ኢትዮጵያ በታሪኳ ከባድ ፈተናዎች አልፋለች:: በአሁኑ ወቅትም ከውስጥ እና ከውጭ ከባድ የሚባሉ ፈተናዎች የተጋፈጠችበት ወቅት ላይ እንገኛለን:: በተለይም ከቀይ ባህር እስከ ዓባይ፤ ከአፍሪካ እስከ ጥቁር አሜሪካውያን የሚዘልቀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በርካቶችን ያስፈራቸዋል፤ ያሳስባቸዋል::
ከዚህም በዘለለ በታሪኳ በቅኝ ገዥዎች እጅ አለመውደቋ እና የድል ታሪኳ ነጮችን የሚያሸማቅቅ ሲሆን ለዓለም ጥቁር ህዝቦች ደግሞ የጀግንነት አርጩሜ ሆኖ ያገለግላቸዋል:: ኢትዮጵያ በጂኦ ፖለቲክሱ ትልቅ ትርጉም ያላት ሀገር ከመሆኗ የተነሳም የበርካቶች የስበት ሀይል ሆና ቀጥላለች:: ታዲያ እነዚህና ሌሎች ነገሮች ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ምን እና ምን ናቸው ስንል ከስትራቴጂክ ጉዳዮች ተመራማሪ ከሆኑት ዶክተር ወሂበእግዜር ፈረደ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ::
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ጉዳይ አውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካ እና ሌሎች ለአንድ ቡድን የወገነ አካሄድ ከምን የመነጨ ነው?
ዶክተር፡– በምስራቅ አፍሪካ እና ቀይ ባህር በአጠቃላይ ቀጣናው ላይ ካለው የለውጥ እንቅስቃሴ፣ የኃይል አሰላለፍ እና ስትራቴጂካዊ ፍላጎቶች ነው:: በተለይ ደግሞ በዚያኛው በኩል ያሉ ስትራቴጂካዊ ፍላጎቶች ምንድን ናቸው ብሎ መለየትና ምን ለውጥ ስለመጣ ብሎ መገንዘብ አሁን ያለውን የእነርሱን አቋምና ሁኔታ ለመረዳት ያግዛል:: የህንድ ውቅያኖስ፣ የቀይ ባህር እና ሜዲትራኒያን ቀጣና ዓለም አቀፋዊ ትኩረት የተጣለበት ቀጣና ነው:: ግዙፍ የንግድ መርከቦች የሚንቀሳቀሱበትና የዓለም ኃያላን ሀገራት መተላለፊያ መስመር ነው:: በዚህ መስመር ደግሞ በበላይነት ተቆጣጥረው መኖር ይፈልጋሉ:: አካባቢው ላይ ያሉ ሀገራት እየተጠቀሙበት አይደለም:: ሆኖም በቀጣናው ያሉ ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ኬኒያ እየተጠቀሙበት አይደለም:: ከፍተኛ ስትራቲጂክ ጠቀሜታ አለው:: በዚህ አካባቢ ላይ ግን እነዚህ ሀገራት ሚናቸው እጅግ በጣም አነስተኛ ነው::
በታሪክ አጋጣሚ ቀጣናውን እንደ መደራደሪያ አድርጋ እየተጠቀመች ያለችው ግብጽ ናት:: በቀጣናው የሚደረጉ ለውጦች፣ መነሳሳቶች፣ ወደ ዴሞክራሲ የሚደረጉ ሽግግሮች፣ ህዝባዊ ብሄርተኝነት ማቆጥቆጥ እንደ አደጋ ተደርገው ይፈረጃሉ:: ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝት ተመልሶ ማንሠራራት፣ ኢትዮጵያ ጠንካራ ሰራዊትና ኢኮኖሚ መገንባት፣ የኢትዮጵያ የድፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት እንቅስቃሴ መጠናከር ብሎም በቀጣነው የሚፈጠሩ ትብብሮችና ትስስሮች እያደገ መምጣቱ በዚህ ቀጣና ፍላጎት ያላቸው አካላት አይፈልጉትም:: በቀጣይ ለሚያደርጉት እንቅስቀሴ እንቅፋት ይሆናል ወይ ደግሞ የቀጣናው ሀገራት መብታቸውን ለማስከበር የሚጠይቁን ነገር ይኖራል ብሎ ስለሚያስቡና በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ይፈጠርብኛል ብለው እንደሚሰጉ መረዳት ተገቢ ነው::
