ኢትዮጵያ በአዲስ ዓመት አዲስ ምዕራፍ በከፍታና አዲስ ተስፋ ለህዝቦቿ የምትመች ሀገር ለመሆን ጉዞዋን ጀምራለች፡፡ በብዙ መልኩ በተሳካ ሁኔታ በተከናወነው 6ኛውን አገር አቀፍ ምርጫ አሸናፊ የሆነው የብልፅግና ፓርቲም አዲስ መንግስት ለመመስረት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ፓርቲው በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ድምጻችሁን ብትሰጡኝ ‹‹አድርግላችኋለሁ ›› ብሎ ለህዝቡ ቃል የገባውን ለመፈፀም ሙሉ ዝግጅቱ እያስመለከተ ይገኛል።
አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ለውጥ የተዘጋጀ፣ ብዙ ተስፋ የሰነቀና ለሀገሩ ሉዓላዊነት ራሱን ያለ ስስት እየሰጠ ያለ ህዝብ የሚመራ መሆኑም በተለይ በቀጣይ ላቀዳቸው የልማት ስራዎች የጀርባ አጥንት እንደሚሆኑም በርካቶችን ያስማማል፡፡ ይሁንና ካለፈው ዓመት የተሻገሩ በርካታ ችግሮች ለአዲሱ መንግስት ከባድ ራስ ምታት እንደሚሆኑበት እርግጥ ነው፡፡
በተለይም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጠብ ጫሪነት በተከሰተው ጦርነት ሳቢያ በታሪኳ አይታ የማታውቃቸውን ሰብዓዊ ቀውሶች በማስተናገድ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህን ቀውስ የመፍታት ከባድ ሃላፊነትም በዚሁ በአዲሱ መንግስት እጅ ላይ የወደቀ ከፍ ያለ ሃላፊነት ሆኗል፡፡
የፌዴራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ካስወጣ በኋላ በአሸባሪው ህወሓት በአፋር እና በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባካሄደው ወረራ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው መሰደዳቸው ያታወሳል። የችግሩ ዋነኛ ተጠቂዎች ሴቶችና ሕጻናት መሆናቸው ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በጦርነት ምክንያት የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር በየቀኑ እያሻቀበ ይገኛል፡፡ እነዚህ ዜጎች በዚህ አሸባሪ ሃይል ተሳደው ጨርቄን ማቄን ሳይሉና ቤሳቢሲቲ ሳይዙ የወጡ እንደመሆናቸው የእለት ጉርሳቸውን ማግኘት ተስኗቸው በእንግልት ላይ መሆናቸው የየቀኑ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል፡፡
በትምህርት ቤቶችና መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ካሉት በላይ በየጥሻውና በርሃው እየተሰቃዩ ያሉት ዜጎች ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ በተለይም ከችግሩ ሰለባዎች መካከል ቁጥራቸው ላቅ ያሉት እናቶችና ህፃናት መሆናቸው የሰብዓዊ ቀውሱን ከባድ ያደርገዋል፡፡
ይህ እንደመሆኑም የፌዴራሉም ሆነ የክልል መንግስታት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሌት ተቀን የሚታትረውን የአሸባሪውን ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ እያደረጉት ካለው ጥረት ጎን ለጎንም በጦርነት ምክንያት ያለ ጥፋታቸው በረሃብና በእንግልት የተዳረጉ ዜጎችን ለመታደግ ሌት ተቀን በቅንጅት እየሰሩ ናቸው፡፡
ከተራው ዜጋ ጀምሮ ባለሀብቱና ታዋቂ የሀገሪቱ ዜጎች ያላቸውን ለወገናቸውን በማጋራት አለኝታቸውን በማረጋገጥም ላይ ናቸው፡፡ ይህም ችግሩን በጊዜያዊነት ከመፍታት ባለፈ ሀገራዊ አንድነቱን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አቅም እየፈጠረ ይገኛል፡፡
