እናት ሀገር ኢትዮጵያ በሚል ዘፈን ያደገ እናት ሀገሩን ከውጪ ሀይሎች ጋር ተባብሮ ለማፍረስ አይሰራም፤ ላይፋቅ የጸና የእናት እና የልጅ ቃልኪዳን መሀላ በመሀላቸው ሰፍሯልና። ይልቁስ ወራሪ ጠላት በገጠማት ጊዜ አጥንቴም ይከስከስ፣ ደሜም ይፍሰስ ሃገሬን ጠላት ጭራሽ አይደፍራትም እያለ ለእናት ሀገሩ ይሰዋላታል። በተለይ የዚ ዘመን ትውልድ በጂጂ አድዋ የአያቶቹን ጀግንነት የተዋወቀ እና ያደነቀ እነሱን ለመዘከር የሚታትር ነው። የእኛ ዘመን ጠላት ድህነት ነው፤ በሚል ድህነትን ድል በማድረግ ታሪክ ለማድረግ ቢንቀሳቀስም በግድ ጠላትነት ያማራቸውን በጦር ሜዳ ለመግጠም ተገዷል። ጀግንነትም ኪነጥበብም የአባቶቹ ነውና በራሄል ጌቱ ዘፈን ‹የእሷን ክፉ ቆሜ ከማይ ያሳደገኝ አፈር ይብላኝ› ብሎ ከዳር እስከዳር ተነስቷል። የዛሬዋ ቀን የድል ቃልኪዳን ብስራት በሚል ተሰይማለች። ኪነጥበብ ለሀገር ድል እንደሚመጣ ከማነሳሳት አንስቶ ድልን ለማብሰር ስለሚኖራት አስተዋጽኦ ከረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ጋር ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም አዲስ ዓመትን መታደስ ያስፈልጋል በሚል ስሜት ግለሰቦች እንጂ በመንግስት ደረጃ ሰፊ ዝግጅት አይታይም ነበር። ባለፉት ሶስት ዓመታት በመንግስት ደረጃ ለጳጉሜ ለእያንዳንዱ ቀን ስም በመስጠት ዝግጅት መደረጉ ምን የሚያመጣው ነገር አለ?
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፡- ይሄ በፊትም ቢሆን በኢትዮጵያ በብዙ ባህሎች ውስጥ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምእራብ በምስራቅም ባሉት ኢትዮጵያን ባህል ውስጥ አዲስ አመት እንደባህሉ እና የቀኑ ሁኔታ ይለያይ ይሆናል እንጂ የዘመን መለወጫ እያሉ የሚያከብሩት በዓል ነው። በዛ ውስጥ አዲስ አመት ብለው የሚጠብቁትን በዓል ለመቀበል በጣም ከፍተኛ ዝግጅት ነው የሚያደርጉት። አንዳንዶቹ የአየር የጨረቃውን የተፈጥሮን የአየር ንብረቱን ሁኔታ በሙሉ የከዋክብቱን እያጠኑ ዘመን መለወጫቸውን እያደረጉ በጣም ተዘጋጅተው ነው የሚሸጋገሩት። አንዳንዶቹ ቦታ ለምሳሌ ከብት አርደው የመልካም ምኞት መግለጫ ስጦታ ተሰጣጥተው፣ አንዳንዶቹ ቦታ ውሀ ዳር ሄደው ገላቸውን ታጥበው አምላካቸውን አመስግነው ነው የሚያከብሩት።
እንዳልሽው ደግሞ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለውጥ ከመጣ ወዲህ ያለው ነገር ደግሞ በህዝባችን ውስጥ ያለውን ወረት መመልከት የሚል ነው። ምክንያቱም ባህል የሰው ልጅን አእምሮ የሚያንጽ፤ የወደፊት ርዕይን የሚተልም እና ሰዎች ከእንስሳ የሚለዩበት የህይወታቸው መገለጫ ነው። ቤተሰብ፣ ጎረቤት፣ አካባቢ የሚባሉ ነገሮች ሁሉ በሰው አእምሮ ውስጥ የሚሰሩት በባህል ነው። አንዱ የምናከብረው ወረታችን የባህል ወረታችን ነው። በአለም ላይ ልዩ የሆነ የዘመን አቆጣጠር እንዲኖረን አባቶቻችን አጥንተዋል፤ ተመራምረዋል፤ ተፈትነዋል። በዚህም በመስከረም አንድ ብሄራዊ የሆነው የዘመን መለወጫ በዓላችን በአለም ዙሪያ የሚያስከብረን እና የራሳችን የሆነ ነው።
መሻገሪያ የምንለው በተለይ ጷጉሜ ከአመት አቆጣጠር የተረፈችዋ በአለም ላይ የኢትዮጵያ መለያ ናት። እቺን እንደድልድይ እንደመሻገሪያ አድርገን በዚህ ጥቂት አመታት ውስጥ ጷጉሜን እያከበርን አዲሱን አመት ራሳችንን ለተሻለ አዲስ ነገር ማዘጋጀት ከጥንት አባቶቻን የወሰድነው ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዛሬ የድል ቃልኪዳን ብስራት ቀን በሚል ተሰይሟል፤ ለመሆኑ ድልን እንዴት ትገልጸዋለህ?