ይህን ለመረዳት ደግሞ ሁለት ሂደቶችን መረዳት አስፈላጊ ነው:: በተለይ ለኤርትራ እንደ ሀገር መወለድ ከኤርትራውያን ጥያቄ በዘለለ ቁልፍ ሚና ስትጫወት የነበረችው አሜሪካ ናት:: ይህ የምናውቀው ታሪክ ነው:: ወያኔ ስልጣን ላይ መንገስ እና አራት ኪሎ በአንቀልባ አዝላ ያስገባችው አሜሪካ ናት:: ይህ ለምን ሆነ ለሚለው ዛሬ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን አቋም ያስረዳል:: ለምን ነበር ይህን ያደረጉት? የሰሩት የታሪክ ደባ እየተጋለጠ ነው:: ወያኔ ከአራት ኪሎ ተባሯል:: ኤርትራ
እና ኢትዮጵያም ወዳጅነታቸውን እያጠናከሩ ነው:: ይህ ማለት አሜሪካ የተከለችው ፕሮጀክት መንቀልና ሴራ ማፍረስ ነው::
ቀይ ባህርን ከአባይ ጋር ማገናኘትም አስፈላጊ ነው:: በጂኦ ፖለቲክሱ ትልቅ ትርጉም አለው:: ቀይ ባህርን ከዓባይ ጋር ማገናኘትና መተንተን ተገቢ ነው:: የቀይ ባህር እና የአባይ ፖለቲካ ግብጽ ላይ ይገናኛሉ:: ሁለቱም በአንድ ነጥብ ላይ ይገናኛሉ:: የቀይ ባህር እና አባይ ፖለቲካ ነጣጥሎ ማየት አይቻልም::
ሌላው ወሳኝ ሁኔታ ደግሞ ዓለም አቀፍ ሁኔታ ከሽብር ዘመቻ ወደ ንግድ የሚደረግ ትንቅንቅ ነው:: አሜሪካ የምትከተለውን ፖሊሲ እና የቻይና ፖሊሲን መመልከት ነው:: በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት እንደተደረገው የሩሲያ ወዳጆች እንዳይበዙ አቅቦ የመያዝ ሥራ ነበር:: አሁንም በተመሳሳይ ቻይና በአፍሪካ ላይ ያላትን ሚና ለመቀነስ የሚደረግ ከባድ ሽኩቻ አለ:: አሁን ባለው ሁኔታ እንደ ቀድሞው ሁኔታ ሶሻሊስት የሆነ ርዕዮተ ዓለም እንዳይስፋፋ ሳይሆን የቻይና ተፅዕኖ አፍሪካ ውስጥ ሥር እንዳይሰድና በአፍሪካ የተፈጥሮ ሃብት መጠቀም ላይ ገድቦ ማቆም የሚል ነው::
ቻይና ደግሞ ወደ አፍሪካ ስትገባ እንደ መግቢያ ያደረገችው ኢትዮጵያን ነው:: በዚህ ረገድ ሲታይ ቻይና እና አሜሪካ ያላቸው ግንኙነት ከቻይና እና አፍሪካ አኳያ ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም:: ቻይና እና አሜሪካ ያላቸው የኢኮኖሚ ግንኙት ከፍ ያለ ነው:: ነገር ግን የቻይናን አካሄድ እገድባለሁ ብሎ ማሰቡ ብዙም ሊያስኬዳት አይችልም:: ሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ትስስር አላቸው:: በመሆኑም ቻይና እና አሜሪካ ያላቸውን ግንኙነት በዚህ ደረጃ ለማሻከር ብትሄድ አሜሪካንም ብዙ አያስኬዳትም፤ ደግሞ ብዙም ተጠቃሚ አትሆንም:: በሌላ ጎን ደግሞ አሜሪካ እና አፍሪካ ወዳጅነትም ስር የሠደደ ነው፤ በብዙ ነገር ተሳስረዋል:: ይህ ወሳኝ ባይሆንም እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀስ ነው:: እነዚህ ምክንያቶች በጣም ወሳኝ ናቸው::
