ነገረ ስም አወጣጥ፤
የግለሰቦች ስም አወጣጥ ብዙ ምክንያት ሊኖረው ይችላል። እንዲያው በደምሳሳው ብዙ ወላጆች ለልጆቻቸው ስም የሚያወጡላቸው የወቅቱን ምኞታቸውን፣ ተስፋቸውን፣ ድንገቴ አጋጣሚዎችን አለያም ቁጭት እርካታቸውን ለመግለጽ አስበው ነው ብንል ያግባባ ይመስለኛል። የቤተሰቡ አውራዎች መራራ ወይንም ጣፋጭ የሕይወት ተሞክሯቸውን ቋሚ የማስታወሻ ሐውልት አድርገው ለመትከል በማሰብም ከቤት የሚወጣው የልጆቻቸው ስም ለመዝገብ እንዲበቃ ምክንያት ሊሆኑ ይቻላሉ።
አንዳንዶች ካደጉ በኋላም የራሳቸውን ስም ራሳቸው ማውጣታቸው አልፎ አልፎ የተለመደ ነው። “በተለያዩ ምክንያቶች ስሜን ጠላሁት” በማለትም በፍትሐብሔር ችሎት ፊት ቀርበው በምስክሮች መሃላ ስማቸውን የሚያስለውጡ ዜጎች ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም። ነገረ ትርክቱ ብዙ ነው።
ለማንኛውም ይህን መሰሉን ዙሪያ ጥምጥም የስያሜ ፍልስፍና እዚህ ላይ ገታ አድርገን በዚህ ጽሑፍ ርዕስ ውስጥ በትምህርተ ጥቅስ ተቀንብቦ በተቀመጠው የስም ፍቺ ላይ ጥቂት ነገር ብለን በዋናው ጉዳያችን ላይ ለማተኮር እንሞክራለን።
“ምናሴ” የሚለው ስም ምንጩ የዕብራይስጥ ቋንቋ ነው። በእኛው ቋንቋ አቻ ሞክሼ ይፈለግለት ከተባለ “ማስረሻ” ከሚለው የተለመደና ለወንድም ሆነ ለሴት ከሚሰጠው የስም ትርጉም ጋር በጣሙን ሊጎዳኝ ይችላል። እንግሊዘኛው “cause for forgetfulness” ብሎ ያብራራዋል። በጠቀስነው የዕብራይስጥ ቋንቋ ውስጥም ሆነ መሰል ትርጉም ባላቸው በየብሔረሰቦቻችን ቋንቋዎች አማካይነት ስም የወጣላቸው ግለሰቦች ለስማቸው አወጣጥ ምክንያት የሆነውን አጋጣሚ አስረዱ ቢባሉ የሚሰጡት መልስ “እኔ በተወለድኩበት ዓመት ቤተሰቦቼ ላይ ከፍ ያለ ችግር ተፈጥሮ ስለነበረ ነው” የሚል ዓይነት ተመሳሳይ መልስ እንደሚሰጡ መገመት አይከብድም።
በጽሑፍ የደረስንን ታሪክ እንደ ዋና ማስረጃ በመውሰድ ቅዱስ መጽሐፍ ስለ “ምናሴ” ስም አወጣጥ በሰጠው ፍቺ ላይ ጥቂት እንንደርደር። “ዮሴፍም የበኩር ልጁን ስም ምናሴ ብሎ ጠራው፤ እንዲህም ሲል፡- እግዚአብሔር መከራዬን ሁሉ አስረሳኝ። የአባቴንም ቤት አስረሳኝ” (ኦሪት ዘፍ. ምዕ. 41፡51)። ዮሴፍ የያዕቆብ ልጅና ከአሥራ ሁለቱ የነገደ እስራኤል አለቆች መካከል አንዱና ባለ ጣፋጭ ታሪክ ገድለኛ ነው። በዚያው በጥንታዊ የዕብራይስጥ ቋንቋ ውስጥ “ዮሴፍ” ማለት “ይደመር፣ ተደማሪ” ማለት ነው።
በራሱ ወንድሞች እስከ ግድያ ደረጃ ክፉ የተዋለበት፣ በልዩ ልዩ መከራ የተፈተነ፣ ለባዕዳን ነጋዴዎች በባርነት የተሸጠ፣ በመጨረሻም በአምላኩ ልዩ ተራዳዒነት ታሪኩ ተለውጦ የግብጽ “ጠቅላይ ሚኒስትር” እስከ መሆን የደረሰው ዮሴፍ ከገናና የቅዱስ መጽሐፍ ባለታሪኮች መካከል አንዱ ነው። ይህ አስደናቂ ህያው ታሪክ ለሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ጥሩ ማጣቀሻ ስለሆነ እነሆ ምናሴንና ዮሴፍን ከአስታወስን ዘንዳ ከታሪኩ ስለሚገኘው ትምህርት አንድምታውን ለአንባቢያን እንተዋለን።
ለመጻዒው መንግስት ለምን “የምናሴ ምኞት?”
መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም በሀገራችን የእስከ ዛሬ ታሪክ በመከራም ሆነ በስኬት፣ የተመዘነና የተፈተነ “አዲስ” የሚሰኝ የፌዴራል መንግሥት ሊቋቋም የቀሩት አራት ቀናት ብቻ ናቸው። አዲስነቱ የሚገለጸው በፈተና አሸናፊነትና በመንግሥት አወቃቀር ባህርይው እንጂ ሊመሩን የተዘጋጁትማ እኛው የመረጥናቸው፣ የምናውቃቸውና የሚያውቁን፣ የፈተንናቸውና የፈተኑን ስለመሆኑ ማብራራት አያስፈልግም።
የፓርላማውም አድራሻና መንበር ያው የምናውቀውና አናቱ ላይ በተሸከመው የሰዓት ደውሉ እያነቃን አዲስ አበቤን ይቀሰቅስ የነበረው የዘጠና ዓመቱ አረጋዊ ሕንጻ ነው። የፓርላማው የደውል ልሳን (አልፎ አልፎ ቢያቃስትም) ለምን ለዓመታት ልሳኑ ተዘግቶ እንደተፈረደበት ከአሁን ቀደም በዚሁ ጋዜጣ ላይ አቤቱታዬን ማሰማቴ አይዘነጋም። ለጥቆማው ጆሮውን የሰጠ ሹም ዛሬም ድረስ አለገመኘቱ በራሱ ታሪክ ነው። አዲሶቹ ወንበረተኞች ከተቻሉ ለታሪኩ ሲሉ የደውሉን ድምጽ ቢያስቀሰቅሱልን አይከፋም።
ያለመታደል ሆኖ የሀገራችን የመንግሥታት ሽግግር ታሪክ ለአንድም ጊዜ ቢሆን በሰላም የተጠናቀቀበት ወቅት አልነበረም። ዳግማዊ አጤ ምኒልክ ሥልጣን ላይ የወጡት የውስጥ ተቀናቃኞችን ሴራ አክሽፈውና በጦር ሜዳ ፍልሚያውም ድል ተቀዳጅተው እንደሆነ አይዘነጋም። ከእርሳቸው በኋላ ለዙፋን የበቁት ልጅ እያሱም ሆኑ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ እንደምን እርስ በእርስ ተጠላልፈው ተሰነካክለው እንደወደቁ ለትውልድ ትዝብትና ማስተማሪያነት ታሪኩ በሚገባ ስለተሰነደ ገጾቹን ገልጦ ማንበብ ይቻላል።
ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴም ከአልጋ ወራሽነታቸው ጀምሮ ኢትዮጵያን በመሩባቸው አርባ ዓመታት ውስጥ ከፋሽስት ወረራ እስከ ቤትኛ ተቃዋሚዎቻቸው ድረስ ሲጎነጎንባቸው የኖረው ግልጽና የረቀቀ ሴራ እንደምን በመልከ ብዙ ባህርይው የተወሳሰበ እንደነበር ታሪክም ሆነ ዕድሜውን ያደለን ዜጎች ህያው ምስክሮች ነን።
