አባታቸው ያወጡላቸው ስም ተፈራወርቅ ሻዉል ኪዳነቃል ነበር፡፡በስሙ ርዝማኔ ወርቁ ቀረና ተፈራ ሻዉል ኪዳነቃል ተብለው እንዲጠሩ ተወሰነ፡፡ከስማቸው ወርቅ የሚለው ቀረ እንጂ የዛሬው እንግዳዬ ወርቃማ የሕይወት ዘመንን አሳልፈዋል፡፡
ውልደታቸው በ1935 ዓ.ም ሸዋ መናገሻ ማርቆስ ደብር አካባቢ ነው፡፡ የቤተ ክህነትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሆለታ ገነት ተምረዋል፡፡ ወደ ደብረ ብርሃን ከተማ በመጓዝ ለሁለት ዓመታት ሁለተኛ ደረጃን ከተማሩ በኋላ በአካባቢው ቅዝቃዜ ምክንያት ሞቅ ወዳለችው የደብረ ዘይት (ቢሾፍቱ) ከተማ በመሄድ ሚሲዮኖች በከፈቱት የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ኮሌጅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መንግስት እየከፈለላቸው ተምረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ወደ ሳይንስ ፋካልቲ ቢገቡም በዛው አልዘለቁበትም፡፡ የስራ ዕድል አግኝተው ወደ ሲዳሞ በመሄድ ሆስፒታል ውስጥ ሲሰሩ የተመለከቱት የህመምተኛ ደም የህይወት መስመራቸውን የቀየረ አጋጣሚ ይመስላል፡፡ የተመለከቱት ደም ውስጣቸውን ስለረበሸውና ስላስደነገጣቸው ከሳይንስ ትምህርት ይልቅ ቀልባቸው ወደ አርት ትምህርት አዘነበለ፡፡ ሁለተኛ ዓመት ወደ መረጡት የትምህርት ክፍል ገቡ፡፡
በቀድሞው መጠሪያው የቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ መከፈቱን ተከትሎ ብስራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ ይቋቋማል፡፡ ጓደኞቻቸውን ለማስፈተንም አጅበው ወደ ጣቢያው ይሄዳሉ፡፡ይሄም ለርሳቸው አጋጣሚ ወይም የህሊና ጥሪ በጣቢያው አመራሮች ተመርጠው የትርፍ ጊዜ ሰራተኛ ሆኑ፡፡ ይሄ አጋጣሚም ከሬዲዮ ጋዜጠኝነት ስራ ጋር አስተዋወቃቸው፡፡
ዜናና ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡ ጆሮ ገብ ድምጻቸውም ተመራጭ አደረጋቸው፣ ለሙያው በውስጣቸው ያደረው ፍቅር ተደማምሮ ወደ ጋዜጠኝነት ስራ እንዲገቡ ምክንያት ሆናቸው፡፡
ጋዜጠኞች ሶስት አይነት መልክ አላቸው ይላሉ እንግዳችን፤ በቀዳሚነት የጠቀሱት ሚሽነሪ የሚባለውንና ሰውን ለመርዳትና መረጃ ለመስጠት ከፍ ያለ ማንነት የተላበሰውን ነው፡፡ ሁለተኛው ራዕይ ያለው ሲሆን፤ ሶስተኛው ለቅጥር ብቻ የሚሰራ ነው፡፡ «ጋዜጠኝነት የህሊና ጥሪ ነው፡፡ ቀጥዬ የተቀላቀልኩትም የዲፕሎማሲ ስራ ከጋዜጠኝነት ስራ ጋር አንድ ናቸው» ይላሉ፡፡
ጋዜጠኝነትና ዲፕሎማሲ፤ ለሀገር፣ ለወገን ዋጋ መክፈልንና ፍቅርን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ እውነቱን ለማጋለጥ፣ ለማስተማር ፍቅር ስለነበራቸው በዲፕሎማሲው መስክም ተቀላቅለው ቀጥለዋል፡፡
ብስራተ ወንጌል በጋዜጠኝነት እየሰሩ በነበረበት ወቅት የጀርመኑ ቻንስለር የቢስማርክ የልጅ ልጅ ለጉብኝት አዲስ አበባ መጥተው ነበር፡፡ ጀርመን ካልቸራል ኢንስቲትዩት እንደተቋቋመ ጀርመንኛ ቋንቋን ይማሩ ነበርና በአገሩ ቋንቋ እንግዳውን ሲያነጋግሩት ደስ ይለዋል፡፡ አጋጣሚውም በግብዣ ወደ ጀርመን እንዲጓዙ ምክንያት ሆኗል፡፡ ቦን አጠገብ በምትገኝ ኮሎኝ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ቋንቋውን በሚገባም ተምረው ለመዱት፡፡ የጀርመንን የተለያዩ አካባቢዎችን ተዘዋውረው ለመጎብኘትም ቻሉ፡፡
ዶቼ ቬሌ የሬዲዮ ጣቢያ የአማርኛ የሬዲዮ ጣቢያ ለማቋቋም እንደሚፈልግና ለዚህ ጉዳይም ዳይሬክተሩ እንደሚፈልጋቸው ተነገራቸው፡፡ ከዳይሬክተሩ ጋር ተገናኙ፡፡ በዩኒቨርሲቲ፣ በንግድና በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማነጋገር ስራ ጀመሩ፡፡ እነጎይቶም ቢሆን፣ ደራጎንና ቦጋለ መኩሪያ፣ ንጉሴ መንገሻና የመሳሰሉትን በማሰባሰብ ራሳቸው አሰልጥነው የአማርኛ ቋንቋን ለማስጀመር በቅተዋል፡፡
የመጀመሪያው የሰርቶ አደር ጋዜጣ ዝግጅት ኮሚቴ አባልና የዓለም አቀፍ ጉዳይ ምክትል ዋና አዘጋጅ የነበሩ፣ ዶቼ ቬሌ የሬዲዮ ጣቢያ የአማርኛ የሬዲዮ ጣቢያን ያቋቋሙ፣ በአምባሳደርነት ያገለገሉ፣ የቀይ መስቀል ዋና ጸሃፊ ሆነው የሰሩ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሂውማኒቴሪያንና በፖለቲካ ተጠሪነት ያገለገሉ፣ የምስራቅ አፍሪካ ጦር አስተባባሪ የነበሩና አሁን ከጓኞቻቸው ጋር የጥናት ማዕከል አቋቁመው ምክር በመለገስ እያገለገሉ የሚገኙት አምባሳደርና ጋዜጠኛ ተፈራ ሻወል ኪዳነቃል ናቸው፡፡ የዳበረ ልምዳቸውንና ተሞክሯቸውን እንደሚከተለው አጋርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን:- ስለቤተሰብዎ ቢነግሩኝ?
አቶ ተፈራ፡- ሶስት ወንዶች ልጆችና ሶስት የልጅ ልጆች አሉኝ፡፡ የመጀመሪያው ልጄ አሜሪካ አገር በግል ስራ ይተዳደራል፡፡ ሁለተኛው አምባሳደር ሄኖክ ነው፡፡ ከእኔ ጋር በርካታ አገራት ይዞር ስለነበር ብዙ እውቀቶችን ቀስሟል፡፡ እርሱ አሁን በሚሰራው ስራ የእግዚአብሄር ጸጋ ነው እላለሁ፡፡ እኔ ህግ እንደምማር ያውቅ ነበር። ልጅ ሆኖ እኔም እንዳባቴ ህግ እማራለሁ ይል ነበር። እንዳባቴ ዲፕሎማት ሆኜ መኪናዬን በፈረንጅ አሳጥባለሁ ይል ነበር፡፡ ታታሪ ነው፡፡ ለሊት 10 ሰዓት ተነስቼ እንደምሰራ ያውቃል፡፡ የዓለም ዜና ይከታተላል። ህግ፣ ኢኮኖሚክስ፣ ዲፕሎማሲ አጥንቷል፡፡ አየር መንገድ ገብቶ ጥሩ ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ዶክተር አብይ ሲመጡ የተሰጠውን የፈረንሳይ አምባሳደርነት ሃላፊነት በደስታ ተቀብሎ እያገለገለ ነው። ሶስተኛው ጀርመን አገር ቢ ኤም ደብልዩ በአማካሪነት ይሰራል፡፡
አዲስ ዘመን:- የዲፕሎማሲ ስራን እንዴት ጀመሩት?
