ከዛሬ 85 ዓመት በፊት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ልዩ ስሙ ገለብና ሀመር ባኮ እየተባለ በሚጠራው አውራጃ ነው የተወለዱት።የበኒ ብሄረሰብ መሪ ከሆኑ አባታቸው የተወለዱት እኚሁ ሰው እንደማንኛውም የበኒ ታዳጊ ከብት የማገድ ሃላፊነት ቢኖርባቸውም እረኝነቱን ይጠሉት ስለነበረ የሚጠብቋቸውን ከብቶች በመግደልና ጥሎ በመጥፋት እምቢተኝነታቸውን ያሳዩ ነበር።ከዚያ ይልቅም ለትምህርት ጥልቅ ፍቅር እንደነበራቸው ይናገራሉ። ይህንን የትምህርት ፍቅርቸውን እውን የሚያደርግ አጋጣሚ ተፈጠረ።
ይኸውም ደጅአዝማች አበበ አውራሪስ በአንድ ወቅት አካባቢያቸውን ለመጎብኘት የመጡበት ወቅት ያገኟቸውና ቤተሰብ ጠይቀው ለማሳደግ ይወስዷቸዋል።እናም በደጅአዝማች አበበ አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ መጥተው የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአስፋ ወሰንና ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተከታተሉ።በመቀጠልም በዲፕሎማ ማዕረግ በመምህርነት ተመረቁ፡፡
የዛሬው የዘመን እንግዳችን ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ተስፋ ኮከብ ትምህርት ቤት በአርበኞች እና በአማሃ ደስታ በመምህርነትና በርዕሰ መምህርነት አገልግለዋል።ከአገር ውስጥ በተጨማሪ ወደ ባህርማዶ አቅንተው ትምህርታቸውን የቀጠሉ ሲሆን በእንግሊዝ አገር ከሚገኘው ማንችስተር ዩኒቨርሲቲ በጎልማሶች ትምህርት ዘርፍ ዲፕሎማ ተመርቀዋል።ወደ ሀገራቸው ተመልሰው አገራቸውን በተማሩበት ዘርፍ ማገልገል እንደቀጠሉም ጀርመን የስልጠና እድል ያገኙና የፌደራል ስርዓት ላይ ልዩ ስልጠና ይወስዳሉ።ከዚህም ባሻገር የመምህራን ማህበር ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ስለነበሩም በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ሀገራቸውን በመወከል ተሳትፈዋል፡፡
እንግዳችን ፊትአውራሪ መኮንን ዶሪ የእድሜያቸውን እኩሌታ በተለያዩ የመንግስት ሃላፊነቶች ላይ ሃገራቸውን አገልግለዋል።ከእነዚህም መካከል በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በቀኝአዝማች ማዕረግ የገለብና ሃመር ባኮ አውራጃ ሀገረ ገዢ እንዲሁም ፊታውራሪ ሆነው ደግሞ በጋሞ ጎፋ ጠቅላይ ግዛት አውራጃ ገዢ ሆነው ሰርተዋል።እንዲሁም በአርሲ ጠቅላይ ግዛት የጭላሎ አውራጃ ገዢ ሆነው አስተዳድረዋል።
በ1967 ዓ.ም ከተካሄደው የመንግስት ለውጥ በኋላም እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ በጋሞ ጎፋ የማጂ አውራጃ አስተዳዳሪ ፣ የጨቦና ጉራጌ አስተዳዳሪ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ቤት ፣ የአምባሳደር ቲያትር ቤት እና የአምቦ ውሃ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ ሆነው ሰርተዋል።እኚህ ሰው ከሚታወቁባቸው ጉዳዮች መካከል ከመንግስታዊ ኃላፊነታቸው ባሻገር በኪነጥበባዊ ሥራዎችም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከታቸው ነው። ከፃፏቸው በርካታ መፅሃፎችና ቲያትሮች መካከልም ‹‹የእጮኛው ሚዜ››እና ‹‹ አይጥ ለሞቷ›› የተባሉ ቲያትሮቻቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የሽግግር መንግስት ሲቋቋምም የደቡብ ኦሞ ህዝብን በመወከል የምክር ቤት አባል መሆን የቻሉ ሲሆን በወቅቱ መንግስት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሆነውም ተሹመው ነበር።ሆኖም በሀገሪቱ ብሔራዊ እርቅ መደረግ አለበት የሚል አቋም ያራምዱ ስለነበርና ይህንንም አቋማቸውን በግልፅ ይናገሩ ስለነበር በአንዳንድ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ዘንድ ነቀፌታ ገጠማቸው።በዚህም ከምክር ቤቱም ሆነ ከመንግስት ሃላፊነታቸው ተባረሩ። ሆኖም ትግላቸውን ሃሳባቸውን ከሚጋሩ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ቀጠሉ።በአሜሪካ መንግስት አደራዳሪነት ተዘጋጅቶ በነበረው የውይይት መድረክ ላይ አቋማቸውን በይፋ መግለፃቸውን ተከትሎ ዳግም ከፍተኛ ማዕረግ ባላቸው የመንግስት ባለስልጣናት ጥርስ ተነከሰባቸው።
