በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ለቀረው የሰኔ 14 ብሔራዊ ምርጫ ድምጻቸውን ሰምቼ የማላቃቸው ብዙ ፓርቲዎች እንቦቃቅላ ፓርቲዎች ብቅ ብቅ ብለዋል። ፓርቲዎች ብቅ ብቅ ማለታቸው የፖለቲካ ምኅዳሩን ያሰፋዋል። ስጋቴ ግን ፓርቲዎቹ ምርጫ ሲመጣ የሚቋቋሙ ምርጫ ሲወጣ የሚከስሙ መሆናቸው ነው።እስካሁን በነበረው የሀገራችን ሂደት ምርጫ ሲደርስ አለን ብለው ብቅ ምርጫ ሲጠናቀቅ ድምጻቸው ጠፍቶ ጥልቅ የሚሉ በርካታ ፓርቲዎችን አይተናል።
ፓርቲዎቹ ዘላቂ መሆን አለባቸው እንጂ ጠላቂና ታይቶ ጠፊ መሆን የለባቸውም። እርግጥ ነው ደጋፊ አባላትም ያስፈልጋሉ ፤እንደ እግር ኳስ ክለቦች ። ደጋፊ ከሌላቸው የገቢ ምንጭ ካጠራቸው ሊከስሙ ይችላል፤መንግሥትም በተመጣጣኝ ዋጋ ቢሮ እንዲያገኙ ማድረግ ይጠበቅበታል።ይህ ግን የሚሆነው አመራሮቹ ሲጠነክሩ ብቻ ነው። የፓርቲዎቹም ስም በየጊዜው ስለሚቀያየር አዲስ የሚመስሉም አሉ።አመራሮቹ ራሳቸው ሆነው የነባሩን ፓርቲ ስም ቀይረው እንደ አዲስ ብቅ የሚሉ ለቁጥር የሚታክቱ ናቸው።ይህን ደግሞ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ በፈረሰው ፓርቲ አመራር የነበሩ በአዲሱ ፓርቲም አመራር የሆኑ ሰዎችን ፊት ማየት የተለመደ ነው።
ፓርቲዎቻችን አሁን ለብሔራዊ ምርጫ ይወዳደራሉ፤የእነዚህ ፓርቲዎች መገለጫ ከሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ሁልጊዜም ለወቀሳ የተዘጋጁ መሆናቸው ነው።ወርቅ ቢዘንብ ማመስገን የሚሉትን ነገር ሲያልፍም አይነካካቸውም።በራሳቸው ፓርቲ ውስጥ ዴሞክራሲን ሳያሰፍኑ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የሚሹ ህልመኞች ናቸው። በሀገር ያልነበረው ኦነግ በደርግና በኢህአዴግ ሲሳደድ የነበረ ነው። ሀገር ውስጥ ሲገባ የተሻለ ሆኖ መገኘት ነበረበት ግን ተሸነሸነ። ዛሬ ብናየው እንኳን ለመረዳት አዳጋች የሆነው አሸባሪው ሸኔ በኦነግ ውስጥ የነበረ ነው። ሸኔ ማለት በአፋን ኦሮሞ አምስት ማለት ነው፤በኦነግ ስም ቢያንስ ወደ አምስት ፓርቲዎች ተመሥርተዋል። እነሱም በውስጣቸው የአመራር ምርጫ የለም ቢኖርም በዕድሜ ይፍታህ መሪነት የሚቀመጡ ናቸው። አዲስ የአመራር ፊት አይታይም፤በውስጣቸው ምርጫ ሳይኖራቸው አውራውን ፓርቲ አውሬ ነው አምባገነን ነው ሲሉ ግን ይሰማሉ።
የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ቅርስ የሆነው የገዳ ሥርዓት የአመራር ስልት በፓርቲያቸው ውስጥ ተግብረው ሊያሳዩን ያልቻሉ በአፍቅሮተ ሥልጣን የተጠቁ ናቸው።በሥልጣን ሽኩቻ ነው፤ ፓርቲው ብዙ ቦታ ሊሸነሸን የቻለው።ኦነግና ኦብኮ በምርጫው አንወዳደርም ብለዋል።እንደፓርቲ ተወዳድረው የሚይዙትን ይዘው ቢያለቅሱ ይሻላቸው ነበር፤ለዴሞክራሲውም ይበጃል ።ለሀገሪቱ ፖለቲካ አንዲት ነገር ጠብ የሚያደርጉት በምርጫ ውስጥ ሲወዳደሩ ነበር። የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲም የሚባልም ሰምቻለሁ ፤ስሙ ደስ ይላል ።እሱ እንኳን እንደ ገዳ ሥርዓት በስምንት ዓመት የተገደበ የፓርቲ አመራር ምርጫ ያሳየናል ብለን ብንጠብቅም የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ።በግሌ የኦሮሞን መብት እናስከብራለን የሚሉ ፓርቲዎች የገዳን የአመራር ሥርዓት ፓርቲያቸው ውስጥ ተግብረው በምርጫ አመራር እየቀየሩ ዴሞክራሲያዊነትን እንዲያሳዩን የዘወትር ምኞቴ ነው።ሆኖም ግን አብዛኞቹ የሀገራችን ፓርቲዎች ሀገር በቀል ዕውቀትን ተጠቅመው ፖለቲካችንን ቤተኛ ማድረግ ሲገባቸው ከውጫቸውም ከሀገሩም ሳይሆኑ ሜዳ ላይ የቀሩ ብዙዎች ናቸው።