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፡- ድል ብዙ አይነት ነው፤ ሀሳቡም ተግባሩም የተለያየ ነው። የሰው ልጅ በአለም ላይ ተፈጥሮ በሚኖርበት ቀን በእያንዳንዱ ቀን ፈተና ይገጥማል። በእያንዳንዱ ቀን ድል አለው፤ ፈተናውን ያልፋል፤ ወይም ደግሞ በእያንዳንዱ ቀን ሽንፈት አለው፤ ይወድቃል። ሰው በእያንዳንዱ ቀን ከሚሸነፈው ሽንፈት እየተማረ ለሌላ ድል እየተነሳ የሚጓዝ ፍጥረት ነው። የሰው ልጅ ግዙፍ የሚያደርገውም ብዙ ጊዜ ወድቆ እንደገና ተነስቶ ወደድል የሚሄድበት ነው። ስለዚህ የድል ሀሳብ በየቀኑ እየተጸነሰ እየተተገበረ እየተለማመድነው ከምንሄደው ነገር ጋራ የሚያያዝ ነው።
የፈተና እና የድል ሁኔታ የሰው ልጆች የእለት ተእለት የህይወት ሙሉ መልክ ነው። እንደሀገር አሁን ባለንበት ወቅት ፈተናዎች አሉ። ምክንያቱም በከፍተኛ የለውጥ እና የሽግግር ዘመን ላይ በመሆናችን እና ምእራባውያን ሶስተኛ አለም የሚላቿውን በንቀት ለመቆጣጠር በተሰማሩበት የቅኝ ግዛት ዘመን አንገዛም ብለን ያሸነፍን በመሆናችን የደረሰብን ፈተና አለ። ይሄ ፈተና ዘመናዊው አለም ድረስ እኛን እየፈተነ የሚኖር ነው።
የአድዋ ድል አንዱ የድል ታሪካችን ነው። ያንን ያገኘነው በህብረት አንድ ላይ በመቆማችን ነው። እንዴት ጥቁር ህዝብ አውሮፓዊ ሀይልን ሊያሸንፈው ይችላል፤ የሚል በቀኝ ገዚዎቹ ሀገራት ከድላችን በኋላ ሌላ ፈተና አስነስቶብናል። እንደምታውቂው አውሮፓውያን በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ሲሄዱ የተለያዩ ጎሳዎችን ነው ያገኙት፤ እነዛን ጎሳዎች እየሰበሰቡ ሀገር የመሰረቱት ወራሪዎቹ ናቸው። ኢትዮጵያ በሚመጡበት ጊዜ ግን ለረዥም አመታት የኖረ የመንግስት አስተዳደር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ነው ያገኙት። ሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ካረጉት በተቃራኒው አንድ ሆኖ ህብረት ይዞ ያገኙትን ለመበተን ነው የሰሩት። ከዛኔ ጀምሮ አንዱን ጨቋኝ ሌላውን ተጨቋኝ የሚያደርጉ መጽሀፍትን እየጻፉ፤ ልጆቻችንን ስኮላርሽፕ እየሰጡ ይሄ የልዩነት ሀሳብ መሰረት እንዲይዝ እና የእስካሁን ፈተናችን እንዲሆን ሰርተዋል።
ዘንድሮ የእስካሁኑ ስራቸው ተሰብስቦ እና ራሱን በሌላ መልክ ገልጾ የኢትዮጵያውያን እና የጸረ ኢትዮጵያውያን ጦርነት የሚታይበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ልክ እንደ አድዋ ሁሉ ሀገራችንን እማንጥል፣ ህብረቷን ለመመለስ እና በእኛ ጊዜ እንዳትፈርስ ለማድረግ የቆምንበት ጊዜ አሁን ነው። ይሄን በድል እንደምንወጣው እርግጠኛ ነኝ፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት ተሸንፎ አያውቅም፤ ኢትዮጵያ ሁልጊዜ ታሸንፋለች። ድል በግለሰብም ሆነ በማህበረሰብ ደረጃ አሁን እንዳጋጠመን አይነት ፈተናን ማሸነፍና ለሚቀጥለው ትውልድ እዳ እንዳይሆን ማድረግ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ድል እንዲመጣ ኪነጥበብ ከመቀስቀስ ጀምሮ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ይታወቃል፤ በዚህ ዙሪያ የሀገራችን የኪነጥበብ ባለሙዎች ምን እየሰሩ ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፡- አንዱ ነገር ሁልጊዜ ማስተዋል ያለብን ኪነጥበብ ይቀሰቅሳል፤ የሚለው ቃሉ እራሱ ብዙ አይነት ትርጓሜ አለው። አንዱ ኪነጥበብ ምንድነው የሚለውን ካለማወቅ የሚመነጭ ነው። ኪነጥበብ ትውፊታዊ እና ዘመናዊ መልክ አለው፤ እናቶቻችን እና አባቶቻችን ሲያሳድጉን እራሱ በጥበብ ነው። እሹሩሩ ብለው እናቶች ልጆቻቸውን ለማስተኛት የሚጠቀሙበት ዜማ ጥበብ ነው። በዚህ ዜማ ውስጥ የሚያነሷቸው ቁምነገሮች ያንን ህጻን ሀገሩን እንዲወድ፤ እናት አባቱን እንዲያከብር፤ ሞራል እንዲኖረው የሚያደርጉ ናቸው። ከፍ ሲል የሚነገረው ተረት፣ አፈ-ታሪክ፣ ስነ-ቃል የምንለው ሁሉ የጥበብ አካል ነው።
ልጅ ሆነን ትዝ ይልሽ እንደሆነ እንቆቅልህ ምን አውቅልህ ብለሽ ይሄ ምንድነው ተብሎ ከተጠየቅሽ በኋላ አላውቅም ስትይ ሀገር ስጪኝ ነው የሚባለው። ኢትዮጵያን ሰጥቼሀለሁ ኢትዮጵያን አግኝቼ ምን አጥቼ ሁሉ በደጄ ሁሉ በእጄ እየተባለ በልጅነታችን በጨዋታ አስመስሎ የሚነገረን ሀገር ካለ ምንም ነገር እንደማናጣ፤ ሁሉ በእጃችን በደጃችን እንደሆነ እየተነገረን ነው ያደግነው። ኪነጥበብ አንደኛ ለሀገር መቆምን ያስተምራል። በልጅነቱ ያልተሰራውን ሰውዬ ዛሬ ተነስተሽ ሀገር ተወሯል ብለሽ የምትቀሰቅሽው እሱም የሚቀሰቀስበት ሁኔታ የለም። የሚቀሰቀሰው በውስጥሽ ያለ ነገር ትንሽ አርምሞ ወስዶ ወይም ተዳፍኖ የነበረ ነው። ግን ምንም ነገር ከሌለ ምኑ ነው የሚቀሰቀሰው፤ ምንም ነገር አይኖርም። ስለዚህ የሚቀሰቀሰውንም ነገር መጀመሪያ የምትፈጥረው ኪነ-ጥበብ ናት።
ኢትዮጵያ ምንድናት የሚለውን በውስጥሽ የምታሳድረው እራሱ በተረት በእንቆቅልሽ በአፈ-ታሪክ በሙዚቃ በዳንስ በሰርግ ዝግጅት በሀዘን ላይ ኪነ-ጥበብ ናት። በብዙ ባህሎች ጀግና ሲሞት ለቅሶው እራሱ ይለያል። አንድ ህጻን ልጅ የተከበረ ሰው ሀዘንን ሲመለከት የሀገር ፍቅር ውስጡ እንዲያድግ ያደርጋል። ከቀማኛው ከሌላው ሰው የበለጠ ይሄ ጀግና ሲከበር ልጆች እያዩ ነው የሚያድጉት። ኪነ-ጥበብ ስራው በዛ ይጀምራል፤ ከዛ በኋላ ትውፊታዊ የሆነውን ዘመናዊ ሙዚቃዎችን በማቀናበር ግጥሞችን፣ ልቦለዶችን እና ትያትሮችን በመጻፍ ይታያል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ ኪነጥበብ በተለይ ከሁለተኛው የጣልያን ወረራ ጀምሮ ጎልቶ ይወጣል። ዛሬ ሀገር ፍቅር ቲያትር የሚባለው ያኔ ሀገር ፍቅር ማህበር በማለት እንደ መኮንን እንዳልካቸው ያሉ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ለጣልያን መቃወሚያ ብለው ያቋቋሙት በዛ ወቅት ነው። ሚኒሊክ አደባባይ አካባቢ ሰዎችን እየሰበሰቡ፤ ጣልያን ምን ሊያደርግ እንደሚችል፤ ነጻነትን ማጣት ምን እንደሆነ፤ ነጻነትን ማግኘት ምን እንደሆነ ለህዝቡ ዲስኩር እና አዝማሪዎችና የሙዚቃ ባለሙያዎች ትርኢት በማሳየት ህዝቡ ተነሳስቶ የመጣውን ጠላት እንዲቋቋም ሲሰሩ ነበር። በዚህ ጣልያን የተወሰኑ አዝማሪዎችን በስቅላት ቀጥቷል። በጊዜው እንደእናንተ አይነት ሚድያ የለም፤ የያኔው ሚድያ አዝማሪዎች ናቸው። ከህዝቡ ወደ መሪዎች፤ ከመሪዎች ወደ ህዝቡ፤ አዝማሪ ምን አለ? እረኛ ምን አለ? ተብሎ መጠየቁ ኪነጥበብ እንደሚድያ ያገለግል እንደነበረ ያሳያል። እና ከዛ ጀምረሽ ታላላቆቹን ጸሀፌ ተውኔቶች እነ መንግስቱ ለማ፣ ጸጋዬ ገብረመድህን በልዩ ልዩ ዘመን ቴዎድሮስን ታሪካዊ የሆኑ ነገስታት