ፈተናቸው ግን በዚህ አላበቃም፤ ከአሜሪካው ስብሰባ ማግስት ሀገራቸው ሲመለሱ በቀጥታ ወደ ወህኒ ቤት ነበር የተላኩት።‹‹በዘር ማጥፋት ወንጀል›› ክስ ተመስርቶባቸው ያለአንዳች ፍርድ ለአስር ዓመታት ታሰሩና በነፃ ተለቀቁ።ከ15 ዓመታት የአሜሪካ ስደት በኋላ በሀገሪቱ የተፈጠረውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ ዳግም የሚወዷትን እናት ሀገራቸውን ምድር ለመርገጥ ቻሉ።በዚህም አልተወሰኑ፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የተወለዱበት ምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍል የሚያዋስኑትን ኬኒያና ደቡብ ሱዳን ህዝቦችን በጋራ የሚያስተሳስር በአይነቱ ልዩ የሆነ ፕሮጀክት ነድፈው በመንቀሳቀስ ላይ ነው የሚገኙት።የዚህ ፕሮጀክት እውን መሆን የቀጠናው ሀገራት ህዝቦች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማስቀረት፤ ብሎም በኢኮኖሚ ልማትና በቱሪዝም መስክ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያስችላል ተብሎ ይታመናል።አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከፊታውራሪ መኮንን ዶሪ ጋር በዚህና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረገውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይዞ ቀርቧል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የመምህራን ማህበርን በመወ ከል በውጭ ሀገር በተካሄደ ስብሰባ ላይ አንድ የተለየ ነገር አጋጥሞት እንደነበር ሰምቻለሁ። እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ያስታውሱንና ውይይታችንን እንጀምር?
ፊታውራሪ መኮንን፡– ልክ ነሽ፤ በዚያም ሆነ በሌሎች ሀገሬን ወክዬ በተሳተፍኩባቸው መድረኮች ሁሉ ፍሬያማ ስራዎች ሰርቼ ነው የመጣሁት። ፓሪስ ተካሂዶ በነበረው የመምህራን ጉባኤ ቀጣዩ ስብሰባ ኢትዮጵያ እንዲካሄድ ከፍተኛ የሆነ መከራከሪያ አቅርቤ ተሳታፊውን ሁሉ በማሳመን ስኬታማ ስራ ሰርቻለሁ። እናም ለመጀመሪያ ጊዜ የአለም መምህራን ማህበር ኢትዮጵያ ውስጥ መካሄድ የቻለው በእኔ ምክንያት ነው። በመቀጠል ኡጋንዳ ካምፓላ ላይ በተካሄደው ጉባኤ በተሳተፍኩበት ጊዜ የኢትዮጵያ ተራ ደርሶ ንግግር ካደረኩኝ በኋላ ጥያቄ ከተሳታፊዎች ለመቀበል በተዘጋጀሁበት ሰዓት አንድ ነጭ መልኬን አይቶ ‹‹አንተ በእርግጥ ኢትዮጵያዊ ነህ?›› የሚል ያልተጠበቀ ጥያቄ በተሳፊው ፊት ጠየቀኝ። ይህ ግለሰብ ይህንን ጥያቄ የጠየቀኝ በፊት ገፅታዬ ነው። በእርግጥ ጥያቄው በወቅቱ ቢያበሳጨኝም ሀገሬን የሚያሳጣ ነገር ግን አላደረኩም።
የሚገርምሽ ግን አስተዋዋቂው መጀመሪያም የኢትዮጵያ ተወካይ መሆኔን ተናግሮ ነበር ። ግን ይህ ግለሰብ ያንን እውነት መቀበል አልፈለገም። እኔ ግን ሀገሬን ሳላጋልጥ በአብዛኛው መድረክ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑት ትምህርት በስፋት የተዳረሰባቸው ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ ምሁራን መሆናቸውን ፤ በአሁኑ ወቅት ግን ትምህርት እየተዳረሰ በመምጣቱ ነው አንተ ዛሬ እኔን በዚህ መድረክ ያየኸኝ የሚል ምላሽ ሰጠሁት።
አዲስ ዘመን፡- ሌላው እርሶ ከሚታወቁባቸው ስራዎች አንዱ ‹‹አይጥ ለሞቷ›› የተሰኘው ቲያትር ነው። የዚህ ቲያትር ዋና ጭብጥ ታሪካዊ ጉዳይ እንዳለው ይነሳል። እስቲ ቲያትሩን የፃፉበት ምክንያትና አጠቃላይ ሁኔታ ምን እንደነበር ያጫውቱን?