ይሁንና ከችግሩ ስፋትና ከተፈናቃዩ ቁጥር አኳያ በመንግስትም ሆነ በለጋሽ አካላት እየተደረገ ያለው ድጋፍ የሚፈለገው ያህል የሆነ አይመስልም፡፡ ይህ እንደመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለወገኑ አለኝታ መሆኑን ይበልጥ ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡
‹‹ሀገር ማለት ሰው፣ ሰው ነው ሃገር ማለት›› እንደሚባለው ፤ ያለ ሰውም ሀገር ‹‹ሀገር›› ተብሎ መቆም ስለማይችል አዲሱ መንግስት በዘርፈ ብዙ የሰብአዊ ቀውስ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን የመታደግ ሃላፊነት አለበት። ከዚህ ጎን ለጎን የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አጠናክሮ መቀጠል ፤ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን በስኬት በመወጣት የተጣለበትን የህዝብ አመኔታ ተጨባጭ ማድረግ ይኖርበታል።
አዲሱ መንግስት ከሁሉም በላይ ለሀገር ስጋት የሆኑ አሸባሪ ሃይሎችን በማስወገድ የሀገርን ህልውና ማስከበር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ትልቁ የቤት ስራው ቢሆንም፤ ከዚህ ባልተናነሰ መልኩ በጦርነት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል፡፡
አሁን ላይ አንገባቢ የሆነውን የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄ በአፋጣኝ ለመመለስ እየተደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል ይጠበቅበታል፡፡ ይህንን ሲያደርግ ጦርነቱ ዛሬም ድረስ ያልተጠናቀቀ መሆኑና መቼ እንደሚበቃም አለመታወቁ የችግሩ አድማስ ሊያሰፋው እንደሚችል ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሆን ይኖርበታል፡፡
ጦርነቱ በአጭር ጊዜ ቢጠናቀቅ እንኳን እነዚህ ሰዎች ይኑሩበት የነበረው መኖሪያ ቤት፤ ይገለገሉባቸው የነበሩ ሆስፒታሎች፤ ትምህርት ቤቶችና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ የወደሙባቸው መሆኑ ተፈናቃዮችን ወደቀዬአቸው የመመለሱን ስራ ፈተኝ ያደርገዋል፡፡
አዲሱ መንግስት እነዚህን የፈረሱ ከተሞችና መንደሮች ወደ ነበረበት ገፅታ ለመመለስ የሚያስችል የፋይናስ አቅም እንኳን ቢያገኝ መሰረተ ልማቶች በአንድ ጀምበር አልያም በአንድ ዓመት የተገነቡ እንዳለመሆናቸው መጠን ዳግም የመገንባቱ ጉዳይ ዓመታትን የሚጠይቅ መሆኑ አይቀሬ ነው ፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥም ተጎጂ የሚሆኑት እነዚሁ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው፡፡ የችግሩ መቀጠል በተለይም የነገው ሀገር ተረካቢ የሆኑት ህፃናትና እናቶችን ጉዳት እንደሚያብሰው ግልፅ ነው፡፡
ለቀጣይ አምስት ዓመታት ሀገሪቱን እንዲመራ የሚሰየመው መንግስት ብዙ የቤት ስራዎች የሚጠ ብቁት ቢሆንም ከምንም በላይ ለሰብዊ ድጋፉ ትኩረት በመስጠት ሊደርስ የሚችለውን ሰብአዊ ቀውስ መቀልበስ ይጠበቅበታል፡፡
ይህም ሲባል ዜጎቹ ዘመናቸውን ሁሉ እጅ ጠባቂ እንዲሆኑ ማድረግ አለመሆኑ ብዙዎችን የሚያስማማ ጉዳይ ነው፡፡ የነበሩበት ቀዬ ወደ ቀድሞ ሰላሙ እስኪመለስ ባሉበት ስፍራ ራሳቸውን የሚረዱበት ሁኔታ መፍጠርም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ይሆናል፡፡
ሜሎዲ
አዲስ ዘመን መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ.ም