ቀናት በቀናት ፤ ወራት በወራት እየተተኩ፤ አሮጌው ዓመት በአዲሱ መተካቱ በዘመን ቀመር ጊዜውን ጠብቆ የሚከወን ተፈጥሯዊ ዑደት ነው።ዓምና ላይ አዲስ ብለን የተቀበልነው ዓመት፤ ዘንድሮ አሮጌ ብለን እንሸኘዋለን ፡፡
በዘመን ሽግግር ዓምናን ዳግም ላንመለስብት ደህና ሁን ብለን ሸኝተን ፤ በአዲስ ዓመት አዲስ ተስፋን ሰንቀን በዘመኑ መለወጥ ተደስተን በፍቅር የምንቀበለው ነው።ዘመኑ ጊዜውን ጠብቆ ዓመት በዓመት እየተካ ወደፊት ሲገሰግስ እኛም አብረን እንጓዛለን ፡፡በእድሜያችን ላይ አንድ ዓመት እየደመርን በማያቋርጠውን ጉዞ ማለፋችን የማይቀር ነው።
ዓምና ያላሳካናቸው ውጥኖች ወደ አዲሱ ዓመት አሸጋግረን ከአዲሱ ዓመት እንዳያልፉ ለማድረግ ለራሳችን ቃል ገብተን ፣ በአዲስ ዓመት ይህንን አደርጋለሁ፤ ይህንን አላደርግም እያልን ቢሆንልን ያልነውን ተመኝተን በቃል አስረን እንዲጸናልን እንመኛለን።አዲሱ ዓመት ጊዜውን ጠብቆ ከፊታችን ሲቆም፤ በአዲስ መንፈስ ለመቀበል ሽርጉዳችንን እናጦጡፋለን፡፡በደስታ ተቀብለን ውጥናችን ከግብ ለማድረስ እንፍጨረጨራለን፤ ታዲያ ቀኑ መሽቶ መንጋቱ አይቀርምና ጊዜው እንዳሰብነው ሳይሆን ይቀርና ቀኑም ፤ዓመቱም በየተራ ይነጉዳሉ፡፡
አንዱን ሳናሳካ የጊዜውን መጠናቀቅ ሲገባ በሀዘኔታ እራሳችንን መነቅነቃችን አይቀርም።ሮጠን አንደርስበት ነገር ሆኖብን ወደኋላ ልንመልስ የማንችለው መሆን ሲገባን ካልተሳፈሩበት ተሽቀዳድሞ “ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቀን ቆሞ “ እንዲሉት ሆኖብን የምንይዘውን የምንጨብጠውን እናጣለን። ያለን አንድ አማራጭ ቀጣዩን ዓመት በተስፋ መጠበቅ ነው።እኛን እዚያው ሆነን፤ እሱ ጥሎን ይከንፋል።እንዲህ እንዲህ እያለን ህይወት ትቀጥላለች፡፡
እስኪ አምና ላይ ልመልሳችሁ።አምና ብለን የተውነው 2013ዓ.ም የሰላም፣ የፍቅር፣ የመተሳሳብ የአንድነት ዘመን ይሁንልን ተባባለን በኢትዮጵያው ባህል ተመራርቀን እንኳን በሰላም መጣህ ብለን ተቀበልን ።ገና በጠዋቱ የናፈቅናት አደይ አበባ ከመርገፏ አፍታም ሳይቆይ ሰላማችን በእጅጉ ደፈረሰ። አዲሱ ዓመት የፈተናና የሰቆቃ ዓመት ሆኖብን አለፈ።
በእማዬ ኢትዮጵያ ምድር ሆኖ የማያውቅ ክስተት ተከሰተ።ሀገር የታመመችበት ህመሟም ጠናባት ስቃይ ውስጥ ገባች።ለጆሮ የሚቀፉ ግፎችና በደሎች በመስማት ጆሯችን ደማ፡፡ውስጣችን ክፉኛ ታመመ፡፡
“ የጉድ ሀገር “ እንዲሉት ሆኖ ሀገር ለማፍረስ እቅድ ይዘው የተነሱት አካላት እቅዳቸውን ለማሳካት የደከሙበት ነው ።በ2013 ዓ.ም አዲሱ ዓመት ሆኖ መምጣት በአዲስ መንፈስ ለመታደስ ሳይሆን ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንፈርሳለን ያሉ የእናት ጡት ነካሾችን የተነሱበት ነው።
ጥቅምት 24 ክፉ ስራቸውን በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ በከፈቱት ጥቃት አሃዱ ያሉበት ሆነ።አንድና አንድ ዓላማቸው ሀገርን ማተራመስ ነበርና ሀገር ፈተና ውስጥ ከተቱ። 27 ዓመት የሰሩት ግፍና በደል ባህር ሲዋኙ የነበሩ የአሸባሪው መሪዎች ይህ አልበቃ ብሏቸው እንደገና ህዝብ ከስቃይና ለመከራ መዳረግ ጀመሩ።በርካታ እኩይ ድርጊቶች ተፈጸሙ፤ ንጽሃ ህይወት እንደቅጠል ረገፈ።ከሰማነው ያልሰማነው እየበለጠ ከአቅማችን በላይ የሆነ ግፍ በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ተፈጸመ፡፡
