ትሕነግ የሚባል የሰው ጉድ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ለማድረግ ይቅርና ለማሰብ የሚዘግንኑ፣ ሰው ሆኖ መፈጠርን የሚያስጠሉ እጅግ የሚከብዱ የጫካኔ ድርጊቶች በሰው ልጆች ላይ ተፈጽመዋል። በሊቢያ የሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ አይ.ኤስ.አይ.ኤስ በተባለ ወንጀለኛ የሽብር ቡድን በኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ላይ ከተፈጸመው እጅግ ዘግናኝ አረመኔያዊ ድርጊት የባሰ ጭካኔ በሚለው ቃል ብቻ ሊገለጽ የማይችል ዓለማችን ዓይታው የማታውቀው ሌላ ዓይነት ጭካኔ እዚሁ በራሳችን ጨካኞች በተደጋጋሚ ተፈጽሟል።
ትሕነግ በማይካድራ የዕለት ጉርሳቸውን፣ የዓመት ልብሳቸውን ለማሟላት ቀያቸውን ጥለው ለጉልበት ሥራ የሄዱ፣ ቀን በሃሩር ሌሊት በቁር ያለእረፍት ላባቸውን እያፈሰሱ የነበሩ፣ እጅጉን በሥራ የደከሙ ምስኪን የቀን ሠራተኞችን ፍጹም አሰቃቂ በሆነ መንገድ በአካፋና በዶማ ቀጥቅጦ ገድሏቸዋል።
ሞቸልሃለሁ፣ ተሰውቸልሃለሁ እያለ በሃሰት በስሙ የሚነግድበትን በተግባር ግን ዕድሜ ልኩን ሲገድለውና ለጥቅሙ ሲሰዋው ለኖረው ትሕነግ “ሕዝቤ” ለሚለው የትግራይ ህዝብ ህይወታቸውን ሰጥተው ሃያ ዓመታትን ከጠላት ሲጠብቁት የኖሩትን፣ ከማትበቃ ደመወዛቸው እየቀነሱ ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ የገነቡለትን፣ ሃያ ዓመት አብረውት የበሉትን የጠጡትን ጋሻ መከታ ወንድሞቹን በተኙበት አርዷል።
በአፋር በጋሊኮማ መንቀሳቀስ የማይችሉ በሰው የሚወጡ የሚገቡ አረጋውያን እናቶችንና አባቶችንእና ህጻናትን በከባድ መሳሪያ በጅምላ ጨፍጭፏል። በሰሜን ወሎ አጋምሳ የተባለች ወረዳን ነዋሪቿን በጅምላ ጨፍጭፎ፣ ምድሯን ሳይቀር አቃጥሎ ሙሉ በሙሉ አውድሟል። ሽንፈቱንና ውርደቱን ለመደበቅ በሚል በጦርነት የሞቱበትን የራሱን አመራሮች ሳይቀር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አንገታችውን ቆርጦ ደብቋል። ትሕነጋውያን ጦርነት ምን እንደሆነ ምኑንም የማያውቁ፣ አውቀውም የማይሸሹ፣ ሸሽተውም የማይደበቁ፣ የማይናገሩ፣ የማያስቡ፣ የማይማከሩ “ነፍሰ እግዚአብሔር” የሚባሉ የቤት እንስሳትንም ገድለዋል፣ አቃጥለዋል። ስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ደግሞ እጅግ አሰቃቂ በሆነ፣ እስካሁን ታይቶ በማይታወቅ መንገድ የሰውን ልጅ አሰቃይተዋል፣ ገርፈዋል፣ ሰውን ከእባብና ከጊንጥ፣ ከአንበሳና ከጅብ ጋር አንድ ላይ አስረዋል፣ የሰውን ልጅ ከእነ ነፍሱ ቀብረዋል፣ የወንድ ልጅን ብልት አኮላሽተዋል፣ በሴት ልጅ ብልት እንጨት ሰደዋል።
በአጠቃላይ ትሕነግ ቅድስት ሃገር በምትባለው በኢትዮጵያ ላይ ይቅርና ምንም ዓይነት ሃይማኖት የሚባል ነገር በሌለበት በየትኛውም የዓለም ክፍል ላይ እንኳን ሊፈጸሙ የማይችሉ፤ ታይተው ተሰምተው የማይታወቁ እንኳንስ ለሰው ልጅ ለፍጡር ሁሉ እንግዳ የሆኑ፣ ብዙ፣ ብዙ ተዘርዝረው የማያልቁ አሳፋሪ ርኩሰቶችንና አሰቃቂ ጉዶችን በሰው ልጆች ላይ ፈጽሟል። ለመሆኑ ግን ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? እንዲህ ዓይነቱ ከሰው ልጅ አዕምሮ በላይ የሆነ እንግዳ ጭካኔስ ከየት መጣ? ስለ ሰው ልጆች ባህሪይና ስለ ትሕነግ ማንነትስ ምን የሚናገረው ነገር አለ?
