በተሽከርካሪዎች ግጭት በመንገድ ሀብት ላይ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ4.3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
በግማሽ ዓመቱ ውስጥ በቀለበት መንገድ ላይ 82፤ ከቀለበት መንገድ ውጪ ደግሞ 190፤ በድምሩም 272 የግጭት አደጋዎች መድረሳቸው ተጠቅሷል፡፡
በግጭት ጉዳት እየደረሰባቸው የሚገኙትም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገዝተው በምሽት አገልግሎት እንዲሰጡ የተተከሉ የመንገድ ሀብቶች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡
ከነዚህ መካከል የመንገድ ዳር መብራት ምሰሶዎች፣ የትራፊክ ምልክቶች፣ የአቅጣጫና ርቀት አመላካች ሰሌዳዎች፣ የእግረኛ መከላከያ አጥሮች፣ የመንገድ ማካፈያ ግንቦች እንዲሁም የውሃ መውረጃ ቱቦዎችና ክዳኖች ይገኙበታል፡፡
እንደ ኢቢሲ ዘገባ የመንገድ ሀብቶቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመጠገን ጉዳት አድራሾች ተመጣጣኝ የሆነ የጉዳት ካሳ እንዲከፍሉ የሚገደዱ ሲሆን በዚህም ባለስልጣኑ በግማሽ ዓመቱ ውስጥ ከ2.6 ሚሊዮን ብር በላይ የጉዳት ካሳ ግምት መቀበሉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የመንገድ ሀብቶች በሚገጩበት ወቅት ከሚደርሰው ጉዳት ባለፈ መልሰው እስኪጠገኑ ድረስ ለተጨማሪ የትራፊክ አደጋ መንስኤ ሊሆኑ ስለሚችሉ በሀብቶቹ ላይ የሚደርሰውን ግጭት በጥንቃቄ በማሽከርከር አስቀድሞ መከላከል እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡
የመንገድ መሰረተ ልማት ለከተማይቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መፋጠን ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ተገንብተው አገልግሎት ላይ የዋሉ መንገዶችን በጋራ መጠበቅ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