የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ከዚህ በፊት በዳያስፖራው ማህበረሰብ የሚነሱ ቅሬታዎችን በአግባቡ ለመመለስ እንዲያስችል ተደርጎ መዋቀሩን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ተናገሩ።
ዳይሬክተሯ የኤጀንሲውን መመስረት አስመልክቶ ዛሬ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ በሰጡት መግለጫ የዳያስፖራ ጉዳዮች ከዚህ በፊት በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር በአንድ ዳይሬክተር ጄኔራል ሲመራ የነበረ መሆኑን አስታውሰው እየጨመረ ከመጣው የዳያስፖራ ፍላጎት አንፃር ይህንን ለማስተናገድ ራሱን የቻለ ኤጀንሲ ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ኤጀንሲው ተቋቁሟል ብለዋል።
ተጠሪነቱ ለውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የሆነውና የፊታችን አርብ በይፋ ስራ መጀመሩ በሸራተን ሆቴል የሚበሰረው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የአደረጃጀት ስራዎችን ሰርቶ አጠናቋል የተባለ ሲሆን ዳያስፖራውን ማስተባበር፣ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ በተጨባጭ ማወቅ፣ ዳያስፖራው በሀገሩ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ተሳታፊ እንዲሆን ማስቻል እና የዳያስፖራውን ሙሉ መረጃ በአንድ የመረጃ ቋት አደራጅቶ መያዝ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ናቸው ተብሏል።
የዳያስፖራ ፍላጎቶችን የጎዱ ተብለው የተለዩ አምስት ማነቆዎች ተለይተው በእነሱ ላይ ለመስራት ዝግጅት መደረጉ በመግለጫው የተነሳ ሲሆን ዳያስፖራው በሀገሩ ሰርቶ ተጠቃሚ የሚሆንበትን መንገድ ያለ ምንም ውጣ ውረድ ለማመቻቸትም ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል።
እንደ ወ/ሮ ሰላማዊት ገለፃ ምን ያህል ዳያስፖራ በየትኛው ሀገር አለ ? የሚለውን መረጃ በመሰብሰብ የዳያስፖራ የመረጃ ቋት ለማዘጋጀት ዝግጅት እየተደረገ ነው፤ ለዚህም በተለያዩ የአለማችን ሀገሮች ከሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አመራሮችና ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጋር መረጃውን በአግባቡ መሰብሰብ የሚያስችል ስምምነት እየተደረገ ነው።
ዳያስፖራ ሲባል በአሜሪካና አውሮፓ ያለው ላይ ብቻ የማተኮር አዝማሚያ ከዚህ በፊት ነበር ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ አሁን የተቋቋመው ኤጀንሲ ይህ አይነቱን አስተሳሰብ የሚያስወግድ፣ በሁሉም አለማት ያሉ ኢትዮጵያውያንን በእኩል አይን የሚያይና የሚያስተናግድ ይሆናል ብለዋል።
በመግለጫው ኤጀንሲው 53 ሰራተኞች ያሉት ሲሆን 60 ያህል ሚሲዮኖች ላይ ቅርንጫፍ ይኖረዋል፤ ለጊዜው ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ህንፃ ስራውን ይጀምራልም ተብሏል።
”እኔ ለኢትዮጵያ ኢትዮጵያም ለእኔ” የሚል መሪ ቃል ይዞ ስራውን የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በመጪው አርብ በሸራተን ሆቴል በይፋ ስራ መጀመሩ ይበሰራል።
በድልነሳ ምንውየለት
ፎቶ፡- በፀሀይ ንጉሴ