እና ለሀገር ክብር የቆሙ ጀግኖችን እንደገጸ-ባህሪ እያደረጉ የሰሩባቸው ስራዎችን ማስታወስ ይቻላል። በኋላ ላይ በፊልም ብትሄጂ እነ ፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ ያሉ አድዋን የመሳሰሉ ታላላቅ ፊልሞችን የሰሩ በሙዚቃ ብትሄጂ ከጥንት እስከዛሬ እነ ጥላሁን ገሰሰ መሀሙድ አህመድ፣ እነ ታምራት ሞላ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ እነ ሂሩት በቀለ ዘመን የማይሽራቸው ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉ ሀገር ለመጠበቅ የሚያስችሉ ትልልቅ ስራዎች ተሰርተዋል።
የኪነጥበብ ወረቶቻችን ትውፊታዊውም ዘመናዊውም በጣም ብዙ የሰራ ነው። አሁንም እንደዛው ነው፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ መልኩ አይቀየርም። የኪነጥበብ ሰውም እንደዚሁ ነው፤ ባለፉት ፈተና በነበረ ጊዜያት እንደድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ያሉ ድምጻዊያን ብዙ ነገር ሰርተዋል። አሁንም ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ሲባል፤ መጀመሪያ እንዴት ሆኖ ብለው የተነሱት እነዚህ ከያኒያን ናቸው። አሁንም በብዙ መስክ እና ሁኔታ ኢትዮጵያን ለመጠበቅ ህብረቷን እና ተስፋዋን ከፍ አርጎ ለመያዝ እየሰሩ ያሉ ታላላቅ ከያኒያን አሉ።
አዲስ ዘመን፡- ስለአድዋ አለም የመሰከረልን ጀግንነት እስካሁን በሀገራችን በዘፈን እና አንተ እንደጠቀስከው ፕሮፌሰር ሀይሌ ገሪማ በዶክመንተሪ ሰርተውት ለጂጂ አድዋ ዘፈን መነሻ ቢሆንም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አላየውም፤ አሁን በየቦታው የሚፈጸሙ የጀግንነት ጀብዱዎች በቀጣይ ለትውልድ እንዲተላለፉ ምን ሊደረግ ይገባል?
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፡- እንግዲህ ቅድም እንዳልኩሽ ኪነ-ጥበብ የሀገርን ምስል እና ትዝታ ይሰራል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ የሚለው የጥላሁን ሙዚቃ ባይኖር እንዴት አርገን አሁን ያለንን ኢትዮጵያ ይዘን የበፊቱንም አስታውሰን ወደፊት እንነሳ እንደነበር ለማወቅ በጣም ያስቸግራል። ይሄ ትልቅ አቅም ነው የፈጠረልን እና መሰራቱ ትልቅ ጥቅም ነው ያለው። የፊልሞቻችንን ሁኔታ ስናነሳ ፊልም ለመስራት እና ለማውጣት ብዙ አቅም ይጠይቃል። አድዋን ፕሮፌሰር ሀይሌ በዘጋቢ ፊልም አይነት ነው የሰራው፤ በፊቸር ፊልም አርጎ ለመስራት ብዙ ይፈልጋል። በህይወቱ ብዙ ይመኛል፤ ግን እንደ አድዋ ያሉ ታሪኮችን በፊልም ለመስራት ከባድ መዋእለ ንዋይ ይጠይቃል። ትልልቅ ሀገራዊ ፊልም የሚሰራበት ኢንዶውመንት ፈንድ አይነት አዘጋጅቶ እንደ እነ ፕሮፌሰር ሀይሌ አይነት ሰዎች ታሪካዊ ፊልሞች የሚሰሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ተገቢ ይመስለኛል። እስከዛው ግን እነ ጋሽ ጸጋዬ እንዳረጉት፤ በኋላም እነ ጌትነት እንየው እና እነ መልካሙ ዘሪሁን እንደቀጠሉበት ታሪካዊ ተውኔት የሆኑ ስራዎችን መስራት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ድልን በማብሰር ሂደት የኪነጥበብ ድርሻ ምንድነው?
