ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት አሜሪካ ራሷን ከዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች የመነጠል ፖሊሲ (Isolation policy) ትከተል ነበር። ነገር ግን ይህ ፖሊሲዋ ሌሎች ሀገራት በአሜሪካ ላይ ከሚያደርሱት ጥቃቶች ሊያተርፏት አልቻለም። ይህን የተገነዘበችው አሜሪካ ራሷን በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ከመነጠል ይልቅ በተለይም የ2ኛው የዓለም ጦርነት ከሚካሄድበት ወቅት ጀምሮ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ ማድረግን መርጣለች። ይህንን ውሳኔዋን እውን ለማድረግም ሁለት ነገሮች ዕድል ፈጥረውላታል።
አንደኛው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መባቻ እና በጦርነቱ ወቅት የዓለም ሀገራት በሁለት ጎራ ተከፋለው ወደ ለየለት ጦርነት በገቡት ወቅት አሜሪካ የእርሻ እና የኢንዱስትሪ ውጤቷን ለተፋላሚ ወገኖች በመሸጥ በሀብት ላይ ሀብት መገንባት መቻሏ በዋናነት የሚጠቀስ ነው። በዚህም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1928 እስከ 1945 ባለው ጊዜ ውስጥ የአሜሪካ ጠቅላላ ብሔራዊ ምርት (Gross National Product) ከ91 ቢሊዮን ዶላር ወደ 213 ቢሊዮን ዶላር ማደግ ችሏል።
ይህም ጠቅላላ ብሔራዊ ምርቷ የብሪታኒያ ዜጎች ከሚያገኙት በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ፤ የሩስያ ዜጎች ከሚያገኙት ደግሞ በሰባት እጥፍ የሚልቅ ነበር። ይህ የአሜሪካ የኢኮኖሚ እድገት አሜሪካ በሌሎች ሀገራት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ጣልቃ በመግባት በምትፈልገው መንገድ ለመጠምዘዝ እንድትችል የተሻለ ዕድል ፈጥሮላታል።
አሜሪካ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንድትችል በር የከፈተው ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መፈጠር ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከአንድ ጎራ የተሰለፉት አሜሪካ እና ብሪታኒያ የአክሲስ ፓወርስ እየተሸነፉ መምጣታቻውን ተከትሎ ድሉ ማጋደሉ ሲገነዘቡ እና የማታ ማታ ድሉ የነሱ መሆኑን ሲረዱ በ1941 እኤአ የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሮስቬልት ጋር በካናዳ አትላንቲክ ኮስት ላይ በምስጢር ስብሰባ በማድረግ አንድ ዓለምአቀፋዊ ድርጅት መመስረት እንዳለባቸው መክረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንትም ስለጉዳዩ ቀደም ብለው እንዳላሰቡበት፤ ወደፊት ግን እንደሚያስቡበት ለእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ነግረዋቸው ቢለያዩም ከሁለት ዓመት በኋላ በ1943 በኢራኗ መዲና ቴህራን ከብሪታኒያ እና አሜሪካ በተጨማሪ ራሽያ ተገኝታ ሊመሰረቱት ስላሰቡት የዓለም አቀፍ ድርጅት ጉዳይ በመምከር እ.ኤ.አ በ1945 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን መስርተዋል ።
