ክፍል ሁለት
የዛሬ ሳምንት ጳጉሜን 3 ቀን 2013 ዓ.ም በፍረዱኝ አምዳችን “ከይሁንታው በስተጀርባ…” በሚል ርዕስ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ቀበሌ 09 የቤት ቁጥር 740 ነዋሪ የሆኑት ሻምበል ተክላይ ገብረሕይወት፤ መንግስት በሰጣቸው ቤት በሰላም እንዳይኖሩ ሁከት እየተፈጠረባቸው ከመሆኑ ባሻገር በመንግስት ቤቶች የኪራይ ውል በፍ/ብ/ህ/ቁ 16781731 በተዋዋሉት መሰረት የአከራይ እና ተከራይ ውል ወረዳው አላድስም በሚል መንግስት የሰጣቸውን ቤት በህገወጥ መንገድ ለማፍረስና ለሌሎች አሳልፎ ለመስጠት እየሰራ ነውና ሕዝብና መንግስት ይፍረደኝ ሲሉ ለዝግጅት ክፍላችን ያቀረቡትን ሙሉ አቤቱታ አቅርበናል።
ሳምንት ቃል በገባነው መሰረት በዚህኛው ክፍል ደግሞ የወረዳውን ምላሽ እና የአጎራባቾችን ሃሳብ አካተን እንዲሁም ሰነዶችን አገላብጠን ያገኘነውን መረጃ በዛሬው የፍረዱኝ አምዳችን የግራቀኙን አቤቱታ መዝናችሁ የበኩላችሁን ፍርድ ትሰጡ ዘንድ ይዘን ቀርበናል።
የወረዳው ምላሽ
የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 የቤቶች ልማት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ንማኒ ዱላ እንደሚሉት፤ ቅሬታ አቅራቢው መኖሪያ ቤት እንዲሰጣቸው የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጽፍላቸው የቤቶች ልማት ኤጀንሲን በማመልከቻ ጠይቀዋል። ግለሰቡ በጠየቁት መሰረት ኤጀንሲው “የጤና እና ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ችግር ያለባቸው ስለሆነ የቀበሌ ቤት ትብብር ይደረግላቸው” ሲል በደብዳቤ ቁጥር 15ሀ/አአ/ከአ/ኮ/ቤ/ል/685/07 በቀን 06/04/07 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ለአራዳ ክፍለ ከተማ ኮንስትራክሽና ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ማሳወቁን ያወሳሉ።
ኤጀንሲው ለግለሰቡ ትብብር እንዲደረግላቸው በጻፈው ደብዳቤ መሰረት የክፍለ ከተማው ኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት በደብዳቤ ቁጥር የአ/ክ/ኮ/ቤ/ል/ጽ/ቤ/5055/2007 በቀን 10/07/07 ለወረዳው ኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ግለሰቡ ካለባቸው የመኖሪያና የጤና ችግር አኳያ ባለ ሁለት ክፍል ቤት እንዲሰጣቸው ስለተወሰነላቸው በወረዳችሁ ክልል ባለ ሁለት ክፍል ቤት ሲገኝ በእናንተ በኩል እንዲስተናገዱ በሚል ለወረዳው ደብዳቤ መጻፉን ይናገራሉ።
ቀደም ሲል በወረዳው 740 የቤት ቁጥርን ይዘው ሲያስተዳድሩ የነበሩ ግለሰብ የጋራ መኖሪያ ቤት ደርሷቸው ቤቱን ሲለቁ፤ ክፍለ ከተማው በጻፈው ደብዳቤ መሰረት ይህንን ባለሁለት ክፍል የቀበሌ ቤት ለሻምበል ተክላይ በ2007 ዓ.ም ወረዳው እንደሰጣቸው ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
ነገር ግን ክፍለ ከተማው ባለሁለት ክፍል ቤት ስጡ ብሎ ለወረዳው በሰጠው አቅጣጫ መሰረት የወረዳው አስተዳደር ለግለሰቡ ባለሁለት ክፍል ቤት ሰጥቶ እያለ፤ በ2007 ዓ.ም እንደአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት ቤቶች ቆጠራ ሲካሄድ ግለሰቡ በአየር ላይ ባለሶስት ክፍል ቤት በሚል ማስመዝገቡን ይናገራሉ።