የዘንድሮ አዲስ ዓመት ግን ከሁሉም ዓመታት ይለያል።የታመመችውን ሀገር ለማዳን ከምንም ጊዜ በላይ የምንተጋበት ነው።ሀገር የማፍረስ እቅዳቸው ቢከሽፍም፤ የሀገርና የወገኑን ወጋግተው ፤አቁስለዋታል።ሀገር የሚያስታምማት ፤ አስታሞ ከህመሟ የሚያድናት አዳኝ ልጆችን ትሻለች።
አዲሱ ዓመት ከሁሉም በላይ በሀገር ጉዳይ የሚደራደር ኢትዮጵያው ከቶ የለምና በሀገር ላይ ያጠላውን ጥላ በመግፈፉ መርዙን መንቀል ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ነው።በመከራ ያለፈውን ዓመት ዘንድሮ የድል ብስራት የሚሰማበት ፤ የደፈረሰው የሚጠራበት፤ እንዲሆንልን ከሀገር ጎን መቆም ያስፈልጋል።አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋን ብርሃን የምናበራበት ፤ የሀገር ነቀርሳ የሆነውን አሸባሪ በነበረበት በመቅበር ለህዝቡ ብርሃን ጮራ መለኮስ በእጅጉ የምሻበት መንገድ ላይ ነን ፡፡
ነቀርሳ በማስወገድ ከድህነት አረንቋ ለመውጣት የምናደርገው ትግል በመቀጠል የተጀመሩ የለውጥ ጅምሮችን ከግብ በማድረስ መትጋት የዜጎች የህልውና ጉዳይ ሊሆን ይገባል።ዛሬ በዓለም አደባባይ ቀና እንዳንል አድርጎ አንገታችንን ያስደፋን አሸባሪ ከፊታችን አስወገደን ፤ በእድገት ጎዳና ለመጓዝ ብዙ መስዋዕትነት እየከፈልን መሆኑ መቼም አይረሳም።
ይህንን በታሪክ መዝገብ የሰፈረ አጸያፊ ታሪክ በተለወጠ መንፈስ በአዲስ ቀይረን ኢትዮጵያን ብልጽግና ,በአንድነትና በአብሮነት ጎዳና ወደፊት አንድ እርምጃ የምናራምድበት መሆን አለበት፡፡
“አማን አማን ቸር ያሰማን” እንዳለው ከያኒው በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያ የድል ብስራት የምትሰማበት ፤በዓለም መድረክ ከፍ ብላ የምትታይ እንዲሆንላት ነው።እኛ ኢትዮጵያዊያን አዲሱን ዓመት ስናከብር መልካም ምኞትን ከመግለጽ ባሻገር የመተሳሳብና መረዳዳት ባህልና እሴቶችንን ማጎልበት አለብን ።
በተለይ በአሁኑ ወቅት በአሸባሪ ጦስ ህይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ዜጎች እንዳሉ ሁሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በክረምቱ የጭለማ ወቅት ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። እነዚህ ማዕዳቸው ሞልቶ ሲፈስ የነበር ከራሳቸው አልፎ ለሌላው የሚተርፍ አርሶ አደሮች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል።በርካታ የእኛ የእርዳታ እጅ ይሻሉ።
በዓል አብረን ማክበር፤ ማዕድ አብሮ የመቋደስ ባህላችንን ከቶ የሚረሳ አይደለምና።ለወገን ደራሽ ወገን ነውና ልንረዳቸውና ልናግዛቸው የግድ ይለናል።በአንድነት ከሆን የማንሻገር መከራ የለም።ነገ የምንናፍቃትን ሀገር እንድትኖር እርስ በርሳችን እየተረዳዳን መኖር የውዴታ ግዴት አለብን፡፡
አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅርና የብልጽግና እንዲሆንልን በለውጡ የፈነጠቀውን የብርሃን ጭላንጭል በመከተል በአንድ መንፈስ እጅ ለእጅ ተያይዙን በለውጥ ጎዳና የምንጓዝበት ይሁንልን ! አሜን አበቃሁ።
ትንሳኤ አበራ
አዲስ ዘመን መስከረም 2/2014