የክፍያ ጣቢያውን በር ይዞ ረጅም ሰልፍ ውጪ ላይ ይታያል፡፡ በክፍያ ጣቢያው የስራ ሰዓት ከመድረሱ በፊት ወትሮም ቢሆን ሰልፍ የማይለየው ቢሆንም፣ የሰሞኑ ግን ቀኑን ሙሉ ረጅም ሰልፍ የታየበት ነው፡፡ የስራ መውጫ ሰዓት ደርሶም ረጅም ሰልፍ ይታያል፡፡ አራት ኪሎ ለሁሉም የክፍያ ማእከል፡፡
ወይዘሮ ወጋየሁ ደምሴ በአገልግሎቱ ሰልፍ ከተማረሩት ሰዎች መካከል አንዷ ናት። በሰልፉ ርዝመት ድካም የተጫጫናት ወይዘሮ ወጋየሁ፣ ጉንጩዋን በመዳፏ ደግፋ ትክዝ ባለ ነበር የገኘናት፡፡ ደክሟት፤ በሰልፉ ክፉኛ መማረሯን ከፊቷ ገጽታ ላይም መረዳት ይቻላል፡፡
የውሃ፣ የመብራትና፣ የስልክ አገልግሎት ክፍያ ያለወረፋ ስትከፍል እንደኖረች የምትናገረው ወይዘሮ ወጋየሁ ሰሞኑን ግን ነገሮች እንዳለፉት ጊዜያት እንዳልሆነላት ትገልጻለች፡፡ ቤላ አካባቢ የምትኖረው ወይዘሮ ወጋየሁ፣ ወደ ክፍያ ማዕከሉ የመጣችው በጠዋት ነው፡፡ ከአንድ ሰዓት በላይ ወረፋ ብትጠብቅም አገልግሎቱን ማግኘት አልቻለችም፡፡
በአራት ኪሎ የለሁሉ ክፍያ ማዕከል የምትገለገለው ወይዘሮ ወጋየሁ፣ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ክፍያ ለመፈጸም ረጃጅም ሰልፎችን መጠበቅ የግድ ሆኖባታል፡፡ ይህን እረጅም ሰልፍ አልፋ ወረፋ ደርሷት ሲስተም ተቋርጧል በሚል በተደጋጋሚ ክፍያ ሳትፈፅም መመለሷን የምታስታውሰው ወይዘሮ ወጋየሁ፣ ክፍያውን ለመፈጸም መመላለስ የግድ እንደሆነም በምሬት ትናገራለች፡፡
የክፍያ ማዕከሉ ገንዘብ ተቀባዮች ጥቂት መሆናቸውን ለችግሩ ምክንያት አርጋ ትቆጥራለች፡፡ ይህም አገልግሎቱን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመስጠት እንቅፋት ሆኗል ነው የምትለው፡፡
ከኬኒያ ኤምባሲ አካባቢ ለውሃ፣ ለመብራትና ስልክ ክፍያ ወደ ማዕከሉ የመጣው ወጣት አሸብር ኤልባሮስ እንደ ወይዘሮ ወጋየሁ በወረፋው ክፉኛ ተማሯል፡፡ በማእከሉ የተገኘው ማለዳ ቢሆንም፣ ክፍያውን መፈጸም አልቻለም፡፡ ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ ለሚሆን ጊዜ ወረፋ ለመጠበቅ ተገዷል ፡፡
ከአንድ ቀን በፊት ረጅም ወረፋ ጠብቆ ተራው ሲደርስ የክፍያ ሂሳብ ጨምሯል በመባሉ ሳይከፍል ተመልሷል፡፡ ወደ ማዕከሉ ሲመጣ ይህ ሁለተኛ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ወረፋው ምንም አይነት ለውጥ እንደሌለው ያስረዳል፡፡
ወይዘሮ ሰሎሜ አበበም ከሳምንት በፊት ከእንግሊዝ ኢምባሲ አካባቢ ክፍያ ለመፈፀም ወደማዕከሉ መጥታለች፡፡ እሷም ሶስት ሰአታት ወረፋ ለመጠበቅ መገደዷን ገልጻ፣ በወቅቱ ክፍያውን ሳትፈፀም እንደተመለሰች ትናገራለች፡፡ ክፍያውን ተመልሳ ወደ ማዕከሉ መምጣቷን የምትናገረው ወይዘሮ ሰሎሜ፣ ክፍያ ለመፈፀም መጠበት ያለባት ወረፋ ግን ክፉኛ አበሳጭቷታል፡፡
የተገልጋዮቹን ቅሬታ እና የተመለከትኩትን ይዤ የማዕከሉን ሃላፊ ለማናገር ወደ ውስጥ ዘለቅሁ፡፡ በማዕከሉ ውስጥ ስድስት የሚሆኑ ክፍያ ተቀባዮች ስራቸውን እያከናወኑ ናቸው፡፡ ከፊት ለፊታቸውም ውጪ ከተሰለፉት በተጨማሪ በርከታ ደንበኞች ተቀምጠው ወረፋ መጠበቃቸውን ቀጥለዋል፡፡