አቶ ንማኒ በ2007 ዓ.ም የቤት ቆጠራውን ያከናወኑት የመንደር ኮሚቴዎች መሆናቸውን ጠቁመው፤ በወቅቱ ኮሚቴዎቹ የቤት ቆጠራውን ሲያከናውኑ ቴክኒካል ጉዳዮችን አይተውና ቤቱን ፈትሸው ሳይሆን ቤቱን ይዘው የሚያስተዳድሩ ግለሰቦች የሚሰጡትን መረጃ መሰረት በማድረግ ብቻ መረጃ መያዛቸውን ይገልፃሉ። በዚህም ግለሰቡ ሁለት ክፍል ቤት ተሰጥቶት እያለ ባለሶስት ክፍል ቤት ብሎ ማስመዝገቡን ይናገራሉ።
ግለሰቡ በሰጠው የተሳሳተ መረጃ መሰረት ወረዳው ላይ ባለሶስት ክፍል ቤት ተብሎ መረጃ በመግባቱ ሶስት ክፍል ቤት በሚል የአከራይ ተከራይ ውል ሲያድስ እንደነበር የሚናገሩት ኃላፊው፤ ነገር ግን በ2009 ዓ.ም በወረዳው ባለሙያዎች የመንግስት ቤቶች ዳግም የቤት ቆጠራ ተደርጓል ይላሉ።
ዳግም በተደረገው ቆጠራ ግለሰቡ ሶስት ክፍል ቤት በሚል ውል ሲያድስ የነበረ ቢሆንም፤ ቤቱ በአካል ወርዶ ሲታይ ባለሁለት ክፍል ቤት እንደሆነና ቀደም ሲልም ክፍለ ከተማውም ለግለሰቡ ቤት እንዲሰጠው በጻፈው ደብዳቤ መሰረት የተሰጠው ቤትም ባለ ሁለት ክፍል ብቻ መሆኑን በባለሙያዎች መረጋገጡን ያስረዳሉ።
ስለዚህ ስህተቱ በስህተት መቀጠል ስለሌለበት መረጃው ተስተካክሎ ግለሰቡ የተከራይ አከራይ ውል ሲያድስ ባለሁለት ክፍል ቤት ተብሎ ውል ይዋዋል ቢባልም፤ ‹‹ከዚህ ቀደም ውል ስዋዋል የነበረው ባለሶስት ክፍል ቤት ብዬ በመሆኑ ባለሁለት ክፍል ቤት ብዬ አልዋዋልም›› በሚል ቅሬታ አቅራቢው አሻፈረኝ ማለታቸውን አቶ ንማኒ ይናገራሉ።
ቤቱ በተጨባጭ ወርዶ ሲታይም ሆነ የተሰጠውም ሰነድ የሚያሳየው ቤቱ ባለሁለት ክፍል መሆኑን አቶ ንማኒ ጠቁመው፤ ቅሬታ አቅራቢው ይዞ የሚያስተዳደረው 740 የቤት ቁጥር እንዲሁም አጎራባቾቹ የቤት ቁጥር 741 እና 742 መካከል አንድ ሜትር ገደማ የጋራ መተላለፊያ ኮሪደር ወይም ታዛ መኖሩን አስታውሰዋል። ይህ መተላለፊያ ኮሪደር ወይም ታዛ የሁሉም ቤቶች ጀርባ ሲሆን፤ የጋራ የውሃ መፋሰሻ አሸንዳ ያለው ከመሆኑ ባለፈ የአደጋ ጊዜ መውጫ እና ሁሉም ከጀርባ ቤታቸውን ለማደስ ቢፈልጉ በዚህ በኩል አልፈው እንደሚያከውኑ ይናገራሉ።
ነገር ግን ሻምበል ተክላይ በቤት ቁጥር 741 እና 742 እንዲሁም 740 መካከል የጋራ መተላለፊያ ኮሪደሩን ወይም ታዛውን መውጫ መግቢያውን አሽገው፤ መተላለፊያ ኮሪደሩን ለራሳቸው ተጨማሪ ክፍል ሲያበጁ እንዳይጠባቸው የቤት ቁጥር 741 እና 742 እንዲሁም የራሳቸውን ቤት ጭምር ውሃ ልኩን አፍርሰው ሊሾ አድርገው፤ የራሳቸውን ቤት ከጀርባ በር ያልነበረውን አዲስ በር አውጥተው ከኮሪደሩ ጋር አገናኝተው ኮሪደሩን እንደአንድ ክፍል ቤት አድርገው እየተገለገሉበት እንደሚገኙ ኃላፊው ይናገራሉ።
በዚህም አጎራባቾቹ ‹‹የቤታችንን ውሃ ልኩን አፍርሶ ቤታችንን ንዶብናል›› በሚል ለወረዳው አቤት ማለታቸውን ጠቁመው፤ በቀረበው አቤቱታ መሰረት ወረዳው ወርዶ ሲያይ ግለሰቡ ኮሪደሩን ዘግቶ ከውስጥ የቤት ቁጥር 741 እና 742 ውሃ ልክ አፍርሶ ግንባታ እያከናወነ በመገኘቱ አስተካክል በሚል አቅጣጫ ሲሰጥ ግለሰቡ ቀጥታ ፍርድ ቤት ሄዶ መክሰሱን ይናገራሉ።
