የኢትዮጵያ ስፖርት ታሪካዊ አመጣጥ ስንመለከት ዘርፉ በመንግስት አደረጃጀት ህጋዊ አውቅና አግኝቶ ተቋማዊ
ቅርፅ በመያዝ እንደ ማህበራዊ ዘርፍ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረው በ1956 ዓ.ም ነው። ከዚህ በኋላ ባሉት ዓመታት ስፖርቱ በተለያዩ
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጥላ ስር በስራ ክፍል ደረጃ እንዲደራጅ እየተደረገ ሲሰራ ቆይቷል።
በ1967 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የባህል፤ ስፖርትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ተብሎ በመመሪያ እንዲቋቋም ተደርጓል። እንደገና በ1968 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 92 /68 የኢትዮጵያ ስፖርትና አካል ማሰልጠኛ ኮሚሽን በሚል ስያሜ በባህልና ስፖርትና ወጣቶች ሚኒስቴር ስር ራሱን ችሎ እንደ መንግስት ተቋም ተደራጅቷል።
ከዓመት በኋላም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ስልጣንና ሃላፊነት ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 127/69 በአማካይነት የባህልና ስፖርት ጉዳዮች በአንድ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስር እንዲዋቀር ተደርጓል። በማስከተልም ከ1976 እስከ 1993 ዓ.ም በዘርፉ ላይ የተለያዩ የአደረጃጀት ለውጦች ሲደረጉ የወጣቶችን ጉዳይ አካቶ በአንድ ላይ የወጣቶች፤ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ በ1998 ዓ.ም ደግሞ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በሚል ተቋቁሟል።
በመቀጠልም የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን መንግስት አስፈፃሚ አካላትን ለማቋቋም ባወጣው አዋጅ ቁጥር 692/2003 መሰረት ተቋቁሞ፤ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይታል። በአሁኑ ወቅትም በፌዴራል ደረጃ የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን፤ በክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በአብዛኛው ራሳቸውን ችለው በስፖርት ኮሚሽን፤ በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ ከወጣቶች ጋር በመጣመር በቢሮ እንዲደራጅ ተደርጓል፡፡
በዚህ መልኩ የአገሪቱ ስፖርት የአደረጃጀት በየጊዜው ሲፈርስና ሲገነባ ቆይቷል። አመራሮቹም እየተቀያየሩ ስፖርቱ በሚፈለገው ልክ ሳይሆን ቀርቷል።
ከ2007 ዓ.ም ወዲህ ያለውን ጊዜ ብቻ ብንመለከት የስፖርት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ስር በኮሚሽን ደረጃ እንዲዋቀር ተደርጓል። በእነዚህ አደረጃጀቶችም አራት አመራሮችን ቀያይሯል።
የአንደኛው ውጤታማነትና ክፍተት ሳይለይ ወደ ሌላ አደረጃጀት የመግባትና ስፖርትን በበላይነት የሚመራው አካል ባልተረጋጋ ሁኔታ መገኘት ስፖርቱ በሚፈለገው ልክ እንዳይጓዝ እያደረገው ነው ሲሉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡
የአገሪቱ ስፖርት አደረጀጃትና መዋቅር መገለባበጥና ወጥ ሆኖ የመጓዝ ድክመትም በተለይም በክልሎች ያለው የስፖርት ዘርፍ አደረጃጀትና የአስፈፃሚ ተቋማት ጉራማይሌ አወቃቀር በስፖርቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደር መጀመሩም እየተጠቆመ ነው። አዲስ ዘመንም ይህን እሳቤ በሚመለከት የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የዘርፉን አካላት አነጋግሯል።
የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ባዘዘው ጫኔ፤ ጉራማይሌ የስፖርት አወቃቀር በስፖርቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳረፉን ይናገራሉ።
