አሜሪካ እና ቻይና የንግድ ውጥረቱን ለማርገብ ተስማሙ

የአሜሪካ እና የቻይና ባለሥልጣናት በእንግሊዝ ለንደን ባደረጉት ውይይት ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ላይ የተቀመጡ እገዳዎችን ለማቃለል እና የታሪፍ ስምምነትን በማስቀጠል የንግድ ውጥረቱን ለማርገብ ተስማምተዋል።

ባለሥልጣናቱ ቻይና ወደ ውጭ በምትልካቸው ብርቅዬ ማዕድናት ላይ የተጣሉ ገደቦችን ለማቃለል እና ለረጅም ጊዜ ለቆዩ የንግድ ልዩነቶች ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት ያላቸውን ፍላጎት አሳይተዋል።

በለንደን የተደረገው የሁለት ቀናት ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላም የአሜሪካ የንግድ ሚኒስትር ሃዋርድ ሉትኒክ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ የስምምነት ማሕቀፉ በሀገራቱ መካከል ያለውን ከፍተኛ የታሪፍ ጭማሪ ለመቀነስ የተደረገውን የጄኔቫ ስምምነት ያስቀጥላል። የጀኔቫው ስምምነት ቻይና ወሳኝ ማዕድናትን ወደ ውጪ የምትልክበትን መንገድ በመገደቧ እና አሜሪካም በምላሹ የራሷን የኤክስፖርት ቁጥጥር በመጣሏ ስምምነቱ ተቋርጦ ቆይቷል።

የንግድ ሚኒስትሩ በለንደን የተካሄደው አዲሱ ስምምነት አሜሪካ ቀደም ሲል ያስቀመጠቻቸውን አንዳንድ ገደቦች እንደሚያቃልል ተናግረው፤ ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድ ውጥረት ለማርገብ ባለፈው ወር በስዊዘርላንድ፣ ጄኔቫ ከተማ ሁለቱም ወገኖች አብዛኛውን ታሪፍ እንዲያነሱ ያስቻለ ቅድመ-ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር። በእዚህም በለንደን በተካሄደው ውይይት የጄኔቫን ስምምነት እና በሁለቱ ፕሬዚዳንቶች መካከል የተደረገውን የስልክ ውይይት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ማሕቀፍ መደረሱን የንግድ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ነገር ግን ወደ ተግባር ከመግባታቸው በፊት ስለ ስምምነቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን እና  የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግን ጨምሮ የከፍተኛ አመራሮችን ይሁንታ ማግኘት እንዳለባቸው ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የማሕቀፉ ዝርዝር ሁኔታ ግልፅ ባይሆንም፤ ስምምነቱ ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ለፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ ቀርቦ እንደሚጸድቅ ተደራዳሪዎቹ መናገራቸውን አል ጀዚራ ዘግቧል።

የዩናይትድ ስቴትስ የንግድ ሚኒስትር ሃዋርድ ሉትኒክ፤ ፕሬዚዳንቶቹ ስምምነቱን ካጸደቁ በኋላ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሞክሩ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

የቻይና ምክትል የንግድ ሚኒስትር ሊ ቼንግጋንግ ውይይቱን “ፕሮፌሽናል ዕሳቤ ያለው፣ ምክንያታዊ፣ ጥልቅ እና ግልጽ” ብለውታል።

ሁለቱ ወገኖች በስብሰባው ላይ የተደረጉትን ንግግሮች እንዲሁም በመርህ ደረጃ የተደረሰው ማሕቀፍ ላይ መሪዎቻቸው መልሰው እንደሚያቀርቡ ሊ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

የቻይና የንግድ ምክትል ሚኒስትር ሊ ቼንግጋንግ በበኩላቸው፤ በመርህ ደረጃ ከስምምነት የደረሰው ስምምነት የመሪዎችን የመጨረሻ ፍቃድ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You