አቶ ተፈራ:- የብስራተ ወንጌል የዜና ሃላፊ ሆኜ በነበረበት ወቅት ሚኒስትር ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ ጠርተውኝ ጀርመንኛ ቋንቋን ታውቃለህ፣ ተምረሃል ስለዚህ ለግርማዊ ንጉሰ ነገስት መንግስት ኤምባሲ ሁለተኛ ጸሃፊ ሆነህ ጀርመን ለመሄድ ትችላለህ ወይ? ብለው ጠየቁኝ፡፡
በዛን ጊዜ ብዙ ገንዘብ ነበር የሚከፈለው፡፡ የአንድ ሚኒስትር ደሞዝ ያክል ነበር ብስራተ ወንጌል የማገኘው። ያንን ጥዬ በዝቅተኛ ደመወዝ በ500 ብር የዳይሬክተር ደመወዝ ውጭ ጉዳይ ገብቼ ወደ ጀርመን ቦን ከተማ እንደገና ተልኬ የንጉሰ ነገስቱ መንግስት ኤምባሲ ሁለተኛ ጸሃፊ የፕሬስ ሃላፊ ሆኜ መስራት ጀመርኩ፡፡
ማንበብ ጀመርኩ፣ የህግ ትምህርት መከታተል ጀመርኩኝ፡፡ ወደ መጨረሻ ወደ ካርቱም የንጉሰ ነገስት መንግስት ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ተብየ በአንደኛ ጸሃፊነት ተዘዋወርኩኝ፡፡ እዛ በነበርኩበት ወቅት የነበሩት ዶክተር ሚናሴ ቀጥለውም ደጃዝማች ዘውዴ ገብረስላሴ ሚኒስትር ሆነው መጡ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን እያገለገልኩ በነበረበት ወቅት የደርግ መንግስት ወታደራዊው ሃይል መንግስቱን በማውረድ ስልጣን ይወስዳል፡፡
እነ ኮሎኔል አጥናፉ ካርቱም መጥተው ተዋወቅን። ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስራት እንዳለብኝ ገለጹልኝ፡፡ ሊቀመንበሩ ጽህፈት ቤት የኤርትራን ጉዳይ የሚከታተል አንድ ቡድን አቋቁመን ነበርና እዛም ገብቼ ሰራሁ በመቀጠልም በውጭ ጉዳይ ተመልሼም የፕሬስ ሃላፊ ሆንኩ፡፡ በወቅቱ አቶ ክፍሌ ወዳጆ አለቃዬ ነበሩ፡፡ ተግባቦት ነበረን፤ ጥሩ ትምህርት የሚሰጡ ሰው ነበሩ፡፡ ብዙዎቹን ወጣት ዲፕሎማቶች የቀረጹት እርሳቸው ናቸው፡፡
በደርግ ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል እርስ በእርስ መገዳደል ሲጀመር በአስተርጓሚም በምንም ስራ ሟቾቹን የቀረበ ሁሉ ጠላት ሆኖ ተፈረጀ፡፡ እኔም ለጀነራል ተፈሪ በንቲ አስተርጓሚያቸው ሆኜ አንዳንዴ አገለግላቸው ስለነበር የእርሳቸው ቡድን አባል ተደርጌ ተቆጠርኩ። የነበሩት ተራማጅ ሃይሎች ሁሉንም ይጠረጥሩ ስለነበር በታላቁ ቤተ መንግስት የጓድ መንግስቱ ሃይለማርያም እንግዳ ሆኜ እዛው ጊቢ ባለው ዋሻ ውስጥ ለሶስት ዓመታት ታሰርኩ፡፡
ከሶስት ዓመታት እስር በኋላ ጠርተው አንተን ማሰር አልነበረብንም ተሳስተናል፡፡ በመሃላችን በነበረው ውዝግብ የምንሰራውን አናውቅም ነበር፡፡ አሁን ወጥተህ አገልግለን፡፡ አዲስ ፓርቲ እናቋቁማለን፤ የአደራጅ ኮሚሽን እናቋቁማለን በምን ትረዳናለህ የሚል ጥያቄ ቀረበልኝ፡፡ እኔ ስራዬ ውጭ ጉዳይ ነው፣ ጋዜጠኝነት ነው፡፡ አገርን ለማገልገል እስከሆነ ድረስ ምንም አይደለም አልኳቸው፡፡ እርሳቸውም ተቀብለው ከሌሎች ቡድኖች ጋር ሞስኮ ላኩኝ፡፡ የፓርቲ አደረጃጀትና የፕሮፖጋንዳ ቅስቀሳ ሰልጥነን ተመለስን።
ስንመለስ የመጀመሪያው የሰርቶ አደር ጋዜጣ ዝግጅት ኮሚቴ አባልና የዓለም አቀፍ ጉዳይ ምክትል ዋና አዘጋጅ ሆኜ አገለገልኩ፡፡
የቀይ ኮከብ ዘመቻ የሚሊቴሪ ሃሳቡን አልደግፈውም ነበር፡፡ የኤርትራን ህዝብ በፍቅርና በወንድማማችነት መያዝ እንደሚያስፈልግ ሁል ዜም አስረግጬ እናገር ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ ለወሬ አቀባዩች ጥሩ አጋጣሚ ነበር። በአሉታዊ መንገድ ስለሚያቀርቡት ከአራት ኪሎ ወደ ቱሪዝም ኮሚሽን እንድዛወር ተደረገ፡፡ በዛን ጊዜ ሃሳብ ስትሰጥ እባክህ እንዲህ የጠነከረ ሃሳብ አትስጥ የሚል ምክር ይሰጣል፡፡
ቱሪዝም ኮሚሽን ከተዘዋወርኩ በኋላ አቶ ማዕረጉ በዛብህ፣ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንን ጭምር በማካተት ህትመቶችን አዘጋጅተናል፡፡ እአአ በ1984 ድርቅ ሲከሰት ቱሪዝም ኮሚሽን ነበርኩኝ፡፡ በዛን ወቅት አሜሪካን አገር ቱሪዝምን በማስተዋወቅ ቱሪስቶችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት አስቸጋሪ ነበር፡፡
በእዚህ አጋጣሚ ስልክ ተደውሎ ሊቀመንበር መንግስቱ ሃይለማርያም ይፈልጉሃል የሚል መልእክት ደረሰኝ፡፡ በአውሮፕላን አቆራርጬ ገባሁ፡፡ ሰው ሁሉ ከደርግ መንግስት እየሸሸ የሚቀርበት ጊዜ ቢሆንም እኔ ግን የገባሁት የማገለግለው አገሬን እንጂ ደርግን አይደለም በሚል ነበር፡፡ ፕሬዚደንት መንግስቱ ተቀብለው ከጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረስላሴ ወግደረስ ጋር ተገናኝተን እንድነጋገር ትእዛዝ ሰጡ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የቀይ መስቀል ዋና ጸሃፊ ሆነሃል ተባልኩ። ዋና ጸሃፊ ሆኜ ስገባ በቋት ውስጥ የነበረው አንድ ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነበር፡፡
በቦንድ ሽያጭና በመሳሰሉት ከሚገኘው ገንዘብ ነበር ለሰራተኛ ደመወዝ ይከፈል የነበረው። ከማህበሩ ፕሬዚደንት ዶክተር ዳዊት ዘውዴና ከሌሎች የቦርድ አባላት ጋር ሆነን መነጋገር ጀመርን፡፡ ባለን ዓለም አቀፍና የዲፕሎማሲ እውቀት መሰማራት መርጠን ከጃፓን እስከ አሜሪካ፣ ሰሜን አውሮፓ፣ እስካንድኔቪያ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን ዞረን በአንድ ዓመት በገንዘብ 200 ሚሊዮን ዶላር፣ በአይነት ደግሞ፤ 500 ሚሊዮን የስዊስ ፍራንክ የምግብና የቁሳቁስ ርዳታ ለወሎ ህዝብ በቀይ መስቀል አማካኝነት ለማድረስ ችለናል፡፡ በዛን ጊዜ ይሄ ከፍተኛ ግኝት ነው፡፡
ፕሬዚደንት መንግስቱ ጋር ተጠርቼ በቀይ መስቀል የሰራሁት ስራ ጥሩ መሆኑ ተነገረኝ፡፡ በመቀጠል ደግሞ ቋንቋውንም ስለምትችል ምስራቅ ጀርመን በመሄድ በወቅቱ የነበሩ አምባሳደር ለማ ጉተማ ሲጨርሱ አንተ ትቀጥላለህ ተብሎ ተነገረኝ፡፡ ሄጄ ቆየሁ እንደተባለውም የምስራቅ ጀርመን አምባሳደር ሆንኩኝ፡፡ ሲዋሃዱ ወደ ቼኮዝላቫኪያ፣ ሀንጋሪና ፖላንድ ጭምር አምባሳደር ሆኜ አገለገልኩ፡፡
ቼኮዝላቫኪያ በነበርኩበት ወቅት የወያኔ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ገባ፡፡ በመጣበት ጊዜ ብዙዎቹን ባለሙያ ያልሆኑትን ዲፕሎማቶች ጠሩ፡፡ አንድ መንግስት ሥርዓት ሲለወጥ የራሱን ሰው ይፈልጋል፡፡ ግን እኔን፣ አምባሳደር ቆንጂትን፣ አምባሳደር ሃይሉ፣ አምባሳደር አሰፋ ወልዴ፣ አምባሳደር ጥበቡና የመሳሰልነውን ባለሙያ የነበርነውን አልጠሩንም፡፡ ስድስት ወራት አቆይተውን ተመለሱ አሉን። በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩ አምባሳደር ስዩም መስፍን ሲያነጋግሩን ትጠፋላችሁ ተብለን ነበር አሉን፡፡
ለምን እንጠፋለን አገሬን ለወያኔ ጥዬ አልቀርም አልኳቸው። ከዚህ የበለጠ አርበኝነት አንፈልግም፤ በል አንድ ክፍል ትመራለህ አሉኝ፡፡
ተመልሼ የፕሬስ ዲፓርትመንት ገባሁ፡፡ የኤርትራ መገንጠል ሲመጣ ብዙ አልጣመኝም ወንድማማቾች እንዴት ይለያያሉ የሚል አመለካከት ነበረኝ፡፡ በነበረው ሥርዓት የማይደገፍ ሃሳብ ነበር፡፡ እአአ 1994 ላይ አንድ ቀን ጠዋት እስካሁን ላገለገሉት እናመሰግናለን፤ ከዛሬ ጀምሮ ተሰናብተዋል የሚል ደብዳቤ ደረሰኝ፡፡
አቶ ተፈራ፡- ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተሰናበቱ በኋላ ምን ቀጠሉ ?
