አዲስ አበባ፡- ለኢትዮጵያ የአረንጋዴ ልማት እስትራቴጂ ስኬታማ ተፈፃሚነት ጣሊያን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተች መሆኑን የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ከጣሊያን የአካባቢ፣ የመሬትና የባህር ሚኒስትርና ከዓለም ዓቀፉ የአረንጓዴ ልማት ተቋም ጋር በመተባባር በታዳሽ ሃይል ምንጭ ቴክኖፖሎጂ፣ የተቀናጀ የቆሻሻ አያያዝ እና ዘላቂ የውሃ ሃብት ዘርፎች ላይ የሚመከር ውይይት ትናንት ራዲሰን ብሉ ኢንተርናሽናል ሆቴል አካሂዷል።
በመድረኩም የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የሃብት ማፈላለግና ፕሮጀክት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወርዲ ሃሺም እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ከሰባት ዓመት በፊት ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ ስትራቴጂን በማዘጋጀት ለተፈፃሚነቱ የተለያዩ ተግባራትን በበቂ ትኩረት እያከናወነች ትገኛለች።
በተለይ የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ ከሶስት ዓመት በፊት ጣሊያንና ኢትዮጵያ የቴክኒካዊ ድጋፍ ስምምነት መፈራረማቸውን ያስታወሱት አቶ ወርዲ፤በአሁን ወቅትም ጣሊያን ሰባት ሚሊየን ዶላር ድጋፍ በማድረግና አራት ፕሮጀክቶችን ወደ ትግበራ ምዕራፍ በማሸጋገር በአገሪቱ የአረንጓዴ ልማት እስትራቴጂ ተፈፃሚነት ላይ ከፍተኛ አስተዋፆኦ በማበርከት ላይ መሆኗን አብራርተዋል።
«በአሁን ወቅት ዓለም ዓቀፍ ፈተና የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ የባለድርሻ አካላትን በተለይም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡» ያሉት አቶ ወርዲ፣ በዚህ ረገድም በኢትዮጵያ የጣሊያን አጋርነትና ድርጅቶች ተሳትፎ እየጎለበተ መምጣቱን አመላክተዋል።
የጣሊያን የአካባቢ፣ የመሬትና የባህር ሚኒስትር ፍራንሲስኮ ላ ኬምራ በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክትም፤ ጣሊያን ለኢትዮጵያ፣ ለሱዳንና ለጅቡቲ የአረንጓዴ ልማት ትግበራ 11ሚሊየን ዩሮ በመመደብ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደምትገኝ አብራርተዋል። አገሪቱን ይህን ጥረቷን በቀጣይም አጠናክራ እንደምትቀጥልና በተለይ በግሉ ዘርፍ የጣሊያን ድርጅቶች ይበልጥ ለማሳተፍ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።
የዓለም ዓቀፉ አረንጓዴ ልማት ተቋም፣ የአፍሪካና አውሮፓ ዳይሬክተር አጉሬዲስ ዲክስፓስ በበኩላቸው፤ ለኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት እስትራቴጂ ስኬታማ ተፈፃሚነት እያደረገች ያለውን ጥረት አድንቀዋል።
‹‹ይህን ጥረት ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግም በተለይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እጅጉን ወሳኝ ነው፡፡» ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህን ለማጎልበትም የተለያዩ የማበረታቻ ማዕቀፎችን ማርቀቅ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል። የጣሊያንና ድርጅቶቿ የምስራቅ አፍሪካ ተሳትፎም ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን መሆኑን ጠቁመው፤ተቋማቸው ኢትዮጵያ የአረንጋዴ ልማት እስትራቴጂ ስኬታማ ተፈፃሚነት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንና ይህንም በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011
በታምራት ተስፋዬ