በግልፅ እንደሚታወቀው ለብዙዎቻችን የአሁኑ ወቅት ተወዳጅ ዜማ “እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ” የሚለው የኤፍሬም ታምሩ ዜማ ነው፤ ወይም እሱን መሰል ሌላ ዜማ። ብቻ ምንም ሆነ ምን፣ የትኛውም አይነት ግጥምና ዜማ ይሁን አጠቃላይ ቅኝቱ “እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ” ነው ።በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሁሉም ሰው የወቅቱ ዜማ ምርጫ ወይም በባህላዊ አገላለፁ ካየነው ይሄ ክረምት ባለፈ፣ ወይም እንደምንም ብሎ መስከረም በጠባ …. አዲስ ዓመት በገባ የሚል ሆኖ ነው የምናገኘው።
ይህን ማለታችን ምንም ስህተት የለበትም። ይህንን ልንል የቻልንበት የራሳችን የሆነ በቂ ምክንያት አለን ፤ በማለታችን ልንወቀስ፤ ወይም በዘፈን አመራረጥ ችሎታችን “ቀሽም” ልንባል አይገባም።
ያለነው በጥቂት ግለሰቦች ምክንያት አገር ወደ እማትፈልገው ጦርነት ውስጥ የገባችበት ክፉ፣ አስተዛዛቢና አወቃቃሽ ወቅት ነው። ወደ ፊት ታሪክ የራሱን ፍርድ የመፍረዱ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ እየሆነ ያለው ግን ከፍ ያለ ሀገራዊ አደጋ የተሸከመ ስለመሆኑ ምንም መጠራጠር አይቻልም።
ወቅቱን ከሁሉ የከፋ የሚያደርገው እዚህ ገባ ለማይባል፣ ምናልባትም ከስልጣንና ገንዘብ ለማያልፍ ጥቅም ያልተገባ ግጭት ውስጥ መግባታችን ብቻ አይደለም፤ ለ”እንደምንም ብሎ ይሄስ ቀን ባለፈ ….” ዜማ መመረጥ ምክንያት የሆነው በአንዲት ምስኪን፣ ነገር ግን ሉአላዊት አገር – ኢትዮጵያ ላይ ጡንቻቸውን ያፈረጠሙ የዓለም ኃያላን የውክልና ጦርነት ማካሄዳቸው (ለዛውም በግልፅ) ነው።
ከነዚህ ኃያላን ደግሞ ፊታውራሪዋ እራሷን አስቀድማ “የዓለም ፖሊስ” ብላ የሰየመችው አሜሪካ መሆኗ ብዙ ድብልቅልቅ ስሜትን የሚፈጥር ነው ። የዴሞክራሲ አቀንቃኝ፡ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ/ ተሟጓች …. የሆነ ከእኔ ወዲያ ላሳር ስትል ከመኖሯ ጋር በቀጥታ የሚላተም ኢሰብአዊ ተግባር መፈፀሟ ደግሞ የበለጠ ድብልቅልቅ ስሜትን ይፈጥራልና ስለ እሷው ትንሽ ሀሳብ እንለዋወጥ።
በአሁኑ ሰዓት አደባባይ ወጥቶ የጠዋት ፀሐይ እየሞቀ ያለ አንድ ዓለም አቀፍ እውነት ቢኖር አሜሪካና አሸባሪው ህወሓት ጋብቻ የመፈፀማቸው ጉዳይ ነው፤ በቃ። በዚህ ላይ የሚከራከር ካለ እሱ በዚህ ዓለም ላይ የለምና ለእሱ ዝምታው ወርቁ ሊሆን ይገባል ፤ ዝም ይበል።
አሜሪካ እፍረት የሚባለውን ነገር ከውስጧ አንጠፍጥፋ የጨረሰች እስኪመስል ድረስ ሁሉ ነገሯ ይሉኝታቢስ ከሆነ ሰንብቷል ። በተለይ በኢትዮጵያ ጉዳይ የአገሪቱን መንግሥት አልፋ ከመሄዷም በላይ ቀበሌና ወረዳ ድረስ ገብቼ እኔ ካላስተዳደርኩ ከማለት ያልተናነሰ ነውር ሁሉ እየፈፀመች ነች ። አይሆንም ስትባል ደግሞ መደበቂያዋ “ማእቀብ” የምትለው አሜሪካ ሰራሽ የጦር መሳሪያ ነው።
በኢትዮጵያ ላይ እያፈራረቀች ተግባራዊ እያደረገች ያለችው እነዚህን ሁለት (የውክልና ጦርነትና ማእቀብ) እኩይ፣ ምናልባትም ፀያፍ ተግባራት ሲሆን ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብም እየተቋቋማት ያለው ይህንኑ የእሷን ኃያል ክንድ ከነ ውስብስብ ሴራዋ ነው። (አሁን ወደ “አጎአ”ው ጉዳይ እንምጣ።)
