ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አክቲቪስት የሚል ቃል በተደጋጋሚ እንሰማለን። በዚህ ላይ በመሰማራት አወንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ያሉ በርካታ አክቲቪስቶችም በሀገራችን ብቅ ብቅ እያሉ ይገኛሉ። በተለይ በፖለቲካው ዘርፍ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ በርካታ አክቲቪስቶች እንዳሉ በተጨባጭ ማየት ችለናል። እናም በዛሬው የእንግዳ አምዳችን የተጋሩ እንቅስቃሴ መስራች እና በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ስለትግራይ ነባራዊ ሁኔታ በርካታ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ የሚታወቁትን አክቲቪስት ሰለሞን ወልደገሪማ በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ አነጋግረን እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በትግራይ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ ሰለሞን፡– በአሁኑ ወቅት ትግራይ በታሪኳ አጋጥሟት የማያውቅ በጣም የሚያሳዝን መከራ እያስተናገደች ነው ያለችው። ልጆቿ ከሁለት ዓመታት በላይ ትምህርት ቤት መሄድ ሲገባቸው የተኩስ ድምፅ እየሰሙ ያሉበት፤ ህፃናት በልተው ጠግበው በመቦረቂያ እድሜያቸው ምግብ ያጡበት፤ ሀብታሙም ድሃውም ተረጂ የሆነበት፤ ገንዘብ ቢኖርም የትግራይ ህዝብ ከጎረቤት ክልሎች ጋር እንዳይገናኝ የሆነበት፤ መብራት፤ ስልክ የሌለበት በጣም አሳዛኝ የጨለማ ጊዜ ላይ ነው ያለችው። አሰቃቂውን ነገር በእግራቸው አምልጠው የሚመጡ ሰዎች እንደሚናገሩት ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው አሸባሪው ህወሓት ነው። ህወሓቶች ከማእከላዊ መንግስት ተነጥለው መቀሌ ገብተው ሳይመሽጉ በፊት ነበር ይሄ ነገር የትግራይ ህዝብን ይዞ ነው ገደል የሚገባው ፤ ከዚህ በፊት የሰራችሁት ስህተት ይበቃል ብለን የነበረው።
የሚያሳዝነው በእነሱ የማይረካ የስልጣን ጥም የተነሳ አሁን የሆነው ሁሉ ሆኗል። አንዲት የትግራይ እናት ለልጆቿ ጨው የበዛበት ምግብ በልተው ውሃ ብቻ እየጠጡ የጠገቡ እንዲመስላቸው የምታደርግበት ሁኔታ ላይ መደረሱን ነው የሚታየው። ለልጆቼ ምን ልስጥ ብሎ ከመጨነቅ የበለጠ ምን አሰቃቂ ነገር ለእናት ይገጥማት ይሆን? የትግራይ እናት በምን ሃጥያቷ ነው እንባዋ የሚፈሰው? ምን አይነት ስሜት ውስጥ ሆና ነው ልጆቿን በጨው እየጠበሰች ያለችው? አሁን ከማንኛውም ጊዜ በላይ የትግራይ ወጣት መፍጠን አለበት፤ ህዝቡን በተለይ ትግራዋይን የሚወድ ከሆነ ከወሬ በዘለለ አሁን ከወገኑ የተለያየውን የትግራይ ህዝብ ከወንድሙ ጋር መልሶ ማገናኘት ይገባዋል።
