በዚያድ ባሬ የሚመራው የሶማሊያ መንግሥት ታላቋን ሶማሊያ ለመመስረት በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ላይ ወረራ ባካሄድበት 1969 ዓ.ም በሬድዮ በሰሙት የመኮንንነት ኮርስ ስልጠና በመመዝገብ የወታደርነት ሕይወትን አንድ ብለው የጀመሩት ሻለቃ አበበ ይመኑ የዛሬ እንግዳችን ናቸው። የመኮንንነት ኮርስ በወሰዱበት ሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት በመቅረት በመኮንኖች አሰልጣኝነት ሀገራቸውን አገልግለዋል።
በጦላይ እና ሁርሶ ማሰልጠኛ ማእከል በርካታ መኮንኖችን አፍርተዋል። የጅቡቲ ነፃ አውጪ ድርጅትን እና የዚምባብዌን ነፃ አውጪ ሰራዊት ዛኑና ዛፑን አሰልጥነዋል። በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ወታደራዊ ስልጠና ተከታትለው ተመልሰዋል። የደርግ ሥርዓት መጨረሻ አካባቢ ባሉት አራት ዓመታት ያኔ አስገንጣይ ተብሎ ከተፈረጀው ወያኔ ጋር ለአራት ዓመታት ትግራይ ውስጥ ወሎና ሸዋ ውስጥ በቀጥታ የጦር ግንባር ተዋግተዋል። ከቀድሞ ባልደረቦቻቸው ጋር በአሜሪካ ሀገር የቀድሞው የሀገር መከላከያና ፖሊስ ሰራዊት ማህበር በመመስረት በዋናነት በወያኔ በኩል የጠፋውን ስማቸውን ለመመለስ እና የተቸገሩ አባሎቻቸውን ለመርዳት ላለፉት ሰባት ዓመታት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ስለሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ተወያይተናል፤ እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም ሽብርተኛው ህወሓት ለሀገር ውለታ የዋለውን የቀድሞ መከላከያ ሰራዊትን ውለታ በመዘንጋት አብዛኛውን ሰራዊት በትኗል፤ በቅርቡ ደግሞ ለበርካታ ዓመታት በዋሻ የትግራይ ሕዝብን ሲጠብቅ የነበረውን ሰራዊት ወግቷል፤ ይሄ ምን ስሜት ፈጠረብዎት?
ሻለቃ አበበ፡- የቀድሞው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ሲበትኑ በከፊል አይደለም፤ የበተኑት ሙሉ በሙሉ ነው። ምንድነው ችግሩ የነበረው ቡድኑ ፈፅሞ ኢትዮጵያዊነት የሌለውና ስለኢትዮጵያም የሚያስብ አይደለም። ወያኔ ስለታሪክም ጉዳዩ ያልሆነ ስለሆነ የቀድሞው ኢትዮጵያ ሰራዊትን በትኗል። የኢትዮጵያ ስንል ዝም ብለን አይደለም የምናወራው፤ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰብ የተውጣጣ፤ በሚገባ የተደራጀ፤ በተለያዩ ሀገራት የተማረ ሰራዊት ነበር። በደንብ የተዘጋጀና ሀገር የሚጠብቅ ኢትዮጵያዊ ሰራዊት ነበር። ምንም በአንድ ወገን ውግንና ያለው አይደለም፤ ለመንግሥት የሚወግን አይደለም። መንግሥት በአግባቡ ለኢትዮጵያ ትእዛዝ በሚሰጥበት ጊዜ ያንን ትእዛዝ የሚፈጽም ሰራዊት ነው። በሶማሌ ታይቷል፤ እንዲሁም አሁን እየረበሹ ካሉት ኢትዮጵያን ከሚበትኑ ኃይላት ጋር ሲዋጋ የነበረ ሰራዊት ነው። ሀገር ለመበትን ከሚሯሯጡ ኃይሎች ጋር ሲዋጋ የነበረ ዳርድንበር ሲያስከብር የነበረ ሲሞት፣ ሲቆስል ሲደማ የነበረ ሰራዊት ነው። በኋላ ግን በሌላ መልኩ ተፈርጆ እንደፋሺስት ሰራዊት የተቆጠረበት ሁኔታ ነበር።
