የፌዴራል መንግሥት የትግራይ ገበሬ እርሻው ጾም እንዳያድር እንዲሁም የጥፋት ቡድኑም ነገሩን ቆም ብሎ እንዲያስብበት የጽሞና ጊዜ ለመስጠት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ የትግራይ ክልልን ለቆ ቢወጣም መንግሥት የወሰደውን ይህንን እርምጃ አሸባሪው ህወሓት አልተቀበለውም። እንዲያውም መሳለቂያ አድርጎታል።
“ሲይዟት ጭብጥ ሙሉ፤ ሲለቋት ሜዳ ሙሉ” እንደሚባለው የመከላከያን ከትግራይ መውጣት ተከትሎ ሰይጣናዊ ግብሩ የማይለቀው አሸባሪው ትህነግ ከጉድጓዱ ወጥቶ፤ በተወለደበት፣ ባደገበትና ባረጀበት ክህደቱ፣ ውሸቱና እብሪቱም ከበፊቱ ብሶት ገልጧል።
ለማንም የማያንቀላፋውና ርህራሄ የሌለው ይህ የጥፋት ቡድን ከተንቤን የቀበሮ ጉድጓድ በወጣ ማግስት የትግራይ ንጹኃን ዜጎችን ለመከላከያ ሰራዊት ምግብ ትሸጡ ነበር። ልኳንዳ ቤት ከፍታችሁ ስጋ ትሸጡ ነበር። ሻይ ትሸጡ ነበር። መከላከያ ቤታችሁ መምጣት ያዘወትር ነበር። ቤታችሁ ቢራና ሻይ ይጠጡ ነበር።
እርዳታና ሰብዓዊ ድጋፍ ታስተባብሩ ነበር። ተረጂዎች ትመዘግቡ ነበር። ጸጥታ ታስተባብሩ ነበር። የመንግሥትና የህዝብ አገልግሎት እንዲጀመር አስተባብራችኋል።ብልጽግናን ስትደግፉ ነበር በሚል ከ300 በላይ ንጽኃን ዜጎችን በቤተሰቦቻቸው ፊት ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ገድሏል።
የትግራይን ህዝብ ባህልና ታሪክ በማይመጥን እና ከሰውነት ተራ በወረደ መንገድ በአሸባሪው ቡድን የዕምነት ቦታዎች ተዘርፈዋል። የሃይማኖት አባቶችን ሳይቀር ከማሰርና ከማንገላታት በዘለለ እስከ ህይወት መስዋትነት እንዲከፍሉ አድርጓል ። እርዳታን በማስተባበራቸው፤ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ እንዲገነባ በመስራታቸው፤ የህዝብና የመንግሥት አገልግሎት መልሶ እንዲጀመር በመጣራቸው ፤ የአካባቢው ጸጥታ እንዲጠበቅ በማገዛቸው፤ በጥቅሉ ምንም አይነት ፖለቲካዊ ውግንናና እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ጁንታው አንገቱን ያስደፋውን ህብረተሰብ ለመካስና የተጣመመውን ለማቃናት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ በተለያየ ደረጃ ሲያገለግሉ የነበሩ ከ55 በላይ አባላትን ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ የጭካኔ ጥግ፣ የህዝቡ ባህልንና ክብሩን በማይገልጽ፣ ለመናገር በሚዘገንን ሁኔታ ገድሏል።
ጁንታው በክልሉ ያደፈረሰውን ሰላም ለመመለስ፣ ያጠፋውን ለማስተካከል፣ የተቋረጠውን ለማስቀጠል፣ የተዘጉ ትምህርት ቤቶችንና ሆስፒታሎችን ለማስከፈት፣ የቆመ ገበያና ትራንስፖርት ለማስጀመር ደፋ ቀና ሲሉ በአሸባሪው ቡድን በግፍ ከተገደሉ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አባላት አንዱ የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ኢንጅነር እምብዛ ታደሰ ናቸው።
ሟቹ ከህግ ማስከበር ዘመቻው በኋላ በክልሉ ተፈጥሮ ከነበረው ቀውስ አንጻር ከየትኛውም የፖለቲካ ውግንና ውጭ ሆነው ህዝቡን ለማረጋጋትና በሙያቸው ህብረተሰቡን ለማገልገል ለሥራ ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ወደ ኤርፖርት በሚያቀኑበት ወቅት የጁንታው ቅጥረኞች መኪናውን ጠልፈው በረሃ ላይ ወስደው ስምንት ቦታ ላይ አካላቸውን ቆራርጠው ለጅብ ሰጥተውታል ። ከሰው በተገኘ ጥቆማም ፖሊስ ከጅብ የተረፈ ቀሪ አካላታቸውን ሰብስቦ የቀብር ሥነሥርዓታቸው እንዲፈጸም አድርጓል።