ፊታውራሪ መኮንን፡- የዚህ ቲያትር ዋነኛ ይዘት በኤችአይቪ/ኤድስ በሽታ ላይ የሚያጠነጥን ነው። ይህ የሆነው እንግዲህ በደርግ ዘመን ገና ኤድስ በአለም ላይ በተከሰተበት ጊዜ ነበር። በወቅቱ በጤና ጥበቃ አስተባባሪነት ዶክተር አክሊሉ ሃብቴ የተባለ ሰው በዚህ ጉዳይ ላይ እንድፅፍ ጠይቆኝ ነው የፃፍኩት። በነገራችን ላይ ዛሬም ድረስ የኤድስ በሽታ አልተሸነፈም፤ ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ብዙ መስራት እንዳለብን ነው የማምነው። ከዚህም በሻገር በኮረና ቫይረስ ሌላ ስራ ለመስራት በዝግጅት ላይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ደግሞ በአዲስ ፕሮጀክት ብቅ ብለዋል። ስለዚህ ፕሮጀክት ዋነኛ አላማና ምንነት ያብራሩልኝ?
ፊታውራሪ መኮንን፡– ይህ ‹‹ያዮ›› የተሰኘው ፕሮጀክት በዋናነት ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ የታመነው የኦሞ ሸለቆ በሚያዋስናቸው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ ፣ ኡጋንዳና ደቡብ ሱዳን ነው። እነዚህ ህዝቦች ምንም እንኳን በቋንቋም ሆነ በባህል የሚያስተሳስሯቸው ጉዳዮች ቢኖሩም በተደጋጋሚ ግጭት ያለባቸው ሰላማዊ ግንኙነት የላቸውም። የእኔ ዋነኛ አላማም እነዚህን ህዝቦች የማስታረቅና ባህላቸው በአንድ ሙዚየም ውስጥ ተሰብስቦ የቱሪዝም መስህብ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር ነው። በነገራችን ላይ ለዚህ የባህል ማዕከል ግንባታ የሚሆን አምስት ሺ ካሬ የሚሆን መሬት በተወለድኩበት አካባቢ ተሰጥቶኛል።
አሁን እዚህ የመጣሁት ህዝቡ ለሰላም ብሎ በሰጠው መሬት ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሰረተ ድንጋይ እንዲያኖሩ ለመጠየቅ ነው። እርግጥ አሁን ባለው ሀገራዊ ሁኔታ ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማግኘት አልቻልኩም። ነገር ግን ከሰላም ሚኒስቴር አንዳንድ ሃላፊዎች ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ሰሞኑን ተወያይተናል። በእርግጥ መንግስትም ሆነ ህዝቡ በቀጠናው እውነተኛ ሰላምና ልማት እንዲመጣ ልባዊ ፍላጎት እንዳላቸው ተረድቻለሁ። ስለዚህ ፕሮጀክቱ እውን የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም ብዬ ነው የማምነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ በነበረው መንግስት በደል ቢደርስቦትም እድሜ ሳይገድብዎ ለተወለዱበት ሀገርና ህዝብ ዛሬም አለኝታነትዎን ለማረጋገጥ ዳግም ተመልሰዋል። እንደእርሶ በተለያዩ ምክንያት ከሀገራቸው ተሰደው ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምን መልዕክት አሎዎት?