አሁንም ሰራዊቱ ሪፎርም ከተደረገ በኋላ ማለትም ዶ/ር ዐብይ ከመጡበት ከሦስቱ ዓመት በኋላ፤ እንደገና ኢትዮጵያዊነት ያብባል ብለው ስለፈሩ፤ ስልጣን ስላጡ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዳይመጣ እና ኢትዮጵያዊነት እንዲበተን ስለሚፈልጉ የሀገር መከላከያ ከጀርባው ጥቃት ተፈፀመበት። በዚህ እጅግ በጣም አዝነናል።
አሁን ያለው ሥርዓት በተቻለ መጠን ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰራዊት ለማቋቋም ደፋ ቀና እያለ ነው። እኔም ሁለቴ ከአሜሪካን መጥቼ የሰራዊቱን አቋም ተመልክቻለሁ። ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ ሰራዊት ነው እየመጣ ያለው፤ ያ እንዳይሆን ነው ፍላጎታቸው። የኢትዮጵያዊነት ፍላጎት ያለው ሰራዊት ከመጣ ሀገር ትጠበቃለች ሀገር አንድ ሆና ትቆማለች ወደፊት ትራመዳለች። ያ እንዲሆን አይፈለግም በወያኔ በኩል፤ ኢትዮጵያዊነት የሚባል ነገር እንዲጠፋ ስለሚፈለግ ነው። ይሄን በአጀማመራቸውም ያየነው ነው፤ አሁንም እያደረጉት ያለው ነው። ለዚህ ነው ይሄ ሰራዊት ከጀርባው እንዲመታ የተደረገው።
እነሱ ይሳካልናልብለው አስበው ነበር፤ አልተሳካም። በሰራዊቱ ላይ የተወሰደው ኢ-ሰብአዊ እርምጃ እጅግ በጣም አሳዝኖናል፣ አከፍቶናል። ይሄንን ሰራዊት እንደገና ተቀላቅሎ ወደ ውጊያ ለመግባት የቀድሞው መከላከያ ሰራዊት አባላት ሁሉ እየተመኙ ነው። ምንጊዜም ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ ነው የእኛ ፍላጎት።
እኔ ውጊያ ላይ በነበርኩበት ጊዜ ኤርትራ ውስጥ ችግር አለ፤ ሶማሌ ችግር አለ፤ ከኦነግ ጋር ችግር አለ። ከወያኔ ጋር ችግር አለ፤ በከፍተኛ ደረጃ ውጥረት ውስጥ የገባንበት ሰዓት ነው። አንድም የውጪ መንግሥት ከጎናችን አልቆመም። በዓለም ላይ ያሉት መንግሥታት ጠቅላላ እኛ ላይ ነው የተረባረቡት። አረቦች ምንም ጥያቄ የለውም፤ የአረብ መንግሥታት ጠቅላላ ከወያኔና ከሻዕቢያ ጋር አብረው የሚሰሩበት ጊዜ ነበር። ገንዘብና መሣሪያ እንደልብ ከውጭ የሚያገኙበት ጊዜ ነበር። ለእርዳታ የሚገባው እህል ሁሉ እየተሸጠ ለነሱ ትግል ነው ይውል የነበረው። እንዲያውም የነበረው መንግሥት 17 ዓመት ሙሉ በዚህ ዓይነት ሁኔታ መታገሉን እንደተአምር ነው የምቆጥረው። ግን ብቃት ያለው ሰራዊት ነበር። በተለያዩ ዓለማት የተማሩ አለቆች ነበሩን ቤልጂየም፣ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ራሺያ እና ኩባ የተማሩ አዛዦች ነበሩ። ያንን ሁሉ አጠናቅረው ነው አንድ ወጥ የሆነ የራሳችንን ትምህርት አስተምረው ብቃት ያለው ሰራዊት የገነቡት። የነበረው ሰራዊት አሁን በጁንታው በኩል እንዳለው እንደልምድ አዋላጅ አይደለም። በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሰራዊት ነበር። ከፍተኛ ተፅእኖ ስለነበረብን ፖለቲካው ተሸነፈ። ሰራዊቱ ምንም ዓይነት ሽንፈት አላጋጠመውም። እንደማንኛውም ይተኩሳሉ እንሄዳለን፤ ልቀቁ እየተባለ እንለቅላቸዋለን፤ እንደገና ደግሞ ይመጣሉ፤ ልቀቁ እየተባለ እንለቅላቸዋለን። ይሄ እንዳይሆን ነው አሁን ጥረት መደረግ ያለበት። ዝም ብለው የትም ቦታ እየዞሩ በተኮሱ ቁጥር ልቀቁላቸው የሚባል ነገር አይሰራም። ወደፊት መሆን የማይገባው ነው። እነዚህ ሰዎች አሁን እንኳን ባለው ሕዝቡ አንድ እየሆነ ነው። የእነኚህን ፀረ-ሕዝቦች ማንነታቸውን እየተረዳ ነው።