“ባጎረስሁኝ እጄን ተነከስሁኝ” እንደሚባለው ኢንጅነሩ በሙያው ህዝቡን ለምን አገለገልህ ተብሎ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉ ሳያንስ፤ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ክልሉን ለቆ ከወጣ በኋላ ከጅብ የተራረፈችው ቅሪት አካሉ ከመቃብር አውጥተው አጥንቱን ለውሻና ለጅብ ሜዳላይ በትነውታል።
ከዚህ ባሻገር በጊዜያዊ አስተዳደሩ የሃገረ ሰላም ወረዳ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበረችውን ነፍሰጡሯን ወይዘሮ ሂሩት ገብረ መድህንን በውድቅት ሌሊት በመኖሪያ ቤቷ ገብተው ጠልፈው በረሃ ወስደው እጇን እግሯን ለብቻ መላ አካሏን ቆራርጠው ጥለውታል ።ከጅብ የተረፈ አካሏ ተፈላልጎም ተቀብሯል።መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ክልሉን ለቆ ከወጣ በኋላ ከጅብ ተርፎ የተቀበረ አካሏን አውጥተው ጥለዋታል።በተመሳሳይ የሃገረ ሰላም ወረዳ የብድርና ቁጠባ ኃላፊ በሆነችው መምህር የሺዓለም ፍቅረማርያም ላይም መሰል ግፍ ፈጽመውባታል።
ኢንጅነር እምብዛን፣ወይዘሮ ሂሩት ገብረ መድህንን እና መምህር የሺ ዓለም ፍቅረ ማርያምን ለአብነት ጠቀስን እንጂ ከዛ በፊት መምህር ይማነን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል ። አቶ ካሳየ ራያ የሚባልም እራያ አላጅ አካባቢ እንደዚሁ ገለው ለጅብ ጥለውት መታወቂያውና ትንሽ ቅሪት አካሉ ነው የተገኘው። የአዲግራትና የውቅሮ ከተሞች ከንቲባዎች፣ የሳምራ ከተማ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ እንዲሁም የመቀለ፣ የአድዋና የአክሱም ንጹኃን ሰዎች በመሰል አሰቃቂ ሁኔታ ጁንታው ገድሏቸዋል።
ጁንታው በተለይ በክልሉ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ላይ አነጣጥሮ በፈጸመው ጥቃት ደግሞ በምሆኒ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች ላይ ዘር የማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል። በትግራይ ክልል ምስራቅ ዞን በስሃርት ግጀት ወረዳ ሃይማኖትን ባነጣጠረ ጥቃት በተለያየ የሥራ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ አካላትን ገድሏል ፤ ከነዚህ ውስጥ የወረዳው ካቢኔ የነበሩትን ማስተር ደሳለው፣ ሙሃመድ ጁሃር፣ አቶ ጌታቸው ይማነ (የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ)፣ አቶ ሃይሎም (የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ)፣ አቶ ሞሳ ከድር (የትምህርት ጽህፈት ቤት አሽከርካሪ) እና አቶ ሃሺም ጣዕመ (የፋይናንስ ጽህፈት ቤት ተላላኪ) እነዚህን አካላት ጉድጓድ እንዲቆፍሩ አድርገው እራሳቸው በቆፈሩት ጉድጓድ ረሽኖ ቀብሯቸዋል።
