ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ እጅግ ፈታኝ ቢሆንም ህዝቦቿ ግን ከጎኗ እንዳሉ በብዙ መንገድ በማሳየት ላይ ናቸው። መዝመት ያልቻለው ካለው ላይ እያዋጣ ድጋፉን ሲያደርግ የቻለው ደግሞ ይህንን ጠላት ለመፋለምና አገሩን ለማቆም ዘመቻውን ተቀላቅሏል። የተፈናቀሉትንም ቢሆን በማገዝ የተሰማራው ቀላል አይደለም። እናም ይህ ፈተና እውን ይታለፍ ይሆን፤ አሁን ያለው ወቅታዊ ፈተና ምን ይመስላል፤ የማንስ ስሪት ነው፤ እንዴት መፈታት አለበት በሚሉና መሰል ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን እንዲያጋሩን በሐረሚያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የሥርዓተ ትምህርት መምህር በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ ከሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው ጋር ቆይታን አድርገናል። ሀሳባቸውንም እንደሚከተለው አቅርበነዋልና ተከታተሉን።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በታሪኳ የተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን ተጋፍጣለች። ለመሆኑ አሁን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ሲታይ ከመጣችበት የታሪክ ውጣ ውረድ አንጻር እንዴት ይታያል?
ረዳት ፕሮፌስር ሲሳይ፡- ኢትዮጵያ አሁን እየገጠማት ያለው ፈተና በታሪክ ከገጠሟት ፈተናዎች የሚበልጥ አይደለም። ነገር ግን ባለፉት ዘመናት የነበረው ፖለቲካዊ ስሪታችን፤ ታሪካችን እናይ የነበረው አንድነታችን አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ አለ ብሎ ለመናገር አይቻልም። ያ ምናልባት እንደፈተና የአሁኑን ችግር ሊያከብደው ይችላል የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም ህወሓት መራሹ መንግስት ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ሀገር ሲያስተዳድር በጎሳ፤ በቋንቋ፤ በአካባቢ፤ በማንነት ስለከፋፈለው እንዲህ ዓይነት ችግሮች ሲመጡ በአንድነት ላይቆሙ ይችላሉ የሚሉ ስጋቶች አሉ። ይሄ ራሱ ተጽዕኖ ፈጥሯል፤ አሁን ላይ ብዙ ሰዎች ከየትኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች መነሳሳትና ድጋፍ አለ፤ በተለይ ለመከላከያ ሰራዊቱ እና ህወሓትን ለሚፋለሙ ኃይሎች በሙሉ ድጋፍ እያደረጉ ነው የሚገኙት። የስንቅ፤ የሞራል ድጋፎችን እየሰጡ ነው። ይሄ እንግዲህ ኢትዮጵያዊነት በዘመናት መካከል የተገለጠበት አጋጣሚ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
ይህ ፈተና ኢትዮጵያ ስትጠቃ ወይንም ጫናዎች ሲደርሱባት ኢትዮጵያዊያን አብረው መቆም እንደሚችሉ ዳግም ያረጋገጡበት ምዕራፍ ነው። ነገር ግን ፈተናው እንዲህ በቀላሉ የሚታይ መሆን የለበትም። የሱዳን ጫና አለ፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ በአሻጥር ተጎድቷል። የምዕራባዊያን ጫና አለ፤ እንዲሁም በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ስሪት በራሱ ሌላኛው ችግር ነው። እነዚህ ፈተናዎች ሲደማመሩ ሀገራችን አሁን ያለችበት ፈተና ቀላል ተደርጎ አይወሰድም። ከባድ ፈተና ላይ ነች።
አዲስ ዘመን፡- የተለያዩ የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ሲያደርጉ የነበረው ጫና ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን የቆየ እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ይነሳል፤ ለምሳሌ በጣልያን ወረራ ወቅት ያጋጠማት ፈተና ነበር፤ ከዚህ አንጻር የቀደሙ የውጭ ጫናዎች እና አሁን ያለው ጫና እንዴት ይታያል?
ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፡– ኢትዮጵያ በታሪክ የገጠሟትን ፈተናዎች ለማለፍ የበቃችው ትልቁና መሰረታዊው ምክንያት በሀገራዊ ጉዳይ ላይ በየትኛውም አካባቢ ያለው ህዝብ አንድነት ስላለው ነው። ሁለተኛው የክተት ጥሪ ሲታወጅ ሁሉም የማህበረሰብ አደረጃጀቶችና የኃይማኖት ተቋማት ጭምር የየአካባቢው አመራሮች ሳይቀሩ ለማዕከላዊው መንግስት ጥሪ ፈጣን ምላሽ በመስጠት በአንድ ላይ በመክተት ባላቸው መሳሪያ ጠላትን መፋለማቸው ነው። ስለዚህ ይሄ ለሀገራቸው አንድነትና ህልውና ሀገረ-መንግስት ቀጣይነት ጠንካራ እምነትና ሞራል ስለነበራቸው አሸናፊነታቸው ሳይቋረጥ ቀጥሏል።
ሌላው የነበራቸው አደረጃጀት ወይንም የዕዝ ሰንሰለት በጣም ጠንካራ መሆኑ ሲሆን፤ እንደ ዛሬው ዘመናዊ ባይሆን እንኳን ለንጉሱም ሆነ ለአካባቢው ገዢዎች የነበራቸው ክብር እና ንጉሱ የሚናገሩትንና የሚያስተላልፉትን መልዕክትና ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ በዕምነት መቀበላቸውና ማመናቸው፤ ሃሳባቸው ሳይበታተን ጠላቶቻቸውን መመከት እንዲችሉ አስችሏቸዋል። ነገር ግን በዚያን ወቅትም ቢሆን የደረሱት ጉዳቶችና የተከፈለው መስዋዕትነት እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
የነበሩት ጫናዎችም ከአሁኑ ጫናዎቹ ጋር በመሰረታዊነት የሚለያዩት በቀደመው ጊዜ ሀገራችን በራሷ የቆመችና የኢኮኖሚ ጥገኝነት አልነበራትምና ነው። ህዝቡ ገበሬ ነው ያርሳል፤ ይበላል። ከውጭ የሚያገኘው ነገር ብዙም የለም፤ በእርዳታ ላይ ጥገኛ የሆነ ማህበረሰብ አልነበረም። ስለዚህም ህዝቡን በእርዳታ ሊያስፈራሩት አይችሉም፤ ወይም በሌላ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ሊያስፈራሩት እድል አልሰጣቸውም። አንዱ የሚያስፈራሩት ነገር እኛ ከእናንተ የተሻለ የጦር ዝግጅትና ወታደራዊ አቅም አለን ብለው ብቻ ነው።
በጀግንነት ወይንም በባህል ሊያስፈራት አይችሉም፤ በአስተዳደራዊ አደረጃጀት ሊያስፈራሩት አይችሉም። አሁን ያለው የመጀመሪያው ጫና ግን ኢኮኖሚያዊ ጫና ነው። ሁል ጊዜ የሚያሰፈራሩን የኢኮኖሚ ማዕቀብ እንጥላለን፤ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀበ በመጣል እርዳታዎች እንዲቋረጡ እናደርጋልን፤ ከውጭ የምታስገቡት ነገር እንዳይኖር እናደርጋለን፤ በዚህም ከፍተኛ ህዝብ ለጉዳትና ለረሃብ ይጋለጣል፤ ያ ደግሞ ረሃብተኛ ማህበረሰብ ደግሞ መንግስቱን ያፈርሳል ብለው በማሰብ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጫና ያደርጋሉ፤ የኢኮኖሚ አሻጥሩም አንዱ ነው።
ያኔ የኢኮኖሚ አሻጥር መፍጠር አይችሉም፤ አሁን ግን ማድረግ ይችላሉ። አሁን ላይ ማዕቀብ መጣል ይችላሉ፤ ያኔ ግን በጣሊያን ጊዜ የተጣለው ማዕቀብ ምንም ጉዳት እንዳላመጣ አይተውታልና ዳግም አላደረጉትም። አሁን ቢጥሉ ግን በራሱ የሚፈጥረው ችግር ይኖራል። ስለዚህም ሀገሪቱ በኢኮኖሚ ራሷን አለመቻሏ፤ እንዲሁም ከዚህ ቀደም የነበረው መንግስታዊ ስርዓትና አሰራር ለእነሱ ተገዢና ታዛዥ መሆኑ ደካማ መንግስት እንዲኖረንና በኢኮኖሚ እንኳን ራሳችንን ችለን የሀገራችንን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ በማንችልበት ደረጃ ላይ ትተዋት የሄዷት ሀገር ስለሆነች ጫናው ከቀደመው ይለያል።
ሁለተኛው ደግሞ ይሄንን ሀገር በጎሳ ተዋቅሮ እርስ በርሱ በጥርጣሬ እንዲተያይና በብሔር ማንነትና በቋንቋ ልዩነት ሀገሪቱን እንበትናለን የሚል ማስፈራሪያና ልዩ ልዩ በተለያዩ አካባቢዎች ታጣቂ ቡድኖችን በማደራጀት፤ ለምሳሌም በሶማሌ የኦጋዴን ነጻ አውጪ፤ በኦሮሚያ የኦሮሚያ ነጻ አውጪ፤ በትግራይም እንደዚያው ነጻ አውጪ ግንባርን የአሁኑን ህወሓትን የመሳሰሉትን በማደራጀትና በመደገፍ ሀገሪቱንም በጎሳ ለመከፋፈልና ለመበተን ከፍተኛ ስራዎችን እየሰሩ እኛ ካልፈቀድን በስተቀር በሚል እነዚህን ቡድኖች በማሰማራት ሀገረ መንግስቱን ለመበተን ሲንቀሳቀሱ ይታያል። ምዕራባዊያን በህቡዕም ሲደግፉ ይታያል። እናም ይሄ ለሀገሪቱ ከቀደሙት ፈተናዎች የተለየ ፈተናው ከባድ እንዲሆንባት አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያ ላይ የከፈተው ጦርነት ከዚህ ቀደሙ በምን ይለያል፤ የሚያደርገው ጦርነትንና እኩይ ድርጊቱን እርስዎ እንዴት ያብራሩታል?
ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፡– የትግራይ ህዝብ በቀደመው የጦርነት ጊዜ የነበረው ተሳትፎ ከአሁኑ ይለያል፤ ምንም ጥርጥር የለውም። የቀደመው ጦርነት ይነስም ይብዛ ደርግ የሚባለው ስርዓት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ አምባገነናዊ ስርዓትን በመዘርጋት በቀይ ሽብር፡ በነጭ ሽብር በጣም ብዙ ሰዎች ህይወታቸውን እንዲያጡ ምክንያት ሆኗል። የዴሞክራሲ ተስፋም አልነበረም፤ አፋኝ የነበረ ስርዓት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ስለዚህ ያንን አፋኝ ስርዓት የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ታግሎ አጥፍቶታል። ብዙ የባላባት ልጆች፤ የቀይ ሽብር ተማሪዎች፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፤ ምሁራን በከተማም ታግለውታል።
ደርግን በብቸኝነት እንደ ታገለ አድርጎ የሚያቀርበው የታሪክ አተያይና ትርክት ውሸት ነው። ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ ደርግን ታግለውታል። በነበረው ስርዓት ደርግ የራሱ ጠንካራ ጎን ቢኖረውም ሀገረ-መንግስቱን በማጠናከርና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት እንዲኖር በማድረግና ለምዕራባዊያን የማይንበረከክ ስርዓት ለመዘርጋት ያደረገው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም በሀገር ውስጥ ግን ዴሞክራሲያዊ ስርዓትንና ህዝቡ የሚፈልገውን ዓይነት ስርዓት መዘርጋት አልቻለም። ስለዚህም ይሄንን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ታግለው አሸንፈውታል። የትግራይ ህዝብም እንደ አንድ የኢትዮጵያ ህዝብ አካልነቱ ታግሎታል እንጂ ብቻውን አላደረገውም። ያ ምክንያት ሆኖ ግን ደረቱን ነፍቶ እንዲሄድ አድርጎት ቆይቷል። ያልሆነው ሆኗልም።
አሁን ጦርነቱን የጫሩት፤ ያወጁት፤ የጀመሩት ራሳቸው ናቸው። ጦርነቱን ደግሞ ሲጀምሩ የጀመሩት የሀገሪቱን የመከላከያ ሰራዊት በማጥቃት ነው። ከዚያ በፊት መንግስት በርካታ ልመናዎችን፤ ማባበሎች አድርጓል፤ ሽማግሌዎችን፤ ምሁራንን፤ የኃይማኖት አባቶችን ልኳል፤ ወደዚህ ጦርነት እንዳይገባ በርካታ ድርድሮችን አድርጓል። ይሄንን ሁሉ የትግራይ ህዝብ አይቷል። ነገር ግን በመጨረሻ ከትግራይ ህዝብ አብራክ የወጡ አሸባሪዎች የትግራይን ህዝብ ለዘመናት ሲጠብቅ የነበረውን፤ የደማውን፤ የቆሰለውን፤ ሲያግዝ የነበረውን፤ የሞተለትን፤ ብቸኛውና የመጀመሪያውን የሉዓላዊነት መገለጫና አስጠባቂ የሆነውን ተቋም መከላከያ ሰራዊትን አጠቃው። ህዝቡ ደግሞ ሲያጠቁ አይቷል፤ በሚዲያ ሲናገሩም ሰምቷል። ስለዚህ የመከላከያ ሰራዊቱ መመታትና መጠቃት ትክክል ነው ብሎ የሚያስብ ህዝብ ካለ ስህተት ነው። ህዝብ አይሳሳትም የሚለውን እዚህ ጋር ልናስተካክለው እንችላለንም።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ በአሸባሪነት የተፈረጀው ቡድን ያኔ ሲመራ ማለትም በነፃነት ስም ሲያደርግ የነበረውና በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የከፈተው ጦርነት በምን ይለያል ?
ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፡– ህወሓት ሀገሪቱን ለ27 ዓመታት ሲመራ የሀገሪቱን ተቋማት የፋይናንስ አደረጃጀት አድርጎ ተጠቅሞ ነው የኢትዮጵያን ህዝብ ሲበዘብዝም ሲጨፈጭፍም የነበረው። በሀገሪቱ በብዙ አካባቢዎች ሰዎች በማንነታቸው እንዲፈናቀሉ፤ እንዲገደሉ አድርጓል። ወደ ፖለቲካው መድረክ የሚመጡ ሰዎችን ጭምር በማሰር፡ በማኮላሸት፡ በመደብደብ አሰቃቂ ግፍ ፈጽሟል። የሀገሪቱን ሀገረ- መንግስት ልዕልናን በትኗል። ይህም በማህበረሰቡ ስነ ልቦና ላይ የተከፈተ ትልቅ ጦርነት ነው።
በሀገር፣ በታሪክ፣ በአንድነት ላይ የተከፈተ ጦርነትና በተግባርም የመንግስትን መዋቅር በመጠቀም በተለይም ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት ተቋምን በመጠቀም፤ በማፈን የሽብር ስራዎችን በመስራት በተለያየ አካባቢዎች ሰዎችን በማንነታቸው እንዲገደሉና እንዲፈናቀሉ በማድረግ፤ በፖለቲካ ምህዳሩ ውስጥ ደግሞ መጥተው ለመሳተፍ የሞከሩ አካላትን በመግደል፤ በማሰርና በማሰቃየት ከፍተኛ ጦርነት ከፍቷል።
ያኛው ጦርነት እንግዲህ የመንግስት መዋቅርና የፋይናንስ አደረጃትን ተጠቅሞ በኢትዮጵያ ላይ የከፈተው ጦርነት ነው። ያ ሁሉ ደግሞ ከዚህ ከተባረረ በኋላ በዚያን ዘመን በዘረፈው ሀብት አንድን ማህበረሰብ መነሻና መቀመጫውን አድርጎ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የከፈተው ጦርነት ነው። ስለዚህም የአሸባሪው ተግባር የቦታና የስልጣን መዋቅር ልዩነት ካልሆነ በስተቀር የሽብር ድርጊቱና ተግባሩ ተመሳሳይ ነው። ብዙም ልዩነት የለውም። ልዩነቱ የፋይናንስ፤ የአደረጃጀት፤ የመዋቅር፤ የሰው ሀይልና አዲስ አበባ ቁጭ ብሎ ጦርነቱን መምራት ብቻ ነው። ትግራይ ላይ ተቀምጦ አሁንም ኢትዮጵያን ማተራመስና ራሱ ያደራጀውን ጦር ሳይቀር ለመበተንና ሀገሪቱን ለመውጋት እያደረገ ያለው ጦርነት በባህሪይው ተመሳሳይ ናቸው። ነገር ግን በአሰራና እየተከተለ ያለው የአካሄድ ስልት ልዩነት አለው።
ያን ጊዜም ሀገሪቱን ለከፋ አደጋ እንድትጋለጥ በቅንጅት ከውጭ ኃይሎች ጋር ይሰራ ነበር፤ የውጭ ኃይሎች ያኔም ድጋፍ ያደርጉለት ነበር፤ አሁንም ድጋፍ ያደርጉለታል። ህወሓት ብቻውን ቆሞ ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደማይችል ጠንቅቆ ያውቃል። ስለዚህም በአሁኑና በቀደመው መካከል መመሳሰሎቹ የድጋፍ እና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የያዘው ፕሮጀክት አካል መሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የአሸባሪውን ሂሳብ እናወራርዳለን የሚለውን ስሌት እንዴት ያዩታል?
ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፡- ህወሓት በባህሪው እንደ ድርጅት አፋኝ ቡድን ስለሆነ አንድን ማህበረሰብ ጠላት አድርጎ በመፈረጅ፤ ያንን ማህበረሰብ ለማጥፋት አቅዶ ሲንቀሳቀስ የነበረ ቡድን ነው። ስለዚህ በእሱ ስር ያደጉት ልጆች በሙሉ የዚህ አስተሳሰብ ሰለባዎች ናቸው። እንደ አለመታደል ሆኖ ህወሓት አጠፋዋለሁ ብሎ የሚያስበው ማህበረሰብ ኢትዮጵያን የሰራ፤ ኢትዮጵያን ያዋቀረ ትልቅ ህዝብ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገር ለመበተን በመጀመሪያ ደረጃ አማራ የሚባለውን ማህበረሰብ መምታት፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኦርቶዶክስ የሚባለውን የእምነት ተቋም ማፍረስ የሚል የጣሊያኖች ፕሮጀክት አለ፤ የዚያ የጣሊያን ፕሮጀክት ወራሽ ስለሆነ ይህንን እያደረገ ይገኛል።