በመላው ሀገሪቱ ያለው ትግራዋይ ደም በመለገስ፤ ገንዘቡን በማዋጣት ይሄንን የትግራይ ነቀርሳ የሆነውን አሸባሪ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መገላገል ይኖርበታል። እዛም ያለው የትግራይ ህዝብ አንድ ጨካኝ አስተዳደር ሲወድቅ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚል ቢሂል ሀገርንና ህዝቡን ይዞ ወደ ሲኦል ማውረዱን መረዳት አለበት፤ ይሄንንም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ተሞክሮ መማር ይቻላል።
አሸባሪው ቡድን ህዝቡን አንተ የተለየህ ነህ፤ ሊበላህ መጣ በማለት ለጦርነት ይማግደዋል። የትግራይ ወጣት ይሄንን ቆም ብሎ በማሰብ እጅ በመስጠት፤ ለጦርነት ጥሪው ምላሽ ባለመስጠት ራሱንና ህዝቡን ማትረፍ አለበት። አሁን ያለው የውክልና ጦርነት ነው። የተለያዩ ሀገራት ሳተላይትን በመስጠት ቲቪ እንዲኖር አድርገዋል። የምእራባውያን ድጋፍም አልተለያቸውም። ማህበራዊ ሚዲያዎች አስክሬን እየለጠፉ እንኳን ሲያስወጧቸው አይታይም፤ ይህ ማለት የምእራባውያን እጃቸውን ሀገራችን ጉዳይ ውስጥ አስገብተው በህወሓት እየተጠቀሙ ሀገር ለማፍረስ እየሰሩ መሆኑን በመገንዘብ መንቃት አለበት።
በጎ አድራጊ ተቋማት ለምንድነው በሱዳን እንዲከፈት የሚፈልጉት? ለምንድነው ቅርቡ የኤርትራ ወደብ እያለ በዛ የማይጠቀሙት? የጦር መሳሪያ ለማስገባት? እርስ በእርስ ለማጨራረስ ነው። የትግራይ ህዝበ ራሱን ለማዳን ሲል መሸነፍ አለበት። የአሸባሪው ህወሓት ቡድን አባላት ለግል ጥቅማቸው ከማሰብ በስተቀር ለትግራይ እንደማያስቡአውቆ የትግራይ ወጣትም ሆነ የመላው የኢትዮጵያ ወጣት በአንድነት ሀገር ለማዳን መነሳት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ህውሓቶች ለትግራይ ህዝብ ሳይሆን ለገዛ ጥቅማቸው ነው የሚያስቡት ብለዋል እስኪ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከመነሻው ጀምሮ እስካሁን የትግራይ ህዝብ ያደረጋቸውን በደሎች ቢገልፁልን?
አቶ ሰለሞን፡– መጀመሪያ ወያኔ ለትግል ሲወጣ እነ ስዩም መስፍን አስመራ አካባቢ በመደራጀት ያነሱት ጥያቄ መሬት ለራሹ ነበር። ያኔ ደርግ መጥቶ የመሬት ላራሹ ጥያቄ ሲመልስ ተመልሰው ወይ ወደ ትምህርታቸው ወይም ወደ ሌላ ዓላማ መሰማራት ነበረባቸው። ግን አልተመለሱም። ለምን ቢባል እነሱ የወጡት በመምራት ፍላጎት እንጂ የህዝቡ ጥያቄ ሃሳባቸው አልነበረም። ይህ የሁሉንም ትኩረት የሚያገኙበት ነበር። ሲፈጠሩ ጀምሮ ለመምራት እንጂ ለህዝብ ጥቅም ብለው አልወጡም።
ህብረተሰቡም ጥያቄያችን የመሬት ነበር፤ ያም ተመልሶልናል፤ ከዚህ በኋላ የምንዋጋበት ምክንያት የለም፤ ሰላማዊ ድርድር ይኑር፤ ያሉ እንደ አጋመ፤ እንደርታና ራያ አካባቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ጥያቄ አቅርቦ ነበር። አድዋ ሽሬ አካባቢ ያሉት ነበሩ የእነሱ ደጋፊ። ይሄን ህዝብ ግን ወደ ዓላማቸው ለማምጣት የተጠቀሙት የሀውዜን ጭፍጨፋ ታሪክን ነው።