አሸባሪው ህወሓት በ17 ዓመት የትጥቅ ትግሉ ከ60 ሺ በላይ ስለኢትዮጵያ አንድነት የሚያቀነቅኑ ታጋዮችን በሴራ ስለገደላቸው ለትግራይ እናቶች መልስ ሳይሰጥ ስልጣን ከተቆናጠጠበት ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ ከ30 ሺህ በላይ የትግራይ ንጹኃንን በግፍ መግደሉ ሳያንሰው፤አሁን ላይ ደግሞ ለጥቂት ቤተሰቦች የሃብትና የስልጣን ጥማት ሲባል ይህ አሸባሪ ቡድን ጭቁኑን የትግራይ ህዝብ ቢያንስ “በአንድ ቀበሌ 50 ታጋይ አዋጡ፤ካላዋጣችሁ እርዳታ የሚባል አታገኙም፤ በትግራይ ምድርም ደብዛችሁ ይጠፋል” በሚል ህብረተሰቡን በማስፈራራት ከትግራይ እናቶች ጉያ ህጻናትን ጭምር በመንጠቅ ከ10 ዓመት እምቦቃቅላ ህጻናት እስከ 74 ዓመት አዛውንት ድረስ በጦር ግንባር በማሰለፍ የእሳት እራት እያደረጋቸው ይገኛል።
ከሰሞኑ መከላከያ በሰጠው መግለጫ በስምንት ወሩ የህግ ማስከበር ዘመቻ የረገፉ የትግራይ ወጣቶች እንደተጠበቀ ሆኗ፤ የተናጠል ተኩስ አቁም ከታወጀ በኋላ ጁንታው ኢትዮጵያን ለመበተን አላማ አድርጎ በገባው ወረራና ዘረፋ ከ10ሺ በላይ የትግራይ ወጣቶችን በጦር ግንባር በማሰለፍ ለዘረፋ በገቡበት ለወሬ ነጋሪ ሳይቀር እንደቅጠል እረግፈው እንዲቀሩ አድርጓል።
በሌላ በኩል “ለውሻ ከሮጡለት፣ ለልጅ ከሳቁለት” እንደሚባለው መንግሥት ያለምንም ውጊያ ለትግራይ ህዝብ ሰላም ሲባል ክልሉን ለቆ መውጣቱን አሸባሪው ህወሓት በእርሱ ኃይል የተገኘ ድል በማስመሰል መንግስት ክልሉን ለቆ በወጣ ማግስት “ከአማራ ህዝብ ጋር የምናወራርደው ሂሳብ ዓለን፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንወርዳለን” በሚል በተለይ ኢትዮጵያን የማፍረስ ዕራይውን ለማሳካት በኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ላይ በግንባር ከሚደረገው ጦርነት ጎን ለጎን የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚ አሻጥር እንዲሁም የስነልቦና ጦርነት ከፍቶ አገር ለማፍረስ የሞት የሽረት ትግል እያደረገ ይገኛል።
የሽብር ቡድኑ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም በአወጀ ማግስት ኢትዮጵያን የማፍረስ እቅዱን ለማሳካት ከ10 ዓመት እምቦቃቅላ ህጻናት እስከ 74 ዓመት አዛውንት አሰልፎ በአማራና በአፋር ክልል የለየለት ወረራና ዘረፋ ውስጥ የገባ ሲሆን፤ በነዚህ ክልሎች ጁንታው በተቆጣጠራቸው ከተሞችና አካባቢዎች የሚፈጽመው ግፍ ሲታይ በክፋትና በክደት ከሳጥናኤል እንደማይተናነስ አሳይቷል ።
ይህ አሸባሪ ቡድን በአፋርና በአማራ ክልሎች ያደረሰውንና እያደረሰ ያለው ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥፋቶች በቃላት የሚገለጹ አይደሉም ።በአማራ ክልል በማይካድራ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ንፁሐን ሰዎች ላይ የፈጸመውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ዳግም በአፋር ክልል በጋሊኮማ ደግሞታል።
የሽብር ቡድኑ በነሐሴ 2013 ዓ.ም በአፋር ክልል በጋሊኮማ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአፋር ክልል በፈንቲረሱ በጋሊኮማ ጊዜያዊ መጠለያ በነበሩ ንፁሃን ዜጎች ላይ ድንገት በከፈተው በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ታሪክ የማይረሳው 107 ህፃናትን፣ 89 ሴቶችንእና 44 አዛውንቶችን እና ሌሎች የህብረተሰብ አካላትን ጨምሮ በድምሮ 270 ንፁሃን አርብቶ አደሮች ገድሏል። በመጋዘን የነበረ የአስቸኳይ እርዳታ እህልና ቁሳቁስ አውድሟል ።