ስለዚህ በየቦታው ቢገቡም አይወጡም፤ አሁን ላሊበላ ገባን አሁን ወልድያን ያዝን የሚባል ነገር አይሰራም። ዝም ብለው በአቦሰጥ እያዋጓቸው ሕዝቡን እያስጨረሱ ነው። እነኚህ የወያኔ መሪዎች ቶሎ በሉና ወልዲያን ተቆጣጠሩ፤ ቶሎ በሉና ላሊበላን፤ ቶሎ ሂዱና ዋጃን፣ አላማጣን፣ እያሉ በአቦሰጥ ነው ሰዎቻቸውን የሚልኩት። ወደፊት መመለሻም እስከሚያጡ ድረስ በጣም ከፍተኛ ችግር ያጋጥማቸዋል። ሕዝብንም ያስጨርሳሉ የነሱም የመጨረሻ ዘመናቸው ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ቡድን እርስዎ ቀደም ሲል ጀምሮ ያውቁታል፤ በተለይ ከቀድሞ ሰራዊት ጋር በነበረው ውጊያም የተለያዩ አሻጥሮችን በመጠቀም ለሥልጣን እንደበቃ ብዙዎች ይናገራሉ፤ ከዚህ አንጻር እርስዎ የዚህን ቡድን ባህርይ እንዴት ይገልጹታል?
ሻለቃ አበበ፡- ወያኔን አውቀዋለሁ፣ በደንብ ነው የማውቀው። በአራት ዓመት ውስጥ በደንብ ነው የምንተዋወቀው፤ ቃል በቃልም እንነጋገር ነበር። ሁልጊዜም በሁሉም ቦታ ሴራ አለ፤ በውጊያም ላይ ጭምር ያላደረጉትን አደረግን፤ ያልተፈጠረውን ተፈጠረ ማለት ባህሪያቸው ነው። አሁን ማሸነፍ ቢያቅታቸው ሌላ ታሪክ ነው የሚፈጥሩት።
ሀውዜን ላይ የተፈጠረውን ሰምተሽ ይሆናል፤ እራሳቸው ካሜራ እና ጋዜጠኞችን አዘጋጅተው ነው ሕዝቡን ያስጨረሱት። ምንድነው የሀውዜን ትልቁ ጥያቄ? የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት እስከተባልን እና ትግራይን ነፃ ካወጣን ወደሌላው ክፍል ለምንድነው የምንዘምተው? ለምንድነው ልጆቻችን የሚያልቁት? ስላለ ነው የሀውዜን ሕዝብ ያ ሴራ የተፈፀመበት። ምንድነው የተፈፀመው ሴራ የሀውዜን ገበያ መቼ እንደሆነ ያውቃሉ። ቀደም ብለው ስብሰባ እንደሚደረግ ሆን ብለው መረጃዎች እንዲወጡ አደረጉ። መረጃው በቀጥታ ለነበረው መንግሥት ለደርግ ፅ/ቤት እንዲደርስ ተደረገ። በዚህ ሰዓት በዚህ ጊዜ ሀውዜን ላይ ዋናው የወያኔ ኃይል ስብሰባ እንደሚያደርግ መረጃ አሰራጩ። የራሳቸው የውሸት ትርኢት ይባላል፤ ሰራዊቱን ሲያስገቡ ዋሉ፤ በሁሉም ዘንድ ሰራዊት ገብቷል እንዲባል፤ የደርግም መንግሥት እንዲያውቅ ማለት ነው። ከዚያ ሌሊቱኑ መልሰው አስወጡት፤ ያ መረጃ በደንብ ስለደረሰው ደርግ እውነት መስሎት ሲደበድብ በደንብ በካሜራ ይቀርፁ ነበር። ሕፃናት ሲደበደቡ፤ወላጆች ሲያልቁ የነበረውን ሁኔታ እናስታውሳለን። ስብሰባ ላይ እንዳሉ እርምጃ ለመውሰድ ነበር የተፈለገው። ከዚያ በኋላ ሕዝቡ ካለቅን አይቀር ሄደን እስከመጨረሻው እንለቅ ብሎ ከወያኔ ሰራዊት ጋር ተቀላቀለ።
