የአምቦ ከተማ ነዋሪ ብቻ አይደሉም።አስታራቂ፣ ሸምጋይና ለብዙዎች አባት ናቸው።አምቦ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ዘልቀውም ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ልጆችን በማህበረሰቡ ተወዳጅ እንዲሆኑ የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ።በተለይም ዩኒቨርሲቲው በተደጋጋሚ ችግሮች የሚፈጠሩበት ስለነበር ፈጥኖ በመድረስና ችግሩ እንዲረግብ አለያም እንዲደርቅ በማድረግ በኩል በአንደኝነት ከሚጠቀሱ አባገዳዎች መካከል ናቸው።ስለዚህም ብዙዎች ይወዷቸዋል፤ አከብሯቸዋልም።
እርሳቸው ካሉበት ነገሮች ይቀላሉ የሚባልላቸው አይነት ናቸውም።15 ልጆችን ወልደው ለወግ ማዕረግ ያበቁና በምሳሌነት የሚጠቀሱ ገበሬም ነጋዴም ሲሆኑ፤ በኢትዮጵያዊነት ስሜትና ባህል የሚኖሩ፣ ልጆቻቸውንም በዚያ ስሜት ያሳደጉና ቤታቸውን በብሔር ብሔረሰብ ያስዋቡ አባወራም እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።ምክንያቱም እርሳቸውና ባለቤታቸው ኦሮሞ ቢሆኑም ልጆቻቸው ግን ከተለያየ ብሔር የመጡ ልጆችን አግብተዋል።በዚህም እነርሱ ቤት ያልገባ ብሔረሰብ አለ ለማለት ያስቸግራል።ይህ ደግሞ ልጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን የልጅ ልጆቻቸው ጭምር ኢትዮጵያዊነትን እየቀመሱት፣ እያጣጣሙት እንዲያድጉ አግዟቸዋል።
ይህ እድገታቸውና መሪነታቸው ለብዙዎች ትምህርት ስለሚሆን ከአቶ ደላሳ ብሩካ የህይወት ተሞክሮ ልምድን ትቀስሙ ዘንድ ለዛሬ የ‹‹ ህይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋልና ተማሩባቸው።
ብቸኛው ልጅ
የተወለዱት ከዛሬ 76 ዓመት በፊት ሲሆን፤ ከአምቦ ስድስት ኪሎ ሜትር በምትርቀው ቱሉ ዲምቱ ቆቦ ቀበሌ ውስጥ ነው።ለቤተሰቡ ብቸኛ ልጅ ናቸው።በዚህም እንክብካቤውና ጥንቃቄው በዝቶላቸው ማደግ ችለዋል።የቤተሰቡ ሀብት ንብረትም ቢሆን ከእርሳቸው ውጪ አልሆነም።ለዚያውም አባት በህይወታቸው እያሉ ነበር ሁሉን ውርስ ያስረከቧቸው።ከዚያ እርሳቸው ቤተሰቡን እየተንከባከቡ መኖራቸውን ቀጠሉ። የራሳቸውን ኑሮ ሲመሰርቱ ደግሞ ሁለቱንም ቤት እያገዙ ደስተኛ ህይወታቸውን አጧጧፉት።
አባታቸው ብዙ ገበሬ ነበራቸው።ሆኖም ለልጃቸው መምህር ሆነው ነበር ያሳደጓቸው።በቤት ውስጥ እንደብቸኛ ልጅ ተቀላቢ ብቻ አላደረጓቸውም።ይልቁንም ሰርቶ መኖር እንዴት እንደሚቻል አሳይተዋቸዋል።ከገበሬዎቹ ሰራተኞቻቸው እኩልም ይለፋሉ።ለዚህ ደግሞ ምክንያቱም ሀብት ንብረት በቅጽበት ውስጥ ሊጠፋ እንደሚችል ያምናሉ።ስለዚህም ሩቅ አሳቢና አላሚ ሆነው እርሳቸው ህይወታቸውን የለወጡበትን ግብርና እና ንግድ በሚገባ አውቀውና ኖረውት እንዲያድጉ አድርገዋቸዋል።