በጠቅሉ በአፋር ክልል ህጻናትና እናቶችን በመድፈር፣ ንጹሃንን በመግደል፣መሰረተልማቶችን በማውደም እና የመንግሥትና የግለሰብ ንብረቶችን ዘርፏል ፤ በተመሳሳይ ጁንታው በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ አማራ ክልል ቆቦ ውስጥ አጋምሳ በሚባለው አካባቢ በአንድ ቀበሌ አርሶ አደር መንደር ላይምንም አይነት የተኩስ ልውውጥ በሌለበት በከባድ መሳሪያ በፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ከ100 በላይ ንጽኃን አርሶ አደሮች ገድሏል ።
በዚህም በአካባቢው የአሸባሪው ቡድን በፈጸመው ጥቃት ከ50 በላይ የአርሶ አደር መኖሪያ ቤቶች በከባድ መሳሪያ ጥቃትና ሆን ተብሎ በእሳት እንዲቃጠሉ የተደረገ ሲሆን፤አንድ ሽማግሌ ከቤት ውስጥ በሽቦታስረው ከቤታቸው ጋር አብረው እንዲቃጠሉ ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪ “ቂልጡ፣ ድቡስቃና አዲውድየ ተባሉት መንደሮች በመድፍ ካቃጠለ በኋላ የጁንታው ታጣቂዎች እሳት በእጃቸው ይዘው እየዞሩ ቤት ለቤት ሲያቃጥሉ እንደነበር የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ የአካባቢው አርሶ አደሮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አሸባሪው ቡድን ወደ ደብረ ታቦር ከተማ ባስወነጨፈው ከባድ መሳሪያ በአንድ የግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ አርፎ፤ የአራት ወር ጨቅላ ህጻን ጨምሮ ስድስት የአንድ የቤተሰብ አባላትን በጅምላ በማጥፋት ከቤተሰቡ ከጥቃቱ የተረፉትን አዛውንት ያለጧሪ ቀባሪ አስቀርቷል። እንዲሁም በደቡብ ጎንደር ዞን በንፋስ መውጫ ከተማ ልጆቻቸውን ይዘው ህይወታቸውን ለማዳን እየሮጡ በነበሩ የቤተሰብ አባላት ላይ ጁንታው በንጹሃን ላይ በከፈተው ተኩስ እናት እና አባቱ እሬሳ ስር በደም ተጨማልቆ የተገኘው የንፋስ መውጫው የሁለት ዓመት ህጻን ከሁሉም የኢትዮጵያ አዕምሮ ውስጥ የሚጠፋ አይደለም።
በገሃሳይ ከተማ ነፍሳቸውን ለማዳን ጠዋት ከቤታቸው ወጥተው ጫካ ውለው ማታ ቤታቸው እግራቸው ከመርገጡ፤ ባል፣ ሚስት፣ የሚስት እናትና የሁለት ዓመት ልጃቸው ማታ ተመልሰው ቤታቸው ከመግባታቸው የጁንታው ታጣቂ ቤታቸው ላይ የተኮሰው መድፍ የሁለት ዓመት ህጻን ልጃቸውን አንድእግሩን ቆርጦ ጥሎት እሩጦ ያልጠገበው ህጻን “እረናቴ እግሬ ጠፋኝ” እያለ የተቆረጠውን እግሩን ሲፈልግ እናት በወቅቱ የተፈጠረውን ድርጊት ስትናገር መስማት ልብን ያደማል፤ ይሰብራል። በሰሜን ጎንደር አደርቃይና ጠለምት ወረዳዎች የንጹኃን የአርሶ አደር ቤቶችን በከባድ መሳሪያ በመደብደብ አንድ የቤተሰብ አባላትን በጅምላ ጨፍጭፎ መነኩሴ ሳይቀር እሬሳቸው እንዳይቀበር ሜዳላይ አስጥቶ መፈራረጃ አድርጓል።
ዓለምን ንቀው ቁሩና ሃሩሩ ሳይበግራቸው፣ ጤዛ ልሰው ድንጋይ ተንተርሰው ስለኢትዮጵያ የሚማጸኑ መነኮሳትን በዋልድባ ገዳም በአሰቃቂ ሁኔታ ደብድቧል፤ገድሏል። እንደነጨጨሆ መድኃኒዓለም አይነት ታሪካዊ የእምነት ቦታዎችን በከባድ መሳሪያ ከማውደም ባለፈ መስጂድና ቤተክርስቲያንን ካምፕ እና የጦር ግንባር በማድረግ ጥፋት ፈጽሟል።
