(የመጨረሻ ክፍል)
እንደ ኤሮፓውያን አቆጣጠር ሴፕቴምበር 17 ቀን 1787 ዓም በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ አለው ይለናል ትንታጉ ጉምቱውና ደማሙ ጋዜጠኛ ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ ነፍሱን ይማርና። መቼም በዚች ምድር እንደሱ ልቅም ጥንቅቅ ያለ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛና አርበኛ ጋዜጠኛ ገጥሞኝ አያውቅም። ወደተነሳሁበት ነጥብ ስመለስ በጦቢያ ፣ ቅጽ 7 ፣ ቁ.2 ፣ 1992 ዓ.ም ፣ “እኛም አንናገር እነሱም አይሰሙ፣ የገዥዎቻችን እዳ የለብንም” በሚል ርዕስ ባስነበበን መጣጥፉ።
39 ልዑካን ከ12 ግዛቶች ተወክለው የሕገ መንግስት ጉባዔ መስርተው የውይይታቸውና የእጃቸው ፍሬ የሆነውን ሰነድ ለህዝቡ ያቀረቡበት ዕለት ነበር። እኔ ደግሞ ወሳኝ መታጠፊያ /critical juncture /እለዋለሁ። ታሪኩ እንደሚለው በዚህ ዕለት አንዲት ሴት ከአሜሪካ መስራች አባቶች አንዱ የነበሩትን ቤንጃሚን ፍራክሊን ዘንድ ቀርባ፤ “እህሳ ዶክተር ምን ተገኘ? ሪፐብሊክ ወይስ ግዛተ ዘውድ!” ብላ ትጠይቃለች ። እሳቸውም ወዲያው ቀበል አድርገው፤ “ሪፐብሊክ ነው_ልትጠብቂው ከቻልሽ” (A Republic if you can keep it) ሲሉ መለሱላት። ባልጠብቀውስ!? ብትላቸው መቼም መልሳቸው ፈላጭ ቆራጭ የእንግሊዝ ግዛተ ዘውድ ወይም አምባገነን ቅኝ ገዥ ነበር የሚሏት ብየ አምናለሁ። የአሜሪካ መስራች አባቶች ይህቺን ወሳኝ መታጠፊያ ሳያባክኑ መጠቀማቸው ለዛሬዋ አሜሪካ በቅተዋል።
ዘመናዊው ኢትዮጵያ ታሪክ ከባተ ማለትም ከአጼ ቴዎድሮስ ንግስና 1847 ዓ.ም እስከ መጪዋ ማክሰኞ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ እልፍ አእላፍ የሆኑ ወሳኝ መታጠፊያዎችን ሳንጠቀምባቸው አባክነናል። በዚህ የተነሳ ዛሬ ለምንገኝበት ምስቅልቅል ተዳርገናል። ይህን የተገነዘበው የለውጥ ኃይል ግን በእጁ የገባውን ወሳኝ መታጠፊያ እንደቀደሙት አገዛዞችና ትውልዶች ሊያባክነው አልፈለገም። ላለፉት ሶስት ዓመታት በበዛ ፈተናና መከራ ውስጥ ሆኖ ወሳኝ መታጠፊያውን እንደ አይኑ ብሌን ተንከባክቦና ጠብቆ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ሊያሸጋግረው በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ቀርተውታል። እንደ የፊታችን ማክሰኞ የሀገራችንን ቀጣይ እጣ ፈንታ በአዲስ የሚበይንና የሚወስን ታሪካዊ ሁነት የለም ማለት ይቻላል።
በአንጻሩ እንደ ሀገርና ህዝብ ያባከናቸውን ወሳኝ መታጠፊያዎች መለስ ብሎ መቃኘት በኢትዮጵያ ታሪክ ከአድዋ ባልተናነሰ ወሳኝ መታጠፊያ የሆነውን የማክሰኞውን ታሪካዊ ሁነት በቅጡ እንድንገነዘብ ይረዳናል። በወታደራዊ ደርግ የተቀማው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ገበሬዎች ላብ አደሮችና ከተሜዎች የ1966 ዓ.ም አብዮት በሀገራችን ታሪክ በወሳኝ መታጠፊያነት ከሚጠቀሱ የታሪክ ገጾች ቀዳሚ ነው። የ66ቱ አብዮት ዛሬ ሀገራችን ለምትገኝበት ሁለንተናዊ ስካርም ሆነ እራሷን ፈጥርቆ ለያዛት የቀውስ ሀንጎቨር የዳረጋት ጌሾው የበዛበት ጥንስስ ነው። አዎ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ለምትገኝበት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ወዘተረፈ ስካር ያ አላዋቂ የጠነሰሰው የዳጉሳ ጠላ ተወቃሽ ተከሳሽ ነው።