በአሜሪካ እና በብሪታኒያ የበላይነት የተመሰተረተው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከጊዜ ወደ ጊዜ የተቋቋመለትን ዓላማ ወደ ጎን በመተው የመስራቾቹ የአሜሪካ እና የብሪታኒያ ጉዳይ አስፈጻሚ ወደ መሆን ተቀይሯል። በዚህም ዓለምን ችግር ውስጥ የከተቱ ወገንተኝነት የተንጸባረቀባቸው ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ወገንተኝነቱን አደባባይ ያወጡ ተግባራትን ፈጽሟል፣ እየፈጸመም ይገኛል።
ለዚህም የሩቁን ትተን በእኛ ሀገር ላይ በዚህ ወቅት እየፈጸመ ያለውን ተግባር እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። የመጀመሪያው በዓለም ታሪክ ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ግልጽ የልማት ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ የግድቡ ሂደት ሌላ ትርጉም እንዲላበስ በማድረግ በጸጥታው ምክር ቤት እንዲታይ ተደርጓል። በዚህም የግድቡን ሥራ ለማስተጓጎል ጥረት ብዙ ርቀቶችን ሲጓዙ ተመልክተናል።
ከሰሞኑ ደግሞ የጸጥታው ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አንቶኖ ጉተሬዝ አሸባሪው ህወሓት ዓለም አቀፍ ሕጎችን በሚጻረር መልኩ በአደባባይ ከፍያሉ ወንጀሎችን እየፈጸመ ባለበት ሁኔታ ቡድኑን ከማውገዝ ይልቅ «ህወሓት ጦረኛ ነው፤ በጦርነት ህወሓትን መፋለም ያስቸግራል ስለዚህ መደራዳር አለባችሁ» ሲሉ የአሜሪካንን ፍላጎት የሚሸከም ሀሳብ ሰንዝረዋል።
የአንቶኖ ጉቴሬዝ አባባል ከጸጥታው ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የማይጠበቅ እና ኃላፊነት የጎደለው እንደሆነ ለመናገር የሚከብድ አይደለም። ምክንያቱም የአንቶኖ ጉቴሬዝን አባባል በሌላ አነጋገር ብንተረጉመው አሸባሪውን ህወሓት በርታ በጦርነቱ ግፋበት እኛ ከጎንህ ነን ዓይነት ትርጉም የሚሰጥ ነው ።
ከዚህም በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አሸባሪው የህወሓት ቡድን የሚያደርሳቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዳላየ እና እንዳልሰማ በመሆን ዝምታ መምረጡ ሌላው የአደባባይ ምስጢር ነው ።
እውነታው አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ምክር ቤቱን እንዴት አድርጋ የፍላጎቷ ማስፈጸሚያ እያደረገች እንደምትጠቀምበት ተጨባጭ ማሳያ ነው። ከዚህም በላይ ምክር ቤቱ በራሱ የቱን ያህል በአሜሪካ ተጽዕኖ ውስጥ ማደሩን እና ቋንቋ ሳይቀር ከአሜሪካ ተፅዕኖ ስር እንዳለ የሚያመላክት ነው ።
በርግጥ አሜሪካ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ እያደረገችው ያለው ያልተገባ ጫና እና ማዕቀብ የአሸባሪውን ትህነግ ከመሞት ሊታደገው የሚችል አይደለም። ይህን ስል በምክንያት እንጂ በግብዝነት ስላለመሆኑ አያሌ አመክንዮችን ማቅረብ ይቻላል። ለዛሬው ግን የተወሰኑትን እንመለከት።
