ክቡርነትዎ የዚህች ክብር መገለጫዋ ሉዓላዊነት መለያዋ በሆነች ኢትዮጵያ ላይ ያሎትን አቋም ይፈትሹ ዘንድ ይሄን ልነግርዎ ወደድኩ።ሀሳብና ጥያቄዬ በአክብሮት ለእርሶ ይደርስ ዘንድ ይህንን አልኩ። ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እርስዎ የልዕለ ሀያልዋ አገር የተከበሩ መሪ ኖትና የክብርን ትርጉም ይረዳሉ ብዬ እገምታለሁ።
ይህም ሆኖ ግን የአገሬን ሰው ስለ ክብር ያለው ትርጓሜን ልነግሮ እወዳለሁ። ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን ክብር ታላቅ ጉዳይ ነው። ለዚያም ነው ሀገራችን ክብራችን ናት የምንለው። ክብርንም በእርስዎ እንለካለን። ለሌሎች የምንሰጠው ክብር ለአገራችን ባላቸው በጎነት ላይ የተመሰረተ ነው። እርስዎን ላከበረ ንግስና፣ ላላቃት ልዕልና መስጠት ያስደስተናል።
ይቺን ታላቅ አገር የሚገባትን ክብር ሊሰጥዋት ያላትን ሀቅ ሊጠብቁላት ይገባል። እርስዎ የልዕለ ሀያልዋ አገር አሜሪካ ፕሬዚዳንት ኖት። ታላቅ መሪ ደግሞ ታላቅ ህዝብን ማወቅ ይኖርበታል። ክቡር ፕሬዚዳንት ቅኔማ ከእኛ ሳይወርሱ አይቀሩም! ያለወትሮዎ አዲስ ዓመት ስናከብር “እንኳን አደረሳችሁ” ሲሉን እኛ በጎነት ልማዳችን ነውና በጎ መስሎን ተቀብለንዎታል።
እኚህ ሰው ስለ ኢትዮጵያ በትክክል መመልከት የሚስችላቸው መነፅር አጥልቀው ይሆን እንዴ? ብለንም ነበር። በመልካም ምኞትዎ እርስዎና አገርዎ እውነት ይገለጥላቸው ጀምሯል ብለን አውርተን ሳንጨርስ ንግግሩ ቅኔ መሆኑን ተረዳን። ሰሞኑን በውድዋ አገሬ ላይ ማቀብ ይሉት ፍርድ አልባ በትርዎ ሊያሰርፉ ማሰቦን ብሎም ማዘዞትን ሰማን ።
የተከበሩ ፕሬዚዳንት አገርዎ ስለ እውነት ከቆመች መንግስትዎ ስለ ሰብዓዊነት እና ፍትህ ዘብ ነኝ ካለ፤ ስለምን የአፍሪካ የነፃነት ተምሳሌት የጥቁር ህዝቦች ቀንዲል በሆነችዋ ኢትዮጵያ ላይ ፍርድዎ ተዛባ? እርስዎ ወደ ስልጣን ይመጡ ዘንድ ድምፅና ድጋፍ የሆንዎ አገሮ ላይ የሚኖሩ እልፍ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ውለታና እውነት አለመስማትዎ አስገርሞናል።
ሀገርዎ ሉዓላዊ አገር ተዳፍራ ለእናንተ ይህ እንዲሆን ፈቅጃለሁ፤ ያኛው ደግሞ በፍፁም እንዳትሞክሩት ልትልና በሉዓላዊነት ኢትዮጵያ ላይ ያሻትን ላድርግ ማለትዋ ፤ ይሄንንም በይፋ መግለጽዎ አያስተዛዝብም።
ይንገሩኝ ክቡር ፕሬዚዳንት ፣ የዴሞክራሲ ትርጉሙ በራስ መወሰን ያሻን መርጦ ለመሪነት ማብቃት መሆኑ ቀረ እንዴ? ታዲያ ምነው ስለእናንተ አገሬ ትወስንላችሁ አሉን? የሰብዓዊነት ትርጉሙ ርህራሄና ከአድሎ ነፃ የሆነ ፍትሃዊነት ማንገስ አልነበር? ታዲያ ስለምን አገሬና ህዝቤን ለበደሉት፣ የዜጎች ክብርና ሰላም ለነሱት የሰላም ጠንቆች ጠበቃ መሆንን ተመኙ?