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፡- ኪነጥበብማ የሌለበት የድል ብስራት የለም። ድል ሲበሰር የመጀመሪያው የእልልታው ዜማ እራሱ ኪነጥበብ ነው። ቀደም ሲል በጎንደር አካባቢ የነበረ የአዳኞች ልማድ አለ። አንበሳ የሚያድን ሰው ከጓደኞቹ ጋር ጫካ ሆኖ ጠብቆ ተናንቆ አንበሳ ሲገድል፤ ጎፈሩን ያወጣና ይለብሰዋል። ጓደኞቹ እዛው ቦታ ላይ ሌሊቱን ጥለውት ይጠፋሉ፤ ይሄ ጀግና አንበሳ መግደሉን ለቤተሰቡ መንገር አለባቸው። ይሄ ድል መበሰር ስላለበት ሄደው አንበሳ ገድሏል ብለው ይነግራሉ። አንበሳውን የገደለው ድሉን የሚያበስርበት ግጥም ሲያጠና ያድራል። የሚፎክረውን ፉከራ ሌሊቱን ሙሉ አንበሳው ላይ ሆኖ ግጥም ያስባል። ግጥሙ ፉከራ የሚሆን ነው፤ እንዴት አንበሳውን እንደገደለ፤ ስለ አስተዳደጉ ስለ ቤተሰብ ሁኔታው በሙሉ ሲያስብ ያድርና የድል ብስራቱን ለማሰማት ሲሄድ ያንን ፉከራ ነው የሚያቀርበው። ይሄ አንዱን ምሳሌ አነሳሁ እንጂ በመላው ኢትዮጵያ በምትሄጂበት ጊዜ ድል የሚበሰረው በተመሳሳይ ሁኔታ ነው።
በተለይ በባህላዊ መንገድ ፉከራ ለማነሳሳት እና ድልን ለማብሰር ያገለግላል። ለምሳሌ ጉሮ ወሸባዬ ጉሮ ወሸባ ጉሮ ወሸባዬ ወሸባ ታጋይ ድል አርጎ ሲገባ። አሁን ይሄ አሸንፎ ለሚመጣው እንዴት ያለ ከፍ ያለ ሞራል ይሰጠዋል። ምክንያቱም ጥበብ የስሜት ህቅታ ናት፤ ለምሳሌ በጣም ስታዝኚ እንዴት አርገሽ ትገልጽዋለሽ? ታለቅሻለሽ፤ ግን የለቅሶሽ ሁኔታ የሚወጣልሽ፤ ሙሾ በማውረድ ያንቺን ሀዘን መናገር የሚችል ሰው ሲናገር በውስጥሽ ያለው ሀዘን በሙሉ ተፍቆ ይወጣል። ደስታም ቢሆን እንደዚሁ ነው፤ ደስታም በጣም በጥሩ ግጥም ሲነገርልሽ ይወጣልሻል። ያለዛ ከሆድሽ አይወጣም፤ ጥበብ ስሜትን ማውጫ ነው።
ድል ቀላል ነገር አይደለም፤ ፈተና መውደቅ መነሳት አለው። ጓደኛን ቤተሰብን ማጣት ሌላም የሚታይ ብዙ ጉዳት አለው። የህልውና ዘመቻም ይሄንን ሁሉ ነገር ታይበታለሽ። የግልም ቢሆን ቤተሰብን ማስተዳደር ትልቅ ትግል ነው። ልጅሽን አሳድገሽ የመጨረሻው ቀን ከዩኒቨርሲቲ ሲመረቅ ወይም ስትድሪው የሚታየው ነገር በጥበብ ያ ድል ነው። የአንድ ግለሰብ ድል ነው፤ የመውጣት የመውረዱ ትርጉም ነው። ይሄንን በምንድነው የምትገልጭው? በጥበብ ነው፤ በግጥም ወይ አንድ ድምጻዊ ዘፈን ሲያቀርብ አብረሽ እስክስ ብለሽ ካልወጣልሽ በስተቀር ከባድ ነው። ጥበብ የደስታም የድልም መፍጠሪያ ናት፤ አነሳስታ ድልም ሲገኝ ደግሞ የድል አብሳሪ እንደገና ደግሞ የስሜቱ መግለጫ ናት።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከተጋረጠባት ችግር ለመውጣት ከኪነጥበብ ባለሙያዎች ምን ይጠበቃል?
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፡- ኢትዮጵያዊ ህዝቡ እራሱ ከያኒ ነው፤ እናቶቻችን አባቶቻችን ገጣሚ ናቸው። ከዚህ ውስጥ የወጣ ከያኒ እውነት ከያኒ ከሆነ የህብረተሰቡን ስሜት ነው የሚያንጸባርቀው። የህብረተሰቡ ስሜት እንደምታይው ነው፤ ኢትዮጵያ በፍጹም በዚህ ዘመን አትፈርስም፤ የሚል ነው። ኢትዮጵያውያን ባጠቃላይ ስሜታቸው ‹እንዴት ሆኖ ሀገራችን በእኛ ጊዜ እንደዚህ ትሆናለች? አይሆንም› ነው። ስለዚህ ይሄንን ስሜት ደግሞ ማንም ሰው አይደለም የሚነግረው፤ ከያኒው ቀድሞ ነው የሚረዳው። በዚህ ምክንያት ነው በጣም ብዙ ስራዎች ስለኢትዮጵያ የሚሰሩት።
አሁን እንኳን በዚህ 20 ቀን ውስጥ ከ100 በላይ የሚሆኑ አርቲስቶች ተሰባስበው አንድ ሙሉ አልበም አሳትመዋል። ስለኢትዮጵያ የሚል 28 አዳዲስ ሙዚቃዎች አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው ተሰርተው የወጡት። ከያኒያን በየቦታው እየሄዱ ህብረተሰቡን እያነቃቁ፤ በግንባር ሄደው የኢትዮጵያ ወታደር ልቡ የሞላ እንዲሆን፤ ሀገሩን መጠበቅ ትልቅ ግብ መሆኑን ለማሳየት እና አብሮ ለመቆም የሚሰሩትን እያየሽ ነው። እኔ መቼም ተነስቼ ለአንድ የኢትዮጵያ ከያኒ ይሄ ነው የሚጠበቅብህ አልለውም። የሚጠበቅበትን እያደረገ ነው፤ ድሮም፤ ዛሬም እያደረገ ነው፤ ወደፊትም እንደሚያደርገው በጣም እርግጠኛ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ሕወሓት በግምባር ጦርነት ላይ ተሸንፎ እያለ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ከዚህ በተቃራኒው መረጃ ሲያሰራጭና ሽብር ሲነዛ ይታያል፤ ይህንን ለመቀልበስ እና የመከላከያ ሰራዊቱ የሚያገኛቸውን ድሎች የሚያበስርበት መንገድ እንዴት ሊሆን ይገባል?
