት ነው።
መልካም የኢሬቻ በዓል ይሁንልን!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2014