ፊቱንና ልቡን ወደ ምሥራቅ አዙሮ ከምዕራባዊያን፣ ከቅርብና ከሩቅ ምሥራቅ ሀገራትና ከራሱ ዜጎች ጭምር ሲጋጭና ሲፋጭ የኖረው ግራ ገቡ የደርግ መንግሥትም በአሥራ ሰባት የአገዛዝ ዘመኑ የተፋለመበት ሻምላ በደም እንደተለወሰ ታሪኩ የተደመደመው ከበረሃ የወጡና “ደም የተቃባቸው ተኩላዎች” የበግ ለምድ በመልበስ አሸንፈውት ከመንበረ ሥልጣኑ ፈንግለው ካባረሩት በኋላ ነበር። ይሄው በተኩላ የተመሰለው የህወሓት/ኢህአዴግ አስተዳደር ለሃያ ሰባት ዓመታት ያህል የፖለቲካ ዕድሜውን ያራዘመውና “የበረሃ ቆሌውን” ሲካድም የኖረው የንፁሐን ዜጎችን ደም እየገበረ፣ እያሰቃየና እያኮላሸ በመኩራራት ነበር።
በሀገር ምጥና ጭንቅ እየፈነደቀ መኖሩም የበላዔ ሰብነቱ ግልጽ ማሳያ ነው። ሥርዓቱ የግፍ ትርዒቱን ሲከውን የኖረው በዜጎች ሰብዓዊ ክብር ላይ እየቀለደ፣ ሀብታችንንና ጥሪታችንን እየዘረፈና እየገፈፈ ብቻም አይደለም። የኢትዮጵያን የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር አዱኛም ለራሱና ለዘር ማንዘሩ ሙጥጥ አድርጎ በማጉረስ የሀገሪቱን ሌማት ጦም አሳድሮ ለተዋራጅነት በመዳረግ ጭምር ነው።
“የሚጠላውን ሀገርና ሕዝብ ሲመራ የኖረ ቡድን” የሚለው አባባል በሚገባ ጠቅልሎ ይገልጸዋል። “ምናሴ” ወይንም “ማስረሻ” እንዲሆንል የተመኘነው “አዲሱና ስመ-መልካሙ” የብልጽግና መንግሥትም “እንደ ስሙ እንዲሁ” እንዲሉ መማጠኛችንንና አቤቱታችንን በንግሥናው ማግሥት ይድረስ ማለታችን የዘረዘርናቸውን መሰል ታሪካዊ መከራዎች እንደማይደግመውና እንደሚያስረሳን ተስፋ በማድረግ ነው።
የህወሓትን “አዛባ” እየጠረገ መንገዱን በማመቻቸት ለሦስት ዓመታት ያህል ሲፈተን የኖረው “የብልጽግና ፓርቲ” የሚያዋልደው መንግሥት የተጋፈጣቸው የፈተና ዓይነቶች ምናልባትም በታሪካችን ውስጥ ከአሁን ቀደም ተከስተው ስለመሆናቸው የነገሮች መለዋወጥ ግራ እያጋባ ፋታ ስለነሳን በጥናት ለማረጋገጥ አላስቻለንም። በአጠቃላይ ግምገማ ምላሽ እንስጥ ከተባለ ግን ለሃያ ሰባት ዓመታት ያህል እንደ መዥገር ተጣብቆ የኖረው የወያኔ ሥርዓት ሀገሪቱንና ሕዝቡን ሲመጥ የኖረው ደምና መቅኒያችንንም ጭምር ነው ብሎ መጠቅለሉ የተሻለ ሊገልጸው ይችላል።
ዘረፋ፣ ክህደት፣ ጭካኔ ወዘተ. ሳይፈጸሙብን የተዘነጉ ምንም የግፍ ዓይነቶች አልቀሩም። የራሱን የጥቅም ተጋሪዎች ሳይመለከት ከግለሰብ ጓዳ እስከ ገሃዱ አደባባይ ድረስ በሥርዓቱ አራማጆች ያልተነካና ያልተዘረፈ ኢትዮጵያዊ ማግኘት በእጅጉ አዳጋች ነው። ፖለቲካን ለራስ ጥቅም፣ ኢኮኖሚን ለገዛ ከርስ፣ ዲፕሎማሲን ለግለሰቦች ክብር፣ ሕዝብን ለመስዋዕት በግነት (Scapegoat)፣ ሀገርን ለውርደት፣ የመከላከያ ኃይልን ለመበቀል ወዘተ. ሲሰራ የኖረ መሰል “ሥርዓት” በዓለማችን ላይ ከአሁን ቀደም ታይቶ ከሆነ የሚያውቁ ቢያሳውቁን አይከፋም። በ2014 ዓ.