ከጣሊያኖች የሚለየው በራሱ ሀገር ላይ የራሱን ሀገር በማፍረስ የዚያ ፕሮጀክት አስፈጻሚ መሆኑ ነው። ስለዚህ አወራርዳለሁ የሚለው፤ አጠፋለሁ የሚለው ያ ማህበረሰብ ካልጠፋ በኢትዮጵያ ላይ የበላይነት ይዤ መኖር አልችልም፤ ኢትዮጵያን መምራት አልችልም፤ ኢትዮጵያን መዝረፍ አልችልም ከሚል አቋም የተነሳ ነው። አሁን በሚዲያ ተናገሩት እንጂ ከ40 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለውና በጽሁፍ ያስቀመጡት አስተሳሰብ ነው።
ይሄንን ማህበረሰብ ፈርጀው ለማጥፋት ሲንቀሳቀሱ እንደነበረ የአደባባይ ምስጢር ነው። ስለዚህ አሁን በሚዲያ ተናገሩት እንጂ የአማራን ህዝብ ለማጥፋት ከፍተኛ ስራዎችን ሲሰሩ ኖረዋል። አሁንም በተግባር እንደምናየው በአብዛኞቹ የሰሜን ወሎ እና ደቡብ ጎንደር፤ በወልቃይት፡ በራያ አካባቢ ወረራ በመፈጸም፤ ህጻናትን፣ እናቶችን በመግደል፣ በመድፈር፣ ቤታቸውን ንብረታቸውን በማቃጠል የማዋረድ ተግባር ጀምረዋል። በመከላከያ ሰራዊት፡፣ በአማራ ልጆች፣በፋኖ ባይመከት እስከ አዲስ አበባ ድረስ መጥቶ ይህንን ህዝብ ከማጥፋት ወደኋላ የማይል ቡድን እንደሆነ በተግባር እያረጋገጠ ያለ ነው።
ከተፈጸመበት ግፍ አንጻር ማወራረድ ያለበትም የአማራ ህዝብ ነው። ላለፉት 27 ዓመታት የአማራ ህዝብ ወደ ትግራይ ሄዶ አንዲትም ነገር አላደረገም። አማራ በሚያስተዳድርበት ዘመን እንኳን ትግራይን ያስተዳደረ አማራ የለም። ትግራይ የሚባለው አካባቢ እራሱን ሲያስተዳድር የኖረ ማህበረሰብ ነው። ከአማራ ጋር ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ወይም የአስተዳደራዊ ሽኩቻዎች አልነበሩትም። ሸዋ ላይ የነበሩት እንኳን የአማራ ነገስታት ወደ ሰሜን ሲሄዱ በራሳቸው ልጆች ትግራይን እንዲያስተዳድሩ ነው የሚደረጉት። ራስ መንገሻ ለዚህም ምሳሌ ናቸው። ከዚያም ወዲህ ትግራይን ሊያስተዳድር የሄደ አማራ የለም። እነሱ ግን የአማራ ክልል ቀበሌ እስከ ጎጥ ድረስ መጥተው የአማራን ህዝብ ሲዘርፉ፤ ሲቀጠቅጡ ሲያስሩ ነው የኖሩት። ስለዚህም ማወራረድም ካለበት አማራው፤ ሶማሌው፣ አፋሩ፣ ኦሮሞው ወይም ሌላው ማህበረሰብ ነው እንጂ እርሱ አይደለም። በዚህ ንግግራቸው ማፈር አለባቸው። ከትግራይ ህዝብ የወጡት እነዚህ ቡድኖች ከፈጸሙት በደል አንጻር የትግራይ ህዝብ በልጆቹ ስም የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በታሪኳ ካጋጠሟት ፈተናዎች ውስጥ አንዱ አሁን የገጠማት ፈተና ነው፤ ለመሆኑ ይህ ፈተና ኢትዮጵያን ወዴት ይወስዳታል ብለው ያምናሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፡- ሁለት እድሎች አሉ። አንደኛው እድል ጠንካራ የሆነ አገር ለመፍጠር ያስችላል። ብዙ አገሮች በታሪክ አጋጣሚ በተፈተኑበት ወቅት ጠንካራ ሆነው ወጥተዋል። ስለዚህም አሁን ያለው መነሳሳት አገረ መንግስቱን ከማጠናከሩም በላይ ተቋማት እንዲጠናከሩና እንዲዘምኑ እንዲያደርግ እድል ይሰጣል። ሁሉም ኢትዮጵያዊ አካባቢውን የመጠበቅ ልምድ እንዲኖረው ያደርጋል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ወዳጅና ጠላቱን ለመለየትና ጠላቱን ድባቅ ለመምታት ሰፊ እድል ይሰጠዋል። ከምንም በላይ ይህ አይነቱ አሰራር ከተጠናከረ አገሪቱ ለማንም የማትበገር ጠንካራ አገር ሆና እንድትወጣ ያግዛታል። ለምዕራባውያንም ትምህርት ለመስጠት ያስችላታል።
