የጥልቅና የረጅም ታሪክ ባለቤቷ ኢትዮጵያ ብዙ የሚነገርላት እሴት እንዳላት ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ መካከል የሰው ዘር ሁሉ መነሻ መሆኗ ይጠቀሳል፡፡ የአፍሪካውያን የእኩልነትና የነፃነት ተምሳሌት መሆኗም ሌላው በከፍታ የሚጠቀስ ማንነቷ ነው፡፡
በየዘመኑ የነበሩት ኢትዮጵያውያን የሰሩት ታላላቅ ገድል የመኖራቸውን ያህል አገሪቱ ዛሬም ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለልማትና ለእኩልነት እጅ ለእጅ በመያያዝ ሌላ ገድል መድገም ግድ ከሚላት ዘመን ላይ ትገኛለች፡፡
በተለያዩ አቅጣጫዎች ብቅ ብቅ እያሉ የሚገኙት የጥላቻና የዘረኝነት አመለካከቶች አብበው ከማፍራታቸው በፊት ከስራቸው ሊነቀሉ ግድ ይላል፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚንፀባረቁ የእኔነት አስተሳሰቦች ጉዳታቸው በግለሰቡ ላይ አይቆምም፤ ባለበት ቀዬ ላይ ብቻም አይወሰንም፤ አገርም እንደ አገር እንዳይቀጥል ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡ ይህ አይነቱ አመለካከት የአንድነት፣ የሰላምና የፍቅርም ፀር ነውና ከወዲሁ መክሸፍ ይኖርበታል፡፡
አንድነት፣ ሰላምና ፍቅርን ለማስፈን የሚያስችሉ የማስፈጸሚያ ስልቶች በርካታ ናቸው፤ ከእዚህም መካከል የኢትዮጵያውያንን አንድነትንና ማንነትን አቆራኝቶ የያዘውን ታሪክ ማንሳት ይጠቀሳል፡፡ አገሪቱን ሊለያያት ከሚችለው ይልቅ አንድ የሚያደርጋትን ጉዳይ ማምጣቱ ለሚፈለገው ህብረት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ገጽታዋን ለመገንባት ከዚህ ቀደም ሉሲን አሜሪካ ድረስ ልካ በታዋቂው ሙዚየም ውስጥ እንድትጎበኝ አድርጋለች፡፡ ሉሲ በአሜሪካ ባደረገችው የዓመታት ቆይታ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱ ያለችበትን አጠቃላይ ሁኔታ ማስተዋወቅ ተችሏል፡፡
ሉሲ አሁንም ይህን ገድሏን በሌላ ዘርፍ ቀጥላለች፡፡ ሀገሪቱ አሁን የሚያሳስባት ሰላም እና አንድነት መሆኑን ለማስገንዘብ በተለያዩ ክልል ከተሞች ሉሲን በመያዝ የጉብኝት መርሀ ግብር ተጀምሯል፡፡
ለዚህም በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አስተባባሪነት የተዘጋጀው የዚህ ‹‹ጉዞ ሉሲ ለሰላምና ለፍቅር›› የሚለው ፕሮጀክት ዓላማ የኢትዮጵያውያን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት መልሶ ለማምጣትና ተፈጥሯቸው ያልሆነውን ዘርኝነትና መከፋፈልን ለማጥፋት መስራት እንደሚያስፈልግ ለማስገንዘብ ነው፡፡
የላላውን የኢትዮጵያውያን የሰላምና ለአንድነት ትስስር መልሶ ለማጥበቅ ሉሲን መጠቀም አስፈልጓል፡፡ በዚህም ሉሲ የሀገሪቱን ከተሞች እንድትጎበኝ ሰፊ መድረክ ተዘጋጅቶ ጉብኝቱ ባለፈው ሳምንት የሉሲ እትብት በተቀበረበት በአፋር ክልል አሀዱ ብሎ ጀምሯል፡፡