ም ሊወለድ “ወረ-ገብ” የሆነውን መንግስት “ምናሴ”- “ማስረሻ” ይሁንልን ብለን ከወዲሁ “ስም” ለመሰየም የተሽቀዳደምነውም ቢጨንቀንና ያለፍንበት የመከራ የግፍ ምሬት ቢጎመዝዘን ነው።
መንግሥታችን ሆይ! አንተን መምረጣችን ተረጋግጦ የአውራ ጣታችን ጥፍር የተኳለበት የምርጫ ቀለም (election ink) ገና ወይቦ አልጠፋም። የቀለሙ ያለመደብዘዝ ለበርካቶቻችን ብዙ ተምሳሌታዊ ትርጉም ይሰጠናል። እነሆ “መንግሥትህ ትምጣ” እያልን የምንጓጓው ያለምክንያት አይደልም። የሚያሳስቡንን በርካታ መሠረታዊ ሀገራዊ ችግሮች ከወዲሁ የምንዘከዝከው የዜግነትና የመራጭነት “ዴሞክራሲያዊ መብታችንን” ለመለማመድ እንጂ በፀጉራችን ቁጥር የተሸከምናቸው ሀገራዊ ፍዳዎች በሙሉ በአንድ ጀንበር ተፈትተው ነፃነት ይታወጃል ብለን ጓጉተን ያለመሆኑ ይታወቅልን።
የምንዘረዝራቸው ችግሮች እንዳይደገሙ፤ ቢቻልም እንዳይታወሱ፤ የመንግሥታችን የሥራ መጀመሪያ ቢሆኑ አንጠላም። የፓርላማው መንበርና “በዮሴፍነት” የሚሾመው “ፊት-ቀደም መሪም” የሕዝብን ድምጽ በሌትም ሆነ በቀን ጆሮውን ከፍቶ ቢሰማን አንጠላም። ከታች የመጡት “ተወካዮቻችን” ወደ ላይ ከፍ ብለው ሲወጣ ነገረ ዓለሙን ሁሉ ዘንግተው ራሳቸውን አግዝገው ሕዝብን ዝቅ አድርገው እንዳይመለከቱ ፈራ ተባ እያልን “ልባችን ያባውን” በብዕራችን መግለጣችንም ስለዚሁ ነው።
ከአሁን ቀደም እንዲህ መሰሎቹን ሹማምንት እያየን ስንጨስ ስለኖርን የዛሬዎቹ የሕዝብ አገልጋዮችም ይሄው ባህርይ እንዳይጣባቸው ከወዲሁ “ቀይ መስመሩ” ተለይቶ ቢሰመርላቸው አይከፋም። መንግሥት የሕዝብን ኡኡታ እያደመጠ እንዳልሰማ በመምሰል “አስፈጻሚዎቼ እኮ የፖለቲካ የበኩር ልጆቼ ናቸው!” እያለ በማንቆለጳጰስና በእሹሩሩ አትንኩብኝ፣ አትድረሱባቸው እያለ እንዳያስደነግጠን እንመኛለን። በሕዝብ ሚዲያ ላይ እዬዬ እያልን ስንጮኽም “ይለፍልፉ! የፈለጉትን ይለቅልቁ! ምን እንዳያመጡ!” እየተባለ የንቀት ምላሽ ባይሰጠንም እንወዳለን። “የሕዝብ ድምጽ የእግዜር ድምጽ ሆኖ” ፍርዱ እንደሚፋጠን ከእኛው ከራሳችን ታሪክ ብዙ ማስረጃዎች ስለምንጠቅስ ሕዝብን መዳፈር እንደማይበጅ ይታወቅልን።
