የአንዳንድ ሰዎች ታሪክ ተወለዱ፤ ሞቱ ብቻ ይሆናል፤ ምክንያቱ ደግሞ ምንም ዓይነት ስማቸው ሊጠራበት የሚችል
ስራ አለመስራታቸው ነው።
ከዚህ በተቃራኒው ያሉት ደግሞ ሌት ተቀን አውጥተውና አውርደው ተጨንቀውና ተጠበው በሰሩት ስራ በግላቸው ስኬትን ከመጎናጸፋቸው ስኬታቸው ከእነሱም ከአካባቢያቸውም አልፎ የሀገራቸውና የአለም ስኬት የሚሆንላቸው አሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ በአለም የሌለ ነገር በመስራት ስማቸውን ከፍ አርገው ለማስጠራት ይጥራሉ፡፡ የተሳካላቸውም የዓለም ድንቅ ስራ መዝገብ ውስጥ ይሰፍራሉ፡፡
ከወደ ፔሩ የተሰማው ዜና ሰዎች ስማቸውን ለማስጠራት ምን ያህል እንደሚጨነቁ ያመለክታል። ዩፒአይ የተሰኘው ድረ ገጽ ሰሞኑን ይዞት በወጣው ዘገባው እንዳስነበበው፤ 50 ሰዎች የተሳተፉበት ፣የማዘጋጀቱ ስራ ስድስት ወራትን የጠየቀው ጂንስ ሱሪ ተሰፍቶ ለእይታ ቀርቧል፡፡ የሱሪው ቁመትም 12 ፎቅ እንደሚያህል ተገልጿል፡፡
ጅንስ ሱሪውን የመስራት ሀሳብ ያመነጨው ባለቤትነቱ ሴንኮሲወድ የተባለው የፓሪስ የገበያ ማእከል ቅርንጫፍ ነው፡፡ ‹‹ካንሳስ›› የሚል የንግድ መለያ (ብራንድ) የተሰጠው ሱሪ አምራች ድርጅትም በስራው ተሳትፏል፡፡
የሀሳቡ አመንጪ«አንድ አስደናቂ ስራ ሰርቼ በዓለም ድንቅ ስራ መዝገብ ላይ ለመስፈር በጣም አስብ ነበር፤50 ሆነንም ለስድስት ወራት ያህል በስራው ላይ ቆይተናል፤ በመጨረሻም ለስኬት በቅተናል››ብሏል፡፡
ይህንን ልብስ ለማዘጋጀትም 6 ቶን የሚመዝን ጨርቃ ጨርቅ ጥቅም ላይ መዋሉንና ጅንስ ሱሪው 215 ጫማ ቁመትና 140 ጫማ ስፋት እንዳለው ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ጊነስም የአለም ትልቁ ጂንስ ሱሪ በማለት በድንቃድንቅ መዝገቡ አስፍሮታል፡፡ይህ የዓለማችን ትልቁ ጅንስ ሱሪ በፔሩ ሞል ላይ ተሰቅሎ ለእይታ እንደሚበቃም ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።
የሱሪው የመጨረሻ እጣ ፈንታ ደግሞ ሌላ ነው፡፡ ሱሪውን ወደ 10 ሺ ከረጢቶች ተቀይሮ በፓሪስ ሱፐር ማርኬት ቅርንጫፎች የፕላስቲክ ከረጢቶችን በመተካት አገልግሎት ላይ እንዲውል የሚደረግ መሆኑም ተገልጸል፡፡ በዚህም የፕላስቲክ ምርቶች ለገበያ ከረጢትነት እንዳይውሉ ማድረግ እንደሚገባ ለማስተማር ስራ እንደሚውልም ተጠቁሟል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011
በእፀገነት አክሊሉ