ፊታውራሪ መኮንን፡-በነገራችን ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ መሄድ የጀመርኩት ከ50 ዓመታት በፊት ነው። በሄድኩኝ ቁጥር የማገኛቸው ዲያስፖራዎች ውስጥ ኢትዮጵያን የሚጠላ አላጋጠመኝም። ሁኔታው አስገድዶት ሃገሩን ጥሎ ከመሰደዱ በስተቀር ሀገሩን ከልቡ የሚወድ ነው። ታዋቂዋ ዘፋኝ አስቴር አወቀ በዘፈኗ ‹‹ሀገር ሀገር ይላል፣ ይሄ ሀገር ብርቁ፤ እኔም ሀገር አለኝ የሚታይ በሩቁ››… እንዳለችው አብዛኛው ዲያስፖራ በሰው ሃገር ምፃተኛ ሆኖ ተንቆና ተዋርዶ ቢኖርም ወደ ሀገሩ የመመለስና ህዝቡን የመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት አለው። ጥቂት የማይባሉ ሃገር ወዳድ ዜጎች ሀገራቸውን ለመለወጥ በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርጉም ሁኔታዎች አላሰራ ብሏቸው የተመለሱበት አጋጣሚ አለ።
በንጉሱ ጊዜ ግን ውጭ ሀገር በተለያየ ምክንያት የሄደ ሰው በምንም ምክንያት እዛ አይቀርም ነበር። ምክንያቱም የተሻለ ነፃነትና ሁኔታ ስለነበር ነው። ከዚያ በኋላ ግን የፖለቲካው ሁኔታ ዳግም ሀገር ለመመለስ ስጋት ፈጥሮ ቆይቷል። በእርግጥ አሁን ላይ የተሻለ ነፃነት አለ። ያም ቢሆን በሰሜን የሀገሪቱ አካባቢ የተፈጠረው ችግር እስካልተፈታ ድረስ አሁንም ለዲያስፖራው ስጋት መሆኑ አይቀሬ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ እኔ ፕሮጀክቴን ተግባራዊ ለማድረግ ባሰብኩበት አካባቢም ቢሆን የፀጥታ ችግር አልፎ አልፎ አለ። በፀጥታ ችግር ምክንያት በአካባቢው የተከፈቱ ኢንዱስትሪዎች ስራ የሚቋረጥበት ሁኔታ አለ። ይህ ችግር ከተወገደ ለአካባቢው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ እንሰራለን ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እርሶም እንዳሉት ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ምንም እንኳን ለልማት እና እድገት ምቹ ሁኔታና የተፈጥሮ ሃብት ቢኖራቸውም አሁን አሁን ዋነኛ የሽብርተኞች መፈልፈያ ስፍራ እየሆኑ እንደሆነ ይነሳል። ለመሆኑ የዚህ ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?
ፊታውራሪ መኮንን፡– ለእኔ የዚህ ሁሉ ምንጭ ብዬ የማስበው እነዚህ ሀገራት አብዛኛው በጎሳ አስተሳሰብ የሚተዳደሩ መሆናቸው ነው። ይህም ማለት አንዱ ጎሳ ከሌላው ለመሻል ሲል የሚፈጥረው ግጭት ነው ፀረ ሰላም ሃይሎች እንዲፈጠሩ እያደረገ ያለው። በመሰረቱ በሰለጠኑት ዓለማትም በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ያላቸው ሀገራት አሉ። ነገር ግን ግንኙነታቸው ዲሞክራሲያዊና በፈቃደኝነት እንዲሁም በእኩልነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ወደ ግጭት የሚያመሩበት ሁኔታ አይስተዋልም።
በተቃራኒው ወደ አፍሪካ ስትመጪ አንዱ በሌላ ላይ የበላይ ሆኖ የቆየበት ስርዓት በመኖሩ ሁልጊዜም ቢሆን ከዚያ የጭቆና ቀንበር ለመላቀቅ ሲባል ፍጅትና እልቂት ይከሰታል። ከዚህም ባሻገር የስልጣንና የጥቅም ግጭት አለ። ይሄ ችግር በምስራቅ አፍሪካ ጎልቶ ሚታይ ነው። ይሄ ችግር እንዲቆም ብዙ መሰራት አለበት። በነገራችን ላይ ጎሳ ያለና የሚኖር ጉዳይ ነው። ጎሰኝነት ግን ጊዜ አመጣሽና ከራስ ባሻገር ለሌሎች ያለማሰብ በራስ ዙሪያ ታጥሮ ከሌሎች ጋር በሰላም እንዳይኖር የማድረግ ችግር ያለበት ነው።
ሁሉም በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ሲኖረው ነው ሀገር የሚቀናው። እንደእኔ ገና ብዙ ስራ አለብን። አሁን ላይ ሁሉም በዚህ ጦርነት ላይ በአንድ መንፈስና በኢትዮጵያዊ አንድነት እየተሳተፈ ነው የሚገኘው። ይህ ለእኔ የሚያስደስተኝ ነገር ቢሆንም ከጦርነቱ በኋላ ደግሞ ቀድሞ ተዘርቶ የነበረው የልዩነት ዘር ምክንያት የርስ በርስ ግጭቱ እንዳያገረሽ ስጋት አለኝ። በመሆኑም ዋናው ድል የሚመጣው ከጦርነቱ በኋላ የህዝቡን አንድነት አስጠብቆ መቆየት ሲቻል ነው። በነገራችን ላይ ለግጭቱ መባባስ ዋነኛ ችግር ነው ብዬ የማምነው የአንቺ ባልደረቦች ነገሮችን አዛብተውና አጣመው ለህዝቡ ስለሚያቀርቡ ነው።