አዲስ ዘመን፡- ቤቴ ቁጭ እንዳልኩ የጀርመን አምባሳደር ይፈልገኝ ነበር ሊያገኘኝ አልቻለም፡፡ ከጂቲዜድ ተደውሎ ከጀርመን ዋና ከተማ ቦን የሚያውቁህ ሰዎች አማካሪ እንድትሆን ጠይቀዋል ከቻልክ ብትመጣ የሚል መልክት ደረሰኝ፡፡
ትግራይ ውስጥ ከኤርትራ የተፈናቀሉ ሰዎች ስላሉ የእነርሱን ሁኔታ በማጥናት ሊሰሩ የሚችሉትን ፕሮጀክት አዘጋጅ ተባልኩ፡፡ በእዛን ጊዜ በወያኔው መንግስት ትእዛዝ ብዙ ምሁራን ከስራቸው ተፈናቅለው ነበር። ትዝ ያለኝ እነዚህን ሰዎች በእዚህ ስራ ማሳተፍ ነው። እችላለሁ ብዬ ጀመርኩ ፕሮጀክቱን ካዘጋጀን በኋላ በቀን 180 ብር ገደማ እየተከፈለኝ ወደ መቀሌ ተጓዝኩ። ለ30 ቀናት ያህል ይህንን ያክል ማግኘት የዓመት ያክል ባጀት የሚሸፍን ነበርና ደነገጥኩ፡፡ ስራውን ሰራን ጓደኞቼም የሚገባቸውን አገኙ። ተፈናቃዮች የሚቋቋሙበትን የውሃ ማቆር፣ የልማትና መሰል ስራዎችን ነበር ያቀድነው። ቀይ መስቀል እያለሁ ወሎ ባቲ ላይ ሰርቼ ነበር፡፡ የማቋቋም ልምድ ነበረኝ፡፡
ለጀርመኖቹ አጠናቅቀን አቀረብን፡፡ ወደ ቤቴ ተመልሼ ቀጥሎ ምን እሰራለሁ እያልኩ አስብ ነበር። ልጆች ማስተማር፣ ማሳደግ አለ፡፡ ከዛው ስልክ ተደወለልኝና መጥተህ እኮ የአማካሪነት ገንዘብህን አልወሰድክም ተባልኩ። የወሰድኩት ገንዘብ እኮ ብዙ ነው አልኳቸው። የለም 10 ሺህ ዶላር አለህ ተባልኩ። ይሄ እኮ በዛን ጊዜ የዓመት ስራ ማስኬጃ ያህል ነው። ይህንን በምስጋናና በጸጋ ተቀበልኩ፡፡ ባለቤቴን ወደ ልጆቼ ውጭ አገር ላኳት። እኔም ወደ ኒውዮርክ ተጉዤ የተባበሩት መንግስታት ወደሚገኙ ጓደኞቼ ጋር ተጓዝኩ፡፡ እዚያ ጓደኛዬ አንተ ዝም ብለህ ቁጭ ማለት የለብህም በተባበሩት መንግስታት የሰላም ጥበቃ መምሪያ ላስተዋውቅህ ብሎ ወሰደኝ፡፡
ሴትየዋ እንግሊዝኛ ንግግራቸው የጀርመንኛ ቅላጼ አለው፡፡ እርሱን ትተን እኔና እርሳቸው ተነጋገርን፤ ጊዜ የለኝም ያሉት ሃላፊ ለሁለት ሰዓታት ያህል አወሩኝ። ምሳ ጋብዘው ወደቦስኒያ ወይንም ደቡብ አፍሪካ እንድትሄድ እንፈልጋለን አሉኝ፡፡ ያን ጊዜ ማንዴላ ከእስር ተፈትተው ምርጫ ሊካሄድ ዝግጅት የተደረገበት ጊዜ ነበር፡፡ እኔ እድሜዬን በሙሉ አፓርታይድን ስዋጋ የኖርኩ የውጭ ጉዳይ አባልና ጋዜጠኛ ስለሆንኩ ደቡብ አፍሪካ መሄድን መረጥኩ፡፡ ደቡብ አፍሪካ ፖርት ኤልዛቤት ከተማ በክልሉ የተባበሩት መንግስታት የምርጫ አስተባባሪ ሆንኩ፡፡
እየሰራሁ ሳለሁ ማንዴላ፣ ዴክለርክን ከእዛ አካባቢ የወጡ ነበሩና ሲመጡ ለማግኘት እድል ነበረኝ። ምርጫውም በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አድርገናል፡፡ ወደ ማዕከላዊና ምዕራብ አፍሪካ ዩኒሴፍ በአማካሪነት ወሰደኝ፡፡ ጥናት ሰርቼ አቀረብኩ፡፡
በመቀጠል ወደ ኒው ዮርክ ገባሁ፡፡ በኒውዮርክ የሰብአዊ ጉዳይ ጸሃፊ አክአሺ የሚባሉ ጃፓናዊ የስራ ልምዴን፣ ተሞክሮዬንና የሰራሁትን ጥናት ከተመለከቱ በኋላ ረዳታቸው ወደ ጃፓን ምክር ቤት ተመርጦ ስለሄደ የቅድመ ማስጠንቀቂያው መምሪያ ሃላፊ እንደሚፈልጉ ነገሩኝ። በኒውዮርክ ስራ ጀመርኩ፡፡ አንድ ዓመት ሙሉ በስኬት ሰርቼ አጠናቀቅኩኝ፡፡ ጃፓናዊው አክአሺ ጡረታ ከወጡ በኋላ የተተኩት ብራዚላዊው ሰርጂው ዴሜልኖ አፍሪካ ውክልናችን ዝቅ ያለ በመሆኑ እዛ ብትሰሩ የሚል ሃሳብ ሲያቀርቡ እኔ የመጀመሪያው ፍቃደኛ ሆንኩ፡፡ አምባሳደር ብርሃኑ ዲንቃም እንደኔ በእስር ያሳለፈ በተባበሩት መንግስታት ከእርሱ የተሻለ አታገኙም ብሎአቸው በእዚህ ሃሳብ ተስማማ፡፡
ለአፍሪካ ህብረትና ለኢሲኤ አዲስ አበባ ከተማ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሂውማኒቴሪያንና የፖለቲካ ተጠሪ ሆንኩኝ፡፡ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ለውሳኔ ሰጪ አካላት የሚጠቅም ጥናት ነው፡፡ ስለቅድመ ማስጠንቀቂያ የተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውሬ ስልጠና ሰጠሁኝ፡፡ በዚህ ስራ ላይ እያለሁ ከጄኔቭ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነሯ በተባበሩት መንግስታት የሚካሄድ የዓለም የጸረ ዘረኝነት ጉባኤ አማካሪ እንድሆን መረጡኝ እርሱን ስጨርስ በማዕከላዊ አፍሪካ የሰብአዊ መብት ተጠሪ ለመሆን ከኮፊ አናን ጋር እንድሰራ መቀመጫውን የካሜሩን ዋና ከተማ ያውንዴ ባደረገ ተቋም እንድሰራ ውሳኔ መተላለፉን ተገልጾልኝ ስራውን ጀመርኩ፡፡ ይህንን ስጨርስ የጡረታ ጊዜዬ ተጠናቀቀ፡፡
ለመልቀቅ ስዘጋጅ እዛው ባጋጣሚ ኮፊ አናንን አገኘኋቸው፡፡ ጡረታ ለመውጣት ሂደት ላይ እንዳለሁ ይሰማሉ፤ ነገር ግን እርሳቸው ወደ ባግዳድ ተዘዋውሬ በእስትራቴጂክ እቅድ ዳይሬክተርነት እንድሰራ አደረጉ፡፡
አንድ ዓመት ተኩል ያህል ቆየሁ፡፡ የጦርነት ቀጠና ስለነበር ብዙ ወዳጆቼ ይሰጉ ነበር፡፡ ሳዳም ሁሴን እስር ቤት ሲገቡ ጀምሮ የገባሁ ተፈርዶባቸው ሲሰቀሉ ነው ከአገሩ የወጣሁት፡፡ በቆይታዬ ስለኢራቅ ብዙ ለማጥናት እድል ነበረኝ፡፡ በእነዶክተር ተቀዳና በአቶ ስዩም በኩል ለሶስት ዓመታት በናይሮቢ የምስራቅ አፍሪካ ጦር አስተባባሪ እንድሆን ተላኩኝ፡፡ በመቀጠልም ሱዳን ውስጥ ዳርፉርና ኮርዶፋን ውስጥ የሂውማኒቴሪያን አስተባባሪ ሆንኩኝ። ይህንን ሳጠናቅቅ ወደ አገር ለመመለስ ፈለግኩኝ፡፡ ወደ አገሬ ከገባሁ በኋም ከእነ ዶክተር ተቀዳ ጋር በመሆን የጥናት ማዕከል አቋቁመን ጥናት እየሰራን ምክር እየለገስን ያለ ክፍያ እያገለገልን እንገኛለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- አምባሳደርነት ከሜሪት ይልቅ ለፖለቲካ ባላቸው ቅርበትና መሰል ምክንያቶች ይሰጥ እንደነበር ይነሳል አሁን ላለው ችግር ተጽእኖ ይኖረው ይሆን በእርስዎ ዘመን ከነበረው ጋር በንጽጽር ይንገሩኝ ?
