በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ በግብር ዙሪያ እየሰበሰበች ያለችው ሀብት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ያህል አይደለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። የአፍሪካ ትልቁ የገበያ ሥፍራ በሚባለው መርካቶ የሚዘዋወረው የገንዘብ መጠን ብቻውን ደግሞ ለዚህ ጥሩ አብነት ይሆናል።
በዚህ የገበያ ስፍራ በግል ባለሀብቶች እና በነጋዴዎች በአክሲዮን ማኅበር አማካይነት ህንጻዎች እየተገነቡ በትንንሽ ቦታዎች ላይም በርከት ያሉ የንግድ መደብሮች እየተከፈቱ አገልግሎት ቢሰጡም፤ በግብር ላይ የመጣ ለውጥ ግን አይታይም። በተለይም ህገ ወጥ ንግድ በማለት በጎዳና ላይ የሚነግዱ አካላትን ለመቆጣጠር የሚደረገው ከፍተኛ ጥረት በእነዚህ ሃላፊነታቸውን በማይወጡ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ላይ ተፈጻሚ ሲሆን አይስተዋልም።
በሌላ በኩልም በምግብ ቤቶችና በሌሎችም የተጨማሪ እሴት ታክስ መቁረጥ ባለባቸው አገልግሎት ሰጪዎች ላይ እየተደረገ ያለ ክትትልም ሆነ አጥፍተው ሲገኙ እየተወሰደ ያለ እርምጃ ያን ያህል ነው፡፡ ከዚህም በላይ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ተወጥተው ተጨማሪ እሴት ታክስን እየቆረጡ በትክክል የሚነግዱ ነጋዴዎችን ለማበረታታት የሚደረግ ጥረትም የለም። ይህ ደግሞ ከህገ ወጦች ጎን እንዲቆሙ ያደርጋቸዋል።
ለአብነት መጥቀስ ካስፈለገ በዚሁ ገበያ ማዕከል አንዋር መስጊድ አካባቢ ያሉ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች መሸጫ መደብሮችን ብንወስድ የሚገዛ ሲመጣ የመጀመሪያ ጥያቄያቸው «ያለቫት እንሽጥልህ?›› የሚል ነው። እንደ «ሸራ ተራ» በመሳሰሉ አካባቢዎች በጎጆ ኢንዱስትሪዎች ብዙ ጫማ፣ የቆዳ ጃኬቶችና ቦርሳዎች ይመረታሉ፡፡ ብዙ መደብሮችም ምርቶቻቸውን ወስደው ይሸጣሉ። እነዚህ ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎች ታዲያ በአክሲዮን ማኅበር የሚያደራጃቸው እና ሕጋዊ ሊያደርጋቸው የሚችል አካል ቢያገኙ ብዙ ዜጎችን ወደ ግብር መረብ ማካተት ያስችሉም ነበር።
በተለምዶ ምዕራብ ሆቴል አካባቢ የሚገኘው የከተማው የጫት ማከፋፈያ ሥፍራ ሌላው ብዙ ሀብት የሚንቀሳቀስበት ነው፡፡ ከሚገኘው ገንዘብና ከሚመላለሰው ህዝብ አንፃር በተለይ የክፍለ ከተማው ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በትኩረት ቢሰራና ነጋዴዎቹን ወደ ግብር መረብ ማካተት ቢችል ምን አይነት ገቢ ሊሰበስብ እንደሚችል መገመት ከባድ አይሆንም። ምክንያቱ ደግሞ በዙሪያው ያሉ ባንኮች የሚያስገቡትንና የሚያስወጡትን ገንዘብ ማየት ብቻውን በቂ ስለሆነ ነው።
በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አብዛኞቹ ለማለት ይቻላል በኪራይ ላይ ያሉ ናቸው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የተለያየ ቢሆንም፤ የአከራይ ተከራይ ውል የሌለበት፣ ገቢው በክፍለ ከተማም ሆነ በወረዳ የማይታወቅ አግባብ የሌለው፣ እንዲሁ ደላሎች የሚጫወቱበት መሆኑ ደግሞ የአደባባይ ምስጢር ነው።
እነዚህ ሁሉ አይን ያወጡና ያፈጠጡ የግብር ክፍተቶች መሙላት ዜጎችም «እኔ ለሀገሬ» ብለው መነሳት ቢችሉ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሊሰበሰብ የሚችለው ግብር እንደ ፌዴራል ከሚሰበሰበው የቱን ያህል እጥፍ ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው።
ሆኖም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለው የግብር አካሄድ ባለፉት ስድስት ወራት መጠነኛ መሻሻሎችን ማሳየቱን ደግሞ መረጃዎች እያመላከቱ ነው።
በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ የገቢዎች ሚኒስቴር 98 ነጥብ 96 ቢሊዮን ብር የሰበሰበ ሲሆን፣ ይህም ገቢ ካባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 7 ነጥብ 78 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ነው። ይህም ገቢ ከአገር ውስጥ ታክስ፣ ከወጪ ንግድ ቀረጥና ታክስ፣ ከሎተሪ ሽያጭና፣ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች የተገኘ ሲሆን፣ አፈፃፀሙም 80 ነጥብ 76 በመቶ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ገልፀው ነበር።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ከፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥር ወጥቶ ራሱን ችሎ በተቋቋመ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 18 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል። ገቢውም ከታክስ፣ ቀጥተኛ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎችና ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የተሰበሰበ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
አፈፃፀሙ የዕቅዱ 95 በመቶ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው፤ ይህም 17 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ያስረዳል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢ የመሰብሰብ እና የማስተዳደር ሥልጣን ከ 2003 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም በውክልና ለቀድሞው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተሰጥቶ የነበረ ሲሆን፣ ከታህሳስ 2010 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ከተማ አስተዳደሩ እንዲመለስ ተደርጓል።
በአዲስ መልክ የተቋቋመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን በሥሩ አራት መካከለኛና አስር አነስተኛ የግብር ከፋይ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አሉት ፤ አገልግሎቱ ለአዲስ አበባ ከተማ የሚመጥንና ለሌሎች ክልሎች አርአያ የሆነ ገቢ ሰብሳቢ ለማድረግ የተለያዩ ሪፎርሞችን በማካሄድ ላይም ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን የታክሰ ጉዳዮች ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ግርማ፣ በከተማዋ ከ 380 ሺ በላይ ግብር ከፋዮች ቢኖሩም እስከ አለፈው ስድስት ወር ድረስ የሚጠበቅባቸውን ግብር በአግባቡ ከፍለዋል ለማለት እንደማያስደፍርና አሁን ላይ ግን መጠነኛ መሻሻሎች እንዳሉም ጠቁመዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት እነዚህን አገልግሎት ፈላጊዎች በተሟላ ሁኔታ ለማስተናገድ ለሁሉም ሠራተኞች በተለይም 900 ለሚሆኑ ከፍተኛ ኦፊሰሮች ሥልጠና መሰጠቱንና በዚህም የሰው ኃይል ብቃትን ለመጨመር ጥረት መደረጉን አብራርተዋል።
በሥልጠናው ወቅት ያለንን ሀብት ተጠቅመን ከነበረው የተሻለ ገቢ እንሰበስባለን በማለት ሠራተኛው ቃል መግባቱን አስታውሰው፤ የገቢዎች ባለሥልጣን ተልዕኮ የታክስ አስተዳደር ሥርዓትን በመዘርጋት ግብርን በፈቃደኝነት የመክፈል ባህልን በማዳበር የግብር (ታክስ) ማጭበርበርና ስወራን መከላከል የሚያስችል ተቋማዊ አቅም በመፍጠር ለከተማ አስተዳደሩ ነዋሪዎች ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ፍላጎቶቻቸው ማሟያ የሚውል ገቢ መሰብሰብ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
እንደ ኮንትሮባንድ እና ሌሎች ሕገወጥ ንግዶች እንዲሁም ታክስ የመሰወር ችግሮች ቢታዩም፤ በአዲስ አበባ ያለው አፈፃፀም የተሻለ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። ከግብር ስወራ ጋር በተያያዘ በህንፃዎችና በጋራ መኖሪያ ቤቶች ኪራይ ገቢ ግብር ዙሪያ ክፍተቶች መኖራቸውን የሪል ስቴት ባለሀብቶች የሊዝ ገቢ ከመክፈል አንፃር ከ108 ሪል ስቴት ኮንትራክተሮች 30 ያህሉ ብቻ ሲከፍሉ እንደነበር አመልክተዋል፤ አንዳንዶቹም መሬት ተቀብለው በከፍተኛ ዋጋ ሲያከራዩ መቆየታቸውን ገልፀዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፌዴራል መንግሥት ምንም ዓይነት ድጎማ የማይደረግለት በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ወጪ የሚሸፈነው ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች በሚሰበሰብ ገንዘብ ነው፤ የከተማው አስተዳደር ከያዘው አጠቃላይ በጀት 83 ከመቶ በላይ ገቢ የሚሰበሰበው በከተማው ገቢዎች ባለሥልጣን ነው፤ በተያዘው በጀት ዓመትም 34 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ ይገኛል።
‹‹ግዴታዬን እወጣለሁ መብቴን እጠይቃለሁ›› በሚለው ብሔራዊ የግብር ንቅናቄ መድረክ ዙሪያ የከተማ አቀፍ የታክሰ ንቅናቄ መድረክ መዘጋጀቱንና ከክፍለ ከተማ እስከ ታችኛው ዜጋ ግንዛቤ ለመፍጠር ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን፣ ይህንን የሚያግዙ 200 ፈቃደኞች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሰልጥነው ተሰማርተዋል። ነጋዴዎችም ለሚሰጡት አገልግሎትና ንግድ ተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ ደረሰኝ ቆርጦ መሥራትን ህዝቡም ደረሰኝ የመጠየቅ ባህል ሊኖረው እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
በከተማው የገቢ ዘርፍ ለማሳደግና ዜጎች ግብር መገበርን እንደባህል እንዲይዙ ለተጀመሩ ሥራዎች የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሃላፊነታቸውን መወጣትም እንዳለባቸው ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ያመላከቱት።
አሁን ላይ በከተማችን የጋራ መኖሪያ ህንፃዎች፣ በባለሀብቶች እና በአክሲዮን ማኅበራት የሚገነቡ ህንጻና ሆቴሎች የንግድ ሱቆች ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች እየተበራከቱ ነው። እነዚህ የአገር ሀብቶች ደግሞ እሳትና ሌሎች አደጋዎች ቢደርሱባቸው መከላከል፣ ኪሳራውንም መቀነስ ወይም መቆጣጠር የሚቻለው መንግሥት በሚያዘጋጀው ተቋምና ተሽከርካሪ ነው ፤ለዚህም ደግሞ ዜጎች በታማኝነት የሚከፍሉት ግብር ወሳኝነት ያለው ነው። ካልሆነ ግን የህዝቡን ደህንነት ይጠብቃል የሚባለው መንግስት አቅመ ቢስ ይሆናል።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011
በኃይለማርያም ወንድሙ