ወደ አንኳር ጉዳያችን እንዝለቅ፤
አዲሱ መንግሥት በሀገሪቱ የዲፕሎማሲ አወቃቀር ላይ ሥር ነቀል እርምጃ እንደሚወስድ እንጠብቃለን። ይሄ ሳይሆን ቀርቶ በየዓለም ክፍሎች የሚመደቡት የሚሲዮን አባላት “በዕድሜያቸው ማምሻ ላይ እፎይ ብለው እንዲያርፉ” የሚለው “የእከክልኝ ልከክልህ” መርህ “በአዲሱ መንግሥትም” የሚቀጥል ከሆነ “ውርድ ከራሳችን” ብለን የመከራውን አሳር እንደለመድነው አብረን እናጭዳለን። የሚበጀው በትምህርት ዝግጅት፣ በልምድም ሆነ በተፈጥሮ ችሎታው ሀገርን የመሸከም ጫንቃው የደነደነ ዲፕሎማት እንዲመደብና “የኤምባሲ ጽ/ቤቶቻችን የኢትዮጵያ ተምሳሌት እንዲሆኑ ነው።” ይህ ሳይሆን ቀርቶ “እባቡን አይተን በልጡ የማንበረይ ከሆነ” እንደግመዋለን “ውርድ ከሕዝብ ራስ ብለን” የሚሆነውን በትዕግስት እንጠብቃለን። ጸሐፊው በፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባልነቱ ይህንን ቀዳሚ መልእክት ደፈር ብሎ አስተላልፏል።
የሀገሪቱ ቋሚ የህልውና እስትንፋስ በዋነኛነት የተመሰረተው ከሕዝብ በሚሰበሰብ የግብር ገቢ ላይ መሆኑ እንኳን እኛን ነፍስ ዐወቅ ዜጎችን መዋዕለ ሕጻናት የምንልካቸውን ልጆቻችንን እንኳን ይጠፋቸዋል ተብሎ አይገመትም። ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በ1887 ዓ.ም የሸዌው ሕዝባቸው ግብሩን በታማኝነትና በጊዜው ወደ ግዛታቸው ግምጃ ቤት እንዲያስገባ “ሰው እንደ አቅሙ፤ እህሎ እንደ ቅርሙ” በማለት ተርተው እንዳበረታቱት ሁሉ፤ ዛሬም እያንዳንዱ ሰው በታማኝነትና በግልጽነት “የቄሳርን ለቄሳር” የሚለውን የቅዱስ መጽሐፍና የመንግሥትንም ሕግ አክብሮ በግብር ክፍያ ረገድ እንዲታመን ግድም ውዴታም ነው።
ይህ ጸሐፊ የሀገሪቱ “የበጎ ፈቃድ የታክስ አምባሳደር” ሆነሃል ተብሎ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ በሕዝብ ስም አደራ ስለተቀበለ ይህንን ጉዳይ ጊዜውን ሁሉ ሰውቶ ኑሮው እያንገዳገደውም ቢሆን አደራውን ለመወጣት አይቦዝንም። መንግሥታችን ሆይ! እውነታው ይህንን ቢመስልም በገቢ ሰብሳቢው መ/ቤት ውስጥ የሚፈጸመው ግፍና እምባ ግን እንዲህ ነው ተብሎ በቋንቋ የሚገለጥ አይደለም። በሀገሬ ምድር የድሆችና የነጋዴዎች እምባ ከትንሽ እስከ ትልቅ እንደ ምንጭ ከሚፈልቅባቸው ሀገራዊ ተቋማት መካከል አንዱና ተቀዳሚው ይህ የግብር ሰብሳቢ መ/ቤት እንደሆነ የማረጋግጠው በበቂ ማስረጃ ነው።