የአቶ ደላሳ አባት ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ከእርሳቸው እኩል ሥራዎችን እንዲለምዱና የኑሮን ውጣውረድ እንዲያውቁትም አስተምረዋቸዋል።በተለይ የቤተሰብን ጥቅምና ማስተዳደርን እንዲረዱት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ነበር ድል ባለ ድግስ የዳርዋቸው።ይህ ደግሞ በራስ ሀይልና አቅም መቆም እንዴት እንደሚቻል በሚገባ አስተምሯቸዋል።
ባለታሪካችን በባህሪያቸው አትንኩኝ ባይ ሲሆኑ፤ ከነኳቸው ማንንም አይምሬ ናቸው።ነገር ግን ታዛዥና ሰውን ማገዝ የሚወዱም አይነት ልጅ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።ከሁሉም በላይ በዚህ እድሜያቸው መስማት የሚመቻቸው፣ ማንበብም የሚመስጣቸውና ስለአገራቸው ማወቅ የሚያስደስታቸውም ናቸው።ይህ ባህሪያቸው ደግሞ ከጓደኞቻቸው ይለያቸዋል።ሌላው ከአካባቢው ልጅ የሚለያቸው ባህሪ አዋውላቸው ነው።ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት ከልጆች ጋር ሳይሆን ከሽማግሌዎች ጋር ነው።ይህ ሁኔታ ደግሞ በስነምግባር ልዩ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።ጨዋና ከማንም ጋር የማይጣሉ፣ ነገሮችን በፍቅር የሚከውኑም እንዲሆኑ አግዟቸዋል።
ሌላው ታሪክን በማወቅ እርሳቸው ልዩ ናቸው።በባህል መኖርንም ከአባቶች እግር ስር ቁጭ ብሎ መማራቸው ያውቃሉና ይለያሉ።ከሽማግሌዎቹ የሚሰሙት ነገር ደግ ደጉን ብቻ በመሆኑም እርሳቸውም ደግ አሳቢ፣ ደግ ደጉን ብቻ አይ አድርጓቸዋልም።
ከልጆች ጋር እንዳይጋጩና ተከባብረው እንዲኖሩም እድል የሰጣቸውም ይህ ነው።ከዚህ በተጓዳኝ ተኩስ በልጅነታቸው ከለመዱ መካከል አንዱ መሆናቸው ይለያሉ።ለዚህ ልምድ ያበቃቸው ደግሞ ጓደኞቻቸው ሲያገቡ በሚዜነት ይመርጧቸው ነበርና እዚያ ሰርግ ላይ ጥይት መተኮስ በመሳተፋቸው ነው።አባታቸውም ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሰንጋ ፈረስና በወቅቱ ዘመናዊ የሚባለውን ሽጉጥ ገዝተውላቸው ነበርና እዚያ ላይ ይህንን ማድረግ ፍጹም ደስታ የሚፈጥርላቸው ሆኖላቸዋል።ከሌሎች እንዲለዩም አድርጓቸዋል።ይህ ልዩነታቸው ደግሞ የልጅነት ፍላጎታቸው እስከመሆን የደረሰ ነው።እንዲያውም እርሳቸው ሲገልጹት ዲሞትፎር በትከሻቸው፣ ሽጉጥ ደግሞ በወገባቸው ታጥቀው በሰንጋ ፈረስ ላይ ሆነው ጥምቀትና ሌሎች በዓላትን ማድመቅ ነው ይላሉ።
የማረሚያ ቤሩ ትምህርት ቤት
