ሀገር በግለሰቦች አስተሳሰብ የቆመች የብዙ አመለካከቶች ድምር ውጤት ናት። ኢትዮጵያውያንም ሀገር የሚስሉ ትውልድ የሚፈጥሩ ግራና ቀኝ አመለካከቶችን የያዝን እንደመሆኑ የሀገራችን አሁናዊ መልክ በእኛ በልጆቿ የተፈጠረ፤ መልኳም የእኔና የእናንተ መልክ ነው። በዚህ ግራ ቀኝ አመለካከታችን የምንፈጥረውም ሆነ የምናጠፋው ሕዝባዊ ታሪክ አለ። በመኖራችን ውስጥ የምናከናውናቸው እያንዳንዱ ሕይወታዊ እንቅስቃሴ በሀገራችን የነገ መልክ ላይ የራሱ አሻራ ይኖረዋል።
በዚህ ረገድ «እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል» በሚል ታሪክ የምናበላሽ ብዙ ነን፤ ዛሬ ላይ ሆነን ነገን አሻግረን ባለማየታችን ብዙ ዋጋ እየከፈልንም እንገኛለን። ለምሳሌ፣ አሁን ላይ በሀገራችን እየሆነ ያለው ነገር ትናንት ያኖርነው የአዳፋ የሥዕል አሻራ ውጤት ነው። በየዘመኑ በጊዜአዊ ጥቅም፣ ስር በሰደደ ራስ ወዳድነት የሳልናቸው እኩይ ምስሎች ዛሬ ላይ እያሰቃዩንና ዋጋ እያስከፈሉን ይገኛሉ። ይሄም ከዛሬ ቀጥሎ የሚመጣ ሌላ ቀን መኖሩን ካለመገንዘብ፤ በዚያ ቀን ላይ ለሚፈጠር አዲስ ትውልድ ካለማሰብ የመነጨ ነው፤ ይሄን ተገንዝበን የተሻለ ነገር ያለመስራታችን ነገ የሚያስከፍለን ዋጋ ቀላል አይሆንም።
ኢትዮጵያ የእኔና የእናንተ መልክ መሆኗን ካመንን፤ ከትምህርት ቤት ስትቀሩ፣ ከሥራ ገበታችሁ ስታረፍዱ የሀገራችሁን ጸዓዳ መልክ እያጠየማችሁ እንደሆነ አስቡ። ጥቅም ለማግኘት እጅ መንሻ ስትቀበሉና ስትሰጡ ሀገራችሁን እያሳደፋችሁ መሆኑን እወቁ። በሙያችሁ ኃላፊነት ሲጎድላችሁ፣ የሀገርና የሕዝብን ሉአላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ተግባራትን ስትፈጽሙ ያኔ ሀገራችሁን እያዋረዳችሁ እንደሆነ ልብ በሉ። ለሕዝብ ግልጋሎት የተሰሩ መሠረተ ልማት ስታወድሙ፣ በውሸት ትርክት በሕዝቦች መካከል መቃቃርን ስትፈጥሩ ያኔ ሀገራችሁን እየገደላችኋት እንደሆነ አስታውሱ።
ዛሬ ላይ ሀገራችን ላለችበት ወቅታዊ ሁኔታ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ብዙ ነገር አድርገናል። የእኔና የእናንተ አመለካከት በሀገራችን ህልውና ላይ የሆነ ቦታ ላይ አለ። የምንሆነውና እየሆንን ያለነው ማንኛውም ነገር በአገርም፤ አገርን እየመራ ባለው የለውጡ ኃይል ላይ አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖ አለው። ምክንያቱም የዛሬዋ ኢትዮጵያ የተፈጠረችው በዜጎቿ ትናንታዊ አስተሳሰብ ላይ እንደመሆኑ፤ የነገዋ ኢትዮጵያም የምትገነባው በዛሬዎቹ በእኛ አስተሳሰብና ምግባር ላይ ነው።