የትሕነግ ጭካኔ ከየት መጣ
አጠቃላይ በሰው ልጆች ላይ ለሚፈጠረው ጭካኔ መሰረታዊ መንስኤው ራስን ብቻ ወዳድነት፣ ስግብግብነት፣ አልጠግብ ባይነትና ትዕቢትን የመሳሰሉ ሴጣናዊ ባህሪያት ሊሆኑ ይችላሉ። በዓለም ላይ ታይተው ተሰምተው ለማይታወቁት እጅጉን የሚዘገንኑ የትሕነግ የጭካኔ ድርጊቶች የቅርብ መንስኤው ግን ጥላቻ ነው። ይኸውም ትሕነግ ወደ ጫካ ከገባበትና ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ዓመታት በሃገሪቱ ሲነዛ የቆየው እጅግ አደገኛ የሃሰትና የጥላቻ ትርክት የወለደው ርኩሰት ነው።
ለብዙ ሽህ ዘመናት አብሮ በኖረ ወንድማማች ህዝብ መካከል በክፋት ፈላስፎች የተፈበረከ ሃሰተኛ የጥፋት ታሪክን የሚያስተምሩ፣ ጥላቻን የሚሰብኩ፣ ወንድም ወንድሙን እንዲያፈናቅል፣ እንዲገድል የሚሰጡ ከአውሬም ከሴጣንም የሚብስ የክፋት፣ የጭካኔና የጥፋት ስብዕና የተላበሱ ታህተ-ሰብዕ ሰዎች ህግና ሚዲያን ሳይቀር ተጠቅመው በሕዝብ ላይ ያሰረጹት መርዝ ነው ለዚህ ሁሉ ዘግናኝ የጭካኔ ድርጊት የቅርብ መንስኤው! የሚገርመው ነገር ጥላቻ አስተማሪዎቹ ከክፋታቸውና ከርኩሰታቸው መብዛት የተነሳ ትምህርታቸው በሕዝብ ልብ ውስጥ ሰርጾ እንዲገባ በርካታ ሚሊዮኖችን አውጥተው ጥላቻን የሚሰብክ ሃውልትም ቀርጸው አቁመዋል።
ከእነርሱ አልፈው ይህንኑ የክፋትና የጥፋት አስተሳሰባቸውን ምንም በማያውቀው(የማያውቀው ክፋትን ብቻ ነው) በየዋሁ ህዝብ ውስጥ ለማስረጽና “አንድ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ማህበረሰብ” ለመገንባት ህገ መንግስት አርቅቀው፣ ፖሊሲ ቀርጸው ሌት ተቀን ያለ እረፍት ሰርተዋል።
ይህንን ገዳይ ህልማቸውን ለማሳካትም ማንኛውንም ዓይነት ወንጀልና ርኩሰት በሰው ላይ የሚፈጽሙ፤ ይኸው አስተሳሰባቸውም “በመቃብራቸው ላይ ካልሆነ በቀር” እንዲቀየርባቸው የማይፈልጉ፤ በክፉ ሥራቸው የሚፎክሩ፣ ራሳቸውን ብቻ ፍጹም ትክክለኛ አድርገው የሚቆጥሩ፣ ርዝራዥ ትህትና ያልፈጠረባቸው፣ ሰውን በጣም የሚንቁ፣ ትዕቢተኞችና ባለጌዎች አሁን ላይ የዘሩት ክፉ ዘር በምናየው መንገድ ጭካኔ ሆኖ በሃገራችን ላይ በቅሏል።
ለመሆኑ ግን መነሻው ምንም ይሁን ምን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ሕወሓትና የአስተሳሰብ ተሸካሚወቹ እየፈጸሙት እንደሚገኘው ዓይነት ዘግናኝ የጭካኔ ድርጊት ስለማንነታቸው ምን ይነግረናል?
