(ክፍል አንድ)
በታሪካዊ ጠላቶቻችን ስምሪት ሰጪነትና ስፖንሰር አድራጊነት በአሸባሪው ህወሓት ተላላኪነትና ፊት አውራሪነት በእነ ሸኔ ፣ በጉሙዝ ፣ በጋምቤላና በቅማንት ታጣቂዎች ተልዕኮ ተቀባይነት በህዝባችንና በሀገራችን ህልውና ላይ ግንባረ ብዙ የሽብር ጦርነት ተከፍቶብናል። በጦር ሜዳ ፣ በሀሰተኛ መረጃ ፣ በኢኮኖሚ አሻጥርና በፖለቲካዊ ዲፕሎማሲ አውደ ግንባሮች የተናበበና የተቀናጀ የሽብርተኝነት ጦርነት ታውጆብናል።
ህወሓት በሜሪላንድ ኮሌጅ ፓርክ በሚተዳደረው ዓለምአቀፍ የሽብርተኝነት የመረጃ ቋት ከ15 ዓመታት በፊት በአሸባሪነት ከተመዘገበ በኋላ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትንና ራሱን የኦሮሞ ሰራዊት ብሎ የሚጠራው ሸኔን በሚያዚያ መጨረሻ 2013 ዓ.ም በአሸባሪነት ፈርጇቸዋል።
ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ በፈጸመው ክህደት ታሪክና ትውልድ ይቅር የማይለውን ጭፍጨፋ በውድቅት ሌሌት የፈጸመ ጊዜ ፤ ሸኔ ደግሞ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች ማንነት ተኮር ተደጋጋሚ ጅምላ ጭፍጨፋ በንጹሐን ላይ ሲፈጽም በአሸባሪነት እንዲፈረጅ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ግፊትና ውትወታ ሲደረግ ቢቆይም በኋላ ላይ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅራቢነት ተግባራዊ ሆኗል ።
መንግስት በመደበኛ አሰራር የተለያዩ የወንጀል ተግባራትን ለመከላከልና ዝርዝር ክትትል ለማድረግ የማይችልበት ሁኔታ ሲፈጠር አንድን ቡድን አሸባሪ በማለት ሊፈርጅ ይችላል ። አንድን ተግባር ‘ሽብር’ ለማለት “የፖለቲካ ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ ህዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን ለማሸበር አስቦ የተፈፀመ ተግባር ሲሆን ፤ መንግሥትን ፣ የውጭ አገር መንግሥትን ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅትን ለማስገደድ ህይወትን ለአደጋ ማጋለጥ ፣ የአካል ጉዳት ማድረስ፣ ማገት ወይም መጥለፍ፣ ንብረትን እንዲሁም የማህበራዊ አገልግሎቶችን ማስተጓጎል” የሚሉትን ጨምሮ የተቀመጡ አምስት ክልከላዎች ተጥሰው ሲገኙ የሽብር ወንጀልን ያቋቁማሉ ፤ አንድ ድርጅት እነዚህን ተግባራት ዓላማው ካደረገ ፣ የድርጀቱ አመራር ወንጀሉን በአሰራር ወይም በግልጽ የተቀበለው ከሆነ ፣ በአሰራር ወይም በአፈፃፀም ወንጀሉ የድርጅቱ መገለጫ ከሆነ፣ አንድ ቡድን አሸባሪ ተብሎ ሊሰየም እንደሚችል፤ የሽብር ሕግ የማርቀቅ ተግባር ላይ የተሳተፉት እና የዐቃቤ ህጉን የአማካሪ ጉባኤ ጽህፈት ቤት የሚመሩት አባድር ኢብራሂምን (ፒኤችዲ) በዚያ ሰሞን ለቢቢሲ አማርኛ ማስረዳታቸው ይታወሳል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በሁርሶ ኮንቲንጀንት ወታደራዊ ማሰልጠኛ የ3ኛ ዙር ሰልጣኞኝች ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ፤”ህወሓት በሽብር ተፈጥሮ በሽብር አድጎ በሽብር መንግስት ሆኖ በሽብር ጫካ የገባ አሸባሪ ቡድን ነው ።” ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝ ጥቃት እና የማይካድራን፣ የጋሊኮማንና የአጋምሳን ትውልድና ታሪክ ይቅር የማይለውን የክፍለ ዘመኑን ታላቅ ክህደትና ጭፍጨፋ ለመፈጸም ዝግጅቱንና ልምምዱን የጀመረው ከደደቢት ውልደቱ ከየካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም አንስቶ ነው ። ለግማሽ ክፍለ ዘመን በዝግ የተዶለተበት የክህደት ደባ እና የጭካኔ ልምምድና ዝግጅት ውጤት ነው።