ከዚህ በዘለለ ሌላው ነጥብ ታሪካዊ ምክንያት ሲሆን የዓድዋ ድል ፖለቲካ ነው:: ይህ ከአሜሪካ ሀገር ውስጥ ፖለቲካ ጋር የሚያያዝ ይሆናል:: የጥቁር ብሄርተኝት መነሳሳት ከዓድዋ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም:: ባለፈው ዓመት በአሜሪካ በነጭ ፖሊስ የተገደለው ጥቁሩ ጆርጅ ፍሎይድ ግድያ የሚያሣየው የጥቁሮች ጥያቄ አለመቆሙና ፖለቲካው ላይ ያለው ጫና ነው:: አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እንኳን በብዛት የምትልከው ጥቁር ዲፕሎማቶችን ነው:: ይህ የሚያሳየው ጥቁሮች እንኳን አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን አቋም ደግፈዋል ለማስባል ነው:: የጥቁር ብሄርተኝትን ለማስቆም የሚረዳና እና ትርጉም አለው ተብሎ ይታሰባል:: በዚህ ረገድ ደግሞ ኢትዮጵያ በጥቁሮች ፖለቲካ በቀዳሚነት የምትነሳ ሀገር በመሆኗ ተጽዕኖ አለው:: በአጠቃላይ የእነዚህ ድምር ውጤቶች ናቸው አሜሪካ እና አውሮፓውያን ኢትዮጵያ ላይ ይህን አቋም ለመያዝ የገፋፋቸው::
እነዚህ ጫናዎች ለመፍጠር ደግሞ ከውስጥ ተዋናይ ይፈልጋል:: እነዚህ ደግሞ በራሳቸው ህልውና የሌላቸውና ጥገኛ የሆኑ ናቸው:: ለዚህ ደግሞ ሕወሓት እና ኦነግ ሸኔ እና ሌሎችም አሉ:: እነዚህ መልካም አጋጣሚ ተፈጥሮላቸው ከፍተኛ ቀውስ እንዲፈጠር እያደረጉ ነው::
አዲስ ዘመን፡- የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ሃብታቸውንና መብታቸውን ከሚጠቀሙት በላይ በቀጣናው ግብጽ በበላይነት ተጠቃሚ እንድትሆን የተደረገው ለምንድን ነው?
ዶክተር ወሂበእግዜር፡– ለዚህ ሲባል ሆን ተብሎ ሶማሊያ እንድትፈርስና እንድትዳከም ተደርጓል:: ኤርትራን ራሳቸው ፈጠሯት፤ ከዚያም በማዕቀብ በጣም አዳከሟት:: ኢትዮጵያንም ለማዳከም ብዙ ሰርተዋል::
ይህ ዞሮ ዞሮ ግብጽ የቀይ ባህርን እና የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ላይም መሰረት ሆና ትልቅ ሚና ትጫወታለች:: የግብፅ ደህንነትና መከላከያ በሙሉ አሜሪካ ሠራሽ ነው:: አሜሪካ ካልፈለገች ግብጽ ማዳከም ትችላለች:: የግብጽ ውስጠ ሚስጥሯ ስለሚታወቅ ይህን ያክል አታመልጣቸውም:: በመሆኑም በዚያ የተነሳ ግብጽ ይዘዋል:: በአንድም በሌላም ከላይ ያነሳነው ዓድዋ ስሜት ከተነሳ ሃያል የመሆንና ማሸነፍ ዕድል አለው:: ይህ ቀጣይ ከተነሳ እና የንግድ ቀጣናውን ከተቆጣጠረ ማስከፈሉ አይቀርም:: ዋናውን የዓለም ጉሮሮ ተያዘ ማለት ነው:: ይህን ስትራቴጂክ ጥቅም እንዲይዙና የበላይ እንዲሆኑ ውስጣዊ ችግሮችን በመፍጠርና በችግር በማጠር ኖረዋል:: አካባቢው ሙሉ ለሙሉ እንዲረበሽ አይፈልጉም:: ከፍተኛ ስደትም እንዲፈጠርና አሸባሪነት እንዲያንሰራፋ እንዲኖርም ስለሚያደርግ ይጠነቀቃሉ:: አካባቢው በአንድም ይሁን በሌላ ከእጃቸው እንዲወጣ አይፈልጉም:: በሌላ ሃሳባቸው ደግሞ እርስ በእርስ በሚናከሱና በቀጣናው ትንንሽ ሀገራት እንዲፈጠሩ ይፈልጋሉ::
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው አካሄድና እሳቤ ምዕራባውያን የሚፈልጉት በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስት ለውጥ ውይስ ኢትዮጵያን መበታተን?
