አሸባሪው ህወሓት ትናንትና ምን እንደነበር ያለፉትን ሃያሰባት ዓመታት ማየቱ ብቻ በቂ ነው እላለሁ። በኢትዮጵያ ጸዐዳ መልክ ላይ፣ ጸዐዳ ታሪክ ላይ፣ ጸዐዳ ትውልድ ላይ የበቀለ አረመኔ ሃይል ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ ትናንትናና ከዛ በፊት ባሉ ዘመኖቿ ላይ በህወሓት ቡድን ይሄ ነው የማይባል ስቃይና በደል አስተናግዳለች። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ዛሬም እያስተናገደች መሆኗ ነው።
የኢትዮጵያ ተስፋዎች ከደበዘዙባቸው አጋጣሚዎች አንዱ የአሸባሪው ህወሓት ወደ ስልጣን መምጣት እንደሆነ አምናለሁ። እንደሚታወቀው ህወሓት እንደ ቡድን ሲመሰረት ዓላማው ሀገር ማፍረስና ህዝብ መለያየት ነበር። ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የሰራቸውን ታሪካዊ ስህተቶች ትናንትና ጫካ ውስጥ ሆኖ ከወዳጆቹ ጋር የነደፋቸው የክፋት ንድፎች ነበሩ። ዛሬ ላይ እየተሰቃየንባቸው ያሉ ሀገራዊም ሆኑ ግለሰባዊ እጸጾቻችን በቡድኑ የጫካ ዘመን የተፈጠሩ ረቂቅ ደባዎች ናቸው።
በብሄር ስም ለደረሱብንና እየደረሱብን ላሉት መለያየቶች ጠንሳሹ ይሄው አሸባሪ ቡድን ነበር። በኢትዮጵያ ታሪክ የማይወዳትን ሀገር የመራ ብቸኛው ቡድንም ነው። የማይወዳትን ብቻ ሳይሆን ስትሰቃይና ስትጠፋ ቆሞ ለማየት በታጠቁ ቡድኖች ተዋቅሮ የቆመ ታሪካዊ ጠላትም ነው።
ዓለም በታሪኳ በርካታ ጨካኞችን አይታ ታውቃለች እንደ አሸባሪው ህወሓት ያለ በወንድሞቹ ላይ የሚጨክን፣ ምንም በማያውቁ ንጹን ላይ ጀግና የሚሆን አረመኔ ግን አይታ አታውቅም። አብዛኞቹ አሸባሪዎች ጦራቸውን የሚያነሱት ጠላቴ በሚሉት ቡድንና በተቀናቃኛቸው ላይ ነው፤ የህወሓት ጭካኔ ግን አስተምራ ለቁም ነገር ባበቃችው ሀገርና ህዝብ ላይ ነው። ይሄ በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የመጨረሻው የጭካኔ ጥግ ነው።
በአሸባሪው ህወሓት የስልጣን ዘመን ተወልደን ያደግን እኛ እድለ ቢሱ ትውልዶች ነን እላለው። እኔ በግሌ የአንባገነኑ የከሀዲው የኢህአዴግ ትውልድ ነኝ ፤ በህይወቴ በጣም የሚቆጨኝ የዚህ ትውልድ አካል መሆኔ ነው። የሚገርመኝን አንድ ነገር ልንገራችሁ በህይወቴ ብዙ ውሸት ብዙ ማጭበርበሮችን ሰምቼ አውቃለው። በታሪክ፣ በወሬ ብዙ ውሸቶችን ብዙ ማስመሰሎችን ሰምቻለው እንደ አሸባሪው ህወሓት መራሹ መንግስት ውሸታምና ህዝብ አጭበርባሪ ግን አይቼ አላውቅም።
በጣም የሚገርመኝና ዛሬም ድረስ ሳስበው የሚያስደንቀኝን ውሸት ልንገራችሁ እንደምታውቁት በኢህአዴግ ዘመን ከወንድም ህዝባችን ከኤርትራ ጋር ሆድና ጀርባ ነበርን በጣም የሚገርመው እሱ ሳይሆን አዲስ አበባ ውስጥም ሆነ ከአዲስ አበባ ውጪ ምንም አይነት ችግር ሲነሳ አሸባሪው የኤርትራ መንግስት የፈጸመው ነው፣ ከሻቢያ በኩል ለጥቃት የተላከ ነው እያለ ህዝቡን ውሸትእየነገረ ለዘመናት ሲያቃቅረን ኖሯል።