ሀውዜን ላይ የተፈጠረው በቅድሚያ “ሀውዜን የህወሓት ታጋዮች ገብተዋል” የሚል መረጃ ለደርግ ሰጡ፤ ህዝቡን የእሳት እራት ሊያደርጉት አስበው ማለት ነው። ሄሊኮፕተር መረጃው ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ ቅኝት ለማድረግ ሲመጣ ከህዝቡ መሃል የተሸሸጉ ሶሰት አራት የወያኔ ሰዎች ወደ ሄሊኮፕተራ መተኮስ ጀመሩ፤ ወዲያው ጄት ተላከ፤ ያኔ እያሱ በርሄ ኩነቱን እየቀረፀ ነበር። እንዴት በትንሽ ሀይል አውሮፕላን ሲመጣ መተኮስ ይታሰባል፤ ዝም ይባላል እንጂ፤ ሁለተኛው እንዴት ድብደባ ሊቀረፅ ይችላል፤ ሊያውም በዛ ወቅት ቴክኖሎጂ እንዲህ ባልተሟሟቀበት ዘመን፤ ሶስተኛ የዛን ሰአት አልታጠቅም ያለውን የትግራይ ህዝብ ለማስቆጣት የሞተች እናት ጡት እየጠባ የሚያለቅስ ህፃንን ጦርነቱን አልፈልግም ላለው ህዝብ አሳይተው አስቆጥተው ማገዱት።
ሰዎቹ ተደራድረው ለህዝባቸው ከመስራት ህዝቡን አስቆጥተው መማገድ ነበርና እቅዱ ተሳክቶላቸው ሁሉም ሰው ወደጦርነቱ እንዲቀላቀል አደረጉት፤ ከዛም ሁሉም ነገር አልቆ አዲስ አበባ ገቡ። ትግል አብቅቷል ወደ እርሻቹ ተመለሱ የተባሉት ታጋዮች በትንሽ ገንዘብ መለሷቸው። ለመናገር በሚያሳቅቅ መልኩ ከትግል ባዶ እጃቸውን መመለስ የከበዳቸው ሴት ታጋዮች ብዙዎቹ ሴተኛ አዳሪዎች ሆነው ነበር። ይህንን እያወቁ እንኳን አደራጅተው አንድ ነገር ከማድረግ ይልቅ ለስልጣናቸው ጠንቅ የመሰላቸውን የገዛ ወገናቸውን የመልቀም ሃሳብ ላይ ተሰማሩ።
በተለያዩ ትላቅ ህንፃዎች የተለያዩ ተቋማት በሙሉ የእነሱ ሼር ያለባቸው ሆነ። ህዝቡ ከዛሬ ነገ ለውጥ ይመጣል እያለ በትእግስት ጠበቀ። ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ በላይ ጭቆና እየደረሰበት እንዲቆይ አደረጉት፤ በትግራይ ልማት የተሰሩ ፕሮጀክቶችን ለህዝባቸው ጠቀሙ እንዳንባል በሚል ተልካሻ ምክንያት ያፈርሱ ጀመር። ለምሳሌ ቀላሚኖ የሚባል ከመንግስት አምስት ሳንቲም ወጪ ያልወጣበትን ትምህርት ቤት አፍርሰውታል።
ለህዝብ ጥሩ ነገር ማድረግ ፖለቲካዊ ትርጉሙ ለስልጣን የሚያሰጋቸው ከመሰላቸው ይዘጋሉ። በወቅቱ አንድም የጠየቀ ሰው አልነበረም። ትግራይ ውስጥ መብትን መጠየቅ ሞት ያስከትል ነበር። በህወሃት ታሪክ ትግራይ ውስጥ መንግስትን የተቃወመ ሰልፍ አንድ ጊዜ ብቻ ነበር የተወጣው፤ እሱም በአንድ አንባሴንት የተባለች ቦታ ወረዳ መሆን እንፈልጋለን ያሉ ሰዎች ሰላማዊ ሰለፍ ወጥተው የመሩት ሰዎች አሰቃቂ ነገር ደርሶባቸው ነበር።
ለመንግስት መደገፍ እድሜ ልክ የተደረገ ነገር ቢሆንም ለመቃወም ግን የአንድ ወረዳ ህዝብ ብቻ ነበር የደፈረው፤ ከለውጡ በኋላ ወደ ትግራይ ከሄዱ ጊዜ ጀምሮ ግን ማእከላዊ መንግስትን የሚቃወም 58 ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጓል። እሱም በሁለት ዓመት ነው። ህገ መንግስት ይከበርና ሌሎች ሃሳቦች የተነሳበት ነበር፤ እውነት ግን ህወሓት በታሪኩ ራሱ ያዘጋጀውን ህገ መንግስትን ያከብር ነበር? ይህ ጥያቄ ነው።
ባጠቃላይ ግን የትግራይ ህዝብን እንደፈለገ ሲያደርገው ኖሯል፤ አሁንም እያደረገው ነው። አሁን ላይ የምግብ እርዳታ የምትፈልግ እናት ልጆቿን ለጦርነት ለመማገድ መስማማት አለባት፤ ልጆቿን ካልላከች አይሰጣትም። ህዝቡን እንደፈለገ እያደረገ ተጠቀመበት። የትግራይ ህዝብ ዘመኑን ሙሉ ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንኳን አልነበረውም። ከለውጡ በኋላ ነበር ዶክተር አብይ የመቀሌን ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ያስጀመሩት። ሌላው ይሄ ፋብሪካ እየከፈቱ የስራ እድል ፈጠርን የሚሉት ሌላ ባለሀብትም ቢመጣ የሚያደርገው ነው። ሀብታቸውን ለማካበት የህዝቡን ደምና ላብ ከመጠቀም ያለፈ ለህዝቡ በተጨባጭ የሚታይ እንድም ስራ አልሰራም።
