አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያዊነት የጥቁር ሕዝቦች የአሸናፊነት ቀንዲል በመሆኑ ከኢትዮጵያውያን አልፎ ሌሎች የሚኮሩበት ታሪካችንን ይዘን መቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያዊነት ቀንን በማስመልከት ትናንት በተካሄደው ውይይት ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በርካታ የምትታወቅባቸው ነገሮች አሏት፣ በታሪኳ እንድትታወቅ ያደረጓትን ቅርሶች መጠበቅ ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም(ዩኔስኮ) ያስመዘገበቻቸውን ቅርሶች በአግባቡ ካልጠበቅናቸውና ካልያዝናቸው ከጊዜ በኋላ ከመዝገቡ መሰረዝም ሊመጣ ይችላልና መጠንቀቅ አለብን ሲሉም አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ ላይ በርካታ አሉታዊ ነገሮች እና ሁኔታዎች መፈራረቃቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፤ ይህ ሁሉ ነገር ለምን ሆነ ብሎ ቆም ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያዊነት የተዘጉ በሮችን ማስከፈት የሚችል እውነት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያዊነት እንደከበረ እንቁ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ልዩ ቦታ ተሰጥቶት የተቀመጠ ከዘመናት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ በእሳት ተፈትኖ የነጠረ፣ በተግባር ተፈትኖ የከበረ ስም ነው” ብለዋል።
የኢትዮጵያዊነት ዋጋው ውድና ማንም ሊያራክሰው የማይችል መሆኑን የገለጹት ምክትል ከንቲባዋ፤ ኢትዮጵያዊነት በጀግንነት፣ በድል አድራጊነት፣ በአልበገር ባይነት፣ በአርቆ አስተዋይነት፣ በተቻችሎ መኖርና በጠንካራ አንድነት የመጣና እዚህ የደረሰ የክብር ስም መሆኑንም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያዊነት የድል ብሥራት አውጊነት እና የአሸናፊነት የክብር ካባ መሆኑን የገለጹት ምክትል ከንቲባዋ፤ ‹‹በሄድንበት የምንኮራበት፣ በደረስንበት የምንታፈርበት፤ ብዙዎችን ያሸበረ፤ ወራሪዎችን ያስደነገጠ፤ ንቀትን የገለበጠ፤ አለማወቅን ያሳወቀ፤ ይቻላልን ያረጋገጠ፤ የጥቁር ሕዝቦች የአሸናፊነት ቀንዲል፤ የስነልቦና ከፍታ ነው›› ብለዋል።
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያዊነት የማይደፈር ወኔ፣ የማይነካ ድንበር፣ ለወራሪ የማይንበረከክ፣ ለግፈኞች እጅ የማይሰጥ፣ ለጉልበተኞች የማይተኛ፣ ለሰንደቁ ክብር የሚዋደቅ፣ እምቢ ለሀገሬ ብሎ ታሪክን የሰራ፤ ዛሬም መስራቱን የቀጠለ፤ የጠንካራ ስብዕና፣ የአይበገሬነትና የጀግንነት መገለጫ የጋራ ስም ነው፡፡
በፓናል ውይይቱ ወቅት ለውይይት መነሻ የሚሆን ፁሁፍ ያቀረቡት የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያዊነት በዘመናት የታሪክ ሂደት እየተገነባ ወደፊትም እየለመለመ የሚሄድና በእያንዳንዱ ዜጋ ማንነት ውስጥ የሚገኝ መንፈስ ነው።
የኢትዮጵያ ማንነት በርካታ መገለጫዎች ያሉት ቢሆንም ሰባት መገለጫዎች ግን አገሪቷን በዋናነት ይገልጿታል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ‹‹ቀደምትነት፣ እምነትና እውነት፣ ህብረ-ብሔራዊነትና ወንድማማችነት፣ ሰላምና ፍቅር፣ ነፃነትና ጀግንነት፣ ኩራትና ክብር እንዲሁም ዘላለማዊነት ናቸው›› ብለዋል።
ሌላኛው ፁሁፍ አቅራቢ ዲማ ነገዎ (ዶክተር) የማንነታችን መገለጫዎች ማሰሪያው ኢትዮጵያዊነት ነው ብለዋል።የኢትዮጵያ ህዝብ የተለያዩ የማንነት መገለጫዎች አሉ፣ እነዚህን ሁሉ አጠቃልሎ አንድ ዓይነት አገራዊ ማንነት የሚሰጠን ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ነው ሲሉ አስረድተዋል። አሁን ያለው ኢትዮጵያዊ ማንነት አንድነትን በብዝኃነት አጣምሮ ሁሉንም ህዝብ በእኩልነት የሚያስተናግድ መሆኑንም ተናግረዋል።
በውይይቱ የተሳተፉት የመከላከያ ሚኒስትር የሰራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ በበኩላቸው፤ ‹‹እኛ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ስለ ኢትዮጵያ መናገር ሳይሆን ህይወት የሚደገም ከሆነ ደግመን ደጋግመን ለኢትዮጵያ ለመሰዋት የተዘጋጀን ነን›› ብለዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 2/2013