ከዚህ ቀደም ቤቱን ይዘው ሲያስተዳድሩ የነበሩ ግለሰብ ከአጎራባቾች ጋር ተስማምተው መተላለፊያ ኮሪደሩን ሳይዘጉ በጋራ ይጠቀሙበት እንደነበርና የእንጀራ ምጣድ አስቀምጠው እንጀራ ይጋግሩበት እንደነበር ኃላፊው ገልጸው፤ ስለዚህ ግለሰቡ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ኮሪደርን አጥሮ ከቤቱ ጋር ቀላቅሎ ስለያዘ ወረዳው ወርዶ አሽጓል። ነገር ግን ፍርድ ቤቱ በህጋዊ መንገድ ያገኘው ቤት ነው ሁከት ይወገድለት ብሎ ወስኗል ይላሉ።
ወረዳውም ቢሆን ግለሰቡ ቤቱን በህጋዊ መንገድ ማግኘቱን አልካደም። ነገር ግን አሁን ላይ በወረዳው እና በቅሬታ አቅራቢው መካከል ያለው አለመግባባት፤ ግለሰቡ ሶስት ክፍል በሚል ውል ላድስ የሚል ሲሆን በወረዳው በኩል ደግሞ መሬት ላይ ያለው ሃቅ ቤቱ ባለሁለት ክፍል ስለሆነ ግለሰቡ አቋሙን አስተካክሎ ዛሬውን ሁለት ክፍል በሚለው ውሉን ማደስ ይችላል ማለቱን ተናግረዋል።
ኃላፊው ይሄንን ምላሽ ሲሰጡ ከዚህ በፊት ወረዳው ከግለሰቡ ጋር ሶስት ክፍል በሚል ውል ሲዋዋል ነበር። ስለዚህ ቅሬታ የተነሳበት ክፍል እራሱ ወረዳው ሳይቀር ህጋዊ አድርጎ ውል እንዲያድሱ ሲያደርግ ነበር። ስለዚህ ባለፉት ዓመታት ለምን ሁለት ክፍል እንጂ ሶስት ክፍል ቤት አናዋውልም አላላችሁም? የሚል ጥያቄ የዝግጅት ክፍላችን ለጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አንስቷል።
ኃላፊውም ከዚህ በፊት የጋራ መተላለፊያ ኮሪደሩን ተስማምተውና ተዋደው ሲገለገሉበት ነበር። ነገር ግን ግለሰቡ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲል የአጎራባቾቹን ውሃ ልክ አፍርሶ ኮሪደሩን ዘግቶ ለራሱ ተጨማሪ አንድ ክፍል አድርጎታል። ይህንን ተከትሎ አጎራባቾቹ ቅሬታቸውን ለወረዳው ባቀረቡት መሰረት ወርዶ ሲያይ ግለሰቡ ትክክል አለመሆኑን አረጋግጧል። ግለሰቡ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በሰጠው የተሳሳተ መረጃ ሶስት ክፍል በሚል ከዚህ ቀደም ውሉን ሲያድስ ኗሯል። ስለዚህ ከተሰጠው ውጪ መሬት ላይ የሌለ ነገር አየር ላይ ሶስት ክፍል ቤት ነው ቢልም፤ ትናንት የተፈጠረው ስህተት ዛሬ መቀጠል ስለሌለበት ሁለት ክፍል በሚል ውሉን አድስ መባሉን ይናገራሉ።
በሌላ በኩል በወረዳው የቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ቡድን መሪ አቶ አሸብር አጥናፉ በበኩላቸው፤ በ2007 ዓ.ም የቀበሌ ቤቶች ቆጠራ ሲከናወን ግለሰቡ ሶስት ክፍል በሚል የተሳሳተ መረጃ የሰጠው አካባቢው በመልሶ ማልማት ሲፈርስ ምትክ ቤት በፈረሰው ቤት ልክ ስለሚሰጥ ቤቱ በመልሶ ማልማት ምናልባት ከፈረሰ ሶስት ክፍል ቤት ለማግኘት አቅዶ ነው። ስለዚህ በሌለ ቤት አየር ላይ ሶስት ክፍል ቤት ብለን አናዋውልህም፤ ሁለት ክፍል ቤት አስረክበን ሶስት ክፍል ቤት ብለን የምናዋዋልበት ምክንያት የለም። በሁለት ክፍል ከሆነ ዛሬውን መዋዋል ትችላለህ የሚል ምላሽ ለቅሬታ አቅራቢው እንደተሰጠው ይናገራሉ።
ቡድን መሪው ይሄንን ምላሽ ሲሰነዝሩ እርሳቸው ራሳቸው ጽህፈት ቤቱን ወክለው ከግለሰቡ ጋር ሶስት ክፍል ቤት በሚል ከግለሰቡ ጋር ባለፉት ዓመታት የአከራይና ተከራይ ውል ፈጽመዋል። ስለዚህ ባለፉት ዓመታት ለምን በሁለት ክፍል እንጂ በሶስት ክፍል ቤት አናዋውልም አላላችሁም? በማለት ቅሬታ አቅራቢው ላለፉት ዓመታት በሶስት ክፍል ቤት ሲዋዋል ከርሞ አሁን ላይ ምን አዲስ ነገር መጥቶ ነው በሁለት ክፍል ካልሆነ ሶስት ክፍል በሚል አናዋውልም ያላችሁት? የሚል ጥያቄ የዝግጅት ክፍላችን ለቡድን መሪውም አንስቷል።