በለውጡ ዋዜማ የሆነውን ደግሞ የምታውቁት ነው ለእርቅ የተጠራው የኤርትራ መንግስት ለሰላም የነበረው እውነታ የአደባባይ ሚስጥር ነበር። ይሄን ሳስብ የኢህአዴግ መንግስት በትውልዱ ላይ የሰራው የውሸትና የማስመሰል ደባ ያበሳጨኛል። የሆነውንና እየተነገረን ያደግንውን ሳስብ በዚህ አስመሳይ መንግስት ዘመን ውስጥ መፈጠሬ ያናድደኛል።
እንደ ወጣት፣ ራዕይ እንዳለው አንድ ዜጋ በዚህ ከሀዲ ዘመን መፈጠሬን ለምን? እላለሁ። መልካም ትውልድ የሚገነባው ዋሽቶ በማስታረቅ ውስጥ እንጂ ዋሽቶ በማለያየት ውስጥ አይደለም። በነገራችሁ ላይ የአሸባሪው ህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን የጎዳው በብዙ ነገር ነው። በብሄር በመከፋፈል በመካከላችን እኔነትን ፈጥሯል። የሀገርና የህዝብ ሀብትን ከሀገር ውጪ በማሸሽ ከባድ ሌብነትን ፈጽሟል። ግራ በገባው የፖለቲካ እቃቃ ጨዋታ ብዙዎችን ለሞትና ለስደት ዳርጓል። በትውልዱ ጭንቅላት ውስጥ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ብሄርተኝነትን በመስበክ ከአብሮነት አርቆናል።
በህይወቴ ውስጥ በቡድኑ የተፈጠሩ በርካታ መጥፎ አሻራዎች አሉ። አሁን የምኖረው እነዛን ክፉ አሻራዎች በማጽዳት የእውነት ሰው ለመሆን ነው። አሁን የምኖረው እነዛን የሃያ ሰባት ዓመታት ጉድፎች አጥርቼ የእውነት ኢትዮጵያ ልሆን ነው። አሁን የምኖረው ከአሸባሪው ህወሓትና ከሥርዓቱ የተላቀቀችን ኢትዮጵያ ለማየት ነው። እንደ እኔ ይሄን እውነት የምትናፍቁ ብዙ ናችሁና እነሆ በትንሳኤው ዋዜማ ላይ እንደሆናችሁ ስነግራችሁ ከልቤ ነው። ምክንያት ካላችሁኝ የአሸባሪው ህወሓት የመጨረሻው ዘመን ላይ ነንና ።
የኢትዮጵያ ህዝብ አሸባሪው ህወሓት ማለት ማን እንደሆነ ትናንትም ዛሬም ጠንቅቆ ያውቃል። ችግር የነበረው መብትን ከመጣስ ባለፈ መብትን ለማስከበር የሚሆን ሥርዓት አልነበረም። ብዙዎች ከቡድኑ አገዛዝ ነጻ ለመውጣት ሲሞክሩ በግፍ ተሰውተዋል። የቀሩትም ለአእምሮ በሚዘገንን መልኩ ግፍና ስቃይ ደርሶባቸው የገቡበት አይታወቅም።
ከትናንት እስከዛሬ የአሸባሪው ህወሓት ቡድን የኖረው በጉልበቱና በውሸቱ ነው። ማንም የማይፈልገው መንግስት ነው። ማንም የማይፈልገው ቡድን ነበር። አዶልፍ ሂትለርና ንጉስ ኒሮ የብዙዎችን ነፍስ የበሉ ዓለምን በጭካኔአቸው የቀየሩ የክፋት አለቆች ነበሩ። የህወሓት ክፋት ከነሱ የሚተናነስ አይደለም። ባለፉት አስር ወራት ብቻ በህወሓት አሸባሪ ቡድን በርካታ ንጹን ተገለዋል። በማይካድራ በርካታ ነፍሶች የዚህ ጨካኝ ቡድን ሰለባ ሆነዋል።
አፋር ውስጥ ጉሊና ወረዳ ጋሊኮማ በሚባል ቀበሌ በትምህርት ቤትና በጤና ጣቢያ በተጠለሉ ተፈናቃዮች ላይ ባደረገው ጭፍጨፋ ከሁለት መቶ በላይ ንጹሃንን ገድሏል። ከነዚህ ውስጥ ከመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ገና ክፉናደጉን ለይተው ያላወቁ ቦርቀው ያልጠገቡ ህጻናት ነበሩ።