እንዴት ህጋዊውን ከህገ ወጡ ጋር በእኩል ፈረጁ። የአገርዎን ታሪክ ወደኋላ መለስ ብለው አላዩ ይሆን እንዴ? ዛሬ እኛ አገር ላይ የእናት ጡት ነካሾች በሰራዊቱ ላይ የፈፀሙት አስነዋሪ ተግባር አንድ ወቅት ላይ የእርስዎም አገር ላይ በተመሳሳይ መልኩ መፈፀሙ ከአገሮ ቀደምት ታሪክ ላይ ሰፍሮ ይገኛል። አገሮትም አገር ሆና የቆመችበትና የፀናችበት ዘመን እሩቅ ስላልሆነ ሳይቸገሩ ታሪኮን ያገኙታል።
ክቡር ፕሬዚዳንት አገሬን ሊንዳት የፈለገ ጠላትዋን ስትዋጋ ለምን ወጋሽ ማለትዎ ተገቢነቱ ምኑ ላይ ነው ? አገርዎ ተደፈርኩ፤ ህዝቤ ላይ ጥቃት ተፈፀመ ብላ ድንበር ዘላ ውቅያኖስ አቋርጣ አገራትን ታፈርስ የለም እንዴ? ታዲያ ስለምን የእኛን ሉዓላዊነት የተዳፈረ አገራችንን ሊንድ የሞከረን ልናስቆም ስንሞክር ተውት የሚሉን። መንግስትዎ ሽብርተኛ ያለውን ሲዋጋ ይኖር የለም እንዴ ? ታዲያ ስለምን የእኛ ህግ ሽብርተኛ ያለው ቡድን ጋር መዋጋት ሲጀምር ተቃረኑ። እንደው ይሄ ዴሞክራሲ የሚለት ፅንሰ ሀሳብ በአገሮ ላይ ለዘመናት ተተግብሮ አርጅቶ መልኩን ቀይሮ ይሆን እንዴ ?
የእርስዎ አገር ቅድመ አያት ከሆነችው አገረ ኢትዮጵያ ይህንን ልሎት ግድ አለኝ። የታላቅዋን ኢትዮጵያ ታላቅ ህዝብ እንዳይመለስ ሆኖ ሊታዘብዎ ከጫፍ ደርሷልና ኢትዮጵያዊያን የሚያዩበት መነፅርዎ ያስተካክሉ ።
ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ሉዓላዊት ሀገር ለዚያውም ኢትዮጵያን የመሰለ የነፃነት ሙክራብ፣ የጥቁሮች አርነት ተምሳሌት የሆነች አገር ላይ ዘመናዊ ባርነት ለመጫን ለመሞከር ማሰቡ ምን ሊባል ይችል ይሆን። ስለ ኢትዮጵያ እውነቱን አለመረዳትዎ አልያም በኢትዮጵያ ላይ የሚያራምዱት አቋም አይቶ “ይተው ልክ አይደሉም!” የሚሎት አማካሪ አጥተው አይመስለኝም። ነገሩ ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ሆኖ እንጂ።
ክቡር ፕሬዚዳንት የአገሬ ሰው መሰል ጉዳይ ሲገጥመው ምን ይላል መሰሎት “መርፌ ሲለግም ቅቤ አይወጋም” ይላል።የእኛን ጉዳይ ጠንቅቀው ያውቁታል። እውነቱን በደንብ ይገነዘቡታል። ክቡርነትዎ የእኛን እውነት ሳያውቁት ቀርተው ሳይሆን ሆን ብለው ላለማወቅ መፈለጎን ከተግባሮ ተረድተናል። ለአገርዎ የእኛ እውነተኛና ትክክለኛ ቁመና አይበጅም ብለው መሆኑ ያሳብቅብዎታል።
እስካሁን ታላላቅ ስህተቶችን ተሳስተዋል። አልያም ደግሞ በዙሪያዎ ያሉ ሰዎች በሰጥዎት መረጃ 120 ሚሊዮን ህዝብ ላይ ፈርደው ያልተገባና ፍትሃዊ ያልሆነ አካሄድ ተከትለዋል። እውነቱ ምንድነው ብሎ ከመረዳትና ለዚያ መፍትሄ የሚሆን ነገር ከማመላከት ይልቅ አባባሽ የሆኑ መንገዶችን መጓዝ መርጠዋል። ታዲያ የአገሮ ለፍትህ፣ ለእኩልነትና ለመብት መከበር መቆርቆርና ከፊት መቆም በምን እንመልከት?