«መሬት ላይ የወደቀ አረም ቶሎ ሊታረም ወይም ሊነቀል ይችላል፤ አዕምሮ ላይ የወደቀ አረም ግን ለመንቀል ዘመናትን ይጠይቃል። » የሚለው አባባል የአሜሪካን ቆመ ቀር የውጭ ፖሊሲ በደንብ የሚገለፅ አባባል ይመስለኛል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይሄን ቆሞ ቀር የሆነውን የአሜሪካ ፖሊሲ በውል በመረዳቱ ኢትዮጵያን ከጥፋት ለመታደግ መስራት ባለበት ልክ እየሰራ ይገኛል። ይህም ምንድን ነው ፤ ከዚህ በፊት ማለትም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አሜሪካ በሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሰበብ በሀገራት ውስጣዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት የፈጠረቻቸውን ምስቅልቅሎች የኢትዮጵያ ከታሪክ መገንዘብ ችሏል።
አሁን ላይ አሜሪካ በተመሳሳይ መንገድ ኢትዮጵያ ላይ በሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሰበብ ለመፍጠር እየሞከረች ያለው ምስቅልቅል እንዴት መመከት እንደሚችል ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ብዙ መማር ይቻላል። በተለይም የአሜሪካ አስተዳደር በ17 ዓመቱ የአሸባሪው ህወሓት የትጥቅ ትግል ወቅት በኢትዮጵያ ላይ በሰብአዊ መብት ጥሰጥና በእርዳታና ማዕቀብ የፈጸመችውን ያልተገቡ ተግባራት በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል።
በወቅቱ የነበረው የአሜሪካ መንግሥት ሀገሪቱ ትከተለው የነበረው የምሥራቁ ዓለም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ወደ አፍሪካ ሊስፋፋ ይችላል በሚል ስጋት በወቅቱ በሽብርተኝነት የሰየመችውን ህወሓት ሕይወት ዘርቶ ወደ ሥልጣን እንዲመጣ ከፍ ያሉ ድጋፎችን አድርጋለች፤ የቡድኑን ኢሰብአዊ ተግባራትን እንዳላየ በመሆን ለጥፋቱ የልብ ልብ ሆናለታለች። ዛሬ እያደረገች እንዳለችው ማለት ነው ።
ይህንን ታሪካዊ እውነታ መንግሥት፣ ተፎካሪ ፓርቲዎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ምሁራን፣ የሚዲያ ባለሙያዎች ወዘተ በአግባቡ ተረድተውታል። ከዚህ መረዳት በመነሳትም ሀገርና ሕዝብን ከተመሳሳይ ሴራ ለመታደግ እያደረጉት ያለው ጥረት የሚበረታታና ፍሬ እያፈራ ነው።
አሜሪካ በሰብአዊ መብት ጥሰት በእርዳታና በማዕቀብ ስም የምታደርገውን ጫና ለመመከት እየሄዱበት ያለው መንገድና ያገኙት ስኬት የሚደነቅ ነው። ሴራውን ለማክሸፍም ትልቁ አቅም ያለው በሕዝባችን ችግሩን መረዳት ላይ ነው፣ ለዚህ ደግሞ አሁን ሕዝባችን ውስጥ ችግሩን የመረዳት አቅም ከፍ ያለ የአላማ ጽናት እየፈጠረ መሆኑ እየታየ ነው። እውነታውም በታሪክ ውስጥ በደማቁ በወርቅ የሚጻፍ፤ እንደ አድዋ ድል በታሪክ ሲታወስ የሚኖር ነው።
ሌላው አሜሪካ ያልተገባ ጫና እና ማዕቀብ በመጣል አሸባሪውን ትህነግ ከመሞት መታደግ የማትችልበት ምክንያት ውስጣዊ ልዩነቶችን በመቻቻል ለማጥበብ እየሄድንበት ያለው መንገድ ነው። አንድ ሰው ሁለት ዓይነት ህመም ሊታመም ይችላል። አንደኛው ውጫዊ ህመም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ውስጣዊ ነው። ውጫዊ ህመም (ቁስል) በቀላሉ ስለሚታይ ለማከም ብዙ የሚያስቸግር አይሆንም።