ቀጣዩ የተወካዮች ምክር ቤት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚቀላቀሉበት “የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ ያስታውቃል” እንደሚባለው ብሂል ጅማሮው ያሳያል። ይህም ምክር ቤቱ በውይይት የሚደምቅበትና የሃሳብ ክርክር የሚኖርበት ተመልካችንም አድማጭንም የሚስብ ይሆናል እንጂ ፤መቼም እንደተሰናባቹ ምክር ቤት አባላት ሃሳብ የማያወጡ ጣት ብቻ የሚያወጡ ይሆናል ብዬ አልገምትም። አንዳንድ ጊዜ እኮ በቴሌቪዥን ጣታቸውን አውጥተው ሳየው አስተማሪ ተማሪዎችን ጠይቆ ምላሽ ሊሰጡ እጅ ያወጡ ተማሪዎች ሁላ ይመስሉኛል።
እርግጥ ነው ያለንበት የለውጥ ዘመን የፖለቲካ ምህዳሩ የሰፋበት በውጭ የነበሩ እና በየድንበሩ አልፎ አልፎ ሲታገሉ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገር ወስጥ የገቡበት ጊዜ ነው።ምን ያህል ውጤታማ ነበሩ የሚለውን እናንሳው ።አንዳንዶቹ ደግሞ አዳዲስ ፓርቲዎች ናቸው፤ ማለቴ ምርጫው ሲደርስ የሚቋቋሙ ።የተወሰኑት ደግሞ ተኝተው ተኝተው ምርጫ ሲደርስ ብቻ ከእንቅልፋቸው የሚነቁና እንደ እሳት እራት ለቀናት ብቻ ቆይተው የሚያሸልቡ ናቸው።ሁሉነገራቸው የጥድፊያና የችኮላ ስለሆነ ስማቸው ሳይቀር ራሱ በግሌ ያስቀኛል፤ አክስት አጎት በሚል መሰል ስያሜ ለምርጫ የተቋቋሙ አሉ።ስማቸውን በየጊዜው የሚቀያይሩ አሉ።ትላንት ህብረት ከነበረ ዛሬ አንድነት ፤ትላንት ውሃ ከነበረ ዛሬ ወንዝ የመሳሰሉ ስም በማውጣት ከምርጫ በረከቱ ተቋድሰው ለማለፍ የሚታትሩ እንደአሸን የፈሉ ፓርቲዎችን ተመልክተናል።
እነዚህ ፓርቲዎች እንደጤዛ ታይተው የሚጠፉበት ምክንያት ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም ከምርጫው ግርግር የሚገኙ ጥቅሞችን አልመው የሚቋቋሙ ፓርቲዎች እንዳሉና ያችንም ተቃምሰው በመጡበት የሚጠፉ እንዳሉም ለማንም የተሰወረ አይደለም።ሆኖም እነዚህ ፓርቲዎች ትንሽ ዕድሜያቸውን አራዝመው ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም ሥራ ቢከውኑ በተወሰነም መልኩ ቢሆን መኖራቸው ትርጉም ይኖረው ነበር። ችግኝ ለመትከልና በበጎ ሥራ ውስጥ እኮ ለመሳተፍ የማንንም በጎ ፍቃድ አይጠይቅም።
ያለነው ምርጫ ዘመን ውስጥ ነው ፤ ለዚያው የአፍሪካ ምርጫ በሚባልለት አህጉር ፤የአፍሪካ ሀገሮች እንደነገሩ ምርጫ ያደርጋሉ፤እንደነገሩ አሸነፉ ይባልላቸው። በዚህ ዓይነት ረጅም ዘመን የተቀመጡ የአፍሪካ መሪዎች ነበሩ አሉ፤ምናልባት ወደፊትም በዚሁ ካልተገታ ሊቀጥሉ ይችላሉ።ቀደም ሲል አፍሪካ የምትታወቀው ሰሞኑን በማሊ እንደተከሰተው ተደጋጋሚ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ነበር ። ተደጋጋሚ መፈንቅለ መንግሥት ያጋጥማት የነበረችው አፍሪካ አሁን ወደ ምርጫ ፊቷን አዙራለች።ቀስ በቀስ የምርጫ ሥርዓቱም ፈር እየያዘ ይሄዳል ብለን እንጠብቃለን። ድኅረ ምርጫ ደግሞ አውራው ፓርቲና ጭራ ፓርቲዎች አሸናፊ ነኝ በሚል ይጋጫሉ።ሰዎች ይሞታሉ ይቆስላሉ ንብረት ይወድማል።
በእኛ ግን እንዲህ እንዳይሆን የፀጥታው አካል ፓርቲዎች ሁሉ ወገባቸውን ታጥቀው ከወዲሁ መንቀሳቀስ አለባቸው።ችግሮች ካሉ በምርጫ ቦርድና በፍርድ ቤት በኩል መፍታት ብልህነት ነው።የአንድ ሀገር ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የዴሞክራሲ ማረጋገጫ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ገለልተኛ መገናኛ ብዙሃን ፍርድ ቤት ፖሊስ አጋዥነት ግድ ነው። ዜጎች የሚገብሩበትን የህዝብ መገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁበት የተደረገው ለምርጫው ስኬታማነት ይረዳ ዘንድ ነው።ስለዚህም ከአንድ ወቅት የምርጫ ሆይሆይታ ወጥተን ሀገራችን እንድትሻገር የበኩላችንን ሚና እንወጣ።
ይቤ ከደጃች.ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2013