የኢትዮጵያ ህዝብ እስካሁን ባደረጉት ተገቢነት የራቀው ጫና የትዝብት ጥግ ላይ አስቀምጥዎታል። ዛሬ እያደረጉት ባለው ወደፊት ታሪክ ይወቅሶታል። ግን የተከበሩ በዚህ ሁሉ ጫና ውስጥ ይበልጥ ለአገሬ ብሎ ማህበሩ ሲነካ እንደ ቀፎ ንብ በአንድነት መቆሙ አልገረሞትም ይሆን። በእርግጥ የኢትዮጵያዊያን ስነ ልቦና ጠንቅቀው ባይረዱም፤ የህዝቡ ጽኑነት ጥያቄ ሳይፈጥርቦ አይቀርም።
ክቡር ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን ጠንቅቀው አያውቁዋትም ይሆን እንዴ? ከታሪክ መዝገብ ላይ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያንን ታሪክ ቢያገላብጡ አሸናፊነት መለያቸው ድል ማድረግ ልማዳቸው እንደሆነ ይረዳሉ። ይህ ለምን ብለው ቢጠይቁ ደግሞ መልሱ እዚያው መዝገብ ላይ እንዲህ ይነበባል። የድላቸው ሚስጥር እውነታ ላይ መቆማቸው ነው። ወደ ሌላ ሄደው ድንበር ተጋፍተው የሌሎችን ሉዓላዊነት አይዳፈሩም፤ ሊወራቸውና ነፃነታቸውን ሊነጥቅ ሉዓላዊነታቸውን ሊዳፈር የመጣን ደግሞ የማይታገሱ ቆራጥ ጀግኖች ናቸው።
የተከበሩ የዚህ ጀግና ህዝብና አገር መተዳደሪያው እውነት፣ መቆሚያው ሀቅ ነው። ይህ ህዝብ ባገሩ ከመጡበት ድርድር የሚሉት ነገር አያውቅም። አገሩን ላለማጣት ብሎ ያለስስት እራሱን ከፊት ያስቀድማል። በሰላም ሊወዳጀው የመጣን አንግሶ ዝቅ ብሎ የሚያስተናግደው እና ፍቅሩን ሳይቆጥብ በተግባር የሚገልጥ፤ በአገሩ ሲመጡበት ደግሞ አራስ ነብር ነው።
ታዲያ ክቡር ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ በጋራ የተሰነደ ቃል ኪዳን መኖሩን እንዳይዘነጉ። ያ ቃል ኪዳንም እያንዳንዱ ዜጋ ለአገሩ የገባው ነው። ቃሉም “አገሬ ሆይ ካንቺ በፊት እኔን ያስቀድመኝ” ብሎ ከምድሪቱ ጋር የተጋባው ጥልቅ ፍቅር ነው። የተከበሩ የዚህ አትንኩኝ ባይ ህዝብ ስነ ልቦና ሊረዱት ይገባል። የራሱን አሳልፎ የማይሰጥና ያላግባብ የሌላውን የማይፈልግ መሆኑን ሊያውቁለት ግድ ይሉታል።
የእርስዎ ፍላጎት የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ካልሆነ እንዴት የፍላጐትዎ ይፈፀም ዘንድ ያስባሉ። ኢትዮጵያዊያን የሚሹት በራሳቸው ማደር ፤ ስለራሳቸው በራሳቸው መሆን እንዳለበት ለእርስዎ ለታላቅዋ አገር መሪና ዴሞክራሲ መተዳደሪያዬ ነው ለሚለው ህዝብዎ መንገር ያለብኝ አይመስለኝም።
