(ክፍል አንድ)
የፊታችን መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም እንደ አለፉት 2 ሺህ 14 ዓመታት እንደመጣች እንደሔደችው መስከረም 24 ዝም ብላ ተራ ቀን አይደለችም። ይቺ ቀን ከቀደሙት የተለየች ታሪካዊ ቀን ናት። አዎ! የኢትዮጵያ ትንሳኤና ህዳሴ በአንድ ላይ የሚታወጅባት ልዩ ቀን። በተለይ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ማለትም ከዘመነ መሳፍንት የስልጣን ሽኩቻ ፤ ከቱርክ ወረራ በኋላ የቋራው ካሳ ሀይሉ ተቀናቃኞቹን ሁሉ ድል በመንሳት እኤአ በ1855 አፄ ቴዎድሮስ ተብሎ ከነገሰበት እስከዚህ ለውጥ ድረስ ከመጡ ከሔዱ መስከረም ሃያ አራቶች የተለየች፤ ወሳኝ መታጠፊያ/critical juncture/እና የኢትዮጵያ ትንሳኤና ህዳሴ በአንድ ላይ የሚታወጅባት አሀዱ የሚባልባት ልዩና ታሪካዊ ቀን ናት።
ይቺን ቀን ምን ያህሎቻችን በዚህ ልክ እንደጠበቅናት እርግጠኛ ባልሆንም ቁጥራችን ቀላል ያልሆነ ሀገር ወዳዶች ግን የኢትዮጵያ ትንሳኤና ህዳሴ መባቻ አሀዱ የሚባልባትና መጀመሪያ ናት። አብዛኛዎቹ የእንደራሴ አባላትም ይቺን ታሪካዊ ዕለትና ቀጣይ አምስት ዓመታትን በዚህ ልክ ዋጋ ይሰጧታል ብየ አምናለሁ።
መጋቢ ኤልደር ዊርዝሊንስ”ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል። ” እንዳሉት የኢትዮጵያችን መከራ አበሳ ውርደት ተምሳሌት የሆነው አርብ አልፎ የትንሳኤዋ ምልክት የሆነው እሁድ እንዲመጣ ኢትዮጵያውያን ቃል ኪዳን የሚገቡበት ከራሳቸው ጋር ውል የሚይዙበት ተናፋቂ ቀን ናት። ባለፉት ሶስት ዓመታትና ከዚያ በላይ በሀገራችን ጨለማ፣የምድር መናወጥ፣ ክረምት፣ ሰደድ፣በረዶ፣ ጎርፍ፣ መገፋት፣ መዋረድ፣ መገረፍ፣ መቸንከር፣መሰቀል፣ መከዳት፣ መሸጥ፣ ወዘተረፈ አርብ ቢሆንም፤ መንጋቱ፣ ብርሃን በጨለማ ላይ መንገሱ፣ የምድር መናወጡ መቆሙ፣ ብራ ፀደይ መምጣቱ፣ መከበሩ፣ መፈወሱ፣ ትንሳኤ፣ ቀን መውጣቱ፣ የተሻለ ጊዜ መምጣቱ ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ እንደተነሳበት እሁድ ሁሉ ለእኛም ሆነ ለሀገራችን ከችግር፣ ከድህነት፣ ከተመፅዋችነት፣ ከኋላ ቀርነት፣ከፈተና፣ ከወረርሽኝ፣ ከጭቆና፣ ከአፈና፣ ከጥላቻ፣ ወዘተረፈ ነጻ የምንወጣበት አንገታችን በክብር ቀና የምናደርግበት፤ ትንሳኤ’ችንን፣ ህዳሴ’ችንን የምናይበት ቀን አሀዱ የምንልባት፤ ተስፋ የምንሰንቅባት ልዩ ቀን ናት መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም።
“ዛሬ አርብ ቢሆንም እሁድ ይመጣል። ” እያልን በተለይ ላለፉት 47 የጨለማና የመከራ ዓመታት በእምነት በተስፋና በናፍቆት በር በሩን እያየን ስንጠብቃት የኖረች ልዩ ቀን ናት። ይህ ብቻ አይደለም። በአውሮፓም ከ14ኛው እስከ 17ኛ መቶ ክፍለ ዘመን በሳይንስና በጥንታዊ የኪነ ጥበብ የታየው ዳግም ልደትና ማንሰራራት /renaissance / በተለምዶ ወርቃማ ዘመን ወይም ህዳሴ የምንለው አይነት ዘመን በኢትዮጵያችን እንዲመጣ አሀዱ ብለን መሠረት የምንጥልበት ልዩ ቀን ናት።