ከትምህርት ጋር የተተዋወቁት በዚያው በተወለዱበት አካባቢ በቄስ ትምህርት ነው።እስከ ዳዊት ድረስ ደግመዋል።የመሸምደድ አቅማቸውንም አጎልብተውበታል።የአብነት ትምህርት ቤቱ በተለይም የማንበብና ፊደላትን የማወቅ ብቃታቸውን በሚገባ የገነቡበት ቦታ ነው።ከዚያ አንደኛ ክፍልን ሳይማሩ ነው ወደ ሁለተኛ ክፍል የገቡት።የተማሩበት ትምህርት ቤት ደግሞ በአቅራቢያቸው ያለ ሳይሆን ራቅ ብለው በእግር ጭምር ተጉዘው የሚገኘው ሲሆን፤ አምቦ ማዕረገ ህይወት ትምህርት ቤት ይባላል።ስለዚህም በዚህ ትምህርት ቤት ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ክፍል መማር ችለዋል።
ቀጣዩን ትምህርት መከታተል ቢኖርባቸውም ይህ እንዳይሆን የሚያግድ አጋጣሚ ተፈጠረ።ኦነግ ተብለው ታሰሩ።እስራቸው ደግሞ አንድ ቦታ ላይ የተወሰነ አልነበረም።ከአዲስ አበባ ውጪና አዲስ አበባ ውስጥ እያሉ ነው ያንከራተቷቸው።በዚህም ቋሚ ትምህርታቸውን መቀጠል አልቻሉም።የተስተካከለ ለመማር የሚያስችል ሁኔታም አልነበረም።ስለሆነም ትምህርት ሳይቀጥሉ ዓመታት አለፉ።ለመቀጠል ሲነሱ ደግሞ አንድ ክፍል ወደኋላ እንዲመጡ ታዘዙ።ተስፋ መቁረጥ በእርሳቸው ዘንድ የለም ነበርና ነገሩን በጸጋ ተቀበሉት።ዳግም ከአራተኛ ክፍልም ትምህርቱን ጀመሩ።
የትምህርት እድሉን ያገኙት ከስምንት በላይ ማረሚያ ቤቶችን ከተዘዋወሩና ብዙ ከተሰቃዩ በኋላ ነው።ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የመጨረሻው ማረፊያቸው በመሆኑም እፎይታን ሰጥቷቸዋል።ትምህርታቸውንም እንዲጀምሩ ሆነዋል።በቃሊቲ ማረሚያ ቤትም እስከ ስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን መማር ችለዋል።በትምህርት ቤቱ ብዙ ነገሮቻቸው የሚሸፈኑት መንግስት ነው።ስለዚህም ምንም አልጎደለባቸውም።የናፈቁትን ትምህርትም እንዲማሩ ሆነዋል።ነገር ግን የልጆቻቸውና የሚስታቸው ነገር እረፍት ይነሳቸዋል።15 ልጆችን ብቻቸውን መመገብና ማስተዳደር እንዲሁም ማስተማር ፈተና እንደሚሆናቸው ያውቃሉና በጣም ተጨንቀው ነበር ዓመታት ያለፉት። በዚህም ጉብዝናቸውን በሚገባ እንዲጠቀሙበት እንዳደረጋቸው ያስታውሳሉ።
ከዚህ ቀደም በነበራቸው የትምህርት ቆይታ የደረጃ ተማሪ እንደነበሩ የሚያነሱት ባለታሪካችን፤ በተለይም ከክፍል ክፍል በመዘዋወር ደብል እየመቱ ያልተማሩባቸው ክፍሎችም እንደነበሩ ይናገራሉ።የማስታወስ ችሎታቸውም ዛሬ ጭምር እንዳለ ያስረዳሉ።ለዚህም በአብነት የሚያነሱት ከዛሬ 60 ዓመት በፊት ያጠኑትን ዳዊት ዛሬም አለመርሳታቸውን ነው።ነገር ግን ለእስር ከተዳረጉ በኋላ የመማር ቅስማቸው ተሰበረ።የቤተሰባቸው ጉዳይም ቦታውን ያዘባቸው።ይህንን ሁሉ ቤተሰብ መመገብና ማስተማሩ ለባለቤታቸው ብቻ መተው እጅጉን አሳቀቃቸው።በዚህም ከሰባት ዓመት ከስምንት ወር እስር በኋላ ከማረሚያ ቤት ልክ እንደወጡ ትምህርታቸውን አቋርጠው ለቤተሰባቸው ወደ መስራቱ ገቡ።ይህ ደግሞ በቁጭት ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ አድርጓቸዋል።ያሰቡት ላይም ሳይደርሱ እንዳያቋርጡ ይደግፏቸዋል።
