በየትኛውም አገር የሚኖር ሰው ‹‹ጀግና›› የሚ ለው ቃል ሲሰማ ቅድሚያ የሚመጣለት አገሩን ከወራሪ ወይም ከጠላት ያስጣለውን ሰው ነው። ቃሉ በራሱ ልብን የሚሞላና የአይበገሬነት ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። በአገራችንም ‹‹ ጀግና›› የሚለው ቃል የጥንካሬና የአሸናፊነት መንፈስ እንዲላብስ ተደርጎ በሁሉም ሰው ውስጥ እንዲቀመጥ ተደርጎ ተቀርጿል።
ጀግና ምን ማለት ነው? ለእኔ ጀግና ማለት በተሰማራበት መስክ በታማኝነት አገሩንና ህዝቡን የሚያገለግል ነው። አገርን ከወራሪ ከጠላት መከላከል የቻለ ለአገሩና ለህዝቡ አሊያም ለብዙሃኑ ህይወቱን የሰጠ እሱ ጀግና ነው፤ በግብርናው ዘርፍ ተሰማርቶ አገርንና ህዝብ በምርት እንዲትረፈረፍ ያደረገ፣ በመንግሥት ሥራ ተሰማርቶ ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ያገለገለ እሱ ጀግና ነው፤ በንግድ ተሰማርቶ የተጣለበትን ግብርና ታክስ በአግባብ የሚከፍል እሱ ጀግና ነው፤ በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ተሰማርቶ ህዝብን በቅንነት የሚያገለግል እሱ ጀግና ነው፤ ወዘተ…ብቻ ሁሉም በተሰማራበት አገርንና ህዝብና አገርን በቅንነት በታማኝነት የሚያገለግሉ ሁሉ ጀግኖች ናቸው።
አብዛኛው የአገራችን ሰው፣ ሆዱን ነገር ሲያምረው አልያም፣ ጥቃት ሲመረው፣ መጀመሪያ ማንጎራጎርን ይመርጣል። ከዚያ ነው ወደ ድርጊት ይገባል። ጀግና ሰው ወደ ድርጊቱ ከመግባቱ በፊት ከሚያንጎራጉራቸው ዜማዎች ውስጥ አንዱን እንመልከት።
ብችለው ብችለው – አንገቴ ደረሰ
እክ ብለው ወጣ – ደም እየለበሰ።
ኧረ ተው አንተ ሰው – አትለፍ በደጄ
እንደ ማታ መብራት – ትጠፋለህ በእጄ።
ኧረ ተው አንተ ሰው – መካር የለህም ወይ?
ምላጩን ከሳቡት – እርሳስ አይደለም ወይ?
ተው በሉት ያንን ሰው – ያን አመሉን ይተው፣
ደርሶ መወዘቱን – ሰው በጎላላቸው።
ሰው መግደል እንደ እግዜር …
ዱር መግባት እንደ አውሬ – መቼ ይቸግራል፣
ከጓደኛ ጋራ – መጫወት ይቀራል።
ካባቱ ባድማ – የተኛውን በሬ፣
ጎስጉሰው ጎስጉሰው – አደረጉት አውሬ …
ጀግንነት ሁሌም የሚገለፀው ጠንካር እና ከፍ ባለ ነገር ነው ። እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ጀግንነትን ብዙ ጊዜ በአንበሳ እንመስለዋለን። ኢትዮጵያዊነት ሁልጊዜ በአንበሳ ምልክት የሚወከለው የጀግንነትና የመሪነት ስሜት በውስጣችን በመኖሩ ነው ብዬ አምናለው። ቀደም ያሉ የጦርነትም ይሁን ሌሎች ታሪኮቻችንን መለስ ብለን ብንመለከት ጀግንነትን የምንገልፀው በቆራጥ አመራርነትና በልበ ጠንካራነት እንዲሁም በአልደፈር ባይነታችን ነው።
በዚህም ብዙ አገር ያስጠሩ ጀግና መሪዎች ልናፈራ ችለናል። እዚህ ጋር መጠቀስ ያለበት ጀግንነት በመግደልና በማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የአገር አንድነትን አስጠብቆ መቆየት በራሱ ጀግና የሚያስብል ተግባር መሆኑን ነው።