አሁንም ይሄንን ነው የሚሰሩት፤ እነሱ ምንጊዜም ቢሆን ሳይችሉ ሲቀሩ ውጊያውን ወደሕዝቡ ነው የሚያስተላልፉት። ከዚያ በኋላ በአቦሰጥ ነው እንደልምድ አዋላጅ በዚህ ቦታ ሂዱ አጥቁ ይሄን ቦታ ብለው የሚሉት። እነዛ የተላኩ ሰዎች እንደምንም ተሽሎክልከው ላሊበላ፤ ተሽሎክልከው ወልዲያን ይይዛሉ፤ ይሄ ለፕሮፓጋንዳ ይመቻቸዋል። ወደፊት እየገሰገስን ነውና አግዙን እርዱን ለማለት እንዲመቻቸው ነው ለፕሮፓጋንዳ። እኛ በሬድዮ እንሰማ ነበር፣ በውጊያ ላይ በነበርንበት ጊዜ የሚሰሩትን ማጭበርበር በሙሉ እናውቃለን። በተወሰነ መልኩ አልፈውን ሄደው ይተኩሳሉ፤ እናውቃለን የተወሰነ ኃይል መሆኑን ከዚያ እንዳይወጡ ይደረጋል። ውጊያው በኢትዮጵያ ሰራዊት አሸናፊነት እንዳያልቅ ይፈለግ ስለነበር ብዙ አሻጥሮች ተሰርተውብናል። ዓለም ተረባረበብን፤ እርዳታ ይገኝ የነበረው ከሶቪየት ህብረት ነበር። የሶቪየት መንግሥት ውጊያ ላይ እያለን በመጨረሻው ሰዓት ከአሁን በኋላ አንረዳችሁም እራሳችሁን ቻሉ የሚል መልስ ነው የሰጠን። ከዚያ በኋላ ምንም ሊደረግ አልቻለም።
በዚያ ሰዓት ይታሰብ የነበረው እንደዚህ የከፋነገር አይደለም። ኢትዮጵያውያን ናቸው። ኢትዮጵያዊ እስከሆኑ ድረስ መንግሥትም ቢቀየር ብዙም ተፅእኖ የሚያመጡ አይመስልም ነበር። ግን ማዕከላዊ መንግሥቱን ከተቆጣጠሩ ወዲህ የሰሩት ሥራ በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ደርሷል። ኢትዮጵያ ምንም ነገር የላትም፤ አጥንቷ ሳይቀር ተግጧል። ገንዘቧ አልቋል፤ ለቤተሰባቸው ለዘመዶቻቸው አውርሰውት ጨርሰዋል። በአብዛኛው የሚታየው ሕንፃ እና ትልልቅ ድርጅቶች በአንድ ወገን ባለቤትነት የተያዙ ናቸው።
በቅርቡ የእብሪታቸው ብዛት ትግራይን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለቆ ሲወጣ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ባንዲራ እንዳቃጠሉና ምን ያህል እንደተጨፈረ አይታችኋል። ይሄን ማየት እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነው። በርግጥ እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው ወይስ ምናዊ ናቸው እስከሚያሰኝ ድረስ ያማል። እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ሲጨፈር ነበር፤ ባንዲራ ሲቃጠል ነበር። እዚያ ሆነን በጣም ነው ያዘንነው፤ ምክንያቱም ሀገር የለንም፤ ሀገሩ ለእነዚህ አፍራሾች ተሰጥቷል፤ እስከምንል ድረስ። አዲስ አበባ ውስጥ በተፈፀመው ድርጊት በጣም ነው ያዘነው። ሰራዊቱን ከጀርባው ከወጉትም በላይ በዚህ ነው ያዘነው።
እኛ ብቻ እንኑር፤ እኛ ካልኖርን ግን ሀገር ትጥፋ ማለት አግባብ አይደለም። ደግሞ ሲኖሩም በሥነ-ሥርዓት ኖረው ቢሆን ኖሮ ሀገራችን ለምታ ቢሆን፤ በእኩልነት ሀገር አድጎ ቢሆን ኖሮ ግድ የለም። ግን የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ እየኖረበት እያደገ አሁን አሜሪካን ሀገር አብዛኛው ስቴት ውስጥ እነሱ ናቸው የሚኖሩት። የተለያየ ስቶር ከፍተው፤ ድርጅት ከፍተው፤ የድሎት ሕይወት ነው የሚኖሩት። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያውቀው የሚገባ አሜሪካ ውስጥ እያንዳንዱ ስቴት ውስጥ ትልልቅ ሪልስቴት ከፍተው የነዳጅ ማደያ ስቶሮች በየቦታው አንድ ግለሰብ ሁለት ሦስት ቦታ እየገዛ በተንደላቀቀ ሕይወት ነው የሚኖሩት።
