ጥንታዊያኑ ግሪኮች አማልክትን ለማስታወስ ስፖርታዊ ክብረ በዓላትን ያዘጋጁ ነበር። በዘጠነኛው ምዕተ ዓመት አካባቢም የሶስቱ ግዛት መሪዎች ጊዜያዊ የተኩስ አቁም አድርገው ነበር። «የተቀደሰ ስምምነት» የሚል ርዕስ የተሰጠው ስምምነቱ ስፖርታዊው ክብረ በዓል «ኦሊምፒክ» እስኪጠናቀቅ የነበሩትን ቀናት የሚሸፍን ነበር።
ታሪክ ይህንን ሲጠቅስ ሰነዶች ደግሞ የኦሊምፒክ ግብ ለሰላም ግንባታ እንዲሁም ለወጣቱ ትውልድ ከልዩነት የጸዳ ሰላማዊ ዓለምን ለማሳየት መሆኑን ይጠቁማሉ። ይህ የስፖርት አስኳል ሃሳብ ሲሆን፤ ስፖርታዊ ውድድሮች ደግሞ መከባበር፣ መረዳዳት፣ አብሮነት፣ ወዳጅነት እና እኩልነት የሚዘመርባቸው መድረኮች ናቸው።
ወደ 19ኛው ክፍለ ዘመን መለስ ብንልም በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት (እአአ በ1914) የገና ወቅት የእንግሊዝና ጀርመን ጦሮች ትጥቅ ፈተው እንደነበር የጽሁፍ ማስረጃዎችን ማንሳት ይቻላል። ለአንድ ቀን በተካሄደው ተኩስ አቁም ሁለቱ ተዋጊዎች ሰላማዊውን ጦርነት በመምረጣቸው ዕለቱን በኳስ ጨዋታ ሊያሳልፉም ችለዋል።
የሚሊኒየሙን ግብ ለማሳካት ከተቀመጡት መንገዶች መካከልም አንዱ፤ ሰላምን በስፖርት ለማሳደግ የሚለው ተጠቃሽ ነው። ዩኔስኮም ስፖርትን ተጠቅሞ ዓላማውን ለማሳካት አቅዶ በመስራት ላይ ነው የሚገኘው።
በስፖርት ምክንያት የበረዱ ግጭቶች፤ ከስፖርታዊ ውድድሮች የተነሱ ወዳጅነቶችንም ዓለም በታሪክ ማህደሯ አስፍራለች። ከጥንታዊው ኦሊምፒክ እስከ አለፈው ዓመቱ የክረምቱ ኦሊምፒክ ድረስም ስፖርት የሰላም ወዳጅና መሰረት መሆኑን በተግባር አሳይቷል።
በኢትዮጵያስ፤ ስፖርት «ለሰላምና ወዳጅነት» እየዋለ ነው ወይስ ሚናው ተዘንግቷል? ይህንን ጥያቄ ይደግፍ ዘንድ አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ። ባለፉት ዓመታት ሃገሪቷ ውስጥ በነበረው ሁኔታ ትልልቅ ውድድሮች ሳይካሄዱ ቀርተዋል። በስፖርት ማህበራት ይዘጋጁ የነበሩ ሻምፒዮናዎችም ገባ ወጣ ይሉ ነበር። ሁኔታዎችን ተቋቁመው በተካሄዱ ውድድሮች ላይም ተሳታፊዎቹ እንደሚጠበቀው ሙሉ አልነበሩም።
እንደ ብሄራዊ የኦሊምፒክ ውድድር የሚታየው የመላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች፤ ለ6ኛ ጊዜ በ2010ዓም መካሄድ ቢኖርበትም እስካሁን አልተካሄደም። በተያዘው ዓመትም ስለመካሄዱ እርግጠኛ መሆን እስካሁን አልተቻለም። ሌላኛው ዓመታዊና በጉጉት ተጠባቂ ከሆኑት ውድድሮች መካከል የሚጠቀሰው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውድድር፤ ከ2007 በኃላ ተቋርጧል። የትምህርት ቤቶች እና የባህል ስፖርቶች ውድድርም በመሃል ተቋርጠው ነበር።
የስፖርት ሚና አንድነትና ወዳጅነትን ማሳየት ከሆነ ግጭቶች በመነሳታቸውና አለመረጋጋት በመኖሩ ምክንያት ውድድሮች ሊቋረጥ አይገባም። እንዲያውም የግጭትና የአለመግባባትን እሳት እንደ ማጥፊያ መሳሪያ መጠቀም ይቻላል።
አንድ የሚታወቅ እውነት አለ፤ ይህም ብሄራዊ ቡድኖች በትልልቅ ውድድሮች ላይ የተሳታፊነት ዕድል ሲያገኙ የህዝቡ አትኩሮት በሙሉ ወደዚያው ይሆናል። አትሌቶች ሮጠው ሲያሸንፉ አሊያም በየትኛውም ስፖርት አሸናፊነት ሲኖር ደግሞ የሃገር ፍቅር ስሜቱ ከምን ጊዜውም በላይ የላቀ ይሆናል። በመሆኑም አለመግባባቶችን ለማለዘብ ስፖርትን ይበልጥ ማጉላትና ማድመቅ ጠቃሚ ይሆናል።
ፊሊፒንስና ኮሎምቢያ ህጻናትን በፕሮ ጀክቶች በመያዝና በማበረታታት ሰላምን ለማሳደግ ፕሮጀክት ቀርጸው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ሃገራት ናቸው። ዓላማውም ህጻናት በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወቅት ማሸነፍና መሸነፍን፣ የቡድን ስሜት እንዲሁም መሪነትን አዳብረው፤ በወደፊት ህይወታቸው ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የሚረዳቸው ይሆናል። ይህም መጪውን ትውልድ ቅድሚያ ለሰላም እንዲሰጥ የሚያደርግ ነው።
ሃገራት በዓለም ላይ ስማቸው ከሚነሳባቸው በርካታ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ስፖርት ነው። አንድ ቡድን ድል አስመዝግቦ ዋንጫ ሲያነሳ አሊያም አንድ ተወዳዳሪ አሸንፎ ሜዳሊያ ሲያጠልቅ ደስታው የግሉ ብቻ አይሆንም። ውጤቱ የስፖርተኞች የጥረት ውጤት ቢሆንም የሚወክለው ግን ሃገርን እስከሆነ ድረስ የጋራ ያደርገዋል።
እንዲህም ሲሆን፤ በከፍተኛ ደረጃ የብሄራዊ ስሜትንና የአብሮነት አስተሳሰብን ያነሳሳል። ህዝቡ ስፖርትን የሚወድ እንደመሆኑም በውድድሮች አለመ ግባባቱን ገታ አድርጎ ትኩረቱን ወደዚያው ለማድረግ ያስችላል። የተለያዩ መልዕክቶችን በማሰራጨትም ህዝቡ ዘንድ በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ ይቻላል።
ይህ የስፖርት ባህሪም ዓለም አቀፋዊ እንደመሆኑ በኢትዮጵያም ኮሽ ባለ ቁጥር ውድድሮች ተቋረጡ ከማለት ይልቅ እንደ መሳሪያ መጠቀሙ የተሻለ እንደሚሆን የሚመለከታቸው ሁሉ ሊያስቡበት ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011
ብርሃን ፈይሳ