በአጠቃላይ የትግራይ ዘራፊ ኃይል በአማራ ክልል በተቆጣጠራቸው ከተሞችና አካባቢዎች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ከቀዬው ከመፈናቀሉ በላይ ከአራት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለከፋ ሰብዓዊና ማህበራዊ ችግር መጋለጡን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል ፤ ጁንታው በክልሉ በወረራ በያዛቸው ከተሞች ላይ ህጻናትን በመድፈር፣ ወጣቶችን ይዘው “ለኛ ተዋጉ ሲሏቸው አንዋጋም” ያሉትን አደንዛዥ እጽ በመርፌ በመስጠት ጦር ሜዳ በማሰለፍ በወንድሞቻቸው እጅ እንዲሞቱ ከማድረግ ባሻገር በመርፌ መርዝ በመስጠት አያሌ ቁጥር ያላቸው የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶችን እየመረዙ ገድለዋል።
ጦርነቱ ተቋጨ እንኳን ቢባል ህብረተሰቡ በኢኮኖሚ እንዳያንሰራራ ለማድረግ ጁንታው የዘረፈውን ዘርፎ ወደ ትግራይ ከመውሰድ ባለፈ መውሰድ የማይችለውን በማቃጠል፣ አፋቸው የማይናገሩ ከብቶችን ሳይቀር በመግደል ዓለም ላይ ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ ወንጀሎችን በአማራ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ይገኛል።በዚህም ዓለም ላይ የመጀመሪያውን “በእንስሳት” ላይ ወንጀል የፈጸመ ብቸኛና ወደር የለሽ አሸባሪ ቡድን ነው።
አሸባሪው ትህነግ በአማራ ክልል በወረራ በያዛቸው ከተሞች ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ውድመት ፈጽሟል፤ “መንግስት ሰሜንወሎን እንደገና ለመገንባት ከእንግዲህ በትንሹ 7 ዓመት ያስፈልጋል” ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናግረዋል።
ቡድኑ በከፈተው ጦርነት በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልል ከ7 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች (ወልድያ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ) በከፊልና ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ እንዲወድሙ በማድረግ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ማድረጉን የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ክ ኢንጅነር) ተናግረዋል።
ስለዚህ የዚህ አሸባሪ ቡድን እኩይ ሥራ አሁን ላይ በግሃድ አደባባይ ወጣ እንጂ፤ ጁንታው በ17 ዓመት የትጥቅ ትግሉ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ያላቸውን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የትግራይ ወጣቶችን በሴራ የገደለና ለእርዳታ የመጣ እህልን ለጦር መሳሪያ መግዣነት በማዋል አያሌ የትግራይ ህዝብን በርሃብ ጨርሷል፤ ስልጣን ላይ በነበረበት ባለፉት 27 ዓመታትም ለትግራይ ህዝብ አማራጭ ሃሳብ እንዳይቀርብ አፍኖ ይዟ ሲያስርና ሲያሰቃይ ነበር። እንዲሁም ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የኢትዮጵያን ህዝብ በጨለማ እስር ቤት አስሮ ሲያኮላሽ ጥፍር ሲነቅል ከመኖሩ ባሻገር አገርን እርቃኗን ያስቀረና የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ሲሰጥ የኖረ ዘራፊና ባንዳ ቡድን ነው።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 2/2013