ግልፅ ነው፤ በእስከ ዛሬ ማእቀቧ የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ እጁን አላስጠመዘዘም፤ ማንነቱን አሳልፎ አልሰጠም፤ ሉአላዊነቱን አላስደፈረም። ይህ ደግሞ በበኩሉ ካፈርኩ አይመልሰኝ ለሆነባት አሜሪካና ተባባሪዎቿ ሊዋጥላቸው አልቻለም። እንደ ውርደትም ቆጥረውት ነው መሰል (በእርግጥ ውርደት ነው) ወደ ኋላ ሸብረክ ሲሉ አይታዩም። ጭራሽ በማእቀብ ላይ ማእቀብ በመደራረብ ኢትዮጵያን እጅ ለማሰጠት ሲጥሩና ሲጣጣሩ ነው የሚታዩት።
የሰሞኑ አሜሪካ ኢትዮጵያን ከ”አጎአ” ( AGOA (African Growth and Opportunity Act) ለማስወጣት እያሴረች፤ ምናልባትም እያስፈራራች የመሆኗ ነገርም የዚሁ ማሳያ ነው። በአሜሪካው «ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት» (“የዕድገትና የዕድል ሕግ” እንበለው?) አማካይነት ለዚህ የበቃው “አጎአ” ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪካ ሀገሮች ያወጣችው ከቀረጥና ታሪፍ ነፃ የንግድ ተጠቃሚነት ዕድል ሕግ ነው።
ከምስረታው ጀምሮ ሲባልለት እንደነበረው በጣም ጥሩና ለታዳጊ አገራትም ጠቃሚ የሆነ ህግ ነው። ኢትዮጵያም ከማድነቅም ባለፈ አስፈላጊነቱን ስታብራራ ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር ከኢትዮጵያ በታች ነውና ለእጅ መጠምዘዣነት የሚውል ከሆነ ኢትዮጵያ የእናንተ “አጎአ” ባፍንጫዬ ይውጣ ለማለት የማትገደድበት ምንም አይነት ምክንያትም ሆነ ህግ የለም። የዚህ ደግሞ ምክንያቱ አጎአ ለኢትዮጵያ እስከጠቀመ ድረስ እንጂ አጎአ ለኢትዮጵያ እጅ መጠምዘዣነት እስከ ሆነ ድረስ በኢትዮጵያ በኩል አስቀድሞም ቢሆን ቀይ ሊሰጠው ይገባል።
ከአጎአ እሰርዝሻለሁ ማለት ድሮም አጎአ የተመሰረተው በድምፅ አልባ የጦር መሳሪያነት ነበር ማለት ነው። በአጎአ የታቀፉ አባል አገራትን በራሱ በአጎአ ማስፈራራት ማለት አጎአ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ አዲሱ ተቋም ነው ማለት ነው። አገራትን “ወይ አጎአን ምረጡ፣ አለያም እኔ እምላችሁን ስሙ፤ እማዛችሁን ፈፅሙ” ማለት አጎአ እነ አሜሪካ ከ100 ዓመታት በፊት አቅደውት የነበረው እቅድ (ሀያላን ደሀ አገራትን እንደፈለጉት የማድረግ ተፈጥሯዊ መብት ያላቸው መሆኑን የሚያፀድቅ ህግ) ማስፈፀሚያ ተቋም ነው ማለት ነው።
አጎዋ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይዋን በኃይል ለማስፈፀም የምትጠቀመው ከሆነ አጎአ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሌላው ግልባጭ ነውና ኢትዮጵያ ከዛ ብትሰረዝ ታተርፋለች እንጂ አትከስርም!!!
እርግጥ ነው ኢትዮጵያ የአጎአ የንግድ ዕድልን ተጠቅማ ምርቶቿን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በመላክ ልትጠቀም ትችላለች፤ ይህ ሁሉ ሊሆን የሚችለው ግን እራሷ ኢትዮጵያ ስትኖር ነውና በኢትዮጵያ ድርድር የለም።
አጎአና ኢትዮጵያም እኩል ሚዛን ላይ ሊቀመጡና ወይ አጎአናን ወይ ኢትዮጵያን ምረጡ ልንባል አይገባም፤ በባህላችንም ካየነው አፀያፊ ነው፣ ነውር ነው፣ ንቀት ነው። ይህንን አሜን ብሎ የሚቀበል ኢትዮጵያዊ ትከሻ ደግሞ የለም። “አለ” የሚል አካል ካለ ደግሞ እሱ እራሱ ከገለባ የቀለለ ነውና ከእነ አጎናው እዛው ሊቀር ይችላል።
የዚህ ምክንያቱ ደግሞ “ዩናይትድ ስቴትስ ከሠሃራ በስተደቡብ ላሉ የአፍሪካ አገሮች የከፈተችው የዕድገትና የገበያ ተጠቃሚነት ዕድል” የተቋቋመበት ስውር ምክንያትና የዚህ ጽሑፍ ርእሳችን የሆነው “የኢትዮጵያውያን ህልውና ኢትዮጵያ እንጂ ‘አጎአ’ አይደለም” የሚለው ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 2/2013