ለእንግዳችን የትምህርት ማቋረጥ ሌላው ምክንያት ከእስር ሲፈቱ 56 ዓመታቸው መሆኑ ነው።እናም በእስተእርጅና ተምሬ ዳጎስ ያለ ገንዘብ አገኛለሁ ብለው አለማመናቸው እንዳይቀጥሉት አድርጓቸዋል።በእርግጥ እርሳቸው አንድ ነገር ያምናሉ።ትምህርት እድሜ አይገድበውም ብለው።እንዲያውም በእስተርጅና መረጋጋትና መሰብሰብ ስለሚመጣ የተሻለ ተማሪ የሚኮንበት ነው ይላሉ።ይህ ቢሆንም ግን በዚያ ሁኔታ እርሳቸውን ትምህርታቸውን እንዳይቀጥሉ ያደረጋቸው የቤተሰባቸው ጉዳይ እንደሆነ ያወሳሉ።ልጆቻቸው በእርሳቸው እንዳይሸማቀቁ ይሰጋሉ።በዚህም ምንም እንኳን ወደዘጠነኛ ክፍል በጥሩ ውጤት ማለፋቸው ቢረጋገጥም ከእድሜ እኩዮቻቸው ጋር ስላልሆነ የሚማሩት መቀጠሉን አልፈለጉትም።ስለዚህም ቁጭቴን በልጆቼ ሲሉ አቆሙት።
እንግዳችን ‹‹ሁኔታው አስከፊና ስቃይ የበዛበት፣ ባልነበርኩበት የተከሰስኩበት፤ ልጆቼን ጭምር ያሰቀቀና ያሰቃየ ቢሆንም ማረሚያ ቤት የቀለም ትምህርት ቤት ብቻ እንዳልሆነ አይቼበታለሁ።የህይወት ትምህርትም የሚገኝበት እንደሆነ አረጋግጫለሁ።ለሌሎች መኖርንም ተምሬበታለሁ።ከሌሎች ጋር እንዴት በፍቅር መቆየት እንደሚቻልም መምህር ሳይቀጠር ትምህርት ያስቀሰመኝ ይህ ቦታ ነው።በተለይም ነጻ ነህ ተብዬ ስለቀቅ ያላግባብ መታሰሬና መንገላታቴ ቢያናድደኝም ይቅርታ ማድረግን ግን አስተምሮኛል፤ መተውን ገንዘቤ እንዳደርግም አስችሎኛል›› ይላሉ ቆይታቸውን ሲያስታውሱት።ከዚህ በመነሳትም መማር በትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን በችግርም እንደሆነም ያስረዳሉ።
የአባት ሥራ ለልጅ
የመጀመሪያ ሥራቸው በመሬት ላራሹ ጊዜ የሰሩት ሲሆን፤ በአካባቢው መጻፍ የሚችልና ጎበዝ የማስተዳደር አቅም ያለው ሰው ሲፈለግ እርሳቸው ተገኙ።በዚህም የቱሉዲምቱ ቆቦ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠው እንዲሰሩ ሆኑ።ለአራት ወር ያህልም በሥራው ላይ አገለገሉ።ከዚያ በኋላ ደግሞ የሚጽፍ ሰው በመታጣቱ በቦታቸው ሌላ ሰው ተክተው ወደ ወረዳ አዛወሯቸው።አምቦ ወረዳ ላይም የወረዳው ገበሬ ማህበር ጸሐፊ ሆነው ለዓመት ከመንፈቅ ያህል ሰሩ።