ዶክተር ወሂበእግዜር፡- ሁለቱንም አስበዋል፤ መጀመሪያ በሀገሪቱ የመንግስት ለውጥ ማምጣት ሲሆን ከዚያ ቀጥሎ እርስ በእርስ እየተፋጁ ኢትዮጵያ ወደ ትንንሽ ሀገራት እንድትከፋፈልና እንድትፈርስ ነው:: የዓድዋ ፖለቲካም ፍፃሜ ማግኘት አለበት ብለው የሚያስቡት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ነው:: ይህ ደግሞ ለሁለተኛው ለሚጀምረው ቀኝ አገዛዝ ሥርዓት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል:: እንደሚታወቀው በኮረና ወረርሽኝ እና ሌሎች በሽታዎችም የዓለም ኢኮኖሚ እየደቀቀ መጥቷል:: በዚህ ላይ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የሃብት ጥማት አለባቸው:: ይህን የሚያገኙት ደግሞ ከአፍሪካ ነው:: በመሆኑም የተፈጥሮ ሃብትን ለመበዝበዝ እና ሃብቱን ለማግኘት አፍሪካ ላይ ማተኮርና ሌላ ችግር መፍጠር ነው ዓላማቸው:: እጅግ የሰፋ ጥሬ እቃ ግብዓት የሚገኘውም ከዚሁ አህጉር ነው:: በማህበረሰባቸው ደግሞ ከፍተኛ ፍጆታ ጠያቂና ሁሉን ነገር ፈላጊ ሆነዋል:: ይህን ጥማት ለማርካት በራሳቸው ሃብት የላቸውም:: በዘላቂነት ችግራቸውን ለመመከትና የሚነሳባቸውን የህዝብ አብዮት ለመቀልበስ አማራጫቸው ይህ ነው::
ለዚህ ያመቻቸው ዘንድ ደግሞ በሁለት እግር የማይቆሙ ነገር ግን በእርዳታ ላይ ብቻ የተመሰረቱና ጥገኛ ትንንሽ ሀገራት እንዲኖሩ መሥራት አለባቸው:: በኢኮኖሚና ፖለቲካም ጥገኛ የሆኑ ሀገራት መፍጠር ነው:: ይህም ለሃብት ምዝበራ ይመቻቸዋል:: በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በዓለም ላይ ያሉ ሀገራት ከ50 አይበልጡም ነበር:: በአሁኑ ወቅት ሀገራት 200 አልፈዋል:: በዚህ መንገድ ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ስለሆነችም መከፋፈል አለባት ብለው ነው አቅደው የተነሱት::
ሌላው ቀርቶ የፖለቲካ እና ታሪክ ፀሃፊ የሆነው ጆን ማርካኪስ (John Markakis) የተባለው ጸሃፊ እንዳለው፤ ‹‹እየሱስ ክርስቶስ በኢትዮጵያ እንኳን ቢነግስም ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሀገር መሆን አትችልም›› ብሎ ፈርጇታል:: ስለዚህ ያላት አማራጭ መፍረስ ነው ብሎ ነው የተነሳው:: ይህን ኢትዮጵያን የማፍረስ ፕሮጀክት ደግሞ በምሁራን ጭምር በአጀንዳ ይዘውታል:: ለዚህ ቅድመ ሁኔታ ደግሞ ኢትዮጵያ ትፍረስ ብለው የሚያቀነቅኑ ቡድኖችም ወይንም ፀረ-ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲፈጠሩ ተደርጓል:: ሕወሓትም ሲከተል የነበረው ይህንኑ ነው::