ዛሬ ላይ የምንሆነውና እየሆንን ያለነው ነገር ሁሉ የእኛንም ሆነ የሀገራችንን መጻኢ ዕድል የሚወስን በመሆኑ ከዛሬ ባለፈ ስለ ነገዋ ኢትዮጵያ ምንድነው የምናስበው? ዛሬ ላይ ምን እየሆንን፣ እያደረግን ነው? ቤተሰቦቻችን የሚያስተምሩን፣ ትምህርት ቤት መምህራኖቻችን የሚሰጡን እውቀት ምን ዓይነት ነው? የምንኖርበት ማህበረሰብም ሆነ እኛን የሚያስተምሩን አካላት የትናንቷን ኢትዮጵያ ምን ያህል አውቀው እያሳወቁን ነው? የሚሉትንና ሌሎችም ጥያቄዎች መልስ መስጠት አለብን። የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በዚህ ጥያቄ ውስጥ ነው ያለችው።
ሀገራችንን እንደፈለግን አድርገን የምንስላት እኛ ነን። ታዲያ እጃችሁ ላይ ያለው ብሩሽ ምን ዓይነት ነው? ቀለማችሁ፣ ሀሳባችሁ ምን ዓይነት ነው? መልካም ሀገር ለመፍጠር መልካም ቀለምና መልካም ሀሳብ ያስፈልጋል። ለዚህም ከሁሉ በፊት አመለካከታችሁን ማጥራት ያስፈልጋል። የእኔና የእናንተ ለውጥ የሀገራችን ለውጥ እንደመሆኑ ለሀገር የሚሆን ብዙ እውነትን ከልባችን ውስጥ ማፍለቅ ይጠበቅብናል። እኔና እናንተ ሳንዘምን የምትዘምን ሀገር አትኖረንም። እኔና እናንተ ሳንሻሻል የሚሻሻል ማህበረሰብ አይኖረንም።
የሚበጀን እያለ በማይበጀን ነገር ላይ እየተባላን ብዙ የስኬትና የለውጥ ዓመታትን በከንቱ አሳልፈናል። የሚጠቅመን እያለ በማይጠቅመን ነገር ስንጋፋ አስቀያሚ ዛሬን ፈጥረናል። ይህንን በሚገባ በመረዳት የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ የከፍታ ዘመን እንዲቀርብ ከሁሉ በፊት እኛ መለወጥ አለብን።
በመለወጣችን የተለወጠች ኢትዮጵያን መፍጠር እንችላለን። እጃችን ላይ ባለው ብርሃናማ ዕድል ብርሃናማ ትውልድ መፍጠር እንችላለን። እጃችን ላይ ባለው ድብልቅ ቀለም የጥቁርን የነፃነት ምድር በተሻለ መልኩ መሳል እንችላለን። ያቺን ምኒልካዊቷን ጥቁር ወይዘሮ.. አብዲሳ አጋይቷን እመቤት፣ የዘርዐ ደረስን ምድር..የበላይ ዘለቀን ርዕስት እውነተኛይቱን ኢትዮጵያን መፍጠር አይከብደንም። የሀገራችን አሁናዊ መልክ ደብዛዛ ነው። ትናንትናዊ ውብ መልኳ የለም። የኢትዮጵያ መነሳት የአፍሪካ መነሳት እንደሆነ የገባቸው ምዕራባውያንና ሌሎችም አካላት እጃችንን ለመጠምዘዝና ለማዳከም እየተጉ ነው።
የአንድነታችን ነጸብራቅ..የትንሳኤአችንን አብሳሪ.. የተስፋችን ምልክት ይሄን ሁሉ የሆነውን ህዳሴ ግድባችንን እንዳንገነባ የነገር ገመድ የሚሸርቡብን ብዙ ናቸው። ከውስጥና ከውጭ ብዙ መከራና ችግር ከበዋት ውብ መልኳን አጠይመውታል። ሁላችንም ኢትዮጵያን ከእነዚህ ችግሮች ለማሻገር እና ለኢትዮጵያ መልካሙን ለማድረግ ትክክለኛው ሰዓት ላይ እንዳለን ልብ ልንል ይገባል። ሀገራችንንም ሆነ ሕዝባችንን ከችግር ለማውጣት ከዚህ የተሻለ ምቹ ጊዜ የለም። ጠላቶቿን በጽናት በመታገል የጀመረችውን የተስፋ ጎዳና ማስቀጠል ይገባናል።