በተቃራኒው ግን እዚህ ሕዝባችን ጫካ ውስጥ እና በየመንገዱ ጎጆ እየቀለሰ ለመኖር ይታገላል። እንደዚያም ሆኖ አልተዉንም፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በበዘበዙት ገንዘብ ነው ዓለምአቀፍ ተፅእኖ ሊያሳድሩብን የቻሉት። ከራሳችን ላይ በሰረቁት ገንዘብ ነው፤ ገንዘብ በዓለም ላይ የማይሰራው ነገር የለም። በሕግም ይታወቃል፤ አሜሪካን ሀገር ሎቢስቶች አሉ። ኮንግረስ ማኖችን የሚይዙ ሎቢስቶች አሉ፤ በዶላር ቀጥረው ነው የሚያሰሯቸው። ከአንቺ ከእህት ከወንድምሽ ከሀገሪቷ ላይ የተወሰደው ገንዘብ እየተከፈለ ነው ተፅእኖ የሚያሳድረው። ለእውነት የሚቆሙ ቢሆን ኖሮ አሁን ሁሉም መንግሥታት ኢትዮጵያን ማገዝ የሚገባቸው ሰዓት ነበር። ግን እንዳየነው ሁሉም ለገንዘብና ለራሳቸው ጥቅም የቆሙ መንግሥታት ስለሆኑ ከኢትዮጵያ በተቃራኒው ቆመዋል። ከተወሰኑ ግለሰቦችና ድርጅቶች በስተቀር ማለት ነው።
አዲስ አመን፡- ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ኅብረተሰቡን ለማሸበርና የሥነልቦና የበላይነት ለማግኘት በሚረጨው ፕሮፓጋንዳ ተፅእኖ ላለመጠለፍ ኅብረተሰቡ ምን ማድረግ አለበት ይላሉ?
ሻለቃ አበበ፡- ይሄ ችግር እዚህ ኢትዮጵያ ብቻ ያለ አይደለም። ውጪም ያለው ኢትዮጵያዊ ተከፋፍሏል። በፕሮፓጋንዳ በሌላ አይደለም ሚድያውም ሆነ ጋዜጠኞች እዚህ ላይ ነው መረባረብ ያለባቸው። ኅብረተሰቡ የውሸት ዜና እንዳይሰማ ሁልጊዜም እውነቱን ለማውጣት ከፍተኛ ሥራ መስራት አለባቸው። እውነቱን የማውጣት እና የማሰራጨት ለወገኖች እና ለውጭው ዓለም እንዲደርስ ሚድያዎችም ሆኑ ጋዜጦች ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ አለባቸው። የውሸቱ ዜና ሕዝቡን ከፋፍሎታል። በመንግሥትም በኩል ድክመት አለ፤ ምክንያቱም ሚድያዎች ላይ መሰራት አለበት። እውነቱ የትጋ ነው የሚለው ሕዝቡ እንዲያውቅ ማድረግ አለበት። ምንም እንቅልፍ አያስፈልግም።
የኢትዮጵያ ሚድያዎች ቀን ከሌሊት ሰርተው እውነቱን ማውጣት አለባቸው። የሚድያ ጉዳይ ተፅእኖ አሳድሯል፤ የውጪ ሚድያዎች በገንዘብ የተያዙ አሉ። ጁንታው ከሕዝብና ከሀገር የዘረፈውን ሀብት በሙሉ ለሎቢስቶችና ሀሰት ለሚነዙ ሚድያዎች እያሰራጨ ነው። ሀገር እንዳትፈርስ እዚያ ላይ ነው መሰራት ያለበት። በተለይ ይሄ ጦርነት ቶሎ የሚያልቅ ካልሆነ ሀገራችን ትኖራለች ብሎ ማለት ዘበት ነው። ሀገራችን ትበተናለች ምንም ጥያቄ የለውም። አሁን የሚባለው ሀገር አትፈርስም ምናምን ውሸት ነው የሚሆነው። ይሄ ጦርነት በአስቸኳይ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ማለቅ አለበት። የሽብር ቡድኑ መጥፋት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ለዚህ ከኅብረተሰቡ ምን ይጠበቃል?