አገሬ የገጠማት ፈተና ህዝቤ የተጋረጠው አደጋ መነሻው ምን እንደሆነ ለእርስዎ የሚጠፋዎት አይደለም። የታላቅዋ ኢትዮጵያ ደመኖች ለእርስዎም የተሰወሩ አይደሉም። እነዚህ ላይ መለዘቦ ነው የሚገርመው። በእርግጥ አጥፊውን በቀጥታ ተው ቢሉት ይብስ እንዳይጠፋ ይጠቅመው ነበር።
ለእርስዎ አጥፊና አልሚው ተደባልቆቦት አይመስለኝም። ይሄን ታላቅ ህዝብ ታናሽ ለማድረግ የሚሰሩ ሴረኞች ይህቺ ታሪካዊት ውብ አገር ለማጉደፍ የሚታትሩ የአገሪቱ ጠላቶች፣ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የጣሉ ሽብርተኞችን ማንነት ፀሐይ ሞቆታል። የእርስዎ መንግስት ግን በፀሐዩም አጥፊዎቹን ላለማየት ፊቱን የሚያዞር ሆነ።
እንኳን ይሄ ይፋ የሆነና ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ቀርቶ በብዙ መሸፈን ውስጥ ያለን ሚስጥር አንፍንፎ ይፋ የሚያደርገው የደህንነት ተቋሞ፤ የኢትዮጵያዊያን እውነት ተሰውሮበት ለእርስዎ የተሳሳተ መረጃ አቅርቦዎል ማለት እንዴት እንዴት እንድፈር። ነገሩ አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማ ነው።
በዓመቱ መግቢያ ላይ እንኳን አደረሳችሁ ብለው ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንዳች አጉል ነገር ይደርስብን ዘንድ “ማዕቀብ ይጣል” የሚል ትዕዛዝ ማስተላለፍዎን ስናውቅ አዘንብዎ። የእርስዎ በዚህች እራሶ ታላቅ ባልዋት አገር ላይ በሚያራምዱት የተሳሳተ እሳቤ የህዝቦችዋ ሰላምና ደህንነት ጥያቄ ላይ መውደቅ እንዴት ግድ አልሰጥ አሎት?
መንግስትዎ የታላቅዋን ኢትዮጵያ ክብር የሚጠብቅ፣ ሉዓላዊነትዋን የሚያከብር አቋም ስለምን አላንፀባረቀም? የእርስዎ አገራችንን ለማፍረስ ሌትተቀን የሚያሴረው ቡድን በለዘብታ ማየት፣ በተግባርና በክፉ ስራው አለመግለፅ፣ አለፍ ሲልም በደሉን አለማውገዙ ስናይ፤ ስለ እውነትና ፍትህ መቆም የቱ ጋር ነው? ብለን መጠየቅ ፈለግን።
በ21ኛ ክፍለ ዘመን ላይ ተገኝቶ እጅጉን ወደ ኋላ የተመለሰ አመለካከት ያለው፣ ተላላኪ የሆነና የአገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል፣ ከኢትዮጵያዊነት ስነ ልቦና ያፈነገጠና አፈጣጠሩም ድርጊቱም ፀረ ህዝብና አገር የሆነውን ቡድን ኢትዮጵያዊያን በቃኝ ብለው አንቅረው ተፍተውታል። ታዲያ ስለምንድነው ልንወደው የማይችለውን ውደዱ ማለቶ?
ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን አይደለም በዚያ በጨለማው ዘመንም ለወዳጅ እንጂ ለጠላት አትምችም ብዮት የለ። አሁንም የኢትዮጵያዊያን ፍላጎት አውቀው ለሰላምና ለእድገትዋ ድጋፍ ካልሆንዋት በቀር በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ ባይገቡ አቋሞትንም ቢፈትሹ መልካም ነው።
ለእውነት እና ስለ ሀገራቸው ነፃነት አንገታቸው የሰጡ ጀግኖች ልጆች ነንና በአገራችን ድርድር የማናውቅ የሚያንበረክከን ፍቅር እንጂ ጫና አለመሆኑን ይረዱ። በሉዓላዊነታችን የማንደራደር፣ በጉዳያችን ሲመጡብን የማንወድ፣ ኢትዮጵያችን ሲነኩብን የማያስችለን ቆራጦች መሆናችንን አይዘንጉ።
የእስካሁኑ ተግባርና አተያዮ ኢትዮጵያንና የህዝብዋን ስነ ልቦና ጠንቅቀው ያወቁ አይመስለኝም። ለስህተትም የዳረግዎት ይህ ይመስለኛል። እርስዎ የልዕለ ሀያልዋና ዲሞክራሲያዊት አገር አሜሪካ መሪ አይደሉ፤ የታላቅዋን ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ያክብሩ።
ለኢትዮጵያ የሚበጀው ከእርስዎ በላይ ኢትጵያዊያን ያውቃሉን ቀና የሆነ ድጋፎን ይስጡን። የውስጥ ጉዳዮቻችን ላይ የመወሰኑ ጉዳይ ለሉዓላዊትዋ ኢትዮጵያ ቢተውላት አይሻልም። የሻውን እና የወደደውን ለስልጣን ማብቃት፤ ያለውን ከስልጣን ማንሳትና ወንጀለኛውን ለህግ ማቅረብ የኢትዮጵያን ህዝብና ህጋዊ መንግስት ስራ ነውና ጉዳያችንን ለእኛ ይተውልን። ኢትዮጵያዊያን ፍላጎት ሰላም አንድነትና ዕድገት ነውና እዚያ ላይ ያግዙን።
ልምዳችን አይደለምና እርስዎን ለማሳመን ከ3ሺ ዓመት ያለፈ ታሪክ ያላትን ውድ አገራችንን አሳልፈን ለአጉራ ዘለሎች አንሰጥም። እርስዎና አገርዎ ለጥቅምና ለበላይነት የምታደርጉትን ጥረትና በላቀ እኛም ስለ አገራችን ጥቅምና ለውጥ እራሳችን ለመስጠት ዝግጁ ነን። ለእስዋ ዘብ በመሆን ሉዓላዊነትዋ እንዲጠበቅ የማድረግ የአባቶች አደራ አለብንና በእርስዋ እንዳይመጡብን።
ለእርስዎና ለአገርዎ እውነትና ሰብዓዊነት ከፖለቲካዊ ትርፍና ጥቅም ዝቅ ያለ ከሆነ ከኢትዮጵያዊያን ጋር መግባባት ያዳግቶታል። በዚህ አቋም ላይ ካሉ እርስዎ የማይመጥን መሆኑን መንገር እንወዳለን። የእርስዎ አገር የቅርብ ጊዜ ታሪክ ከእኛዋ ታሪካዊና ቀደምት አገር ኢትዮጵያ የመንግስት ምስረታ ታሪክ ጋር ሲነፃፀር የተራራቀ ነው። በአመሰራረታችንም የምንለያይ መሆኑ ይረዱልን።
ሀገሮ በተለያዩ ወቅቶች በፈጠረችው ያልተገባ ትርክት ጥንታዊ የሆኑ ለዓለም ከፍ ያሉ እሴቶችን ያበረከቱ ሀገራት ከሀገር ቁመና መውጣታቸው ህዝባቸውም መበተናቸውን የሚያጡት አይመስለኝም ፤ኢትዮጵያ ግን ይተዋት ።
እርስዎ ማቀብ ሊጥሉ ይችላሉ፤ እኛ ግን አሳልፈን የምንሰጦት ሉዓላዊት የለም። ከምንም በላይ የአገር ክብር የሚገደን እስዋን ሲነኩብን ደማችን የሚሞቅ ነፃ ህዝቦች ነን። በሉዓላዊነታችን ከማንም ጋር ተደራድረን የማናውቅ፤ የአገር ክብር የሚገደን ነፃነታችን ማጣት የማንፈቅድ የጀግኖች ልጆች ነን። ለኢትዮጵያ የሚገባትን ክብር የሚሰጣት ክብሩ ከፍ ያለ ነው፤ ይህንን እንዲገነዘቡ እወዳለሁ፤ ይህም የሆነው ከእውነት ጋር ካለን ትስስርና ለእውነት ካለን ቀናዊነት ነው፤ አበቃሁ።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም