የአንዳንዶችን ወላዋይነት፣ እየታዘብኩ በሁለት ባላ ልንጠልጠል ማለታቸውን ባየሁ ቁጥር፡- የከያኔው ዜማና ግጥም ውል ይለኛል። ምን ነበር ያለው ?
በምን አወቅሽበት- በመመላለሱ፣
ሲታሰር ወደ እኔ -ሲፈታ ወደ እሱ።
አከከከከ … ሰውዬው እንዴት አድርጎ ገልጾታል ጃል! መቼም የአባባሉን ውስጠ ሚስጥር የሚያውቅ ሁሉ ያውቀዋል። ምንአልባትም የግጥሙ ደራሲ ሊገልጸው፣ የፈለገው እውነት የውስጡን እሳትና ወላፈን ሊሆን ይችላል። አልያም ደግሞ ሀሳቡን እንደነገሩ ጣል አድርጎ ማለፍ አስቦም ይሆናል። እኛ ግን በዚህ የግጥም ቅኔ ብዙ ማለት እንሻለን። አዎ! ብዙ።
እንዲህ እንደከያኔው ሀሳብ ሁሉ ከወዲያ ወዲህ መመላለስ ልምዳቸው የሆነ አሸባሪዎች ሁሌም አቋም ይሉትን አያውቁትም። የትም ቢሆኑ የመንገዳቸው አቅጣጫ ወደነፈሰበት ያጋድላል። እነሱ በሰፌድ ላይ እንዳለ ውሀ ይመሰላሉ። ዳር ዳሩን ሲይዙት ከወዲያ ወዲህ እንደሚዋልል የሰፌድ ውሀ ።
ወዳጆቼ! የዘመኑ ጠላቶቻችን ሀገር አፍርሶ፣ ህዝብ ለመበተን ያልገመዱት፣ ያልሸረቡት ሴራ የለም። ይህን እኩይ ተግባር ዕውን ለማድረግም ኢትዮጵያን ታህል አገር ለባዕዳን አሳልፈው እስከመሸጥ ደርሰዋል። ‹‹መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል›› አሉ። ይኸው የተረቱ ታሪክ ዛሬ ዕውን መሆን ይዟል።
እነሱ በወርሀ ጥቅምት 2013 የመከላከያ ሰራዊትን በጀርባው በወጉት ጊዜ ክፋታቸውን ከታላቅ ገድል ቆጠሩት። አለን በሚሉት የመገናኛ ብዙሀንም ብዙ ሊያወሩ፣ ዕልፍ ሊለፈልፉ ሞከሩ። የዛሬን አያድርገውና የእነሱ አፈቀላጤ የነበረው ሴኮ ቱሬ አሳፋሪውን ታሪክ መብረቃዊ ድል ሲል በኩራት ገለጸው።
ይህን የሰማ የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ከልቡ አነባ። ከአንጀቱ አለቀሰ። እነሱ ግን ዜናውን እየተቀባበሉ ለመላው ዓለም ዘሩት ። በወቅቱ የተማመኑባቸው ምዕራባውያንም ከጎናቸው መቆማቸውን በገሀድ አሳዩን። ይህኔ የወገን ትዕግስት ተሟጠጠ። የመንግስት ዝምታ ተሰበረ። የግፈኞች ክንድ ከስሩ ይነቀል ዘንድም የህልውና ዘመቻው ተቀጣጠለ።
የዛኔ አሸባሪዎቹ በማንአለብኝነት በትግራይ የራሳቸውን ምርጫ ፈጸምን ያሉበት ማግስት ነበር። በወቅቱ የተንኮል ዕቅዳቸው ሁሉ አልጋ በአልጋ ይሆን መስሏቸው የማይታጠፍ ምላሳቸውን ሲዘረጉ ቆይተዋል። ያሰቡት ሳይሆን ቀረና ታሪክ ተገለበጠ። አሉን የሚሏቸው ጉምቱ መሪዎች ከነውርደታቸው ከመሬት በታች ዋሉ። ጀግንነትና ድል የኢትዮጵያ ህዝብ ሆኖም እውነታው ሁሉ ገሀድ ወጣ።
ጉድ መፍላት የጀመረው ከእዚህ በኋላ ነበር። እነ ነውር አይፈሬዎቹ ወደለመዱት ጉያ መወሸቃቸውን ያዙ። የፈጸሙትን አሳፋሪ ድርጊት በመንግስት አላከውም አዲስ ታሪክ ፈጠሩ። በየአገራቱ የበተኗቸው ደጋፊ ነን ባዮች ሲሻቸው እንደ አህያ እየተንደባለሉ፣ እንደውሻ ማላዛናቸውን ቀጠሉ።
ለጭካኔ ድርጊታቸው የእጃቸውን ያገኙት ጨካኞች የአሜሪካንን ዋሾ መንግስት ‹‹ድረስልን›› ለማለት አልዘገዩም። ወትሮም ወዳጅነታቸው ‹‹እከክልኝ፣ ልከክልህ›› ነበርና እመት አሜሪካ ‹‹እህ…›› ስትል ጆሮ ሰጠቻቸው። ከዓይኗ ገሀዳዊ እውነታ ጆሮዎቿን አምናም ከዕቅዳቸው ተቀላቀለች።
በጣም የሚገርመው ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን የሚያሳብረው መንገድ ሁሌም ተመሳሳይ መሆኑ ነው። በውጊያው ሜዳ ጥቂት ፋታ ባገኘ ጊዜ ድሉ የእኔ ነው፡ ለማለት የሚያህለው አይገኝም ፤ ይህኔ በህልሙ የሚስለውን ምኞት አከማችቶ የሚማርከው መሳሪያ፣ የሚያሰልፈው የእግረኛ ጦር ይበረክታል። ዜናው፣ ልፈፋው፣ ውሸት፣ ቅጥፈቱ ያይላል።
አሸባሪው ሕወሓት እንዲህ ሆኗል ባለ ጊዜ ከበሯቸውን አለስልሰው እንጨፍር የሚሉ የአደባባይ ቅሌታሞች ይበዛሉ። በየሚዲያው ብቅ እያሉ አገር ትፍረስ ባዮቹ ባዶነታቸውን ያሳያሉ። የዛኔ የሀሰት ትርክትን ጆሯችን መስማት እስኪሰለቸው፣ ዓይናችን ማየት እስኪታክተው በግርምታ እንከርማለን።
ወዳጆቼ! የጉድ አይፈሬዎቹ ጉድ የሚታየው በጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን ተጋድሎ ድባቅ በተመቱ ጊዜ ነው። ይህኔ እነሱን አለማየት ያሰኛል። ዱላ እንዳነሱበት ህጻን በፍርሀት እየንቀጠተቀጡ እናቱ ቀሚስ ውስጥ ለመደበቅ እንደሚሮጥ ልጅ ይርበተበታሉ። ቀድሞ በአካኪ ዘራፍ የተሞረደው አንደበታቸው በድረሱልን ጩኸት ይታበሳል። አለብላቢ ምላሳቸው ትህትና ተምሮ ‹‹እንደራደ፣ እንነጋገር›› ይላሉ። ይህን ያዩ በርካቶች ታዲያ
ወትሮ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ
ይሉትን ተረት ቢደጋግሙላቸው መስሚያ ጆሮ የላቸውም። በለመዱት ሸፍጠኛነት ተጠቅመው መሹለክለኪያቸውን ያበጃሉ። እየዘረፉ፣ ተዘረፍን እየገደሉ ተገደልን፣ እያሳደዱ ተሰደድን፣ ተራብን፣ ተጠማን ይላሉ። ሁሌም ቢሆን አረመኔው የሕወሓት ቡድን ሲገረፍና ድል ሲነሳ የሚያሰማው ድምጽ በወጉ ይለያል።
ዱላው በበረታ ጊዜ እሪታ ጩኸቱ የደመቀ ነው። በአሜሪካ ሰፊ ቀሚስ ተሸሽጎ ለማንባት ብሶት ሰቆቃውን ለማሰማት የሚቀድመው የለም። በየአደባባዩ ተንከባላይ አህዮቹን አሰማርቶ የውሸት ዓመዱን ሲነሰንስ ይከርማል።
ጥቂት ፋታ ሲያገኝ ደግሞ የጣለውን ከበሮ አንስቶ እልልታውን ያደምቃል። በለመደው ትርክቱ ዓለምን ሊያሳስት ሰሚዎቹን ሊያደናግር ይሮጣል። ሁሌም በማያልቅበት የድል ዜና እየፏለለ በንጹሀን ህይወት መቀለድ ማፌዙን ይቀጥላል።
እንግዲህ የአረመኔው ሕወሓት ትክክለኛ መልክ እንዲህ ሆኖ ተስሏል። ጭራው ሲረገጥ አምርሮ መጮህ፣ አንገቱ ሲለቀቅ ካሰበው መወሸቅ መገለጫው ሆኗል። ይህን ማንነቱን የተረዱ ብዙዎች ታዲያ የከያኔውን ዜማ እያንጎራጎሩ ማንነቱን ይገልጹታል። በምን አወቅሽበትን እየደጋገሙ ‹‹ሲታሰር ወደ እኔ፣ ሲፈታ ወደ እሱ›› ይሉትን ግጥም ይደጋግሙለታል።
አረመኔው የሕወሓት ቡድን መቼም ቢሆን ሀሰት ለማውራትና ዓለምን ለማሳሳት ደክሞት አያውቅም። ጌታቸው ረዳን የመሰሉ መርዘ ምላሶችም በየቀኑ የሽንፈታቸውን ምልክት ሲያሳዩን ይውላሉ። እነሱ እኮ! የኢትጵያን የምታክል ታላቅ አገር ለማፍረስ ያለሙ ወገኞች ናቸው። እነሱ እኮ! አገር ሸጠው፣ ህዝብ በትነው የራሳቸውን ዓለም መስራት የሚያስቡ ህልመኞች ናቸው።
‹‹ወግ ነው›› አሉ እማማ ሻሼ። አገር ማፍረስ ህዝብ መበተን እንዲህ ቀልድ ነው እንዴ? ኢትዮጵያ እኮ የጭቃ ጀበና አይደለችም። በእጅ ተሰርታ በእጅ አትፈርስም። ኢትዮጵያ ማለት የአፍሪካ መሰረት የነጻነት ማማ ናት። ይህች አገር ለመላው ጥቁር ህዝብ ተምሳሌት ሆና በጀግንነቷ ዘልቃለች።
እነ አጅሬ ዛሬ ላይ ተነስተው ክፉ ቢያስቡባት ተንኮል ሴራ ቢሸርቡባት ዕልፍ ጀግኖችን አፍርታለች። ሞቷን ቀርቶ ዕንቅልፏን የማይሹ የቁርጥ ቀን ልጆቿ ዘብ ሊሆኗት ደጀንነታቸውን አስመስክረዋል። ሁሌም ቢሆን ጥቂት እንክርዳዶች በመልካም ዘር መሀል መገኘታቸው አዲስ አይደለም። እነሱን ለቅሞ ከቆሻሻ መደባለቅ ደግሞ አይቀሬ ይሆናል። ዘንድሮ እየሆነ ያለው እውነትም ይኸው ነው። አሜኬላዎችን እየነቀሉ ከጉድጓድ መቅበር፣ እንክርዳዶችን እየለቀሙ ከቆሻሻው መጣል።
ዘንድሮ ለአሸባሪው ቡድን የጥቃት ክንድ በርትቶበታል። በየደረሰበት በጀግኖቹ ሀያላን እየተደቆሰ ነው። እንዲህ በሆነ ጊዜ ተላላኪዎቹ በየደረሱበት እሪታ ያሰማሉ። ቁራሽና ትራፊ ከሚጥሉላቸው ጌቶቻቸው ደጃፍ ቆመውም ኡ.ኡ.ኡ .ኡ .ሲሉ ይንከባለላሉ። ከብለለል፣ ደብለለል… ውይ ሲያሳዝኑ።
ይህ ድርጊት ልማዳቸው ነው። እንዲህ በሆነ ጊዜ እነ አጅሬ ክንፋቸው መሰበሩን እናውቃለን። ምርኳቸው መነጠቁ ይገባናል። ሁሌም ቢሆን ምልክታቸውን አሳምረን እንለየዋለን። አንገታቸውን ሲደፉ፣ እጃቸውን ሲቆረጡ ብሶታቸው ያይላል፣ ለቅሷቸው ይበረክታል፣ ይህኔ ደም ዕንባ እያነቡ እንደራደር፣ እንነጋገር ይላሉ።
እኛ ደግሞ በለቅሷቸው እየሳቅን፣ ‹‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ››ን እንተርታለን። የከያኔውን ስንኝ ደርድረንም ‹‹ሲታሰር ወደ እኔ ሲፈታ ወደ እሱን እናዜማለን። በምንአወቅሽበት.. እያልን፣ መመላለሱ፣ መወላወሉ እንደማይበጅ እያስታወስን፣ እናዜማለን፡ አዎ! አድምቀን፣ አደማምቀን እንዘፍናለን። ይኸው።
በምን አወቅሽበት – በመመላለሱ፣
ሲታሰር ወደ እኔ- ሲፈታ ወደእሱ።
ከሰሞኑ ደግሞ ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን ሲቀምረው የቆየው አገር የማጥፊያ ሰነድ ከህዝብ ዓይንና ጆሮ ደርሷል። በእሱ ቤት የቁም ቅዠቱን፣ የሚፈታበት፣ የህልም እንጀራውን የሚጎርስበት መስሎታል። ጉድ እኮ ነው ! ‹‹በማን ላይ ቆመሽ ..›› አለ ሰውዬው። እውነት ግን
በማን ላይ ተቁሞ ነው ይህ ሁሉ የተንኮል ቅመራ፣ በማን ምድር ላይ ይሆን ይህ ሁሉ ባዶ ፉከራ !
ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን በ‹‹ስልጣን ተቀማሁ›› ሰበብ ያልፈጸመው ግፍና በደል የለም። ይህን ክፋቱን ዕውን ከማድረጉ አስቀድሞም ከአንድ ዓመት በፊት ፊልም የሚመስል ህልሙን የመንደፍ ሂደት አካናውኗል። የዛኔ በድንገቴው ለውጥ ተደናግጠው መቀሌ የመሸጉት የሕወሓት አመራር ተብዬዎች አስገራሚውን ሰነድ ለመቅረጽ ዕንቅልፍ አጥተው ከርመዋል። ‹‹እንሞትልሀለን›› እያሉ በየቀኑ በሚገድሉት የትግራይ ህዝብ ጉያ ተወሽቀውም አገር የማፍረሻ ሰነዱን ቀምረዋል።
አስገራሚው ጉዳይ ዕውን እናደርገዋለን ያሉት መርዛም ሰነድ በጀማሪ ጸሀፊ እንደተሞነጨረ ድርሰት መሆኑ ነው። ‹‹እናሸንፍበታለን›› ያሉት ቅመራም ፈጽሞ አልበጃቸውም። ርቀው ሳይጓዙ፣ ፈጥነው ሳይራመዱ ጠልፎ ጣላቸው። ህልመኞቹ አልሆነላቸውም እንጂ ቅዠታቸው አያሌ ነበር። አሁን ያለውን መንግስት ለመጣል ጠልቀው ቆፍረዋል፡ ርቀው ተጉዘዋል።
እነሱ በአፍሪካ ቀንድ አገራት የሚነሱ ውስጣዊ ችግሮች ጭምር የዕድሚያቸው ማራዘሚያ እንዲሆኑ ሲያስቡ ከርመዋል። ይህ አጋጣሚ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት እንዲዳከምና መቀመጫውን ከኢትዮጵያ እንዲያነሳ በማድረግ ተስፋ ጥለውበት ነበር። ‹‹ልብ ዕንቅርት ይመኛል›› እንዲሉ።
የሰነዱ ሰማንያ ስድስት ገጾች የሕወሓትን የመነሻ መንገድና የፍጻሜውን ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። አሸባሪው ህቅታው ከመታወጁ በፊት ባሰፈረው ምኞቱ ብዙ ትልሞችን አስፍሯል። የትግራይን ዘላቂ ጥቅም በማይነካ መልኩ በድርድር የማይሻገራቸውን አጥሮችን አስቀምጦ ጥቅምና ፍላጎትን ለማሳካት እንደሚሰራ በግልጽ አስቀምጧል።