በሚገርም ሁኔታ ሌሎች የክልሉ ተወላጅ ባለሀብቶች እንኳን በክልሉ ኢንቨስት ማድረግ አይፈቅድላቸውም ነበር። ይህ ሁሉ አሸባሪው ህወሓት ለትግራይ ህዝብ ከመከራ ያለፈ ምንም አላተረፈለትም የሚል ድምድሜ ላይ ያደርሰናል ማለት ነው።
ከሁሉ የሚገርመው በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ እንዲጠላ ያደረጉ ሰዎች ናቸው፤ መድረክ ላይ ወጥተው ህወሓት ማለት የትግራይ ህዝብ ነው ያሉበትም ጊዜ ነበር፤ ግን የትግራይ ህዝብና ህወሓትን አንድ የሚያደርጋቸው ሁለቱም በትግራይ አካባቢ መፈጠራቸው ብቻ ነው። እነሱ ሲባልጉ፤ ሲጠጡ ሲሰክሩ፤ ሲሰርቁ ኖረው ያንን ጨዋ ህዝብ ለመወከል ሲያምራቸው ይገርማል።
ህዝቡ አሁን እየከፈለ ያለው መከራ የእነሱ ሀጥያት ክፍያ ነው። ለትግራይ ህዝብ ሲባል እነዚህ ነቀርሶች ባልተፈጠሩ ያሰኛል፤ እሴቱን ቀምተውታል፤ የሰው በደል የሚቆጨው ለፍትህና ለነፃነት የሚቆም የነበረውን ህዝብ እንዳልነበረ አድርገውታል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ አሻባሪ ቡድን በአማራና በአፋር ክልል ህዝቦች ላይ ጦርነት መክፈቱ ለትግራይ ህዝብ ምን አንድምታ አለው ብለው ያምናሉ?
አቶ ሰለሞን፡– አሸባሪው ህወሓት አፋርና አማራ የገባበት ምክንያት ሀይል የመበተን ሃሳብ ይዞ ነው። በአፋር በሁመራ ሰንጥቆ ወደ ሱዳን የማስከፈት ሃሳብ የነበረው ይህ ቡድን ያ አልሳካ ስላለው ነው፤ ለማዘናጋትና ሰንጥቆ የመውጣት ሃሳብ ይዞ ነው፤ ይህም የውጭ ድጋፍ የሚያገኝበትን ምቹ ሁኔታ የማመቻቸት ነበር። ሰዎቹ የትግራይን ህዝብ ከአማራ ህዝብ ጋር በተለያዩ ምክንያቶች አጣልተውት መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ከጎረቤት አፋር ጋር እንዳይታረቅ ለማድረግ የተለያዩ ጭፍጨፋዎችን በመፈፀም ላይ ይገኛሉ።
የሚገርመው በትንሽ መጠን ሽብር የመንዛት ስትራቴጂን የሚከተሉት ቡድኖች መከላከያ በሌለበት በኩል 50 በመሆን ከፊት ህፃናትን በማስመራት ከኋላ ሲኖ ትራክ ይዘው ባንክና የባለሀብቶችን ቤት ዘርፎ መግደል የፈለጉትን ገድለው ከመመለስ ያለፈ በተጠንቀቅ የቆመውን የመከላከያ ሃይል ወግተው የገቡበት አንድ ቦታ የለም።
ህዝቡን አንተ የተለየህ ነህ፤ አንድ ለሺ የሚል ዘፈን አውጥተው በአጉል ወኔ ውስጥ በመክተት ህዝቡን የመማገድ ስራ ይሰራሉ። የተበደለ ሀቅ የያዘ ህዝብ ነው አሸናፊ፤ የሚገርመው ሁለት ሶሰት ሆነው ፎቶ በመነሳት የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የማሰራጨት ስራ ብቻ ነው የሚሰሩት።
አዲስ ዘመን፡- ይህን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ህዝቡ እንዴት ሊለየው ይችላል? እንዴትስ ነው ማስቆም የሚቻለው?