እርሳቸውም ግለሰቡ በ2007 ዓ.ም የቤቶች ቆጠራ ሲካሄድ ሶስት ክፍል የሚል የተሳሳተ መረጃ በመስጠታቸው ወረዳው ላይ ሶስት ክፍል በሚል መረጃው መስፈሩን ገልጸው፤ በገባው የተሳሳተ መረጃ መሰረት ግለሰቡ ባለፉት ዓመታት ሶስት ክፍል በሚል ውሉ ሲያድሱ ቢቆዩም፤ በ2009 ዓ.ም በባለሙያ በተደረገው የቤቶች ቆጠራ ቤቱ ወርዶ ሲታይ መጀመሪያ ለግለሰቡ የተሰጣቸው ቤት ሁለት ክፍል ነው። ከዚህ በፊትም ቤቱን ይዘውት ሲያስተዳድሩ የነበሩት ግለሰብም ሁለት ክፍል በሚል ነበር ውል ሲያድሱ የነበሩት። ስለዚህ አዲስ በተደራጀው የመረጃ ሲስተም መሰረት ቤቱ መሬት ላይ ያለው ባለሁለት ክፍል ስለሆነ በሁለት ክፍል እንዲያድሱ ሲባሉ አሻፈረኝ ብለው ቅሬታ ለወረዳው የህዝብ አቤቱታ ሰሚ ጽህፈት ቤት ማቅረባቸውን ይናገራሉ።
የሕዝብ አቤቱታ ሰሚ ጽህፈት ቤቱም የወረዳውን ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ቤቱን በምን አግባብ ለግለሰቡእንደሰጠ በጠየቀው መረጃ መሰረት ክፍለ ከተማው ባለሁለት ክፍል ቤት እንዲሰጣቸው የትብብር ደብዳቤ በጻፈው መሰረት ባለሁለት ክፍል ቤት መስጠቱን በመረጃ አስደግፎ መልስ ሰጥቷል። በዚህም ቅሬታ ሰሚ ጽህፈት ቤቱ የቀረበለትን መረጃ አገላብጦ አይቶ መሬት ላይ የሌለውን ሶስት ክፍል ቤት ተብሎ ልትዋዋል አትችልም የሚል ምላሽ ለቅሬታ አቅራቢው እንደሰጠ ተናግረዋል።
የወረዳው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ክብሩ ዱላ በበኩላቸው፤ ከቤት ቁጥር 740 የቤት ቁጥር ጋር ተያይዞ ረዥም ጊዜ ያስቆጠረ ጭቅጭቅ እንዳለ ጠቅሰው፤ ጉዳዩ ከአጎራባቾች ጋር የተያያዘ ሲሆን አስተዳደር ድረስ የዘለቀ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ በተደጋጋሚ ለዚህ ችግር ዕልባት በመስጠት ከምንም በላይ ደግሞ አብሮ የሚኖር ማህበረሰብ ተግባብቶ እንዲቀጥል ማህበራዊ ሕይወታቸው የተሻለ እንዲሆን በመካከላቸው ያለውን ማህበራዊ ቀውስ ለማርገብ ብዙ ጥረት ቢደረግም እንዳልተሳካ ይናገራሉ፡፡
ዋነኛው ምክንያት ከ740 የቤት ቁጥር ጋር አጎራባች የሆኑት 742 እና 741 የቤት ቁጥር ነዋሪዎች ጥቅማቸውን ማዕከል ያደረገ ጥያቄ በመኖሩ ነው የሚሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በጎረቤታማቾቹ መካከል ያለውን ቅራኔ ለመፍታት የወረዳው አመራር ቦታው ድረስ በመገኘት ሽማግሌዎች እና የአካባቢውን ነዋሪዎች በመሰብሰብ ህግ ከሚለው ባሻገር ያለውን ለማጣራት እንደሸንጎ ለመቀመጥ መሞከሩን ይናገራሉ፡፡
አሁን ላይ ቅሬታ የተነሳበት ኮሪደር ወይም ታዛ ቀደም ሲል የቤት ቁጥር 740ን ይዘው ሲያስተዳድሩ የነበሩት ግለሰብ ቤታቸው ስለጠበባቸው ከጎረቤታቸው ጋር ተስማምተውና ተዋደው የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ አስቀምጠው ይገለገሉበት ነበር ይላሉ።
በጊዜው አብሮ መኖር እና መዋደድ ስለነበር ቀበሌም ሳያውቀው ግለሰቧ ከሁለቱ ክፍል በተጨማሪ ኮሪደሩን እንደ ሶስተኛ ክፍል አድርገው ከአጎራባቾቻቸው ጋር በጋራ ተስማምተው ይጠቀሙበት እንደነበር አውስተው፤ በአጎራባቾቹ መካከል ተስማምተው ይጠቀሙት ስለነበር ማንም ለወረዳው አቤቱታ ባለማቅረቡ አልታወቀም ነበር ይላሉ።