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፡- አባቶቻችን እውነት እና ንጋት እያደር ይጠራል ይላሉ። እውነት የያዘ ህዝብ ደግሞ ሁልግዜም እውነቱ ይወጣለታል። ያድር ይመሽ ይሆናል፤ ግን መሽቶ አይቀርም፤ ይነጋል። ጸሀይ በሚወጣ ጊዜ ይታወቃል፤ እዚህ ላይ ብዙ አባባሎች አሉ። ሰጎኗ ጭንቅላቷን አሸዋ ውስጥ ደብቃ ሰው አያየኝም አለች፤ የእሷ ጭንቅላት ነው እንጂ የተደበቀው የቀረው አካሏን በሙሉ ሰው ያየዋል። ስለዚህ ኢትዮጵያን ነካክተው አፈርሳለሁ ብለው፤ የሰዎችን መብት ገፈው እና ሂወት ቀጥፈው፤ ይሄ ሳይበቃቸው የኢትዮጵያን ሀቅ ለመደበቅ የሚፈልጉት እነሱ አሸዋ ውስጥ እንደገባ ሰጎን አንገታቸውን ቀብረዋል፤ የኢትዮጵያም የአለምም ህዝብ ይሄን ይመለከታል።
በነገራችን ላይ ሰዎች የአሁኑን የሀገራችንን ሁኔታ የፌደራል መንግስት ከአንድ አሸባሪ አካል ጋር የሚያደርገው ጦርነት አድርገው ያስቡታል። ግን እንደሱ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን እና ጸረ-ኢትዮጵያዊያን የተፋጠጡበት ነው። ሀገር አትፈርስም፤ ኢትዮጵያን ከችግር እናወጣለን ብለው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን በአንድ ጎራ፤ ኢትዮጵያን ከጥንት ከመሰረቱ የሚጠሏት እና ትልቅ እንዳትሆን የሚፈልጉት እና ለዚህም የሚሰሩት ሀይሎች በሌላ ጎራ ተሰባስበው የሚፈትኑን ወቅት ነው። ይሄው ተመልከቺ በየአካባቢያችን ማደሪያ የሌላቸው እና ጎዳና ላይ የሚተኙ እርጥባን የሚፈልጉ አሉ፤ ከዚህ ህይወት ለመውጣት ብለን እንደህዳሴ ግድብ ሰርተን ትልቅ ለመሆን ስንፍጨረጨር የሚመጣውን ፈተና ተመልከቺው። ከግራ ከቀኝ ነው ፈተናው የሚመጣብን።
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተለይ በትግራይ ተነስቶ አሁን በተለያየ የኢትዮጵያ ክልል ግጭቱን ለማስፋፋት የሚፈለገው፤ የቀኝ ገዢዎች ኢትዮጵያን በታትኖ የማዳከም ሀሳብ አንዱ ማሳያ ነው። የኢትዮጵያ ፈተና እንግዲህ ኢትዮጵያውያን ከጸረ-ኢትዮጵያ ጋር የተሰለፉበት ነው። የሚደረገውን ጫና በአጠቃላይ ስትሰበስቢው በውስጥም በውጪም ያለው ኢትዮጵያን የሚጠላው ሀይል በሙሉ በአንድ ላይ ተረባርበው ሀገራችንን እየፈተኗት ነው። በዚህ መሀል የሚነገር የውሸት እና ማታለል በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጋለጥ ነው። እውነት ያልያዘ ደግሞ ሁልጊዜም የሚሸነፍ በመሆኑ በአጭር ጊዜ የሚጠፋ ነው።
ነገር ግን ሁኔታዎችን ዝም ብለን አይናችንን ከፍተን እያየን ይጠፋሉ ብለን መሞኘትም የለብንም። በውጪም በሀገር ውስጥም ተሰባስበው የሚያደርጉትን እያየን የምናልፈው ሳይሆን ነቃ ብለን እያንዳንዱን ነገር እየተከታተልን እውነታችንን ማውጣት እና ሀቃችንን ለኢትዮጵያ ጠላትም ሆነ ወዳጅ በግልጽ እንዲረዱት ማድረግ ያስፈልጋል። እውነት አድሮ የሚወጣ ቢሆንም፤ ይሄ ዘመን ለጊዜው የማደናገር እና የማወናበድ አቅም ይኖረዋል። በአሁኑ ጊዜ መረጃ በፍጥነት ነው የሚሰራጨው፤ በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ያልተጠበቀ ችግር አላስፈላጊ ክፍያ እንዳያስከፍለን ብዙ ማየት አለብን። ዜጎቻችን እንዳይጎዱ ማድረግ ያስፈልጋል። መጀመሪያ በግጭቱ አካባቢ በትግራይ ያለው ህዝብ ከፍተኛ ጉዳት ይደርስበታል። ለህዝብ እውነተኛው መንገድ ባለመነገሩ እና የተወሰኑ ሰዎች የተሳሳተ መረጃ ስለሚያገኙ ባለማወቅ የተሳሳተ ወገን ይደግፋሉ። ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኝ መሰራት አለበት። ኢትዮጵያዊነት ከሁሉም የሚሻል ተስፋ ያለው መሆኑን፤ የሚታዩት ችግሮች ሊቀረፉ የሚችሉት በመወያየት፣ በመነጋገር፣ መረጃ በመለዋወጥ እውነትን በመያዝ እንጂ ከዚህ ውጪ በሆኑ ነገሮች ሀገራችንን ወደፊት መውሰድ እንደማይቻል መግባባት አለብን።