ደርግ ይህን ታሪካዊ መታጠፊያ አሳታፊ ፖለቲካዊ ምህዳር እና አካታች ኢኮኖሚያዊ ማዕቀፍ በማዘጋጀት የሀገሪቱን መጻኢ እድል በአዎንታዊ መበየን ይችል ነበር። ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ህዝባዊ የሽግግር መንግስት በማቋቋም በቀጣይ ነጻ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ማካሄድ ይችል ነበር። ደርግ ግን እንደነ ሌኒን ለስልጣኔ ያሰጉኛል ያላቸውን የአጼ ኃይለስላሴ ባለስልጣናትን እና የደርግ አባላት ሳይቀር መግደል ጀመረ። እነ አጥናፉ አባተንና ተፈሪ በንቲ በመንግስቱ የሚመራው የደርግ ክንፍ ገና በማለዳው በግፍ በመግደል ስልጣኑን ካደላደለ በኋላ መጀመሪያ ወደ ኢህአፓ በኋላ ፊቱን ወደ መኢሶን በማዞር መተኪያ የሌለውን የተማረ አንድ ትውልድ ጨረሰ። ለዛውም ባለብሩህ አእምሮ ምሁራንና በትምህርታቸው ጎበዝ የነበሩ ሀገር ተረካቢ ወጣቶችን።
በነገራችን ላይ በዛን ጊዜ የተፈጠረ ክፍተት ዛሬ ድረስ ሊሞላ ባለመቻሉ ዳፋው እንደ ጥላ ይከተለናል። የአጼውን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ገርሶሶ የባሰ አምባገነናዊ ሆኖ አረፈው። መሬት ለአራሹን አውጆ ብዙም ሳይቆይ የገበሬውን ምርት በርካሽ በኮታ መሰብሰብን ተያያዘው። መሬቱን በእጅ አዙር ተቆጣጠረው። ንጉሳዊ አገዛዙ እንዳሻው ያዝዝበት የነበረውን ኢኮኖሚ በሶሻሊዝም ስም ተቆጣጠረው። አፈናውን አባብሶ ቀጠለበት።
የደርግን አዝማሚያ ገና በውል ሳያጤን ትህነግ/ህወሓት የሻእብያን የትጥቅ ትግል መንገድ መከተል መረጠ። እነዚህ ኃይሎች እየተጋገዙ በደርግ ላይ የሚሰነዝሩት ወታደራዊ ጥቃት እየተጠናከረ ሄደ። ከዓመት ዓመት እየተጠናከሩ ፤ የሚቆጣጠሩት ነጻ መሬት እየሰፋ ፤ ትግሉን የሚቀላቀል ወጣት ቁጥር እየጨመረ ፤ በጦር መሳሪያና በትጥቅ እየደረጁ መጡ። በመጨረሻም አሸባሪው ትህነግ ከ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል በኋላ በ1983 ዓ.ም አዲስ አበባን ተቆጣጠረ ፤ የደርግ አምባገነን አገዛዝ በሌላ ለዛውም ሀገርን አምርሮ በሚጠላ ዘረኛ ፣ ከፋፋይና ዘራፊ አገዛዝ ተተካ።
ባለፉት 27 ዓመታት በፌዴራልና በኋላ በትግራይ አገዛዝ ላይ የነበረው “ነጻነትን የማያውቀው ነጻ አውጭ !” ትህነግ ለዜጎች ነጻነትና እኩልነት ታገልሁ ቢልም በተግባር ግን ከደርግ የባሰ አምባገነን ፣ ዘራፊና ቀውስ ቀፍቃፊ ሆነ። እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራል ሥርዓት የማቆም እድል ቢያገኝም እሱ ግን አስመሳይ የሞግዚት ዴሞክራሲን እንዲሁም ከፋፍሎ ለመግዛት የሚያመቸውን እና በዜጎች መካከል መጠራጠርን ፣ ልዩነትንና ጥላቻን የሚጎነቁል አገዛዝ ተከለ። የማንነትና የጥላቻ ፖለቲካ በተለይ ለ30 ዓመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ ሌት ተቀን በመሰበኩ ምክንያት ኢትዮጵያዊ ማንነት እየኮሰመነ አክራሪ ብሔርተኝነት እየገነገነ መጣ።
በዚህም የሀገር ህልውናና የግዛት አንድነት ፈተና ላይ ወደቀ። በዜጎች መካከል ጥላቻ ፣ ልዩነትና መጠራጠር ሰፈነ። የአንድ ቡድን የበላይነት ገነነ። ኢኮኖሚውን ከሽንኩርት ችርቻሮ እስከ ጅምላ ንግድ ተቆጣጠረው። ፖለቲካዊ ስልጣኑን ጠቅልሎ በመዳፉ አስገባ። የዜጎች ነጻነትና ዴሞክራሲ ባዶ ተስፋ ሆኖ ቀረ። ደርግ በአዲስ አይነት ማፊያ ቡድን ተተካ። ጭቆናው ከዓመት ዓመት እየተባባሰ ሄደ። ዘረፋ የአገዛዙ መለያ ሆነ። የስብሀታዊ ስረወ መንግስት ሀገሪቱን በአጥንት አስቀራት። ዜጎችን ሁለተኛ ዜጋ አደረጋቸው። በዚህ የተማረረው ህዝብ በተደጋጋሚ በተለያየ መንገድ ለውጥን ቢጠይቅም መልሱ ማብቂያ የሌለው ግድያ ፣ ስቃይ ፣ አፈናና እስር ሆነ። በመጨረሻ ህዝባዊ ተቃውሞው እየተጠናከረ በመጣበት ወቅት በትህነግ/ኢህአዴግ ውስጥ የነበረው የለውጥ ኃይል ከህዝባዊ ተቃውሞው ጋር እየተናበበና እየተንሰላሰለ ከሶስት ዓመታት በፊት ለውጡ እውን ሊሆን ቻለ።