ስለ ጀግንነት ስናነሳ የኢትዮጵያ ሰራዊት በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ዘመቻ ላይ ያከናወነውን የጀግንነት ተግባር እንጥቀስ። ሰሜን ኮሪያ በደቡብ ኮሪያ ላይ ባካሄደችው ወረራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባደረገው ጥሪ ኢትዮጵያ ‹ቃኘው ሻለቃ›› እየተባለ የሚጠራውን ሰራዊቷን ልካለች። በጦርነቱን ዓለምን ያስደነቀ የጀግንነት ተግባር ፈፅመዋል። በጦርነቱ ማብቂያ ከአሜሪካ ወገን ሆነው ከተዋጉት ሃያ አንድ ሀገራት መካከል ሁሉም በሰሜን ኮሪያ እጅ የወደቁ ምርኮኛ እስረኞች ሲኖሯቸው ኢትዮጵያ አንድም ምርኮኛ እስረኛ ያልነበራት ብቸኛ አገር ነበረች።
ጦርነቱ አብቅቶ የምርኮ ልውውጥ ሲደረግ ደቡብ ኮሪያ ስምንት ሺህ 343፣ አሜሪካ አራት ሺህ 714፣ እንግሊዝ 977፣ ቱርክ 244፣ አውስትራሊያ 26፣ ካናዳ 33፣ ፈረንሳይ 12፣ ግሪክ ሶስት፣ ኮሎምቢያ 28፣ ታይላንድ አምስት፣ ኔዘርላንድ ሶስት፣ ቤልጅየም አንድ ፣ ፊሊፒንስ 97፣ ደቡብ አፍሪካ ዘጠኝ፣ ኒውዚላንድ አንድ ፣ ኖርዌይ ሶስት ምርኮኛ ሲመለስላቸው ኢትዮጵያ ግን አንድም ሰው ያልተማረከባት ብቸኛ ሀገር ነበረች። ይህን የኮሪያ ዘማቾችን ወደር የለሽ ጀግንነት አዝማሪዎች ‹‹አይዞሽ አሞራ አይዞሽ ጭልፊት ቃኘው ሻለቃ አልፏል ከፊት›› በሚል በስንኝ እንዲወደሱ አድርጓል።
እንግሊዛዊው የጦርነት ታሪክ ጸሐፊ ጆን ኬጋን፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን እልኸኞች ናቸው። መማረክን አይቀበሉም። ያለ ድል ለመመለስ ፈጽሞ ፍላጎት የላቸውም። ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከፍ ብሎ ማየት የዘወትር ሕልማቸው ነው፤ ቃኘው ማለት ይህ ነው በቃ›› ሲል በማወደስ ጽፎላቸዋል። እንዲህ አይነት መሰል የጀግንነት ተግባራት በደቡብ ኮሪያ ብቻ ሳይሆን በኮንጎ፣ በቡሩንዲ፣ በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳንና በሱማሊያ ብቃት ላይ በተመሰረተ መልኩ ለዓለም ማሳየት የተቻለበት ሁኔታ አለ።
በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በህልውና ዘመቻ ላይ የምትገኝ እንደመሆኗ ሁሉም ከሽብርተኛው ቡድን ፕሮፓጋንዳ ተጠብቆ የተቃጣውን የውጭና የአገር ውስጥ አገር የማፍረስ ዘመቻ መመከት ጀግንነት ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ለአገር ዳር ድንበር የሚቆሙ ጀግና የአገር መከላከያ መፍጠር ተችሏል። ለዚህ መከላከያ ኃይል ደግሞ ቀደም ብለው የነበሩ ዳር ድንበር ያስጠበቁ አርበኞች እንደ ተምሳሌት ወስዶ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል። ለመከላከያ ሰራዊት ጀግና መሆን ከአያቶቹ የወረሰው የጀግንነት ደም ቢኖረውም በሚሰማራባቸው ግዳጆች ከህብረተሰቡ የሚያገኘው የሞራል ስንቅ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ አለው። ለዚህ ደግሞ የህልውና ዘመቻውን ማንሳት በቂ ነው።