አቶ ሰለሞን፡- ለትግራይ ህዝብ የእነሱን ፕሮፖጋንዳ እንዳይቀበል ለማድረግ ምንም አይነት ማስተባበያ የሚሰጥበት መንገር የለም። ህወሓትን በማስወገድ ነው እውነቱን ለህዝቡ አስረድቶ እንዲገባው ማድረግ የሚቻለው። ሶሰት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከኳታር ባገኙት ሳተላይት እያስተላለፉ ነው፤ ህዝቡ የእነሱን ውሸት ብቻ ነው የሚጋተው።
ህፃናትን አንድ መሳርያ ለአምስት ህፃን በማሰታጠቅ ከፊት ያሰልፏቸውና፤ ልጆቹ ጥይት ሲያልቅባቸው እጅ የመስጠት ሃሳብን እንኳን ሳይነግሯቸው ወደፊት እንዲገሰግሱ ከማድረግ በላይ ሬሳ ለቅሞ ጭኖ በመምጣት ለዓለም ህዝብም ሆነ ለሌሎች የውሸት መረጃ በማስተላለፍ የማጭበርበርያ መንገዶችን ይጠቀማሉ። ይህን ውሸት በማህበራዊ ሚዲያ ለማጋለጥ እየተጠቀምንበት ነው፤ ነገር ግን የትግራይ ህዝብ የእነሱን ትእቢትና ውሸት ከማዳመጥ በስተቀር ምንም አማራጭ አላገኘም።
የዚህን የውሸት ፕሮፖጋንዳ በማጋለጥና ህዝቡ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን እንዲቆም የተያዙ ቦታዎች ሬዲዮና ቴለቪዥንን እንዲመለከቱ ማድረግ ይገባል። የተለያዩ ሬዲዮች ላይ የተለያዩ መረጃዎችን በመስጠት ህዝቡ እንዲያውቀው የማድረግ ቃለመጠይቆችን በሬዲዮም እየሰጠሁ ነው።
የሀሰት ፕሮፖጋንዳቸው ማሳያ መቀሌ የገቡ ጊዜ ምርኮኛ አለ ብለው ያሳዩት ፎቶ ከፊት የተማረኩትን በማድረግ መካከል ላይ ራሳቸው ተሰልፈው ፊታቸው እንዳይታይ ተሸፍው የነበረ መሆኑን ለማየት ይቻላል። የተማረኩት ልጆች መሀል አሁን በአፋር የተማረከች የህወሓት ወታደር አለችበት፤ ይሄን ለምን አደረጉ ሲባል የትግራይ ህዝብን ለማታለል፤ እኛ እያሸነፍን ነው ለማለት ሲሆን፤ ሌላው ሰራዊቱ ከተደበቀበት ወደ ከተማ ሲገባ የአየር ጥቃት እንዳይደርስበት ነው። ሶስተኛው ደግሞ ምርኮኞችን ይዘናል እርዳታ ይሰጠን በማለት ለመጠቀም ነው። በአይሱዙ ከመለሱት አንድ ሺ ምርኮኛ ውጪ አንድም ሰው በእጃቸው የለም።
እድሜ ልካቸውን በውሸት በማታለል መኖራቸውን የኢትዮጵያ ህዝብ የተረዳው ሲሆን ይህ ሳይገባው የቀረው የትግራይ ክልል ህዝብን ለማሳወቅ ደግሞ ጥረት ይጠይቃል። የዓለም ህዝብ የተምታታ መረጃውን በማጥራት ጋዜጠኛውም ሁሉም ህብረተሰብ የራሱን ጥረት ማድረግ አለበት።
ለትግራይ ህዝብ ግን ማድረግ እየፈለግኩ ያልቻልኩትና የሚቆጨኝ ነገር ቢኖር ይህን የከሰረ ጦርነት በበለጠ ለትግራይ ህዝብ ይጎዳል ፤ ይህም ወጣቱን አሳምኜ ከኣሸባሪዎቹ ህወሓት ሴራ እንዲያመልጥ ማድረግ አለመቻሌና የትግራይ ህፃናት እንደ ቅጠል ረገፉ ተብዬ ሲነገረኝና ሳይ ማስጣል አለመቻሌ ነው።
የትግራይ ህዝብ 45 ዓመት ያልታደለ፣ 27 ዓመት የህወሓትን ክፋት የቀመሰ ነው፤ የሚያሳዝነው ደግሞ የትግራይ ህዝብ ላይ አሁንም አሸባሪው ህወሓት እንደመዥገር ላዩ ላይ ተጣብቆ ደሙን እየመጠጠው መገኘቱ ነው።
አሁንም ጦርነቱ በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ የጋራ ጥረት ቢደረግና ጦርነቱም ከተጠናቀቀ በኋላ መንግስት ይህን የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ከማህበረሰቡ ውስጥ ለማውጣት ቢሰራ መልካም ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ህወሓት የሰላም ጥሪ ቢቀርብለትም በተደጋጋሚ ሳይቀበለው ቀርቶ ህዝቡን ለዚህ ችግር ዳርጓል፤ ይህን እንዴት ታየዋለህ?