የሚገርምሽ ህብረት ያላቸው ትልልቅ ሀገራት ህዝቦች፤ አንድ ስለሆኑ ሩቅ ያለነውን ሰዎች ይሄን አርጉ ብለው ያዙናል። ህብረት ሀይል ሆኖአቸው ነው፤ እኛ ደግሞ ሀገራችን ላይ ቁጭ ብለን ያለንን ህብረት እያላላን፤ እንዴት ሆነን ነው ታላቅ የምንሆነው? መረጃ አንዱ የግጭቱ ማስፋፊያ መንገድ ነው። መረጃ የሚመጣበት የሚተነተንበት እና ለህዝብ የሚደርስበት መንገድ ብዙ ፈተና ያለበት ነው። ይሄንንም መወጣት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት አሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከዳር በአንድነት ተነስተዋል፤ ይሄንን የአንድነት ሀይል ከድሉ በኋላ ኢትዮጵያን በማሻገር ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል፤ ይህንን ሀይልስ እንዴት አስተባብሮ ወደፊት መሄድ ይቻላል?
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፡- ትልቁ ነገር ይሄ ነው። ኢትዮጵያ ተዳከመች፤ አለቀላት በምትባል ጊዜ ባልታሰበ መልኩ የምትነሳ ሀገር ናት። በታሪክም ላይ ትልልቆቹ ድሎቻችን በተዳከምንበት ጊዜ በአስደናቂ መልኩ ተባብረን ያለፍናቸው ናቸው። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን እናፈርሳለን የሚሉ ሰዎች ከውስጥም ከውጪም ተባብረው የቆሙበት ጊዜ ነው። ይሄ ነገር ሲያጋጥመን ብዙዎቻችን አዝነናል፤ ምክንያቱም ሁሉም ነገር እያየን የሆነ ነው። ለምሳሌ የጦርነት ጉሰማ ሲሰማ፤ የተለያየ ሰልፍ ሲደረግ፤ ከዚህም የተለያየ ሽማግሌ ሲላክ የኢትዮጵያ ህዝብ ጸጥ ብሎ ተመልክቷል፤ አይቷል። ይሄ ነገር ወደመጥፎ መንገድ ሊሄድ ነው ብሎ ሲያስብ፤ ጸሎት እና ምህላ አድርጓል። ፈጣሪውን ለምኗል ግን የኢትዮጵያ አምላክ አላማ ነበረው። በዚህ ጥቃት የተነሳ፤ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ያሉት ሰይጣናዊ ሀሳብ እንዲመክን እና መላው ኢትዮጵያ አንድ እንዲሆን አድርጓል።
ኢትዮጵያውያን ህብረትን አጠናክሮ አንድ ላይ መቆም ጥቅም እንዳለው እያዩ ያለበት ጊዜ ነው። ይሄ ግጭት ለረዥም ጊዜ የሚቆይ አይደለም፤ መቋጫ ያገኛል፤ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች። መጪው ዘመን የኢትዮጵያ አሸናፊነት የሚረጋገጥበት እና ኢትዮጵያ አብሮነቷ ተረጋግጦ የሚሄድበት ዘመን እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም።
አዲስ ዘመን፡- አንተን የምናውቅህ በኪነ-ጥበብ ባለሙያነትህ እና በመምህርነትህ ነው፤ በአዲስ ዓመት በአዲስ በሚከፈተው የአዲስ አበባ ምክር ቤት የህዝብን አደራ ተቀብለህ ትገባለህ። እንደ አንተ አይነት ሰዎች ወደውሳኔ ሰጭነት ቦታ መምጣታችሁ ለኪነጥበብ ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል?