እንደ ኮሚሽነሩ ገለፃ፤ የአስፈፃሚ ተቋማት አደረጃጃት ከአንድ አገር ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ደረጃ እየተቃኘ በየጊዜው ይቀያየራል። በኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት የአደረጃጃት መዋቅር ተዘጋጅቷል።
ይሁንና የስፖርት ዘርፉ ብቻ አንድ ጊዜ ራሱን ችሎ ሲቆም፤ሌላ ጊዜ በሌሎች ዘርፎችና መስኮች ላይ እየተለጠፈ ሲወዛወዝ ተስተውሏል። በአሁኑ ወቅትም የፌዴራል አወቃቀሩን ተከትሎ ክልሎች ባላቸው ስልጣን መሰረት ባካሄዱት አወቃቀር አንዱ ኮሚሽን ሌላው ቢሮ አድርገው አዋቅረዋል፡፡ በተጠሪነት ረገድም አንዱ ለባህልና ቱሪዝም ሌላው ለሴቶች ወጣቶችና ህፃናት ተጠሪ እየተደረገ ተደራጅቷል።
ምንም እንኳን አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ አዲስ አወቃቀር ሊፈጠር ቢችልም ፣ በየጊዜው እንዲወዛወዝ ማድረግ ግን አግባብ አለመሆኑን ነው ኮሚሽነር ባዘዘው የሚናገሩት፡፡ አወቃቀሩ እርስ በእርስ ለመደጋገፍና ወጥነት ያለው ተግባር ለመፈፀም የሚጎለው እንዳለም ይጠቅሳሉ፡፡ በተለይ በፌዴራል ደረጃ የስፖርት ኮሚሽን በባህልና ቱሪዝም ስር መሆኑ አግባብ አለመሆኑን ይገልጻል፡፡
እንደ አቶ ባዘዘው ገለፃ፤ በፌዴራል ደረጃ ይህ አደረጃጃት ሲዋቀር ዋናው ፍኖተ ካርታ ጥናት ላይ ተመስርቶ መሆኑ እርግጥ ነው። ስፖርቱ ባህልና ቱሪዝም ስር ተጠሪ ሆነ ማለትም ሚኒስቴሩ በስፖርቱ ስራ ገብቶ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴውን ይሰራል ማለት አይደለም። ሚኒስቴሩ በድጋፍ ሰጪነት ግን ሊሳተፍ ይችላል።
ይሁንና የአደረጃጃት ተግባራዊነቱ በጥንቃቄ መመራት ይኖርበታል። ምክንያቱም የአንድ ተቋም ተልዕኮ መሰራት ያለበት በራሱ ብቻ ነው። ይህ እስከሆነ ድረስም የአገሪቱ ስፖርት ፖሊሲ መፈፀምና መመራት ያለበት በአዲሱ አወቃቀር በፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ሊሆን ግድ ይላል።
‹‹በአሁኑ ወቅት በአንድ በኩል ባህልና ቱሪዝም በሌላ በኩል በስፖርት ኮሚሽን የሚመጣ የስራ አቅጣጫና አንዳንዴም ዋናው ባለቤቱ ቀርቶ ተጠሪ ነኝ የሚለው ተቋም የሚሰራው ተግባር አለ» የሚሉት አቶ ባዘዘው፤ በዚህ ረገድ የሚስተዋለው መጓተትና መጣረስም በፍፁም መስተካከል እንደሚኖርበት ያስገነዝባሉ።
እርሳቸው እንደሚገልፁት፤ ኮሚሽኑ የተቋቋመበት ዓላማና የተሰጡት ሃላፊነቶች አሉ።ይህን በባለቤት መምራት ያለበት ራሱ ብቻ ነው። በተጠሪነት ምክንያት እናት መስሪያ ቤቱ የሆነው ተቋም ኮሚሽኑን ተክቶ ሊሰራ ከቶውንም አይገባም። ዘርፎች የሚደጋገፉበት ሁኔታ ቢኖርም፤ አደጋገፉ ግን በኃላፊነታቸው ልክ ሊሆን ይገባል። በተጠሪነት ሰበብም ስራን ወዲህና ወዲህ ማመላለስ ትክክለኛነት አይደለም።
በመጀመሪያ አንድ ተቋም ሲዋቀር ባለሙያዎችን ማማከር እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት አቶ ባዘዘው፤ በሌሎችም ዘርፎች እንደሚስተዋለው በስፖርቱ አወቃቀር ግን ባለሙያዎችን የማማከር ተግባር አልተስተዋለም ይላሉ፡፡ አሳታፊ ባለመሆኑ ችግሮች እያፈጠጡ የሚመጡት ፀድቆ ወደ ስራ በሚገባበት ጊዜ መሆኑን ይናገራሉ።
የሚያጋጥሙ መሰናክሎችን ለመሻገርም መፍትሄ የሚሉትን ኮሚሽነሩ ይጠቁማሉ፡፡ ኮሚሽኑ በተደራጀ መልኩ ራሱን ችሎ መውጣቱን ቀዳሚ የሚያደርጉት አቶ ባዘዘው፤ የስፖርቱን አደረጃጃት በየጊዜው ከማወዛወዝና አፍርሶ ከመስራት የህዝብን ፍላጎት ሊያሳካ የሚችል ጠንካራ ተቋም መገንባት እንደሚገባ ያመለክታሉ፡፡ ኮሚሽኑ በፌዴራል ደረጃ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ፤ በክልል ደግሞ ለርዕሰ መስተዳድሮች መሆን እንዳለበት ይገልጻሉ።