ሻለቃ አበበ፡- አሁን እኮ ያለን አማራጭ አንድና አንድ ነው። ወይ ሀገራችን ትፍረስ ወይ ለሀገራችን ህልውና እንሙት ማለት አለበት ሕዝቡ፤ በቃ ምን የሚጠበቅ ነገር አለ። እኔ አሁን ሬንጀር ቢያለብሱኝ እሄዳለሁ፤ ደመወዝ አልፈልግም፤ ማእረግ አልፈልግም፤ ምንም የምፈልገው ነገር የለም ዩኒፎርም ይስጡኝ እሄዳለሁ። እያንዳንዱ ሕዝብ ይሄንን ካላደረገ ነገ ኢትዮጵያን አያገኝም። ነገ የልጆቹንና የልጅ ልጆቹን ሀገር አያገኝም። ይሄ ነገ ዛሬ የሚባል አይደለም፤ በአስቸኳይ ነው መሆን ያለበት። ከዚህ በኋላ ሽንፈት ከመጣ እነዚህ አሸባሪዎች ወደመሀል ሀገር መተው ሌላ ነገር ውስጥ ከገባን ሀገር የሚባል ነገር አይኖረንም።
አዲስ ዘመን፡- በጦርነት ቀጣና ውስጥ የሚገኙ የሌላ ሀገር ስደተኞች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ምን ዓይነት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል?
ሻለቃ አበበ፡– በጦርነት ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል። ሰራዊቱ ትግራይን ለቆ እንዲወጣ ትእዛዝ ሲሰጠው ቀይ መስመር ሊሰመር ይገባ ነበር። አሁን ለቀን የምንወጣው መቶ በመቶ አይደለም። ለምሳሌ መቀሌን ኮሃን እና የተወሰነ አካባቢ ተለቆ ከዚህ በኋላ አርፋችሁ ተቀመጡ መባል ነበረበት። ቀይ መስመር መኖር ነበረበት። ቢቻል ለስደተኞቹ ጥበቃ መደረግ ነበረበት፤ ያ አልተመቸ ይሆናል። ምናልባት እነዚያን ስደተኞች ቀደም ብሎ ለማውጣት ለደህንነቱ ባለመመቸቱ፤ አንዳንድ መረጃዎችም ይወጣሉ በሚል ሊሆን ይችላል እንጂ እነዚያ ስደተኞች ቀደም ብለው መውጣት ነበረባቸው።
አዲስ ዘመን፡- የእርሻ ወቅት መግባትን ተከትሎ በፌዴራል መንግሥት በኩል የተወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ከመቀበል ይልቅ ጁንታው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለመስፋፋት እየተጠቀመበት ነው፣ ይሄ ከምን የመነጨ ነው?
ሻለቃ አበበ፡- ድሮም አንድ እግር በመሬት ይባላል። ማፈግፈግ ስልት ነው፤ ምንም ጥያቄ የለውም። በተኩስ ተፅእኖ ስር ከሆነ አንድ ሰራዊት ያፈገፍጋል፤ ግን በተወሰነ መልኩ እራሱን እየጠበቀ፤ እራሱን እየተከላከለ ምንም ሳይሆን መውጣት መቻል አለበት። የተኩስ አቁም እርምጃው በተናጠል ነው የሆነው፤ ግን ቅድም እንደነገርኩሽ ቀይ መስመር መሰመር ነበረበት። ከዚህ ክልል ውጪ መንቀሳቀስ የለባችሁም፤ በዚህ ክልል ብቻ ነው፤ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ልታደርጉ የምትችሉት ብሎ ተኩስ አቁሙን የተወሰነ ቦታ ነበር መፍቀድ የነበረበት። ግን ያንን ተጠቅመው እነሱ ልክ እንዳሸነፉ ቆጥረው አሁን ለሌላ ድርድር እንዲመች ነው፤ የአማራውን እና የአፋሩን አካባቢ እያጠቁ ያሉት። ለሌላ ድርድር ሲያመቻቹ ነው። ምክንያቱም እነዚህን አካባቢዎች ከያዝን የመውጫ በር እናገኛለን በሚል ነው፤ ወይ በሱዳን ወይ በአፋር መውጫ በር እናገኛለን ብለው በማሰብ ነው። በአፋር በኩል እንደምታውቂው ተመትተዋል፤ በሁመራም ፈፅሞ ያልተቻለ አቅጣጫ ነው። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ታፍነዋል። የመሣሪያም ሆነ የሌላ ድጋፍ ለማግኘት በር ይፈልጋሉ፤ ያቺን በር ለማግኘት ነው ጥረት የሚያደርጉት። ስለዚህ በሮች ስለተዘጉ ለመደራደሪያ የሚሆን ነገር ነው እየፈለጉ ያሉት።
አዲስ ዘመን፡- በጁንታው በኩል ሕፃናትን ለጦርነት ማሳተፉ ከምን የመነጨ ነው?