አምባሳደር ተፈራ፡- በእያንዳንዱ የመንግስት ሥርዓት ደካማ ጎን አለ፣ ጠንካራ ጎንም አለ፡፡ በንጉሰ ነገስቱ ዘመን ቋንቋ እስከቻሉ፣ አገራቸውን በፍቅር እስካገለገሉ፣ ሃሳባቸውን በመግለጽ የንጉሰ ነገስቱን ሃሳብ ለሚላኩበት አገር መግለጽና ማሳመን እስከቻሉ ድረስ ዘር፣ ሃይማኖት ሳይመረጥ ይሾማሉ፡፡ ታማኝነታቸው ለንጉሰ ነገስቱና ለአገር ነው፡፡ በፖርቲ፣ በጎጥ የሚባል ነገር አልነበረም፡፡
ደርግ ሥልጣን ሲይዝ አንድም ባለሙያ አምባሳደር አልተሻረም፡፡ የነበሩትም ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ በደርግ ሥርዓት ቆይቶ ሂደቱ እየተበላሸ ሄደ፡፡ 120 ንጉስ ያለበት አገር አስቸጋሪ ነው፡፡ 120 የደርግ አባላት ራሳቸውን እንደ ንጉስ ይቆጥሩ ስለነበር እርስ በእርሳቸው መሻኮት ሲጀምሩ አስተዳደራዊ ስራዎች መበላሸት ጀመሩ፡፡ በርግጥ ለአገራቸው ፍቅር ነበራቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ አምባሳደሮች እንደወጡ ቀሩ፡፡ ደርግም ሆነ ሌላ ቢመጣ አገራችንን እናገለግላለን ያሉም ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
ደርግ ሻምበሎች፣ አስር አለቃዎች የተሻለ ብቃት ያላቸውን መሾም ሲጀምር መበላሸት ጀመረ፡፡ ትልቁ ነገር መበላሸት የጀመረው ሜሪት ቀርቶ በወገናዊነት መሆን ሲጀምር ነው፡፡ በመቀጠል ኢህአዴግ ሲመጣ መጀመሪያ ባለሙያዎችን ትተው በጥንቃቄ ይዘው ነበር። ግን ቀስ በቀስ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የክልል ኮታ ጀመረ፡፡ ኮታው ይሁን ስድስት ሚሊዮን የትግራይ ህዝብ በአብላጫ አምባሳደር ወይም በአብላጫ ጀነራሎች መወከል የለበትም። ያ ሚዛኑን አዛባ ቀስ በቀስም ሂደቱን አበላሸው፡፡ መጨረሻ ጭራሽ ከወረዳ ጀምሮ እስከ አውራጃ ድረስ የሚገኙ የኢህአዴግ ካድሬዎች ውጭ ጉዳይ ካልገቡና አምባሳደርና ዲፕሎማት ካልሆኑ ተብሎ ተበረዘ፡፡
እንደውም ኢህአዴግ ለሾማቸው ሚኒስትርም ቢሆን ችግር የሚሆነው የዚህ አይነቱ ሹመት ነበር፡፡ እኛ የምንፈልገው ታማኝነቱን ነው እንጂ እውቀት ቢኖረው ባይኖረው ብለው አቶ መለስ እኮ በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ይሄ አይን ያወጣ ወገናዊነት ነበር፡፡
እኔ እስከማውቀው ዋና የሆኑት የዲፕሎማሲ ስራዎች ሂደታቸውን ጠብቀው እየተካሄዱ ነበር። ዶክተር ዐቢይ እንደመጡ የሰዎቹን ብቃት ቋንቋና ሌሎች ሁኔታዎችን መዝነው መሾም ጀመሩ፡፡ አሁንም ቢሆን መንገራገጭ አለ። ምናልባት ሶስት እንሆናለን ለሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ ዲፕሎማቶች ትምህርት በሚሰጥበት ጊዜ እውቀታችንንና ልምዳችንን እንድናካፍል የምንጋበዘው፡፡ ግን ሌላው አገር እኮ ጡረታ የወጣ አምባሳደር፣ ዲፕሎማት፣ ሚኒስትር አይጣልም፤ አይወድቅም፡፡ ለስራ ይፈለጋል። ልዑካን ሲኖር አብሮ ይጓዛል፣ አማካሪ ይሆናል፡፡ የተከማቸ እውቀት በከንቱ እንዳይቀር የማድረግ ሂደት ነው። እኛ ችግራችን ያለፈውን መወቀስ እንጂ ማሞገስ ብዙም ልምዱ የለንም። ከችግርና ከስህተት ነው ይህች አገር እየተማረች የሄደችው። አሁንም ስህተት አለ። በዲፕሎማትም ፍላጎቱ ያለው፣ ዝም ብሎ ተቀጥሮ የሚሰራና ቢችልም ባይችልም ዲፕሎማት ልሁን ብሎ የሚሞክር አለ። ግን መርጦ በሜዳው ላይ የሚሆነውን ማሰማራት ያስፈልጋል።
በአሁኑ ጊዜ በደርግ ጊዜ በሶማሊያ ጦርነት ሰሞን ይካሄድ እንደነበረው አገሪቱ ትልቅ ተግዳሮት አለባት። የዲፕሎማቱ፣ የኢኮኖሚስቱ፣ የወታደሩ፣ የሲቪሉ፣ የቱሪስቱ፣ የእናቶች ድጋፍ የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። የዲፕሎማቱ ደግሞ የበለጠ፡፡ ዲፕሎማሲ ብዙ አቅጣጫዎች አሉት፡፡ አንዳንድ ጊዜ አካኪ ዘራፍ ብለን ሌላውን አገር መስደብ ሳይሆን መጀመሪያ በውስጥ ጠላት የሚያዝበት መንገድ መታየት አለበት፡፡
በንጉሱ ጊዜም አጠቃላይ ምህረት ተደርጓል። መሳሪያውን አስረክቦ ነጭ ባንዲራ እስካውለበለበ ድረስ ምህረት ይደረግለታል፡፡ በርግጥ በወንጀለኝነት የሚፈለግ፣ በሰው ልጆች ጭፍጨፋ የሚፈለገው የሀገሪቱ ህግ በሚያዘው መሰረት ለፍርድ መቅረብ አለበት፡፡ አጥቂና ተጠቂ ቁጭ ብለው ይደራደሩ የሚባለው ነገር ምንም አይነት ትርጉም የለውም፡፡ አጠቃላይ መንግስት ሁሉንም አቃፊ ነው በሚባለው መርህ ተሳስቻለሁ ያለው ምህረት ይደረግለታል፤ ይሄ መኖር አለበት፡፡ በሂደት ወደ ህብረተሰቡ ይቀላቀላል፡፡ ህዝቡም ወንጀለኛውን አሳልፎ መስጠት አለበት፡፡
አሁን በዲፕማሲው መስክ የተለየ ሂደት ያስፈልጋል። ምክንያቱም አሁን የዲጂታል ዘመን ነው። በዲጂታል ዘመን ጠላትህም ወዳጅህም ሚሊዮን ሊሆን ይችላል። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ እውቀቱ ሳይኖራቸው በመሰለኝና በደሳለኝ የሚዘረግፉ አሉ። ይሄንን መስመር ለማሳየት ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ በመንግስት ደረጃና አገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ሳይፈራ ፊት ለፊት ተጋፍጦ በዲጂታሉ መስመር መዋጋት አለበት፡፡
በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው እንደ ባለሙያ ስታዘብ በዜና አቀራረብ ዜናና ኮሜንተሪ አይለያዩም፡፡ በዜናና በትንታኔው ልዩነት መኖር አለበት፡፡ ትንታኔውም ይበዛል። መስተካከል አለበት፡፡ በጥናት በፕሮፖጋንዳ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ ያለንበት ዘመን፣ ያሳለፍናቸው ብዙ ጊዜያት ትምህርት ሊሰጠን ይገባል፡፡
አንድ አስተያየት ሰጪ አሜሪካ አፍጋኒስታን ውስጥ 20 ዓመታት በመዋጋት፣ በትሪሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በማጥፋት ያደረገው ታሊባንን በታሊባን የመተካት ስራ ነው የሰራው ብሏል፡፡ ይሄ በእኛ አገር ላይ እንዳይሆን ህገ ወጥ የሆነ፣ በህግ የሚፈለግ ማንኛውም ድርጅት
