የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኦሊምፒክ ማጣሪያ አንደኛ ዙር ጨዋታውን በመጪው ወር አጋማሽ እንደሚያደርግ የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አብረሃም መብራቱ አስታውቀዋል። በኤርትራ አስተናጋጅነት የሚካሄደው «የሠላም እና ወዳጅነት ዋንጫ» ደግሞ በሚያዚያ ወር ይካሄዳል።
ከማሊ ጋር የሚኖረው የመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ጨዋታ በካፍ መርሐ ግብር ማሻሻያ ተደርጎበት መጋቢት 14 አዲስ አበባ ላይ ከቀናት በኋላ በባማኮ የመልሱ ጨዋታ እንደሚደረግ የሶከር ኢትዮጵያ ዘገባ ያሳያል። የጊዜውን መጣበብ ከግምት በማስገባት ሀገራቱ አመቺ በሚሆን መልኩ ቀኑን ለማስተካከል ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም አሰልጣኙ በጋዜጣዊ መግለጫው ጠቁመዋል።
ተጫዋቾችን ለመምረጥ ከረዳቶቻቸው ጋር በተለያዩ ቦታዎች በመገኘት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መሆኑን የጠቀሱት አሰልጣኙ፤ ሁሉም ባይዳረስም የሚገባቸውን እንዳዩ በዘገባው ተመልክቷል። ቡድኑ ከፕሪምየር ሊጉ እና ሌሎች ሊጎች ሦስት ሶስት (በድምሩ 33) ተጫዋቾችን አካቷል። በተያዘው ሳምንት መጨረሻም ቡድኑ ተሰባስቦ ካምፑን በአዲስ አበባ ያደርጋል።
ጨዋታው እስኪካሄድም ከሱዳን እና ሲሸልስ ጋር ሶስት የወዳጅነት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። የሱዳን የዋናው እና ከ23 ዓመት በታች ቡድኖች የሚመጡ በመሆኑ ከሁለቱም ጋር ጨዋታ የሚደረግ ሲሆን፤ በዚያ ላይ በመመርኮዝም ቡድኑ ወደ 22 የሚቀነስ ይሆናል።
ከ20ዓመት በታች «የሠላም እና ወዳጅነት ዋንጫ» ደግሞ በሚያዚያ ወር በአስመራ ይካሄዳል። በቡድኑ የሚካተቱ ተጫዋቾችንም ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ክለቦች ተዟዙረው በመመልከት ላይ እንደሚገኙም አሰልጣኙ አስታውቀዋል። ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለማዋቀር በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ውድድሩ ሲቃረብ ቡድኑን የሚመራውን አሰልጣኝ መድበው እንደሚያሳውቁም ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011