ሥራቸው ውጤታማ መሆኑ ሲታይ ደግሞ የአውራጃው ማለትም የጅባክና ሜጫ አውራጃ የገበሬዎች ማህበር ዋና ጸሐፊ እንዲሆኑ ተወሰነ።በዚህ ቦታ ላይም ከስድስት ዓመት በላይ መስራት ቻሉ።ይሁንና በዚህ መቆየት ለእርሳቸው ምቾት አልሰጣቸውም።ምክንያቱም አገልጋዩነቱ ሙሉ በሚባል ደረጃ ወደ ፖለቲካ ተቀየረ።አገልጋይነትም ቅጡን አጣ።ህዝብ ሳይሆን በወቅቱ የነበሩ ባለስልጣናት ብቻ የሚጠቀሙበት ሁኔታ ተፈጠረ።ስለዚህም እኔ ማገልገል የምፈልገው ህዝብን እንጂ ባለስልጣንን አይደለም ሲሉ ሥራቸውን አቆሙ።ይህ ደግሞ ስድብ የሆነባቸው ብዙ አመራሮች ነበሩና ኦነግ ነው በማለት እንዲታሰሩ አደረጓቸው።በዚህ ችግር ምክንያት ፍርድ ቤት እንኳን ለመቅረብ በብዙ ፈተና እንደነበር አይረሱትም።ግርፋቱና የነበረው ስቃይ ከአንዱ ማረሚያ ቤት ወደአንዱ መዘዋወሩና መንገላታቱም በቃላት የሚገልጹት እንዳይደለ ይናገራሉ።ማውራትም የማይፈልጉት ጉዳይ እንደሆነ አጫውተውናል።
ከሥራ ጋር ዳግም የተገናኙት ከእስር በኋላ ሲሆን፤ ከአባታቸው የወረሱትን ሥራ በመስራት ቀጥለውታል።ሁለቱም ማለትም አባትና ልጅ ነጋዴ ነበሩ።የንግድ ሁኔታቸው ግን የተለያየ ነው።አባት የጣቃ ነጋዴ ሲሆኑ፤ እርሳቸው ደግሞ ቤት ሰርተው ሆቴል በመክፈት ነው ወደ ንግዱ አለም የተቀላቀሉት።ከዚህ በተጓዳኝ የእርሻ መሬትም አላቸውና ገዝተው ሳይቀር እያረሱ ወደድ ሲል ይሸጣሉ። ይህም የንግዱ አካል አንዱ ሆኖላቸው የገቢ ምንጫቸውን ያገኛሉ።
አቶ ደላሳ እንደአባታቸው ጠንካራ ገበሬ የነበሩ ሲሆን፤ ልጆቻቸውን ጭምር በማሰለፍ ይሰሩ ነበር።ይህ ደግሞ ቤቱ እንዲሞላና እህል ገዝተው እንዳይመገቡ አድርጓቸዋል።ተርፎም ለሌላ ሥራ የገቢ ምንጭ እንዲሆን አግዟቸዋል።አሁንም ቢሆን በሆቴሉ፣ በግብርናውና ቤት ሰርተው በሚያገኙት ገቢ ይተዳደራሉ።በእርግጥ ቀደም ሲል ልጆቹም ተምረው የራሳቸውን ኑሮ እስኪጀምሩ ድረስ ያግዟቸው ነበር።አሁን ግን ማንም ቤት ውስጥ ባለመኖሩ የሚያግዛቸው የለም።እርሳቸው ደግሞ አቅማቸው ደክሟልና ማረስ አይችሉም።ስለዚህም እኩል እንዲያርሱላቸው በመስጠት ገቢያቸውን ያገኛሉ።እንደቀደመውም ብዙ የሚያስተዳድሩት ልጅ ስለሌላቸው አይቸገሩም።በዚያ ላይ ልጆቻቸው ስለሚያግዟቸው ቤታቸው ሙሉና ደስተኛ ሆነው ነው የሚኖሩት።
አቶ ደላሳ ከዚህ በተጓዳኝ አገርን ማገልገልም ሥራ ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው።በዚህም በእስተርጅናቸው የአካባቢውን ነዋሪ በማስታረቅ፤ በማስተሳሰር የሽምግልና አገልግሎትን ይሰጣሉ።በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሳይቀር አባ ገዳ ሆነው ያገለግላሉ።በዚህ ሥራ ከከተማ ውጪ በመውጣት ጭምር ይሰራሉ።ይህ ደግሞ የደስታቸው ምንጭ እንደሆነላቸውና ከሁሉም በላይ በዚህ ሥራቸው በረከት እንዳገኙበት ነግረውናል።
ሽምግልና በእርሳቸው ዓይን