ፍርዱን ሳያገኝ እንደገና ተመልሶ ወደ ስልጣን እንዲወጣ የሚያደርጉት የአሜሪካ ልእለ ሃያል ለምንድን ነው? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ካርተር በደርግ ጊዜ በሶማሌ ስንወረር የተገዙትን አውሮፕላኖች፣ የጦር ጀልባዎችና መርከቦችን ሳይሰጠን በመቅረቱ ልንጎዳ ስንል ከሶቭየት ህብረትና አጋሮች ጋር ሆነን ቀለበስን፡፡
አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የባህር ሃይል አቋቁማለሁ ሲሉ በፈረንሳይ ላይ ተጽዕኖ በማድረግ የፈረንሳይ መንግስት የብድር ትብብር ስምምነቱን አግጃለሁ አለ፡፡ ይሄ አገሮች ሁል ጊዜ ከራሳቸው ጥቅም፣ አፍሪካን ከመበዝበዝ ጥቅም አኳያ ያዩታል። እኛ ደግሞ ይሄንን አውቀን በስሜት ሳንገፋፋ በብልህነት የምናደርገውን ማሰብ አለብን፡፡ አሁን በዶክተር አብይና በሌሎችም የሚካሄድ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ስራ አለ፡፡ ብዙ ያልተዘመረላቸው ጥሩ ጥሩ ስራ የሰሩ ዲፕሎማቶች አሉ፡፡ እያንዳንዱ ጋዜጠኛ ዲፕሎማት ነው፤ አምባሳደር ነው፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ለአገሩ አምባሳደር ነው መቆርቆር ይኖርበታል፡፡
ከማኦ ጊዜ ጀምሮ ወደ ቻይና ተመላልሻለሁ፤ እያንዳንዱ ቻይናውያን አንድ ቋንቋ ነው የሚናገሩት፤ አገራቸውን ይወዳሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አመራሩ የቻይናን ህዝብ ስለቀየረው ነው፡፡ ቻይናውያን የትም አገር ጥገኝነት አይጠይቁም፡፡ ያ ህዝብ በሀገር ፍቅር አይደራደርም፡፡ ህንዶችም እንደዚሁ ናቸው፡፡ ቤተ መንግስቱን በማጽዳት ዶክተር ዐቢይ የጀመሩት ስራ ጥሩ ነው፡፡ ይሄ በስነ ልቦናውም በአካላዊም ሁኔታ ወደ መላው አገሪቱ እየተስፋፋ በመሆኑ በጠላት በኩል ከባድ ቅናት አለ፡፡
ኢትዮጵያውያን ሁሉንም የማድረግ ችሎታ አላቸው በሚል ይሰጋሉ፡፡ አፍሪካ ውስጥ ለአፍሪካ ነጻነት የታገልነው እኛ ነን፡፡ ዲፕሎማሲያችን ይሄንን ነው ማስረዳት ያለበት። ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣው በእኛ ላይ የሚያቆም አይደለም ወደ እናንተም ይደርሳል በሚል ማስረዳት አለብን። ቋንቋ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ቋንቋን መካን ማወቅ በእዛ ቋንቋ ደግሞ ለሁሉም ማስረዳት ይገባል። የውጭ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የአገር ውስጥ የተለያዩ ቋንቋዎችንም መልመድ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኞች ከራሳቸው ቋንቋ በተጨማሪ ትግርኛ፣ ወላይትኛ፣ ኦሮምኛ፣ ሱማልኛ ወይም ሌሎቹን ቋንቋዎች ለምን መናገር አለባቸው፡፡ ለመግባባት ይጠቅማቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ሃይሎች ፍላጎት በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ምንድን ነው ?
አምባሳደር ተፈራ፡- ምስራቅ አፍሪካ መቆራቆዣ መሆኑ ከ100 ዓመታት ወዲህ ጀምሮ ያለ ነው። ምስራቅ አፍሪካ ብለን ግብጽን ብንጨምር እንኳን እነ ከዲፍ እስማኤል የቱርኩ ግብጽን ይገዛ የነበረው የአሜሪካ ሜርሲነሪዎችን ቀጥሮ በኢትዮጵያ ላይ ጦር ልኮ ነበር። ለወሬ ነጋሪ ሳይቀር የአጼ ዮሃንስ ጦር ጉና ላይ ድባቅ መትተውታል፡፡ በመተማ ላይ አጼ ዮሃንስ አንገታቸው እስኪቀላ ድረስ ዋጋ የከፈሉት ይህችን አገር ከመሃዲስቶችና ከሌሎች ተስፋፊዎች ለማዳን ነው። ከእዛ በኋላ የጣሊያን ወረራ መጣ፡፡ ኢትዮጵያን ሲሰልሉ ከርመው ያለውን ሀብት በማወቅ ሃያል ነን ለማለት ቅኝ ለመግዛት መጡ። ያ ሳይሆን ቀረ መለስናቸው፡፡ በአድዋም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስትም አልተሳካላቸውም፡፡ በሶማሌ በኩልም ወረራዎች መጥተው ነበር፡፡ በእጅ አዙር፡፡ ይህች አገር በርካታ እምቅ ሀብት አላት፡፡ እንቁ ማእድናት ጀምሮ ዩራኒየም፣ ወርቅ፣ ቤንዚን፣ ፔትሮሊየም፡፡
ወጣት ዲፕሎማትና ጋዜጠኛ እያለሁ ቴናኮ የሚባል የአሜሪካ ኩባንያ ኦጋዴን ውስጥ ቤንዚን ያገኛል። እንደተገኘ ንጉሱ እንዲወርዱ አገር እንዲተራመስ ሁኔታዎችን አመቻቸ፣ ቀጥሎ ቆልፎ ወጣ፡፡ በደርግ ዘመን ደግሞ ሽቭሮን የሚባል ኩባንያ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አግኝቶ ነበር ዘግቶ ወጣ፡፡ ፔትሮናስ የሚባል ሌላ ኩባንያ መጣ አገኘ እንደውም የግብጽ ኢንጅነሮች መጥተው እንዲዘጉት አደረገ፡፡ ለምን ? ብለህ ከጠየቅከኝ ምላሹ እኛን እንደመጠባበቂያ ነው የሚቆጥሩን፡፡ ሌላው ቦታ ሲሟጠጥ ለመጠቀም ነው ፍላጎታቸው፡፡ ሀብቱ ጠፍቶ አይደለም አፍሪካ ለእዚህ ሀብት እምብርት ነው፡፡ ለሎጅስቲክም ምስራቅ አፍሪካ በተለይ ከኢትዮጵያ ለማጓጓዝ ማዕከል ነው፡፡ ፋብሪካ ቢከፈት ምቹ ነው፡፡
አሜሪካኖች የጂኦፖለቲካል ግምታቸውንና ስጋታቸውን ያጋንናሉ፡፡ ብሄራዊ ስጋት አለብን ሶማሊያ ሄደን ሶማሊያን እንውጋ ይላሉ፡፡ ዴሞክራሲን እናስተምር ሊሉም ይችላሉ። ከአፍጋኒስታን ተባርረው ሲወጡ እኛ ዴሞክራሲን ለማስተማር አይደለም የሄድነው ሰላም እንዲያገኙ ነው አሉ፡፡ ትናንት ያሉትንም ዛሬ አይደግሙትም፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ለእስትራቴጂም ቅርብ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የነጻነት ስሜትንም አይወዱትም፡፡ ለሌላው ምሳሌ ስለሚሆን ይፈሩናል። ከነጻነት ትግል፣ ከአፍሪካ አንድነት መቋቋም ጀምሮ አሁን እስካለው ሁኔታ ሌላው አፍሪካ አገር ኢትዮጵያን እንደምሳሌ ስለሚከተል ለእኛ ጠላት ነው የገዛልን። እኛ ግን በደስታ የምንቀበለው ነው፡፡ ምክንያቱም ወንድሞቻችን ነጻ እንዲወጡ፣ የነጻነት ተቋዳሽ እንዲሆኑ አድርገናል፡፡ ዞሮ ዞሮ ልዕለ ሃያላን የሚባሉት አውሮፓ ህብረትና አሜሪካ የፖለቲካ የበላይነትን ለመያዝ ስለሚፈልጉ ነው፡፡
ቻይናዎች ለምን ወደ ኢትዮጵያ መጡ? የአፍሮ ኤሲያ ሶሊዳሪቲ ጉባኤ ሲቋቋም ንጉሱ ወደ አሜሪካ ሄደው የማይረባ እርዳታ ይሰጣቸዋል ቀጠሉና ማኦሴቱንግ ጋር ቻይና ሄዱ፡፡ በዛን ጊዜ ቻይና ደሃ ነው በሚባልበት ዘመን 400 ሚሊዮን ብር ነው ለኢትዮጵያ ለልማት ርዳታ ብድር የሰጡት፡፡ ሶቭየት ህብረትም እንደዛው። ይሄ ኢትዮጵያን የማበልጸጉና የማሳደጉ ሂደት እንበልጣለን ቀጥቅጠን እንግዛችሁ ከሚሉ ሃይሎች የተለየ ስለሆነ ትልቅ ችግር አምጥቶብናል፡፡ ግን ለዘመናት ተቋቁመነዋል፤ ለወደፊቱም እንቋቋመዋለን፡፡ ትናንት ቬየትናም ተዋርደው ወጥተዋል። ሶማሊያ፣ የመን ተዋርደው ወጥተዋል፡፡ በየቦታው በውርደት ነው የወጡት፡፡ አንድ ቦታ በስኬት የወጡበት የለም፡፡
ኢትዮጵያ ምን ጊዜም ቢሆን በማንም ላይ ወረራ ፈጽማ አታውቅም፡፡ ይሄንን ያውቃሉ፡፡ ግን በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ለመፈጸም የተቃጣው እስከዛሬ ለበርካታ ጊዜ በእነዚሁ ምክንያት ነው፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ዕጣ ፈንታ በመንፈስ ጽናት፣ በፍቅር፣ በወንድማማችነት፣ በይቅር ባይነትና ሁሉን አቀፍ በሆነ ፖለቲካ አንድነትን መመስረት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የውጭ አገራት በኢትዮጵያ ላይ ሉዓላዊነትን የሚጋፋ ነገር ሲያደርጉ ይስተዋላል የእነዚህ ዋና ምክንያቱ ምንድን ነው ? በህዳሴ ግድብ ድርድር የውሃ ጉዳይ የደህንነት ስጋት ተደርጎ በጸጥታው ምክር ቤት መታየቱን እንዴት ይመለከቱታል?
አምባሳደር ተፈራ፡– ሉዓላዊነት ማለት የራስን ጉዳይ በራስ መወሰን ማለት ነው፡፡ እኛን እንዳንወስን ነው የሚፈልጉት፡፡ ታዛዣቸውን ነው የሚፈልጉት። አሻንጉሊት መንግስት ለማስቀመጥና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ነው ጥረታቸው፡፡ ላግኝህ ሲባል አይ በደረጃ ተናገር የሚል መሪ ለእነርሱ አስቸጋሪ ነው፡፡
የደህንነት ስጋት የሚባለው በጣም የተጋነነ ውሸት ነው፡፡ ሱዳን መጀመሪያ ውሃው ይደርቅብኛል አለች። ግብጽም እንደዛው፡፡ ጎርፍ ሲያጥለቀልቃቸው ደግሞ አሁን እንተባበር አብረን እንስራ አሉ፡፡ ሱዳን ለአንድ ዓመት ተኩል በዲፕሎማትነት ሰርቻለሁ፡፡ እናውቃቸዋለን። ትናንት ያሉህን ዛሬ አይደግሙትም፤ ይታጠፋሉ፡፡ ይሄ በባህሪያቸው፣ በባህላቸው ያለ ስለሆነ አይገርመንም፡፡ ግን እኛ ለእነርሱ ምናልባት ኦማን አልበሽር ይሆናል የህዳሴው ግድብ ለሱዳንም እንደሚጠቅም በደንብ የተረዳው፡፡
አሁን ባለው ሁኔታም በአንድ መልኩ ኤሌክትሪክ ሽጡልን ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ውሃው በዛ፣ አነሰ የሚል ነገር ያሰማሉ፡፡ ውሃው ተርባይኖቹን አዙሮ አንድም ጠብታ ሳያስቀር ወደእነርሱ ይሄዳል፡፡ ችግር በሚኖር ጊዜም ከቋቱ እንዲፈስላቸው ይደረጋል ይሄንንም ያውቁታል። እኛ አቋማችንን ይዘን መቀጠል፣ ባለን መንፈስ መጽናት ይገባናል፡፡ ግን የልዕለ ሃያላኑ ፍላጎት ከግብጽ ተላላኪዎች፣ ከሱዳን የዋሃን ፖለቲከኞች ጋር በማናቆር እኛን ማናጋት ነው የሚፈልጉት፡፡
አዲስ ዘመን፡- የውጭ ሃይሎች ጫና የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ በተለይም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ (የኢጋድ አገራት) ከመቼውም ጊዜ በተለየ አንድ የመሆን ስጋት የፈጠረው ይሆን?
አምባሳደር ተፈራ፡- እርሱ ብቻ አይደለም ጂኦ ፖለቲካ ቅርጹም እየተለወጠባቸው መጥቷል፡፡ አውሮፓ 100 ዓመት ሙሉ ሲዋጋ እርስ በእርስ ሲናቆር ቆይቶ ከብዙ እልቂት፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአውሮፓ ህብረት ተመሰረተ፡፡ ቀስ በቀስ በአንድ አይነት ገንዘብ፣ በአንድ አይነት የፖለቲካ ሥርዓት፣ በአንድ አይነት የጉሙሩክ ሥርዓት፣ የህዝብ ዝውውር ሥርዓት መመራት ጀመሩ፡፡ ያም ሆኖ ይሄ ታሪካዊ ችግራቸው ያልለቀቃቸው እንግሊዞች መጀመሪያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ከሰሩ በኋላ ተውጠው የቀሩ፣ ያሳነሳቸው መሰላቸው፡፡ ይሄ የትንሽነት ምልክት ነው፡፡ ድሮ የብሪትሽ ኢምፓየር ጸሃይ የማይጠልቅበት ነው ይባል ነበር፡፡ ከኢስያ ጀምሮ እስከ አሜሪካ ድረስ ግዛቶች ነበሯቸው፡፡
ፓርላማዎቻችን አንድ እንዲሆኑ፣ በንግድ ቀጠና፣ የገንዘባችንን ሁኔታ ለማዋሃድ፣ ህዝቦቹ በአንድ ፓስፖርት እንደፈለጋቸው እንዲመላለሱ ጥረት ይደረጋል፡፡ በአፍሪካ ህብረት የሚሰራ ትልቅ ስራ ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ እንዳይሳካ ከውስጥም ከውጭም ሆነው፣ ተወካዮቻቸውን በመላክ እንዲጨናገፍ የማያይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ምክንያቱም ይሄ ቀጠና አንደኛ እስትራቴጂክ ቦታ ነው። እምቅ ሀብቱ፣ የህዝቡም ታታሪነትና ስራን ቶሎ የመለማመድ ባህል የበላይነታቸውን ያሳንሳል፡፡
አሁን እኛ ራሳችንን የቻልን ሉዓላዊ አገር ነን። እናንተም ሉዓላዊ ሀገሮች ናችሁ እንከባበር ነው ያልነው። ሰጥቶ በመቀበል መርህ ላይ ሊመሰረት ይገባል፡፡ የቻይናዎች ግንኙነትን መመልከት ጥሩ ነው። በመንገድ ስራና በተለያዩ ተግባራቶች አብረን ነን፡፡ የእነርሱ መግባትም ትልቅ ጸጋ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ በይፋ ግንኙነትና ስምምነት የመጀመራቸው አዝማሚያ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን የማድረግ እሳቤ ያለው አይደለም?