ይህ ለውጥ ግን ከደርግም ሆነ ከትህነግ/ኢህአዴግ በመሠረቱ ፍጹም የተለየ ነው ማለት ይቻላል። እንደ ቀደሙት አንድን አምባገነነ በሌላ የተካ ሳይሆን ምን አልባት የለውጥ ኃይሉ እንደ ሀገር እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት የመጨረሻው ዕድል እንደወጣለት በውል የተገነዘበና ወሳኝ መታጠፊያ እጁ ላይ እንደገባ በማጤን ፖለቲካውን አሳታፊ ፤ ኢኮኖሚውን አካታች ለማድረግ ተቋም መገንባት አሰራርን ማሻሻል የማይተካ ሚና እንዳላቸው በመረዳት ሶስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ እንደ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ያለ አኩሪ ተቋም ገንብቶ ሀገርን በአሸባሪው ትህነግና በታሪካዊ ጠላቶቿ ተደግሶላት ከነበረ አደጋ መታደግ ቻለ።
ህዝባዊ አመጹና በትህነግ/ኢህአዴግ ውስጥ የተነሳው የለውጥ ኃይል አሸናፊ ሆኖ ወደ ስልጣን እንደመጣ የቀደመውን አገዛዝ መንገድ ልከተል ቢል ኖሮ ሀገራችን ዛሬ ድረስ ስለመዝለቋ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም ነበር። በድጋሚ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተመራው የለወጥ ኃይል ምስጋና ይግባውና በህይወቱ ተወራርዶ ይሄን ወሳኝ መታጠፊያ እንደ ቀደሙት አገዛዞች ሳያባክን አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓት እና አካታች የኢኮኖሚ ፈለግን መከተል መምረጡ ሀገራችንን ከማያበራ ቀውስና ፍርሰት ታድጓታል። መሠሪ እና አሸባሪው ትህነግ በገዥነት የማይቀጥል ከሆነ ደግሶላት የነበረው መበታተንና ማብቂያ የሌለው የእርስ በርስ ጦርነት ነበርና።
ይህ የለውጥ ኃይል ይቺን ሀገር ከዚህ በመታደጉ በልኩ እውቅና ሊቸረው ይገባል። ይቺ ሀገር ትንፋሽ አግኝታ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትገነባ መደላደሉን ፈጥሯልና። ሶስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ዘብ የነበረውን የመከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያና የሕዝቧ ዘብ በማድረግ እጅን በአፍ ያስጫነ አኩሪ ጀብድ በመፈጸም አሸባሪውን ትህነግ መደምሰስ ችሎ ነበር። ለዛውም ትውልድና ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደት በፈጸመበት ማግስት።
ወደድንም ጠላንም ይህ ለውጥ ከቀደሙት በፍጹም የተለየ ነው። የአምባገነንነትንና የፈላጭ ቆራጭነትን ቀለበት መስበር የቻለ ለውጥ ነው። ለ27 ዓመታት አገዛዝ ላይ የነበረውን አፋኝና ዘራፊ ቡድን የተካው የለውጥ ኃይል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የቆረጠ የለውጥ ኃይል በመተካት በዘመናዊት የኢትዮጵያ ታሪክ ፋና ወጊ ሆኗል። ወደ ኃላፊነት በመጣ የመጀመሪያዎቹ ቀናት በአስር ሺህዎቹ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት ከቀደሙት አገዛዦች የአፈና መንገድ መለየቱን አብስሯል።
በአሸባሪነት ተፈርጀው በስደት ላይ የነበሩ ድርጅቶች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ አድርጓል። ታግደው የነበሩ ድረ ገጾች ፣ ጦማሮች ፣ የህትመት ውጤቶች ፣ ሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፣ ወዘተረፈ እገዳቸው ተነስቶ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል። በአሸባሪነት ተከሰው ሞትና እድሜ ልክ ተፈርዶባቸው የነበሩ የፖለቲካ እስረኞች ተፈተዋል። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው እውን እንዲሆን ምቹ መደላደል ለመፍጠር የሄደበት