ከሀዲውና የባንዳ ዲቃላው የትህነግ ገዥ ቡድን በ1968 ዓ.ም ባሰናዳው የርዕዮት ዓለም መርሀ ግብር /ማንፌስቶ/ የአማራን ህዝብንና ባህሉን በጠላትነት እንዲህ ይፈርጀዋል። “ጨቋኟ የአማራ ብሔርም ጭቆናዋን እስስካላቆመች ድረስ ህብረተሰባዊ እረፍት አታገኝም ። የትግራይ ህዝብ ብሔራዊ ትግል ጸረ አማራ ብሔራዊ ጭቆና ጸረ ኢምፔራሊዝም እንዲሁም ጸረ ንዑስ ከበርቴያዊ ጠጋኝ ለውጥ ነው ።
ስለዚህ የአብዮታዊ ትግል ዓላማ ከባላባታዊ ሥርዓትና ከኢምፔራሊዝም ነጻ የሆነ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን ማቋቋም ይሆናል። አሁን ያለውን አሮጌና አድሃሪ የአማራ ባህል ደምስሶ በአዲስ አብዮታዊ ባህል መተካት የተህሐት /የህወሓት/ ዓላማ ነው። “ በዓለማችን ከናዚው አዶልፍ ሒትለር ቀጥሎ አንድን ህዝብ በጠላትነት የፈረጀ ፓርቲ ቢኖር ከሀዲው ትህነግ ሁለተኛው ነው። ሒትለር አይሁዶችን በጠላትነት ፈርጆ ፖለቲካዊ ሀቲቱን አዋቅሯልና። በነገራችን ላይ በወረራቸው አካባቢዎች ይህን እቅዱን ነው ተግባራዊ እያደረገ ያለው ። በደቡብ ጎንደር በዋግ ኽምራና በሰሜን ወሎ የፈጸመው ህልቆ መሳፍርት የሌለው ዘግናኝ ገፍ ማንነቱን ቁልጭ አድርጎ አሳይቶናል ።
ባንዳው ትህነግ አገዛዝ ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታትም ሆነ ከስልጣኑ በህዝባዊ ተቃውሞና በለውጥ ኃይሉ ተፈንግሎ በመማፀኛ ከተማው በመሸገባቸው ከሶስት ዓመታት በላይም ሆነ በትጥቅ ትግል ላይ በነበረባቸው 17 ዓመታት በተለይ አማራን ኢላማ ያደረጉ ህልቁ መሳፍርት የሌላቸው ለማየት የሚዘገንኑ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ጥቃቶችን ሰንዝሯል። ከ70ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ ፣ ዘር ማጽዳትና ግፍ ለ47 ዓመታት ዘልቋል ።
ወልቃይቴዎች በማንነታቸው በግፍ ተገለዋል፣ ተሰቃይተዋል፣ ተደብድበዋል፣ ተግዘዋል፣ ታስረዋል። በቋንቋቸው እንደይናገሩ እንዳይማሩ ተደርገዋል። በቁማቸው ከአንገት በታች ተቀብረው ከብት ተነድቶባቸዋል ። ግህንብ በተሰኘ የምድር ውስጥ /አንደርግራውንድ / እስር ቤት ይሰቃዩ በመርዝ ይገደሉ፤ ይታፈኑና በዛው ጠፍተው ይቀሩ እንደነበር በሙሉቀን ተስፋው፣ “ የጥፋት ዘመን “ መፅሐፍ ተሰንዶ ይገኛል። መች ይህ ብቻ የወልቃይት ሴቶችን በትግራዋይ ወንዶች በግዳጅና በጠለፋ እየተወሰዱ እየተደፈሩ ማህበረሰቡን ከአካባቢው የማጽዳት ስራው / ኤትኒክ ክሌንሲግ / ሆን ተብሎ በዕቅድ ተሰርቷል።
የሚያሳዝነው ከሀዲው ትህነግ በወልቃይት ጠገዴ አማራዎች ላይ ግፍ ሲፈጽም የነበረው ከሱዳን ጋር እየተቀናጀ መሆኑ ነው።
ይህ የከሀዲዎችና የባንዳዎች ዲቃላ ወደ ገዥነት ከመጣ በኋላ በማንፌስቶው መሰረት አማራን ለማዳከም፣ ለማሸማቀቅ፣ አንገት ለማስደፋት፣ ለማደህየት፣ ቋንቋውን ለማኮስመን፣ ማህበራዊ ወረቱን /ሶሻል ካፒታል/ ለማክሰር ፣ መሬቱን በመውረር ለነገሩ ከተናጠሉ የተኩስ አቁም በኋላ እያደረገው ያለውም ይሄንኑ ነው ።
ከሽግግሩ ጀምሮ ፖለቲካዊ ውክልናና ተሳትፎ እንዳይኖረው በማድረግ ፤ የአማራ ክልል በልጆቹ ሳይሆን እሱ በመደባቸውና አማራ ባልሆኑ ሞግዚት ተላላኪዎች እንዲገዛ በማድረግ ቅስሙን ለመስበር ሌት ተቀን ሰርቷል። ከሀዲውና አማራ ጠል የሆነው ትህነግ ብሔሩ በሌሎች ብሔሮች እንዲጠላ በጥርጣሬ እንዲታይ አቅዶ በስፋት ሰርቷል። እንደ ሸኔ ኦነግ ባሉ ተላላኪዎቹ ጥቃት እንዲፈጸምበት ስምሪት ሰጥቷል። ስፖንሰር አድርጓል። በዚህም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አማራዎች ተገለዋል። አካላቸው ጎድሏል። ተፈናቅለዋል።
ከሀዲው ትህነግ አገዛዝ ላይ በነበረባቸው 27 የግፍ ዓመታት በበጀት ተደግፎ መዋቅራዊና ተቋማዊ በሆነ አግባብ በአማራ ህዝብ ላይ ለማየት የሚዘገንን ለመስማት የሚሰቀጥጥ ጭፍጨፋ ፈጽሟል። አስፈጽሟል።