ይህ ፈተና የፖለቲካዊ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ አንድነት እንዲመጣና በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በአንድነት መቆማችንን እንድናሳይበት በአንድ በኩል ያስችላል። ለአገሪቱ የፖለቲካ መከፋፈልና ምስቅልቅል ውስጥ መግባት መድሀኒት ሊሆን ይችላልም። አሁን ባለው ፈተና ከሱማሌና ከኦሮምያ እንዲሁም ከደቡቡ ሄዶ ሰሜን ኢትዮጵያ ላይ ሲሞት ለኢትዮጵያዊያን ትርጉም አለው። ኢትዮጵያን ለማዳን የተከፈለ መስዋዕትነት መሆኑን ሁሉም ይረዳዋል። ይህ መሆኑ ደግሞ ምዕራብአዊያን ሰርተው ህወሓት እንዲፈጽምላቸው ያደረጉትን ፍላጎት አክሽፎ አንዲት ጠንካራ አገር እንድትቀጥል የማድረግ ሀይል አለው።
ሀሳቡ መቼም የማይሳካ መሆኑ ቢታመንም ችግሮቹ ተባብሰው ከመጡና ይህንን ጦርነት ማሸነፍ ካልቻልን ግን አገሪቱ ልትበተን ትችላለች። አገሪቱ በዚህ ውስጥ ወደቀች ማለት ደግሞ የማያባራ ጦርነት ውስጥ እንገባለን። ክልሎች በርካታ አገር ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህም ይህ ችግር በመኖርና አለመኖር ውስጥ የሚደረግ ጦርነት እንደሆነ ሁሉም መውሰድ አለበት። በእርግጠኝነት ከዚህ ቀደም እንደፈጸመችው በገድልና ታሪክ ይህንንም ጦርነት በድል አሸንፋ ደስታዋን ታከብራለችና ለዚህ ሁሉም ይትጋ እላለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዊነት ከብዙ አመታት መዳከም በኋላ ዳግም የማንሰራራት ሁኔታ እያሳየ ይገኛል፤ ኢትዮጵያዊነት እንዲዳከም ደግሞ አሁን ኢትዮጵያን ለማረስ እየሰራ ያለው ህወሓት እንደሆነ የሚያነሱ አሉ፤ ከዚህ አንጻር በተለይ የታሪክ ትምህርት ላይ የተሰራው ደባ ይጠቀሳልና ከዚህ አንጻር የነበረውን ችግርና ከዚህ ለመውጣት መደረግ ያለበትን ሁኔታ ቢገልጹልን?
ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፦ እንደ ቡድን ህወሓት ታሪክ የለውም። ስለዚህም ታሪክ እንዲነገር አይፈልግም። ይህ ማለት የትግራይ ህዝብ ማለት አይደለም። የትግራይ ህዝብ ባለታሪክ ህዝብ ነው። እነአሉላ አባ ነጋን የመሰለ ጀግና ያፈራ እንደሆነ ይታወቃል። ጠላትን እንዴት መዋጋትና መመከት እንዳለበት ለአገር ያስተማረ። አንገቱን አሳልፎ መስጠት የሚችል ባለታሪክ ፣ ገናና ህዝብ ነው። በዚህ የታሪክ ሂደት ውስጥ ግን ብዙ የባንዳ ልጆች ተሰባስበው የዚህን አገር ታሪክ በማጥፋት አገሪቱን ለመበተን የተንቀሳቀሱ ቡድኖች ስለሆኑ ታሪክ የላቸውም። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክ እንዳይኖር ሰርተዋል።
ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥልና ቀጥ ብላ እንድትቆም ያደረጓት ሶስት ምሰሶዎች አሏት ይባላል። አንዱ ታሪክ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሀይማኖት ሲሆን፤ ሦስተኛው ጠንካራ ህዝብ ነው። እነዚህን በማጥፋት ባለታሪክ የሆነውን ህዝብ ታሪኩን በማጥፋት የእኔ ታሪክ ብቻ ይነገር በማለት ጀግንነት የእኛ፣ ጀግንነት የእኔ፣ ለነጻነት ትግል የእኔ፣ መንግስትነት የእኔ በሚል ከእርሱ በፊት የነበሩ የመንግስት ስርዓቶችንና ደማቅና ገናና ታሪኮችን በማፍረስ የዚያ ባለታሪክ ልጆች እንዲያፍሩና እንዲሸማቀቁ ብሎም አንገታቸውን እንዲደፉ ሰርቷል። ስለዚህም ከታሪክ ጋር ያለው ጥላቻ ከበታችነት ጋር የተያያዘ ነው። ምንጩም የበታችነት ስሜቱ ነው።