አሽባሪው ቡድን ባረቀቀው የጥፋት ሰነድ ባለፉት ሁለት ዓመታት በትግራይ ባደረገው ትግል ለብቻው ያካሄደው ምርጫ የዓለምን ቀልብ እንደገዛለት ይተርካል። በዚህም የተፈላጊነቱን መጠን በተወሰነ ደረጃ ከፍ ማድረግ እንደቻለ በእርግጠኝነት ይናገራል።
ጉዳዩ ሁሉ ‹‹ይሉሽን በሰማሽ ገበያ ባል ወጣሽ›› የሚያሰኝ ነው። ሁሌም ራሱን በመካብ ተፈላጊነቱን ከፍ የሚያደርገው ቡድን ዘላለም ካልገዛሁ በሚለው ምኞቱ ዓለምን በማሳሳትና ህዝብን በማታለል ወደር አልተገኘለትም። በዚህ የማንአለብኝነት ጉራውም በኢትዮጵያ ቁልፍ ሀይልና አቅም እንሆናለን የሚል መተማመን እንዳለው አስፍሯል።
አሸባሪው ሕወሓት ከዚህ ተልካሻ ዕምነቱ በዘለለ ወደ አነ አሜሪካ ሻገር ይልና የውስጥ ሀሳቡን ይገምታል። በዘመኑ በነበረው ምርጫ ዴሞክራቶች ሊመረጡ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል እንደሚኖርም ያስቀምጣል። ወደፊት ለሚኖረው ዕቅዱ የባይደንን መመረጥ እንደሚሻው ይናገርና እሱ ከተመረጠም የኦባማ ቁልፍ ሰዎች ወደስልጣን እንደሚመጡ ይገምታል።
አሸባሪው ሕወሓት የአሜሪካ ምርጫ እንዲህ ከሆነለትም ከአገሪቱ ጋር ወደፊት የተሻለ ግንኙነት ለመፍጠር መንገዱ ቀና እንደሚሆን የሚያስቀምጠው ሀሳብ እርግጠኝነት ያለበት ሆኗል። ቡድኑ ከዚሁ ቅዠቱ አያይዞ ከዶናልድ ትራምፕ በኋላ የአብይን መንግስት የሚሰማው እንዳማይኖር ሲናገር በሙሉ መተማመን ነው።
የአሜሪካን መንግስት የራሱን ጥቅም ማዕከል ያደረገ አማራጭ ላይ እንደሚሰራ አውቂያለሁ ያለው የሽብር ቡድን እነሆ ዛሬ ጥቅሙን ዕውን ለማድረግ የህልም ሩጫው ላይ ይገኛል። የሮጠ ሁሉ አያሸንፍ! ያሰበ ሁሉ አያገኝ ሆኖበትም ከገባበት ጉድጓድ ለመውጣት መዳከሩን ይዞታል።
እነ እመት አሜሪካ ዛሬ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል ራስ ወዳድ ቡድን ማግኘታቸው አኩርቷቸዋል። በየቀኑ አቤቱታውን ለመቀበል ጆሯቸው ሰፊ ነውና አሁን ለአረመኔው ቡድን ከለላ ለመስጠት ዋርካቸው ቢሰፋ የሚያስገርምም አይሆንም።
እኛ ግን ትግላችንን ቀጥለናል። ለአገራዊው ጥቅም ማስከበር ዜጎች ሁሉ ዘብ ቆመናል። ዛሬ ቁንጥጫው የበዛበት አሸባሪ ቡድን ህመሙ ሲበዛ ኡኡታውን ቢያሰማ አይገደንም። ሁሉም ነገር ገብቶናልና ካለንበት ሆነን ‹‹ሲታሰር ወደ እኔ ሲፈታ ወደ እሱ›› እያልን እናንጎራጉራለን። ሕወሓት ሆይ! ይሰማል ? ተቀበል!
ከአትጠገብ
አዲስ ዘመን መስከረም 13/2014