በሽብርተኛው ህወሓት ቡድን መከላከያ ሰራዊት ላይ በተቃጣው ድንገተኛ ጥቃት ምክንያት የህወሓት የጥፋት ቡድንን ለማጥፋትና አገርን ሰላም ለማድረግ ሁሉም ወጣት አባቱን፣ የአያቱንና ቅድመ አያቱን ስም እየጠራ ወደ ጦር ግንባር እየተመመ ይገኛል። ይህ የሚያሳየው የጀግንነትና የአገር ዳር ድንበር ማስጠበቅ ሥራ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ የጀግንነት አስተሳሰብ መሆኑን ነው።
ወጣቱ አገርን አንድ የማድረግ አላማውን ሰንቆ በሚጓዝበት ወቅት የተቀረው ህዝብ የአገርን ልማትና እድገት በሚያፋጥኑ ተግባራት ላይ ተሰማርቶ የጀግንነት ተግባር ሊፈፅም ይገባል። ምክንያቱም ለአንድ አገር እድገት በወታደራዊው መስክ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የጀግንነት ተግባር የሚፈፅም ትውልድ ያስፈልጋል። ምክንያቱም የአገር ዳር ድንበር ከተጠበቀ በኋላ እድገት በሚያመጡ ሥራዎች ላይ የሚሳተፍ ጀግና ትውልድ ስለሚያስፈልግ ነው።
ሌላው የዚህ ትውልድ ጀግንነት እየታየበት ያለው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ነው። የግድቡ መገንባት ከአገሪቱ ከሚያመጣው ፋይዳ አንፃር ሁሉም ህብረተሰብ ያለውን በማዋጣት አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ አድርጓል። በዚህ ግድብ ዙሪያ ከግብፅና ከሱዳን በተጨማሪ ሌሎች የውጭ አገራት ተፅዕኖ ፈጥረው ለማስቆም ጥረት ቢያደርጉም በጀግንነት ልቡ የተሰራው የኢትዮጵያ ህዝብና አመራር ግንባታውን እያቀላጠፈ ይገኛል። ለአገር ልማትና እድገት በጀግንነት አስተሳሰብ እየተሳተፈ የሚገኘው ህዝብ የግድቡን መጠናቀቅ በጉጉት እየጠበቀና የሚጠበቅበትን እያዋጣ ይገኛል።
ያስተሳሰብ ጀግና ሲባል ደግሞ ሰው ባመነበት ነገር ላይ ገትሮ ሲይዝ ለማለት ነው። ባጭሩ ያስተሳሰብ ጀግና ማለት አንድ ሰው ያሰበውን ለማሳካት በቀጣይነት የሚያደርገው ሃሳባዊ ትግልና ጥልቅ ፍላጎት ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው በሃሳቡ ከጊዜና ከሁኔታ ጋር ፊት አድርጎ ይሄዳል እንጂ አይቀያየርም። መሰረታዊ ሃሳብና እምነቱ አንድ አይነት ነው። ምክንያቱም አስፈላጊ ነኝ ብሎ ያስባል። በራሱ ይተማመናል። ማንኛውም ሰው ከተለማመደ በራሱ መተማመን ይችላል።
ይኸ ጀግናዊ ጥልቅ ፍላጎትና አስተሳሰብ ለመልካም ወይም ለመጥፎ አላማ ሊሆን ይችላል። እኔ ግን እዚህ ለማስረዳት የሚመቸኝ ስለ ጥሩ አላማ አስተሳሰብ ነው። በሰፊው እንደምናውቀው፤ ወኔ ወይም ጀግና ማለት ጦር ሜዳ ሄዶ ጀብዱ መስራት ብቻ አይደለም። ተናዶ ጠረጴዛ መምታት አይደለም። ሰዎችን ልክ ልካቸውን ነግሮ ቲፎዞ ለማግኘትና ለጊዜው ለማሸነፍ አይደለም።