አቶ ሰለሞን፡– ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት “እኔ ከሞትኩ” ባዮች፣ ለግል ጥቅም ሲሉ እናታቸውን በሚሸጡና ሀገራቸውን አሳልፈው በሚሰጡ፣ ጠላት እንደፈለገው በሚጋልባቸው ከንቱ ልጆችዋ ምክንያት ኢትዮጵያ ከአንዴም ብዙ ጊዜ ብርቱ ፈተና ውስጥ ገብታለች፤ ዛሬም ኢትዮጵያ በደህናው ቀን እፍታዋን ያጎረሰችው፣ የማጀቷን ምርጥ በልቶ የጠገበው የጁንታው ኃይል፣ ሀገርን ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት ዐይኑን የማያሽ ውስጥ አዋቂ ባንዳ በመሆኑ ምክንያት ፈተናው ጠንክሮብን ይሆናል፤ በአንድነት ከቆምንና ተደምረን ከተጋን ግን ይህን ፈተና አሸንፈን፣ ችግሩን ወደ ዕድል፣ ዕድሉንም ወደ ታላቅ ድል ለውጠን፣ ሀገራችንን ወደ አየንላት የሰላምና የብልጽግና ከፍታ ማማ ላይ እንደምናደርሳት ለአፍታም ልንጠራጠር አይገባም፤ ለዘመናት በሀገራችን የሰራ አካል ውስጥ ተሰግስጎ የኖረው ህወሓት አለ፤ ይህ ቡድን ራሱን እያፋፋ፣ ኢትዮጵያን በአንጀት – በደም ሥርዋ ሰርጎ ሲጣባ – ሲመርዛት ኖሯል፤ አሸባሪው ህወሓት አሁን ተጠራርጎ ሊጠፋ በመንፈራገጥ ላይ ይገኛል፤ እድሜውን ለማራዘም የመጨረሻ መፍጨርጨርና የሞት ሽረት ትግል ላይ ነው፤ የአልሞት ባይ አትርሱኝ መወራጨቱ በዝቷል፤ ከግብአተ መቃብሩ በፊት ልትወጣ ያለች ነፍሱ እስካለች ድረስ መንፈራገጡና የሰላም ደንቃራ መሆኑ አይቀርም፤ ክፉ መርዙን ተክሎ ጥገኝነቱን ከመሠረተበት የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተነቅሎና ተጠራርጎ እስኪወጣ ድረስ ደዌ ነውና ህመሙን ችለን፣ የማሻሪያ መድኃኒት እየወሰድን እንቆያለን፤ “ኮሶ ሊያሽር ይመራል” እንደሚባለው፣ የማያዳግም ፀረ ሽብር መድኃኒቱ የጎን ጉዳት የሆነውን ምሬትና ህመም ታግሠን ከቆየን፣ ህወሓትም ሆነ ማንኛውም እናቱን ለመሸጥ የሚደራደር ኃይል የሀገራችን ክፉ ትዝታ ከመሆን የዘለለ ፋይዳ ላይኖረው በቅርቡ ለዘለዓለሙ ይሰናበታል።
ጁንታው ቀሩኝ የሚላቸውን የክፋት ካርዶች ሁሉ ተጠቅሞ ሊያሸብረን፣ ሊያበጣብጠንና ሊለያየን የሚችለውን ድንጋይ ፈንቅሏል፤ በገንዘብ ኃይል ህዝባችን ላይ እሳት እየለኮሰና እርስ በእርስ እያጋጨ እሱ በምቾት እሳት ሲሞቅና ህዝባችን ላይ ሲሳለቅ ነበር፤ የሽብር ነጋሪቱን እየጎሰመ ጀሌዎቹን አስከትሎ ዘምቷል፣ አሁን በተቃራኒው ተሳዳጅና የሞት ሽረት ሩጫ ውስጥ ነው፤ ጀንበሩ እየጠለቀች ነው። በሞት ሽረት ሩጫ ውስጥ የቀበረውንና የቀረውን የመጨረሻ ጥይቶቹን እየተኮሰ ነው። ከመጨረሻዎቹ ምሽጎቹ የጣር ድምጹንና የተስፋ መቁረጥ ቀረርቶውን ስሙልኝ ብሎ ነጋ ጠባ ያላዝናል፤ የሀገራችንን እጅ ለመጠምዘዝ የሚፈልገው የምዕራቡ ዓለም ዲፕሎማሲና የሚዲያ ጩኸትም የጁንታውን ድምጽ በማስተጋባት ደጀን ሊሆን ጥረቱን ቀጥሏል፤ ተባብረን ጫናውን ለመቋቋምና ለመመከት ከቆረጥን ይሄ ኃይል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያልቅለታል።
አዲስ ዘመን፡- የትግራይ ተወላጆች ላይ በጅምላ የመታሰርና የንግድ ቤቶቻቸው እየተዘጉ ነው የሚባል ነገር አለ፤ ይህንንስ እንዴት ያዩታል?