የኢትዮጵያ የስበት ማዕከል የሆነውን ሀገር መከላከያ ሰራዊት መምታት ደግሞ የዚሁ ስትራቴጂ ትልቁ ሥራ ነው:: በመሆኑም በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ለተፈጸመው ክህደት ታላላቅ ሀገሮች እጅ አለበት:: ባገኘነው መረጃ መሠረት በአሁኑ ወቅትም ከሸሸው ኃይል ጋር አብረው መቐለ ሆነው ይህንኑ የሚሠሩ አሉ:: ቀደም ሲልም ትግሉ ከብሄር ወደ መንግስት ለውጥ እንዲቀየርም ሲሠሩ ነበር:: አሁን እየተካሄደ ያለው ጦርነትም ከአንድ አሸባሪ ቡድን ጋር ሳይሆን የውክልና ጦርነት ነው:: ቀለል ተደርጎ እንደሚወራው አይደለም:: በዚህ ውስጥም በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ የሚሳተፉ አሉ:: መረጃ በማቀበል፤ ሎጂስቲክስ በማስታጠቅ፣ የደህንነት ድጋፍ በማድረግ ያሰፈሰፉ ኃይሎች አሉ:: ይህን መንግስትም ይረዳዋል:: ለዚህም ነው ጦርነቱ ቀላል የማይሆነው:: ጦርነቱ በአሸባሪ ሕወሃት እና በአማራ ልዩ ኃይል ወይንም በአፋር ልዩ ኃይል መካከል ብቻ ተደርጎ መውሰድ ነገሩን በሚገባ ካለመረዳት የመነጨ ሊሆን ይችላል:: በዚህ ደረጃ መታሰቡም ትልቅ ስህተት ነው:: የጦርነቱን ባህሪ፣ መጠን እና ግብ የመረዳት ችግሮች አሉ::
አዲስ ዘመን፡- ጦርነቱ ወልቃይ ጠገዴ፤ ራያ እና የመሳሳሉ ቦታዎችን ለመያዝ ነው ብለው የሚያቃልሉ አሉ:: እውነታው ይህ ነው?
ዶክተር ወሂበእግዜር፡- ይህ በጣም የተሳሳተ ግንዛቤ ነው:: ለወያኔ ራያ እና ወልቃይት ቢሰጠው የመጨረሻ ፍላጎት ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ነው:: መዳረሻው ምንድን ነው ካልን መጨረሻ ዓላማው የትግራይ ሪፐብሊክ መመስረት ነው:: ይህን ደግሞ የምናደርገው በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ነው ብሎ የወሰነው:: ነገር ግን ኃያል የሆነች ኢትዮጵያ ካለች እኛ ላይ ጫና ትፈጥራለች ብለው ነው የተነሱት:: ይህን የማይረዳ ካለ አሳዛኝ ነው:: ትግሉ የመንደር ትግል ሳይሆን ቀጣናዊ ኃይሎችን ያስተሳሰረ የውክልና ጦርነት መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ሊገነዘብ ይገባል:: የመጨረሻ ዳፋው ደግሞ ኢትዮጵያን ትንንሽ አድርጎ ማለፍ ነው:: አሁን የሚጠበቅብን ኃላፊነት ካልተወጣን አደጋው የከፋ ይሆናል:: የመሬት ማስመለስ ብሎ ነገሩን ማቃለል ተገቢ አይደለም:: ይህ ቢሆን ኖሮ የሀገር መከላከያም በዚህ መስዕዋትነት ውስጥ መግባት አይጠበቅበትም ነበር:: በአጠቃላይ መሬት ላይ ያለውን እውነታ እና ሁኔታ በደንብ መገንዘብ ይገባል::
አዲስ ዘመን፡- የአረብ ሀገራትን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሚደግፉ ሀገራት አሉ:: በሌላ በኩል እነዚህ ደግሞ ከአሜሪካም ጋር ጥልቅ ወዳጅነት የፈጠሩ ናቸው:: ይህ እንዴት ይታያል?