ሻለቃ አበበ፡- ከፋሺስትነት የመነጨ ነው። መቼም እኔ፤ እኔ ሳልሞት ልጆቼን ሂዱና ተዋጉ አልልም። ምንም ማድረግ የማይችሉትን ሕፃናት መሣሪያ እያስታጠቁ ማዋጋት የጦር ወንጀል ነው። በዚህ መልኩ መንግሥት ጥሩ ሰርቷል፤ በምርኮም የተያዙትን ሕፃናት ሰብስቦ ለዓለም መንግሥታት አሳይቷል።
ለነገሩ እነሱ ሽብርተኛ ናቸው፤ የሽብርተኛ ደግሞ ተግባሩ ይሄ ነው። ምክንያቱም ለሽብርተኛ አንዱ መገለጫው ይሄ ነው። ሕፃናትን፣ አረጋውያንን እና መነኮሳትን መሣሪያ እያስታጠቀ ተዋጉ፤ አልቃችኋል፤ እያለ በግድም ሆነ በውድ ለእሳት መማገድ ከፍተኛ የጦር ወንጀል ነው። ማነው የሚጠይቀው፤ እንዴት ነው የሚጠየቁት፤ የሚለው ወደፊት የሚታይ ነው የሚሆነው። ወታደር እንኳን ሲቀጠር አስራ ስምነት ዓመት ካልሞላው ይባላል፤ ሰውነቱ ከፍ ብሎ እንኳን ዕድሜው ካልደረሰ መመልመል የማይታሰብ ነው። አሁን እኮ መሣሪያም መሸከም የማይችሉ ልጆች ናቸው እያየን ያለነው። ካለምንም ስልጠና መሣሪያውን እንዲህ አድርገህ አቀባብል እንዲህ ተኩስ እየተባሉ ነው ወደግንባር እየተላኩ ያሉት። ይሄ በምድርም በሰማይም የሚያስጠይቅ ግፍ ነው።
አዲስ ዘመን፡- የጁንታው ቡድን ለሰብአዊ እርዳታ መጓጓዣ የሚሆኑ አማራጭ መንገዶችን እየዘጋ እና ድልድዮችን እያፈረሰ፤ በሱዳን ድንበር ለእርዳታ ማጓጓዣ ይከፈትልኝ ማለቱ ከምን አንጻር ነው?