ወደ ኋላ ታሪክን መለስ ብለን ስናይ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1960 አካባቢ ላይ አፍሪካውያን ከነጮች አገዛዝ ነጻ ለመውጣት በሚፍጨረጨሩበት ዘመን በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ሥርዓት 176 የሚሆኑ ህጻናት ተገለው ነበር። በወቅቱ ይህ ዜና መላው ዓለምን በማዳረስ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። አለም ይሄን ዜና ሲሰማ ጉድ ነበር ያለው..የነዚህን ህጻናት ሞት ተከትሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ የህጸናት ቀን እንዲከበር ሆነ። ዛሬ ላይ ለብዙዎቻችን የምናከብረው የህጻናት ቀን የነዚያ ህጻናት ሞት የፈጠረው ድል ነው።
በእኛም ሀገር በተመሳሳይ የአሸባሪው ህወሓት ቡድን በህጻናት ላይ እያደረሰ ያለው ኢሰብዓዊ በደልና ግፍ፤ ከዚህ ባለፈ በሀሽሽና ባልተገባ እጽ አእምሯቸውን በማደንዘዝ እድሜአቸው ያልደረሰ ህጻናትን ለጦርነት በማሰለፍ ዓለም አቀፉን ህግ በመጣስ ተደጋጋሚ ወንጀል ሲፈጽም ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ከማውገዝና ለህግ የሚቀርብበትን አግባብ ከመፍጠር ይልቅ ዝምታን መርጧል ።
ይህ የልብ ልብ የሰጠው አሸባሪው ህወሓት ከድርጊቱ ከመቆጠብ ይልቅ መዋሸቱንና ማጭበርበሩን፤ መግደል ማስገደሉን ቀጥሎበታል። ሀገር እያጠፋ፣ ታሪክ እያበላሸ ራሱን ፍትህ ፈላጊ አድርጎ እየቆጠረ ነው ፤ አብረው በፍቅርና በመቻቻል በሚኖሩ ህዝቦች መካከል ጥላቻንና ከዛም በላይ ጦርነት በማወጅ መሰረተ ልማቶችን በማውደም ፣ በህዝቦች ላይ ሞትና መፈናቀል እየፈጠረ እንደተበዳይ እራሱን እየቆጠረ ነው። ይህ ሁሉ የፍጥረታዊ ማንነቱ መገለጫ ናቸው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ግን አሸባሪው ህወሓት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአግባቡ የተረዳበት ወቅት ነው። አሁን ላይ ስለ ቡድኑ ህዝቡ አንድ አይነት አቋም ይዟል። ቡድኑ እስካልጠፋ ድረስ ኢትዮጵያ ሰላም እንደማይኖራት መግባባት ላይ ደርሷል። ለዚህም ከመላው ሀገሪቱ በርካታ ወጣቶች ሰራዊቱን እየተቀላቀሉ መሆኑ ትልቅ ማሳያ ነው።
በአሸባሪው ህወሓት ልብ ውስጥ ሀገርና ህዝብ የለም። ታሪክና እውነት የለም። መነሻቸውም መድረሻቸውም ውሸትና ተንኮል ነው። በለመደው የውሸት ትርክት ዛሬም እንደትናንት በንጹሃን ሞትና ስቃይ እየነገደ ነው። ከእንግዲህ የኢትዮጵያ የተስፋ የመንጋት ዘመን ነው። ህዝቡ በውጭ ሚዲያዎችና በየፌስቡኩ የሚወሩ በሬ ወለደ ወሬዎችን ሳይሰማ ሁሉንም ነገር በንቃት በመከታተል የድሉ ባለቤት መሆን ይጠበቅበታል።
ልብ ሊባል የሚገባው ሌላው ነገር አሸባሪው ህወሓት ገና ከዚህም በላይ ሊዋሽ እንደሚችልና እስካሁን ከነገረን ውሸት በአስር እጅ የሚበልጥ ሌላ ውሸት ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ነው። እስከ ፍጻሜው ድል ድረስ ሁላችንም ከሰራዊቱና ከመንግስት ጎን በመቆም የዚህን ጁንታ ቡድን ግብዓተ መሬት ማፋጠን አለብን እያልኩ ላብቃ። ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መስከረም 20/2014