በተለይ ያልተማረው የህብረተሰብ ክፍል በጋዜጠኞች የሚቀርብለትን ነገር ሁሉ እውነት ስለሚመስለው ተቀብሎ በሰላም ለዘመናት ከኖረው ማህበረሰብ ጋር ሲጣላ ይስተዋላል። ስለዚህ እዚህ ላይ ጋዜጠኛውም በዚህ በኩል የራሱን የቤት ስራውን መስራት አለበት። በተለይም የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ተዛብቶ የቀረበለትና በዚያ አስተሳሰብ የቀረፀውን ወጣት ማንነት መቀየር ብዙ ጊዜ ይፈልጋል።
ስለዚህ የእኩልነት መጥፋት እና ምቀኝነት መኖሩ ነው ኢትዮጵያን የከፋፈላት። ያ እንዲቀር ማድረግ የምንችለው ስናወራ ብቻ ሳይሆን መሬት ላይ የወረደ ስራ ስንሰራ ነው። ለምሳሌ የእኔ ፕሮጀክት ተግባራዊ መሆን ከኢትዮጵያ አልፎ አጎራባች ሀገራት ህዝቦች መካከል ያሉ መቃቃሮችን ለመፍታት ያግዛል። እኔ ይህንን ፕሮጀክት የቀረፅኩት ከሌላው ሰው የተለየ ስለማስብ አይደለም፤ ነገር ግን ለተግባራዊነቱ ቆርጬ በመነሳቴ ነው።
አዲስ ዘመን- አንዳንድ ሰዎች ይህ ህገመንግስት እያለ ኢትየጵያዊ አንድነት ይመጣል ብሎ ማሰብ ዘበት እንደሆነ ያምናሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
ፊታውራሪ መኮንን፡– በነገራችን ላይ የጎሳ ምድር የጎሳ ነው። ይህንን ደግሞ ማመን ያስፈልጋል። ሀገር ግን የጋራችን ናት። ኢትዮጵያ የራሳችን ናት። ለምሳሌ ትግራይ ክልል የኢትዮጵያ አንዱ ክፍል ነው። ሆኖም በዋናነት በክልሉ የሚኖረው ህዝብ ምድር ነው። ሌላውም በተመሳሳይ መልኩ የመሬቱ ባለቤት ነው። ከዚሁ በላይ ግን ሁላችንን የምታቅፍ ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር አለችን። የጎሳ ምድር ይዘን ተከባብረን በኢትዮጵያዊነት በጋራ ለመኖር የሚከለክለን ነገር የለም። ኢትዮጵያ የሁላችን ሳለች አንዱ ‹‹የእኔ መሬት ነው›› ብሎ ለብቻ ገንጥሎ ለመውሰድ ቢፈልግ ፈፅሞ ተቀባይነት አይኖረውም።
አይደለም አንድ ሙሉ ክልልን ይቅርና ስንዝር መሬት ቆርሶ መውሰድ በህልም እንኳን አይታሰብም። ይልቁኑ የሚሻለው አብሮ እየኖሩ የተፈጠሩ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት መጣር ነው። የህዝቦችን እኩልነትና አንድነት እያጠናከሩ መሄዱ ነው ጠቃሚ የሚሆነው። ይህ የመገንጠል ሃሳብ ፈፅሞ ሊሆን እንደማይችልማ አሁን ላይ ያለው ጦርነት ጥሩ ማሳያ ነው። ይህ አሁን ላይ እንዲህ በህብረብሄራዊነት በዚህ ጦርነት ላይ እየተሳተፈ ያለው እኮ! የሀገሩን አንድነት ለማስቀጠል ነው። ያም ቢሆን ግን ጦርነት ችግሮችን ሁሉ ይፈታል ብዬ አላምንም። ከሃይል አማራጭ ይልቅ በጠረጴዛ ዙሪያ መምከሩ የተሻለ ነው።
አንቺ ከጠየቅሽው ጥያቄ አንፃርም አሁን ስራ ላይ ያለው ህገመንግስት እንደሚቀየር እምነት አለኝ። በነገራችን ላይ ህገ-መንግስት ከመፅደቁ በፊት የመገንጠል ሃሳብ ተነስቶ ውይይት ሲደረግበት እኔም ተሳትፌ ነበር። እኔ ከታሰርኩኝ በኋላ ነው ህገ-መንግስቱ የፀደቀው። ግን በውይይቱ ጊዜ የእኛ መረዳት የነበረው የዚያ አንቀፅ በህገ-መንግስቱ መካተት መከባበርን ያመጣል፤ መነቃቀፍን ያስወግዳል የሚል ነበር።
ምክንያቱም ሀገሩን የሚወድ ሰው ሌላውን መውደድ አለበት። ኦሮምያ ክልል ውስጥ ያለውን ጥቅም ወዶ ህዝቡን መጥላት አይኖርም የሚል እሳቤ ነበረን። ስለዚህ አንቀፅ 39 እንዳውም አንድነትን ያጠናክራል፤ መፈቃቀርን፣ መከባበርን ያመጣል በሚል መንፈስ ነው የተነጋገርነው። ነገር ግን በአፈፃፀም የታየው ከመከባበር ይልቅ መቃቃርን ነው የወለደው። በተለይም ሕወሓት መራሹ መንግስት የአንድ ጎሳ የበላይነትና ተጠቃሚነት በመላው ሃገሪቱ እንዲንሰራፋ በማድረጉ ምክንያት የህዝቦችን እኩልነት ማምጣት አልተቻለም። በአጠቃላይ ህገመንግስቱ ላይ ብዙዎቻችን ቅሬታ ስላለን መቀየር አለበት ብዬ ነው የማምነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ይህን ሲሉ እንደአንድ ባለድርሻ አካልና በወቅቱ እንደነበረ ሰው በህገ-መንግስቱ ላይ የነበረው መግባባት ወይም መተማመን ትክክል አልነበረም በሚል መንፈስ ነው?
ፊታውራሪ፡– በነገራችን ላይ በዚህ ህገመንግስት በተለይም አንቀፅ 39 አደገኛው ቃል መገንጠል ነው። ይሁንና ብሄር ብሄረሰቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው መወሰናቸው ትክክልና እኔም የምደግፈው ነው። ይህ መብት ደግሞ ከሰው የተሰጠ ሳይሆን ከፈጣሪ የተሰጠ ነው ብዬ ነው የምወስደው። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ይህንን የተቋጨውን፤ ደም የፈሰሰበትን፤ የሰው ልጅ ክቡር ህይወት ያለፈበትን ሀገር አንድነት አፈርሳለሁ፤ እገነጥላለሁ ብሎ ማለትም ይቻላል፤ ግን ፈፅሞ አይሳካም!።
ቀድሞም ቢሆን በአንቀፅ ደረጃ ይቀመጥ እንጂ ይህ አይነቱ አስተሳሰብ አልነበረም። እንደእኔ እምነት ወደፊትም ይህንን የሚያስብ ህዝብ አይኖርም። ይህ ማለት እኮ እኔን ሙሉ ሰው ያደረገኝ አንድ የሰውነቴን ክፍል ቆርጦ በመውሰድ ሁለት ማንነት እንደመስጠት ነው። ግን የተቆረጠውም የሰውነቴ ክፍል ሆነ ቀሪው አካሌ እንደቀደመው በጤንነት ሊቀጥሉ አይችሉም። ልክ እንደዚያ ሁሉ ትግራይ ያለኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያም ያለትግራይ መኖር አይቻላቸውም። በተለይ ደግሞ ለትግራይ ህዝብ ከቶ የሚቻል አይሆንም፤ የበለጠ ተጎጂ የሚሆነውም ያ ህዝብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ ይህንን ቢሉም የሕወሓት አሸባሪ ቡድን አመራሮች በቅርቡ በግብፅ ሚዲያ ላይ ቀርበው ‹‹ትግራይ›› የምትባል ሀገር ለመፍጠር የሚከፈለውን ሁሉ መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ ተናግረዋል። ከዚህ አንፃር የዚህን ፅንፈኛ ቡድን ምኞት ተግባራዊ የሚሆንበት እድል ይኖራል ተብሎ ይታመናል?