እርግጥ ነው የግብር አሰባሰቡ ጉዳይ የሌባና ፖሊስ መሰል ድብብቆሽ የሚስተዋልበት እንደሆነ መዘንጋት አይገባም። ችግሩ በተቋሙ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በነጋዴው ዘንድም እጅግ ጎልቶ እንደሚስተዋል መካድ በፍጹም አይቻልም። ቢሆንም ግን በራሱ የተዝረከረከ ተቋማዊ አሰራር የራሱን እድፍ ሳያጸዳ እንዳቅሙ ግብር የሚከፍለውን ዜጋና “በኪሳራ ምክንያት ድርጅቴን ዘጋሁ” የሚለውን ግለሰብ “ኮተታ ኮተት እስከማሸጥ” ድረስ እንዴት እንደሚያስለቅስ ጎራ ብሎ ዓይቶ እውነቱን መመስከር ይቻላል። ኢትዮጵያ የምትሰበስበው የግብር ገቢ በእንባ የወረዛ ስለመሆኑም አያከራክርም።
በግሌ በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ አዲሱ መንግሥት በመጀመሪያ ሊወስድ ካሰበው የሪፎርምና የተሃድሶ ተግባራት መካከል አንዱ ጊዜ የማይሰጠው ይህ የገቢ ሰብሳቢ መ/ቤት ስለመሆኑ በአምባሳደርነቴ መሃላና በህሊናዬ ምስክርነት የምገልጸው እውነት ስለሆነ ነው። ምናልባትም መንግሥትን እያዘናጋ ያለው “ይህንን ያህል ቢሊዮን ብር በዚህን ያህል ጊዜ ሰበሰብኩ” የሚለው ሪፖርት ይሆንን ብልን እንጠረጥራለን። ሰሞኑን የተቋሙን አሰራር በተመለከተ የሚኒስትሮች 100ኛ ጉባዔ የወሰደው የማሻሻያ ውሳኔ ምን እንደሆነ በዝርዝር ቢገለጽልን ባልከፋ ነበር። ለማንኛውም ሥር ነቀል መፍትሔ ተሰጥቶበት ከሆነ እሰዬው! እንደተለመደው ተነካክቶ ታልፎም ከሆነ የገቢዎች መስሪያ ቤት ጉዳይ በጥብቅ እንዲታሰብበት ደግመን ደጋግመን አደራ እንላለን።
ወጣቶቻችን በብሔራዊ አገልግሎት መርሃ ግብር የዜግነት ድርሻቸውን ስለሚወጡበት መንገድ አዲሱ መንግሥት አንድ ሀገራዊ ውሳኔ ላይ ቢደረስ ምኞታችን ነው። ይህ አሰራር ምን ተግባራት እንደሚፈጸሙበትና እንደሚተገበር ዝርዝሩን ለአጥኚዎቹ በመስጠት ሃሳቡን ብቻ ጠቁመን እናልፋለን። በየከተማው ያገነገኑ ወጣቶች ያሻቸውን የግለሰቦችና የመንግሥት መሬት እየወረሩና እያስወረሩ መፏለላቸው የተለመደም የሚያስፈራም ክስተት ከሆነ ውሎ አድሯል። ማን ፊት እንደሚሰጣቸውና ማን ከኋላ እንደሚገፋቸው በሚገባ ተጠንቶ የማያዳግም እርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ “በቆይ ብቻ” ሪፖርት መቆዘሙ ችግሩን እያከፋው ስለሆነ አዲሱ መንግሥት በአዲስ ጉልበት ከሚፋለምባቸው ቀዳሚ አጀንዳዎች መካከል አንዱ ሊሆን ይገባል።