ስሜቱ የትምህርት ስርዓቱ ላይ፣ ህጻናት ታሪካቸውን እንዳያውቁ ፣ አዳዲስ ታሪኮችን በመጻፍ የተዛቡ ታሪኮችን እንዲማሩና በታሪክ ላይ እርስ በእርስ እንዲጣሉ ከፍተኛ ስራዎችን ሰርቷል። ይህ የሚመነጨው ደግሞ ለታሪክ ካለው ጥላቻና የራሱን ታሪክ ብቻ ለትውልድ ለማስተላለፍ ካለው ፍላጎት ነው። በዋናነት ግን የባንዳ ልጆች ታሪክ ስለሌላቸው ታሪክን ሊያውቁትና ሊወዱት አይችሉም። ግብራቸውን የሚገልጥን ታሪክ ማጥፋት እንጂ ትውልዱ እንዲማረው አይፈልጉም።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያዊነት ቤተሰባዊነትና ወንድማማችነት እንደ ኢትዮጵያ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነ ይነገራል። አሁን ግን የተለየ ነገር እየታየ ነው። ለዚህ ችግር መንስኤው ማን ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፡– ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ አይነት የፖለቲካ ፍላጎት አለ። የፖለቲካ ፍላጎታችን ደግሞ ታሪክና ባህላችንና እምነታችን ላይ ጭምር ጫና ፈጥረዋል። አገረ መንግስቱ ላይ ሳይቀር ጫና እየፈጠሩ ናቸውም። በተለይም አንድነትና ወንድማማችነታችን ላይ ክፉ ጥላ አጥልተዋል። በአንድ ቤተክርስቲያን የሚያስቀድሰውና በአንድ መስኪድ የሚሰግደው ሰው እንዲለያይ ሆኗል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ በዘሩና በፖለቲካ ፍላጎቱ መለያየቱ ነው። በዋናነት ይህንን የሰራው ደግሞ መንግስታዊ መዋቅሩ ነው እንጂ ማህበራዊ መሰረት የለውም። ማህበራዊ ስሪትም አይደለም።
በቀደመው ጊዜ ሙስሊሙም ክርስቲያኑም ይጋባል ይዋለዳል። አብሮ የሚያደርጋቸው ነገሮችም ብዙ ናቸው። የሀይማኖት ተቋማትን ጭምር ተጋግዞ ሲገነባ ነው የሚታወቀው። ስለዚህ ጠንካራ ወንድማማችነት ነበረው። ነገር ግን ይህ አሸባሪ ከመጣ በኋላ እነዚህን ተቋማት የማፍረስ ሥራና አገራዊና ማህበረሰባዊ አንድነትን በሞራል፣ በታሪክ በመናድ ከፍተኛ ስራ ሰርቷል። ይህ ደግሞ ማሰሪያ አድርጎ የሰራው የፖለቲካ ጥቅምና ፍላጎትን ነው። ስለዚህም ለእነዚህ ሁለት ፍላጎቶች ሲባል በእነዚህ መሰረታዊ ምሶሶአችን ላይ ከፍተኛ በደል ተፈጽሟል። በዚህ በአካባቢያዊነት መጠቃቀምና መሿሿም እንዲገን አድርጓል። ይህ አስተሳሰብ ደግሞ አውዳሚ እንደሆነ ዛሬ ድረስ እያየነው ነው። ጠንካራ አገር ሲኖረን ጠንካራ ማህበረሰብ ይኖራል። አገርም እንድታድግ ይህ ግድ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው የዘራው አስተሳሰብ ማህበራዊ ስሪት የለውም ብለዋል። ታዲያ ይህ ካልሆነ ማህበረሰቡ ይህንን አካል ለመገርሰስ ለምን ተሳነው
ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፡- እነዚህ ቡድኖች ስራቸውን ሲያከናውኑ ፖለቲካዊ መዋቅሩን ተጠቅመው ነው። ፖለቲከኛ የሆነና መዋቅር ውስጥ ያለ አካል ደግሞ ጉልበት ይኖረዋል። ስለዚህም አሻፈረኝ የሚል ካገኘ ይገለዋል፣ ያሰቃየዋልም። ስለዚህ በህይወቱ ውስጥ ይህ እንዳይሆንበት ሲል በግዳጅ የእርሱ አስተሳሰብ አራማጅ ይሆናል። የያዙት መንገድ ስተት መሆኑን ደፍሮ የሚናገራቸውም አይኖርም። ስለዚህም ማህበረሰቡ ወዶ ሳይሆን በግዳጁ ተሸንፎ ነው ተግባሩን የሚከውንለት። ማህበረሰቡን አፍነውት ከአስተሳሰቡ ውጪ እንዲራመድም አድርገውታል። ስለዚህም ይህንን ቡድን የሚደግፈው ወንበዴ እንጂ ማህበረሰቡ ነው ማለት አይቻልም።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከራሷም አልፋ ለቀጣናው አገራትና ለመላ ጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት የሆነች ሃገር ናት፤ አሁን የተፈጠረው ችግር ይህንን መልካም ስም ወዴት ይወስደዋል?
ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፡- ይህ ክስተት በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቁር ጠባሳ ከጣሉና አሰቃቂ ከነበሩ ታሪኮች አንዱ እንደነበር መጻፉና መታወሱ አይቀርም። ይህ አዋራጅ የሆነ ቡድን ቅጥረኞችን በመግዛት በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ክፉ ተግባራትን ፈጽሟል፤ ኢትዮጵያን የማጥፋትና ስሟን የማጠልሸት ሥራዎችን ሰርቷል። ይህ ደግሞ በራሱ የሚፈጥረው ጠባሳ አለ። ነገር ግን በደንብ ከተጠቀምንበትና በደንብ ማስረዳት ከቻልን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ባለፉት ዓመታት ቡድኑን ሲደግፉና ይህንን ሁሉ ጫና ሲፈጽሙ ከጎኑ የነበሩትን ሀይሎች አፍረው ኢትዮጵያን የሚክሱበት አማራጭ የምናገኝበት ነው።
አሁን እየተከናወነ ያለው ነገር በአግባቡ ካልሄደና አንድነታችን ካልተጠናከረ ህወሓት የፍላጎቱ ይሟላልና በኢትዮጵያ አሳዛኝ ክስተት ይፈጠራል። ጥቋቁር ታሪኮችም መመዝገባቸው አይቀርም። ስለሆነም ይህ ከመሆኑ በፊት ሕግን ማስከበሩ ከአገር ክብርና ልዕልና ጋር ተቀናጅቶ ሊራበት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በየጊዜው አዲስ ሀሳብና እንቅስቃሴ በምዕራባውያንና በአጎራባች አገራት እየተደረገ ነው። የዚህ ምስጢር ምንድነው፤ ለምን ኢትዮጵያ ላይ ይህንን ያህል ጫና ማሳረፍ ፈለጉ?
ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፡- ምዕራባዊያን ላለፉት መቶ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ብሔራዊ ጥቅምም አላቸው። ብሔራዊ ጥቅማቸው የሚመነጨው ደግሞ ኢትዮጵያ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ የናይል ወንዝ ምንጭ ነች። ስለዚህም ወንዙን መቆጣጠር በምስራቅ አፍሪካ ያለው አገር ለመግዛት ትልቅ መሳሪያ ነው። ሁለተኛው ኢትዮጵያ ያለችበት አካባቢ መልከአ ምድር በጣም ጠቃሚ ነው። ለአረቡ አገር ቅርብ ከመሆኑም በላይ ለአፍሪካ አገር መግቢያ ነው። ለኤዥያም መረማመጃ ነው። ስለሆነም በዚህ ቀጣና ይህችን አገር በቁጥጥራቸው ስራ አደረጉ ማለት ሁሉንም የእጃቸው አደረጉ ማለት ነው። በዚህም ኢትዮጵያን ተገዢ አገር ማድረግ ይፈልጋሉ።
ሌላው በገልፍ ኦፍ ኤደንና በቀይ ባህር አካባቢ ያለውን ትልቁን የንግድ እንቅስቃሴ እንደልባቸው ለመጠቀምም ኢትዮጵያን በራስ ቁጥጥር ስር ማድረግ ግድ ነው ብለው ያምናሉ። ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ኤርትራ ከመገንጠሏ በፊት ትልልቅ መርከቦችና የባህር በር ነበራት። በዚህም ትልቅ ተጽዕኖ ፈጣሪ አገር ነበረች። ሆኖም ህወሓት አገሪቱን ከኤርትራ ጋር አጋጭቶ ባህር በር እንዳይኖራት አደረገ። ምዕራባውያንም በዚህ ስራቸው ከትንሿ ኤርትራ ጋር ለመደራደር ሞክረዋል። ሆኖም አልተሳካላቸውም።
ኢትዮጵያ በውድም ሆነ በግድ የእኛን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር መንግስት ብቻ ነው ሊኖራት የሚገባው ብለው ስለሚያምኑም ሽብር ፈጣሪውን ሁሉ አልገዛም ስንላቸው ይጠቀሙበት ጀመር።
አዲስ ዘመን፡- አገር ከእነዚህ ሁለቱ ፈተናዎች እንዴት መውጣት ትችላለች ፤ ማን ምንስ ማድረግ አለበት ይላሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፡- አሁን ያለው አገራዊ ችግር በታሪክ የገጠመን ትልቅ ፈተና ነው። ይህንን ፈተና ለማለፍ ደግሞ በምድር ላይ የሚንቀሳቀስ ሰው ሁሉ መሳተፍ አለበት። ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ ለክብሯ መታገል አለበት። የኢትዮጵያን አገረ መንግስትና የአባቶቹን አገር ማስቀጠል የሚፈልግ ሁሉም ሊሳተፍበት ይገባል። ምክንያቱም ዘመቻው አገርን ማዳንና አለማዳን ነው። ይህ ዘመቻ ለክብር የሚደረግም ነው። ስለሆነም ወጣቱ ሰልጥኖ አገሩን ለመታደግ መዘጋጀት ይኖርበታል።
በሁለተኛ ደረጃ ባለሀብቱ በአለው ሁሉ በመደገፍ አገሩን ከዚህ ፈተና ማውጣት አለበት። ሀብትና ንብረት የሚፈራው አገር ሲኖር መሆኑን ሊረዳና ድጋፉን ሊያጠናክር ይገበዋል። ምሁራን፣ የሚዲያ ባለሙያዎችም ቢሆኑ በተሰማሩበት ሙያ ለአገራቸው መስራት አለባቸው። ለውጪውም ሆነ ለአገር ውስጥ ነዋሪዎች እውነቱን ማስረዳትና ከእኛ ጎን እንዲቆሙ ማድረግ ላይ ያላሰለሰ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን።
ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2014