ሻለቃ አበበ፡– ይሄ ሁሉ ቀልድ ነው። የሚገርመው ነገር ይሄንን ቀልድ የሚቀበሉት መንግሥታት አሉ። የወያኔ ቡድን አሸባሪ የተባለው ዝም ብሎ አይደለም፤ በዚሁ ምክንያት ነው። ድልድዮችን በማፍረስ፤ መንገዶችን በመዝጋት እና ሥርዓት የሌለው ሥራ በመስራት ነው የሚታወቀው። አክሱም ውስጥ የሚገኘውን የአውሮፕላን ማረፊያ እንዴት አድርጎ እንደሄደ ታስታውሻለሽ፤ ሌሎች አካባቢዎችም ድልድዮችን ከጥቅም ውጪ አድርጓል። ለዚህም ነው ሽብርተኛ የሚለው ስም የሚያንሳቸው። እነዚህ ሰዎች አሁንም ይሄንኑ እየፈፀሙ ነው። አሁንም ሽብርተኝነቱን እየፈፀሙ ነው ያሉት፤ እርዳታማ እንደልብ የሚገባ ከሆነ ከዚያ በላይ ምንድነው የሚፈለገው። መሣሪያ ማስገባት አለብን ነው። በር ስጡን ማለት መሣሪያ እንደልብ እንድናስገባ ፍቀዱልን ማለት ነው።
ይሄ ምንም የሚሸሸግ አይደለም። ከጎረቤት ሀገር ጋር ተገናኝተን እንደልባችን መግባት መውጣት እንቻል፤ የጎደለንን ታንክ፣ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች እና መድፍ ተጨማሪ ጥይቶች ቀለብ እናስገባ ማለታቸው ነው፤ ሌላ አይደለም ጥያቄው። እርዳታ ከደረሰላችሁ ምንድነው የምትፈልጉት እንዳባይሉ ነው እነዚህን የእርዳታ ማስገቢያ አማራጮች የሚዘጉት። መንግሥት ያንን ሊያደርግ አይችልም፤ መንግሥት ሊያደርግ የሚችለው መፈተሽ ነው። እሱንም ዓለምአቀፍ ሕግም ይፈቅዳል፤ ወደዚያ የሚገቡትን ተሽከርካሪዎች እርዳታም ሆነ ማንኛውንም ተሽከርካሪ ፈትሾ የማስገባት መብትም ግዴታም አለበት።
ስለዚህ ልፈትሽ ይላል እንጂ መንገድ አይሰብርም፤ ይሄን የሚያደርጉት መንግሥት አደረገ ለማለት እና ለእኛ ክፍት መንገድ ተሰቶን መሣሪያ እንደልባችን እናስገባ ነው ጥያቄው እንጂ እርዳታ አልመጣልንም አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- መጨመር የሚፈልጉት ነገር ካለ ዕድሉን ልስጥዎት
ሻለቃ አበበ፡- ሀገራችን በጣም አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነው ያለችው። በተለይ በሰሜኑ በኩል ያለው ሁኔታ ያሳስባል። ሀገር የምናጣበት ነው ወይ እስከዘለዓለም ጠብቀን የምንኖርበት ሁለት አማራጭ ብቻ የያዝንበት ሰዓት ነው። እነዚህ ሰዎች ይጥፉ ወይስ እኛና ሀገሪቷ ትጥፋ ከሁለት አንዱ ነው አማራጩ። ይጥፉ ስንል የትግራይን ሕዝብ አይደለም፤ የሽብርተኛው ቡድን አባላት ጠቅላላ ይጥፉ ወይስ ሀገራችን ትጥፋ የሚለው ነው ምርጫ ውስጥ መግባት ያለበት። መቼም ሀገርን የማይፈልግ አለ ብዬ አልገምትም፤ በምንም መልኩ ሀገራችንን እንፈልጋታለን። ስለዚህ ካለው መንግሥት ጎን መቆም ምንም ሌላ አማራጭ የለም፤ ግራ ቀኝ እንኳን እምናየው አይደለም። ያለውን መንግሥት ረድተን ለውጤት ማብቃት የሕዝባችን ድርሻ ነው። ሁሉም በሞያው መረባረብ መቻል አለበት፤ ወደኋላ የሚባል ነገር መኖር የለበትም። ግድየለም ለጊዜው አያስፈልጉም ስለተባልኩ እንጂ እኔ እራሴ ዩኒፎርም ለብሼ ብዋጋ ለሀገሬ ደስተኛ ነኝ። በወያኔ ምክንያት በግድ ስለተሰደድኩ በዜግነት አሜሪካዊ ነኝ፤ ግን ምንጊዜም ቢሆን የትውልድ ሀገሬን ልረሳ አልችልም። አሁን ደግሞ በጣም ወሳኝ ጊዜ ነው። በተፈለኩ በማንኛውም ጊዜ ዝግጁ ነኝ፤ ይሄ ደግሞ የእኔ ብቻ ሀሳብ ሳይሆን እዚያ ያሉት የሁሉም ጓደኞቼም ነው። ለሀገራችን ለመሞት ዝግጁ ነን። አንድ ሰው ከሞተ በኋላ የሆነውን ነገር አያውቅም፤ በቁማችን ግን ሀገራችን ስትደፈር ማየት አንፈልግም።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ሻለቃ አበበ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2014