ሽምግልናን የሚያነሱት በልጅነታቸው ሽማግሌዎች ከሚሉት ንግግርና ተግባር በመነሳት ነው።ይህም ‹‹ብቻዬን ወጥቼ ሁለት ሆኜ ከመግባት አድነኝ›› ብለው መጸለያቸው ነው።ይህንን ያሉበት ምክንያት ደግሞ ከሀቅ ውጪ ሌላኛውን አስቀይመው እንዳይገቡ፤ እውነቱን እንዲፈርዱ በማሰብ የሚለምኑት ነው።እናም ሽምግልና ለሌሎች መጨነቅ፣ እውነት እንዲሰፍን ማድረግ፣ ትውልዱን በእውነት መስራት የሚያስችል የብስለትና የትምህርት መጨረሻ ማዕረግ ነው ይሉታል።ቀጥለውም ሽምግልና ለመንጋው የሚያደርገውን እንክብካቤ ሁሉ እንደሚመለከት ይናገራሉ።
እንደእርሳቸው አባባል ሽምግልና መመገብን፣ ፊት ፊት በመሄድ መንገዱን እያሳየና እየቀደመ መምራትን፣ የደከመውን ማበርታትን፣ የታመመውን ማከምን፣ የተሰበረውን መጠገንን፣ የባዘነውንና ግራ የተጋባውን መመለስን፣ የጠፋውን መፈለግን፣ ከክፉ ነገርና ከአደጋ መንጋውን መጠበቅንና ለመንጋው ደህንነት የሚደረግን ማንኛውንም አይነት እንክብካቤና የሚከፈልን መስዋዕትን (ነፍስን እስከ መስጠት) ሁሉ መክፈልን የሚጠይቅ ክብር ነው ባይ ናቸው።
ሽምግልና በእድሜ መግፋት ብቻ የሚለካ አይደለም። ከዚያም ይልቃል።ከአመራረጣቸው ጀምሮ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው መንገድ ነው።በዚህም በእድሜ ጠና ማለት አንዱ መለያው ነው። በአስተሳሰብ መብሰል፣ በአካሄዳቸውና በህይወት በጎ ምሳሌ መሆን፣ ለሚያስታርቁት ሁለቱንም አካል ሊጠቅም የሚችል ውሳኔ የሚያስተላልፉ መሆኑም እንዲሁ መሰረታዊ ባህሪው ነው። ስለዚህም ሽምግልና የእድገት፣ የመቻል፣ የማስተዋል፣ የመሪነት ብስለት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ሽምግልና ብቻ የሚገለገልበት ሙያና ስም አይደለም። ብዙዎችን የሚያቅፍና ልዩ ልዩ አስተሳሰቦች ያሉበት ግልጋሎት እንደሆነ የሚያነሱት አቶ ደላሳ፤ ሽምግልና መልካም በሆነው ሁሉ መንጋውን መቅደምና ማስተማርም ነው። በዚህም ሰብሰብ ብለው ያሉትና ውሳኔ የሚያስተላልፉት ሰዎች በሕይወታቸው ይህንን እያስተማሩ የሚጓዙ ናቸው። ለዚህ ደግሞ የህዝቡን ሁኔታ ማወቅ ግዴታ አለባቸው። ምክንያቱም እያንዳንዱ ተግባራቸው የሚወሰነውና ሀቁ የሚወጣው በአካባቢው አኗኗርና ባህል ሲቃኝ ብቻ ነው። ስለዚህም እንደ አባትነታቸው በጸሎት፣ በስልጣን፣ በልባቸው፣ በዓይንና በህይወታቸው እንዲሁም በአዕምሯቸው አገልጋይነታቸውን ማሳየት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ቤተሰብ
ከባለቤታቸው ጋር የተገናኙት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እያሉ ነው።በቤተሰብ ጉትጎታና ምርጫም ነው ያገቧቸው።እርሳቸው በአካባቢው ዘንድ ትልቅ ክብር የሚሰጣቸው በመሆናቸው የሚመጥናቸው ተፈልጎም ነው እንዲያገቡ የተደረጉት።የቤተሰብም ቢሆን