እርቀት በሶስት ዓመታት የተከወነ አይመስልም። እዚህም እዚያም የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች ፣ ማፈናቀሎች ፣ ዘረፋዎችና ውድመቶች ተደጋጋሚ ነጥብ ቢያስጥሉትም ለውጡን ተቋማዊ ለማድረግ አደረጃጀቶችንና አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ ከአምባገነናዊ አገዛዝ አዙሪትና ቀለበት ሰብሮ በመውጣት ተቆራርጧል።
የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አዕማድ የሆኑ ተቋማትን ቅድሚያ በመስጠት ማሻሻያዎችን አድርጓል። የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፣ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ፣ የፍትህና የዳኝነት ሥርዓቱ ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ፣ የኢትዮጵያ እምባ ጠባቂ ኮሚሽን ፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ፣ የብሔራዊ ደህንነትና የመረጃ ተቋም ፣ ፌደራል ፕሊስ ፣ መገናኛ ብዙኃን ፣ ወዘተረፈ ላይ የተፈጠሩ የአደረጃጀትና የአመራር ለውጦችን በአብነት ማንሳት ይቻላል።
የለውጥ ኃይሉ በምርጫ ዋዜማ ክብርት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፤ ክብርት መዓዛ አሸናፊን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፤ አቶ ዳንኤል በቀለን (ፒኤችዲ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነርነት መሾሙ የለውጥ ኃይሉ የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፈንታ በዴሞክራሲ ፣ በፍትሕ ፣ በእኩልነትና በነጻነት ለመዋጀት የቆረጠ መሆኑን ያረጋግጣል። የዴሞክራሲያዊ ተቋማት አዕማድ የሆኑ እነዚህን ተቋማት በኃላፊነት እንዲመሩ የተሾሙ ሰዎች ገለልተኝነትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለሰብዓዊ መብት መከበር ያላቸው ቁርጠኝነት የለውጥ ኃይሉ ሀገሪቱን ከፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አርነት ለማውጣት መወሰኑን በተግባር አረጋግጧል።
የለውጥ ኃይሉ የዴሞክራሲያዊ ተቋማትን በአደረጃጀትና ገለልተኛ አመራሮችን ከመመደብ ባሻገር የትህነግ አገዛዝ ለአፈና መዋቅሩ እንደ መሳሪያ ይጠቀምባቸው የነበሩ ሕጎች በገለልተኛ ምክር ቤት እንዲሻሻሉ የአንበሳውን ድርሻ ተጫውቷል። የሲቪል ማህበራት ፣ የመገናኛ ብዙኃን ፣ የጸረ ሽብር ፣ የምርጫና የፖለቲካ ድርጅቶች አዋጆች የተሻሻሉ ሲሆን ቀሪዎችን ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ ነው። እነዚህ የማሻሻያ ስራዎች እየተከናወኑ ያሉት ለዚህ ተግባር በገለልተኝነት በተቋቋመ ምክር ቤት መሆኑ ፤ የምክር ቤቱ አባላትም በገለልተኝነታቸው የታወቁ ምሁራን ፣ ጠበቃዎችና የሙያ ማህበራት መሆናቸው ፤ በሕግ ማሻሻያ ሒደቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሙያ ማህበራትና የህዝብ ወኪሎች በሒደቱ በንቃት መሳተፋቸው ሌላው የለውጥ ኃይሉ አካታች የፖለቲካ እና አሳታፊ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመትከል ምን ያህል እንደተነሳሳ እማኞች ናቸው።
የለውጥ ኃይሉ ሀገራችን ድሃ ፣ ኋላቀርና አምባገነናዊ አገዛዝ ሲፈራረቅባት የነበረው ተረግማ ወይም ሕዝቧ ጥቁር ስለሆነ ሳይሆን አሳታፊና አካታች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ባለመከተሏ መሆኑን በመገንዘብ በእጁ የገባውን ወሳኝ መታጠፊያ እንደ ቀደሙት ላለማባከን ቃል ኪዳን ገብቶ እየሰራ ይገኛል። ሀገራችንን ለዘመናት ቀስፎ የያዛትን ችግር ለይቶ ለማያዳግም መፍትሔ እየሰራ ነው። በዚህም ስሙ በፋና ወጊነት ሲወሳ ይኖራል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2014