አምቦ፡- በአምቦ ከተማ አዘጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 16ኛው የመላው ኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ውድድርና
12ኛው የባህል ፌስቲቫል አምስት ክልሎች አለመሳተፋቸው ታወቀ።
በውድድሩ ቤንሻንጉል ጉምዝና ጋምቤላ ክልል በበጀት እጥረት ምክንያት እንደማይሳተፉ ቀድመው ያሳወቁ ሲሆን፤ ትግራይ፣አፋር፣ ሱማሌ ደግሞ ምክንያቱ ባልታወቀ መልኩ በውድደሩ አለመገኘታቸው ታውቋል። በውድድሩም 900 ተሳታፊ እንደሚጠበቁ የተገለጸ ቢሆንም፤ በአምስቱ ክልሎች መቅረት ምክንያት የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 500 ዝቅ ሊል ግድ ብሎታል።
በአምቦ ስታዲየም እየተካሄደ ባለው ውድድር አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ ስፖርተኞች በከፍተኛ ሁኔታ ፉክክር እያደረጉ ይገኛሉ። ድምቀቱን በጠበቀ መልኩ እየተጓዘ ባለው ውድድሩ ከትናንት በስቲያና ትናንት ውድድሮች ተካሂዷል።
በዚህ መሰረትም በኩርቦ ሴቶች በተደረገው ውድድር ወደ ግማሽ ፍጻሜ ያለፉት ክልሎች የተለየ ሲሆን፣ ከአማራ ክልል ትጓደድ አረጋ እና ዘውዴ መለሰ 10 ነጥብ በማምጣት አንደኛ ወጥተዋል። አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በእናት አጥናፍ እና መክሊት ግርማ 8 ነጥብ በማምጣት ሁለተኛ ሲሆን፣ ብርሀኔ ብሬ እና ትዝራ ሀይሌ ከደቡብ ክልል 8 ነጥብ በማምጣት ወደ ቀጣዩ ዙር ተሸጋግረዋል።
በድብልቅ ኩርቡ ደግሞ እማሙ አብዱና መሰረት ኬኛ ከአዲስ አበባ አንደኛ፣ አብተው ይርጋ እና ወርቅነሽ አገኘው ከአማራ ክልል ሁለተኛ ሆነዋል። ለማ ሽንጤ እና ብርቱካን አቡ ከደቡብ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል።
በውድድሩ ከተከናወኑ ጨዋታዎች የሴቶችና ወንዶች ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን፣ በ53 እስከ 57 ኪሎ ግራም የሴቶች ኦሮሚያ እና አማራ ተጫውተዋል። ብርቱ ፉክክር በታየበት በዚህ ትግል ኦሮሚያ 2 ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በ53 እስከ 57 ኪሎግራም የወንዶች ኦሮሚያ ደቡብን 2ለ0 ረቷል። በገና ውድድር ኦሮሚያ ከደቡብ እንዲሁም አማራ ከድሬዳዋ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።
16ኛው የመላው ኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ውድድር እስከ የካቲት 24 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ በ13 የባህል ስፖርት አይነቶች ይካሄዳል።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011
በዳንኤል ዘነበ