የዓለም ታላቁ ስፖርታዊ ውድድር ኦሊም ፒክ፤ በየወቅቱ አዳዲስ የውድድር ዓይነቶችን በማካተት ይታወቃል። ፓሪስ በታሪኳ ለሶስተኛ ጊዜ እአአ በ2024 በምታስተናግደው ኦሊምፒክ ላይም አዳዲስ ውድድሮች የሚጨመሩ መሆኑ ታውቋል። የመጀመሪያው በማራቶን ስፖርት ላይ መሳተፍ የሚፈልግ ማንኛውንም ሰው ማካተት ሲሆን፤ «ብሬክ» በመባል የሚታወቀው ዳንስ፣ በ«ስኬት ቦርድ» መንሸራተት፣ በውሃ ላይ መንሳፈፍ እንዲሁም ተራራ መውጣት የኦሊምፒኩ የውድድር ዓይነቶች ናቸው።
ከአትሌቲክስ ስፖርቶች ረጅሙን ርቀት የሚሸፍን ውድድር እንደመሆኑ ከፍተኛ ጽናትና ጥንካሬን ይጠይቃል፤ ማራቶን። 42ኪሎ ሜትር መሸፈኑ ከባድ ቢያደርገውም በተለያዩ የዓለም ከተሞች በየሳምንቱ የሚካሄድ የውድድር ዓይነት በመሆኑ ብዙዎች ይሳተፉበታል። በተለይ በዚህ ርቀት እንደ ኦሊምፒክ ባሉ የውድድር መድረኮች ተሳትፎ የሜዳሊያ ባለቤት መሆን ከፍተኛ ክብርን ያስገኛል። በዚህም ምክንያት በኦሊምፒክ የርቀቱ ተካፋይ የሚሆኑት፤ ታዋቂና ልምድ ያላቸው አትሌቶች ናቸው።
በፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ግን የትኛውም መሮጥ የሚፈልግ ሰው ተካፋይ መሆን እንደሚችል የዓለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል። ይህንን ዜና ተከትሎም የኦሊምፒኩን አስተባባሪ ኮሚቴ በፕሬዚዳንነት የሚመሩት ቶኒ ኢስታንጉዌት «ውድድሩን ልዩ ለማድረግ አንድ እርምጃ ተራምደናል። በርካቶችን የሚያሳትፉ የተለያዩ ውድድሮችም እንዲካተቱ አድርገናል። ተሳ ታፊዎች በየትኛውም ደረጃ ላይ ቢገኙም በኦሊምፒኩ የተለየ ልምድ እንዲኖራቸው ማድረግ እንፈልጋለን» ሲሉ ገልጸዋል።
በአሜሪካዋ የኒው ዮርክ ከተማ እአአ ከ1970 እንደተጀመረ የሚነገረው «ብሬክ» የተባለው የዳንስ ዓይነት፤ ባሳለፍነው ዓመት በቦነስ አይረስ በተካሄደው የወጣቶች ኦሊምፒክ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ አንድ የውድድር ዓይነት ተካሂዶ ነበር። ይህንን ተከትሎም በዋናው የኦሊምፒክ ውድድር ላይም ለማካተት መወሰኑን ፕሬዚዳንቱ ይጠቁማሉ።
ሊቀመንበሩ አክለውም ከዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንዲሁም የስፖርት ማህበራት ጋር በመስራት ላይ እንደሚገኙና ልምዱ በሌሎች ስፖርቶችም እንዲንጸባረቅ እንደሚሹም ገልጸ ዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011
ብርሃን ፈይሳ __