ለግብርናው ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረት ተከትሎ ምርትና ምርታማነት በየአመቱ እያደገ ነው፡፡ የአርሶ አደሩም ሕይወት በዚሁ ልክ እየተለወጠ ይገኛል፡፡ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦም አሁንም ከፍተኛ ነው፡፡ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ ኢንዱስትሪው በተለይ የአገልግሎት ዘርፉ ጉልህ ስፍራ እየያዙ ቢመጡም ግብርናው 40 በመቶውን እየሸፈነ ነው፡፡
ይሁንና ግብርናው በሚጠበቅበት ልክ እየተጓዘ ነው ወይ የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ፣ መልሱ አይደለም የሚል ነው፡፡ ችግሩ አንድም ከዘርፉ አለመዘመን ጋር ይያያዛል፡፡ ሀገራችን ዛሬም በእንስሳት ጫንቃ ላይ ተመስርታ ነው ግብርናዋን እያካሄደች የምትገኘው፡፡ ባለሀብቶች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ቢሰራም የተፈለገውን ለውጥ ማምጣት አልተቻለም፡፡
ግብርና የሚጠበቅበትን እየተወጣ ላለመሆኑ ስንዴ በቢሊዮን ዶላሮች እየወጣ የሚገባዘበት ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ሀገሪቱ ስንዴ ለማምረት የሚያስችል መሬትም ስነ ምዳርም እያላት ነው ለተለያዩ የልማት ስራዎች ከሚያስፈልጋት ላይ የውጭ ምንዛሬ እያወጣች ስንዴ የምትገዛው፡፡
የግብርናው አለመዘመን ግንባታቸው እየተካሄደ ለሚገኘው የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎችም ስጋት ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎቹ የግብርና ምርትን በግብአትነት የሚጠቀሙ እንደመሆናቸው ይህ ግብአት በሚፈለገው መልኩ ካልተገኘ ከኢንዱስትሪዎች የሚጠበቀውን ማሳካት ያዳግታል፡፡
ይህ ሁሉ ግብርናውን ይበልጥ የማዘመን አስፈላጊነትን ያስገነዝባል፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም የግብርናውን መዘመን አስፈላጊነት በተደጋጋሚ አስገንዝበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በመስኖ እርሻ ላይ በትኩረት የመስራት አስፈላጊነትን የሀገሪቱን የውሃ ሀብት በመጠቀም በረሃዎቻችን ገነት ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡ የሚቀጥለው በጀት አመትም በመስኖ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡
በእርግጥም የግብርናውን ምርታማነት ለማረጋገጥ የመስኖ ልማት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል፡፡ እስከ አሁን በተከናወኑ ተግባሮች በአነስተኛ መስኖ አርሶ አደሩ በዓመት አንዴ ከሚያመርትበት ሁኔታ ወደ ሁለት እና ሶስቴ ማድረስ እየተቻለ ነው፡፡
ይህ የመስኖ ልማት ግን ከአትክልት እና የተወሰኑ ሰብሎች ልማት ያለፈ አይደለም፡፡ ሀገሪቱ ኢኮኖሚዋ የሚጠይቀው የግብርና ምርት ከፍተኛ እየሆነ እንደ መሆኑ ሰፊ የግብርና ልማት ስራ ውስጥ መግባት ይኖርባታል፡፡ ለእዚህ ደግሞ መስኖ ትልቅ አቅም አለው፡፡
በኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 7 እስከ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት አለ፡፡ ከዚህ ውስጥ በመስኖ እየለማ ያለው ግን 7 እስከ 10 በመቶው ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ሰፊ መሬት ማልማት የሚችል የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ አለ፡፡ ስለሆነም ይህን እምቅ አቅም አውጥቶ መጠቀም ወሳኝ ነው፡፡ መንግስት ይህን አቅም ለመጠቀም ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት በሰው ሀብት፣በፋይናንስ፣በቴክኖሎጂ እና በአደረጃጀት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችም ተለይተዋል፡፡
ፍኖተ ካርታው የመስኖ እርሻ አስፈላጊ ነው ብሎ ብቻ የእስከ አሁኖቹን መለስተኛ የመስኖ ስራዎች ተሞክሮ ብቻ ይዞ ወደ ልማቱ ዘሎ ከመግባት ያድናል፡፡ በፍኖተ ካርታው ላይ በመመስረትም ቀጣይ ስራዎችን ማከናወን ይገባል፡፡
አሁን የሚያስፈልገው ወደ ልማቱ በቀጥታ መግባት ብቻ ይሆናል፡፡ መንግስት የመስኖ ልማቱን አስፈላጊነት በፍኖተ ካርታውም አረጋግጧል፡፡ ስራው ግን ከዚህም በላይ ያለፈ መሆን ይኖርበታል፡፡ ስራውን መሬት ላይ ለማውረድም ቁርጠኝነቱን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡
ስራው በእርግጥም ግዙፍ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ልማቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ፣ የሃይል ማመንጫዎችን ፣የስኳር ፋብሪካዎችን ወዘተ ለመገንባት የተወሰደውን ቁርጠኝነት በመስኖ ልማቱም መድገም ያስፈልጋል፡፡
ለመስኖ ልማት የሚወጣ ሀብት በትክክል ከተሰራበት አትራፊ እንደሚሆን የዘርፉ ባለሙያዎች ይጠቁማሉ፡፡ ልማቱ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ በተለይ በሰፋፊ የመስኖ ልማት ስራዎች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር እየጨመረ ነው፤ ኢኮኖሚው በኢንዱስትሪው እንዲመራ ይጠበቃል ፤ የኢንዱስትሪዎች ግብአት እንዲሆን የሚጠበቀው ደግሞ የግብርና ምርት ነው፡፡ ለልማታችን የምንፈልገውን የውጭ ምንዛሬ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መሰረት ማስገኘት የሚችለውም ግብርናው ነው፡፡
እነዚህ እውነታዎች የግብርናውን መዘመን በእጅጉ ይፈልጋሉ፡፡ መዘመኛው አንዱ መንገድ በዓመት ከአንድ ጊዜ በላይ ማምረት የሚያስችለው የመስኖ እርሻ እንደመሆኑ መስኖን የልማቱ መዘወሪያ ማድረግ ይገባል፡፡
ህዝቡን በበቂ ሁኔታ መመገብ፣ የኢንዲስትሪዎችን ግብአት ማሟላት ፣ ለቀጣይ ልማት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሬን ማስገኘት የሚቻለው ግብርናውን በማዘመን ነው፡፡ ይህን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ ዘመናዊ ግብርና ለማካሄድ ሲታሰብ ብዙም በአጠገቡ ያልዞርንበትን ከፍተኛ እምቅ እቅም ያለውን የመስኖ ልማት ለመጠቀም የመንግስት ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011