ከሽግግር መንግስቱ አንስቶ ከአገዛዝ እስከተፈነገለባቸው ዓመታት አማራ በመላው የሀገሪቱ ክፍል በማንነቱ እንዲጠቃና እንዲጨፈጨፍ አድርጓል። በምስራቅ ሐረርጌ በጋራ ሙለታ፣ በወተር፣ በበደኖና በድሬዳዋ፤ በምዕራብ ሀረርጌ በገለምሶ፤ በአሰቦት ገዳም፣ በአርሲ፣ በአርባ ጉጉ፣ በአጋሮ፣ በሸቤ፣ በጉራ ፈርዳ፣ በወለጋ፣ በኖኖ፣ በአማያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በከማሺ፣ በመተከል፣ በአፋር እና በራሱ ክልል ዘርፈ ብዙ ጥቃት እንዲፈጸም አድርጓል።
በዚህ የተነሳም ከፍ ብዬ እንደገለጽሁት በበዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል፣ አካለ ጎደሎ ሆነዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ ተዘርፈዋል። ከለውጡ ወዲህም አሸባሪው ህወሓት በዚህ ብሔር ላይ የሚፈጸመው ግፍ ተባብሶ ቀጥሏል ። በሶማሌ ክልል በተለይ በጅግጅጋ፤ የአርቲስት ሀጫሉን ግድያ ተከትሎ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በሌሎች የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎችን በአብነት ማንሳት ይቻላል ። በሰሜን ዕዝም ሆነ በማይካድራ ንጹሐን ማንነትን መሰረት አድርጎ የተፈጸመው ጭፍጨፋም የከሀዲው ትህነግ የ47 ዓመታት የጸረ ኢትዮጵያና አማራ ፕሮጀክት አካል ነው ። ለመሆኑ የህወሓት የግፍ ጽዋ ሞልቶ የፈሰሰባት ማይካድራ ማን ናት ።
ማይካድራ ከተማ በትግራይ ክልል በምዕራባዊ ዞን በሃፍታ ሁመራ ወረዳ የምትገኝ የከተማ አስተዳደር ናት። ከተማዋ ከሁመራ ከተማ በስተደቡብ በ30 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ እንዲሁም ከምድረ ገነት ከተማ (ወይም አብዱራፊ በመባል የምትታወቅ) ደግሞ በ60 ኪ.ሜ. ርቀት በስተሰሜን አቅጣጫ ላይ ትገኛለች። በከተማዋ የትግራይ፣ የወልቃይትና የአማራ ተወላጆች እንዲሁም የሌሎች ብሔረሰብ ተወላጆችን ጨምሮ ከ45 እስከ 50 ሺህ የሚገመት ህዝብ ይኖራል። በወልቃይት የተወለዱ ወይም ለረጅም ጊዜ የኖሩ የአማራ ተወላጆች በአካባቢው በተለምዶ ወልቃይቴዎች በሚል ስያሜ ይጠራሉ ። ይህ መጠሪያቸው ወንጀል ሆኖ ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ማይካድራው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ድረስ ግፍ ተፈራርቆባቸዋል።
በማይካድራ ከተማ ነዋሪና ለቀን ስራ ከክልሉ አጎራባች ዞኖች በመጡ አማራዎች በተፈጸመው ግፍ ቢያንስ ከ1000 በላይ በአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና ‘ሳምሪ’ በተባለ ኢ-መደበኛ ገዳይ የወጣቶች ቡድን መገደላቸውንና ቁጥሩም ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ተመልክቷል ። የተናጠል የተኩስ አቁሙን ተከትሎ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተስፋፋው የአሸባሪው ወረራ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዘረፋና የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል። የእንግሊዙ ዘ ቴሌግራፍ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ አጋምሳ በተባለ መንደር በሀምሌ አጋማሽ አሸባሪው ህወሓት ከ300 በላይ ንጹሐንን መጨፍጨፉን እና በክልሉ ከ500ሺህ በላይ ህዝብ መፈናቀሉን ዘግቧል ።
በክፍል ሁለት መጣጥፌ በጋሊኮማና በአጋምሳ የተፈጸሙ የሽብር ጥቃቶችንና ተያያዥ ነጥቦችን አነሳሳለሁ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በሀቀኛና ጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2014