በኦሮሚያ ክልል እየተገነቡ ከሚገኙ ትላልቅ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች አንዱ በምዕራብ ባሌ ዞን በደሎመና ወረዳ እና በሃረና ወረዳ የወልመል ጎዳ ወንዝን በመቀልበስ የሚገነባው የወልመል መስኖ ልማት ግድብ ነው። ግንባታው ታህሳስ 2012 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን ታህሳስ 2015 ዓ.ም ይጠናቀቃል ተብሎ እቅድ ተይዟል።
ፕሮጀክቱ በሁለት ሎቶች ተከፍሎ የሚሰራ ሲሆን ሎት አንድ በ2013 በጀት ዓመት መጨረሻ 40 ነጥብ 18 በመቶ ሎት ሁለት ደግሞ 21 ነጥብ 19 በመቶ ደርሷል። የሎት-አንድ በ2013 በጀት ዓመት መጨረሻ ከነበረበት 40 ነጥብ 18 በመቶ በ2014 በጀት ዓመት 40 ነጥብ 17 በመቶ በማከናወን በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 80 ነጥብ 35 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል።
ሎት-ሁለት በ2013 በጀት ዓመት መጨረሻ ከነበረበት 21 ነጥብ 19 በመቶ በ2014 በጀት ዓመት 59 ነጥብ 49 በመቶ በማከናወን በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 80 ነጥብ 68 በመቶ ለማድረስ እቅድ መያዙን የኢፌዴሪ መስኖ ልማት ኮሚሽን ይፋ አድርጓል።
የኢፌዴሪ መስኖ ልማት ኮሚሽን የኮሙንኬሽንና የውጭ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት መረጃ እንደሚያመ ላክተው፤ የግንባታው ወጪ ሎት-አንድ 1 ነጥብ 72 ቢሊዮን ብርና ሎት-ሁለት 1 ነጥብ 88 ቢሊዮን ብር ሲሆን የፕሮጀክቱ አጠቃለይ ወጪ ሶስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር ነው።
የፕሮጀክቱ ግንባታ የሚያካትተው የ34 ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር የዋና ቦይ ግንባታ፣ የወንዝ መቀልበሻ ግንባታ፣ 18 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ፣ በግራና በቀኝ የሚከፈል 58 ነጥብ 48 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የሁለተኛ ቦይ ግንባታ፣ 72 ነጥብ አራት ኪሎ ሜትር ሶስተኛ ቦይ እና አራተኛ ቦይ 350 ኪሎ ሜትር የሚሆን ልዩ ልዩ የመስኖ ልማት መዋቅሮች ግንባታ እንደሚኖሩትም የዳይሬክቶሬቱ መረጃ ያሳያል።
ፕሮጀክቱ በሶስት ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖሩ ከ22 ሺ በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የገለጸው የዳይሬክቶሬቱ መረጃ የመስኖ ልማት ግድብ ግንባታው ሲጠናቀቅ በአጠቃላይ ከ11 ሺ በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት እንደሚያስችል አብራርቷል። የአካባቢው አርሶ አደሮች በአካባቢው በስፋት የሚለሙትን በቆሎ፣ ሰሊጥ፣ ማሽላ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማልማት በዓመት ውስጥ ከሁለት እስከ ሦስት ጊዜ ምርት እንዲያገኙ እንደሚያስችልም አብራርቷል።
የወልመል ወንዝ ከፍተኛ የውሃ መጠን ያለው እና ለመስኖ ልማት ሊውል የሚችል ለም መሬት የሚገኝበት አካባቢ ለዘመናት ሲፈስ የቆየ ቢሆንም እንደ አብዛኞቹ የሀገራችን ወንዞች ቀደም ባሉ ጊዜያት በወንዙ ላይ ይህ ነው የሚባል የልማት ስራ ሳይሰራ ቆይቷል። ነገር ግን የለውጡ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ለመስኖ ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት የመልማት እድል ካገኙት ወንዞች አንዱ ነው።
የወልመል የመስኖ ልማት ፕሮጀክት የአካባቢውን አርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነትን ከፍ ከማድረጉ እና ሀገሪቱ ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ ለምታደርገው ርብርብ በምርት እድገት ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ ባሻገር ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች ጊዜያዊ እና ቋሚ የስራ እድል እየፈጠረ ይገኛል። ከፕሮጀክቱ ኮንትራክተር የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ፕሮጀክቱ ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሥራ አጥ ዜጎች ጊዜያዊ እና ቋሚ የስራ እድል ፈጥሮላቸዋል።
የፕሮጀክቱ ኮንትራክተር እንደሚሉት ፕሮጀክቱ ከተያዘለት ጊዜ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ ሀሳብ የነበረ ቢሆንም በሀገሪቱ አጋጥሞ የነበረው የሲሚንቶ እጥረት እና ግንባታው የሚከናወንበት አካባቢ ከመሀል ሀገር ወጣ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመንገድ መሰረተ ልማት እጥረት የሚስተዋልበት መሆኑ የግንባታውን ሥራ አሁን እየተገነባ ካለበት ፍጥነት በላይ ለማፋጠን አዳጋች በመሆኑ ከተያዘለት ጊዜ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ እንቅፋት ሆኗል።
እያንዳንዱ የፕሮጀክት ግንባታ ያለ እንቅፋት እንዲካሄድ የአካባቢው ህብረተሰብ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን የዳይሬክቶሬቱ መረጃ የሚያሳይ ሲሆን ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ እና ህብረተሰቡም ተጠቃሚ እንዲሆን ድጋፉን አጠና ክሮ መቀጠል እንዳለበት ይጠቁማል። በባለድርሻ አካላት መካከል ያለው የተቀናጀ አሰራርም ተጠንክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
የኢፌዴሪ መስኖ ልማት ኮሚሽን በባለቤትነት የሚያስገነባው ይህ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ኮንስት ራክሽን ዲዛይንና ቁጥጥር ሥራዎች ኮርፖሬሽን አማካሪነት እንዲሁም በስራ ተቌራጭነት ሎት-አንድ የወንዝ ውሃ መቀልበሻና ዋና ቦይ ግንባታን በሚገነባውን ዓለማየሁ ከተማ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ እና ሎት-ሁለት የመስኖ ልማት መሰረተ ልማት ግንባታን በሚገነባውን በኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ግንባታው እየተከናነው ይገኛል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15/2013