ዶክተር ወሂበእግዜር፡- ልክ ነው:: ሳውዲ አረቢያ ኢትዮጵያ ውስጥ ከማን ጋር ነው የተሰለፈችው፤ ከየትኛው ቡድን ጋር ነው ብሎ ማሰብ ይገባል:: ፍላጎቷ ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው:: ይህን አቋም በሚገባ መመርመርና መረዳት ይጠቅማል:: የኢትዮጵያ ወዳጅ ያልናቸው በሙሉ ስትራቴጂክ ግብና ፍላጎት አላቸው:: ግባቸውን ለማሳካት ብዙ ዘዴ ይከተላሉ:: አንዱ ጊዜያዊ ወዳጅነት ፈጥረው ፍላጎታቸውን ማሳካትና የእኛን አካሄድ መረዳት ነው::
ለመሆኑ እነዚህ ሀገራት የሚፈልጉት በውስጧ ችግር የበዛባትን ኢትዮጵያ ወይስ ጠንካራ ሀገር፤ ጠንካራ ኢትዮጵያ ነው የሚፈልጉት? አንዳንዶቹ ደግሞ የአንዱን ተዋናይ ተጠግተው የኢትዮጵያ ፍላጎት አስመስለው የሚንቀሳቀሱ አሉ:: በቀይ ባህር አካባቢም ብዙ ፍላጎት ያላቸው ሀገራት አሉ:: ከአሜሪካ ጋርም ሆነ ከቀጣናው ሀገራት ጋርም የሚወዳጁት ብሄራዊ ጥቅማቸውን በማሰብ ነው:: በመሆኑም ከራሳቸው ጎራ ኢትዮጵያን የማሰለፍ ፍላጎት ቢኖራቸውም ከአሜሪካ ፍላጎት በተቃራኒ ይቆማሉ ብሎ ማሰብም የዋህነት ነው::
አዲስ ዘመን፡- ጫናው የበረታው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ተመልሰው ይዋሃዳሉ ብለው በመሥጋት ይሆን?
ዶክተር ወሂበእግዜር፡– አንደኛው የተቃርኖ መሠረት የታሪክ ተጋላቢጦሽ ይመጣል ብለው ነው:: አሜሪካ እና ሌሎች የሰሩትን ሴራ እና ስህተት ተመልሶ ይገለበጣል ብለው ይሰጋሉ:: የለፋንበት ሴራ ይከሽፋል ብለው ይፈራሉ:: አንድ መሆን እና አለመሆን የሁለቱ ሀገራት ውሳኔ እና አካሄድ ይወስነዋል:: ነገር ግን በራሱ ሁለቱ ሀገራት ወደ ሠላማዊ መንገድ መምጣታቸው ስኬት በመሆኑ ምቾት አይሰጣቸውም::
አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ ላይ በማማተራቸው ምዕራባውያን ተንታኞች በጣም ሲተቹት ነበር:: ይህስ ከምን የመነጨ ነው?
ዶክተር ወሂበእግዜር፡- አዎ! እንዲያውም ‹‹የእርኩሳን ህብረት›› ብለውታል:: ይህን ማድረግ ለምን አስፈለገ ብለን እንጠይቅ:: በቀጣናው የበላይነት እንዲመጣ አይፈልጉም:: በቀጣናው አምባገነንነት ይሰፍናል ብለው ይናገራሉ:: ለመሆኑ ሕወሓት በቀጣናው ምን ሲሠራ ነበር፤ የመላዕክት ስብስብ ነበርን? በአጠቃላይ ምዕራባውያን ፍላጎታቸው ከተነካ ወይንም የሚነካ ከመሰላቸው ሥም ከማጠልሸት በዘለለም የሚቻላቸውን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አይመለሱም::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር ግንኙነቷን ማጠናከሯስ ለቀጣናው ፖለቲካ ፋይዳው ምንድን ነው?
