ፈረንሳዊው የቀድሞ የአርሰናል አስልጣኝ አርሰን ቬንገርና ፖርቹጋላዊው የቀድሞ የቼልሲና የማንችስተር ዩናይትድ
አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኒሆና በእንግሊዝ በነበራቸው ቆይታ ከእግር ኳሱ ሜዳ ፍልሚያ ብቻም ሳይሆን ለተዳጋጋሚ ጊዜ ከቃላት ውርርፍ ባለፈም
ለድብድብ ሲጋበዙ ተስተውለዋል። የሁለቱ አሰልጣኞች ፍልሚያም አንዳንዶችን ሲያዝናናቸው ሌሌችን ደግሞ ምነው ክብርና እድሜያቸውን
የሚመጥን ተግባር ቢያሳዩ ሲሉ እንዲያዝኑባቸው ምክንያት ሲሆንም ታይቷል።
የሁለቱ አሰልጣኞች የቃላት ጦርነት አሃዱ ያለው እኤአ 2005 አርሰን ቬንገር አንድ ጨዋታ ላይ ካሰለፏቸው ተጫዋቾች ውስጥ አንድም እንግሊዛዊ ተጫዋች አለመኖሩን ተከትሎ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ከእኛ በላይ ከአንድ ጆን ቴሪ በስተቀር ቼልሲን እንግሊዛዊ ተጫዋችን አላካተተም ማለታቸውን ተከትሎ ነው።
ይህን የመድፈኞቹ አለቃ አስተያየት የሰሙት ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኒሆ በወቅቱ መልስ ለመስጠት አልፈለጉም። ይልቅስ በሚቀጥለው የውድድር ዓመት በጠንካራ የመከላከል አጨዋወት የታነፀ ቼልሲን እውን በማድረግ የሊጉ ሻምፒዮን መሆን ቻሉ።
የሰማያዊዎቹ ሻምፒዮን መሆንና የታክቲክ አቀራረባቸውን በሚመለከት የመድፈኞቹ አለቃ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ‹‹በዚህ አይነት የአጨዋወት ፍልስፍና እግር ኳስ ውበቱን ተነጠቆ አደጋ ውስጥ እንደሚገባ እንዳትጠራጠሩ›› የሚል አስተያየት መስጠታቸው ግን ለቼልሲው አለቃ ምቾት አልሰጣቸውም።
ሞሪኒሆ፣ «ቬንገር ከኛ ጋር ችግር አለበት፤ እሱ ሌሎችን ሰዎች ማየት የሚወድ ሰው ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ትልቅ ቴሌስኮፕ ገዝተው ጎረቤት ምን እየተካሄደ እንደሆነ ያያሉ፤ ቬንገር እንደዛ አይነት ሰው ነው፡፡ የራሱን የቤት ስራ በመተው የሌሎችን ይከታተላል›› ሲሉ ወርፈዋቸዋል። ይህን የሰሙት አርሰን ቬንገርም፤ ‹‹ሞሪኒሆ ከእውነታ ጋር የተለያየ፤ የማይረባና ክብረቢስ ሰው ነው፡፡ አንዳንዴ ደደብ ሰዎች ስኬትን ሲያገኙ አዋቂ ከመሆን ይልቅ ድድብናቸው ይባባሳል›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጆዜ ሞሪኒሆ፣ እንግሊዝን በመልቀቅ በጣሊያን የኢንተር ሚላን እንዲሁም ከስፔን የሪያል ማድሪዶች አለቃነታቸውን አገባደው ሲመለሱ ማረፊያቸውን የቀድሞው ቤታቸው ቼልሲ ካደረጉ በኋላም የሁለቱ አሰልጣኞች ፍልሚያ መቋጫውን አላገኘም።