ውስጣዊ ሲሆን ግን ለማከም እንደሚከብድ እሙን ነው። ይህን ወደ ዲፕሎማሲው እና ፖለቲካው አምጥቶ ማየት ተገቢ ነው። ለአንድ ሀገር ህልውና በከፍተኛ ደረጃ ስጋት የሚሆነው ከውጫዊ ህመም ይልቅ ውስጣዊ ህመም ነው። በሌላ አባባል የአንድን ሀገር ህልውና በከፍተኛ ደረጃ ሊጎዳው የሚችለው የዜጎች ውስጣዊ ስምምነት ማጣት ነው። የውጫዊ ችግሩን ግን በተጠናከረ የውስጥ አንድነት መመከት ይቻላል። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን በውል ተረድቶ እየተንቀሳቀሰ ነው። አሁን ላይ ያለውን የውስጥ አንድነት ከውጭ ለሚሰማን ህመም ማሻሪያ ሁነኛ መፍትሄ እንዲሆን አድርጎም እየሰራ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል የኢትዮጵያውያንን ሰብአዊም ሆነ ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመጣስ ሰዎችን ሲገድል፣ ሲያስር፣ ሲያፍን፣ ለጆሮ እና ለዓይን በሚዘገንን መልኩ ኢትዮጵያውያንን ሲያሰቃይ የነበረ እና ከዚያም በኢትዮጵያውያን የጋራ መራር ትግል ከሥልጣን ተባሮ መቀሌ ከመሸገ በኋላ ኢትዮጵያን ለማፍረስ መከላከያን ሲመታ፣ በማይካድራ፣ በጋሊኮማ፣ በአጋምሳ፣ በጭና፣ በጋይንት ዘግናኝ ጭፍጫፋ ሲደረግ እና በግፍ ላይ በግፍ ሲፈፅም አሜሪካ ስለእውነት ለሰብዓዊም ሆነ ለዴሞክራሲያዊ መብቶች ጠበቃ ነኝ ካለች ከአሸባሪው ትህነግ ጎን መቆም አልነበረባትም።
አሸባሪው ትህነግ በኢትዮጵያውያን ላይ በበደል ላይ በደል ሲፈፅም አሜሪካ እና አጋሮቿ ቡድኑ የሚያደርጋቸውን የሽብር ተግባሮች ከማውገዝ ይልቅ አይዞህ በርታ ከጎንህ ነን በሚል መልኩ ስለእውነት እና ለነፃነት በሚፋለሙ ኢትዮጵያውያን ላይ ማዕቀብ ለመጣል ሲተጉ እያየን ነው።
ይህን የአሜሪካ አካሄድ የሚመለከት ማንም ሰው የታዋቂውን ገጣሚ የመንግሥቱን ለማን ግጥም ማስታወሱ የማይቀር ነው ።
በርሃ እያለ ሰሃራ ደረቁ ፣
ካላሃሪ እያለ በረሃው ደረቁ፣
ኦጋዴን እያለ ክው ያለው ገጠር
የኩርንችት መደብ የግብርና ጠር።
የት ይዘንባል ዝናብ ? ውቂያኖስ ላይ
ጉልህ ነው ስህተቱ ለዕውር የሚታይ። (መንግስቱ ለማ )
እውነት ነው! የዝናብ ዶፍ ሕንድ ውቂያኖስ ላይ ውርጅብኝ ከሚያወርድ ምን አለበት ውሃ በናፈቃቸው የበርሃማ ቦታዎች ላይ ቢዘንብ። አሜሪካም እያደረገች ያለው ልክ የዝናቡ ዓይነት ነው። ለተበደለ ሳይሆን ለበደለ ጠበቃ በመሆን እውነትን እና ነጻነትን ፈልገው ፍትሃዊ ጦርነት እያደረጉ ከሚገኙት ኢትዮጵያውያን በተቃራኒው በመቆም ኢትዮጵያውንን በመግደል እና በማፈናቀል ሀገሪቱን እያጎሳቆለ ከሚገኘው አሸባሪው ትህነግ ጋር «የረከሰ ጋብቻ » በመፈጸም ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራች ነው ።
ይህ የአሜሪካ እና የአሸባሪው ትህነግ የረከሰ ጋብቻ ለሰብአዊ እና ለዴሞክራሲያዊ መብት መከበር ከእኔ በላይ ላሳር የምትለውን አሜሪካ በታሪኳ ሲያስወቅሳት የሚኖር አሳፋሪ ድርጊት ነው።
ከዚህ ባሻገር ይህ የረከሰ ጋብቻ ፍትሃዊ ጦትነት እያደረጉ ለሚገኙት ኢትዮጵያውያን ጠላታቸው ማን እንደሆነ ጠንቅቀው እንዲያውቁ ያስቻለ ነው። ጠላታቸውን ጠንቅቀው ማወቃቸው ደግሞ ጠላታቸውን ለመከላከል የሚወስደውን የትግል ጊዜ እንደሚያሳጥርላቸው ይታመናል።
