ላለፉት 60 ዓመታት የብስክሌት ስፖርት በኢትዮጵያ ሲዘወተር ቆይቷል። ይህም በአፍሪካ ቀዳሚ ሲሆን፤ እስከ ኦሊምፒክ (ከአትሌቲክስ ቀጥሎ በርካታ ተሳትፎ የተደረገበት ስፖርት) የደረሰ ተሳትፎም አለው። ይሁን እንጂ እንደ ሌሎች ስፖርቶች ትልልቅ ውድድሮችን የማዘጋጀት እድል አልተገኘም ነበር።
በዚህም የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ላለፉት ሦስት ዓመታት ጥያቄውን ሲያቀርብ ቆይቷል። የዘንድሮውን ውድድር ለማዘጋጀት ካመለከቱት አምስት ሃገራት መካከልም ኢትዮጵያ ለመጀመ ሪያ ጊዜ ተመራጭ ለመሆን ችላለች።
በአፍሪካ ብስክሌት ኮንፌዴሬሽን የሚመራው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮና በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፤ የዘንድሮው ለ14ኛ ጊዜ ነው። ያለፈው ዓመት መጨረሻ የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ጋር በመወያየትም ከመግባባት ላይ መደረሱን፤ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ወርቁ ገዳ ይገልጻሉ። በዚህም በመንግስት በኩል ላለፉት ስድስት ወራት ዝግጅት ሲካሄድ ቆይቷል።
ውድድሩን ለማዘጋጀት አንድ ከተማ መመረጥ ስለነበረበት ፌዴሬሽኑ መስፈርቶችን በማውጣት ሁሉንም ክልሎች የጋበዘ ሲሆን፤ ፍላጎት ያሳዩት ግን የትግራይና የአማራ ክልል ነበሩ። በመስፈርቱ መሰረትም የአማራ ክልል በመመረጡ ውድድሩ በባህርዳር ከተማ እንዲካሄድ መወሰኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ያስረዳሉ። የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ፌዴሬሽኑ እንዲሁም ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት የተወጣጡ ኮሚቴዎችም ተዋቅረዋል።
በዚህ መሰረት ወደ ስራ የተገባ ሲሆን፤ ከመጪው መጋቢት 5-እስከ 10 ለሚካሄደው ሻምፒዮና የመንገድ፣ የሆቴል፣… መረጣ እንዲሁም ሌሎች ቅድመ ዝግጅቶች ወደ መጠናቀቁ ይገኛሉ። በውድድሩ ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ሃገራት በኮንፌዴሬሽኑ በኩል ምዝገባ በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ ለተመዘገቡትም ቪዛ የማስተካከል እና ሌሎች ስራዎችን እየተከናወኑ ነው። ከዚህ በተጓዳኝ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉትን ሃገራት ለማበረታታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅናሽ ማድረጉንም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይገልጻሉ።
ውድድሩን ከሌላው ጊዜ ለየት የሚያደርገው የ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ማጣሪያ በመሆኑ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም በርካታ ሃገራት በውድድሩ ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። የአምናውን ውድድር የሩዋንዳዋ ኪጋሊ ያስተና ገደችው ሲሆን፤ ከ46ቱ የኮንፌዴሬሽኑ አባል ሃገራት 32 የሚሆኑት ነበሩ የተካፈሉት፤ ዘንድሮ ቁጥሩ ከዚህም ይልቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ውድድሩ አራት ተግባራት አሉት እነርሱም፤ በቡድን የሰዓት ሙከራ፣ በግል የሰዓት ሙከራ፣ የጎዳና ውድድር እንዲሁም ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የቅልቅል ውድድር ናቸው። ይህ ውድድር 50 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፤ ሶስት ሴት እና ሶስት ወንዶች ርቀቱን እኩል ተካፍለው በቅብብል ይወዳደራሉ።
ኢትዮጵያ ከአዘጋጅነቷ ባሻገር በውድድሩ ተሳታፊ የምትሆን ሃገር እንደመሆኗ ዝግጅቷን ቀድማ መጀመር ይኖርባታል። በዚህም መሰረት በታህሳስ ወር የብሄራዊ ቡድን ምልመላ መካሄዱን አቶ ወርቁ ይጠቁማሉ።
በሃገሪቷ ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች በሙሉ ዝግጅት እንዲያደርጉ ፌዴሬሽኑ በመስከረም ወር ጥሪ ያስተላለፈ ሲሆን፤ በታህሳስ ወር በተካሄደው የማጣሪያ ውድድር 190 የሚሆኑ ብስክሌተኞች ተሳትፈዋል። በድጋሚ በተደረገው ማጣራትም 35 የተሻሉ ብስክሌት ጋላቢዎችን በብሄራዊ ቡድኑ በማካተት ልምምድ እየተደረገ ይገኛል። እስከ ውድድሩ ድረስም የአንድ ወር ዝግጅት ይኖራቸዋል። የቡድኑ አባላት በውድድሩ በዕድሜ ገደብም ይሁን በተለያዩ ርቀቶች በሚካሄዱ ሁሉም ውድድሮች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ያረጋግጣሉ።
በአፍሪካ አህጉር ኢትዮጵያ በስፖርቱ በቀደ ምትነት የምትነሳ ብትሆንም በመሃል በመቀዛቀዙ ምክንያት የተዳከመ መስሎ ነበር። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በማንሰራራት በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የኦሊምፒክ ተሳትፎን ጨምሮ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል። በአምናው ሻምፒዮናም ቡድኑ ሁለተኛ በመውጣት አመርቂ ውጤት አስመዝግቧል። አሁን ደግሞ በራሳቸው አየር ላይ በሚያደርጉት ውድድር የተሻለ ውጤት ሊያስመዘግቡ የሚሉ ብስክሌት ጋላቢዎች እየታዩ መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይጠቁማሉ።
ውድድሩ በመካሄዱ የእርስ በእርስ የባህል ልውውጥ ከማድረግ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው መልካም እድል መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይጠቁማሉ። ለውድድሩ ከ350-450 የሚሆኑ ልኡካን እንደሚመጡ ይጠበቃል፤ በመሆኑም የባህር ዳር ህዝብ እንግዳ ተቀባይነቱን እንዲያሳይ እና ውድድሩ እስኪጠናቀቅ ድረስም ትብብር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011
ብርሃን ፈይሳ