የተሻለ ምርጫ ላይ ጥሏቸዋልና ከትዳር አጋራቸው 15 ልጆችን ማፍራት ችለዋል።አንድ የነበሩት ብዝሀ ዘርም አድርጓቸዋል።ይህንንም የቤተሰብ ምርቃት የሰጠን ነው ይላሉ።በተለይም አሁን ቅድመ አያት መሆናቸውን ሲመለከቱ ‹‹ለአምላክ የሚሳነው ነገር የለም።አንድ ሆኜ ተፈጥሬ እንድበዛና ደስታዬን እንዳጣጥም እድል ሰጥቶኛል›› ይላሉ።በቤተሰባዊ ህይወታቸውም ደስተኛ የሆኑት ከዚህ የተነሳ እንደሆነ ይናገራሉ።
ለእርሳቸው ቤተሰብ ከወለዷቸው ልጆችም በላይ ነው።ምክንያቱም የልጆቻቸው ሚስቶችና ባሎች እነርሱን አባዬና እማዬ ነው የሚሏቸው።የፈለጉትንም ከእነርሱ እኩል እየጠየቁ ነው የሚኖሩት።በእርግጥ የእነርሱ ተወዳጅነት በጋብቻ የተዛመዳቸውንም ብቻ እንዳልሆነ የአካባቢውን ልጆች ማየትና ሲጠሯቸው መስማት በቂ ነው።እንደአማቾቻቸው ሁሉ እነርሱም አባዬ እማዬ እያሉ ነው የሚጠሯቸው።ይህ ደግሞ ምን ያህል ተወዳጅ እንደሆኑ በግልጽ ያሳየናል።የአካባቢው አስታራቂና አስተማሪ ያደረጋቸውም ይህ ባህሪያቸው እንደሆነ ያስታውቃል።
እንግዳችን ከሰፈር ያለፈ ሥራም ነው የሚሰሩት።ትንሿ ኢትዮጵያ ትገኝበታለች በሚባለው ዩኒቨርሲቲ ውስጥም ይህንኑ ተግባራቸውን ያከናውናሉ።በተለይም ጸብ ሲፈጠር እርሳቸው ካልመጡ አይቆምም ነው የሚባለው።ምክራቸው ልብ የሚያስገዛ ነው።ነገሮችን ቆም ብለው እንዲያዩም ያደርጋል።እንቢ፣ አይሆንም የሚላቸው ባለመኖሩም ሽምግልናን በደንብ የተላበሱ ናቸው ያስብላቸዋል።እንደ አምቦ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች መልካቸው እንዲቀየር ያደረጉም ለመሆናቸው ብዙዎች ምስክርነታቸውን ይሰጡላቸዋል።ምክንያቱም እንደሳቸው ያሉ የአገር ሽማግሌዎች በመሰባሰብ ከሌላ ቦታ የመጡ ተማሪዎችን ምንም እንዳይነካቸው ይከላከላሉ።ባዕድነት እንዳይሰማቸውም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ።
አቶ ደላሳ የቤቱ ብቻ ሳይሆን የአካባቢው ብሎም በዩኒቨርሲቲ የሚኖረው ማህበረሰብ መምህር፣ አስታራቂና መካሪ ዘካሪ ናቸው።አለፍ ብለውም እስከ አገር ድረስ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚታትሩ የአገር ሽማግሌም ናቸው። በዚህም ቤታቸው ሳይሆን የሚውሉት አንድም ሰፈር ውስጥ አለያም ከከተማ ወጥተው እነዚህን ተግባራት ሲከውኑ ነው።በዚህ ሥራቸው ደግሞ ሁሉም ሰው ይወዳቸዋል፤ ይኮራባቸዋልም። በተለይ ልጆቻቸው በእርሳቸው ፍጹማዊ ቅናት ይይዛቸዋል። እርሳቸውን መሆንንም ይመኛሉ።በባህሪ ብዙዎቹም እንደሚመስሏቸው ነገርውናል።