ገዥውና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተቋማት ማለትም የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች፣ ብዙኃን መገናኛዎች፣ ፍርድ ቤቶች፣ የፍትሕ ሥርዓቱ፣ የደህንነትና የጸጥታ መዋቅሩ፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሲቭል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ሌሎች የሰብዓዊና የዴሞክራሲ ተቋማት፣ ልሒቃን፣ ወዘተረፈ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ በመሆን ይቺን ታሪካዊ ቀን እንደ መላ ኢትዮጵያውያን እኩል ዋጋ ሊሰጧት፤ የኢትዮጵያ ትንሳኤና ህዳሴ መባቻ መሆኗን አምነው ሊቀበሏት፤ ታላቅና ታሪካዊ ቀን መሆኗንተገንዝበው በልኳ በሰገባዋ መገኘት አለባቸው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት 27ና ከዚያ በላይ ዓመታት መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ በአሸባሪው ወያኔ የተነዛውንና የተዘራውን ጥላቻ ልዩነትና ጎሰኝነት፤ ይህን ተከትሎ እንደ ናዳ የወረዱበትን የትየለሌ ጫናዎችንና መከራዎችን ተቋቁሞ ለዚህ ታሪካዊ ቀን ያበቃ ህዝብን የሚመጥንና የሚገባውን መንግስትና መሪ ማሰናዳት ይጠይቃል።
ደጋግሜ በዚሁ ጋዜጣ እንደገለጽሁት ሀገራችን በ3 ሺህ ዓመት ጥንታዊ ታሪኳ እንዲህ ያለ ከባድና ውስብስብ ፈተና ፤ ለዛውም ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቿ ተናበውና ተልዕኮ ተቀባብለው ሊያጠቋት ተነስተው አያውቅም ። በአንድ በኩል ለ30 ዓመታት በቁሟ የጋጣት የዘረፋት ፤ በታሪኳ እየገዛት አምርሮ የሚጠላት ስሟን ለመጥራት እንኳ የሚጸየፋት ፤ የገዛ ሀገሩን 80 በመቶ ጦር ከድቶ የጨፈጨፈ የጦር መሳሪያ ዘርፎ መልሶ ያጠቃ አረመኔ በታሪኳ ተነስቶባት አያውቅም ።
ይህ ሳያንስ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ከዚህ ከሀዲና አሸባሪ ጎን ተሰልፈው ጥቃት ከፍተውባታል። ምዕራባውያን እንደአሁኑ በኢትዮጵያ የመንግስት ለውጥ ለማምጣት ፍኖተ ካርታ ቀርጸው ተንቀሳቅሰው አያውቁም ። “From Basma to Ethiopia – How C2FC is Using Lethal Journalism to Conduct Information Warfare and Lawfare against Ethiopia” በሚል ርዕስ በጂኦፖለቲክስ ፕሬስ የወጣው ሰነድ ይህን የክፍለ ዘመኑን ታላቅ ሴራ አደባባይ አሰጥቶታል።
ይህ ታላቅ ህዝብ ብዙ መልስና መፍትሔ የሚሹ ጥያቄዎች ቢኖሩትም እንደ አሸባሪዎች ወያኔና ኦነግ ሸኔ ያሉትን የውስጥ ጠላቶቹንና እንደ ትሮይ ፈረስ የሚጋልቧቸውን የግብጽንና የምዕራባውያንን ጥቃትና ጫና በአንድነትና በቅንጅት በመመከት ከሀገሩና ከመንግስቱ ጎን በመቆሙ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊባል በሚችል ነጻ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ከስምንት ሰዓታት በላይ በብርድ በዝናብና በቁር ተሰልፎ ድምጹን ይሁንታውን በመስጠት ለዚች ታሪካዊ ቀን አብቅቶታል። ለዚህ እንደቀደሙት አምስት መንግስት ምስረታዎች በሸፍጥ በሴራና የአንድን ቡድን የበላይነትና ጥቅም ብቻ ለማስከበር የሚመሠረት መንግስት ሳይሆን በዚህ ህዝብ ከፍታ ልክ በእኩልነት በፍትሐዊነት በተጠያቂነት በአሳታፊነትና በዴሞክራሲያዊነት የሚመራ መንግስት ይመሠረታል ተብሎ ይጠበቃል።