በተለይ ቼልሲ በውድድር ዓመቱ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ያለበትን ሁለት የሊግ ጨዋታ ካገባደደ በኋላ፤ ስፔናዊው ሁዋን ማታን ለቀያይ ሰይጣኖቹ ለመሸጥ ሲወስን፤ይህ የፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ የብልጣብልጥ ሂሳብ እንዳልተመቻቸው የሚያሳብቅ አስተያየትን ሲሰጡ፤ ሞሪኒሆ በምላሻቸው ‹‹ከታሪክ ልምድ በመነሳት የቬንገር አስተያየት የሚጠበቅ ነው፤ በተጫዋቹ ዝውውር ያልተደሰተውም ተፈጥሮው ስለሆነ ነው፡፡›› በማለት ተናግረዋል፡፡
ከቆይታዎች በኋላ በቬንገር የጨዋታ ፍልስፍና ላይ ተቀናቃኞቻቸው የሚያነሱትንና ውበት ብቻውን ውጤት አልባ ከሆነ ምን ዋጋ አለው ሲሉ የሚያጣጥሉት ለምን ይሆን በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ፤ ‹‹ውድቀትን መፍራት ይመስለኛል፡፡›› ሲሉ፤ ይህን የሰሙት ጆዜ ሞሪኒሆ «ሌላ ማንም ሳይሆን የውድቀት ስፔሻሊስት ራሱ ነው፡፡» ማለታቸው የሁለቱን አሰልጣኞች ፍጥጫ ይበልጥ አክርሮታል።
ይህ እሰጥ አገባ እየከረረ ሄዶ በፈረንጆቹ ጥቅምት 2014 ስታንፎርድ ብሪጅ ጨዋታ በመምራት ላይ እያሉ በተፈጠረ ግጭት ሁለቱ አሰልጣኞች እስከመተናነቅና ከረቫት እስከመጓተት ደርሰው ታይተዋል።
ከሰሞኑ ታዲያ ጆሴ ሞሪኒዮ ለአርሰን ቬንገር የተሰጣቸውን የመታሰቢያ ሽልማት ምክንያት በማድረግ የቀድሞ ተቃናቃኛቸውን «አርሰን ቬንገር በእግር ኳስ ታሪክ ከታዩ ምርጥ አሰልጣኞች ውስጥ አንዱ ነው፡፡» ሲሉ ማሞካሸታቸው ብዙዎች ያልጠበቁት አስደንጋጭ ዜና መሆኑን የስካይ ስፖርት ዘገባ አስነብቧል።
አርሰን ቬንገር በፈረንሳይ ሞናኮ በተደረገው የላውረንሰን ሽልማት የህይወት ዘመን ስኬታማ አሰልጣኝ የሚለውን ሽልማት ካሸነፉ በኋላ እራሳቸውን ዘ ስፔሻል ዋን እያሉ የሚጠሩት ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ፤ «እውነት ባለን የፉክክር ስሜት በጣም ነበር የምዝናናው፤ ሁሌም ቢሆን ለቬንገር እውነተኛ የሆነ ክብር አለኝ፡፡›› ሲሉ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ተናግረዋል።
«ቬንገር ለክለባቸውም ይሁን ለዓለም እግር ኳስ አስደናቂና በርካታ ታሪኮችን ሰርተዋል፤ ቅፅላ ስማቸው ‹‹የማይበገር›› ( the Invincible) ነው። አስደናቂ አሰልጣኝና በአጨዋወት ፍልስፍናውም ምርጥ ቡድን የመሰረተ ነው፡፡›› ሲሉም አሞካሽተዋቸዋል። ይህን የጆዜ አድናቆት የሰሙ ታዲያ እግር ኳስ የፉክክር ፍልሚያ ከመሆን ባለፈ የእርስ በእርስ መቃቃሪያ እንዳልሆነ ምስክር የሚሰጥ ነው ብለውታል።
በአሁኑ ወቅት ሁለቱ አሰልጣኞች ክለብ አልባ ሲሆኑ፣ ፈረንሳዊው አርሰን ቬንገር ሁለት አስርት ዓመታትን ከቆዩበት አርሰናል ሲለቁ፤ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ከማንችስተር ዩናይትድ ቤት በውጤት ድርቅ መሰናበታቸው ይታወሳል። ሁለቱ የቀድሞ ተቀናቃኝ አሰልጣኞች በአሁኑ ወቅት በቢን ስፖርት ላይ በተንታኝነት እየሰሩ ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011
በታምራት ተስፋዬ