አሜሪካ የትኛውንም ያህል አሸባሪውን ትህነግ ብትደገፍ ከመሞት ልታድነው የማትችልበት ሌላው ዓብይ ምክንያት ደግሞ ጀግንነት የኢትዮጵያውያን ሀብት መሆኑ ነው። ይህን ስል በግብዝነት ስላለመሆኑ አያሌ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። የኢትዮጵያውያን የጀግንነት ታሪክ ከሁለት ሺህ ዓመት በላይ እንደሆነው የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
ለምሳሌ በ336 ዓመተ ዓለም ገደማ በግሪክ የነገሰው ታላቁ እስክንድር ኢትዮጵያን ለመውረር ፍልጎት ነበር። ነገር ግን የታላቁ እስክንድር ፍላጎቱ በኢትዮጵያ ጀግኖች የጀግንነት ገድል ከፍላጎት በላይ መሄድ እንዳልቻለ በወቅቱ የነበረ ኩዌንተስ ኩሪቲዎስ የተባለ የታሪክ ጸሐፊ ስለኢትዮጵያውያን ጀግንነት በጻፈው መጻሐፉ አስፍሮታል።
ሌላው ስለኢትዮጵያውን ጀግንንት ምስክርነት የሰጠው ደግሞ ሴኔካ የተባለ የሮማን ኢፓየር ሰላይ እና የታሪክ ጸሐፊ የነበረ ሰው ነው። በ29 ዓመተ ዓለም የሮም ቄሳር የነበረው ኦጎስቶስ ቄሳር ኢትዮጵያን ለመውረር መጥቶ ሱዳን ድንበር ላይ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ መመለሱን ይናገራል ።
ከሰላሳ ዓመት በኋላ የኦጎስቶስ ቄሳርን ሽንፈት ለመበቀል ኔሮ የተባለ ሌላኛው የሮም ቄሳር ኢትዮጵያን ለመውረር ፈልጎ የነበረ ቢሆንም ወደ ኢትዮጵያ በላካቸው ሰላዮቹ አማካኝነት በተሰበሰበ መረጃ ኢትዮጵያን ማሸነፍ እንደማይችል ይገነዘባል። በዚህም ከኢትዮጵያ ጋር ከጦርነት ይልቅ ዝምድና ለመፍጠር የተሻለ ጥቅም እንደሚያስገኝለት በመገንዘብ ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነት ለመፍጠር የተለያዩ ሙከራዎችን ማድረጉን ሴኔካ በከተባቸው የታሪክ ድርሳናት በግልፅ ተቀምጠው ይገኛሉ።
በዘመናዊት ኢትዮጵያም ግብፅን፣ ጣሊያንን፣ ሶማሊያን ወዘተ የመሳሰሉ የውጭ ወራሪዎችን የኢትዮጵያ ጀግኖች አሳፍረው እንደመለሱ የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። ለዚህ ሁሉ የኢትዮጵያውያን ጀግንነት ዋነኛው ምክንያት እና ምንጩ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ሁሉ ያደረጓቸው ጦርነቶች የውጭ ኃይላት ኢትዮጵያ ላይ በሚፈፅሟቸው ግፎች እንጂ ኢትዮጵያ በፀብ ጫሪነት ያካሄዷቸው አለመሆናቸው ነው። ኢትዮጵያውያን ያደረጉአቸው ጦርነቶች ስለእውነት እና ለፍትህ የተደረጉ ጦርነቶች በመሆናቸው ብዙ ጀግኖችን አፍርተዋል፤ የጀግንነት ታሪክና ሕዝብ ባለቤት አድርጓቸዋል።
ይህ ታሪካዊ እውነት ኢትዮጵያን በማን አለብኝነት ከውስጥ ባንዳዎች ጋር ሆነው ለማፍረስ የሚሰሩ ኃይሎች ፍላጎት እንደማይሳካ የሚያረጋግጥ ነው። ስለፍትህ የሚደረግ ትግል የቱንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍል በድል ስኬት እንደሚጠናቀቅ የሚያመላክ ነው። እኛም የአባቶቻን ታሪክ በጽናት በመድገም ባለታሪክ መሆናችንን የሚያረጋግጥ ነው።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን መስከረም 18/2014