ለዚህ ህዝብ የሚገባውና የሚመጥነው መንግስት ሊመሠረት ይገባዋል ሲባል፤ ትውልዱንም ዘመኑንም የሚዋጅ፤ ለውጡ ለሀገሪቱም ሆነ ለህዝቡ ምን አልባትም ከዚህ በኋላ ሊገኝ የማይችል ወሳኝ መታጠፊያ መሆኑን፤ የሚመሠረተው መንግስትም ይህ ታሪካዊ ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑን ልብ ማለት ያሻል።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርን ወደ ኃላፊነት ያመጣው ለውጥ ከቀደመው አብዮትም ለውጥም ፍጹም ይለያል። ደርግ ንጉሳዊውን አገዛዝ በመፈንቅለ መንግስት ገርስሶ በምትኩ የባሰ ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ተከለ። አሸባሪው ትህነግ/ኢህአዴግ ሶሻሊስታዊ አምባገነን ገዥ የነበረውን ደርግ ለ17 ዓመት ነፍጥን ከሴራና ደባ አጃምሎ ለስልጣን ቢበቃም ታገልሁለት ያለውን እኩልነትና ነጻነት ክዶ የአንድን ቤተሰብና አውራጃ የበላይነት ብቻ ሳይሆን ለ30 ዓመታት አንድም ቀን የመንግስትነት ባህሪ ሳያሳይ በአሳፋሪ ሁኔታ ራሱን በራሱ አጥፍቷል። መንግስት የመሆን ቅን ፍላጎትም አልነበረውም። ሕገ መንግስት ያለው ብቸኛ ማፊያ እንጂ።
በመጨረሻዎቹ የክህደትና የአረመኔነት ቀናት ያረጋገጠልን ይህን ማፊያነቱን ነበር። ሆኖም በፖለቲካው መልክዓ የነዛው የጥላቻ፣ የልዩነትና የመጠራጠር መርዝ በቀላሉ አይረክስም። እንኳን ለ46 ዓመታት የተለፈፈ የጥላቻና የፈጠራ ትርክት፤በጣሊያን የአምስት ዓመታት ቆይታ ለዛውም በጀግኖች አርበኞች ተጋድሎ ለአንድ ቀን እንኳ ያለ ስጋት ውሎ ባላደረበት ለከፋፍሎ መግዛት እንዲያመቸው የዘራው የማንነት ጨቋኝ ተጨቋኝ የፈጠራ ትርክት በቀላሉ ሰኮናው ሳይነቀል ኖሮ በ60ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከሶሻሊዝም ጋር ተላቁጦ የሀገራችንን ፖለቲካ እስከመበየን ደርሷልና ከዚህ አባዜ ሰብሮ ለመውጣት ብርቱ ጥረትና ቁርጠኝነት ይጠይቃል።
ይህ ጥረት ግን የአፄ ሃይለስላሴ ፣ የደርግና የአሸባሪው ትህነግ አገዛዞች ያባከኗቸውን ወሳኝ መታጠፊያዎች ሀገራችንን ምን ያህል ውድ ዋጋ እንዳስከፈሏት በውል ተገንዝቦ ከሶስት ዓመት ወዲህ በእጁ የገባውን ወሳኝ መታጠፊያ በብልህነትና በአስተዋይነት መጠቀምን የሞት ሽረት ጉዳይ ማድረግን ይጠይቃል ። ከእነ ውስንነቶቹ
ምስጋና /እውቅና/ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለሚመራው የለውጥ ኃይል ይሁንና ይቺ ሀገር እንደ ቀደሙት ሶስት የቅርብ ዓመታት መታጠፊያዎች የምታባክነው እድልም ሆነ አጋጣሚ እንደማይኖርና እንደ ከዚህ በፊቱ ብታባክነው አምባገነናዊ አገዛዝ በመተካት ብቻ የሚቆም ሳይሆን በሀገር ቀጣይ ህልውና ላይ አደጋ የሚደቅን መሆኑን በውል ተገንዝበው የአምባገነንነት ቀለበቱን ሰብሮ ለመውጣት የሚያግዝ ስልት ተልመዋል ። አሳታፊ ፖለቲካዊ ሥርዓትና አካታች የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለማስፈን ቆርጠዋል ።