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፡- የኪነጥበብ ባለሙያም መምህርም መሆን ስለሀገር ብዙ ነገር እንድታውቂ ያደርጋል። ሀገርሽን ሌላው ከሚያይበት በተጨማሪ አይን ማየት ያስችልሻል። ከያኒ ልዩ አይን አለው ይባላል። ከያኒያን ክፉ ነገር አይወዱም፤ ውበትን፣ መልካምነትን፣ የመሳሰሉትን መልካም እሴቶች ነው የሚወዱት። መምህርም በመጪው ትውልድ ላይ የሚሰራ እና ልጆችን በእውቀት ኮትኩቶ የሚያሳድግ ነው። በዚህ በሁለቱ ሞያ ውስጥ ያለፍኩ መሆኑ፤ በአሁኑ ዘመን የመጣው የተስፋ የህብረት የፍቅር የአንድነት ሀሳብ የሚገዛኝ ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ያስተማረችኝ፣ ያሳደገችኝ፣ የወላጆቼ የጎረቤቶቼ ያደኩበት ትዝታ ይሄ ሁሉ ያለበት የተዳርኩበት ልጆቼን የማሳድግበት ክብር እና እውቅና ያገኘሁበት ሀገር ማገልገል ትልቅ ክብር ነው። እስካሁን ብዙ ተምሬባታለሁ፤ እውቅና አግኝቼባታለሁ፤ ተከብሬባታለሁ፤ እኔ ደግሞ አሁን ለእሷ ይሄንን የሰጠችኝን ነገር ለሀገሬ ለኢትዮጵያ መልሼ መስጠት አለብኝ ብዬ የወሰድኩበት ነው። እስከዛሬም እንግዲህ በማስተማሩ በጥበቡ በመሳሰለው ነገር አስተዋጽኦ አለ። ግን ሀገርን ደግሞ ማገልገል ትልቁ አስተዋጽኦ ነው። አዲስ አበባን የምታክል ትልቅ ታሪክ ያላት የአፍሪካ ዋና መዲና ህዝቧ ምንድነው የሚያስበው? ምንድነው የሚጨንቀው? ምንድነው የሚያስፈልገው? የሚለውን ለመናገር እድል አግኝቻለሁ። የተወዳደርኩበትም አካባቢ ሰው ወክለን ብሎ እድል ሰቶኛል። ያለኝን ልምድ ተጠቅሜ ከህዝቡ ጋር እየተማከርኩ የምሰራበትን እድል አግኝቻለሁ።
ብቻ መስራት አይቻልም፤ በተለይ አብረው የተወዳደሩ ፓርቲዎች አብረው መስራት አለባቸው። ምክንያቱም ለሀገር ነው፤ እኔ ምክርቤት የምቀመጥባት ወንበር እኔ የተወዳደርኩበት አካባቢ ያለውን ህዝብ በሙሉ የምትወክል ናት። እንጂ አንዱን ፓርቲ ብቻ የምትወክል አይደለችም። ስለዚህ የዛን ሁሉ ህዝብ ፍላጎት መሸከም ያስፈልጋል፤ እኔ ደግሞ ለዛ የማስበው ከያኒ ወገንተኝነት የለውም ለሁሉም የመቆም ተፈጥሮም ልምድም አለው። ይሄን ተጠቅሜ ከመረጡኝም ካልመረጡኝም ሰዎች ጋር አብሮ ለመስራት አስባለሁ።
በሞያዬ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ መሰራት ያለባቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ብዘረዝርልሽ ረዥም ጊዜ የሚወስዱ በመሰረተ ልማት እንኳን የተውኔት እና የኮንሰርት ማሳያ ቦታዎች እጥረት አለ። የሰው ሀብት ልማት ላይ አሁን ዩኒቨርሲቲዎች ብዙ ተከፍተዋል፤ ግን እነዛ ልጆች ምን አይነት ትምህርት ነው የሚማሩት? ወተው ምን መስራት አለባቸው? የሚለው እራሱን የቻለ ትልቅ ሀላፊነት ነው። በሌላ አንጻር ደግሞ በህግ ብዙ ክፍተቶች አሉ፤ የፊልም የቲያትር ባለሙያዎች ብዙ የሚያማርሩባቸው የህግ ክፍተቶች መሞላት አለባቸው። ከህዝቡ ጋር ብዙ የመገናኘት ስራዎች መሰራት አለባቸው። ከያኒያን መንገዱ ሊቀናቸው ይገባል። የስራቸው ሁኔታ የተቃና እንዲሆን ይገባል። ምንም እንኳን የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ምረጡኝ ብዬ ባልገባም፤ እኔ በሙያዬ ያለውንም ሀሳብ ለመስጠት ባጠቃላይም ለመረጠኝ ህዝብ አንደበት ለመሆን እሞክራለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለአዲሱ አመት የምታስተላልፈው ምኞት ካለ እድሉን ልስጥህ?
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፡- እኔ የምመኘው መጪው አዲስ አመት በታሪክ ቀኝ የምንቆምበት፤ በጨለማው ኢትዮጵያን በሚያጠፋው ቦታ፤ ወደፊት ሲታወስ አይ ያ መጥፎ ዘመን የምንባልበት እንዳይሆን እግዚአብሄር እንዲረዳን እመኛለሁ። ለታሪክ መጥፎነት ሳይሆን ለበጎ ታሪክ፤ ኢትዮጵያውያን እኮ የገጠማቸውን ፈተና በታላቅ ህብረት እና ተስፋ በዚህ ጊዜ ተወጥተውታል እንድንባል እንዲያረገን እመኛለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ እና በአንባቢያን ስም አመሰግናለሁ!
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ፡- እኔም አመሰግናለሁ!
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2013 ዓ. ም