‹‹ጉዞ ሉሲ ለሰላምና ለፍቅር›› የተሰኘው ፕሮጀክት በይፋ ተጀምሮ ሉሲ ወደተለያዩ የአገሪቱ ዋና ዋና ከተማዎችና ከተማዎቹ ወዳሉባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከማቅናቷ በፊት በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሸኛኘት ሥነ-ሥርዓት ተካሂዶላታል፡፡
በአሸኛኘት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሰው ልጅ ቅሪተ አካል ተመራማሪና ሳይንቲስት ዶክተር ብርሃኔ አስፋው የፕሮጀክቱን አላማ አስመልክተው የሰጡትን ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
የማንነት መገለጫ
ሉሲ የሁሉንም አድናቆት፣ ፍቅርና ይሁንታ ያገኘንባት ታሪካችን ናት፡፡ አገራችን እጅግ በጣም ታድላለች፡ እኛ የሰው ዘር መነሻ አገር ነን ስንል እንዲሁ በቃላት ብቻ አይደለም፡፡ እኔ እንኳ በሰራሁበት ባለፉት 38 የምርምር ዓመታት ጉዞዬ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊና እንደ አንድ ተመራማሪ በኩራት በየመድረኩ በእጄ ያለውን መረጃ ሳቀርብ እደሰታለሁ፡፡
የዓለምን ህዝብ ታሪክ መዝግቦ ያልያዘ ቦታ ማግኘት እጅግ በጣም ያስቸግራል፡፡ የኢትዮጵያ ምድር ግን የዓለምን ህዝብ ታሪክ መዝግቦ ይዟል፡፡ የሰው ዘር ባለፉት ስድስት ሚሊዮን ዓመታት እየኖረና እየሞተ ታሪኩን ትቶባት ያለፈባት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ነች፡፡
የዓለም ህዝቦች ታሪክ ተጠብቆ የሚገኘው ሉሲ እንደተገኘችበት እንደ ሃዳር ባለው መካነ ቅርስ ቦታ ነው፡፡ በአፋር አካባቢ ያለውና ያገጠጠ የሚመስለው ምድረ በዳ ስፍራ የያዘው የእኛን የኢትዮጰያውያን ታሪክ ብቻ አይደለም፤የዓለምን ታሪክ ጭምር እንጂ፡፡ በታሪክ መዛግብት ውስጥ ከአንድ ገፅ ወደ ሌላ ገፅ እንዲሁም ከአንድ ምዕራፍ ወደ ሌላ ምዕራፍ እንደሚኬደው ታሪኮቻችንም እንዲሁ በዚሁ አካባቢ ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡
‹‹ድንቅነሽ›› ብለን የምንጠራት ሉሲ ስትገኝ በ1966 ዓ.ም ብዙዎቻችን ወጣቶች ነን፣ ገሚሶቻችን ደግሞ ገና አልተወለድንም፣ ሌሎቻችን ደግሞ ጎልማሶች ነበር፡፡ የሉሲን ጉዳይ የዓለም ህዝብ ካወቀ ከብዙ ዓመት በኋላ ነው ወደኛ ጆሮ ያወቅነው፡፡ ነገር ግን ታሪካችን ጥልቅ እንደሆነ የሰው ዘር አመጣጥ ከሁለትና ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዓመታት አያልፍም እየተባለ በሚነገርበት ዘመን ላይ ሶስት ሚሊዮን ዓመት እድሜ ያለው የሰው ዘር ኢትዮጵያ ላይ እንዳለ ያበሰረችው ሉሲ ናት፡፡
ብዙ ዓመታት አልፈውም በ1984 ዓ.ም በተደረገው ምርምር እኔም ራሴ አብሬ በሰራሁበት የጥናት ቡድን የሰው ዘር አመጣጥ ታሪክ በሶስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዓመት የሚገደብ አለመሆኑ ታውቋል፡፡
ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ በተደረጉት ምርምሮች አፍሪካ በተለይም ኢትዮጵያ የሰው ዘር ታሪክ ማህደር መሆኗ እንደገና ተረጋግጧል፡፡ እንደ አንድ ተመራማሪ የማገኘው መረጃውን ነው፡፡ እንደ አንድ ተመራማሪ ግን ይህ ለኔ ትልቅ ኩራት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ በመሆኔ በዚህ ጥልቅ ታሪክ የበለጠ እኮራለሁ፡፡
ዶክተር ብርሃኔ ከሉሲ በኋላ በ1984 ዓ.ም አራት ነጥብ አራት ሚሊዮን እድሜ ያላት አርዲ መገኘቷን፣ከዚህ ከሶስት አመት በኋላም 6 ሚሊዮን ዓመት እድሜ ያለው አርዲፒቲከስ የተሰኘው የሰው ዘር ቅሪተ አካል መገኘቱን አብራርተዋል፡፡
ዶክተር ብርሃኔ እስካሁን በኢትዮጵያ በተደረጉ የሰው ዘር አመጣጥ ጥናቶች ከ13 የሚያንሱ ዝርያዎች ባለፉት ስድስት ሚሊዮን ዓመታት ውስጥ እየተተካኩ አሁን ምድርን ከተቆጣጠረው የሰው ዘር ደርሰዋል ይላሉ፡፡ እነዚህ በጥናት የተደረሰባቸው ናቸው እንጂ እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት ግን አይደለም ይላሉ፡፡
ብዙዎቹ የሰው ልጅ ዝርያዎችም የተገኙት በስምጥ ሸለቆ ከአፋር እስከ ኦሞ ባለው የሀገሪቱ ክፍል ቢሆንም፤ በዚህ ስድስት ሚሊዮን ዓመት ውስጥ ከሰሜን ትግራይ እስከ ባሌ ተራራዎች ድረስ ባሉ ስፍራዎች ብዙ ታሪካዊ ቦታዎች አሉ፡፡ በምዕራብ ከመተማ በምስራቅ እስከ አፋር በሚባል ደረጃ በሙሉ በኢትዮጵያ ምድር የሰው ዘር ያልረገጠበት ቦታ እንደሌለ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ኢትዮጵያ የሰው ዘር መነሻ ናት፤ የሰው ዘር መነሻ ብቻም ሳትሆን አሁን ያለው ዘመናዊው ሰው የተፈጠረባት መሆኗ እሙን ነው፡፡ በዚህም ለዓለም ህዝብ ሁሉ ኩራት የሆንን ህዝቦች ነን፡፡ እርስ በእርሳችን ያለን ስብዕናም በጣም ጠንካራ ነው፡፡ ከዓለም ህዝቦች ጋርም የበለጠ እንቀራረባለን ስንል ማስረጃ ይዘን ነው፡፡
የተገኘው የሰው ዘር ብሄር የሌለው መሆኑ
በኢትዮጵያ የተገኘው የሰው ዘር ከአሁኑ ዘመን ሰው ጋር መልኩ ቢቀራረብም አፋርም፣ አማራም፣ ትግሬም፣ ኦሮሞም፣ ወዘተ አይደለም፤ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ምድር የተፈጠረ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ሁላችንም የተገኘነው ደግሞ ከዚሁ ዘር ነው፡፡
ከኢትዮጵያም አልፎ ዓለምን ሁሉ ያደረሰው ይኸው ዘር ነው፡፡ በተለያየ ጊዜ የተገኙ ዘሮች በሙሉ የተፈጠሩት ከኢትዮጵያ ምድር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በምድር ላይ ያሉት የሰው ዘሮች የሚለያዩት በቆዳ ቀለማቸው ብቻ ነው፡፡ ይህ የቆዳ ቀለም የተፈጠረው ከጊዜ በኋላ ነው እንጂ የሰው ዘር በተገኘበት ዘመን ሁላችንም የነበረን አንድ አይነት ቀለም ብቻ ነበር ፡፡
የሚገርመው ደግሞ በቅርብ ጊዜ በተደረገው ጥናት የዛሬ 29 ሺ ዓመት በለንደን የተገኘ አንድ ቅሪተ አካል የቆዳው ቀለም ጥቁር የአይኑ ቀለም ደግሞ ሰማያዊ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው በአሁኑ ወቅት የሚታየው ሙሉ ለሙሉ ሰማያዊ አይን የመጣው በጣም ዘግይቶ መሆኑን ነው፡፡