አምባሳደር ተፈራ፡- እነዚህ ድርጅቶች ሳይስማሙ የቀሩበት ጊዜ መቼ ነው ? ሲጠነሰሱም የፈጠራቸው አንድ ሃይል ነው፡፡ የውጭ ሃይል ነው የፈጠራቸው። አልሸባብን ብትል ከኢስላሚክ ፋንዳሜንታሊስቶች አልቃይዳና ሌሎች መካከለኛው ኢስያን ሲያምሱ የነበሩት ሃይሎች ከአፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ ሶሪያ፣ ጆርዳን፣ ኢራቅ ሌላ አጀንዳ ይዘው ኢስላሚክ ለማድረግ የሞከሩት ነው፡፡
በአንድ በኩል ይፈርጇቸዋል፤ ግን የእነርሱ ብትር እስከሆኑ ድረስ ደግሞ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ በምስራቅ አፍሪካም ሸኔም በለው ሌላም ሌላም ስም ጥራ ሁሉም ቀጣሪያቸው አንድ ነው፡፡ ለቀጣሪያቸው እስካጎበደዱ ድረስ ችግር አለ፡፡ ዋናው ነገር የውጭም የውስጥም ዲፕሎማሲ ማግባባት የሚጀምረው ወይም የሃይል ብትር ውጤታማ እንዲሆን የሚደረገው ውስጥ ተሰግስገው በገቡት የቀጠናው ተወላጆች ነው፡፡ ሌላውን ትእዛዝ ከመቀበል ተቆጥበው አደብ ገዝተው እንደገና ወደቀጠናቸው ህዝብ በበጎነት እንዲመለሱ ማድረግ አንዱ ነው፡፡ በሃይል፣ በማግባባትም ቢሆን ሁሉም አሸባሪዎች ወደ ቀጠናው ህዝብ በበጎነት መግባት አለባቸው፡፡
የውጭ ሃይሎች ዋናው ዓላማቸው ጥቅም ነው። በቀጠናው ብዙ ንግድ በርካታ ተጠቃሚነት አለ፡፡ የደከመ መንግስት በሩን ከፍቶ ያስገባቸዋል፡፡ የፈለጉትን እንዲያደርጉ ይፈቅድላቸዋል፡፡ እነርሱ ይሄንን ነው የሚፈልጉት። ትግላችን ከአገር በቀል ታጣቂዎች ጋር ብቻ አይደለም ከአሜሪካም፣ ከእንግሊዝም ስውር እጅ ጋርም ነው፡፡ ይሄንን መረዳት ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እያቆጠቆጠ ያለው ሸብርተኝነትና ጽንፈኝነት እንዲመክን ከማግባባቱ ባሻገር ምን መተግበር አለበት ?
አምባሳደር ተፈራ፡– ከማግባባቱ ባሻገር ህጋዊ እርምጃ (legitmate force) መጠቀም ይገባል፡፡ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ያንን አፍራሽ ሃይል መቋቋም፣ መደምሰስ፣ ማስወገድ አስፈላጊ ነው፡፡ የተጽዕኖ ሃይል አንዳንድ ጊዜ አሜሪካ ዛሬ ደህና ነው ያለውን ነገ መጥፎ ነው ይልሃል፡፡ ለእነርሱ በሚመቻቸው ጊዜ ነው የሚያደርጉት። የግጭቶች ሁሉ ትልቁ ሰለባ እውነት ነው፡፡ እውነትን በማጣመም በተለያዩ የመገናኛ መንገዶች ዛሬ አመስግኖህ ነገ ይኮንንሃል፡፡ ቀድሞ ማሰብና መገኘት ያስፈልጋል፡፡ ቀድሞ በነበረው የፕሮፓጋንዳና የፖለቲካ ስራ ኢትዮጵያን አቆይተናል። ዛሬ ደግሞ በዲጂታል ዘመኑ በሚጠይቀው አቀራረብ መተግበር አለበት፡፡
የሶቭየት ውህደት ጊዜ ጉሩ በሚሉት አጠራር (departemente of disinformation) የሚባል ክፍል ነበራቸው። ይሄ ክፍል አሜሪካኖችን ሶቭየት ህብረት ይሄንን ያህል ሮኬት ተክሏል በሚል በተመሳሳይ የሃሰት መረጃ የማወናበድ ስራ ነበረው፡፡ ይሄ የሥነ ልቦና ጦርነት ነው፡፡ አሁንም የስነ ልቦና ጦርነት በማድረግ አንድ የሽፍታ ቡድን (አጋሚዶ ቡድን) ሁለት ሶስት ሰዎችን ጠሽ ጠሽ አድርጎ ተቆጣጥረናል ይልሃል፡፡ ያን ጊዜ ልቦናህን ሰለበው ማለት ነው፡፡ ሰው ጥሎ ይሸሻል በቃ ተይዟል፣ ተቆጣጥሯል በሚል፡፡ ተጋትረህ ምን እንደተፈጠረ እውነቱን በማጋለጥ ያ የሃሰት መረጃ ይፈርሳል፡፡ ሶቭየት ህብረት 70 ዓመት ሙሉ በሃሰት መረጃ ኖሮ እኮ ፈራርሷል፡፡ እኛ እንዴት በሃሰት መረጃ እንፈታለን። የምንጽፈው የምንናገረውና የምናስተላልፈው ሁሉ ተመዝኖ ምን ተጽእኖ ወይንም እንድምታ ይኖረዋል የሚለውን ከማስተላለፋችን አስቀድመን አንደ ጋዜጠኛም እንደ ዲፕሎማትም ራሳችንን መጠየቅ አለብን፡፡ ይህንን እስካላደረግን ጊዜ ድረስ በደሳለኝና በመሰለኝ ካልከው ተያይዞ ገደል መግባት ነው የሚሆነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ አንድ ዲፕሎማትና ጋዜጠኛ የትህነግ የሃሰት ፕሮፖጋንዳ የኢትዮጵያ ብዙሃን መገናኛ ከዚህ አኳያ እየሰሩት ያለውን ነገር እንዴት ይገመግሙታል?
አምባሳደር ተፈራ፡– የኢትዮጵያ ብዙሃን መገናኛ በተቻላቸው መጠን በእውቀታቸው መሰረት የተቻላቸውን እንዳደረጉና እንደሚያደርጉም አምናለሁ፡፡ ያም ሆኖ ከትችት ነጻ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም አንዱን ዜና እስኪሰለች ድረስ ይደጋግሙታል፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ እኮ ከሰራዊቱ ጋር ጦር ግንባር ሄደው የሚዘግቡ ባለሙያዎች አላየሁም። ሰው የሚያምነው ባለሙያው በቦታው ተገኝቶ ሲዘግብ ነው፡፡ በቴሌቪዥንም ቢሆን በገበያ ቦታ ተገኝቶ ስለጦርነቱ ምን ታስባለህ ብሎ የሚጠየቅን አስተያየት ሊሆን አይገባም። እስኪሰለች ድረስ ከባሌ እስከ ጉለሌ ድረስ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ሰብስበህ ትንተና ማቅረብ ዋጋ የለውም፡፡ በትንተናው ምንድን ነው ሃሳብ የሚሰጡት? ምክረ ሃሳብ ያስፈልጋል፡፡
በዜና ሰዓት ዜና ብቻ፣ ሐተታን በሐተታ ጊዜ አቅርቡ፣ ዓላማው ምንድን ነው፣ ምን ይጠቅመዋል፡፡ ይሄንን አውቆ የፕሮፖጋንዳ እቅድ ዝግጅት ካልተደረገ ችግር ነው፡፡ በእኛ አገር ያሉ በጣት የሚቆጠሩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አንዳንድ ጊዜ ሲታዩ የኮሜንተሪና የዜና መስመር አይታይም፡፡ ሰው ዜና አሁን ይቀርብልኛል ሲል ሌላ ይቀርባል፡፡ ለእኔ ዜና ሱስ ነው አንዳንዴ ስመለከት ዜና ሳይሆን በኮሜንተሪ ይጀምራል፡፡ ምሁራን የሚነግሩንን ሳይሆን የሚዲያ ተቋሙ ባለሙያዎች በስፍራው ተገኝተው የተመለከቱትን ሊያሳዩን ይገባል፡፡ እውቅ የተባሉ ጋዜጠኞች እነ ክርስቲያን አማፖር ታሊባን መንደር ገብተው ነው ሪፖርት የሚያቀርቡልን፡፡ አልቃይዳ መንደር ገብታ የእነርሱን ልብስ ለብሳ ሪፖርት ታደርጋለች፡፡ የሀሰት ፕሮፖጋንዳውን በቦታው ተገኝቶ በመዘገብ ማጥራት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ነው የጎደለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያውያን የአርበኝነት ስሜትና የህዝቡን አንድነት እንዴት ይመለከቱታል?