ቀደም ብሎ ቤቱን ሲያስተዳድሩ የነበሩ ግለሰብ የጋራ መኖሪያ ቤት ሲደርሳቸው ቤቱን አሁን ላሉት ግለሰብ እንደተሰጠ የሚናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ አዲስ የገባው ግለሰብም ቀድሞ ቤቱን ይዞ ሲያስተዳድር እንደነበረው ግለሰብ ሲገለገልበት ነበር።
ነገር ግን መሬት ላይ ተወርዶ የቤት ቆጠራ ሲካሔድ ግለሰቡ ውል የሚያድስበትና የተሰጠው ቤት ክፍል ብዛት የማይገናኝ ነው የሚሉት አቶ ክብሩ፤ ባለሁለት ክፍል ቤት ተሰጥቶት እያለ ባለሶስት ክፍል ቤት እየተባለ ውል ያድስ እንደነበር ወረዳው አያውቀውም ነበር። እንደዚህ ዓይነት ክፍተት በዚህ ቤት ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቤቶች ላይም ያጋጥማል፡፡ ስለዚህ የቤቶች ልማት በመመሪያ ቁጥር 2ም ሆነ በመመሪያ ቁጥር 3 እንዲሁም በመመሪያ ቁጥር 4/2009ኝም ሆነ በመመሪያ ቁጥር 5 በአጠቃላይ የመንግስት ቤቶች ኦዲት መደረግ እንዳለባቸው በሚያስቀምጠው መሰረት ኦዲት ሲደረግ ማለትም ቤቱ ስንት ክፍል ነው የሚለው ሲታይ አንድ ተጨማሪ ክፍል ተገኘ፡
በተለያየ መልኩ ሰዎች ተጨማሪ ህገወጥ ግንባታዎችን ሊያከናውኑ እና ክፍል ሊጨምሩ እንዲሁም የቤቶች ቅርፅ ሊለውጡ ይችላል፡፡ አምስት ስድስት ክፍል ቤት የነበረውን ቤት ‹‹እንዲሰፋልኝ›› ብለው ክፍሉን አፍርሰው ቀላቅለው ሁለት ወይም አንድ ክፍል ሊያደርጉ ይችላል፡፡ ወይም ቤቱን ሸንሽነው ብዙ ክፍል ሊያድርጉ ይችላሉ።
ነገር ግን እነዚህ ሁኔታዎች በመንግስት ቤቶች መተዳደሪያ ደንብ የተከለከለ ነው፡፡ ቤቱን ከሚያስተዳድረው አካል ዕውቅና ውጪ ይህን ማድረግ አይቻልም፡፡ ይህ ሲደረግ ከተገኘ ተቋሙ የማረም የማስተካከል እና ወደ ነበረበት የመመለስ ካልሆነም የመንግስት ጥቅም ሊያሳጣ የሚችል ከሆነ የመንግስትን ጥቅም ማስከበር የተቋሙ ግዴታ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይናገራሉ፡፡
ከዚህ አንፃር ከ740 የቤት ቁጥር ጋር ተያይዞ በቀረበው ቅሬታ ችግር እንዳለ ተደረሰበት። ወረዳው ችግሩን ከደረሰበት በኋላ የመንግስትን ጥቅም ወደጎን በማለት ኅብረተሰቡ በጋራ ተስማምተው እንዲጠቀሙበት ለማስታረቅ ተሞከረ፡፡ ነገር ግን ወረዳው ከተስማማችሁ በነበረበት ይቀጥል ቢልም የመብት ጉዳይ ስለሆነ አጎራባቾቹ መብታችን ተጥሷል በሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን ይናገራሉ።
የወረዳው አስተዳደርም ሁሉንም አካል በእኩል ዓይን በማየት ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያላሰለሰ ጥረት ማድረጉን አቶ ክብሩ ጠቁመው፤ ቅሬታ አቅራቢው ባለሶስት ክፍል በሚል ውል ሲያድስ የነበረበት ሰነድ ቢኖርም በአንጻሩ የግለሰቡ አጎራባቾቹ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ስለዚህ አጎራባቾቹ ከሰውየው በፊት ከ20 እና ለ30 ዓመት ይዞታቸውን ይዘው ሲያስተዳድሩ ችግር ባይኖርም፤ ግለሰቡ ቤቱን ይዞ ማስተዳደር ከጀመረ 5 ዓመት ወዲህ ችግር ተፈጠረ፡፡