“የዕለት እንጀራችንን አታሳጣን” የሚለው የሕዝባችን የሠርክ ጸሎት በእግዚሃሩ ዘንድም ሆነ በመንግሥት በኩል ጆሮ የተነፈገው ይመስል ጦም ውሎ ጦም ማደር የሕዝቡ የዕለት “ሲሳይ” ከሆነ ሰነባብቷል። የገበያውና የኑሮ ጡዘቱ ሕዝቡን “ጨርቅ አስጥሎ” ካሳበደም ዓመታት ተቆጥረዋል። እግዚኦታውም ሆነ እዮታው ስላለቀብን አዲሱ መንግሥታችን ሆይ እንድታውቀው ብቻ ጉዳዩ ለጆሮህ ይድረስ ብለናል። ከቶውንስ መች ጠፍቶህ!
የገበሬውን “የእኔስ ጉዳይ?”፣ የሕዝቡን የፍትሕ ያለህ ጩኸት፣ የትምህርት ሥርዓቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ መዝቀት፣ የፌዴራል አወቃቀሩን ከፋፋይነት፣ የሕገ መንግሥቱን አንካሳነት ጫን ብዬ “ለአዲሱ መንግሥት” በአቤቱታዬ ውስጥ ያላካተትኩት በጓዳው ውስጥ ሲሰራቸው ከከረመባቸው አጣዳፊ አጀንዳዎች መካከል ተቀዳሚ ጉዳዮች እንደሆኑ ከውስጥ አዋቂዎች አንደበት በሹክሹክታ ስለሰማሁ ነው።
በተረፈ አዲሱ “የብልጽግና መንግሥት” ሆይ! ይቅናህ። እስከ ዛሬም በአደራ ጠባቂነት ስላከናወንካቸው እጅግ መልካም ተግባራት ምሥጋናችንን ተቀበል። አዲስ አበባን እንዳስዋብካት ሁሉ እጅህን ለሌሎቹም ዘርጋላቸው። ትልቁ የመነሻ አደራችን ግን “ምናሴ” – “ማስረሻ” ሁንልን ነው። የመርግ ያህል ብንጭንብህም የአደራ ጉዳይ ነውና በፍጹም አስፈጻሚ ሹማምንትህን አታሞላቅቃቸው። ተራ ሆነው እንደኖሩት ተራ ሆነው ያገልግሉ። ተራ ማንነት የሚከብዳቸው ከሆነ ለተረኛው ወንበራቸውን ይልቀቁ።
“ሲሾም ያልበላ” በሚል የፍልስፍና መርህ የተጠጉህን ሁሉ ጠረናቸውንና ጓዳቸውን እየፈተሽክ የምታደርገውን አድርግ። “ምናሴ ሆይ!” የቤት ሥራውን አበዛሁብህ መሰለኝ። “በመስከረም ደረሰልኝ ገብሴ፣ በጥቅምት እላለሁ ጥቂት፣ በህዳር እላለሁ ዳር ዳር፣ በትሣሥ እጅንፉ ደረስ” አለ ይባላል የዋሁ የሀገሬ ተስፈኛ ገበሬ። አሜን ይሁንልን! ሰላም ለሀገራችን! ሰላም ለሕዝባችን! በሁሉም ዘርፍ የተትረፈረፈ ሰላም ይብዛልን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 19/2014