ይህ ሁሉ የሚያሳየን እኛ በቅሪተ አካላችን ብቻ ያስመዘገብነው የዘር አንድነት ከዛ በኋላ ሌላ አጥኚ የሆነች ሌላ ምርምር ስታደርግ እኛ ቅሪተ አካላት ያስመዘገቡት እውነታ መሆናችንን ነው ያሳየችው፡፡ የዓለም ህዝቦች በሙሉ ዘራቸው የሚነሳው ከኢትዮጵያ እስከ ታንዛኒያ ባሉት ህዝቦች መካከል ነው፡፡ በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን የሰው ዘር መነሻ ነን ስንል ማረጋገጫ የሆነንን ሳይንሳዊ መረጃ ይዘን ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የሚታየው ልዩነት ትስስርን የሚበጥስ አለመሆኑ
ይህ ሁሉ የመልክ እንዲሁም የባህል ልዩነት በሙሉ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን፣ የዘር ትስሰራችንን የሚያሳይ እንጂ የሚለያየን እና ትስስራችንንም የሚበጣጥስ አይደለም፡፡
እኛ እርስ በእርሳችን በኢትዮጵያ አጥር ውስጥ የምንኖር ሰዎች ነን፤ በዘራችን ብንመረመር አንዳችንን ከአንዳችን መለየት አይቻልም፡፡ የምንለያየው በልብሳችን፣ በላያችን ላይ በምንጨምረው ጌጣጌጥ፣ አሊያም በሂደት በመጡ ባህሎቻችን ሊሆን ይችላል፡፡ በቅርብ ጊዜ በተፈጠሩ ቋንቋዎች አሁን እንደምናየው ስር በሰደደ አይነት ሁኔታም ሊሆን ይችላል የምንለያየው፡፡ ይህ ልዩነት ግን ምንም ቁም ነገር የለውም፡፡
ዘራችን ስነ ባህሪው ሲመረመር አንድ ህዝቦች መሆናችንን ነው የሚያመለክተው፡፡ አንዱን ከአንዱ መለየት በፍፁም አይቻልም፡፡ እናም ‹‹ዛሬ የእከሌ ነው፤ የእከሊት ነው›› ማለቱ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ሁሉም ሊያውቀው ይገባል፡፡
ታሪካችን እጅግ ሰፊ ነው፡፡ አንድ ሳልናገረው ማለፍ የማልፈልገው ነገር ቢኖር እንደ ኢትዮጵያ ያለ ለዓለም የሚያስግርም አገር የለም፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ከእኛ ኢትዮጵያውያን በላይ ሌላው የዓለም ክፍል አብዝቶ ይገልጸዋል፡፡ እኛ የሌላውን የዓለም አገር ያህል ስለራሳችን ግንዛቤ ያሳነስን ሆነን ነው የተገኘነው፡፡
በ1930ዎቹ አንድ የውጭ አገር ታሪክ አዋቂ ‹‹እምነት ኢትዮጵያ ለዓለም የሰጠችው ስጦታ ነው፡፡›› ሲል ተናግሯል፡፡ እውነት ነው፤ እኔ እንደ አንድ ተመራማሪ የምናገረው ሁልጊዜም በመረጃ ላይ ተመስርቼ ነው፡፡ የእምነት ምልክቶችን በኢትየጵያ ከተገኙት የሰው ዘር ቅሬተ አካሎች ማግኘት ችለናል፡፡
እምነት የአንድነት ማጥበቂያ ገመድ
አንድ አጠንክሬ መናገር የምፈልገው የኢትዮጵያ ህዝብ ያለእምነት ኖሮ አለማወቁን ነው፡፡ የሚያስተሳስረን የዘር አንድነታችን ብቻ አይደለም፡፡ የእምነቱ አይነት ሊለያይ ይችል ይሆናል እንጂ ሁላችንም ያለ እምነት ኖረን አናውቅም፡፡ ይህ ደግሞ ከጥንት ከስር መሰረታችን ጀምሮ አብሮን የቆየ ጉዳይ ነው፡፡
