• በሽታዎች ሲከሰቱም በቶሎ ሪፖርት አይደርሰውም
አዲስ አበባ፡- በመጀመሪያው የ100 ቀናት እቅድ የህብረተሰብ ጤና አደጋ መቆጣጠሪያ ማዕከላትን በክልሎች እንዳላቋቋመ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለፀ፡፡ በሽታዎች በተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ሲከሰቱ በቶሎ ሪፖርት እንደማይደረጉለትም አስታወቀ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የህብረተሰብ ጤና አደጋ መቆጣጠሪያ ማዕካላት በክልሎች መገንባት ሥርዓትን የመዘርጋት፣ የሰው ሃይልን አብቅቶ የመመደብና ለተቋሙ አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን ማሟላትን ይጠይቃል፡፡ ይሁንና ሥርዓት የመዘርጋትና የሰው ሃይል የመመደብ ስራዎች የተከናወኑ ቢሆንም፤ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችና መሰረተ ልማቶች ባለመሟላታቸው ምክንያት ማዕከላቱን በክልሎች ማቋቋም አልተቻለም፡፡
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች በወቅቱ አለመሟላታቸውና በተለይ በአንዳንድ ክልሎች በቂ ቢሮዎች ባለመገንባታቸው ማዕከላቱን ሙሉ በሙሉ ማቋቋም ሳይቻል ቀርቷል፡፡ ይሁን እንጂ የቀሩ ግብዓቶችን በማሟላትና በሁለተኛው የመቶ ቀን እቅድ ውስጥ በማካተት ሶስት ማዕከላትን ማቋቋም እንደተቻለ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የጠቀሱ ሲሆን፣ ቀሪ ስድስት ማዕከላትን በቀጣይ ለማቋቋም በሂደት ላይ ናቸው፡፡
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሽታዎች ሲከሰቱ በቶሎ ለኢንስቲትዩቱ ሪፖርት ያለማድረግ ችግሮችም እንዳሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው የገለፁ ሲሆን፣ የጤና ተቋማት አቅም ማነስ፣ የግንዛቤ እጥረትና ሌሎችም ለሪፖርቱ መዘግየት መንስኤ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ከተደረገባቸው 22 የሚሆኑ በሽታዎች ውስጥ አስራ አምስቱ ሲከሰቱ ለኢንስቲትዩቱ በቶሎ ሪፖርት መደረግ አለባቸው፡፡ ቀሪዎቹ አምስቱ ደግሞ ከተከሰቱ ቢያንስ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሪፖርት እንዲደረጉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ ይሁንና በሽታዎቹ ሲከሰቱ በቶሎ ሪፖርት የማድረግ ችግሮች እንዳሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ የበሽታዎቹ ምልክቶች ከሌሎች በሽታዎች ጋር ተቀራራቢ መሆን፣ በሽታዎች በአብዛኛው ምልክታቸው በቶሎ የማይታወቅ መሆኑና ህመምተኞችም በመዘናጋት በቶሎ ወደ ህክምና ጣቢያዎች አለመምጣታቸው በሽታዎቹን በመለየት በቶሎ ሪፖርት ለማድረግ ተጨማሪ እንቅፋት መሆናቸውንም ተናግ ረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም ከፌዴራል ጀምሮ እስከታችኛው እርከን ድረስ የአቅም ግንባታ ስራዎችን እንደሚያከናውንና በተለይም የኤሌክቶትሮኒክ ሪፖርት ሥርዓትን በመዘርጋት በሽታዎቸ ሲከሰቱ ፈጣን ሪፖርት እንዲደርሰው በማድረግ ለበሽታዎቹ ፈጣን ምላሽ እንደሚሰጥም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2011
በአስናቀ ፀጋዬ