አቶ ሰለሞን፡– መንግስት እያሰረ ነው ለሚለው አዎ ነው መልሱ። ለዝህም ተጨባጭ መረጃዎች አሉ። ሆቴሎች ውስጥ የኢትዮጵያ ባንዲራ ሲቃጠል አይቶ አለመቅጣት አይቻልም፤ ሁለተኛ ከመቀለ የፅሞና ጊዜ ለመስጠት መንግስት ሲወጣ እነሱ ቡራ ከረዮ ቢሉም በፌዴራል መንግስት ጥላ ስር እየኖረ እምበር ተገዳላይ መጨፈር አሸንፈናል ብሎ መበጥበጥ በቁጥጥር ስር አያውልም ትላላችሁ? እርግጥ አንዳንዶች በጥቆማ ብቻ ቢያዙም ከተጣራ በኋላ ይለቀቃሉ። በርካታ የትግራይ ተወላጅ ሆቴሎች ሳይዘጉ ይታያሉ። ሥርዓት አልበኛን ማሰርም ሆነ ንግድ ቤቱን መዝጋት መንግስትን ሊያስወቅሰው አይገባም። ህወሓቶች ራሳቸው ተጋሩዎችን ማለትም እነሱን የማይደግፉትን ጥቆማ እያደረጉ በምሬት እነሱን እንዲቀበሉ የማድረግ ስራ ላይ ናቸው። እኔ እንኳን ከመንግስት ጋር እየሰራሁ በነሱ ጥቆማ ምክንያት ታስሬ ነበር፤ አሁን ጠቋሚዎቹም እንዲያዙና እንዲጣራ እየተደረገ ነው።
መንግስት እስኪያጣራ ድረስ ለአጭር ጊዜ የተቀመጡ ቢኖሩም ግን ዋናው ስጋት እራሱ የህወሓት ቡድን ተቀላቅሎ እየሰራ መሆኑ ነው። ተስፋ ቆርጠን የእነሱ ደጋፊ እንድሆን ሀገር የማፍረስ ስራቸውን ተባባሪ መሆን አይገባም። ሁሉም ሲፀዳ ግን እነደነበረ ይመለሳል። በቅርቡም ራእይ የተጋሩ እንቅሰቃሴ የሚባል ማህበረ ተመስርቷል፤ ይህም ንፁሃንን ነፃ የሚያስወጣ ስራ ይሰራል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ራዕይ ለተጋሩ ኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ህዝባዊ ንቅናቄ ለምን ዓላማ ተመሰረተ?
አቶ ሰለሞን፡– ይህ በትግራይ ተወላጆች አማካኝነት ራዕይ ለተጋሩ ኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ህዝባዊ ንቅናቄ የተመሰረተው የትግራይ ህዝብ ላለፉት ሶስት ሺህ ዓመታት ለሀገረ መንግስት ግንባታ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር የራሱን አሻራ ያስቀመጠ ህዝብ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከአድዋ በተፈለፈሉ ትግራይን ለመገንጠል አስበው ሳይሳካላቸው በቀሩ ለህዝብ በማይጠቅሙ ቡድኖች መጠቀሚያ ሊሆን የማይገባው መሆኑን ለማሳየት ነው። የትግራይን ህዝብ በተሳሳተ መንገድ ባይተዋር እንዲሆን እየሰሩ ያሉ ሃይሎችን ለመመክት ያለመ፤ በአሁኑ ሰአት በትግራይ የሚካሄደው ጦርነት የአንድ ቡድን እኩይ ዓላማን ለማሳካት መሆኑን አውቆ በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረው የትግራይ ህዝብ በቃችሁ እንዲላቸው ነው።
ህወሓት በትግራይ ህዝብ ላይ ስፍር ቁጥር የሌለው በደል ከማድረሱም በላይ 27 ዓመት የሰራው በደል አልበቃው ብሎ ህዝቡን ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል። ንቅናቄው ምንም አይነት የፖለቲካ አቋም የሌለው በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ተጋሩን በማደራጀት የሚሰራ ሲሆን ህዝባዊ ንቅናቄው 7 ምሶሶዎች ያሉት ሲሆን 5 ምሶሶዎች ከቀዳማይ ወያነ የተወሰዱ ናቸው።
ንቅናቄው የማንም ፖለቲካ ድርጅት ውግንና የሌለው ሲሆን፤ የንቅናቄው አበይት ዓላማዎችም፤ ትግራዋይ ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚሉ ተጋሩ ጥቂቶች እና የትግራይን ህዝብ የማይወክሉ ናቸው። የትግራይን ህዝብ ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ ያስገቡም ልክ አለመሆናቸው እና የትግራይ ህዝብ ከወንድሞቹ ኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ ሀገሩን እንዲያፀና ይሰራል፤ በመላ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ተጋሩ ህገ መንግስታዊ መብታቸው ተከብሮ እንዲኖሩ ከሚመለከታቸው ጋር እንሰራለን፤ ጦርነት ሀገር ነው፤ የትግራይ ወጣት ለጥቂት የስልጣን ጥመኞች ብሎ መስዋእት መክፈል እንደሌለበት ከሌሎች ወንድም ኢትዮጵያውያን ጋር በሰላም እንዲኖር ለመስራት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ሸኔ ከህወሓት ጋር የፈጠረው ጥምረት እንዴት ይታያል?