በመጀመሪያው አካባቢ በሚታዩና በሚዳሰሱ አማልክት የምናምንበት ዘመን ነበር፡፡ ቀጥሎ ደግሞ በማይታየው አምላክ በፈጣሪ የምናምንበት ዘመን መጣ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ዘመናትን ያስቆጠሩ ባህላዊ እምነቶችም አሉን፡፡ እነዚህ ሁሉ በአንድ አገር ውስጥ ተሳስረው እና ተያይዘው የሚገኙባት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ነች፡፡ ይህ ትስስራችን ዛሬም ለበጎና ለፍቅር እንዲሁም ለአንድነት መሆን አለበት፡፡
ኢትዮጵያ ፈጣሪን ማለትም የማይታየውን አምላክ ማምለክ የጀመረችው አውሮፓውያንና ኢስያውያን ከመቀበላቸው በፊት ነው፡፡ ለእምነት ቦታችን ትልቅ ስፍራ ሰጥተን መኖር የጀመርነው ከሌሎችም አስቀድመን ነው፡፡
በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሁሉም አውሮፓና ኢስያ ቀድመን ክርስትናን በአግባቡ የተቀበልን ነን፡፡ ሌሎች ክርስትናን በክብር መቀበል ሳይችሉ ቀርተው ኢትዮጵያ ግን የተቀበለችው በክብር ነው፡፡ እኛ ለአማኞች ትልቅ ክብር ያለን ነን፡፡ እስልምና በተወለደበት ቦታ መኖር አቅቶት ሲቸገር ነብዩ መሀመድ የላኩት ወደ ኢትዮጵያ ነው፡፡ የነጃሽ መስጂድ ለዚህ ምስክር ነው ፡፡
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ብቻም ሳይሆን እስካሁን ዘመን ድረስ ክርስትና እና እስልምና አብረው በክብር የሚኖሩባት አገር መሆኗ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ይህን አይነት እሴት የተገኘባት አገር አብሮነትን በሚሸረሽሩ ጉዳዮች መጠመድ አይኖርባትም፡፡
አገሪቱ የምትታወቀው በከፍተኛ ደረጃ በፍቅር እና አብሮ እየሰሩ የሚኖሩባት አገር መሆኗ ነው፡፡ ይህም ለዘመናት ያቆየነው እሴት ነው፡፡ በሰላም መኖር የሚችል ህዝብ ያላት ሀገር ናት፡፡ ታሪካችን በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የእምነት መቻቻሉ ብቻ አይደለም፡፡ ሁሉንም እምነት አምኖና አክብሮ እንዲሁም ተቀብሎ አብሮ መኖር እኛ አዲስ የፈጠርነው አይደለም፡፡ አብሮን የኖረና የተሳሰረ ባህላችን ነው፡፡
እሬቻ፣ ጨምባላላ፣ መስቀልና ሌሎች መሰል በዓላት የዓለምን ቀልብ የሳቡ የአገራችን የማይዳሰሱ ቅርሶች ናቸው፡፡ ይህ የአንድነታችን መገለጫ ነው፡፡ ወጣቱ ትውልድ ታሪኩን አውቆና በዘርና በሃይማኖትም ያለውን ትስስር አጎልብቶ መቀጠል አለበት፡፡ እንዲሁም እኛ በብዙ ጉዳይ የተሳሰርን ህዝቦች መሆናችንን ተረድቶ መጓዝ አዋጭ ነውና እንዳለፈው ሁሉ ለዓለም ህዝብ ምሳሌ ለመሆን ራስን ማስተካከል ተገቢ ነው፤ ጊዜውም አሁን ነው ፡፡
ብሄር የለሽዋ ሉሲ ወደተለያዩ ክልሎች ዋና ዋና ከተሞች ጉዞ ማድረጓ ብሄርን፣ ልዩነትንና ሌላውን ጉዳይ ለመስበክ ሳይሆን የላላውን ፍቅር፣ ሰላም፣ አብሮነትና አንድነት ለማጥበቅ ነውና ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ከሁሉም የሚጠበቅ ድርሻ ነው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011
በአስቴር ኤልያስ