ቁርጠኝነታቸውንም የዴሞክራሲ ተቋማትን በመገንባትና ኢኮኖሚውም ፍትሐዊ እንዲሆን ማሻሻያ ቀርጸው ወደ ትግበራ ገብተዋል ። ሆኖም ለውጡ ከቀደሙ አብዮቶቹም ሆነ ለውጦች በፍጹም ሊባል በሚችል ሁኔታ የተለየ በመሆኑ፤ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ የተዘራው ልዩነትና ጥላቻ፤ አሸባሪው ትህነግ ጥርሱን በነቀለበት ሴራና ደባ መቐሌ ላይ መሽጎ እንዲቀጥል ጊዜ ማግኘቱ፤ በሰሜን ዕዝ ላይ ታሪክም ትውልድም ይቅር የማይሉት ክህደትና ጭፍጨፋ መፈጸሙ፤ መንግስት ለሰብዓዊነት ሲል ያወጀውን የተናጠል የተኩስ አቁም እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ወደ አማራና አፋር ክልሎች ወረራ በማካሄድ ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍ ጭካኔና ውድመት መፈጸሙ፤ ለውጡ ቢያንስ ሆን ተብሎ የባረቁ ሶስት ለውጦችና አብዮት ዘርፈ ብዙ ቀውስን እንደ ትኩስ ድንች ተቀባብለው ተቀባብለው የጣሉበት በመሆኑ የቀውሶች ቋጥኝ ስለ ወደቁበት እና በለውጡ ተዋንያን ወጥ ቁርጠኝነት ባለመያዙ ምልዑ – በኩሌ ሳይሆን ቀርቷል። ምንም እንኳ የእውነተኛ ለውጥ መንገድ አሚካላና ኩርንችት የበዛበት ቢሆንም የተገኘው አበረታች ውጤት በዚህ ሁሉ እሾህ ታንቆ ያለፈ እንዳይመስል አድርጎታል።
የሰው ልጅ ከፍ ሲልም ሀገርና ህዝብ በያለፉበት መንገድና በየተገለጡበት ገጽ የየራሳቸው የሆነ ወሳኝ መታጠፊያ /critical juncture / አላቸው። ቀጣይ እጣ ፈንታቸውን በአዲስ የሚበይንና የሚለውጥ ሁነት አልያም አጋጣሚ ይከሰታል። ዛሬ በዓለማችን እየተመለከትነው ያለ የኢኮኖሚ ብልፅግና የዴሞክራሲያዊነት ልዩነት ጥንስሰ የተጠጀው የዓለምን ግማሽ ህዝብ እንደጨረሰ በሚነግርለት እኤአ በ1346 ዓ.ም በተከሰተ ጥቁሩ ሞት ወሳኝ መታጠፊያ ሳቢያ ነው።
ዳረን አኪሞግሉ እና ጄምስ ሮቢንሰንን በጣምራ በዘጋጁት ፤ “ WHY NATIONS FAIL” በተሰኘ ግሩም ድንቅ መጽሐፍ ገጽ 101 ላይ ስለ ወሳኝ መታጠፊያ ፤”…ጥቁሩ ሞት የወሳኝ መታጠፊያ ጉልህ ማሳያ ነው። ወሳኝ መታጠፊያ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች እንደ አዲስ የሚበይኑና የሚጠረምሱ ዓበይት ሁነቶች ናቸው። የማህበረሰብን ፈለግ በአወንታ ወይም በአሉታ የሚያስቀይር ባለሁለት ስለት ሰይፍም ነው። በአንድ በኩል ለዘመናት ተንሰራፍቶ የኖረውን የብዝበዛና የጭቆና ቀለበት በመስበር እንደ እንግሊዝ ነጻና አሳታፊ ሥርዓት ለመገንባት መሠረት ሲሆን በሌላ በኩል በምስራቅ አውሮፓ በታሪክ እንደተመዘገበው ወሳኝ መታጠፊያ የከፋ አምባገነን አገዛዝንና ብዝበዛን ሊያሰፍን ይችላል ።
“እንደ ፈጣሪ ፈቃድ በክፍል ሁለት መጣጥፌ የዚችን ታሪካዊ ቀን ወሳኝነትና አንድምታ ለማሳየት እሞክራለሁ። አዲሱ ዓመት የሰላም ፣ የጤና ፣ የብልፅግና እና የአንድነት ይሁን !!!
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2014