አቶ ሰለሞን፡– ይህ የሽብር ቡድን በሽብር ከሚመሳሰለው ከህወሓት ጋር ጥምረት መፍጠሩ ለኦሮሞ ህዝብ ከህደት ነው። የትግራይ ህዝብ ከተካደ ቆይቷል። ህወሓት አሸባሪ ብሎ ሲያሳደደው የነበረውን በኦነግነት ሰበብ ስንት የኦሮሞ ወጣት ይሄንን ነቀርሳ ለመጣል ሲታገል የኖረ የኦሮሞ ወጣት ደም ተከፍሎበታል። ለዚህም ከመላው ሀገሪቱ ተረጋግቶ የክረምትን የእርሻ ወቅት እየተጠቀመ ያለውም የኦሮሞ ገበሬ ነበር። የመላው ሀገሪቱ ገበሬ እርሻ ባቆመበት ወቅት ተረጋግቶ እያረሰ ያለውን የኦሮሞ ገበሬ ለምን ሰላም ሆነ በሚል ቅናት ነው ጥሪ ያቀረበው።
ከትጥቅ ትግል በኋላ ገና አዲስ አበባ እንደገቡ ትጥቅ አስፈትተው ሂድ ውጣ እንዳላሉት እና አባላቱን አሸባሪ ብለው ሲያሸማቅቋቸው ኖረው ቋሚ ጠላት የለም ማለት ንቀትን ያሳያል። ሁሉም አንድ ካልሆነ ሁሉም ካልተሰቃየ በሚል ምክንያት ጥሪ ስታደርገ ግን መቀበላቸው እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው።
ሰው ግን ይሄንን እስከመቼ ብሎ ማስቆም አለበት። እኔ ካልመራሁ ሀገር ትፍረስ ከሚል ወገን ጋር ስምምነት ያደረጉት ሸኔዎችን ግን ህዝቡ ራሱ አንቅሮ ይተፋቸዋል። ወያኔ እኮ በእሬቻ ላይ ህዝብን እንዴት እንዳደረገ አይረሳም። ዳግም መጥቶ ለማጥፋት ካልሆነ ሌላ ተግባር የለውም። ይህ አሸባሪ ቡድን ዛሬ ተጠቅመውባቸው አኝኮ ከመተፋት ያለፈ ግን ምንም ሰራ የለውም፤ የህወሓትን ውሸት፤ የህወሃትን ማጭበርበር መረዳት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡- ከፖለቲካዊ አስተሳብ ነፃ የሆኑ ትግራዋይ የሆኑ ምሁራንን ሀገር በማዳን ተሳትፎ ውስጥ እንዲኖሩ ለማድረግ የራእይ ለተጋሩ እንቅስቃሴ ምን ያስባል?
አቶ ሰለሞን፡- በራእይ ለተጋሩ ጥሪው ለሁሉም ሰላማዊ የትግራይ ህዝቦች ነው። በተለይም ግን በጣም የተመረጡ የታወቁ ምሁራንን ለመጥራት ይታሰባል። አሁን ያለውን አስተሳሰብ የሚፀየፉትን በመሰብሰብ ለትግራይ ብሎም ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቅም ስራ እንዲሰሩ ትግራይንም ከወደቀችበት ለማንሳት ምን መደረግ እንዳለበት ከሌላው የኢትዮጵያ ወንድም ጋር በማበር ምን መደረግ እንዳለበት ማሰብ ያስፈልጋል።
በእያንዳንዱ ዘርፍ ምሁር የሆኑ ሰዎችን ከቂም በቀል የፀዳ ትግራዋይነትና ኢትዮጵያዊነትን በአንድ የሚዘምር ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚነሳ ንቀናቄን ሀሳብ የመላው ሀገሪቱ ህዝቦች እንዲጋሩት ጥሪዬን አቀርባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ?
አቶ ሰለሞን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን መስከረም 5/2014