ትሕነግ ከአውሬም የሚያንስ ወራዳ ፍጡር ነው
ሰው ከሰውነት ባህሪ የወጣ የጭካኔ ድርጊቶችን ሲፈጽም “ምን ዓይነት አውሬ ነው” እያሉ ከእንስሳት ወይም ከአውሬ ጋር ማወዳደር በሰው ዘንድ የተለመደ ነው። ይሁን እንጅ ይህ ፍጹም ስህተት ነው፤ ምክንያቱም አውሬው እኮ “የጭካኔ” ድርጊቱን የሚፈፅመው ተፈጥሯዊ ባህሪው ስለሆነ ነው። አዳኝ ታዳኝን አሳድዶ በዘግናኝ ሁኔታ ሲገድለው እንደ ትሕነግ በጥላቻ አይደለም፤ አውሬው በዚህ መንገድ እንዲኖር ተደርጎ ስለተፈጠረ ነው እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት የሚፈጽመው። ይህም ስህተት አይደለም፣ በቃ የሆነውን ነው የሆነው።
ሰው ግን በፍፁም እንዲህ ዓይነት ጨካኝ ድርጊቶችን እንዲፈፅም የሚያደርግ አረመኔያዊ ባህሪይን ይዞ አልተፈጠረም! ሰው እንዲህ ዓይነት ክፉ ባህርያትን ያበቀለው ከራሱ ነው። ስለሆነም በተፈጥሮው መልካም ሆኖ የተፈጠረው ሰው በራሱ ክፋት የሚያመነጨውን ክፋትና ጭካኔ በተፈጥሮ ከመጣው የአውሬ ጭካኔ ጋር ማነጻጸር ፍጹም ስህተት ነው።
ሰው በፈጣሪው አምሳል ተፈጠረ ከሚለው ሃሳብ በተቃራኒ “ሰው ከጦጣ መሰል ፍጡር ነው የተገኘው” ብለው በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑ አንዳንድ ዘገምተኞች ሰው የመገዳደል ባህሪን የወረሰው ከዝንጀሮ መሰል አራዊቶች መሆኑን ቢናገሩም የሥነ አዕምሮ ሊቁ ኤሪክ ፍሮም ግን ራስ ወዳድነቱን ለማርካትና ያልተገባ ደስታ ለማግኘት መሰሉን ሆን ብሎ በክፉ እሳቤ የሚገድል ፍጡር ግን እንደ ትሕነግ ዓይነቶቹ በጥላቻ የተመረዙ “ሰዎች” ብቻ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
የስግብግብነትና የአልጠግብ ባይነት ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰደው ጅብ እንኳን ከመሰሎቹ በልጦ ለመገኘት ሲል እርስ በእርሱ አይጠፋፋም፤ ፉክክሩ ከሌሎች ሥጋ በል እንስሳት ጋር እንጅ ከጅቦች ጋር አይደለም፤ ተሰባስቦ በሕብረት ያጠቃል እንጅ ተከፋፍሎና ተቧድኖ እርስ በእርስ አይጠቃቃም። እናም ክፉና አረመኔ እንደ ትሕነግ ዓይነት ሰወች “አውሬ” ተብለው ሊሰደቡ አይገባም፤ ሰው በተፈጥሮው የሌለውን ክፋትና አረመኔነት በጥላቻ ፈልገው ያመጡ ሰወች “አውሬ” ተብለው ሲጠሩ ሙገሳ ይሆንባቸዋልና!