ዶክተር ወሂበእግዜር፡- ጥሩ ነው:: በትንሹ መጀመር ጥሩ ነው:: ቱርክ እና ግብጽ በሊቢያ ጉዳይ የነበራቸውን የተለያ አቋም ማወቅ በቂ ነው:: ለጊዜው ፍቱን መድሃኒት ነው:: ግን ቱርክ ስትራቴጂክ አጋር ናት ወይ ብሎ ማሰብ ይገባል:: በርዕዮተ ዓለምስ እንዴት አብሮ መሥራት ይቻላል፤ አብረን ለመስራት እንስማማለን ወይ ብለን ማሰብ ይገባል:: ነገር ግን አሁን ባለው የውክልና ጦርነት ጠቃሚ አጋር ናት:: ሌላው በሱዳን በኩል እየሆነ ለሚደረገው ነገር ቱርክ አስፈላጊ ናት:: በእርግጥ ሱዳን ውስጥ አሁን የሚታየው ፀረ
ኢትዮጵያ አቋም ሱዳን ውስጥ የተፈጠረ አስተሳሰብ ወይንም ሀገር በቀል ሳይሆን የሌላ አካል ፍላጎት ያለበት መሆኑን መረዳትና እንደአስፈላጊነቱ መያዝና መከታተል ይገባል::
ሱዳን ውስጥ ሰፊ የእርሻ መሬት አለ:: በርካታ አረብ ሀገሮች ይህን መሬት ይፈልጋሉ:: ለእርሻው ደግሞ ውሃ ምንጭ የምትሆነው ኢትዮጵያ ናት:: ለዚህም ሲባል ስትራቴጂክ የሆኑ ጉዳዮችን መመልከትና በጥንቃቄ መረዳት ተገቢ ነው:: በሱዳን ያለው የፖለቲካ ቀውስ ኢትዮጵያን እንደ ወዳጅ የሚያይ አለ:: በተለይ ጥቁር ሱዳናውያን ኢትዮጵያን በጣም ይፈልጋሉ:: ሱዳን አሁን የምትከተለው አካሄድ የውጭ ጫና አለበት:: ይህም የሚመጣው ከግብጽ እና ከአሜሪካ ነው:: በሱዳን አጠቃላይ ወታደራዊ ኃይል ውስጥ ገብተዋል:: የሱዳን ደህንነት ክንፉም በግብፅ እጅ ይዘዋወራል:: በሱዳን ያለው የሲቪል መንግስቱም ያን ያህል አቅም የለውም:: ሚዛኑ ወደ ወታደሩ ያደላ ነው::
አዲስ ዘመን፡- የሱዳን ወታደራዊ ልምምድ፣ ዝግጅትና ትንኮሳ ኢትዮጵያን ለመውረር ያሰበች አይመስልም?