ፊታውራሪ መኮንን፡- በተደጋጋሚ እንዳልኩሽ እነሱ የፈለጉትን ቢሉም ይህ የመገንጠል ሃሳብ እውን ሊሆን የሚችልበት እድል የለም። ቀዳማዊ ኃይለስላሴ እንዳሉት ሃይማኖት የግል ነው፤ ሀገር የጋራ ነው። በጋራ ሀገር አንዱ ብቻውን የመወሰን ስልጣን የለውም። ሊያውም ጥቂት የትግራይ ሃይሎች ይህንን አሉ ተብሎ ሀገር አትፈርስም። ደግሞስ በእርግጥ የትግራይ ህዝብ ይህንን ይፈልጋልም ብዬ አላምንም። ምክንያቱም የኩሽ ስርወ-መንግስት የተመሰረተባት፤ አሁን ላለችው ኢትዮጵያ ዋነኛዋ ትግራይ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያን ያለትግራይ ማሰቡ ከባድ ነው። በመሰረቱ እኮ የትግራይ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለየ የተጎዳበት
ነባራዊ ሁኔታ ሳይኖር እንዴትስ ነው እንደተበደለ ለመገንጠል የሚያስበው። እንደእኔ እምነት እንዳውም ሕወሓት ሀገሪቱን በሚያስተዳድርበት ጊዜ የበለጠ ተጠቃሚ የሆኑት የዚህ ክልል ተወላጆች ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብትም በገፍ እየተዘረፈ ይሄድ የነበረውም ወደዚያ ክልል ነው። ሊያኮርፉም ሆነ ቅር ሊሰኙ ይገባ የነበረው 30 ዓመት ሙሉ ምንም አይነት የልማት ጮራ ያላዩት እነ ገለብና ቦዲ የመሳሳሉት ብሄረሰቦች ናቸው። እነዚህ ብሄረሰቦች አንድ ቀን ሰው ያገኘውን ልማት እናገኛለን ብለው በተስፋ ሀገራቸውን ዛሬም እንደጥንቱ የሚወዱ ለሀገራቸው ህልውና የሚቆሙ ናቸው። በአጠቃላይ ግን የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ወገኖች ጋር ለመለየት ፍላጎት አለው ብዬ ከቶ አላምንም። ደግሞም እንገንጠል ቢሉ የበለጠ ተጎጂ እንደሚሆኑ ያውቁታል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠረው ችግር በዋነኝነት የምዕራባውያንና የግብፅ መንግስት እጅ እንዳለበት ይታመናል። ከዚህም አንፃር በተለይም በዲፕሎማሲው ረገድ ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
ፊታውራሪ መኮንን፡- በነገራችን ላይ እዚህ ላይ አንድ ነገር ሊሰመርበት ይገባል ባይ ነኝ። ይኸውም የትኛውም ሀገር ቢሆን የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል የማያደርገው ነገር የማይምሰው ጉድጓድ አለመኖሩን ነው። ሁለት ተፃፃሪ ቡድኖች በሚኖሩበት ጊዜ ለሀገሬ የሚጠቅመው የትኛው ነው ብሎ አስቦ ነው በአንድ ሀገር ላይ እጁን የሚያስገባው። ይጠቅመኛል ለሚለው መንግስትም ሆነ ተቃዋሚ ሃይል በግልፅም ሆነ በስውር ከመደገፍ ወደኋላ አይልም። እኔ የውጭ ሃይሎች ለምን እንዲህ አደረጉ ብዬ አልወቅሳቸውም። ምክንያቱም ለሀገራቸው ጥቅም ቆመው መስራታቸው መብታቸው ነው። እኔ የምወቅሰው የራሳችንን መንግስትና ተቃዋሚ ሃይሎችን ነው።
ይህንን የምልሽ ከማንም ጎን ሆኜ ወይም ይጠቅመኛል ብዬ ተስፋ ያደረኩት አካል በመኖሩ አይደለም። የውጭ ሃይልን መቋቋምና ማስተማር የሚችለው የሃገሪቱ መንግስት ነው። በተለይም አሁን ያለው የዶክተር አብይ መንግስት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያሳየውን ጠንካራ አቋም በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚሞክሩት የውጭ ሃይሎች ላይ ሊደግም ይገባል የሚል እምነት አለኝ።
ሀገርን ለመገንጠል የሚሰሩ የውጭና የውስጥ ኃይሎች ጠንካራ አቋም መያዝና በተጨባጭ ያለንን ፅኑ መንፈስ ማሳየት ይገባናል። ይህ ደግሞ የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው። በተለይም የተማረው የህረተሰብ ክፍል ገንጣይ ሃይሎችን አፍ የማስያዝ ስራ በስፋት መስራት አለበት። ከዚህ ጋር ተያይዞ ለትግራይ ፖለቲከኞች የማስተላልፈው መልዕክት ለትግራይ ህዝብ ከዚህም በፊትም ሆነ አሁን የሚጠቅም ነገር እንዳልሰሩ ማመን እንደሚገባቸው እና አሁንም የበለጠ ችግር ውስጥ ለመክተት እየሰሩ ያሉትን ስራ እንዲያቆሙ ነው። ህዝቡም በህግ የሚፈለጉትን አጋልጦ መስጠት ይገባዋል። ይህም ማለት ያለፍትህ መፍረድ ማለቴ አይደለም። በአጠቃላይ አሁን ቢሆን በጠብመንጃ አፈሙዝ የሚመጣ ሰላም ባለመኖሩ ሁሉም ሃይሎች ወደ ውይይት ሊመጡ ይገባል ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ እርሶ እንደ ሀገር ወዳድ ዜጋ የኢትዮጵያን ገፅታ የሚያዋርዱ ተግባራትን እየፈፀሙ ላሉ አንዳንድ የትግራይ ዲያስፖራ አባላት የሚያስተላልፉት መልዕክት ምንድን ነው?