ሀገራችን የምትለወጠው በውጭ እርዳታ ሳይሆን በእኔና በእናንተ አብሮነት ነው። አንድነት ምን ያክል ኃይል እንዳለው አድዋን ማየት ብቻ በቂ ነው። አድዋ መላው የጥቁር ሕዝብ ቀና ያለበት፣ መላው ነጭ የተዋረደበት የጥቁሮች የይቻላል መንፈስ ያበበበትና የተጀመረበት ታሪካዊ አውድ ነው። ኢትዮጵያ ጣሊያንን በማሸነፏ ጣሊያን ብቻ አልነበረም የተዋረደችው በአደዋ ድል መላው የጥቁር ሕዝብ የመኩራቱን ያክል መላው ነጭም የተዋረደበት ሁኔታ ነበር የተፈጠረው። እነርሱም የኢትዮጵያን የማሸነፍ ታሪክ ከአንድነት ጋር ያያይዙታል። ኢትዮጵያውያን አንድ መሆን ባይችሉ ኖሮ ዛሬ ላይ የአድዋ ታሪክ የጣሊያኖች ታሪክ ይሆን ነበር የሚሉ ብዙ ናቸው። አሁንም ከፊታችን የተጋረጠውን አሁናዊ የጠላት በትር በለመድነው አንድነታችን በመመከት ዳግማዊ አድዋን መጻፍ አለብን።
እኛ ተለውጠን አገራችንን በመለወጥ ሂደትም በአስተሳሰባችን፣ በኑሮ ዘይቤአችን መቀየር ይኖርብናል። የመለወጥ እሳቤና ሥልጣኔ ያለው ደግሞ አእምሯችሁ ውስጥ ነው። የዚህ ዓለም የለውጥ ኃይል ያለው ልባችሁ ውስጥ ነው። በአእምሯችን እናሳድግ ..በልባችን እንለወጥ። በሕይወታችን ውስጥ ለራሳችን ሆነ ለሌሎች አስፈላጊዎች መሆናችንን እንቀበል።
ለችግሮቻችን መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ በሀገራችን አሁናዊ ሁኔታ የምንዘባበት ብዙዎች ነን። ይሄ የአእምሮ እድገት ውስንነት የፈጠረው ነው። በአካል ስለጎለመስን ..ከአንተነት ወደ አንቱነት ስለተሸጋገርን ትልቅ ነን ማለት አይደለም። ትልቅነት ያለው ትልቅ አስተሳሰባችሁ ውስጥ ነው። ትልቅ የምንባለው ለሀገራችንና ለሕዝባችን የሚሆን በጎ ህሊና ሲኖረን ነው። ዛሬ ላይ ሸብተውና ጎልምሰው አንቱ በተባሉ ሰዎች መከራችንን እያየን መሆኑንም መዘንጋት የለብንም።
በጎ የሚያስብ ሰው ሁሌም ትልቅ ነው። እኛ ብዙ መልካም ፍሬን ማፍራት የሚችል ዛፍ ላይ ያሉ ቅርንጫፎችና አበባዎች ነን። እኛ የኢትዮጵያ ብዙ ተስፋና ብዙ እውነት ነን። ግንዱ ጸንቶ ይቆም ዘንድ ሁላችንም እናስፈልጋለን። አገራችን ግንዳችን ናት። የቆምነው በእሷ ላይ ነው። ማማራችን ፣ ወጥተን መግባታችን ፣ አግብተን መውለዳችን፣ ብዙ የብዙ ራእይ ባለብት መሆናችን በእሷ ነው። እናም ምሳራችንን እንጣል። መገዝገዛችንን እንተው። ዋርካ ሆና ለብዙዎቻችን ጥላ እንድትሆን እንስራት።
አንድ ዛፍ ያለ ስር፣ ያለ ቅርንጫፍ፣ ያለ አበባና ፍሬ ብቻውን ዛፍ መሆን አይችልም። ሀገራችን ዛፍ ናት፤ እኛ ደግሞ ስርና ቅርንጫፎቿ፣ ፍሬና አበባዎቿ ነን። በዚህ እውነት እና በዚህ ሥርዓት ውስጥ ነን። አእምሯዊ እሳቤያችንን በማዘመን ለሌሎች አስፈላጊዎች ሆነን እንቁም። የእኔና የእናንተ ለውጥ የሀገራችን ለውጥ ነው። የእኔና የእናንተ ትልቅ መሆን የሕዝባችን ትልቅ መሆን ነው። በአካል ሳይሆን በአእምሮ መሰልጠንን ባህል እናድርግ። አንድነታችንም ለኢትዮጵያችን ጸንቶ መሻገሪያ ነውና በጋራ ቆመን ተሻግረን ሀገራችንን እናሻግራት! አበቃሁ ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መስከረም 19/2014