ትሕነግ ከራሱ ከሴጣንም በላይ ርኩስ ነው
በእግዚአብሔር አምሳል ከተፈጠረው ሰው የሚወጣው ክፋት በዚህም ምክንያት የሚፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ጭካኔ፣ ጥፋትና በደል ከሴጣን ክፋትም ይገዝፋል! ለምን ቢሉ ቢያንስ ሴጣን ክፉ የሆነውና በደል የፈጸመው “ለምን በአምሳልህ አልፈጠርከኝም” በሚል በእግዚአብሔር አኩርፎና ተቀይሞ ሊሆን ይችላል! ሰው ግን በምን ያመካኛል፤ ከእርሱ በቀር በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ(ቅዱሳን ትጉሃን መላዕክትም ቢሆኑ) ሌላ ፍጡር የለምና! በታላቁ በእግዚአብሔር አምሳል ከመፈጠር የበለጠ ትልቅ ነገርስ ምን ሊኖር ይችላል።
እናም በገዛ ፈቃዱ ክፉና አረመኔ የሆነ እንደ ትሕነግ ዓይነት ሰዎችን “ሰይጣን” ብሎ መስደብም ትክክል አይደለም። ምክንያቱም በመልካሙ እና በርህሩሁ እግዚአብሄር አምሳል ተፈጥረው በተፈጥሮ የሌለባቸውን ክፋት ሁሉ የሚበልጥ ክፋት፣ ከበደል ሁሉ የሚከፋ የጭካኔ በደልን በራሳቸው በመሰሎቻቸው ላይ የሚፈጽሙ፤ ወንድሞቻቸውን አሰቃይተው በጭካኔ የሚገድሉ እንደ ትሕነግ ዓይነት ክፉና አረመኔ ሰዎች ከአውሬም ብቻ ሳይሆን ከራሱ “ከመጀመሪያው ክፉ” ከሴጣንም የሚያንሱ ወራዳ ፍጥረት ናቸውና!
ትሕነግ ለሰው ፍጥረት ኀፍረት ነው
ሰው የተፈጠረው ከእርሱ ውጭ ያሉ በምድር ላይ የሚኖሩ ሌሎች ፍጥረታትን ሁሉ “ይገዛ” ዘንድ ታላቅነትን ብቻ ሳይሆን አለቅነትንም ጭምር ይዞ ሁሉን በሚችለው ፈጣሪ የዚች ምድር ታላቅ ፍጡር ሆኖ መፈጠሩን በመንፈሳዊው የሥነ ፍጥረት እሳቤ ዘንድ ዋነኛ ማጣቀሻ ሆኖ የሚያገለግለው መጽሃፍ ቅዱስ በማያሻማ ቋንቋ በግልጽ መዝግቦት ይገኛል።
ሆኖም ታላቅ ሲባል እንደ አንሶ፣ ክቡር ሲባል ወርዶ፣ መአምር ሲባል መሃይም ሆኖ የተገኘ በክፋትና በስግብግብነት ታውሮ፣ በጥላቻ ተመርዞ በራሱ ፍጥረት ላይ የጭካኔ ፍላጻን የሚወረውር እንደ ትሕነግ ዓይነት የሰው ፍጡር ግን ለሰው ልጆች ታላቅ ውርደት ነው።