ፊታውራሪ መኮንን፡– አስቀድሜ እንዳልኩሽ እነዚህ ጥቂት ፅንፈኛ ሃይሎች የሚያራምዱት አቋም የትግራይ ህዝብ አቋም አለመሆኑን መገንዘብ ይገባል። ጥቂት የትግራይ ዲያስፖራዎች የፈለጉትን ቢሉም አይሳካላቸውም። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብም ሌላው ኢትዮጵያዊ ሀገሩ ሲፈርስ ዝም ብሎ አይቀመጥም። ምንም እንኳን ባለፉት ዓመታት እርስበርስ የመቃቃር ስሜቶች ቢፈጠሩም የኢትዮጵያን አንድነት በሚመለከት ሁሉም ተመሳሳይ አቋም ነው ያለው። በመሆኑም እነዚህ ጥቂት ዲያስፖራዎች ወደ ልቦናቸው ሊመለሱ ይገባል የሚል አቋም ነው ያለኝ። ይህ ማለት ግን ሁሉም የትግራይ ዲያስፖራ ተመሳሳይ አቋም አለው ማለት እንዳልሆነ ልብ መባል አለበት።
አዲስ ዘመን፡- አብዛኞቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራ መስራት እየሞከሩ ነው ያሉት። ይህ ግን ለምዕራባውያኑ ስጋት የፈጠረበት ሁኔታ አለ። ለመሆኑ ስጋታቸው ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
ፊታውራሪ መኮንን፡- እንደሚባለው ጠንካራ መሆን የምችለው በህብረት መስራት ስንችል ብቻ ነው። ሀገራቱ በዚህ ደረጃ በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ አብረው እየሰሩ መሆናቸው የሚደገፍና ህዝቦቻቸቸውን የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን ጠላቶቻቸውን በጋራ የመከላከል አቅም ያጎለብታሉ። ለዚህም እኮ ነው አፍሪካ ህብረትን ማቋቋም ያስፈለገው። ይህም ደግሞ የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር ለሚንቀሳቀሱ ሃይሎች በምንም መልኩ ምቾት ሊሰጣቸው እንደማይችል ግልፅ ነው።
በመሆኑም ሀገራቱ በሠላም ጉዳይም ሆነ በልማት በጋራ መስራታቸው የበለጠ ተጠቃሚ ስለሚያደርጋቸው አጠናክረው ሊቀጥሉበት ይገባል። ለዚህ ደግሞ እኔ እንደቀረፅኩት ዓይነት ሀገራትን የሚያስተሳስሩ ፕሮጀክቶችን መደገፍ ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ። በሌላ በኩል ግን ከኢትዮጵያ ተቃራኒ ሆኖ የቆመው የአሜሪካ መንግስት አሁን በያዘው አቋም ይቀጥላል ብዬ አላምንም። ብዙም ሳይርቅ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመተባበር እጁን ይሰጣል ብየም አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የሀገሪቱን ህልውና ለማስቀጠል መሰራት አለበት ብለው የሚያስቡትና ሊያስተልፉት የሚፈልጉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጦትና ውይይታችንን በዚሁ እናብቃ?
ፊታውራሪ መኮንን፡– እኔ በዋናነት መልዕክት ማስተላፍ የምፈልገው ለኢትዮጵያ ህዝብ ነው። ህዝቡ ሞኝ ሊሆን አይገባም። ደግሞም የጀግና ልጅ መሆኑን መዘንጋት አይገባውም። ባለብዙ ታሪክ ያላት ሃገር ባለቤት መሆኑንም ማስታወስ ይገባዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ሊበታትኑት ባደቡ የውጭና የውስጥ ሃይሎች ሴራ መታለል አይገባውም። ከምንም በላይ ከግል ጥቅም ይልቅ የሃገርን ጥቅም ማስቀደም ይገባዋል። እርግጥ ነው፤ አባቶቻችን ነፃነቷን ያስጠበቀች ድንቅ አገር ቢያስረክቡንም ችግር እንዳወረሱን የምንክደው አይደለም። እርስበርስ መናናቅ ነበረብን። በተለይም ባለፉት 30 ዓመታት መገፋፋትና ልዩነትን አጎልብተን ነው የቆየነው። በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከተነሳ ጦርነት ጋር ተያይዞ ግን የቀደም አንድነት እየተመለሰ ነው ያለው። በመሆኑም ይህንን አንድነት ማስቀጠል ይገባዋል የሚል ነው መልዕክቴ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ፊታውራሪ፡- እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2014