ከዚህ በፊትም ኮሪደሩን ወይም ታዛውን 740 የቤት ቁጥርን ይዘው ሲያስተዳድሩ የነበሩ ግለሰብ እንጀራ ይጋግሩበት እንደነበር እና አጎራባቾቹም እንጨትና የተለያዩ እቃዎችን ዝናብ እንዳይመታባቸው በጋራ ያስቀምጡበት እንደነበር ጠቁመው፤ በመጨረሻም ግለሰቡ በህገወጥ መንገድ መተላለፊያ ኮሪደሩን ሲጠቀምበት ለወረዳው ቅሬታ እንዳላቀረቡ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ግለሰቡ ኮሪደሩን ተጨማሪ ክፍል ሲያደርግ እንዲሰፋለት የአጎራባቾቹን (የቤት ቁጥር 742 እና 741) ቤት ውሃ ልክ በማፍረስ ሊሾ ማድረጉን ተከትሎ ወደ አጎራባቾቹ ቤት ውሃ ሰርጎ በመግባቱ ቤታቸው የፈረሰባቸው ግለሰቦች ለወረዳው አቤት ማለታቸውን ይናገራሉ።
አጎራባቾቹም ግለሰቡ የወሰደው የእድሳት ፈቃድ ይታገድልን በሚል ዕድሳቱ እንዲቆም ጥያቄ ለወረዳው ማቅረባቸውን ገልጸው፤ የወረዳው አስተዳደርም ጉዳዩን ወርዶ ባየው መሰረት ግለሰቡ ኮሪደሩን ለራሱ ተጨማሪ ክፍል ለማድረግ የአጎራባቾቹን ውሃ ልክ በማንሳቱ ችግሩ መፈጠሩን በማየቱ የሚያከናውነውን የግንባታ ሥራ እንዲያቆም ወረዳው ማገዱን ያወሳሉ።
አቶ ክብሩ ግለሰቡ ለራሱ ተጨማሪ ነገር በመፈለግ በፈጠረው ችግር እኛ መኖሪያ ማጣት የለብንም በሚል የአጎራባቾች ቅሬታ እየበረታ መምጣቱን ገልጸው፤ ስለዚህ ወረዳው ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ያደረገው ጥረት አልሳካ ሲል፤ ግለሰቡ ያልተገባ ተጨማሪ ጥቅም ለማግኘት በሚያደርገው ግብ ግብ ሌላ ሰው መጎዳት ስለሌለበት መታረም ፤ መስተካከል አለበት በሚል አቋም በመያዝ ኮሪደሩ የጋራ መተላለፊያ እንጂ የአንድ ግለሰብ ስላልሆነ ሶስት ክፍል በሚል ውል አታድስም ተብሏል ብለዋል።
ሌላው ቅሬታ አቅራቢው ባለቤታቸው እንጀራ ጋግራ ለገበያ ለማቅረብ ቅሬታ በተነሳበት አንድ ክፍል የንግድ ፈቃድ አውጥታበታለች በሚል ወረዳው ቤቱን በተለያየ መንገድ ህጋዊ አድርጎታል ሲሉ ላነሱት ሃሳብ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ምላሽ ሲሰጡ፤ ማንኛውም ሰው በጥቃቅንና አነስተኛ ከኢኮኖሚ ጥገኝነት እንዲወጣ በሚኖርበት ቤት በአንድ ክፍልም ሆነ በሁለት ክፍል ለመኖር አይቸግረኝም፤ ኑሮዬን ለመደጎም ይረዳኛል ብሎ እስካመነ ድረስ እንዲሠራ ይፈቀዳል ካሉ በኋላ ስለዚህ ጽህፈት ቤቱም ፈቃድ ቢሰጥም፤ ፍቃድ የሚሰጠው በቤት ቁጥር 740 በሚል እንጂ የንግድ ፈቃድ፤ ቅሬታ በተነሳበት አንድ ክፍል ተለይቶ እንደማይሰጥ ተናግረዋል።
የፍርድ ቤት ውሳኔ አልተፈጸመልኝም በማለት ላቀረቡት አቤቱታም በህጋዊ መንገድ ያገኙትን ቤት ውሉን መዋዋል አሁንም መብት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ የሚዋዋሉት ግን ባለው ለእርሳቸው በሚገባቸው ልክ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በማይገባው ልክ በፈለጉት መንገድ ብቻ ልዋዋል የሚሉ ከሆነ የሌላ ነዋሪ መብት የሚጋፋ በመሆኑ ለግለሰቡም የማይገባ ጥቅም አንሰጥም፤ ጎረቤቶችም ጉዳት ሊደርሰባቸው አይገባም ብለዋል፡፡ ግለሰቦች ከተለያየ ነገር ጋር አጣብቀው የራሳቸው ጥቅም ለማሳካት የሚያደርጉት ሙከራ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ታግሎ ሊያስቆመውእንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እርቅ እንዲወርድ ጥረት ቢደረግም ግለሰቡ ፈቃደኛ እንዳልነበሩ አስታውሰው፤ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቢቀሩም ዋናውን ቤት እንዲያድሱ በተሰጠው የግንባታ ፍቃድ መሰረት ቤቱን እንዳያድሱ ያገዳቸው ሰው የለም ብለዋል። ነገር ግን ጥያቄ የተነሳበትን መተላለፊያ ኮሪደር ግንባታ ሊያከናውኑ ሲሉ የማሸግ ሥራ የተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በህገወጥ መንገድ የጋራ መተላለፊያ ኮሪደር ዘግተው የፈጠሩትን አንድ ክፍል ቤት እንዲያድሱ የግንባታ ፈቃድ አልተሰጣቸውም። ነገር ግን የጓሮ በር ሰርተው በቤቱ ውስጥ ወደታዛው እያለፉ ቤቱን ዘግተው ህገወጥ ግንባታ ማካሔዳቸው መዘንጋት የለበትም ብለዋል።
‹‹በአጠቃላይ አጎራባቾቹ ግለሰቡ ውሃ ልካችንን አፍርሶ ቤታችንን በላያችን ላይ ሊወድቅ ነው። ስለዚህ ቤታችን በላያችን ላይ ወድቆ ጉዳት እንዳይደርስብን ውሃ ልኩን መልሰን እንስራ፡፡›› በሚል የግንባታ ፍቃድ ጠይቀው ለአጎራባቾቹ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል። ነገር ግን በተሰጣቸው ፈቃድ መሰረት የፈረሰባቸውን ውሃ ልክ ሊያድሱ ሲሉ አትሰሩም ብሎ በጉልበት አግዷቸው፤ አሁን ድረስ ቅሬታቸውን ለወረዳው ያለመታከት እያቀረቡ እንደሚገኙ ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
የአጎራባቾቹ ምላሽ
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 የቤት ቁጥር 742 ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ትዕግስት ፍሰሃ በዚሁ ቤት ለ22 ዓመት ኖረዋል፡፡ ወይዘሮ ትዕግስት ቀድማ ከነበረችው ወይዘሮ ሀረገወይን ከበደ ጋር ለ17 ዓመት ያህል በጉርብትና አብረው ቆይተዋል። በእነዚህ 17 ዓመታት ምንም ዓይነት ነገር ተፈጥሮ እንደማያውቅ ገልጸው፤ በግቢው ለአምስት ዓመት የኖሩት ሻምበል ተክላይ ከመጡ በኋላ ግን ከሻምበል ተክላይ ጋር የተለያዩ ቅሬታዎች መፈጠራቸውን ይናገራሉ።
ወይዘሮ ትዕግስት እንደሚገልፁት፤ ቤታቸው ከጀርባ በታዛው በኩል ውሃ ልክ ነበረው፡፡ ሻምበል ተክላይ ታዛውን አስፋፍቶ፤ የጋራ ኮሪደሩን አስፍቶ ለራሱ አንድ ክፍል ቤት ለመቀጠል ሲል ውሃ ልኩን አፈረሰው። ውሃ ልኩን አፍርሶ ቤቱን ሲጠቀምበት በመሃል በፊት የነበረው የውሃ መፋሰሻ አሸንዳው ማፍሰስ ጀመረ፡፡ የ741 እና 742 ግድግዳ ውሃ ልክ ስለሌለው በውሃ ፍሳሹ የቤቱ ግድግዳ እየበሰበሰ መናድ ጀመረ፡፡ እንዴት ፈረሰ ብለው ለማጣራት ሲሞክሩ የቤቱ ውሃ ልክ መፍረሱን ተረዱ። በዚህ ጊዜ ግጭት ተጀመረ። ለወረዳው አቤቱታ ሲያቀርቡ ‹‹ለሶስት የውሃ መፍሰሻ አሸንዳውን አሰሩ። ሻምበል ተክላይ ደግሞ ውሃ ልኩን ያሰራ፡፡›› ተባሉ፡፡
ሻምበል በጉዳዩ ተስማምቶ ቀድሞ ውሃ ልኩ ከተሰራ አሸንዳውን ሲሰሩ ሲረግጡት ይናዳል በሚል ሰበብ መጀመሪያ ‹‹የውሃ አሸንዳው ይሰራ›› ተብሎ እያንዳንዳቸው 1ሺህ 300 ብር አዋጥተው አሸንዳው ተሰራ፡፡ ነገር ግን ሻምበል ውሃ ልኩን አላሰራም ማለታቸውን ወይዘሮ ትዕግስት ያስረዳሉ።
ጎረቤት ይዘው ‹‹ውሃ ልኩን የማትሰሩልን ለምንድነው›› የሚል ጥያቄን ለሻምበል ተክላይ ማቅረባቸውን ገልፀው፤ ሻምበሉ ውሃ ልኩን ለማሰራት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን እና የወቅቱ ደንብ አስከባሪም ከአቅሟ በላይ ስለሆነባት በወቅቱ የቤቶች አስተዳደር ኃላፊ ለነበሩት ለአቶ ጎሹ የሻምበሉን እምቢ ባይነት ማስታወቋን ያስረዳሉ።