የሰው ልጅ ከፍጡር ሁሉ በልጦ የተሰጠውን ይህን ሁሉ ዕውቀቱንና ኃይሉን ሁሉ ከፈጣሪው ጥበቃ በታች ከራሱ ሳይሆን ከሌሎች ፀረ ሰውና ፀረ ህይወት ፍጡራን ሊደርስበት የሚችለውን ጥቃት ለመከላከል እና መልካም ነገርን ለማድረግ ሊጠቀምበት ሲገባው እንደ ትሕነግ ከፍጥረቱ በተቃራኒ መቆጣጠር የሚችለውን አዕምሮውን በጥላቻ ተሰልቦ ለዘግናኝ ጥፋትና ጭካኔ ከተጠቀመበት ይህ ሰብዓዊ ማንነትን የሚያዋርድ ክፉ ርኩሰት ነው፤ ለሰው ልጆችም ኀፍረት ነው።
እናም የሰው ልጅ በፈጣሪው የተቸረውን ታላቅ ተፈጥሮውን፣ ኃያል ማንነቱን ማወቅ ተስኖት እንደ ትሕነግ ከሰውነት ወርዶ ሰው መሆን አቅቶት በአስከፊ ጭካኔ ውስጥ ተዘፍቆ ሲገኝ ታላቁን ውርደት ይዋረዳል። ለእርሱ ብቻ ተዳልቶ በተሰጠው በታላቁ አዕምሮው ምክንያት የምድራችን ታላቁ ፍጡር መሆን የቻለው ሰው ስጦታውን ማወቅ ሳይችል ቀርቶ ሰው መሆን ባልቻለ ጊዜ ሰው ከሁሉም የከፋውን ጥፋት አጥፍቷልና ከምድር ፍጥረታት ሁሉ የሚያንስ ወራዳ ፍጥረት ይሆናል።
ክፉና በጎን፣ ስህተትና ትክክልን፣ እውነትና ሃሰትን፣ ልማትና ጥፋትን፣ ሞትና ህይዎትን የተሻለውን አመዛዝኖ እንዲመርጥበት ከፍጥረት ሁሉ ተዳልቶ “አዕምሮ” የተባለ ውድ ስጦታ የተሰጠው የሰው ልጅ ልክ እንደ ትሕነግ ይህንን ታላቅ ስጦታውን ማወቅ የተሳነው(ወይም ማወቅ ባልፈለገ ጊዜ) ጭካኔን ይሞላል፣ ርህራሄ ያጣል፣ ከሰውነት በታች ሆኖ ከሁሉም አንሶ የጭካኔ የውርደት ተግባር ይፈጽማል።
ሰው ምንም እንኳን ስጋዊ ጠባይ ቢኖረውም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ በመሆኑ አምላካዊም፣ መለኮታዊም ሆኖ ሳለ ይህንን ታላቅ ስጦታውን ረስቶ ያለተፈጥሮው እንደ ትሕነግ በጭካኔ እና በአረመኔያዊ ባህሪይ ተመልቶ መኖር ከጀመረ፣ በራሱ ስህተት ከታላቁ የሰውነት ባህሪው ይጎድላል፣ ከሁሉም የከፋ ታላቅ ውርደትን ይከናነባል።
ሰብዓዊ ፍጡር እንደ ትሕነግ ከሰውነት ባህሪይው በራሱ ጊዜ ከጎደለ፣ ሰው ሆኖ ያለ አግባብ ሰውን ከበደለ፣ በፍቅር ፋንታ ጥላቻን ከመረጠ፣ በበጎነት ፋንታ ክፋትን ካስበለጠ፣ ከሰላም ይልቅ ጦርነትን ከናፈቀ ያኔ ሰው ከሰውነቱ ብቻ ሳይሆን ታናሽ ከሚባሉ ፍጥረታትም በታች አንሶ ተዋርዷል። ማሰብ መሰላሰል ማመዛዘን ከማይችለው፣ አንጎል እንጅ አዕምሮ ከሌለው ከእንስሳም በታች እንስሳ ሆኗል።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ጳጉሜ 1/2013