የማእከሉ ሃላፊ ቢሮ የቱ እንደሆነ ጠየቅሁ፡፡ ከፊት ለፊት በሩ ገርበብ ያለው ቢሮ መሆኑ ተነገረኝ፡፡ ወደ ውስጥም ዘለቅሁ፡፡ ወደ ሃላፊዋ ተጠጋሁና ከየት እንደመጣሁና ምን እንደምፈልግ አስረድቼ መረጃው እንዲሰጠኝ ጥያቄ አቀረብሁ፡፡
መጀመሪያ ደብዳቤ ካላመጣህ መረጃ መስጠት አልችልም በሚል ትንሽ ያመነቱት ሃላፊ ከጥቂት ክርክር በኋላ መግባባት ላይ ደርሰን ስለአጠቃላይ ሁኔታው ሊነግሩኝ ተስማሙ፡፡
ሃላፊዋ ወይዘሮ ወይነሽት ገብረፃዲቅ ይባላሉ፡፡ በማዕከሉ ረጅም ሰልፍ መታየት የጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሆነ ሃላፊዋ ይገልጻሉ፡፡ የመብራት፣ ውሃና ስልክ አገልግሎት ክፍያ የሚፈጸምባቸው ፕሮግራሞች እንዳሉ የሚናገሩት ወይዘሮ ወይንሸት፣ የደንበኞች የውሃ አገልግሎት ክፍያ ዳታ በወቅቱ ለማዕከሉ አለመድረሱ ማዕከሉ ወረፋ እንዲበዛበት ማድረጉን ይገልጻሉ፡፡
የእያንዳንዱ ደንበኛ የውሃ አገልግሎት ክፍያ ዳታ በተለያየ ጊዜ ወደ ክፍያ ማዕከሉ ስለሚገባ ድብልቅልቅ ያለ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ወይንሸት፣ በዚህ የተነሳም አገልግሎቱን በተቀላጠፈ መልኩ ለመስጠት አለማስቻሉን ይጠቁማሉ፡፡የተፈጠረው ችግር የአገልግሎት ክፍያውን በተቆረጠው የመክፈያ ጊዜ ለመቀበል አዳጋች አርጎታል ይላሉ፡፡
ችግሩን ለመፍታት በማዕከሉ ባሉ የአገልግሎት ሂሳብ ተቀባይ ባለሙያዎች ሃይል ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ህብረተሰቡ ሌሎች የክፍያ ማዕከላትን በአማራጭነት ቢጠቀም ችግሩን ለጊዜውም ቢሆን መፍታት እንደሚቻልም ይጠቁማሉ፡፡
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ባለሞያ አቶ ንጉስ ደሳለኝ ባለፉት ሳምንታት በለሁሉ የክፍያ ማዕከላት ለተፈጠረው ወረፋ እና መጨናነቅ ምክንያቱ የውሃ አገልግሎት ከፋይ ደንበኞች ዳታ መዘግየት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ባለስልጣኑ የደንበኞችን ዳታ ሲሰተም የማሻሻል ስራ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል እየሰራ መሆኑን ተከትሎ ችግሩ እንደተፈጠረም ገልጸው፣ በዚህም ወደ ለሁሉ የክፍያ ማዕከላት የሚገባው የደንበኞች የክፍያ ዳታ መዘግየቱን ያብራራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ሲስተሙን የማሻሻሉ ስራ እየተጠናቀቀ ነው ያሉት አቶ ንጉስ፣ በዚሁ መሰረት የደንበኞች ዳታ ወደ ለሁሉ የክፍያ ማዕከላት እየገባ እንደሚገኝም ይገልጻሉ፡፡ ችግሩ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ እንደሚፈታም ባለሙያው ያመለክታሉ፡፡
የውሃ ክፍያ ደረሰኝ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ተዘጋጅቶ ከታተመ በኋላ እያንዳንዱ ደንበኛ የሚደርስበት የክፍያ መጠን ወደ ለሁሉ የክፍያ ማዕከላት እንዲተላለፍ ይደረጋል የሚሉት አቶ ንጉስ፣ ይህም የክፍያ መዘግየቱን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011
በአስናቀ ፀጋዬ