ቤተሰብን አናጺ አባትና እናት ነው።በአስተዳደግ ባህሉን አክባሪ፣ አገሩን ወዳድና በእውቀት የጎለበተ ካላደረገው ከአደገ በኋላ መስበር እንጂ ማቃናት አይቻልም። ስለዚህም በመሆን፤ በማሳየትና እንዲሆኑት በመገፋፋት ልጆቼን ኢትዮጵያዊ አድርጌያለሁ የሚሉት አቶ ደላሳ፤ አሁን ያላቸው ቤተሰብ በብሔር ብሔረሰብ የተሞላ መሆኑን አጫውተውናል።ለምን የዚህ ብሔር አገባችሁ ማንም አይላቸውም።ይህ ደግሞ ቤተሰቡ የሌላውን ባህል ጭምር ለመኖርና ለማወቅ እንዲጥርና እንዲፋቀር እንዳደረገውም ነግረውናል።
መልዕክት
አገር በተለይ ከሽማግሌዎች ብዙ ነገር ትጠብቃለች።በእነርሱ ተግሳጽ ወጣቶች ተመልሰው፣ አገራቸውን አልምተው፣ እነርሱም ተለውጠው ማየት ትሻለች።በእነርሱ አርአያነት የቀደመ ባህልና ታሪኳን መመለስም ትፈልጋለች።ስለሆነም ሽማግሌዎች መካሪ ፣ዘካሪ መሆን አለብን።ለወጣቱ መንገድን ማሳየትም ይጠበቅብናል።እኛ ባለመስራታችን ትውልዱ የፈለግነው ላይ መድረስ አልቻለም።አገሩን ከጠላት ለመመከትም ዝግጁ አልሆነም።አሁን ማንቃት ስንጀምርና ሁኔታዎችን ሲያይ ነው መስመሩ ውስጥ የገባው።ስለዚህም ለአገር የሚበጀውን ሁሉ ማድረግ የዛሬ ሥራችንና ግዴታችን መሆን ይኖርበታል ብለዋል።
ከድጋፍ ጋር በተያያዘም ያሉት ነገር አለ።መስማማትና ፍቅር ኖሮ ቢሆን ኖሮ ይህ ባልተፈጠረ ነበር።ከቤት ንብረታቸው ባልተፈናቀሉም።ነገር ግን ተንኮልና ክፋት ስላለ ይህ ሆኗል።ባላሰብነውና መሆን በሌለበት መልኩ ችግሩ ተፈጥሯል።ስለዚህም ወደመፍትሄው መምጣት ከተጨማሪ ችግር ያድነናል።እናም የእኔ ብሔርና ወገን ሳንል ማገዙ ላይ መረባረብ አለብን።እያንዳንዱ ጉዳት የደረሰበት ሰው የእኛው ዜጋ ነው።በሰውነትም ብንመጣ እኛን የሚመስልና በሥላሴ አርአያነት የተፈጠረ ነው።ስለዚህም እርሱን እያሰብን ካለበት ማቅ ውስጥ ማውጣት ይገባናል።
አሁን ያለንበት ጊዜ ሰው ሞቱን እያሰበ የሚሰራበት ላይ ነን።ሞት ሲታሰብ ደግሞ መዘጋጀትና መልካም መልካሙን መስራት ግድ ነው።ለዚህ ደግሞ መሰረት መጣል ያለብን በአንድነታችን ላይ ነው።አንድነት ሀይል፣ መለያየት ደግሞ ድህነት ነው።ምክንያቱም ስንለያይ የምናየው የግል ጥቅማችንን ብቻ ነው።ሌላውን መግፋት እንጀምራለን።ለማስቀየምም ቅርብ እንሆናለን።ይህ ደግሞ መልካም ነገሮች እንኳን ቢኖሩን ማንም እንዳያያቸው ይገርድብናል።በዚህም ከሌላው ብቻ ሳይሆን ከራሳችንም እንጣላለን።ስለሆነም አሁን የሚያዋጣንና ልንኖረው የሚገባው ጉዳይ በመተባበር ችግሮችን ማለፍ ብቻ ነው።በመተባበር አብሮ ማደግ ይመጣል።አገርንም ያሳድጋል።መጥፎውን ማየታችንም ያከትምለታል።ዓይናችን መልካሙን ብቻ እንዲያስተውል ይሆናልም።እናም አገራቸውን እንወዳለን የሚሉ ሁሉ ይህንን ያድርጉ መልዕክታቸው ነው።እኛም ይህንን እውነታ እውን አድርጉት ስንል ለዛሬ የያዝነውን አበቃን።ሰላም!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 16/2014