አሁን አንዳንድ ተጨባጭ ነገሮችን ልጥቀስ። ለምሳሌ እንጀራ ለመብላት ሥራ መስራት እንዳለብን ሁላችንም እናውቃለን። ሥራው ግን በጥራት መሰራት አለበት። ሥራ ማለት በአካል የሚታየው ውጤት ብቻ አይደለም። ሥራውን ስንሰራ ሶስት አብረው የሚሄዱ ሃሳቦች አሉ። የመጀመሪያው ሥራውን ለመስራት የምንቀይሰው እቅዳዊ አስተሳሰብ ነው። ሁለተኛው ሥራውን ስንሰራ በሥራው ሲደት ውስጥ የምንሰጠው ትኩረታዊ አስተሳሰብ ነው። ሶስተኛው ሥራው ካለቀ በኋላ የሚሰጠን ውጤታዊ አስተሳሰብ ነው። ሶስተኛው ደረጃ ላይ የምናገኘው እርካታ ወይም ክለሳ ሊሆን ይችላል። ባጭሩ አባባል የትኛውም የሥራ ሂደትና ፍጻሜ ላይ፤ ሃሳብ ከፍተኛ ቦታ አለው። ቀለም ለመቀባት እንኳን ቀለምና ቁሳቁስ ለመግዛት ማሰብ አለብን። ደረጃውን ጠብቆ እንዲያምር ተጠንቅቀን እያሰብን መቀባት አለብን። ስንጨርስ ደግሞ ውጤቱ ላይ እያሰብን እንኖርበታለን።
ብዙ ነገሮች ቢያንስ ሶስት ደረጃ አያጣቸውም። ለምሳሌ ልክ እንደ መወለድ፣ መኖርና ህልፈት። ያደጉ አገራት ጥቁር ህዝብ በሥራ ሰነፍ ነው ብለው ያስባሉ። ሆኖም ግን ከሥራው ይልቅ አስተሳሰብ ይቀድማል ይመስለኛል። ዞሮ ዞሮ ግን ማሰብም መስራት ነው። ለምሳሌ ያደጉ አገራት በሥራና በሃገራቸው ላይ ቀልድ የለም። ሀገራቸውን ሀገሬ ይላሉ። ህዝባቸውን ህዝቤ ወይም ወገኔ ይላሉ። የአገራቸውን ሃብት የኛ ይላሉ። ሃሳባቸው ውስጥ ቁርጥ ያለ አቋም አላቸው። እንዲሁ በድንገት አላደጉም። ያስባሉ። ይሰራሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ከሆነ ግን ቀለም ለማስቀባት፣ ድንጋይ ለማንጠፍና፣ ሲሚንቶ ለመለሰን እንኳን ባለቤቱ ቆሞ መከታተል አለበት። ምክንያቱም ሥራው ነካ ነካ ስለሚሆን መተማመና የሚሆን ዋስትና የለም። የሥራ ባህላችን ገና አልዳበረም። በቀላሉ ማዳበር ግን እንችላለን።
ከላይ እንደጠቀስሁት መስራት አቅቶን ሳይሆን ሥራችን ላይ ጀግናዊ አስተሳሰብ ስለማይጨመርበት ነው። ጥሩ አላማ ላይ ማጋነን ቆንጆ ነው። ለምን ብትሉኝ ሥራውን ስንሰራ ጥራቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ ይረዳናል። በተጨማሪ ሃሳባዊ ወኔ ውስጣዊ ስለሆነ የትም ብንሄድ ይከተለናል። የትኛውንም ሥራ ብንሰራ ጥራት ያስታውሰናል። ሥራችን ያኮራናል። ያስከብረናል። ተቀጥረን የምንሰራም ከሆነ አሰሪያችን ያምነናል። መከታተል ሳይሆን መጨረሻ ላይ ለማስረከብ መቆጣጠር ብቻ በቂ ይሆናል። ጥራት መፈለግ ቅንጦት አይደለም።በሰሪና ባሰሪ መሃከል እምነት ይጨምራል።
ስለዚህ ጀግንነትን በሁሉም መስኮች ማምጣትና መተግበር እንደሚቻል ከላይ በዘረዘርናቸው ሁነቶች መመልከት ይቻላል። በአሁኑ ወቅት ጀግንነት ከጦርነትና ከሀገር ዳር ድንበር ማስጠበቅ በዘለለ በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲሁም በአገር አመራርነት ጥበብ እስከመገለፅ ደርሷል። በኢትዮጵያም በግብርናው፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራና በአመራርነት ጀግና ተብለው የተሸለሙና እውቅና የተሰጣቸው ሰዎች እንዳሉ እየተመለከትን እንገኛለን።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4/2013