የትግራይ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ዘርፍ ተተኪ ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ሃዲሽ፤ ባህልና ቱሪዝም ከስፖርት ኮሚሽን ጋር መተቃቀፍ አግባብ አለመሆኑን ይስማሙበታል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ባህልና ቱሪዝም ራሱን የቻለ ግዙፍ ተቋምና በርካታ ሃላፊነቶች ያሉበት ነው። በሚፈለገው ልክ ካልተሰራባቸውና በሚገባ ተጠቃሚ መሆን ካልተቻለባቸው ዘርፎች መካከል አንዱ ይህ ተቋም ነው። በራሱ በርካታ ስራዎችን መስራት በሚጠበቅበት ተቋም ላይ ስፖርቱ መደረብም አግባብ አይደለም።
‹‹በአሁኑ የስፖርቱ አደረጃጀት መዋቅር የባህልና ቱሪዝም ድጋፍ ሰጪነት አያስፈልግም ባይባልም የኮሚሽኑን ሃላፊነት እንዳይጋፋ መጠንቀቅ ግን እንደሚገባ የሚናገሩት አቶ ኪሮስ፤ በሚኒስቴሩ መስሪያ ቤቱና በኮሚሽኑ መካከል የስራ ጣልቃ ገብነት እንደሚስተዋል ይጠቅሳሉ።
ጣልቃ ገብነቶችን ለማስቀረትና ህዝቡን ከስፖርቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ከተፈለገ ዘርፉን በሚኒስቴር ደረጃ መዋቀርና ቀጥታ ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ በመግለጽ የኮሚሽነር ባዘዘውን ሃሳብ ያጠናክራሉ፡፡
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ትርፉ ፣ የ«ስፖርቱ ዘርፍ አደረጃጃት በአግባቡ ተጠንቶ አንድ ቦታ እንዲቆም አልተደረግገም›› ይላሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንኳን ለ12 ጊዜያት ከሌሎች ተቋማት ጋር ተጋብቶ ተፋቷል ይላሉ።
በአሁኑ ወቅትም የስፖርት ዘርፉ ከባህልና ቱሪዝም ጋር በመጋባቱ ገና ከጅምሩ ጉራማይሌ የሆኑ አሰራራሮች እያስመለከተ፤ ተጠሪነት በሚል ስም ጣልቃ ገብነት እየተስተዋለ በርካታ ወገኖችም ስጋታቸውን እየገለፁ መሆናቸውን የሚጠቁሙት አቶ ዳዊት፤ይህም ተጠያቂነት እንዳይኖር ያደርጋል ነው የሚሉት፡፡ አዋጭ ባለመሆኑም ሊስተካከል እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።
እንደ አቶ ዳዊት ገለፃ፤ ስፖርት ትልቅ ተቋም ነው። ፖሊሲውም ስፖርቱ ህዝባዊ እንዲሆን ነው የተቀረጸው። ህዝባዊ ከሚያደርጉት አሰራሮች አንዱ የስፖርት ምክር ቤት ነው። ይህን ምክር ቤት የሚሰበስብው እንደ ክልል ፕሬዚዳንቱ፤ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደግሞ ከንቲባው ናቸው።
የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን አሳማኝ ባልሆነ መንገድ፤ ተጠሪነቱ ለወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ሆኗል። የሚሉት አቶ ዳዊት፣ ይህን አይነት አደረጃጀት ሲዋቀር ባለሙያዎች እንዲወያዩበት አለመደረጉን ይናገራሉ፡፡ ወደ ህዝቡ እንዳልወረደም፤ መድረኮች እንዳልተፈጠሩለት፣ በርካታ ወገኖች ሃሳብ እንዳልሰጡበትም ያብራራሉ።
ይህን ችግር ለመፍታት ተገቢና አፋጣኝ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ የሚያሰምሩበት አቶ ዳዊት፤ችግሮች ከመስፋታቸው በፊት ባለሙያዎችን ባሳተፈ መልኩ ውይይት ማድረግና መስተካከል የሚገባቸውን ሁሉ እያስተካከሉ መጓዝ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ።
የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የ2011 በጀት ዓመት የስፖርት ዘርፍ የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማውን በአዳማ ከተማ ባካሄደበት ወቅትም የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር እርስቱ ይርዳው፤ የተቋማት አደረጃጀት ችግር የሚስተዋለው በስፖርቱ ዘርፍ ብቻ እንዳልሆነ ገልጸዋል፤ ችግሩ በሌሎች ዘርፎችም እንደሚስተዋል ጠቅሰው፣ ወጥ የሆነ መፍትሄ እስኪሚገኝ ችግሮቹን በውይይት መፍታትን እንደ አማራጭ መጠቀም እንደሚገባ አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011
በታምራት ተስፋዬ