በመካከለኛና ረጅም ርቀት የሩጫ ውድድሮች የምትታወቀው አትሌት መሰረት ደፋር በተያዘው ወር መጨረሻ በጃፓን ናጎያ የማራቶን ውድድር ላይ ትሳተፋለች። በውድድሩ የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ከፍተኛ የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት አግኝተዋል።
መሰረት ባሳለፍነው ዓመት ለ12ኛ ጊዜ በተካሄደው የጃፓን ቶኪዮ ማራቶን ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሳተፍ ወስና የነበረ ቢሆንም፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በአምስተርዳም ማራቶን 2:27:25 በሆነ ሰዓት ስምንተኛ መውጣቷ ይታወሳል። የ 35 ዓመቷ አትሌት አሁን ደግሞ በጃፓን ናጎያ ማራቶን ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ ልትካፈል መሆኑን ዥንዋ ኔት ዘግቧል።
በውድድሩ ከመሰረት ደፋር ባለፈ ኬንያዊያን አትሌቶችም እንደሚሳተፉ የታወቀ ሲሆን፤ ቫለሪ ጄሚሊ እንዲሁም ቪዝሊን እና ሞኒካ ጄፕኪሹ ውድድሩን ፈታኝ እንደሚያደርጉት ይጠበቃል። ጄሚሊ ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው የበርሊን ማራቶን 2ሰዓት ከ 20 ደቂቃ 53 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ሶስተኛ መውጣቷ ይታወሳል።
በ5ሺ ሜትር የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቷ መሰረት፤ በተመሳሳይ ርቀት የሁለት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ናት። በ3ሺ ሜትር የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና አራት ጊዜ ወርቅ አግኝታለች።
አትሌት መሰረት ደፋር በ1999 በፖላንድ የ3 ሺ ሜትር ዓለም ዓቀፍ ውድድር አድርጋ ሁለተኛ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ በ1ሺ500፣ በ5ሺ እና በ10 ሺ ሜትር ውድድሮች ኢትዮጵያን በመወከል የተለያዩ ስኬቶችን ተጎናጽፋለች። ከዓመት በፊት በአሜሪካ ሳንዲያጎ ግዛት በተካሄደ የግማሽ ማራቶን ውድድር 1 ሰዓት ከ8 ደቂቃ ከ27 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ማሸነፏም ይታወሳል።
በ10 እና በ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድሮች እንዲሁም በግማሽ ማራቶን ውድድር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011