አምባሳደር ተፈራ፡- ኢትዮጵያን ያዳናት የአርበኝነት ስሜቱ እና የሕዝቡ አንድነት ነው፡፡ ኦሮሞ፣ ትግራይ፣ ሱማሌ፣ ቤኒሻንጉልና ሁሉም ብሄረሰቦች አንድ ኢትዮጵያ ናት ያለችን ብለው በአንድ ቤት ውስጥ የተሰባሰበ ወንድማማችነት አለን ማለታቸው ነው አገርን ያዳነው፡፡ ከአገር ውጭም ከጫፍ ጫፍ ያሉ ዜጎችን የሚያነቃንቃቸው የአንድነቱ ስሜት ነው፡፡ ያ ስሜት እንዲዳብር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ያ ስሜት ነው ኢትዮጵያን ያዘለቃት እንጂ የጦር ሃይል ብዛት አይደለም።
ጣሊያን እኮ የታጠቀው ሌላ ነበር፡፡ አሜሪካ ቪየትናም ሲገባ የታጠቀው ወደር የሌለው ሃይል ነበር። ግን የቪየትናም ህዝብ አንድነት፣ የቪየትናም ህዝብ ጽናት፣ የቪየትናም ህዝብ አርበኝነት ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ጽናት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኝነት አገሮቹን ያዳናቸው፡፡ ይሄንንም አጠናክሮ መቀጠል አማራጭ የሌለው ነው፡፡ ቆም ብለን ያለብንን ስህተትና ክፍተት መፈተሽ አለብን፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሶሻል ሚዲያው አስደሳች ዜና፣ አስደንጋጭ ዜና ይላሉ። እነርሱ ራሳቸው አዘጋጆቹ ናቸው የደነገጡት፡፡ ህዝቡን ለማስደንገጥ፤ የእነርሱ ድንጋጤ እኛን ሊፈታን አይገባም።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብነቱን ለመቋቋም ልትከተለው የሚገባ የፖሊሲ አማራጭ ምን መሆን አለበት?
አምባሳደር ተፈራ፡– አማራጭ ፖሊሲ መያዝ ሳይሆን ፖሊሲ እንዲኖር ነው የሚያስፈልገው። ዲፕሎማሲ ከግንድ ጋር መጋጨት አይደለም፡፡ አሜሪካ ትልቅ ግንድ ነው፡፡ ራሺያ ትልቅ ግንድ ነው። ቻይና ትልቅ ግንድ ነው። እነዚህን በዘዴ ነው መያዝ የሚገባው፡፡ በደጋፊዎቻቸው በኩል ወይም በቀጥታ የሚገባበት መንገድ አለ፡፡ እንዴት አድርገን የጋራ መግባባት ላይ እንድረስ ብለህ ማነጋገር ይገባል፡፡ እንጂ ወጣቱንም ሌላውንም አንስተህ ይውደሙ ብለህ አካኪ ዘራፍ በማለት ዲፕሎማሲውን አትሰራም፡፡ አነጋግረህ ለስለስ ግን ጠንከር ብለህ ነው መሆን ያለበት። ከዚህ ቀይ መስመር እናንተም አትለፉብን ብለህ ማሳመን ይጠበቅብሃል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የምስራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) እንዴት ይገልጹታል? ውህደቱን ለማሳካት አባል አገራቱ ሚናቸው ምን ሊሆን ይገባል?
አምባሳደር ተፈራ፡– ኢጋድ መጀመሪያ ሲመሰረት የድርቅን ሁኔታ ለመቋቋም፣ የከብት አርቢዎችን፣ የድንበር ተሻጋሪ ሁኔታን ለመቆጣጠር ነበር፡፡ ከእዛ በኋላ ወደ ሰላምና ደህንነት ጥበቃ ውስጥም ገባ፡፡ ይሄ ደግሞ ጥሩ መሳሪያ ስለመሰላቸው አሜሪካውያኖችም፣ አውሮፓውያኖቹም ትንሽ ይደጉሙታል፡፡ አሁን ደግሞ ዋና ጸሃፊው ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡
ኢጋድ እንደ ሰላም መሳሪያ ልንጠቀምበት የምንችለው ድርጅት ነው፡፡ ሌሎቹንም ማሳተፍ የሚችል ነው። ኢጋድን ማጠናከር አማራጭ የለውም፡፡ ነገ አገሮቹ በኢኮኖሚ፣ በሳይንስ፣ በግብርና በገንዘብ ውህደት ውስጥ ትልቅ ሚና የሚኖረው ነው፡፡ ግን እንደ አለመታደል ሆኖ ራዕይ ያለው የሰው ሃይል አልተዋጣለትም፡፡ በውስጡ ራዕይ ያላቸው ሰዎች ሊገቡ ይገባል፡፡ ኢጋድን በገንዘብ የሚደግፉት አባል መንግስታት ለውህደት ያላቸውን ራዕይ እውነት እንዲሆን መዘጋጀትና መፍቀድ አለባቸው፡፡ ህሊናዊ ዝግጅት ያስፈልጋቸዋል፡፡
የኢጋድ አባል አገራት መሪዎች በመካከላቸው ያለውን ቅራኔ በመተው በዚህ ድርጅት አማካኝነት ለጋራ ዓላማ እንዴት እንሰለፍ ብለው መወሰን አለባቸው፡፡ ጸብ ሲነሳ ለማስታረቅ፣ ችግር ሲኖር ለመፍታት የፖለቲካ ፍቃደኝነት ያስፈልጋቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሜሪካና ሌሎች ሃይሎች በሌሎች አገሮች ጣልቃ የሚገቡበት አንዱ ምክንያት ጠንካራ መንግስት መኖሩ ነው ተብሎ ይነሳል። እነርሱ የሚፈልጉት ሎሌ መንግስት መሆኑ ይነገራል።አሁን ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለው ጫና የእዚህ አመላካች ነው ማለት ይቻላል?
አምባሳደር ተፈራ፡- ልክ ነው እነርሱ ሎሌ መንግስት ነው የሚፈልጉት፡፡ የእዚህ አመላካች ከመሆኑም ባሻገር ስትጠነክርም ይፈሩሃል ወይም ደስ አይላቸውም፡፡ ግን በጠነከርክ ቁጥር ያከብሩሃል፡፡ ሸብረክ ካልክላቸው ሁል ጊዜ አንተን ይዘው ለመጠምዘዝ ነው የሚፈልጉት። አንድ ጊዜ ፈሪነትህን፣ ታዛዥነትህንና ባርነትህን ካሳየህ እነርሱ በዛው ነው የሚቀጥሉት፡፡ ነገር ግን ጠንካራነትህን ካሳየህ ሁል ጊዜ ከመተናኮል ወደ ኋላ አይሉም። ያከብሩሃል ግን መተናኮል አይተውም፡፡ አንተ ሁል ጊዜ አይንህን ከፍተህ ነቅተህ የሚመጡበትን ቀዳዳዎች ሁሉ ዘግተህ መጠበቅ አለብህ። ያከብሩኛል ብለህም በጣም እንዳትደሰት፣ ይጠሉኛል ብለህም አታርቃቸው። በተወሰነ ደረጃ በብልሃትና በብልህነት መጓዝ ይገባል። ንጉሱ እኮ ከሳላዛር የመሰለ ፋሽስት፣ ማኦን ከሚያህል ኮሚኒስት፣ ብሬዥኔቭን ከሚያህል ኮሚኒስት፣ ከኬኔዲ ፤ ከእንግሊዝ ንግስት ጋር እንደየመልኩ ነበር የሚይዙት፡፡ ይሄ ያስፈልጋል፡፡
ትልቁ ነገር ጋዜጠኞችን የምለምናቸው ታሪክ አንብቡ። ታሪክ ትምህርት ነው፡፡ ታሪክን ያላነበበ ጋዜጠኛ መሳሪያውን ሳይይዝ ጦርነት የሚገባ ወታደር ነው፡፡ ታሪክን ያነበበ ጋዜጠኛ ሁል ጊዜ አሸናፊ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ!
አምባሳደር ተፈራ፡- እኔም ለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ!
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2014