ዶክተር ወሂበእግዜር፡– በዘላቂነት እንደማይጠቅማት ሱዳን ታውቃለች:: በውስጧ ብዙ ችግሮች አሉባት:: ውስጣዊና ውጫዊ ጫና አለባት:: በተለይ ግን የውጭው ጫና ኢትዮጵያ ጋር እንድትቃረን እያደረጋት ነው:: ሱዳን ይህን ስሌት ሰርታ የገባችበት አይመስለኝም:: በውጭ ግፊትና ጫና ለዚህ እየገፋፋት ነው:: ውስጣዊ ችግሮቿን እንኳን ለማቃለል ዕድሉን አላገኘችም:: በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የሱዳን አቋም ምንድን ነው ብለን ብንመለከት ግልጽ የሆነ አቋም የላትም:: በግብጽ ሳንባ የሚተነፍሱ ናቸው:: አሁን ደግሞ በአሜሪካ ሳንባ ሆኗል::
በሱዳን በኩል የኢትዮጵያን ግዛት የሆነው ቤኒሻንጉልን ጉሙዝ ክልል የእኔ ነው የሚለው እሳቤም ኃያላን ሀገራት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ለሚያደርጉት ሂደት አጋዥ ለማድረግ በውጭ ተጽዕኖ የመጣ ነው:: በአጭሩ ለኢትዮጵያ አዲስ ካርታ ተሰርቷል:: ግማሽ ሶማሊያ፣ ግማሹ ሱዳን፤ ግማሹ ኬኒያ እንዲሆን ነው:: ይህ ከሆነ ደግሞ በድንበር ይገባኛል እሰጣ እገባ ውስጥ እንድትሆንና እንድትቆረቁዝ ነው:: ይህን ሁሉ አስበንና ጠንክረን መሥራት አለብን::
አዲስ ዘመን፡- ቱርክ የኔቶ አባል ናት:: በአሰራራቸው ደግሞ አባል ሀገራት በመተባበር በጋራ ጥቅም መሥራት እንጂ መፃረር እንደሌለባቸው ይገልፃል:: ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ እና ቱርክ ግንኙነት ፈተና አይገጥመውም?
ዶክተር ወሂበእግዜር፡– ልክ ነው:: በዚህ በኩል አሜሪካም እዚህ ውስጥ አለች:: ግብጽን እየረዳች ነው:: ለመሆኑ አባል ሀገራት ይተማመናሉ ወይ የሚለውን ማሠብ ይገባል:: ቱርክ ከኢትዮጵያ ጋር ስትወዳጅ ከአሜሪካ ተቃርኖ ቆማ መሆኑ እሙን ነው:: ዞሮ ዞሮ ግን ቱርክ የግብጽ ማንሰራራት አትፈልግም:: በመሆኑም አመቺ ሁኔታ መጠቀም ትፈልጋለች:: ነገር ግን በመርህ ደረጃ ከሆነ ብዙ ነገር አለ:: አሁን ዓለም ላይ ሥርዓት አልበኝነት ሰፍኗል:: ይህ ባይሆን ኖሮ ችግሮች ባልተከሠቱ ነበር::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረት መስራች ሀገር ናት:: መሥራች እንደመሆኗ መጠንና በዚህ በኩል ወዳጅ በማፍራት ተፅዕኖ መፍጠር አትችልም?
ዶክተር ወሂበእግዜር፡– የአፍሪካ ተቋማትና ሀገራት ያሉበት ቁመና ይታወቃል:: ብዙ ቀውሶችን መፍታት ሲገባቸው ሌሎች ኃያላን ሀገራት እንዲገቡበት እያደረጉ ነው:: ለአፍሪካውያን መፍትሄ በአፍሪካውያን የሚል እንቅስቃሴው መነሻው ይህ ነው:: ግን በደንብ አልተሰራበትም:: ይህን ከማድረግ በዘለለ የጥቁር ብሄርተኝነትም ኢትዮጵያ በሰፊ ልትሰራበት ይገባል:: ይህ እስከ አሜሪካ ድረስ በመዝለቅ ብዙ ውጤት ያስገኛል::
በአሁኑ ወቅት የሚካሄደው የውስጥ ትግልም ዋንኛ መዘዙ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው:: ግብጽ በዚህ ወቅት በውክልና ጦርነት እየተሳተፈች መሆኑ መረዳት ወሳኝ ነው:: አሜሪካም ፀረ ኢትዮጵያ የሆኑ አካላትን በመደገፍ ዓላማዋን ለማሳካት ብዙ ትለፋለች:: በመሳሪያ እና ሳተላይት መረጃ በማቅረብም መደገፋቸውንም ይቀጥላሉ:: ነገር ግን እንደ አፍጋኒስታን ቀጥታ ጦርነት በቀጥታ ላይ አይገቡም:: ነገር ግን ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ከተጠናከረች እና ከገፋችበት ሉዓላዊነቷን አስከብራ መቀጠል ትችላለች::
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ሙያዊ ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ሥም አመሰግናለሁ::
ዶክተር ወሂበእግዜር፡- አመሰግናለሁ::
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን መስከረም 12/2014