እንደወይዘሮ ትዕግስት ገለፃ፤ በክርክሩ መሃል ሻምበሉ ቀድሞ እንደከሰሰ እና አሁንም ድረስ ሁለታቸውንም የሚያዋስነውን ኮሪደር እንደ አንድ ቤት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ስለዚህ በሻምበል ተክላይ ጥፋት ምክንያት ቤታቸው ፈርሷል፡፡ የአደጋ ጊዜ መግቢያና መውጫ አጥተዋል። ስለዚህ የጋራ መተላለፊያው መከፈት አለበት በሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ምክንያቱም ግለሰቡ በህገወጥ መንገድ ቤቱን መስራቱ ብቻ ሳይሆን ውሃ ልኩን በመፍረሱ ሳቢያ ተጎጂ ሆነዋል፡፡
በ741 የቤት ቁጥር ነዋሪ የሆነችው ወጣት ሜሮን አክሊሉም በበኩሏ በግቢው ተወልዳ እንዳደገች እና ለ 30 ዓመታት እንደኖረችበት ትናገራለች፡፡ ወጣት ሜሮን መጀመሪያ ቤቱን ይዛ ስታስተዳድር የነበረችው ግለሰብ ቦታውን ብትጠቀምበትም፤ ቦታው የጋራ መጠቀሚያ በመሆኑ ታዛው ስር ልጆች ሆነው ጸጉራቸውን እንደሚሰሩበትና ሳማ እና አረም ያድግበት እንደነበር ታስታውሳለች።
በግቢው 32 ቤት ያለ ሲሆን፤ አንዳንዴ በዛው ታዛ በኩል መውጫ በመኖሩ በታዛው ሥር ሰዎች ያልፉ ነበር፡፡ አንዳንዴም እንደአደጋ መውጫ በመጠቀም ወደ ሹፌር ሰፈር ይታለፍበት ነበር። ከጊዜ በኋላ ሌባ እየተመላለሰበት በማስቸገሩ ተነጋግረው በህብረት ቆርቆሮ ተገዝቶ ተዘጋ ትላለች፡፡
በሻምበሉ ቤት ቀድሞ ይኖሩ የነበሩ ግለሰብ ታዛው ላይ የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ አስቀምጠው ለ17 ዓመታት እንጀራ እየጋገሩ ሲሸጡ ጎመን ዘር፣ እንጨት እና እንጀራውን የሚያስቀምጡት በዛው በውሃ ልኩ ላይ ነበር፡፡ አዲሱ ሰው ሲመጣ ግን ቦታውን ጠቅልሎ አካቶ ከቤቱ ጋር ከመቀላቀል በተጨማሪ ሳይታወቅ ከስር ከስር እየቆረቆረ ውሃ ልኩን አፈረሰ ስትል ወጣት ሜሮን ትገልፃለች።
ጉዳዩን ለሚመለከተው አሳውቀው ‹‹አንድ የቀበሌ ቤት ችግርን ለመፍታት ዓመት ሊፈጅ አይገባም›› በሚል ከወረዳ አመራሮች ጋር እስከመጣላት መድረሳቸውን ገልፃ፤ ግለሰቡ መኝታ ቤት እና ሳሎን ብቻ ሳይሆን የቆጥ አንድ ክፍል ሳይቀር ሰርቶ ጨምሮ መተላለፊያ ኮሪደሩን ወይም ታዛውን በማጠር አራተኛ ክፍል ሰርቶ ከነዋሪው ጋር መጋጨቱ ተገቢ አለመሆኑን ትናገራለች።
ግለሰቡ ግንባታ እያከናወነ መሆኑ ታውቆ፤ ቀደም ሲል የቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ በነበሩት በአቶ ጎሹ ቤቱ የታሸገ ቢሆንም፤ በታሸገ ቤት ላይ ሻምበሉ ገብቶ ወለሉን ሊሾ አድርጎ በውስጥ በኩል በር ከፍቶ ወደ መተላለፊያ ታዛው አገናኝቶ ቦታውን እየተገለገለበት መሆኑን ገልፃለች፡፡
ወረዳው ራሱ የግለሰቡ ጉዳይ ከአቅሙ በላይ እንደሆነበት እና በግቢው የሚኖረው ሰው ተባብሮ እና ተሳስቦ ሲኖር እንደነበር አስታውሳ፤ ሻምበሉ አራት ክፍል ቤት ይዞ አንድ ክፍል ቤት ያላቸውን ሰዎች ቤታቸው እንዲፈርስ ማድረጉ እጅግ ያበሳጫት መሆኑን እና ይህንን ሕዝብ አይቶ እንዲፈርድ መፈለጓን ትናገራለች። አያይዛም መፍትሔው ለግለሰቡ ቅያሬ ቤት መስጠት ወይም ለእነርሱ ቅያሬ ቤት መስጠት ብቻ ነው ትላለች፡፡፡
ሰለሞን በየነ
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2014